የህጉ ሰውን በእግዚአብሄር ፊት ለማቆም ያለመቻል ድካም ምንን ያሳየናል?
– እግዚአብሄር ከህጉ የተሻለ መንገድ እንደሚከፍት ያሳያል
– ህጉ ከሰው የሚጠብቀው ድርጊት፣ እንቅስቃሴና ውሳኔ እንደተጠበቀው እንዳልተሟላ ያሳያል
– የሰው ልጅ ችሎታ ጎዶሎ፣ ደካማና ጽድቅን የማይሰራ መሆኑን ያሳያል
– የሰው ልጅ በህግ እንደማይጸድቅ ያሳያል
– እግዚአብሄር በህግ ፋንታ ጸጋን እንደሰጠ ያሳያል
– ህግና ጸጋ ሁለቱም መንፈሳዊ ሲሆኑ ህግ ጠባቂ (ከሰው ልጆች ጽድቅ የሚፈልግ) ጸጋ ግን የሚያስችል፣ የሚያበቃና ፍጹም የሚያደርግ አሰራር (ነጻ መንፈሳዊ ስጦታ) መሆኑን ያሳያል
– ጸጋ ሰውን ከህግ በላይ በማድረግ ወደ እግዚአብሄር ፊት ማቅረብ የሚችል የእግዚአብሄር አሰራር እንደሆነ ያሳያል።
የህጉ ድካም መታወቅ የእግዚአብሄርን የተሻለና የተመረጠ መንገድ መገለጥ አመልካች ነበር፤ አስቀድሞ ህግ ለባለ አደራው የአብረሃም ዘር መሰጠቱ በእምነት ጽድቅን ካገኘው የእምነት አባት አብረሃም ጋር ጽድቅን እንድናገኝና ከእርሱ እምነት ጋር የተስተካከለ እምነት በክርስቶስ በኩል በመቀበል እንድንድን ነው፤ ይህ መንገድም የአብረሃምን እምነት ለማጽደቅ እግዚአብሄር የሰራው እንጂ የተለየ አሰራር ለሰው ልጆች ሊያስተዋውቅ አልነበረም። እግዚአብሄር ለአብረሃም ቃል የገባለትና ይህን እምነት አስቀድሞ ለእርሱ የሰበከለት በእርሱ እምነት በኩል አህዛብ ወደ እግዚአብሄር ዘላለማዊ በረከት እንዲመጡ እግዚአብሄር ስለወሰነ ነበር። ነገር ግን የእግዚአብሄር አሰራር ይገለጥ ዘንድ አስቀድሞ ለህዝቡ በሙሴ በኩል ህግ ይሰጠው ዘንድ የግድ ነበር። ይህ እንዲህ ሆኖ ሳለ ወገኖቹ እስራኤላውያን በጊዜ የተገለጠውን የእርሱን መንገድ ሊያስተውሉ እንደተሳናቸው እናያለን። በዚህ ሰበብ ህዝቡ ከእግዚአብሄር ፈቃድ ጋር ተጣልተው በአመጸኝነት ከመንግስቱ የጎደሉበት ሁኔታ እንደተፈጠረባቸው ታሪካቸው ያሳያል። የእግዚአብሄር ፈቃድ ግን በአዲስ ኪዳን የአብረሃምን እምነት እንድናገኝ አዲስ መንገድን ገለጠልን፦
ዕብ.7:11-12 ‘’እንግዲህ ህዝቡ በሌዊ ክህነት የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና በዚያ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ቢሆን፥ እንደ አሮን ሹመት የማይቈጠር፥ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ግን የሆነ ሌላ ካህን ሊነሳ ወደፊት ስለ ምን ያስፈልጋል? ክህነቱ ሲለወጥ፥ ሕጉ ደግሞ ሊለወጥ የግድ ነውና።’’
አዎ እግዚአብሄር ህዝቡን ባለአደራ አድርጎ በብዙ ሃላፊነት የሾማቸው በትእዛዙ በኩል ወደ ፍጹም የደህንነት መንገድ እንዲደርሱ እንጂ እነርሱ ሊሄዱ የመረጡትን መንገድ ሊያጸና አልነበረም። እግዚአብሄር ለሙሴ ህግን ሰጠ፤ ያን ሲያደርግ የአብረሃምን እምነት ረስቶ አልነበረም፤ ህጉ እምነቱን የሚሽር ሳይሆን ሞግዚት ሆኖ እስከ ጌታ መገለጥ ድረስ አስተዳዳሪ የሆነ ነበር።
(ገላ. 3:6-10) ‘’እንዲሁ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ። መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ። በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ። እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ። ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና።’’
ህጉ ብቃት ከሰው ይጠይቃል፤ የእግዚአብሄር ስራ ደግሞ በሰው ብቃት አይፈጸምም፤ ሰው ምን መልካም ቢሆን ከእግዚአብሄር ትእዛዝ አንጻር ፍጹም አይደለም፤ ይህን በቀድሞው ወላጆች አዳምና ሄዋን ላይ ታይቶአል፣ በእኛም ላይ በየትውልዱ መሃል ሰልጥኖአል፤ ስለዚህ እኛ በእግዚአብሄር ህግ ፊት ብቁ ሆነን መቆም ካስፈለገ ፍጹም የሚያደርግ የእግዚአብሄር እርዳታ እጅግ አስፈላጊ ነው፤ እግዚአብሄርም የሰውን ድካም አስቀድሞ ስላወቀ ሁዋላም በፈጠራቸው ላይ ስላየ እርዳታውን ሙሉ አድርጎ ሊገልጥ አስፈልጎታል፤ ይህም ፍጹም እገዛ በክርስቶስ ውስጥ በሙላት የተገለጠው የጸጋ ስጦታ የሚያከናውነው ነው፤ ኢየሱስን በማመን የሚገኝ ብቃት በእግዚአብሄር ፊት ያቆማል፤ ባላንጣውን ጠላት ዲያቢሎስን ደግሞ ያሸንፋል።
(ገላ. 3:11-12) ‘’ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎአልና ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው። ሕግም ከእምነት አይደለም ነገር ግን፦ የሚያደርገው ይኖርበታል ተብሎአል።’’
ህግ ከእግዚአብሄር በሙሴ በኩል ተሰጠ፤ ጸጋ ግን ከእግዚአብሄር በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠ። ሙሴ በሲና ተራራ ላይ ተገልጦ ከነበረው የሚነድድ የእግዚአብሄር ክብር ወጥቶ ወደ ህዝቡ ሲመጣ በእጁ ላይ ለህዝቡ መመሪያና መኖርያ የሚሆን ህግ ይዞ ነበር፤ ክርስቶስ ደግሞ ከእግዚአብሄር ውስጥ ወጥቶ (ተወልዶ) ስጋ በመሆን ወደ ገዛ ወገኖቹ ሲመጣ ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ነበር፤ ነገር ግን ጌታ የሰጠው ስጦታ ሙሴ እንደሰጠው ያለ ሳይሆን ከሙሴ የተሻለ ነገር ያለበት የጸጋ አሰራር ይዞ ነበር። ቃሉ ሲያረጋግጥም እንዲህ ይላል፦
‘’ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።’’ (ዮሃ. 1:14)
ህጉ በፈጠረው የብሉይ ኪዳን አገልግሎት ውስጥ ትልቁ ስፍራ የክህነቱ አገልግሎት ነበር፤ የክህነቱ አገልግሎት በህጉ በኩል በትውልዶች ላይ ጸንቶ ኖሮአል፤ ህጉ ግን ፍጽምና ስላልነበረው ክህነቱም ፍጹም ሆኖ ሊጸና አልቻለም፤ ስለዚህ እግዚአብሄር ህጉን በመለወጥ የክህነቱን አገልግሎት ይለውጥ ዘንድ በተሻለ የክህነት አገልግሎት ሊተካው ወስኖ ነበር። በሌላ በኩል ህጉ የሾመው ሙዋች ሰውን ነበረና ድካሙ በደካማ ሰዎች አገልግሎት ምክኒያት ታይቶአል፤ የእግዚአብሄር የተስፋ ቃል ግን ለዘላለም በመልከጸዴቅ መሃላ ዘላለማዊ ክህነትን ስለሚሰጥ አገልግሎቱ ፍጹም ሆኖአል።
ዕብ.7:28 ‘’ሕጉ ድካም ያላቸውን ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሐላው ቃል ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ይሾማል።’’ ስለሚል።
ነገር ግን እግዚአብሄር የምስራች ተናገረ፤ በዕብ.10:1 እንደተመለከተው፦ ‘’ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፥ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም ከቶ አይችልም።’’ ህጉን የተቀበሉ እኮ መጠበቅ ተስኖአቸው በብዙ ተቀጡበት፣ የህጉ ጉልበት እስራኤልን እስኪረግም ጠንካራ ነበርና፤ በአዲስ ኪዳን የተገለጠ ጸጋ ግን የተረገመውን የሰው ልጅ ከዚያ አውጥቶ በሰማያዊ ስፍራ በክርስቶስ እስኪያስቀምጥ ድረስ ከፍ አደረገው። ይህን ስጦታ ያላመኑና ያልተቀበሉ ጌታን አልተቀበሉም፤ አብረሃም አባታቸው ያመነውን እምነትም አላገኙትም፤ በዚህ ሰበብ ከጽድቅ ወደቁ፣ በገላ.5:4 ላይ ያለው ወቀሳ እንደሚለው፦ ‘’በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል።’’ ይላል።
ነገር ግን የጸጋው እርዳታ የበዛለት ይህ ሃዋርያ አጥብቆ ሊይዘው እንዲገባ እኛም ያን እንድናስተውል ይናገራል እንዲህ ሲል፦
‘’የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም፤ ጽድቅስ በሕግ በኩል ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።’’ (ገላ.2:21)
ጸጋ ከፍ ያለ የእግዚአብሄር አሰራር በመሆኑ መንፈሳዊ ከፍታ ላይ ያኖረውን አሰራር ቢጥል ሊያርፍበት የሚችልበት ስፍራ ታውቆታልና አልጥለውም ሲል ለራሱ ጥብቅ ውሳኔ ያኖራል፤ ጸጋ የሌለው በህግ ስር ነውና፣ ጸጋ የማያኖረው ህግ ያኖረዋልና፣ ጸጋ ያልተሰጠው ህግ እንደ ባርያ ይገዛዋልና፣ የጸጋው መንፈስ ግን ከዚህ ስብራት ያድናል፣ የእግዚአብሄር ቸርነት እንዴት ድንቅ ነው። ለዚህም ነው፦
‘’ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም’’ የሚለው። (ኤፌ2:8)
ጸጋ የእግዚአብሄር ስጦታ፣ እንዲያውም ከስጦታም የላቀ ስጦታ እንበለው፣ በእምነት የሚያድን፣ ሰውን በመንፈሳዊ ህይወት ውስጥ የሚያጸና በመንፈስ ቅዱስ ወደ ህይወታችን የሚተላለፍ ነው። ይህ ስጦታ አብልጠው ሊጠብቁት ሊንከባከቡትና ሊኖሩበት የተገባ የእግዚአብሄር ታላቅ ስጦታ ነው። በህይወታችን የሚሰራውም ቀላል ነገር አይደለም፤ ህይወታችን በሞት ፍርድ ውስጥ ከታሰረበት አሰራር በጸጋው ብቻ እንዲድን እናውቃለንና። ጌታ ኢየሱስን በማመናችን ግን ነጻነትና መፈታትን አግኝተናል፤ እግዚአብሄር ለእኛ ላመንነው የሚያስበው ሁሉ በጸጋው በኩል እንደሚከናወን ማስተዋልም ይህን የጸጋ መንፈስ እንድንጠማ ያደርጋል።
ሮሜ.7:6-7 ‘’አሁን ግን ለእርሱ ለታሰርንበት ስለ ሞትን፥ ከሕግ ተፈትተናል፥ ስለዚህም በአዲሱ በመንፈስ ኑሮ እንገዛለን እንጂ በአሮጌው በፊደል ኑሮ አይደለም። እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ ኃጢአት ነውን? አይደለም፤ ነገር ግን በሕግ ባይሆን ኃጢአትን ባላወቅሁም ነበር፤ ሕጉ፦ አትመኝ ባላለ ምኞትን ባላወቅሁም ነበርና።’’
ሃዋርያው የእኛነታችንን ይዘት በሁለት ሁኔታ ሲጠቀልለው ከላይ እመለከታለን፤ ይሀውም፦
የመጀመሪያው ከህግ ተፈትተን የነጻነት ህይወት የምንመራበት አዲሱ በመንፈስ የሆነ ኑሮ ሲሆን ይህ ህይወት መንፈሳዊ ሆኖ እግዚአብሄርን የምንገናኘው በመንፈስ፣ የምናመልከውም በመንፈስ የሆነ አሰራር ያለበት ነው፤ በሌላ በኩል አስቀድሞ የነበርንበት የህይወት መርህ በአሮጌው በፊደል ኑሮ ወይም በህግ የሆነ እንደነበር እንገነዘባለን።
ሮሜ.3:20 ‘’ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና።’’
ህግን ለመኮነን የሚፈጥኑ ወገኖች ይህን ጥቅስ ያሳያሉ፤ የቃሉ ይዘት ግን መዳን በተገለጠው የእግዚአብሄር መንገድ እንጂ ሞግዚት በሆነ ህግ እንዳይደለ ያሳያል፤ ህግ በጸጋው ወደሚዳንበት አሰራር ያደረሰ ጠባቂ እንጂ የደህንነት መሳርያ አይደለም፤ ያንን ሳትረዱ የህግን ስራ የደህንነት ስራ አድርጋችሁ እንዳትቆትሩ ሲል ማስገንዘቢያ ይሰጣል፤ ነገር ግን ሃጢያተኝነታችን የሚገለጠው በህጉ ምክኒያት እንደሆነ እናስተውል። ቃሉ እንደሚያስረዳው ለምሳሌ አትግደል የሚል የአምላክ ህግ ባይሰጠን ኖሮ መግደል ሃጢያት እንደሆነ ባላወቅን ነበር። ህጉ አትግደል ሲል አስጠንቅቆ ከገደልን እኛንም በሞት ይቀጣል፤ ጸጋው ግን ከዚህ ከፍ ያለ አሰራር በመሆኑ ሃጢያታችንን በጌታ ኢየሱስ ደም አጥቦ ስርየት እንድናገኝና የጽድቅ ህይወት እንድንኖር የሚያስችል ጉልበት በውስጣችን የሚፈጥር ነው።
ሐዋ.13:38-39 ‘’እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፥ በእርሱ በኩል የኃጢአት ስርየት እንዲነገርላችሁ፥ በሙሴም ሕግ ትጸድቁበት ዘንድ ከማይቻላችሁ ሁሉ ያመነ ሁሉ በእርሱ እንዲጸድቅ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን።’’
አንዳንድ የአይሁድ አማኞች ግን ከሕግ በታች ዳግመኛ ሊሆኑ ተመኝተው በዋጃቸው ጌታ ስጦታ ውስጥ የህግን ስራ ሊያስገቡ ፈልገው ነበር። ህግን በመታዘዛቸው መጽደቅንና መዳንን ፈልገዋል። የአይሁድ አባቶች ሊሸከሙት የማይችሉት የባርነት ቀንበር አግቡጦአቸው ሲኖሩ ሳለ በእንቢተኝነት ክርስቶስን ሳይዩ አልፈዋል፣ ክርስቶስን ያገኙ ልጆቻቸው ደግሞ አባቶቻቸውን ያጎበጠ የሕግ ቀንበር ናፋቂ ሆነው በርሱ ሥር የመሆን መሻት ውስጣቸው መፈጠሩን ቃሉ ይመሰክርባቸዋል።
በገላ.4:21 ውስጥ ያለው የቃል ይዘት የሚያስገነዝበን እውነት አለ፦ እናንተ ከሕግ በታች ልትሆኑ የምትፈልጉ ንገሩኝ …. ከህግን በታች ሆናችሁ፣ በሃጢያትና በመተላለፍ እፍረት አጎንብሳችሁ፣ በባርነት ተሸማቅቃችሁ፣ ወደ ፈጠራችሁ አምላክ በነጻነት ቀና ማለት ሳትችሉ ፈጽማችሁ እንደ ቅዱስ ፣ ጻድቅ እና በጎ ስለምን ለመምሰል ትደክማላቹሁ፤ ደግሞስ ነጻ እንሆናለን፣ በነጻነትም እንኖራለን፣ ከፍርድ ውጪ ነን (ፍርድ በእኛ ላይ አይሆንም) እንዴት ትላላችሁ? ፣ ከፍቅር መርህ ስታችሁ በጸጋው ላይ በመነሳት እሱን እንደታዘዛችሁ ለምን ትቆጥራላችሁ?
በእርግጥ በህግ ስር ሆነው ሰዎች ፈጽመው ለእግዚአብሔር መገዛትን እና ምስጋናን ማቅረብ አይችሉም፣ አልተፈቱማ፣ ነጻ አይደሉማ፣ ወደ ጸጋው ዙፋን አልደረሱማ! ግን ያን ሊያስተውሉ አልቻሉም። ሃዋርያው በአሳባቸው ተደንቆ ይጠይቃቸዋል፦ ሕጉን አትሰሙምን? እስኪ ንገሩኝ ይላቸዋል፤ ይህም ማለት የሙሴ ሕግ የሚናገረው ቋንቋም ሆነ የሚያሰማው ድምፅ ለሕግ ተላላፊዎች የሚሆን የማስደንገጫ ድምጽ ነው ማለት ነው፤ በዚህ ህጉ ወደ እነርሱ የክስ ደብዳቤ ይልካል፣ የከሰሳቸው ቃልም በእግዚአብሔር ፊት ጥፋተኞች እና ፍርደኞች ያደርጋቸዋል፣ አሳልፎ የተረገሙ እና የተፈረደባቸው ያደርጋቸዋል ማለት ነው፤ የህጉ አገልግሎት እነርሱን ወደ በጎ ነገር ሳይሆን ወደሞት የሚመራቸው፣ ወደ እግዚአብሄር ሳይሆን ወደጥፋት የሚልካቸው ነበር፤ የሞትም አገልግሎት ስለነበር እንደዚህ ባለ ሁኔታ አባቶቻቸውን አገለገላቸው። እነርሱም አሁን እንደዚህ ባለው ህግ ስር መሆን ይፈልጋሉ ማለት ነው?
‘’ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና። ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎአልና ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው።ሕግም ከእምነት አይደለም ነገር ግን፦ የሚያደርገው ይኖርበታል ተብሎአል።’’ (ገላ.3:10-12)
ትልቁ ግባችን የሰማይ መንግስት ከሆነ መዘናጋት አይቻልም፣ ማየት የምንናፍቀው በፈጠረን ጌታ ፊት መጽደቅ እስከሆነ ድረስም እንደተራ ነገር ልንቆጥረው አንችልም፣ እግዚአብሄር በቃሉ ሃጢያታችንን ይቅር እንዳለን ማረጋገጥ የምንፈልግ እስከሆነ ድረስ ደግሞ ከእርሱ መለየት አይታሰብም፣ ከምንም በላይ በፊቱ ሞገስ እንዳገኘን የሚያረጋግጥልን ከሆነና መንፈስ ቅዱስን በማውረድ ካጸደቀን ሁሉም እንደሞላልን እርግጠኛነትን ተቀበልን ማለት ነው። ከዚህ አስቀድሞ ግን እምነታችን በኢየሱስ ላይ ሊሆን እንደሚገባ በትህትና ማወቅ ይገባናል።
‘’እኛ በፍጥረት አይሁድ ነን ኃጢአተኞችም የሆኑ አሕዛብ አይደለንም፤ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል።’’ (ገላ.2:15-16)