የመስቀሉ ቃል የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን መከራ መቀበልና በሀይል ከሞት መነሳት የሚሰብክ የወንጌል ክፍል ነው፡፡
በዕብ.9:28 እንደተጻፈው፡-
”እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ፥ የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል።” ይላል፡፡
የሚበላ የህይወት እንጀራ ክርስቶስ ህያው በሆነው ስጋውና ደሙ ሊቀድሰንና ህይወትን ሊሰጠን ተገልጦአል፡፡ ወንጌልን አስደሳች የሚያደርገው በእርሱ መከራ የእኛ ደህንነት በመረጋገጡ፣ በእርሱ ሞት የእኛ የዘላለም ህይወት መምጣቱ፣ እንዲሁም በእርሱ ትንሳኤ ህያው ሆነን እንድንኖር የምስራች ማወጁ ነው፡፡ ሌላው ወንጌልን አስደናቂና አስደሳች ያደረገው በጻድቁ ሞትና ትንሳኤ የሀጢያተኛው ነጻነት መታወጅ በመቻሉ ሲሆን በሰው ገዳይና ጨካኝነት ላይ አምላክ ምህረት ማወጁ፣ በርሱ ላይ የተከፈተው ፍርድና የእዳ ጽህፈት/ፋየል በሞተልን በእርሱ ደም ሊሰረዝ መቻሉ የመስቀሉን ቃል ለተቀበለ ታላቅ ዋጋ ያሰጠዋል፡፡ የመስቀሉ ቃል መስቀሉ አካባቢ የተሰራውን መለኮታዊ አሰራር ባይገልጥ፣ አለምም ያንን ባታስተውል ከዘለለሙ አምላክ እቅድ ውጪ ትሆናለች ማለት ነው፡፡ መስቀሉ አካባቢ ምን ሆነ? መስቀሉስ ላይ? የመስቀሉን ፍርድ አዘጋጆችስ? የፍርዱስ ዋጋ? ከፍርዱ በሁዋላ የመጣው ነገርስ? እነዚህ እንቆቅልሾች የመስቀሉ ቃል የሚገልጣቸው ምስጢራት ናቸው፡፡
ማር.1:14-15 ”ዮሐንስም አልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና፡- ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ እያለ ወደ ገሊላ መጣ።”
ጌታ ኢየሱስ ወደ ምድር ከመጣና አገልግሎቱን በይፋ ከጀመረበት እስከ ፈጸመበት ጊዜ ድረስ የነበረው የአዋጁ ማእከላዊ ይዘት ወንጌል ነበር፤ ይህን ለደቀመዛሙርቱ አስረክቦ ወደ ሰማይ አርጎአል፡፡ ዘመኑ ተፈጽሞአል፣ የመጨረሻው ለሰው የተዘጋጀው የደህንነት በርም (ወደ እግዚአብሄር መንግስት የሚያስገባው) ተከፍቶአል ሲል ወንጌል በሚያስተምረው የመስቀል ስራ ደህንነትን በእምነት ተቀበሎ መዳን ተችሎአል፡፡ ደቀመዛሙርቱም ያንኑ መንገድ ተከትለዋል፤1ቆሮ.15:3-8 ውስጥ ባለው መልእክት ይህን ምስክር እናገኛለን፡-
”እኔ ደግሞ የተቀበልሁትን ከሁሉ በፊት አሳልፌ ሰጠኋችሁ እንዲህ ብዬ፡- መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነሣ፥ለኬፋም ታየ በኋላም ለአሥራ ሁለቱ፤ ከዚያም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ፤ ከእነርሱም የሚበዙቱ እስከ አሁን አሉ አንዳንዶች ግን አንቀላፍተዋል፤ ከዚያም በኋላ ለያዕቆብ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ ታየ፤ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ።”
መጽሀፉ የመዘገበው በመስቀሉ አካባቢ የሆነውን ድርጊት ሲሆን ያም በጌታ መከራ፣ ሞትና ትንሳኤ ላይ ያተኮረ እንደሆነ እንመለከታለን፡፡ የመስቀሉ ቃል ምስጢር ፋሲካን በአዲስ ኪዳን የገለጠ፣ ትንሳኤንም ያበራ ምስጢር ይዞአል፡፡ ይህ የመስቀሉ ቃል ሞኝነት የሆነባቸው እንዴት ምስኪኖች ናቸው? ሃዋርያትን በደስታና በትምክህት የሚንጥ የመስቀሉ ስራ ግን እንዴት ያለ እውቀት እንደተሸከመ ቀጥሎ ያለው ቃል ያሳያል፡-
1ቆሮ.2:1-8 ”እኔም፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ ለእግዚአብሔር ምስክርነቴን ለእናንተ እየነገርሁ አልመጣሁም። በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና። እኔም በድካምና በፍርሃት በብዙ መንቀጥቀጥም በእናንተ ዘንድ ነበርሁ፤እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፥ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፥ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም። በበሰሉት መካከል ግን ጥበብን እንናገራለን፥ ነገር ግን የዚችን ዓለም ጥበብ አይደለም የሚሻሩትንም የዚችን ዓለም ገዦች ጥበብ አይደለም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን። ከዚችም ዓለም ገዦች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር”
ቃሉ ሃዋርያው ጳውሎስ ወደ አማኞች ያደረገው ጉዞ እንደ ፈላስፎች፣ ተንታኞች ወይ ጻፎች ሆኖ ሳይሆን እንደ አንድ የክርስቶስ አምባሳደርና ምስክር ሆኖ እንደነበር ያመለክታል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተሰቀለ የሚያበስረውን የመስቀሉን ቃል ለማወጅ እንደቆረጠም ውሳኔውን አሳውቆአል፡፡ በእርሱ ዘንድ አንድ መረዳት ነበር፡- አይሁድ ከሚሹት ምልክት በላይ ግሪኮችም ከሚያዘወትሩት የጥበብ ምርምር ይልቅ እጅግ አስፈላጊ የሆነው የክርስቶስ መስቀል የፈጠረው ደህንነት እንደነበር ያሳስባል፡፡
ለሰዎች የተሰቀለው ጌታ ብቸኛው ትኩረት ካልሆነ ወንጌል መደናቀፍ እንደሚያገኘው ጠቁዋሚ ቃል ነው፡፡ ሀዋርያው ወንጌሉ ለሰዎች በማባበያ ቃል እንዲሰበክ ፈጽሞ እንደማይሻ በግልጽ አሳይቶአል፡፡ ክርስቶስን በመግለጥ ሰዎች እንዲለወጡና ወደ እውነት እንዲደርሱ ማድረግ እንጂ መሸንገል ሰውን ወደ ወንጌል እንደማያቀርብ አለማዊ መንገድ መከተልም ወደ ህይወት እንደማያደርስ አሳይቶአል፡፡ ሰዎች የተያዙትና የሚያምኑት በሰው ጥበብ መንገድ ከሆነ እውነትን ከሚገልጠው ወንጌል የህይወት መንፈስን ሊቀበሉ አይችልም፤ የእግዚአብሄርን መንግስት በቃሉ እንጂ በሰው ጥበብ መግለጥም አይቻልም፣ ሰማያዊው ብርሀንም በዚህ መንገድ ለሰዎች አይደርስም፡፡
ከማይደረሰው መንፈሳዊ አለም ክልል ውጪ የሆነው ከዚህ አለም የተቀበልነው እውቀት ሆነ ጥበብ መለኮታዊውን አሳብ ሊያሳውቀን ካልቻለ እለት እለት ከምንጋጠመው የጥፋት ተንኮል ልናመልጥ የነጻ ህሊናም ልንጎናጸፍ አንችልም ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የአለም እውቀት የሰማይ አምላክን ራእይ ስለማያመጣ ምስጢር የሆነው ክርስቶስን አያበራልንም፡፡ ነገር ግን ለመለኮታዊ ፈቃድ እንቅፋትን በመፍጠር፣ ከንቱ ፍልስፍናን ወደ መንፈሳዊ እውቀት በማስረግ የዘላለሙን አሳብ ከሰው ልጅ ተስፋ ውስጥ የሚነጥቅ፤ ያልተጠነቀቁ አማኞችንም ወግቶ የሚጥል ይሆናል፡፡
በቆላ.2:8 ”እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።” ያለው እናን ለማስጠንቀቅ ነው፡፡
በሌላ በኩል መድሀኒት የሆነውን የእግዚአብሄር ልጅ አውቀን ከዳንን በሁዋላ በሌላ አለማዊ እውቀት በኩል ከሚመጣ የትምህርት ነፋስ እንዳንወሰድ አጥልቀን በእምነት መመስረት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
ኤፌ4:12-14 ”ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም”
2.በመገረፉ ቁስል እንፈወስ ዘንድ ስለእኛ በመስቀል ላይ ሞቶአል
ጌታ ኢየሱስ ተሰቅሎ ስጋውን ቆረሰ፣ ደሙንም አፈሰሰ፡፡ ደም ሳይፈስ የሀጢያት ስርየት እንደሌለ የሚደነግገው የደህንነት ማረጋገጫ ጌታን እንዲህ አስከፍሎታል፡፡
1ጴጥ.2:22-25 እርሱም ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።”
ሀጢያት ያለበት ስጋና ደም ከቅዱሱና ጻድቁ አምላክ በሚመጣ መድሀኒት መዋጀት ያስፈልገዋል እንጂ አንዱ ለመሰሉ ራሱን ሰጥቶ ከፍርድ ሊታደግ አይችልም፡፡ ጌታ ኢየሱስ ግን ጻድቅና ቅዱስ ስለሆነ ስለሰው ሀጢያት ቤዛ መሆን ቻለ፡፡
በሮሜ.8:3-4 ውስጥ እንደተብራራው ክርስቶስ ኢየሱስ የሚቆስል፣ የሚደማና የሚደክም ስጋ ይዞ በሕግ ውስጥ የተቀመጠውን በከብቶች ደም የሚደረገውን የሀጢያት ስርየት ተክቶ ፍጹም በሆነው መለኮታዊ አሰራር ሰውን ነጻ ያደርግ ዘንድ ራሱን ለመስቀል ሞት አሳልፎ ሰጠ፡፡ ይህ የእግዚአብሔር አሰራር ሲሆን እግዚአብሄር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በኃጢአትም ምክንያት ልኮ ያን እንዳደረገው ቃሉ ያሳያል፤ እኛም ይህን የመስቀል ስራ ተቀብለን በቀረልን ዘመን እንደ መንፈስ ፈቃድ በሆነ የሥጋ ፈቃድን ባስወገደ ህይወት መመላለስ ይጠበቅብናል።
ሮሜ.5:6-9 ”ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና። ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን።” ሲል የደህንነት ብስራት ያነሳል፡፡
የተጣለን ማን ይወዳል፣ የተጠላንስ ማን ያነሳል? ሰዎች ጻድቅን የማጥፋት ዝንባሌ ተላበስን እንጂ ስለጻድቅ ራሳችንን መስጠት መች አዘወተርን? የምስራቹ ቃል ግን የክርስቶስን ሞት ለእኛ ለደካሞች ካለው ፍቅር ጋር ያስተሳስረዋል፡፡ የርሱ ፍቅር አሰቃቂው ፍርዳችንን በስጋው ሊቀበል ምህረትና ደስታ ያለበትን ደህንነት ከእርሱ ወደ እኛ ሊያስተላለፍ በራሱ ላይ እንደጨከነ ያሳያል፡፡ የማያስተውሉ ሁኔታውን ብቻ ያዩ ግን ከመመለስ ይልቅ መራቅን፣ አስተውሎ እግዚአብሄርን ከመፍራት ይልቅ ከሀጢያቱ የተነሳ ፍርድ እየተቀበለ እንዳለና በእግዚአብሔር እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም መቁጠርን መረጡ (ኢሳ.53:4)፡፡
3. አማኝ ህይወቱን እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ እንዲመራ
መጽሀፍ ቅዱስ በመስቀሉ ስራ ክርስቶስ ያመጣውን ጸጋ በግልጽ ያሳያል፡- ጌታ በመስቀል ላይ የሰራው ስራ በፍጥረት ጥረት የማይሳካ፣ በሀይሉና በብርታቱ የማይሞላ፣ እንዲሁም በአእምሮው ማስተዋል የማይታሰብና የማይከናወን ስለመሆኑ ቃሉ ያሳያል፡፡ እርሱ ለእኛ ለኃጢአተኞች የሞተው ገና በአስተሳሰብ ደካሞች፣ በማስተዋል ደካሞች፣ በተግባር ደካሞች፣ በአጋንንት ፊት ደካሞች፣ በአለም ፊት ደካሞች… በሁሉ ፊት ደካሞች ሳለን ነበር እንጂ አንዳች የራሳችን የሆነ መንፈሳዊ ጉልበት ወይም ጸጋ ኖሮን ሳለ እንዳልነበረ ግልጽ ነው፡፡
በ1ጴጥ.4:1-2 ላይ የምናገኘው መልእክትም የእኛን ቀሪ ህይወት በምን አይነት ውሳኔ ልንኖረው እንደሚገባ ምክር የሚሰጥ ነው፣ እንዲህ ይላል፡-
”ክርስቶስም በሥጋ ስለ እኛ መከራን ስለተቀበለ፥ ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋ ልትኖሩ በቀረላችሁ ዘመን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት እንዳትኖሩ፥ እናንተ ደግሞ ያን አሳብ እንደ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ ያዙት፥ በሥጋ መከራን የተቀበለ ኃጢአትን ትቶአልና።”
ጌታ መከራን ተቀብሎ የርሱን ደስታ ሰጥቶናል፣ መከራችንን በሞላ ከእኛ ወስዶ አርነትን ሰጥቶናል፤ ይህን ሲያደርግ እርሱ ተቀብሮ የቀረ ሳይሆን የተነሳ፣ ተስፋውን ይዘው የሞቱ ቅዱሳኖችንም ከሲኦል ያወጣ፣ ያም ብቻ ሳይሆን በትንሳኤው ሀይል በአዲስ ህይወት ከእርሱ ጋር እንድንኖር ያደረገው ነው፡፡
ስለዚህ በእግዚአብሄር ፈቃድ መሰረት የእኛ ቀሪ ዘመን ሀይል የሚመራው ዘመን መሆን አለበት፡- ይህም በስጋ ሳይሆን በመንፈስ መመራትን የሚፈቅድ፣ በራስ ፈቃድ ሳይሆን በእግዚአብሄር ፈቃድ ለመመራት ቦታ የሚሰጥ ሊሆን ይገባል፡፡
4. ጌታ እንደተሰቀለልን እኛም ለአለም መሰቀል ይገባናል
የመስቀሉ ቃል ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሰራውን ስራ የሚያጎላ ስለነበር የቃሉ ስልጣን በሃዋርያት ህይወት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ጎልቶ ታይቶአል፤ ትምህርቱም በአገልግሎታቸው ውስጥ ተገልጦአል፡፡ ወንጌሉ ሰውን ከአለም ተጽእኖ ነጻ በማውጣት ከእግዚአብሄር ምህረት ጋር የሚያጣብቅ በመሆኑ አስፈላጊነቱን አጉልተው ሰብከዋል፡፡ ክርስቶስ በመስቀሉ ፍቅር የጠራቸው አገልጋዮች የርሱን ማዳን ለሰው ልጆች ያደርሱም ዘንድ የእርሱን መከራ ተካፍለዋል፡፡ እነርሱም ሲናገሩ፡-
”የክርስቶስ ሥቃይ በእኛ ላይ እንደ በዛ፥ እንዲሁ መጽናናታችን ደግሞ በክርስቶስ በኩል ይበዛልናልና። ዳሩ ግን መከራ ብንቀበል፥ ስለ መጽናናታችሁና ስለ መዳናችሁ ነው፤ ብንጽናናም፥ እኛ ደግሞ የምንሣቀይበት በዚያ ሥቃይ በመጽናት ስለሚደረግ ስለ መጽናናታችሁ ነው።ተስፋችንም ስለ እናንተ ጽኑ ነው፤ ሥቃያችንን እንደ ተካፈላችሁ እንዲሁም መጽናናታችንን ደግሞ እንድትካፈሉ እናውቃለንና።” (2ቆሮ.1:5-7) ብለዋል፡፡
እግዚአብሔር በልጁ ስቃይ በኩል የሚሰጠን ምህረት በውስጣችን ደስተኞች እንድንሆን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም እንድተርፍ የሚያበቃ ነው። ይህ አሰራሩም ሃዋሪያት ላይ የተገለጠ ነበር፡፡
ጌታ ለተጨነቀ ሕሊና ሰላምን መስጠት እንዲሁም የታወከችውን ነፍስ ማረጋጋት ይችላል። እነዚህ በረከቶች በጌታ የተሰጡ ምህረቶች ናቸው። ወደ እርሱ ለሚመጡት ልባችሁ አይታወክ እያለ ያጽናናል። ይህንንም በተግባር ሲገልጥ የኃጢአትን ነጻ ይቅርታ በመስጠት ሲሆን ስራው ለነፍሶች ሰላምን አኑሮአል፤ በመንፈስ ቅዱስ መውረድ በጸጋው ብዙ ምሕረት ሰጥቶ ሰዎችን አጽናንቶአል፣ ዛሬም ያን ያደርጋል። የታሰሩትን መፍታት፣ ልባቸው የተሰበረውን መጠገን፣ መራራ መንፈሶችን ማጣፈጥ፣ የሚያሰቃዩ ቁስሎችን መፈወስ፣ እንዲሁም በከባድ ሀዘን ስር የተቀመጡትን ተስፋ እና ደስታ መስጠት ያውቃል።
ነገር ግን የጌታን ምህረት ከንቱ የሚያደርግ ትዕቢት፣ ከንቱ ስራና ሥጋዊ ልብ፣ ፍትሃዊነት ያጣ የህይወት ውጥንቅጥና ለመንፈሳዊ ማንነት የማይመች የህይወት ይዘት በስንፍና ለተወረሰ ሰው የማያመልጠው ወጥመድ ለህይወቱም የወንጌሉ ጠላት ያደርገዋል፡፡
ገላ.6:14 ”ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።”
እንግዲህ ትምክህት ቢያስፈልግ ከራስ በሚመነጭ እውቀት፣ አሳብም ሆነ ሃይል ሳይሆን በመስቀሉ ስራ ሊሆን የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ከወደደን በላይ እራሳችንን ልንወድ አንችልም፤ ስለዚህ እርሱ ከሰራልን የጽድቅ ስራ በላይ የሚያጸድቀንን ስራ አንመኝ፤ በዚህ ሀይላችንን፣ ተስፋችንን፣ በጎነትና መታመኛችንን ላለማጣት መጠንቀቅ እንዲሁም ስራውን የህይወታችን መታመኛ ማድረግ ይገባናል፡፡