እግዚአብሔር እረኛዬ ነው[3/3]

የእግዚአብሄር ፈቃድ

መዝ.23:3 ነፍሴን መለሳት፥ ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ።

ነፍስ ከየት ወዴት ተጉዛ ወዴት ትመለሳለች? ወይስ ምን የሚያሳስባት ጉዳይ ቢገጥማት ከመንገድዋ ፊትዋን ትመልሳለች? በነፍስ ጉዳይስ የሚያሳስብ ጉዳይ ምን ኖሮ መመለስን ትመርጣለች? መቼም ቢሆን ከተቃናልን የህይወት እርምጃ መመለስ፣ከተሳካልን ድል ወደ ሁዋላ ማለት፣ከተጉዋዝንበት ርዝመት ያለው መንገድ  ማፈግፈግ ወይም የማስጠንቀቂያ ደውል ሰምተን የእኛ የምንላቸውን ለመሸሸግ ሙከራ ማድረግ፣ እንዲህ ቀላል ጉዳይ ላይሆን ይችላል፡፡ ያ አሳማኝ ውሳኔ ሊያውም ዋጋ የሚያስከፍል፣ውጤቱን ነፍሳችን መርጣ ታከናውነው ዘንድ ልብዋን ሙልት የሚያደርግ እውነት ትፈልጋለች፡፡

ሰዎች ሁላችን እግዚአብሄር አስረግጦ በቃሉ የተናገረው ሀጢያት ያለብን፣ በየእለቱም ሳናቁዋርጥ ያን ከማድረግ የማናቆም መሆኑን ይመሰክርብናል፡፡በተለያየ ደረጃ የሚገለጥና በውስጣችን ያለ ትእቢት የተባለ ታላቅ ድፍረት ብዙውን የእግዚአብሄር ህግጋትና ስርአት በመጣስ እንድንጉዋዝ ያደርጋል፡፡በዚህ ምክኒያትም ሀጢያት እንድንሰራና እንድንተላለፍ መንገድ ሆኖአል፡፡የሃጢያታችን ውጤትም የህይወት ጥፋት መሆኑ አስፈሪ እውነት ነው፡፡

ኢዮ.33:14-18 “እግዚአብሔር በአንድ መንገድ በሌላም ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውለውም።በሕልም፥ በሌሊት ራእይ፥ አፍላ እንቅልፍ በሰዎች ላይ ሲወድቅ፥ በአልጋ ላይ ተኝተው ሳሉ፥ በዚያን ጊዜ የሰዎችን ጆሮ ይከፍታል፥ በተግሣጹም ያስደነግጣቸዋል፥ሰውን ከክፉ ሥራው ይመልሰው ዘንድ ከሰውም ትዕቢትን ይሰውር ዘንድ፤ነፍሱን ከጕድጓድ፥ በሰይፍም እንዳይጠፋ ሕይወቱን ይጠብቃል።”

እግዚአብሄር ሰው የተባለን ፍጥረቱን ከጥፋት ሊመልስ ምን ያህል ርቀት እንደሚጉዋዝ ቃሉ ያሳያል፡፡ነፍስ አንድ ያልተሳካ መንገድ ላይ ሆና ስትቀዝፍ የሚያይ ጌታ በእርሱ አሰራር አንዱን መንገድ ይጠቀምና ከዚያ ያድናታል፡፡ነገር ግን ሲናገር ድምጹን ትለያለችን? በምላሹስ ፈጣን መልስ ትሰጣለች ወይ?

መዝ.116:7 “ነፍሴ ሆይ፥ ወደ ዕረፍትሽ ተመለሺ፥ እግዚአብሔር መልካም አድርጎልሻልና፤ነፍሴን ከሞት፥ ዓይኔንም ከእንባ፥ እግሬንም ከመሰናከል አድኖአልና።በሕያዋን አገር በእግዚአብሔር ፊት እሄዳለሁ።”

የእግዚአብሄር ማስደንገጥና ተግሳጽ ለስጋችን ጭንቅና ህመም ሊሆን ይችላል፡፡ነፍሳችን ግን ከጉድጉዋድ እንድትተርፍ ህይወታችንም ከሰይፍ ጥፋት እንድትድን ያደርጋል፡፡እግዚአብሄር ሲመልሰንም ወዲያው ወደ ጽድቅ መንገድ ውስጥ ያስገባናል፡፡ጉዳትን የሚክስ አምላክ በተምችና ኩብኩባ የተበላውን በረከት ወዲያው ካሳ አድርጎ ይሰጣታል፡፡ዓይናችን ከእንባ፥ እግራችንም ከመሰናከል ይድንና በሕያዋን አገር በእግዚአብሔር ፊት እንሄዳለን።

መዝ.17:14 “አቤቱ፥ ከሰዎች፥ እድል ፈንታቸው በሕይወታቸው ከሆነች ከዚህ ዓለም ሰዎች በእጅህ አድነኝ፤ ከሰወርኸው መዝገብህ ሆዳቸውን አጠገብህ፤ ልጆቻቸው ብዙ ናቸው የተረፋቸውንም ለሕፃናቶቻቸው ያተርፋሉ።እኔ ግን በጽድቅ ፊትህን አያለሁ፤ ክብርህን ሳይ እጠግባለሁ።”

የተመለሰች ነፍስ በህያው አምላክ መንገድ ስለምትገባ በመንገዱ ላይ ያለው የአምላክ ክብር ያገኛታል፡፡በዚያም የተወሰደባት ይመለስላታል፣የተነጠቀችውን ሁሉ ምርኮ አድርጎ ይሰጣታል፣ለምና ያልተሳካላት አሁን አካሄድዋን አሳምራለችና  በሙሉ መልስ ሆኖ ወደ ጎተራዋ ይዘረገፋል፡፡ምክኒያቱም እርሱ ተናግሩዋልና፡፡

መዝ.23:4 በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኵዝህ እነርሱ ያጸናኑኛል።

ኢዮ.10:20-22 “የሕይወቴ ዘመን ጥቂት አይደለምን? ወደማልመለስበት ስፍራ፥ ወደ ጨለማና ወደ ሞት ጥላ ምድር፥ እንደ ጨለማም ወደ ጨለመች፥ ሥርዓትም ወደሌለባት ወደ ሞት ጥላ፥ ብርሃንዋም እንደ ጨለማ ወደ ሆነ ምድር ሳልሄድ፥ ጥቂት እጽናና ዘንድ ተወኝ፥ ልቀቀኝም።……”

የሰው ልጅ ገጠመኝ እንዴት ብዙና ውስብስብ ነው? ከፍታውና ዝቅታው ብዛቱ፣ማጣትና ማግኘቱ፣ማዘንና መደሰት መፈራረቁ፣መሳቅና ማልቀስ ያለመጥፋቱ፣መኖርና መሞት አይቀሬ መሆኑ…. ብዙ ብዙ ነገር አለበት፡፡እንዲያውም ከተሰጠው እድሜ ጋር ሲነጻጸር የሚገጥመው ውጣ ውረድ ከዘመኑ ይልቅ የበዛ ነው፡፡ብዛቱና ውስብስብነቱ በአካባቢ፣በሀገር፣በስልጣኔ በጾታና በመሳሰለው የሚለያይ ቢሆንም ያው የተባለው ገጠመኝ ግን በተረገመችው ምድር ላይ ለሰው ልጅ እድል ፋንታው ነው፡፡ደግሞ ህልውናውን እግር ለእግር  የሚከታተል ያ ሁሉ አስጨናቂ ገጠመኝ ሳያንስ መጨረሻው ላይ አለሁ ባይ ሞት ከሁሉም ይልቅ አድካሚ፣አስፈሪና አስጨናቂ  ሆኖ ይመጣል፡፡የሰው ልጅ እድሜ እንደምትጠልቅ ጸሀይ ወደ ማምሻው ሲያዘግም በመንገድ ላይ ወለል ብሎ የሚታይ ያህል ሞት ደርሶ ግልጥና እውን ይሆናል፡፡ይሄ ግን የማይቀረው የስጋ እድል ፈንታ ነውና ሰዎች ሁሉ አምነው ቢቀበሉት የተሻለ ነው፡፡መኖር እንዳለ መሞትም አስገዳጅ የተፈጥሮ ክስተት መሆኑን መቀበል የግድ ነው፡፡ነገር ግን ቢያሳስበን ልናስብበት የሚገባን፣ቢያስጨንቀን እጅግ ልንጨነቅበት የሚያስፈልግ ዘላለማዊው የነፍስ ሞት ነው፡-ያ ዘላለማዊ ፍርድ ነው ስለዚህ ያስጨንቃል፡፡ሰው ለሰባ አመት ኑሮ ከተጨነቀ ለዘላለም ህይወት እንዴት አብልጦ መጨነቅ አያስፈልገው!

እዮብ ሄዶ ሊመለስ የማይችልበትና ለዘላለምም ተይዞ የሚቀርበት አንድ ስፍራ ታይቶት ስለዚያ በፍርሀት ጻፈ፡፡እንዲያውም ስፍራው ብቻ አይደለም፣ያን ስፍራ የተቆጣጠረ አንድ አስፈሪ ድባብም ታይቶታል፡፡ስፍራው ደስታ የለበትም ፣ጭልም ድርግም ያለ የእግዚአብሄር ተስፋ መቼም የማያገኘው አስፈሪ የፍርድ ስፍራ ነው፡፡ያን ስፍራ ደግሞ የተቆጣጠረ መንፈስ አለ፡፡የሰው ነፍስ ወደዚያ እንድትወረወር የሚያደርግና ሀጥያት በተባለ መሳርያ ሰውን ከእግዚአብሄር የሚያለያይ ክፉ የሞት መንፈስ አለ፡፡እርሱ ሁሌም ጥላውን በነፍስ ላይ ያጠላል፣ነፍስ አርነት እንዳታገኝ የሚጨቁን ክፉ ነው፡፡ሀዋርያው ጳውሎስ ስለእርሱ ምን አለ?      

እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ።(ዕብ.2:14-15)

የኢየሱስ ስራ ግን አስደናቂ ነው?! የሞት መንፈስ ሁልጊዜ  ስለሞት እያሰብን ተስፋ እንድንቆርጥ እንዳላደረገ፣ጌታ ኢየሱስ ለእኛ የተመደበውን ሞት ራሱ በመሞት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በትንሳኤ ሀይሉ ሻረው፡፡ጌታ ኢየሱስ ዲያቢሎስ ሲያስፈራራበት የነበረውን ሞት በሞቱ አስወገደበት፡፡ይህ ብስራት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲነገር የነበረውን አስደሳች ሁኔታ እኛም አሁን ልናነሳ በጣም ያስፈልጋል፣ የእኛን ነገር ለዘላለም የለወጠው ዜና እርሱ ነውና፡፡ እንዲህም ይላል፡-

ሉቃ1:67-79 “….ዘካርያስም መንፈስ ቅዱስ ሞላበትና ትንቢት ተናገረ እንዲህም አለ።የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፥ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና፤ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያት አፍ እንደ ተናገረ፥ በብላቴናው በዳዊት ቤት የመዳን ቀንድን አስነስቶልናል፤….ለአባታችን ለአብርሃምም የማለውን መሐላውን ቅዱሱን ኪዳን አሰበ፤በእርሱም ከጠላቶቻችን እጅ ድነን በዘመናችን ሁሉ ያለ ፍርሃት በቅድስናና በጽድቅ በፊቱ እንድናገለግለው ሰጠን።……ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፤ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል።”

የሞት ጥላ በተለያየ መንገድ ሰው ላይ ያጠላል፡፡የሞት ጥላ በነፍስ ላይ፣በመንፈስ ላይና በአእምሮ ላይ ያጠላል፡፡የሞት ጥላ ነፍስን ሊያጠምድ በላይዋ ይወጣል፡፡ያኔ ነፍስ ትታሰራለች፣ሞት ወጥመድ ውስጥ ትገባለች፡፡እንዲሁም የሞት ጥላ መንፈሳችን ላይ ሲያጠላ ከእግዚአብሄር ጋር ያለን ግንኙነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ግንኙነታችን ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ የቁዋረጣል፡፡መንፈስ ብርሀንዋ በጨለማ ይዋጣል፣ያኔ ከመለኮታዊ ማስተዋል ውጪ ትሆናለች፡፡የሞት ጥላ በአእምሮ ላይ ሲያጠላ መንፈሳዊ እውቀትና ማስተዋል እናጣለን፣በእግዚአብሄር ነገር ላይ ድፍረትም ይከተላል፣የድፍረት ሀጢያትና ጸጸት የሌለው አካሄድ ይወርሰናል፡፡

ሰው ግን ከአምላኩ ጋር ከተስማማ ይህችን አለም አስፈራርቶ በያዘው የሞት ጥላ መካከል ያለ ፍርሀት ሊመላለስ ይችላል፡፡ነገሩ ያለው የእግዚአብሄር እርዳታ ላይ ነው፡፡ዳዊት እንዳለው የእርሱ በትርና ምርኩዝ ስለሚያጸናኑ ክፉን መፍራት አይኖርም፡፡

ነገር ግን ጌታ ኢየሱስ በተወለደ ዘመን  አይሁድ  የአእምሮና የአመለካከት ጨለማ ወርሶአቸው ነበር፡፡ዘመኑን ማስተዋል ያለመቻልና ሊገለጥ የነበረውን የእግዘአብሄር ጽድቅ በጊዜው ሊቀበሉ ያለመቻል የነበሩበትን የጨለማ ሕይወት ያመለክታል፡፡ ቃሉን በትክክል ያለመረዳትና መሲሁ የሚመጣበትን ሁኔታም  ያለመረዳት እጅግ እንዲጎሰቆሉ አድርጎአል፡፡

ሐዋ.28:27 “በዓይናቸው እንዳያዩ በጆሮአቸው እንዳይሰሙ በልባቸውም እንዳያስተውሉ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል በላቸው…ሲል ይናገራል፡፡”