የሀዋርያት ስራ መጽሀፍ – የሀይማኖቶች መከራከሪያ ሜዳ[misunderstanding the book]

በክርስትና እምነት ውስጥ የሚጠቃለሉ አብዛኛዎቹ እምነቶች የጋራ የሆኑ ወይም ብዙም የማያከራክሩ የመጽሀፍ ቅዱስ ክፍሎችን ይጋራሉ፡፡ስለዚህ ሁሎችም በሚባል ደረጃ በህግ በመዝሙራትና በነቢያት የተጻፉ መጻህፍትን (የብሉይ ኪዳን መጽሃፍትን)ያለብዙ ልዩነት ሊቀበሉ ይችላሉ፡፡ከዚህ በተጨማሪ የወንጌል መጽሀፍቶችንና መልእክቶችን ጭምር ያለክርክር ያስተምሩዋቸዋል፣ያምኑአቸዋል፡፡ነገር ግን ሁሎችም በሚያስብል ደረጃ በሀዋርያት ስራ መጽሀፍ ላይ የተለያየ አመለካከትና እምነት ያንጸባርቃሉ፡፡
መጽሀፍ ቅዱስ የመዘገበውን የቤተክርስቲያን አመሰራረት ያለማወላወል ከተቀበልን ዛሬ የምናያት ቤተክርስቲያን ይዘትና መልክዋ ከመጀመሪያዋ ጋር አንድ እንዲሆን መሞገታችን አይቀርም፡፡የዛሬዋ ቤተክርስቲያን በበአለ-ሀምሳ ቀን በተመሰረተችው ቤተክርስቲያን አመሰራረት ላይ አሁንም ጸንታ ወንጌሉን ለፍጥረት ማድረስ እንደሚገባት አጥብቀን ማመን ይገባል፡፡በዚህ አንጻር ቤተክርስቲያን በግልጽ ለሰው ልጆች መስበክ ያለባትን ሃዋርያቶች ቤተክርስቲያን በኢየሩሳሌም የተወለደች እለት ሰብከዋል፡፡ጴጥሮስ በኢየሩሳሌም ለመጀመሪያ ጊዜ የሰበከው የደህንነት ወንጌል ማጠቃለያ በሐዋ.2:38-39 ላይ እንዲህ ይላል፦ “ጴጥሮስም:- ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና አላቸው።“
ጴጥሮስ ለአዲስ ኪዳን ትውልድ ሁሉ የተናገረው የተስፋ ቃል በግልጽ የሚያሳስበው ስለንሰሀ፣ ስለኀጢያት ስርየትና ስለመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ነው፦ በኢየሱስ ስም ስለሚቀርብ ንሰሀ፣ በኢየሱስ ስም በጥምቀት ስለሚገኝ የሀጢያት ስርየትና በኢየሱስ ስም ስለሚሰጠው የመንፈስ ቅዱሳ ስጦታ፡፡ከኢየሩሳሌም የተነሳው ይህ ትምህርት በይሁዳ፣ በሰማርያ፣ በኤስያና በቀረው የአለም ክፍል ሊስፋፋ ችሎአል፡፡በዚህ ትምህርት የዳኑ ክርስቲያኖችም ከሃዋርያት ስራ መጽሃፍ በመቀጠል ከተቀመጡት የመልእክት መጽህፍት ውስጥ የተጠቀሱ ናቸው፡፡
በአሁኑ ዘመን የምንገኝ አማኞች እምነታችንን ማነጸጸር የሚገባን ከሃዋርያው ጴጥሮስ ትምህርት ጋር መሆን አለበት፡፡ሌላ ማንም አስተማማኝ ዋስትና ሊሆን አይችልም፡፡ ሰማይ የተቀበለውን ትምህርት እንድንቀበልና እንድንበት ዘንድ ጥንቃቄ ማድረግ ከዚህ ይጀምራልና።ከላይ የተቀመጠው ፊተኛው የቤተክርስቲያን አስተምህሮ በተለያየ ስፍራና ወቅት ሲገለጥ ቆይቶአል።ሃዋርያው ጴጥሮስ ወደ ቆርኖሌዮስ ቤት በተላከበት ወቅት ይህን አስተምህሮ አጉልቶ ተናግሮአል። እንዲህ ብሎም ነበር፦
“እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ በኃይልም ቀባው፥ እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤ እኛም በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ባደረገው ነገር ሁሉ ምስክሮች ነን፤ እርሱንም በእንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት። እርሱን እግዚአብሔር በሦስተኛው ቀን አስነሣው ይገለጥም ዘንድ ሰጠው፤ይኸውም ለሕዝብ ሁሉ አይደለም ነገር ግን በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተመረጡ ምስክሮች ለሆንን ለእኛ ነው እንጂ፤ ከሙታንም ከተነሣ በኋላ ከእርሱ ጋር የበላን የጠጣንም እኛ ነን።ለሕዝብም እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ በእግዚአብሔር የተወሰነ እርሱ እንደ ሆነ እንመሰክር ዘንድ አዘዘን። በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል። ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። ከጴጥሮስም ጋር የመጡት ሁሉ ከተገረዙት ወገን የሆኑ ምዕመናን በአሕዛብ ላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለ ፈሰሰ ተገረሙ፤ በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና።በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው? አለ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው።“       (ሐዋ.10:38-48)
ይህ የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍል የሚያሳየን ብዙ መገለጥ አለው፣ ከእግዚአብሄር የዘላለም እቅድ አንስቶ የእቅዱ ፍጻሜ በክርስቶስ የማግኘቱ ነገርና ለዚያም የምስራች ሃዋርያቶች ዋነኛ ሆነው መሾማቸውን በማሳየት።
በወንጌል የጉዞ ታሪክ ውስጥ ጎልተው የታዩት አሳዛኝ ክስተቶች ግን መነሻቸው የጴጥሮስ ትምህርት መሆኑ የሚያስቆጭ ነገር ነው። በዚህ ትምህርት መገለጥ ወይም ያለመገለጥ ምክኒያት አማኝ ፈተና ውስጥ ወድቆአል -ዛሬም ድረስ። እጅግ ብዙ ውጣ ውረዶች ክርክሮችና መለያየቶች በየቤተ-እምነቶች ዛሬም ድረስ አሉ።የመለያየቱ ስፋት በየቀኑ አዳዲስ አይነት “ቤተ-ክርስቲያን“ ይወልዳል።አስተምህሮዎች ከጴጥሮስ መገለጥ አፈንግጠው ሰፍተውና ተለጥጠው ልዩ ወንጌል ሆነዋል። በዚህ ዘመን ያለን አማኞችም የጌታን ትእዛዝና የሃዋርያትን ትምህርት እያነጻጸርን ትምህርቶቹ ተለያይተው ወይስ አንድ ሆነው ነው የቀጠሉት ብለን መጠየቃችን አልቀረም።ዛሬም አንዳንዶቹን ደግመን እንጠይቃለን፦
1.ኢየሱስ በማቴ.28:19 ያዘዘው ትእዛዝና በሀስ.2:38 የተሰበከው ትምህርት የተለያየ ከሆነ ለምን? የእኛን ፍርድ እንተውና ጌታ ኢየሱስን እንጠይቅ -ለምን ጴጥሮስ ላስተማረው ትምህርት ይሁንታ ሰጠህ? ቃሉ እንዲህ ስለሚል… ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ። ከጴጥሮስም ጋር የመጡት ሁሉ ከተገረዙት ወገን የሆኑ ምዕመናን በአሕዛብ ላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ስለ ፈሰሰ ተገረሙ፤ በልሳኖች ሲናገሩ እግዚአብሔርንም ሲያከብሩ ሰምተዋቸዋልና።በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው? አለ። በኢየሱስ ክርስቶስ ስምም ይጠመቁ ዘንድ አዘዛቸው።“
2.ጌታ የቆርኖሊዎስን ጸሎት ሲሰማ ቆይቶ መልስ ሲልክ ቅድሚያ የወጣው መልአክ ነበር፤ ቀጥሎ ሃዋርያው ጴጥሮስ።የሃዋርያው ጴጥሮስን ትምህርት ተከትሎ መንፈስ ቅዱስ በመውረድ ምስክር ሆነ።የዚህ ሃዋርያ ትምህርት በጌታ በራሱ ተቀባይነት ካገኘ፣ መልአክ ከተላከበትና መንፈስ ቅዱስ እውነትነቱን ካጸናው የጌታ ትእዛዝም ሆነ የሃዋርያት ትምህርት እንዴት ሊለያዩ ይችላሉ? እንዲያውም ሃዋርያው ወደ ሁዋላ ተመልሶ ትምህርቱን ከብሉይ ኪዳን ትንቢት ጋር ሲያስተሳስረው እንመልከት፦ “….በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ስርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል። ጴጥሮስ ይህን ነገር ገና ሲናገር ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ።“ በማለት።
3.በእኛ ዘመን ላሉ አስተምህሮዎች ጥያቄ ማቅረብ እንችላለን፦ሰው በስሙ እንዲያምን ትመሰክራላችሁ? በዚያ ስም ሰው የሃጢያት ስርየት እንዲቀበልስ ታደርጋላችሁ? የእግዚያብሄር መንፈስ ንሰሃ ገብቶ በጥምቀት የሃጢያት ስርየት ሲገኝ ብቻ እንደሚወርድስ ትመሰክራላችሁ? ለክርስትርና ሃይማኖት ከጌታ የተሻለ ምስክር አይገኝምና ይህ ነገር ቸል ቢባል ዋጋ አይገኝበትም።
4.በተለያዩ የሃይማኖት እምነቶች ዘንድ ሊመለስ የማይችል ጥያቄ እነሆ፦የማቴ.28:19 ትእዛዝ የማይለወጥና እውነት ነው።ነገር ግን በየትኛውም የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም የተጠመቀ ሰው ያለመገኘቱ ለምን ይሆን?
ለመጽህፍ ቅዱስ ትምህርት ያለጥርጥር የእግዚአብሄር ብርሃን እንደሚያስፈልግ በጣም ግልጽ ነው።ለዚህ ዘመን ደግሞ ከምን ጊዜም በላይ የእግዚአብሄር እርዳታ ያስፈልጋል።የመጭረሻው ዘመን የክህደት መንፈስ ግፊት ያለቅጥ እየጭመረ ስለሄደ ይሄ አስፈላጊ ነው።
ሃዋርያቶች ግን ለትውልድ ሁሉ ቃላቸው የጎላና የጸና ነው።እንዲህ ይላል፦
“ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።… “(ይሁ.1:3)
1ዮሐ.4:6 “እኛ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም። የእውነትን መንፈስና የስሕተትን መንፈስ በዚህ እናውቃለን።“ 
በይሁ.1:3 ባለው ጥቅስ ውስጥ የሚገኘው ዋና ነገር ከሀዋርያት ጋር የምንካፈለው መዳን ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፍጹም ሆኖ ላይለወጥ፣ ላይቀነስና ላይጨመር አንድ ጊዜ የተሰጠ ሀይማኖት መሆኑና፣ ይህን ሀይማኖት በመንፈሳዊ ጠላት ላለመነጠቅ ተጋድሎ እንደሚያስፈልግ የሚያመለክት ነው፡፡በበአለ ሃምሳ ቀን የተወለደችው ቤተክርስቲያን በሺ በሚቆጠሩ ክፍልፋዮች ተወክላ በዚህ ዘመን መታየትዋ ቀርቶ ጌታ በተከላት አንድ ትምህርት ላይ ዳግም ጸንታና ከፍ ብላ በአለም እንድትታይ የዛሬዎቹ ክፍልፋዮች ወደ እርሱዋ በትምህርትዋ በኩል አንድ እንዲሆኑ መጸለይ ግድ ነው፦ጌታ እንዲቀበለን ካስፈለገ ማለት ነው።
ማቴ.16:13-19“ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፡- ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ። እነርሱም፡- አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት።እርሱም፡- እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው።ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፡- አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ።ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፡- የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።“