እግዚአብሄርን የሚጸየፈው መስዋእት አለ፣ እግዚአብሄር የማያውቀው መስዋእትም አለ፣ ደግሞ እግዚአብሄር የሚቀበለው መስዋእት አለ (ይህን መስዋእት መልአክ ራሱ ይዞት ወደ ሰማይ ያርጋልና ታላቅ መስዋእት ነው)
“ማኑሄም የፍየሉን ጠቦትና የእህሉን ቍርባን ወስዶ በድንጋይ ላይ ለእግዚአብሔር አቀረበው። መልአኩም ተአምራት አደረገ፥ ማኑሄና ሚስቱም ይመለከቱ ነበር። ነበልባሉም ከመሠዊያው ላይ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ የእግዚአብሔርም መልአክ በመሠዊያው ነበልባል ውስጥ ዐረገ፤ ማኑሄና ሚስቱም ተመለከቱ፥ በምድርም በግምባራቸው ተደፉ።”(መሳ.13:19-20)
የእግዚአብሄር ቅዱሳን ጸሎት ወደ ሰማይ ወደ እግዚአብሄር ፊት እንደሚያርግ ማወቅ ከፍተኛ እምነት ይሰጣል። በደሙ በመቀደስ በፊቱ ነውር የሌለው መስዋእት ማቅረብ እግዚአብሄርን ደስ ያሰኛል።
ራእ.8:2-5″በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፥ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው። ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሰዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ።መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሰዊያውን እሳት ሞላበት ወደ ምድርም ጣለው፤ ነጐድጓድና ድምፅም መብረቅም መናወጥም ሆነ።”
1.እግዚአብሄርን የሚጸየፈው መስዋእት
ይህን መስዋእት እግዚአብሄር ለምን ይጸየፈዋል? ሰዎች እግዚአብሄርን እያወቁ እንደ እግዚአብሄርነቱ ካላከበሩት በርሱ ዘንድ የነርሱ ነገር ሁሉ ጸያፍ ነው። ቅዱሱን አምላክ ያለመከተል፣ ግን አውቀዋለሁ ብቻ ማለት ከእርሱ ጋር አያኖርም፤ ከርሱ ጋር በአንድነት ካልተመላለስንም ከእርሱ ጋር ያለን ግንኙነት ጤናማ አይደለም ማለት ነው።
“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው? እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ። በሬን የሚያርድልኝ ሰውን እንደሚገድል ነው፤ ጠቦትንም የሚሠዋ የውሻውን አንገት እንደሚሰብር ነው፤ የእህልን ቍርባን የሚያቀርብ የእርያን ደም እንደሚያቀርብ ነው፤ ዕጣንን የሚያጥን ጣዖትን እንደሚባርክ ነው። እነዚህ የገዛ መንገዳቸውን መረጡ፤ ነፍሳቸውም በርኵሰታቸው ደስ ይላታል፤ እኔ ደግሞ የተሳለቀባቸውን እመርጣለሁ፥ የፈሩትንም ነገር አመጣባቸዋለሁ፤ በፊቴ ክፉ ነገርን አደረጉ፥ ያልወደድሁትንም መረጡ እንጂ በጠራሁ ጊዜ አልመለሱልኝምና፥ በተናገርሁም ጊዜ አልሰሙኝምና።”(ኢሳ.66:1-4)
ከአምልኮና ምስጋና አስቀድሞ እግዚአብሄር በልጆቹ ህይወት ማየት የማይፈልገው እንዲወገድም የሚፈልገው ባህሪ ትእቢት (ትሕትና ማጣት)፣ ልብ መደንደን (የመንፈስ ጥንካሬ) እና ቃሉን ያለመፍራት (በቃሉ ያለመንቀጠቀጥ) ናቸው። በዚህ ባህሪ ንጉስ ሳኦል እስኪወድቅ ድረስ ተጠምዶ ነበር፣ በስተመጨረሻ ገፍቶ ከንግስና አወረደው።
“ሳኦልም ሳሙኤል እንደ ቀጠረው ጊዜ ሰባት ቀን ቆየ፤ ሳሙኤል ግን ወደ ጌልገላ አልመጣም፥ …ሳኦልም፦ የሚቃጠል መሥዋዕትና የደኅንነት መሥዋዕት አምጡልኝ አለ። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አሳረገ። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ማሳረግ በፈጸመ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሳሙኤል መጣ፤ ሳኦልም እንዲመርቀው ሊገናኘው ወጣ።ሳሙኤልም፦ ያደረግኸው ምንድር ነው? አለ። ሳኦልም፦ …ፍልስጥኤማውያን አሁን ወደ ጌልገላ ይወርዱብኛል፥ እኔም የእግዚአብሔርን ሞገስ አልለመንሁም አልሁ፤ ስለዚህም ሳልታገሥ የሚቃጠልን መሥዋዕት አሳረግሁ አለ። ሳሙኤልም ሳኦልን፦ አላበጀህም፤ አምላክህ እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዝ አልጠበቅህም፤ ዛሬ እግዚአብሔር መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም አጽንቶልህ ነበረ። አሁንም መንግሥትህ አይጸናም፤ እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሆነ ሰው መርጦአል፤ እግዚአብሔርም ያዘዘህን አልጠበቅህምና እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ አዝዞታል አለው።” (1ሳሙ.13:8-14)
ሳኦል ወደ እግዚአብሄር የሚቃጠልን መስዋእት አሳረገ፣ መስዋእቱን ማሳረግ የነበረበት ሳሙኤል ሆኖ ሳለ የእግዚአብሄርን ሥርአት በትእግስት አልጠበቀም። እግዚአብሄር በሳኦል ልብ የነበረውን ቸልተኝነት ተመልክቶ አዘነበት። ወደ እርሱ መመልከትም አቆመ፣ ሳኦል ተጨንቆ በጠራውም ጊዜ አልመለሰለትም። የሳኦል መጨረሻም አላማረም፦ በጠላት ተከቦ፣ ተሸንፎና ተዋርዶ ሞተ፣ ስልጣኑን ከቤቱ ተገፈፈ፣ ከርሱ በሁዋላ የሚነግስ ልጅም አጣ።
2ዜና.26:13-21 ውስጥ እንደምንመለከተው እግዚአብሄርን የሚወድ ንጉስ በይሁዳ ተነስቶ ነበር፤ ይህ ንጉስ እግዚአብሄርን ባስቀደመ ዘመን ሁሉ በሁሉ ነገር ስኬታማ ነበር፤ በተለይ እግዚአብሔርን መፍራት ባስተማረ በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ይፈልግ ዘንድ ልብ አደረገ፤ እግዚአብሔርንም በፈለገ ጊዜ እግዚአብሔር ነገሩን አከናወነለት። ነገር ግን በበረታ ጊዜ ለጥፋት ልቡ ታበየ፣ ብርታትና ችሎታ የርሱ የራሱ ሃይልና ችሎታ መሰለውና አመጸ፥ ያገዘውን አምላኩንም እግዚአብሔርን በደለ፤ ጭርሱን ወደ መቅደስ ገብቶ በዕጣን መሠዊያ ላይ ዐጠነ፣ ዖዝያን መንፈሱ በትቢት ምክኒያት ተበላሸ፣ ራሱን ለቅጣት አሳልፎም ሰጠ።
አስቀድሞ እግዚአብሄርን መፍራቱን ያውቅ የነበረው ካህኑ ዓዛርያስ ከእርሱም ጋር ጽኑዓን የነበሩ ሰማንያ የእግዚአብሔር ካህናት ተከትለው ወደ መቅደስ ገቡ። ንጉሡንም ዖዝያንን ይከለክሉት ዘንድ ሞከሩ፣ በህጉ ላይ ስለክህነት የተጻፈውን ከሌዊ ክህነት ውጪ ማጠን የሚያመጣውን ቅጣት አስተውለው ለመኑት፦ ዖዝያን ሆይ፥ ዕጣን ማጠን የተቀደሱት የአሮን ልጆች የካህናቱ ሹመት ነው እንጂ ለእግዚአብሔር ታጥን ዘንድ ለአንተ አይገባህም፤ በድለሃልና ከመቅደሱ ውጣ አሉት፤ አስቀድሞ እንደሆነው ያለ ክብር በዚህ ድርጊትህ አይሆንልህም ተው አሉት። ዖዝያን ግን በነርሱ ተቈጣ፣ እንዴት ተናገሩኝ በሚል ትእቢት ተናወጠ፤ ግን አልበጀውም፣ ከመቅሰፍትም አላመለጠም፣ ካህኑ እንደተናገረው እግዚአብሄር ቀሰፈው፤ እንዲያውም ሰው ፊት እንዳይቀርብ፣ ተደብቆ እንዲኖር፣ እንዲያፍርና እንዲሸማቀቅ፣ እስከህይወቱ ፍጻሜም ወደ አደባባይ እስካይወጣ ድረስ በከባድ ለምጽ መታው።
“ንጉሡም ዖዝያን እስኪሞት ድረስ ለምጻም ነበረ፤ ለምጻምም ሆኖ ከእግዚአብሔር ቤት ተቈርጦአልና በተለየ ቤት ይቀመጥ ነበር፤ ልጁም ኢዮአታም በንጉሡ ቤት ላይ ሆኖ በምድሩ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ነበር።” ከእግዚአብሄር ቤት ተቆርጦአልና ከአምልኮ ተቆረጠ፣ አሳዛኝ ነገርም ሆነበት።
2.እግዚአብሄር የማያውቀው መስዋእትም አለ
እግዚአብሄርን የማያውቁ ሰዎች የሚያቀርቡትን ምስጋና፣ አምልኮና ጸሎት አይሰማም፣ በፊቱ የተጠሉ በመሆናቸው እርኩስ ናቸው። አህዛብ የሚያመልኩትና የሚሰዉት ለጋንንት ነው፦
“አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳቸው ዘንድ የምትሄድባቸውን አሕዛብን በፊትህ ባጠፋ ጊዜ፥ አንተም በወረስሃቸው ጊዜ፥
በምድራቸውም በተቀመጥህ ጊዜ፥ ከፊትህ ከጠፉ በኋላ እነርሱን ለመከተል እንዳትጠመድ። እነዚህስ አሕዛብ አማልክቶቻቸውን ያመለኩት እንዴት ነው? እንዲሁ ደግሞ እኔ አደርጋለሁ ብለህ ስለ አማልክቶቻቸው እንዳትጠይቅ ተጠንቀቅ። እግዚአብሔር የሚጠላውን ርኵሰት ሁሉ እነርሱ ለአማልክቶቻቸው አድርገዋልና፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን ደግሞ ለአማልክቶቻቸው በእሳት ያቃጥሉአቸዋልና አንተ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር እንዲሁ አታድርግ።”(ዘዳ.12:29-31)
የአህዛብን ልማድ እግዚአብሄር የጠላው ህያው አምላክን ማምለክ ስላልለመዱ፣ ዝምድናቸውም ከአጋንንት ጋር በመሆኑ ነው፦
“ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ዕለት ዕለት ማዳኑን አውሩ። ክብሩን ለአሕዛብ፥ ተአምራቱንም ለወገኖች ሁሉ ንገሩ። እግዚአብሔር ታላቅ፥ ምስጋናውም ብዙ ነውና፤ በአማልክትም ሁሉ ላይ የተፈራ ነው። የአሕዛብ አማልክት ሁሉ ጣዖታት ናቸው፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ። ክብርና ግርማ በፊቱ፥ ኃይልና ደስታ በስፍራው ውስጥ ናቸው። የአሕዛብ ወገኖች ለእግዚአብሔር አምጡ፥ ክብርንና ኃይልን ለእግዚአብሔር አምጡ። ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር አምጡ፤ ቍርባንን ይዛችሁ በፊቱ ግቡ፤ በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ።” (1ዜና 16:14-23)
3. እግዚአብሄር የሚቀበለው መስዋእት አለ
(ይህን መስዋእት መልአክ ራሱ ይዞት ወደ ሰማይ ያርጋልና ታላቅ መስዋእት ነው)
“ኑ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን፤ ለአምላክ ለመድኃኒታችን እልል እንበል። በምስጋና ወደ ፊቱ እንድረስ፥ በዝማሬም ለእርሱ እልል እንበል፤ እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነውና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ ታላቅ ንጉሥ ነውና። እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥላቸውም፤ የምድር ዳርቻዎችም በእጁ ውስጥ ናቸው፥ የተራሮች ከፍታዎች የእርሱ ናቸው። ባሕር የእርሱ ናት እርሱም አደረጋት፥ የብስንም እጆቹ ሠሩአት። ኑ፥ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ፤ በእርሱ ባደረገን በእግዚአብሔር ፊት እንበርከክ፤ እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና።” (መዝ.95:1-5)
-መስዋእታችን ተቀባይነት እንዲኖረው በእግዚአብሄር ፊት ሞገስን እንቀበል
በምድር ከበቀለው ፍሬና ከከብቶች ፍሬ ለማቅረብ ከምንሻው መስዋእት በላይ ራሳችንንና የከንፈራችንን ፍሬ በማቅረብ እግዚአብሄር እንዲያሸተው በፊቱ ሞገስን ማግኘት ያስፈልጋል፦
ዘጸ12፡23-29 “እግዚአብሔር ግብፃውያንን ይመታ ዘንድ ያልፋልና፤ ደሙንም በጉበኑና በሁለቱ መቃኖች ላይ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር በደጁ ላይ ያልፋል፥ አጥፊውም ይመታችሁ ዘንድ ወደ ቤታችሁ እንዲገባ አይተውም። ለእናንተ ለልጆቻችሁም ለዘላለም ሥርዓት አድርጋችሁ ይህችን ነገር ጠብቁ። እንዲህም ይሆናል፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ወደ ሚሰጣችሁ አገር በገባችሁ ጊዜ ይህን አምልኮ ጠብቁት። እንዲህም ይሆናል፤ ልጆቻችሁ፦ ይህ አምልኮ ለእናንተ ምንድር ነው?ባሉአችሁ ጊዜ፥ እናንተ፦ በግብፅ አገር በእስራኤል ልጆች ቤቶች ላይ አልፎ ግብፃዊያንን በመታ ጊዜ፥ ቤቶቻችንን ያዳነ የእግዚአብሔር የማለፉ መሥዋዕት ይህች ናት ትሉአቸዋላችሁ። ሕዝቡም ተጎነበሰ ሰገደም፦ የእስራኤልም ልጆች ሄዱ፥ እንዲሁም አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ። እንዲህም ሆነ፤ እኩል ሌሊት በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር፥ በዙፋን ከተቀመጠው ከፈርዖን በኵር ጀምሮ በግዞት እስካሉት እስከ ምርኮኞቹ በኵር ድረስ፥ የግብፃውያንን በግብፅ ምድር የተገኘውን በኵር ሁሉ፥ የእንስሳውንም በኵሮች ሁሉ መታ።”
የእግዚአብሄር ህዝብ ሊተወው የማይችል ሁሌም የሚፋለመው ጠላት አለው (የእስራኤላውያን ጠላቶች የገዟቸው ግብጻውያን እንደነበሩት ሁሉ)፤ ስለዚህ ከጠላት ዲያቢሎስ ለማምለጥና ተፈትተን እርሱን ማምለክ እንድንችል ነጻ መውጣት አለበት፤ መታመኛችንም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ብቻ ነው። በዚህ እግዚአብሄር ፍጹሙን መስዋእት ለእኛ አቅርቦአል፤ ስለዚህ ከራሳችን መጠበብ ይልቅ ወደ እግዚአብሄር የምንቀርብበትን መንገድ ማወቅ ያስፈልጋል። እግዚአብሄርም የሚፈልገውን በኢሳ.1:14-20 ሲናገር፦
“መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፥ ልታገሣቸውም ደክሜያለሁ። እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ፥ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል። ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ፤ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግን ተዉ፥መልካም መሥራትን ተማሩ፥ ፍርድን ፈልጉ፥ የተገፋውን አድኑ፥ ለድሀ አደጉ ፍረዱለት ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ። ኑና እንዋቀስ ይላል እግዚአብሔር፤ ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች።እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እምቢ ብትሉ ግን ብታምፁም፥ ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።”
እግዚአብሄር እንዲቀበለን እግዚአብሄር ራሱ እንዲሰራልንም አሰራሩን ብንመርጥ ይሻላል፤ ያን የሚያስተውል ይጠቀማልና፤ ስለዚህ ታጠቡ ሰውነታችሁንም አንጹ፤ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፤ ክፉ ማድረግን ተዉ፥መልካም መሥራትን ተማሩ፥ ፍርድን ፈልጉ፥ የተገፋውን አድኑ፥ ለድሀ አደጉ ፍረዱለት ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ ያለውን አጥብቀን መያዝና መታዘዝ ይገባል።በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ምሥዋእትን እንዴት ማቅረብ እንዳለብን የሚያስተምረን ክፍል አለ፦
-ቅድሚያ ራስን የተወደደ ተቀባይነት ያለው መስዋእት አድረጎ ማቅረብ
ሮሜ.12:1 “እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው።”
-የተወደደ መስዋእት በመንፈስ ቅዱስ በመቀደስ
ሮሜ.15:19″ነገር ግን አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ ተቀድሰው የተወደደ መሥዋዕት ሊሆኑ፥ ለእግዚአብሔር ወንጌል እንደ ካህን እያገለገልሁ፥ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ እሆን ዘንድ ከእግዚአብሔር በተሰጠኝ ጸጋ ምክንያት ተመልሼ ላሳስባችሁ ብዬ በአንዳንድ ቦታ በድፍረት ጻፍሁላችሁ።”
-ለእኛ ከሆነ ነገር በፍቅር መስዋእት አድርገን ማቅረብ
ፊል.4:18-19 “ነገር ግን ሁሉ አለኝ ይበዛልኝማል፤ የመዓዛ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት የሚሆነውን ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታችሁን ከአፍሮዲጡ ተቀብዬ ተሞልቼአለሁ። አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል።”
-ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሆኑ የምስጋና መስዋእትን እናቅርብ
(እብ.13:16-17) “እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት፥ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፥ በእርሱ እናቅርብለት። ነገር ግን መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና።”
ቃሉ እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ የሚለው እግዚአብሄር በህይወታችን የሰራው አዲስ ሰውን የመፍጠር ስራ በእኛ ላይ ስለተከናወነ ነው፤ አስቀድሞም በቁጣ ስር ስለነበርን ከእርግማን የምናመልጥበት ማምለጫ መንገድ አልነበረም፣ ነገር ግን እግዚአብሄር ማረን፤ እናንተ ምሕረት ያገኛችሁ አልነበራችሁም በተባልንበት አሁን ግን ምሕረትን አገኘን፣ ቀላል ነገር አይደለም። ስለዚህ ጌታ ቸር መሆኑን የቀመስን፣ ህይወትን የተካፈልን ህያው መስዋእት ለማቅረብ ክርቶስን የለበሰችን ነፍስ ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት እንርቅ ዘንድ የእግዚአብሄር ቃል ያሳስባል።
-መንፈሳዊ መስዋእት ለማቅረብ መንፈሳዊ ቤት መሆን
“በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ። በመጽሐፍ፦ እነሆ፥ የተመረጠና የከበረን የማዕዘን ራስ ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ በእርሱም የሚያምን አያፍርም ተብሎ ተጽፎአልና። እንግዲህ ክብሩ ለእናንተ ለምታምኑት ነው፤ ለማያምኑ ግን አናጢዎች የጣሉት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ የዕንቅፋትም ድንጋይ የማሰናከያም ዓለት ሆነ፤ የማያምኑ ስለ ሆኑ በቃሉ ይሰናከሉበታልና፤ ለዚህ ደግሞ የተመደቡ ናቸው።”
መንፈሳዊ መስዋእትን ለማዘጋጀትና ለማቅረብ የሚተጉ ወገኖች የአዲስ ኪዳን ካህናት ናቸው፤ መንፈሳዊ ቤት ሆነው ክርስቶስን በለበሰ መንፈሳዊ ማንነት የተዘጋጁና ከኖሩበት ጨለማ ወጥተው ወደሚደነቅ ብርሃኑ የተጠሩ ስለሆነ መንፈሳቸው እርሱን ለማምለክ ዝግጁ ነው፤ ከውሃና ከመንፈስ የተወለደና የተመረጠ ትውልድ፣ የአዲስ ኪዳን አዋጅ ነጋሪዎች፣ የንጉሡ የኢየሱስ ክርስቶስ ካህናት፥ በደሙ የነጹ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለሰማያዊው ርስት ከምድር አህዛብ የተለየ ወገን ናቸው፤ መንፈሳውያን ስለሆኑም መንፈሳዊ መስዋእት ማቅረብም የሚችሉ ናቸው።