እግዚአብሄርንና ሀይሉን የሚያውቁ ሰዎች በሁኔታዎች አካሄድና በነገሮች መፈጠር አይደናገጡም፣ በአጋጣሚዎች ድንገት መከሰት አይርበተበቱም፤ ምክኒያቱም ከእነርሱ በላይ ያለውን ስለሚያወቁ፣ ከርሱ በቀር ማንም እንደሌለ ስለሚረዱ፣ ያለ እርሱ ፈቃድ የሚሆን ነገር እንደሌለ ስለሚያውቁ፣ ደግሞም የእርሱ አሳብ ለሰው ልጆች ሁሉ መልካም መሆኑን ስለሚያስተውሉ ነው፡፡ ነቢዩ ኤልሳ በአስጨናቂ ጠላቶች ተከቦ ሳለ የተናገረውን እንመልከት፡-
2ነገ.6:15-17 ”የእግዚአብሔር ሰው ሎሌ ማለዳ ተነሥቶ በወጣ ጊዜ፥ እነሆ፥ በከተማይቱ ዙሪያ ጭፍራና ፈረሶች ሰረገሎችም ነበሩ። ሎሌውም። ጌታዬ ሆይ፥ ወዮ! ምን እናደርጋለን? አለው። እርሱም፡- ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ አለው። ኤልሳዕም። አቤቱ፥ ያይ ዘንድ ዓይኖቹን፥ እባክህ፥ ግለጥ ብሎ ጸለየ። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ዓይኖች ገለጠ፥ አየም፤ እነሆም፥ በኤልሳዕ ዙሪያ ያሉት የእሳት ፈረሶችና ሰረገሎች ተራራውን ሞልተውት ነበር።”
ይህ ሁኔታ ከመከሰቱ አስቀድሞ የሶርያ ንጉሥ እስራኤልን ሊወጋ ከመኮንኖቹ ጋር ሲመክር እግዚአብሄር በነቢዩ በኩል እስራኤልን ሲያስጠነቅቅ ነበር፡፡ በመለኮታዊ ምሪትም ሁለት ጊዜ የእስራኤል ንጉስ ከሶርያውያን ጥፋት ራሱን አዳነ። የሶርያም ንጉሥ ምክሩ እንዳልሰራ አይቶና ተበሳጭቶ ምስጢሩን ስላሾለከበት ሰው በጠየቀ ጊዜ ሰዎች መለሱለት፡-ጌታዬ ሆይ፥ እንዲህ እኮ አይደለም፤ ነገር ግን በእልፍኝህ ውስጥ ሆነህ የምትናገረውን በእስራኤል ዘንድ ያለ ነቢይ ኤልሳዕ ለእስራኤል ንጉሥ ይነግረዋል አሉት። እርሱም፡- ልኬ አስይዘው ዘንድ ሄዳችሁ ወዴት እንደ ሆነ እዩ አለ። እነርሱም፡- እነሆ፥ በዶታይን አለ ብለው ነገሩት። ወደዚያም ፈረሶችንና ሰረገሎችን እጅግም ጭፍራ ሰደደ፤ በሌሊትም መጥተው ከተማይቱን ከበቡ።
በዚህ አሰራር ውስጥ ብዙ ሁኔታዎች ሲለዋወጡ እናያለን፡፡ የሆኑት ሁሉ የሆኑት ግን በእግዚአብሄር ፈቃድ ነበር፡፡ የሶርያ ንጉሥ ያልተሳካለት በእግዚአብሄር ፈቃድ ነበር፣ የእስራኤል ንጉስ ያመለጠውም በእግዚአብሄር ፈቃድ ነበር፤ ደግሞ ኤልሳዕ እስራኤል ምድር ላይ ተቀምጦ የሶርያን ንጉስ ጉዋዳ፣ ምክርና ውሳኔ ያይ የነበረው በእግዚአብሄር ፈቃድ ነበር፡፡ ይህንን ያስተዋለ የእግዚአብሄር ሰው ኤልሳዕ ብቻ ስለነበር እርሱን ለመያዝ ስለመጡት የሶርያ ወታደሮች ብዙም የሚያስጨንቀው አልነበረም፤ ያላስዋለው ሰው ግን ጠፋን ሲል ጮሆእል፡፡
ሙሴም በዘጸ.15:1-3 ያለውን ዝማሬ ያቀረበው የእግዚአብሄር ሀያል እጅ ተገልጦ የፈርዖንን ሰረገሎች ሠራዊቱንም በባሕር ስለጣላቸው፤ የተመረጡት ሦስተኞች በኤርትራ ባሕር ስለሰጠሙ ነበር። እስራኤል ግን አሰራሩን ስላልተረዱ ግብጻውያን አጠፉን ወዮ አሉ፡፡ እስራኤላውያን የእግዚአብሄርን አሰራር ባለማወቅ ጠንቅ በጉዞአቸው ሁሉ አጉረምራሚ ነበሩ፣ ሀይሉን አላወቁምና፡፡ ሙሴም እንዲህ ብሎአቸው ነበር፡-
”በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዓመፃችሁ እንጂ ወደ እርስዋ መውጣትን እንቢ አላችሁ፤ በድንኳናችሁም ውስጥ እንዲህ እያላችሁ አጕረመረማችሁ፡- እግዚአብሔር ስለ ጠላን እንዲያጠፋን በአሞራውያን አጅ አሳልፎ ይሰጠን ዘንድ ከግብፅ ምድር አወጣን። ወዴት እንወጣለን? ሕዝቡ ብዙ ነው፥ ቁመቱም ከእኛ ይረዝማል፥ ከተሞቹም ታላላቆች የተመሸጉም እስከ ሰማይም የደረሱ ናቸው፥ የዔናቅንም ልጆች ደግሞ በዚያ አየናቸው ብለው ወንድሞቻችን ልባችንን አስፈሩት። እኔም አልኋችሁ፡- አትደንግጡ፥ ከእነርሱም አትፍሩ፤ በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር፥ እናንተ ስታዩ በግብፅና በምድረ በዳ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፥ ስለ እናንተ ይዋጋል፤ ወደዚህም ስፋራ እስክትመጡ ድረስ በሄዳችሁበት መንገድ ሁሉ፥ ሰው ልጁን እንዲሸከም አምላክህ እግዚአብሔር እንደተሸከመህ አንተ አይተሃል። ዳሩ ግን ለሰፈራችሁ የሚገባውን ስፍራ እንዲፈልግላችሁ፥ ትሄዱበት ዘንድ የሚገባውንም መንገድ እንዲያሳያችሁ ሌሊት በእሳት፥ ቀን በደመና በፊታችሁ በመንገድ ሲሄድ የነበረውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን በዚህ ነገር አላመናችሁም።” (ዘዳ.1:26-33)
የመለኮት ሀይል ምንጭ
የእግዚአብሄር ክንድ ከሀይሉ ጋር ነው፤ የእግዚአብሄር ሀይል የሚገለጥበት መንገድ ክንዱ ነው፡፡ እኛን ለመታደግ የሚገልጠው መንፈሳዊ ጉልበትና በክንዱ የሚመሰል የሀይሉ ብርታት መገለጫ መለኮታዊ ጉልበቱ ነው፡፡
መዝ.89:11-14 ”ሰማያት የአንተ ናቸው፥ ምድርም የአንተ ናት፤ ዓለምንና ሞላውም አንተ መሠረትህ። ሰሜንና ደቡብን አንተ ፈጠርህ፤ ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል። ክንድህ ከኃይልህ ጋር ነው፤ እጅህ በረታች ቀኝህም ከፍ ከፍ አለች። የዙፋንህ መሠረት ጽድቅና ፍርድ ነው፤ ምሕረትና እውነት በፊትህ ይሄዳሉ።” ይላል፡፡
አህዛብ ግን ሰማያዊውን መለኮታዊ ሀይል ሊያስተውሉ አይችሉም፡፡ ለነርሱ ሀይል አጋንንታዊና ከጣኦት የሚመነጭ ነው፤ እግዚአብሄር ግን ህያውና በሁሉ ላይ የሚሰለጥን ሀያል አምላክ ነው፡፡
መዝ.96:5 ”የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸውና፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።”
ቅዱስ አምላክ ለልጆቹ የሚያስታጥቀው ሀይል ሰዎችን ብቻ ሳይሆን መናፍስትንም ማንበርከክ የሚችል ሲሆን ያን የማያስተውሉ ሁሉ ጉዳዩ የስጋና ደም ይመስላቸዋል፡፡ የእስራኤል አምላክ ልዩ ነው፣ ለአህዛብ ባይተዋር የሆነባቸው ምስጢሩም አምነውና ቀርበው ስላላወቁት ስላልተገለጠላቸውም ነው፡-
መሳ.16:5” የፍልስጥኤማውያንም መኳንንት ወደ እርስዋ ወጥተው፤- እርሱን ሸንግለሽ በእርሱ ያለ ታላቅ ኃይል በምን እንደ ሆነ፥ እኛስ እርሱን ለማዋረድ እናስረው ዘንድ የምናሸንፈው በምን እንደ ሆነ እወቂ፤ እኛም እያንዳንዳችን ሺህ አንድ መቶ ብር ሺህ አንድ መቶ ብር እንሰጥሻለን አሉአት።”
ጠላት የእግዚአብሄርን ህዝብ የሚማርክበት፣ የሚያድንበትና ከሀይሉ የሚያስጥልበት መንገድ በቃሉ እንደተመለከተው ነው፡፡ ከጠላት ጋር መደራደር የሚያስከፍለው መነጠቅ ብቻ ሳይሆን መጥፋትም ስለሆነ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ እግዚአብሄርን የሚተማመኑና ራሳቸውን በአምላክ ጥላ ውስጥ የሚያሳድሩ ግን ራሳቸውን የማያጋልጡ መሆን አለባቸው፡፡ በእግዚአብሄር ሀይል የተቀባ አገልጋይ ከስፍራው ተነቅሎ ጠላት ሰፈር ሲያንዣብብ እንዴት ባለ ኪሳራ ውስጥ እንደሚወድቅ የሶምሶን ህይወት ትምህርት ሊሆን ይገባል፡፡
የመለኮት ሀይል በመንፈሱ ይወርዳል
በእግዚአብሄር ምሪት መውጣት የመንፈሱን እገዛ እንደሚሰጥ የሶምሶን ህይወት ያስተምራል፡፡ ሶምሶን ባላስተዋለባቸው ጊዜያት የሆኑበት ውድቀቶች እንዳሉ ሆነው ለተጠራበት አላማ በወጣበት ጊዜ ግን የእግዚአብሄር እገዛ አልተለየውም ነበር፡፡ እግዚአብሄር የቃል ኪዳን አምላክ ለታመኑት፣ ቃሉን ለጠበቁና ለታዘዙት እንዳለው ያደርግላቸዋል፡፡ ይህ እውነት የታመነ ነው፡-
መሳ.14:5-6” ሶምሶንም አባቱና እናቱም ወደ ተምና ወረዱ፥ በተምናም ወዳለው ወደ ወይኑ ስፍራ መጡ፤ እነሆም፥ የአንበሳ ደቦል እያገሣ ወደ እርሱ ደረሰ። የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ በኃይል ወረደ፤ ጠቦትን እንደሚቆራርጥ በእጁ ምንም ሳይኖር ቈራረጠው፤ ያደረገውንም ለአባቱና ለእናቱ አልነገረም።”
በሀይል የተሞላ ፈርጣማ አንበሳ ሶምሶንን ቆራርጦ ሊጥለው ድንገት በመንገዱ ላይ ቢከሰትም ሊቆራርጠው የተመኘውን አውሬ እንዴት ባለ ሀይል ጠቦት እንደሚቆራርጥ ቆራርጦ እንደበታተነው እናያለን፡፡ ለሰው ልጆች ባስፈለገው ስፍራ ሀይልን የሚያስታጥቅ የእግዚአብሄር ቅዱስ መንፈስ አለ፡፡ አቀባበሉን ያስተዋለ፣ የፈለገ፣ የጠየቀና የተጠባበቀ ያን ሀይል ሊቀበል እንዳለው የእግዚአብሄር ቃል ኪዳን አለ፡፡
መሳ.15:14” ወደ ሌሒ በመጣ ጊዜም ፍልስጥኤማውያን እልል እያሉ ተገናኙት። የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ወረደበት፤ ክንዱም የታሰረበት ገመድ በእሳት እንደ ተበላ እንደ ተልባ እግር ፈትል ሆነ፥ ማሰሪያዎቹም ከእጁ ወደቁ።”
የእግዚአብሄር መንፈስ፡- የሚታደግ መንፈስ፣ የሚያስመልጥ መንፈስ፣ አቁዋም የሚያሲዝ መንፈስ ሀይልን በመስጠት መሆንን/ብቃትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፡፡
እግዚአብሄር ለአላማ ሀይል ይሰጣል
ታላቁ አምላክ እግዚአብሄር ወደ ምስኪኑ የሰው ልጅ ለምን ይመጣል? አይኑንስ ስለምን ወደ እርሱ ያደርጋል? ምን ፈልጎ ነው፣ አላማውስ ምንድነው? ሰው ትልቅ እንግዳ በቤቱ ድንገት ሲደርስ ይደነግጣል፣ እስኪገናኘውም ይዘጋጃል፣ ቤቱን በጥድፊያ ያስተካከላል፤ ስለእንግዳው ክብር፣ ስለእንግዳው ታላቅነትም ብዙ ጥንቃቄ ያደርጋል፡፡ ይሄ የተለመደ አቀራረብ ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ደግሞ ንጉሱን እግዚአብሄር የምንቀበልበት አቀባበል ከምንም በላይ የላቀ ሊሆን ተገቢ ነው፡፡ ያን አሰራር ያላስተዋሉ ነገር ግን የእግዚአብሄርን የሀይል መንፈስ ተቀብለው የነበሩ እንዴት ሊከስሩ እንደቻሉ ቀጥሎ ባለው ጥቅስ ውስጥ ከሳኦል ህይወት እንመለከታለን፡-
” …ከዚያም በኋላ የፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ወዳለበት ወደ እግዚአብሔር ኮረብታ ትመጣለህ፤ ወደዚያም ወደ ከተማይቱ በደረስህ ጊዜ፥ በገናና ከበሮ እምቢልታና መሰንቆ ይዘው ትንቢት እየተናገሩ ከኮረብታው መስገጃ የሚወርዱ የነቢያት ጉባኤ ያገኙሃል። የእግዚአብሔርም መንፈስ በኃይል ይወርድብሃል፥ ከእነርሱም ጋር ትንቢት ትናገራለህ፥ እንደ ሌላ ሰውም ሆነህ ትለወጣለህ።” (1ሳሙ.10:5-6)
”ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ በኃይል መጣ። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ አርማቴም ሄደ። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ፥ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ አሠቃየው። የሳኦልም ባሪያዎች፡- እነሆ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያሠቃይሃል” (1ሳሙ.16:13-15)
ንጉስ ሳኦል የንጉስ ቅባት ከማግኘቱ በፊት ፈሪና አይናፋር የነበረ ሰው ነው፡፡ የእግዚአብሄር ሀይል ሲወርድበት ደፋርና ሀያል መሪ ሊሆን በቃ፡፡ ንጉሱ ከእግዚአብሄር ጋር በተጣላ ጊዜ ግን የተቀበለው መንፈስ ሸሸውና ፈሪና አላማ ቢስ ሆነ፣ ጻድቁን ዳዊት አሳዳጅ፣ የእግዚአብሄርን ነቢይ ሳሙኤልንም የሚያሳዝን እግዚአብሄርንም የማይሰማ እልኸኛም ሆነና በፍጻሜው ተሸናፊ ሆነ፡፡
ይህ ንጉስ የእግዚአብሄር አላማ የገባው አይመስልም፤ ብዙ ጊዜ በራሱ ፈቃድ ሲወጣና ሲገባ እንጂ በእግዚአብሄር ፈቃድ ሲመራ አልታየምና፤ እንዲሁም የእግዚአብሄርን ስራ ብዙም ያስተዋለ አልሆነምና ከእግዚአብሄር ፈቃድ ጋር የሚጋጭ ሆነ፣ በዚያ አካሄዱ እየገፋ ሲሄድም መጨረሻውን በውድቀት አበላሸ፡፡
የእግዚአብሄርን አላማ ካስተዋልን አይቀር እንደብላቴናው ዳዊት፣ ፈቃዱን ከተከተልን አይቀር ከእረኝነት እስከ ንጉስነት ከእግዚአብሄር አላማ ጋር እንደተጉዋዘው እንደዚያ እንደ ዳዊት፤ ይሄ መቼም ያማረ እጣ ነው፡፡
ለድካማችን ሀይል ያስፈልጋል
እግዚአብሄር እንዲህ ይላል፡-
”ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቍጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም። ያዕቆብ ሆይ፥ እስራኤልም ሆይ፡- መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች ፍርዴም ከአምላኬ አልፋለች ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ? አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም። ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፥ ጕልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል። ብላቴኖች ይደክማሉ ይታክቱማል፥ ጐበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ፤ እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፥ አይደክሙም።” (ኢሳ.40:26-31)
የእግዚአብሄርን ቃልኪዳን ላነሳን ሀይል እንድንቀበል ብርቱ ተስፋ ገብቶልናል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሄር ተስፋ ቆርጣችሁ ከምታጉረመርሙ የኃይሌን ብዛትና የችሎቴን ብርታት መገለጫ የሆኑ ስራዎቼን ተመልከቱ አስተውሉም ይላል፡፡ ይህን እርሱ ሲል ለምን እስራኤል እግዚአብሄርን ከመለመን ደከመ?
መቼም ሀይል አያስፈልግም እንዳንል ከብዙ ነገር ጫና በታች እንደሆንን የሚታይ የሚታወቅም ነው፡፡ ምን ተመክተን ሀይልን አንለምንም፣ ወይም ምን አለን ብለን ተማምነን ቸል እንላለን? ይሄ መቼም ለማብራራት የሚያስቸግር ነገር ነው፣ በተለይ እግዚአብሄርን እናምናለን በሚሉት ዘንድ እየተዘወተረ ሲታይ ለበጎ እንዳልሆነ የሚታወቅ ብቻ ሳይሆን የሚያስፈራም ነው፡፡
እግዚአብሄር ሊታደገው የፈቀደ ነቢይ ግን ልቡንም እምነቱንም ወደ እርሱ ሲያነሳ የምንመለከትበት የመጽሀፍ ቅዱስ ክፍል አለ፡፡ ለዚህ ነቢይ እግዚአብሄር እምነትና ራእይ ልኮለት በዚያ ሁሉንም ስላመለከተው ነቢዩ ወደ እግዚአብሄር በልመና፣ በጾምና በጸሎት ቀርቦአል፤ የለመነውም እግዚአብሄር ሰምቶ ትምህርት፣ ራዕይና ታላቅ የማስተዋል ሀይል ሲሰጠው በዚያም ለወገኖቹ የሚሆንን የሩቅ ጊዜ መልእክትና ምሪት ሲቀበል እንመለከታለን (ዳን.9:3-27)፡፡
እርሱም፡-ማቅ ለብሼ በአመድም ላይ ሆኜ ስጾም እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ ወደ አምላክ አቀናሁ አለ፡፡… በጸሎት ስናገር አስቀድሜ በራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ፤ በማታም መሥዋዕት ጊዜ ዳሰሰኝ፣ አስተማረኝም፥ ተናገረኝም አለ።