ፍጹማን ሁኑ!

የእውነት እውቀት

ፍጹማን ሁኑ፦ በእግዚአብሄር የምትለወጡ ሁኑ፣ የራሳችሁን ችሎታ፣ አቅምና እውቀት ውስንነት አምናችሁ ተቀበሉ ሁሉን ለሚችል አምላክ ለርሱ ስፍራውን ልቀቁ፣ በቃሉ ላይ ያላችሁ እምነት ሙሉ ይሁን፣ የራሳችሁ ፈቃድ በእርሱ በእግዚአብሄር ፈቃድ ለመገዛት ፍጹም የተመቸና የተደላደለ ይሁን፣ በሙሉ ልባችሁ ለርሱ አሳብ ተሰጡ፣ ጉልበታችሁን ለርሱ፣ አሳባችሁን ለርሱ፣ ሃይላችሁን ለእርሱ፣ ሙሉ ፍቅራችሁ ለርሱ፣ ንጹህ አምልኮአችሁ ለርሱ (ከእርሱ በቀር ላለመስገድ፣ ላለመገዛት…) ይሁን፤ ይህን ስታደርጉ በእርሱ በኩል ሙሉ የሚያደርጋችሁን እርዳታ ይልካል (በቃሉ እያሳደገ፣ በመንፈሱ እየቀደሰ እያበረታ)፣ ጉድለታችሁን ይሞላል፣ አቅም ይሰጣችሁዋል፣ ለትእዛዙ ታዛዥ የምትሆኑበትን አቅም ይሰጣችሁዋል፣ ወደ ፍጹም ሙላት ያደርሳችሁዋል።
ፍጹማን ለመሆን የተጠራነው በርሱ ተሰርተን ለመጠናቀቅ ነው፣ ለማደግ ነው፣ በእኛ ውስጥ ያለው ስጋዊና አለማዊ ነገር ተራግፎ አልቆ መንፈሳዊ ነገር እንዲተካ፣ እግዚአብሄርን ወደ መምሰል እንድናድግም ነው፤ ለዚህ ሁሉ እድገትና ለውጣችን ከእግዚአብሄር የሚመጣልን ድጋፍ ጸጋ ነው። መለስ ብለን የብሉይ ኪዳኑን ፍጹምነት ስንመለከት የእስራኤል ህዝብ እንዲሆኑ የተጠየቀበትን መንገድ መመልከት እንችላለን፤ ይህም በአዲስ ኪዳን የተሰጠንን የእግዚአብሄር እርዳታ እንድናስተውል ይረዳል፦
እግዚአብሄር ህዝቡን እስራኤልን ፍጹም ሁኑ ሲል የሚጠይቀው እርሱ ለሰጣቸው ቃል በፈንታው እነርሱ ሙሉ ልባቸውን እንዲሰጡ፣ ባወጣው ትእዛዝ ላይ ማክበራቸውን እንዲያኖሩ፣ መታዘዛቸውንም በፍቅር እንዲያሳዩና የተነገራቸውን ሳይዘነጉና ሳይሰለቹ እንዲጠብቁ ብሎ ነው። ይህንም ያደርግ የነበረው ባተኮረበት ጉዳይ ላይ ፍጽምናቸውን እንዲጠብቁ በማዘዝ ነበር፦
በዘጸ.23:4 ውስጥ እስራኤላዊውን ‘’የጠላትህን በሬ ወይም አህያውን ጠፍቶ ብታገኘው በፍጹም መልስለት።’’ ሲል ያስጠነቅቀዋል። አንድ ሰው ለበቀል የሚፈልገውን ጠላቱን ማግኘት፣ ማሸነፍና ማጥፋት እያሰበ እጁ ላይ የጠላቱ ንብረት ድንገት ቢወድቅ አይቶ ዝም ሊል እንዴት ይችላል? በበቀል ሳይረካስ እንዴት በቤቱ ያርፋል፤ እግዚአብሄር ግን አታጠፋውም፣ አታጎድልበትም፣ ተንኮል አስበህና የእግዚአብሄርን ትእዛዝ ቸል ብለህ በተንኮል ንብረቱን በምስጢር እንዳታበላሽ፣ እንዳታጓድል ወይም እንዳታጠፋ ተጠንቀቅ፤ ይልቅ ባገኘሀው ሁኔታ መልስ ሲል ፍጽምናውን እንዲጠብቅ አዘዘ።
በዘሌ.22:21 ላይ ሲናገር ‘’ማናቸውም ሰው ስእለቱን ለመፈጸም ወይም በፈቃዱ ለማቅረብ የደኅንነትን መሥዋዕት፥ ወይም በሬን ወይም በግን፥ ለእግዚአብሔር ቢያቀርብ፥ ይሠምርለት ዘንድ ፍጹም ይሁን፥ ነውርም አይሁንበት።’’ አለ።
ከቃሉ በመነሳት በመስዋእት አካባቢ አንድ የፍፁምነት ቅድመ ሁኔታ እንዳለ እናያለን፣ ያንን ህዝቡ ያስተውል ዘንድ እግዚአብሄር ህጉን አሳወቃቸው፤ ስለዚህ ከህዝቡ መሃል አንድ ሰው ስእለቱን ይፈጽም ዘንድ በፈቃዱ ለማቅረብ ቢወድድ፣ የደኅንነትን መሥዋዕት አቅርቦ እንዲሰምርለትም መስዋእቱ ፍጹም እንከን አልባ ሊሆን ይገባል አለ። ስለመስዋእት የሚገባውን ፍፁምነት ጨምሮ ሲናገር፦
‘’የወዘወዛችሁትን ነዶ ከምታመጡበት ቀን በኋላ ከሰንበት ማግስት ፍጹም ሰባት ጊዜ ሰባት ቀን ቍጠሩ’’ (ዘሌ.23:15)
ፍጹም ሰባት ጊዜ ሰባት ቀን ቍጠሩ ብሎ ቀኑ ሳይጎድል ሙሉ ሊሆን እንዲገባው ያመለክታል፣ ፍጹምነቱ የቀኑ ቁጥር ሙሉ መሆን ላይ ስላለ። በእያንዳንዱ ቀን መለኮታዊ እቅዱን የሚፈጽም አምላክ ያዘዘው ትእዛዝ በቀኑ እንዲቀርብና የርሱም ስራ እንዲፈጽም እኛን በስፍራችን ሳንጎድል ማየት ይፈልጋል፤ የሚፈለገውን ሲጠይቅም ጊዜው ወደ ፊት ሳያልፍ ወደ ኋላም ሳይዘገይ እርሱ በቀጠረው ሰአት ብቻ ፍጹም ሙሉ በሆነ መንገድ እንዲከናወን ይፈልጋል።
በሌላ በኩል እግዚአብሄር ከፍ ያለ ነገር ሲጠይቅ እኛነታችንን ፍጹም አድርገን እንድናቀርብ በመጠየቅ ነው፤ በብሉይ ኪዳን ይህን ያደረገው እርሱን በተመለከተ ጉዳይ ላይ መሆኑን ቃሉ ያሳየናል፦
ዘዳ.6:4-5 ‘’እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው፤ አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ።’’
እስራኤል እንዲያስተውል በተላለፈው ጥሪ ውስጥ የተጠየቀው የሰው ፍጹም እኔነት ነው፣ ማንነት ነው፣ አስተሳሰብ ነው፣ እምነት ነው፣ ፍቅር ነው፣ ጉልበቱንም ጭምር ነው።
ይሄ ሁሉ ሲሆን ከእግዚአብሄር ዘንድ ይደረግ የነበረ እርዳታ በላካቸው ነብያት ላይ የተወሰነ ነበር፣ መንፈሱን በውስጣቸው አሳድሮም ጉልበት ሆኖአቸዋል። ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ እግዚአብሄር የሰራውን ታላቅ ነገር እናገኛለን፤ በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሄር እርዳታ፣ ምህረትና እገዛ ከክርስቶስ መወለድ ጋር የተገለጠ ነው፤ ይህም በርሱ ላመነ በጸጋው በኩል የምንቀበለው የእግዚአብሄር ቸርነት ነው፦
ዮሐ.1:14 ‘’ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።’’
በብሉይ ኪዳን የነበረ ታላቅ ተስፋ አንድያ የእግዚአብሄር ልጅ እንደሚወልድ ያመለክታል፣ ልጁም ጸጋን ለአይሁድ ብቻ ሳይሆን ላመንነው ሁሉ እንደሚሰጠን፣ ከአባቱም የመንፈስ ቅዱስ ተስፋ ተቀብሎም እንደሚያፈስልን፣ እንደተነገረው እንዲሁ እንደሚሆንልንም ጭምር የሚያረጋግጥ ነበር። ስለዚህ የጌታ ደቀመዛሙርት የሆንን ፍጹምና ጻድቅ መሆን እንችል ዘንድ፦
1. እግዚአብሄር በስጋ ለባሽ ላይ መንፈሱን እንደሚያፈስና የሚደግፈን ሃይል እንደምንቀበል እርግጠኛ ሆኖአል
2. በመንፈስ ቅዱስ መውረድ ጸጋ ስለምንቀበል በጸጋው መንፈስ ፍጹምነት ማግኘት እንደምንችል ታይቶአል። እግዚአብሄር ሰውን በጸጋው ስለሚያስችል ለቃሉ ታዛዥ በመሆን በፊቱ ቅዱስና ያለነውር መኖር ችለናል። የጸጋው ጉልበት በህይወታችን ብዙ ነገር አድርጎአል፦ ለምሳሌ ካለመቻል ወደ መቻል፣ ካለማወቅ ወደ ማወቅ፣ ካለመቆም ወደ መቆም፣ ካለማስተዋል ወደ ማስተዋል፣ ካለመውደድ ወደ መውደድ፣ ከስጋዊነት ወደ መንፈሳዊነት መሻገር ችለናል። ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ሆነ፣ ሃይልን በሚሰጠን በክርስቶስ አሸናፊ መሆን ተቻለ፣ ከጸጋ በታች ከህግ በላይ መኖርም እንዲሁ ተቻለ። አሁን በአዲስ ኪዳን እንደ ብሉይ ዘመን አንድ ወይም የተወሰነ ነገራችን ብቻ ሳይሆን መላ እኛነታችን ፍጹም ይሆን ዘንድ ተፈልጎአል፤ እንዴት እንችላለን? አንልም፣ በጸጋው መሰጠት፣ በእምነት ከክርስቶስ በመቀበል እርሱ አስችሎናል።
በብሉይ ኪዳን እግዚአብሄር ያደረገውን፣ ህጉ ከህዝቡ ይጠይቅ የነበረውን ፍጹምም ነገር ማወቅ በዘመናችን ለእኛ የተደረገልንን፣ አዲስ ኪዳንም ፍጹም አድርጎ ስላቆመው የጸጋ ጉልበት እንድናውቅና እንድናመሰግን የሚያደርግ ነው። ለምሳሌ ጸጋ በእምነት የምንቀበለውና በርሱ ችሎታ ፍጹምነትን መለማመድ የምንችለው ሲሆን ህጉ የሚጠይቀው ፍጹምነት የሰው ልጆችን የማድረግ አቅም የሚጠይቅና የሚፈትን ስለነበር ሰው በዚያ ያለመቻሉና ደካማነቱን ተጋልጦ በእግዚአብሄር ፊት ባዶነቱ ታይቶአል፤ እግዚአብሄር ግን ማስቻልን የሚሰጥ አምላክ በመሆኑ ይህን ድካማችንን አስወግዶልናል፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስራ የኛ ስራ ተፈጽሞአል፤ በዚህ ከእምነት በቀር ከእኛ የሚፈለግ ነገር አንዳች የለም።
ሮሜ.8:3-4 ‘’ከሥጋ የተነሣ ስለ ደከመ ለሕግ ያልተቻለውን፥ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በኃጢአትም ምክንያት ልኮ አድርጎአልና’’
መለስ ብለን ስንመለከት ግን በብሉይ ኪዳን እግዚአብሄር የህዝቡ ፈቃድ ፍጹም እንዲሆን የሚጠይቅበት ጊዜ እንደነበረው እናያለን፤ ያኔ በዚህ ነገር ላይ ጥብቅ ማስጠንቀቂያውን በትእዛዙ ውስጥ አኑሮ ለህዝቡ ይሰጥ ነበር፣ እንዲህ ሲል፦
‘’አንድ ሌዋዊ ሰው ከሚቀመጥባቸው በእስራኤል ሁሉ ዘንድ ካሉት ከአገር ደጆች ከአንዲቱ ቢወጣ፥ በፍጹም ፈቃድም እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ቢመጣ፥ በእግዚአብሔር ፊት እንደሚቆሙት እንደ ወንድሞቹ እንደ ሌዋውያን ሁሉ በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ያገለግላል።’’ (ዘዳ.18:6-7 )
በዚያ ዘመን የትኛውም በእግዚአብሄር የተመረጠ ሌዋዊ ክህነቱ ተጠብቆ እንዲኖር እግዚአብሄር ተቀመጥ ባለው ስፍራ መኖር ግዴታው ነበር፣ ይህን ነገር መጠበቅ ለርሱ ፍጹምነት ነው፤ እግዚአብሄር ተቀመጥ ካለው ስፍራ ተነቅሎ እንደሆነ በራሱ ፈቃድ ክህነቱን ጥሎአል፤ ወደ ክህነቱ ሊመለስ ቢፈቅድ ግን እንደገና ያለማወላወል ወደ ስፍራው ሊመለስ በዚያም እየኖረ አምላኩን ሊያገለግል ግዴታው ነበር።
ቃሉ በአምልኮህ ፍጹም ሁን፣ እርሱን ብቻ በማምለክ ፍጹምነትህን ጠብቅ የሚል ጥብቅ ትእዛዝ ሲያስተላልፍ፦
‘’አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በገባህ ጊዜ እነዚያ አሕዛብ የሚያደርጉትን ርኵሰት ታደርግ ዘንድ አትማር።ወንድ ልጁን ሴት ልጁን በእሳት የሚያሳልፍ፥ ምዋርተኛም፥ ሞራ ገላጭም፥አስማተኛም፥ መተተኛም፥ በድግምት የሚጠነቍልም፥ መናፍስትንም የሚጠራ፥ ጠንቋይም፥ ሙታን ሳቢም በአንተ ዘንድ አይገኝ።ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው፤ ስለዚህም ርኵሰት አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ ያሳድዳቸዋል።አንተ ግን በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ ፍጹም ሁን።የምትወርሳቸው እነዚህ አሕዛብ ሞራ ገላጮችንና ምዋርተኞችን ያዳምጣሉ፤ አንተ ግን እንዲሁ ታደርግ ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር ከልክሎሃል።’’ (ዘዳ.18:9-14)
ህዝቡን ታማኝ በመሆን እውነተኛ ሁን፣ ይህን በመጠበቅ ፍጹምነትህን አሳይ፣ በሚስጥር ተንኮለኛ አትሁን ይልም ነበር፦
ዘዳ.25:13-16 ‘’በከረጢትህ ውስጥ ታላቅና ታናሽ የሆነ ሁለት ዓይነት ሚዛን አይኑርልህ።በቤትህ ውስጥ ታላቅና ታናሽ የሆነ ሁለት ዓይነት መስፈሪያ አይኑርልህ።ይህን የሚያደርግ ሁሉ ክፋትንም የሚያደርግ ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነውና አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ ይረዝም ዘንድ እውነተኛና ፍጹም ሚዛን ይሁንልህ፤ እውነተኛና ፍጹም መስፈሪያም ይሁንልህ።’’
የእስራኤል በረከት፣ ምህረትና ህልውና የተቁዋጠረው በትእዛዙ ፍጹምነት ላይ መሆኑን በዋናነት የሚያመለክተው ቃል እንዲህ ይላል፦
ዘዳ.30:1-10 ‘’እንዲህም ይሆናል፤ እኔ በፊትህ ያኖርሁት ይህ ነገር ሁሉ፥ በረከቱና መርገሙ፥ በወረደብህ ጊዜ፥ አምላክህም እግዚአብሔር በሚበትንህ በአሕዛብ ሁሉ መካከል ሆነህ በልብህ ባሰብኸው ጊዜ፥ወደ አምላክህም ወደ እግዚአብሔር ተመልሰህ እኔ ዛሬ እንደማዝዝህ ሁሉ አንተና ልጆችህ በፍጹም ልብና በፍጹም ነፍስ ለቃሉ በታዘዝህ ጊዜ፥አምላክህ እግዚአብሔር ምርኮህን ይመልሳል ይራራልህማል፤ አምላክህም እግዚአብሔር አንተን ከበተነበት ከአሕዛብ ሁሉ መካከል መልሶ ይሰበስብሃል። ሰዎችህም እስከ ሰማይ ዳርቻ ድረስ ፈልሰው እንደ ሆነ አምላክህ እግዚአብሔር ከዚያ ይሰበስብሃል፥ ከዚያም ያመጣሃል።አባቶችህም ወደ ወረሱአት ምድር አምላክህ እግዚአብሔር ያጋባሃል፥ ትወርሳትማለህ፤ መልካምም ያደርግልሃል፥ ከአባቶችህም ይልቅ ያበዛሃል።በሕይወትም እንድትኖር፥ አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ እንድትወድድ አምላክህ እግዚአብሔር ልብህን የዘርህንም ልብ ይገርዛል።አምላክህም እግዚአብሔር ይህችን መርገም ሁሉ በጠላቶችህና በሚጠሉህ በሚያሳድዱህም ላይ ያመጣታል። አንተም ተመልሰህ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ትሰማለህ፥ ዛሬም እኔ የማዝዝህን ትእዛዙን ሁሉ ታደርጋለህ።የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ፥ በዚህም ሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዙንና ሥርዓቱን ብትጠብቅ፥ በፍጹምም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ብትመለስ፥ እግዚአብሔር በአባቶችህ ደስ እንዳለው በመልካሙ ነገር ሁሉ እንደ ገና በአንተ ደስ ይለዋልና አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ በሆድህም ፍሬ በከብትህም ፍሬ በእርሻህም ፍሬ እጅግ ይባርክሃል።’’
በዚህ ትእዛዝ ላይ የተጻፈው የእግዚአብሄር የቸርነት ቃል አስደሳች ቢሆንም የሰው ልጅ ጠብቆ ሊፈጽመው ያለመቻሉ አንጋጦ ዛፍ ላይ የተንጠለጠለን ጣፋጭ ፍሬ እንደመጠበቅ ሆኖበት ነበር፤ አምላኩን መስማትና መታዘዝ ያለመቻሉ፣ ትእዛዙን ሊፈጽም አቅም ማጣቱ ከዚህ አጉድሎታልና ፍጹምነት ርቆት እንደነበር እንመእከታለን።
ዘዳ.26:16-19 ‘’አምላክህ እግዚአብሔር ይህን ሥርዓትና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ዛሬ አዝዞሃል፤ አንተም በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ጠብቀው፥ አድርገውም። አንተ በመንገዱ ትሄድ ዘንድ፥ ሥርዓቱንና ትእዛዙን ፍርዱንም ትጠብቅ ዘንድ፥ ቃሉንም ትሰማ ዘንድ እግዚአብሔር እርሱ አምላክህ መሆኑን ዛሬ አስታውቀሃል። እግዚአብሔርም እንደ ሰጠህ ተስፋ ገንዘቡና ሕዝቡ መሆንህን፥ ትእዛዙንም ሁሉ ትጠብቅ ዘንድ፥ ከፈጠራቸውም አሕዛብ ሁሉ በምስጋና በስም በክብር ከፍ ያደርግህ ዘንድ፥ እርሱም እንደ ተናገረ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕዝብ ትሆን ዘንድ ዛሬ አስታውቆአል።’’
እነዚህ የፍጹምነት ግዴታዎች በብሉይ ኪዳን ውስጥ በእኛው በራሳችን እንድንፈጽማቸው ስለሚጠበቁ ብዙ እንቅፋት ነበረባቸው፣ ሰዎች አቅም ስላልነበረን፣ ችሎታ ስላነሰን፣ ደካማ ማንነት ስለያዝን፣ ከስጋ የተነሳ ህጉ በእኛ ውስጥ ፍጹምነትን ሊያደርግ አልቻለም፣ ይህን የተመለከተ እግዚአብሄር ግን ልጁን በሃጢያተኞቹ በእኛ ምሳሌ ልኮ ህጉን ፈጸመው፣ ለእኛ ለምናምነውም ፍጹምነትን ሰጠን፤ ይህንንም በጸጋው በኩል ተቀበልን።
በህጉ እንደተደነገገው እስራኤላውያን ፍጹማን እንዲሆኑ የተጠየቀው ነገር ሁሉ በነርሱ ደካማነት ሊሙዋላ አልቻለምና ባለመቻል ማነቆ ታሰረው ለብዙ ዘመናት ኖሩ፤ እግዚአብሄር የርሱን ፈቃድ ባስታወቀበት በዚያ ቃል ከነርሱ ሆኖ መገኘት የሚችል ድርጊት ሳይሆን በርሱ ላይ ተጣብቆ በመኖር የሚቻል የህይወት ይዘት መሆኑን እያመለከታቸው ነበር፤ ምክኒያቱም የዚህ መልስ ያለው ከጸጋው ዘንድ ብቻ ነውና።
1ጢሞ.1:8-11 ‘’ነገር ግን ሰው እንደሚገባ ቢሰራበት ሕግ መልካም እንደ ሆነ እናውቃለን፤ ይኸውም፥ ለበደለኞችና ለማይታዘዙ፥ ለዓመጸኞችና ለኃጢአተኞች፥ ቅድስና ለሌላቸውና ለርኵሳን፥ አባትና እናትን ለሚገድሉ፥ ለነፍሰ ገዳዮችና ለሴሰኞች፥ ከወንድ ጋርም ለሚተኙ፥ በሰዎችም ለሚነግዱ፥ ለውሸተኞችም በውሸትም ለሚምሉ፥ የብሩክ እግዚአብሔርንም ክብር እንደሚገልጥ ለእኔ አደራ እንደ ተሰጠኝ ወንጌል የሆነውን ደኅና ትምህርት ለሚቃወም ለሌላ ነገር ሁሉ ሕግ እንደ ተሰራ እንጂ ለጻድቅ እንዳልተሰራ ሲያውቅ ነው።’’
ሮሜ.3:19-25 ‘’አፍም ሁሉ ይዘጋ ዘንድ ዓለምም ሁሉ ከእግዚአብሔር ፍርድ በታች ይሆን ዘንድ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንዲናገር እናውቃለን፤ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና።አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ።እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው’’

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *