1.1 ወንጌል የኢየሱስን መወለድ ያበሰረ የደስታ ዜና፡፡
የምስራች! አስደናቂና ታላቅ የሆነ ዜና፣ የሰው ልጆችን በደስታ የሚሞላ ብስራት በጌታ መወለድ ምክኒያት በምድር ላይ ወጥቶአል፡፡የጌታ ኢያሱስ የመወለድ አዋጅ በመላእክት በኩል የተነገረ ነበር፡፡ይህም የእግዚአብሄር ፈቃድና ፍቅር ለፍጥረት ሁሉ የመገለጡ ምስራች ሲሆን አለም ከመፈጠሩ በፊት እግዚአብሄር አቅዶ በእርሱ ዘንድ የጠበቀው፣ ቀኑና ዘመኑ ሲደርስ ከእግዚአብሄር የወጣ የደህንነት አዋጅ ነው፡፡ያም መላእክትን ሳይቀር በደስታ የሞላ ክስተት ነበር፡፡ክስተቱ ልዩ መገለጥ፡-የክርስቶስን መገለጥ ፣ እንዲሁም ልዩ ልደት ፡- የክርስቶስን ከድንግል መወለድ በምድር ላይ ያወጀ ነው፡፡የእግዚአብሄር የተስፋ ቃላት እና በብሉይ ኪዳን በነብያት አፍ የተነገረ ትንቢት ሁሉ ፍጻሜ ያገኝ ዘንድ ክርስቶስ ተወለደ፡፡እግዚአብሄር ለሰው ልጆች ሊሰጠው ያለው ደህንነት፣ሰላም፣ይቅርታ፣ጽድቅና የዘላለም ህይወት በዚያ ህጻን መወለድ ምክኒያት ተገለጠ፡፡ታላቅ ደስታ ከመንፈሱ አለም ለምድር በእርሱዋም ለሚኖሩ ሁሉ ሆነ፡፡ይህ ደስታ ስጋዊ አልነበረም፡፡ጊዜያዊ ወይም የይምሰል ያይደለ ነገር ግን እግዚአብሄር ለሰው ልጆች በጌታ መወለድ ምክኒያት የገለጠው ነበር፡፡የምስራቹ ለሰው ልጅ በሙሉ የደስታ ምንጭ ሲሆን ለጨለማው አለም ግን ፍርሀትና ፍርድ ሆነ፡፡የምስራቹን ይዘው ወደ ምድር የወረዱ መላእክት በሉቃ2:9-14 ውስጥ እንደሚከተለው ታይተዋል፡-
“እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ።መልአኩም እንዲህ አላቸው። እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ: ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ።” በዚህ አስደናቂ የመላእክት መገለጥ ትእይንት ውስጥ አንድ ለህዝብ ሁሉ የተፈቀደ መድሀኒት ሲበሰር እንመለከታለን፡፡መንፈሳዊ ጨለማ ላይ የፈነጠቀ ሰማያዊ ብርሀን በምድርም ላይ ተገለጠ፣ለሰዎችም የጌታ ክብር ሊያበራ በመላእክት ላይ ታየ፣ምድር ከጌታ ክብር የተነሳ አበራች፣ደስታ ሆነ፡፡የምስራችም ከመላእክት ወጣ፣የደስታው ምክኒያት ክርስቶስ የአለም መድሃኒት ተወልዶአልና፡፡
በኢሳ.9:2-3፣6 ውስጥ አስቀድሞ “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው።ሕዝብን አብዝተሃል፥ ደስታንም ጨምረህላቸዋል፤ በመከር ደስ እንደሚላቸው፥ ሰዎችም ምርኮን ሲካፈሉ ደስ እንደሚላቸው በፊትህ ደስ ይላቸዋል።…..ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” ተብሎ የታወጀው በዚያን ጊዜ ተፈጸመ፡፡
የተስፋ ልጆች በሀጢያት ተዘግተው ልቦናቸው በጨለመበት ዘመን የእግዚአብሄር ብርሀን ያለማስተዋል እስራትንና የሞት ጥላን ሰብሮ በመካከላቸው ተገለጠ፡፡
እስራኤል በጌታ ብርሀን በተጎበኘበት ዘመን ያለማወቅና ያለማመን በምድሩ ላይ በርትቶ ህዝቡን ለእስራት ዳርጎ ነበር፡፡የጌታ የወንጌል ምስራች ግን የህዝቡን ታሪክ ሁሉ ለወጠው፡፡በጨለማ እየሄዱ ባለማስተዋል ከሚመሩት የጭንቀት ህይወት ጌታ በብርሀኑ ጉብኝት ፈታቸው፡፡የእስራኤላውያን መንፈሳዊ ክልል በሞላ በጨለማው መንፈስ በመወረሱ የህዝቡ ህይወት ሞት ያጠላበት ነበር፡፡ጌታ ግን ያን ጨለማ ይሰብር ዘንድ ተወለደ፡፡የምስራች የጌታ መወለድ፣መከራ መቀበል፣መሞትና መነሳት ለሰው ሁሉ ደስታ ሆነ፡፡ህጻን ለምን ተወለደ? ይህ ህጻን የመወለዱ ምስጢር የጌታ ብርሀን በጨለማው አለም ላይ ሊያበራ የሰውን ልጅም ከዚያ ሊያወጣ እግዚአብሄር አማኑኤል መሆኑን (እግዚአብሄር በስጋ ውስጥ አድሮ በህዝቡ መሀል መገኘቱን) የሚገልጽ የምስራች ምክኒያትና ምልክት ስለነበር ነው፡፡በሞት ጥላ ምድር ፣የሀጢያት ቀንበር፣ሀዘንና እስራት በተስፋ ልጆች /በአብረሃም ዘሮች/ ላይ ወድቆ ስለነበር ሀያል አምላክ በስጋ መጥቶ ሊሰራ ያለውን ማዳን አወጀ፡፡እግዚአብሄር በመድሀኒቱ ጉብኝት ሀጢያትን ያለማስተዋልንና የመንፈስ እስራትን የሚያስወግድ እቅድ ይዞ ነበር ወደ ምድር የወረደው፡፡ስለዚህ፡-
“…. እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ፡- የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ።ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።” (ማቴ.1:20-21)
በመንፈሳዊ ስፍራ በአጋንንት ቀድሞ የተሰራ ሀጢያት በአዳምም ምክኒያት ወደ አለም ገብቶ ሁሉን የተቆጣጠረ የምስራች ከታወጀ ወዲህ እንደዚያው ሊቀጥል አልቻለም፡፡ምክኒያቱ ደግሞ የሀጢያትን ቀንበር የሚሰብር መድህን ተወልዶአልና፡፡የምስራች በሰው ዘር ላይ የሰፈነ አጋንንታዊ ቀንበር በሀጢያት ምክኒያት የተፈጠረም የዘላለም ሞት በኢየሱስ ክርስቶስ ይገፈፍ ዘንድ ከድንግል ተወለደ፡፡የእግዚአብሄር ቃል በመለኮት አሰራር ከእግዚአብሄር ውስጥ ወጥቶ በማርያም ማህጸን ውስጥ በማደር ጽንስ ሆኖ በሰው ልጅ አወላለድ ስርአት በማለፍ ልጅ ሆነ፡-ከህግ በታች ያለውን የሰው ልጅ በሙሉ ይዋጅ ዘንድ ከህግ በታች ተወለደ፡፡የእግዚአብሄር ልጅ አዳማዊ ስጋ፣አጥንት፣ነፍስና መንፈስ ሳይጣበቅበት ወይም ሳይዋሀደው ሰማያዊነቱን እንደያዘ የእግዚአብሄር የክብሩ መንጸባረቅና የባህሪው ምሳሌ ሆኖ ሀጢያታችንን በራሱ ደም አንጽቶ ለእግዚአብሄር መንግስት ብቁ እንሆን ዘንድ ተወለደ፡፡
ስለዚህ “እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች…ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና” ተባለ፡፡