በኤፌ2:20፣3፡16 ላይ ቃሉ ሲናገር፦ በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ …በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ ክርስቶስም በልባችሁ በእምነት እንዲኖር እንደ ክብሩ ባለ ጠግነት መጠን ይስጣችሁ፤ የእናንተ ሥርና መሠረት በፍቅር ይጸና ዘንድ፥… ይላል፡፡
ሀዋርያትና ነብያት መሰረት የሆኑት እውነተኛ የወንጌል አገልጋይ በመሆናቸው ነው፡፡ እነዚህ የእግዚአብሄር አገልጋዮች ኢየሱስ ክርስቶስ በእነርሱ አድሮ ለሚሰራው ስራ ራሳቸውን የሰጡ በመሆናቸው በነርሱ ትምህርት ላይ መታነጻችን በእርሱ ላይ መታነጻችን እንደሆነ ሙሉ በሙሉ የሆነ መተማመኛቸውን ሰጥተዋል፡፡ ሃዋርያት የኢየሱስን ዋስትና ያለው ምስክር ሊያውጁ የወጡ፣ የመሰከሩ፣ በእምነት የእግዚአሄርን ስራ የሰሩ በመሆናቸው እግዚአብሄር መስክሮላቸዋል፤ በዕብ.2:1 እንደተናገረው፦ ‘’ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ፥ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል።በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ፥ መተላለፍና አለመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ፥ እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፥ እንዴት እናመልጣለን? ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፥ የሰሙትም ለእኛ አጸኑት፥እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም፥ መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ መሰከረለት።’’ ይላል። ቃሉ፣ መንፈሱ እንዲሁም መላእክቱ ሳይቀሩ የመሰከሩለት ይህ አስተማማኝ የመዳን ቃል ሁሉም በሙሉ እምነት ሊቀበሉት የተገባ ነው።
ወንጌል መድሀኒት የሆነውን ጌታ ስለሚገልጠው መዳን ተብሎ የተጠራ ነው፡፡ የወንጌል ደራሲ ጌታ ኢየሱስ ነው፤ አለም ሳይፈጠር እግዚአብሄር በልጁ ሞትና ትንሳኤ የሰውን ልጅ ከፍርድ ያድን ዘንድ ወስኖአል፤ ዘመኑ ሲደርስም ቃሉን ገለጠ፡፡ ወንጌሉ የማዳን ምስጢር መገለጫ ስለመሆኑ በሰው ልጆች ዘንድ እንዲታወቅና ሁሉ እንዲቀበሉት ወንጌሉ በተነገረ ጊዜ የእግዚአብሄር ታምራት ፣ምልክቶችና ድንቆች ይከተሉት ነበር፡፡
ወንጌል በቅድሚያ የተሰበከው በራሱ በጌታ ነበር፡፡ ከእርሱ ተከትሎ ጌታ የጠራቸው ሀዋርያት እርሱ የሰበከውን ደግመው በመናገር ለእኛ አጸኑት፤ ደግመው ሲናገሩ የነበረው ራሱ የማይለወጠውን ወንጌል ነበር፡፡ ወንጌል የብሉይ ኪዳንና የአዲስ ኪዳን ቅዱሳንን የሚያድን በመሆኑ አስቀድሞ ለአብረሃም ተሰብኮ ነበር፡፡ አብረሃምም ያን አምኖ የጌታን መገለጥ በሩቅ አይቶና ተሳልሞ አልፎአል፡፡
በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ እጅግ ልዩ ስፍራ ያለው አጋጣሚ የጌታ ኢየሱስ መሞት፣ መቀበርና ከሞት መነሳት (ትንሳኤ) ነው፡፡ የጌታ ሞትና ትንሳኤ ለእኛ ህይወት ዘላለማዊነት ማረጋገጫ ነውና ወንጌል ያን በግልጽ ያውጀዋል፡፡ በወንጌል ውስጥ የወንጌሉ መሰረት ስለሆኑት ደቀመዝሙርት፣ የቃሉን አገልጋዮች በመንፈስ ቅዱስ ወንጌሉን በሀይል ስለመስበካቸው፣ ነፍሳትንም ወደ እግዚአብሄር መንግስት ስለማፍለሳቸው… ለእኛ ምስክር ይሆኑልንና ያጸኑን ዘንድ በግልጽ ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡
1ቆሮ.3:10-11 ‘’የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ።ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።’’
የእምነታችን መሰረት መንፈሳውያን አናጺዎች በሆኑት ሃዋርያቶች ተመስርቶአል፤ መሰረቱ ግን ክርስቶስ ነው፤ ሃዋርያቶች ጅማሬያቸውም ፍጻሜአያቸውም ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው፤ በመሰረቱ ላይ የሚታነጸው መቅደስ አንድ በመሆኑ ሌላ መሰረት ከተመሰረተው በቀር አስፈላጊ አይደለም፤ የሚጠበቀው ግድግዳውና ጣራው ነው፤ ማንም በዚያ ላይ ሊመሰረትና የጌታ መቅደስ ለመሆን ቢፈቅድ በመሰረቱ ላይ መተከልና እየታነጸ ማደእግ ያስፈልገዋል፤ ለማደግ ደግሞ ወንጌሉን መመገብ፣ መጠንከርና ማደግ አለበት። የወንጌሉ እንጀራና መጠጥ ጌታ ራሱ ነው። ስለዚህ ሰው ከጌታ ኢየሱስ ያፈነገጠ ትምህርት ሊሻና ሌላ ትምህርት ሊቀበል አያስፈልገውም። አሰራሩ እንዲህ ነው፣ ለዚያም ነው ሃዋርያት አገልግሎታቸው ላይ ሙጥኝ ብለው ሰውን ወደነርሱ ትምህርት የሳቡት፦
‘’ነገር ግን አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው የተወደደ መሥዋዕት ሊሆኑ፥ ለእግዚአብሔር ወንጌል እንደ ካህን እያገለገልሁ፥ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ እሆን ዘንድ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ጸጋ ምክንያት ተመልሼ ላሳስባችሁ ብዬ በአንዳንድ ቦታ በድፍረት ጻፍሁላችሁ። እንግዲህ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሚሆን ነገር በክርስቶስ ኢየሱስ ትምክህት አለኝ።’’ (ሮሜ.15:15-17)
በእግዚአብሄር ቃል እምነት ጌታ ኢየሱስን ያመኑ፣ ለአዲስ ልደት ለሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በሆነ ጥምቀት የተጠመቁና በመንፈስ ቅዱስ የተቀደሱ ሁሉ ማደግ በሚባል ሂደት ያልፉ ዘንድ ይገባቸዋል፤ ማደግም በቅድስና በመኖርና እንደቃሉ በመመላልስ የሚሆን ነው። ወንጌል አዲስ የተወለደን ክርስቲያን በቃልና በመንፈስ ቅዱስ ያሳድጋል፣ ይንከባከባል፣ ከክፉ ሰራተኞችና መናፍስት ከልሎ ያኖራል። በዚህ ስራ ውስጥ ካህን ሆነው የሚያገለግሉ የቃሉ አገልጋዮች ሲሆኑ መሰረታቸውና መነሻቸው ወንጌል ብቻ ነው። ወንጌል ላይለወጥና ላይነካካ ነገር ግን ከጌታ በተሰጠበት መንፈስ እንደ ባለቤቱ ሆኖ ሊሰበክ ግድ ነው። ይህን የሚያምኑ፣ የተቀበሉና የተሰጡ ሰዎች ለጌታ እጅግ ያስፈልጉታል፤ ሃዋርያው አንዳንድ የማይታመኑ አገልጋዮች ገጥመውት ሳለ በሃዘን ሲናገር እናያለን፦
‘’በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ። ነገር ግን ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፥ እያሳቱና እየሳቱ፥ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ።አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር፥ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን አውቀሃል። የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።’’ (2ጢሞ.3:12-17)
በክርስቶስ ወደ እግዚአብሄር ባህሪ መድረስም እርሱን መምሰልም የሚቻለው በወንጌል በተገለጠው እውነት በኩል ብቻ ነው፤ በወንጌሉ ላይ ያመጹ ግን በአገልጋይ ላይ ክፉዎች ሆነው ትምህርቱን ሲቃወሙት ነበር፤ አሁንም ወደፊትም ግን ህያው ወንጌልን የተቀበሉ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን፥ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡ የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍትን በእውቀት በመቀበል፣ በመኖርና በመስበክ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ እንዲያድጉ በጸጋ በመደገፍም ለመንግስቱ ማብቃት ይቻላል።
በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተገለጠውን መዳን ያለማቁዋረጥ የሚገዳደር ሰይጣናዊ ትምህርት እንዳለ በመገንዘብ ሁሌም በቃሉ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፤ የዚህ መፍትሄ ሌላ ሳይሆን እግዚአብሄርን መፍራትና ማክበር፣ በቃሉ ላይ መደገፍ፣ ከቃሉ ውጪ ያለመታመን፣ ቃሉ በህይወት እንዲሰራ መፍቀድና ለቃሉ መኖር ነው። የቃሉ ቅን አገልጋዮች እንዳሉ ሁሉ ቃሉን እንደምድራዊ ሸቀጥ ለትርፍ የሚጠቀሙበትም አሉ፤ ይህን ያደርጉ የነበሩ ከአይሁድ ወገን የነበሩ አማኞች ነበሩ፣ ከአህዛብም ወገን ተመሳሳይ ስራ የሚሰሩ እጅግ የበዙ ይኖራሉ። እነዚህ የጥፋት ልጆች እስከ አለም ፍጻሜ እንደማይጠፉ በመንፈስ የተረዳው ሃዋርያ አገልጋዩን በጥብቅ ሲመክር እንመለከታለን፤ ለጢሞቲዎስ በሚሰጠው ምክር እንዳለው በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ ብሎአል። አሳዳጆች በቃልም በአካላዊ ጉድትም እንዲሁም በስነልቦናዊ ነገር ሁሉም የሚያደርሱባቸውን ጉዳት ተቁዋቁመው በእውነት ምስክርነት ላይ እንዲቆሙ ቃሉን በእውነት ለሚያገለግሉ በሙሉ የተሰጠ ማጽናኛ ማስጠንቀቂያም ነው።በ2ጢሞ. በተሰጠው ማስጠንቀቂያ ውስጥ ስለመጨረሻው ዘመን እውነት ተመልክቶአል፤ የመጨረሻው ዘመን አስጨናቂ ይሆናል፣ አስጨናቂ ያደረገው የሰዎች ክፋትና ድፍረት በእግዚአብሄር እውነት ላይ በሙሉ ሃይሉ ስለሚነሳ ነው፤ የዚህ ክፉ ተዋናይ አለማውያን ሳይሆኑ በእምነት በወንጌል ተለይተው የነበሩ በአመጽ ስለሚነሱ ነው፤ አለም ተስፋና እረፍት ሊሆንላት የሚገባው በሰላም ወንጌል ሆኖ ሳለ ወንጌሉን እናምናለን እንሰብካለንም የሚሉ ሰዎች ተነስተው የከፋ ምግባራቸውን ሲያሳዩ ተስፋ ከምድር ይጠፋል፤ ይህን በመንፈስ ሲመለከት አስጨናቂነቱ አሳስቦት ሃዋርያው ያን ተናገረ፦
‘’ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ።ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥ ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ፥ቅድስና የሌላቸው፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ዕርቅን የማይሰሙ፥ ሐሜተኞች፥ ራሳቸውን የማይገዙ፥ ጨካኞች፥ መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ከዳተኞች፥ ችኩሎች፥ በትዕቢት የተነፉ፥ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ፤ የአምልኮት መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል፤ ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።’’ (2ጢሞ.3:1-5)
እንዲህ ያሉ ሃሰተኛ አስተማሪዎች ከእውነተኞች ይልቅ ሃይለኞች ናቸው፣ አቅማቸውን በሙሉ ተጠቅመው ሃሰታቸውን ያሰራጩ ዘንድ እንደሚሹለኮለኩ ይህም ብዙዎችን ከህያው ወንጌል እንደሚነቅል ቃሉ ያሳያል፦
‘’ወደ ቤቶች ሾልከው እየገቡ፥ ኃጢአታቸው የተከመረባቸውን በልዩ ልዩ ምኞትንም የሚወሰዱትን ሁልጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉትን ሞኞችን ሴቶች የሚማርኩ፥ ከእነዚህ ዘንድ ናቸውና። ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደ ተቃወሙት፥ እንዲሁ እነዚህ ደግሞ አእምሮአቸው የጠፋባቸው ስለ እምነትም የተጣሉ ሰዎች ሆነው፥ እውነትን ይቃወማሉ።ዳሩ ግን የእነዚያ ሞኝነት ደግሞ ግልጥ እንደ ሆነ፥ ሞኝነታቸው ለሁሉ ይገለጣልና ከፊት ይልቅ አይቀናላቸውም።’’ (2ጢሞ.3:7-9)
የምለውን አስብ…
በክርስቶስ ጸጋ እንዲጸና ሐዋርያው ለጢሞቴዎስ የሰጠው ምክር አለ፤ በታማኝነትና በጌታ ችሎት ለሰዎች የወንጌልን ትምህርት ለፍጥረት እንዲያቀርብ፣ መንፈሱ በአላማ ጨክኖ እንደ ወታደር ለወንጌል የህይወት ተልእኮ ቆራጥ እንዲሆን፣ እንደ ሯጭ ለወንጌል ባለመታከት እንዲሮጥ፣ እንደ ታጋይ እየወደቁ እየተነሱ በጌታ ጸጋ እስከፍጻሜው ስለወንጌል መታገልን፣ እንደገበሬም አመቺ ወቅትን ተጠቅሞ ውጤታማ መሆንን ምሳሌ እንዲይዝ በዘመኑ ለነበረው ለርሱ፣ እንዲሁ አሻግሮ ሊመጡ ላላቸው የወንጌል አገልጋዮች ምክሩን አካፍሎአል።
ስለዚህ እውነተኛው አገልጋይ ስለወንጌል ፍቅር ምድራዊ ምቾትና እረፍት መጠበቅ የለበትም፤ ብርታቱን በእግዚአብሄር ጸጋ ላይ ያደረገ መንፈሳዊ ጦርነትን ከመናፍስት ጋር ይዋጋልና፤ ይህ በወንጌሉ ላይ ባለው ትምክህት የእግዚአብሄርን ስራ የሚሰራ አገልጋይ ችግር ቢገጥመው፣ ድካምና ማጣት ቢፈታተነውም በጌታ በኢየሱስ የጸጋ ጉልበት ተበራትቶና ጨክኖ እውነትን እንዲሰብክ ምክሩ ያስገነዝበዋል። የደህንነት ባለቤት የሆነውና ወንጌል በግልጽ በአለም ላይ እንዲሰበክ ያዘዘው ጌታ የሮጠበትን ሽልማትና አክሊል የድካሙንም ሁሉ ፍሬ ዋጋም የሚከፍል የእረኞች አለቃ በመሆኑ አገልጋይ የጸጋውን የክብር ሽልማትና ዘላለማዊ ሕይወት ሩጫውን ሲያጠናቅቅ እንዲያስረክበው ታምኖ ስራውን እንዲፈጽም ቃሉ ይመክራል።
‘’በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ፤ ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ።እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ።’’ (2ጢሞ.4:1-4)
እንግዲህ የመጨረሻው ቀንን በብዙ ሁኔታዎች የወንጌል ቀን እንደሆነ በመቁጠር አገልጋዮች የእግዚአብሄር ፈቃድ መፈጸሚያ ዘመን መሆኑን አምነው የቃሉን መንፈስ በመያዝ የጌታን ትእዛዝ ይፈጽሙ ዘንድ ያስፈልጋል፤ ይህ የመጨረሻው ዘመን የፍጻሜውን ቀናት የሚያመለክት አድርገን በማየት እኛ አምነን ዳግመኛ ከእግዚአብሄር የተወለድንና ሊመጣ ካለው ቁጣ የዳንን በፍርሃትና በጥንቃቄ የወንጌሉን መንፈስ እንታዘዝ። ብዙዎች ከዚህ የእውነት መንፈስ አፈንግጠዋልና። በመልክ አማኝ የሚመስሉ መንፈሳቸው ግን እውነትን የሚጋፋ ሃሰተኛ አማኞች ይኖራሉ፤ ያለመታዘዝ መንፈስ የመጀመሪያውን አባታችንን አዳምን እንደጣለው እነዚህ ወገኖችም በዚያ መንፈስ ተይዘው ከመዳን ፈቀቅ ይላሉ፤ በውስጣችው የሚያደርጉት መራቅና ፈቀቅ ማለት በመልክ እስኪገለጥ በመንፈሳዊ ህይወት ህጻናት የሆኑትን በምኞታቸው ያስታሉ፣ በቃሉ መረዳት ላይ ያልቆሙትንም በስህተታቸው ይጥላሉ፣ ይህ በመጨረሻው ዘመን የሚገለጥ ደፋር የሚያደርግ የፍልስፍናና የአጋንንት ትምህርት መደበላለቅ በወንጌሉ ላይ ባለው ጸጋና እውነት ካልተመከተ ባለፉት ትውልዶች እንደሆነው በኑፋቄ ብዙዎችን እንዳይጥል በትኩረት ሊፈተሽ የሚገባ ነው።