ዲያቢሎስን መቃወም

የእግዚአብሄር ፈቃድ

ክርስቲያኖች ጠላትን ስንቃወም በቃልም በስራም እንቃወመዋለን።የመቃወሚያ መሳሪያችን ደግሞ በመንፈስ የምንጠራው የኢየሱስ ስም ነው። ጠላትን ለመቃወም ስንነሳ ለምን እርሱን እንደምንቃወመውና ተቃውሞአችን ምን እንደሚሰራ/ውጤቱ ምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋል።በቅድሚያ ለመቃወም ምክኒያታችን ዲያቢሎስ የሚያቅዳቸውና የሚሰራቸው የክፋት ስራዎቹ ናቸው። በተጨማሪ በክፉ ባህሪው ምክኒያትም እንቃወመዋለን። የህይወታችን ጥፋት መሰረቱ እሱ ነው፣የምንኖርበትን ማህበረሰብና የኑሮ ሲስተምም የተቆጣጠረው እሱ ነው።
ለመቃወም መቃወሚያ መንገዱን መረዳት ይጠይቃል። ሰዎች ክፉውን ለመቃወም የምንችለው ወደ እግዚአብሄር ከቀረብን ብቻ ነው፣ከእግዚአብሄር ውጪ የእግዚአብሄር ነገር ከየት ተገኝቶ! ስለዚህ ወደ እግዚአብሄር የመቅረብ እድል ያገኘን በእርሱ ዘንድ ያለውን መንፈሳዊ ትጥቅ እንታጠቃለን፣የጠላትን እቅድና ግብ መመልከት እንችላለን፣ራሳችንን እናጠራለን እናውቃለንም፣ከምንም በላይ ደግሞ እግዚአብሄርንና ማዳኑን እንቀበላለን በዚያ ውስጥ በመንፈስ ሆነን እንዋጋለን።
መጋደላችን ከስጋና ከደም ጋር አይደለም።ጠላት ዲያቢሎስ ስጋና ደም የለውምና ስጋና ደም ያለው ሰውን/ወንድማችንን በጠላትነት ፈርጀን አንዋጋው።እንዲያውም ስጋና ደም የሆነ ሰው በጠላትነት ቢነሳ እንኳን እንዲነሳ ምክኒያቱ መንፈስ የሆነው ሰይጣን ነውና የውጊያ ትኩረታችን ከስጋና ደም ላይ ተነስቶ ወደ ክፉው መንፈስ አቅጣጫ ሊዞር ይገባዋል።
በየእለት ህይወት ውስጥ ከክፋት መንፈሳዊ ሰራዊት ጋር የማያቋርጥ ትግል አለ።ትግሉ አንድም የራስን መንፈሰዊ ይዞታ ላለማስነጠቅ ነው፣ሁለተኛም ጠላት የዘረፈውን ለማስመለስ ነው።ለዚያ መንፈሳዊ ትግል ለመብቃት ደግሞ መንፈሳዊ ጉልበት ይፈለጋል።መንፈሳዊ ጉልበት መንፈስ ከሆነ አምላክ የምንቀበለው ነው።በራሳችን መንፈሳዊ ጉልበት ማመንጨት አንችልም።ከቅድመ አባትና እናታችንን ተነስተን ስንመለከት (አዳምና ሄዋንን) በክፉው ሃይል የተሸነፍነው መንፈሳዊ ጉልበት በራሳችን ስላልነበረን ነው።
1.ጠላትን በቃልና በስራ መቃወም
ጠላትን በቃልና በስራ የምንቃወመው አመጣጡ በዚያ በኩል ስለሆነ ነው፦ዲያቢሎስ የተለያዩ ጉዳዮችን ይዞ በሃሳባችን በኩል ውስጣችን ዘው ስለሚልና በህይወት እንቅስቃሴያችን መሃል እየገባ የራሱን አሳብ ስለሚገልጥ ሁልጊዜ እነዚህን ነገሮች እየተጠባበቅንና እየፈተሽን እንዋጋለን።ሃሳብ ሃሳብ ስለሆነ ብቻ ማስተናገድ አንችልም፣ምን አይነት ሃሳብ እንደሆነ መፈተሽ አለብን(እንዲሁም ከየት እንደሆነም መለየት አስፈላጊ ነው)።አሳብ በአሳብነት ደረጃ ከተከሰተበት ወቅት አንስቶ ተግባር ሆኖ በውስጣችን እስኪለወጥ ባለው ጊዜ ውስጥ በእግዚአብሄር ቃል መሰረት ስንፈትሸው ምንጩን እንደርስበታለን።ሁሉንም ነገር አንጠራጠርም ወይም አንቀበልም።ነገር ግን ሁሉንም ነገር እናረጋግጣለን።ማረጋገጫችንም ህያው የእግዚአብሄር ቃል አስተማማኝና ብቸኛ መሳሪያ የሆነ ነው።በተለያየ መንገድ የሚመጣ ድምጽ በውስጣችን ብርቱ አሳብን ይወልዳል።በሔዋን ህይወት የሆነው እንደዚያ ነው።ቃሉ ስለዚያ በ2ቆሮ.11:3 ላይ ሲናገር፦
“ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ።“ ይላል።
ጠላት ዲያቢሎስ በመንፈሳዊ ስፍራ ላይ አንድ ተንኮል አቀናብሮ ወደ አለም ውስጥ ሊያመጣው ሲንቀሳቀስ መግቢያ አድርጎ የተጠቀመው አሳብን ነው።የርሱ ክፉ አሳብ የሄዋንን ቅን አሳብ እንዲያበላሽ የሚያባብል ድምጽ አሰምቶአታል።ያንን ድምጽ ለይታለች?ለይታስ ተቃውማለች? አዎ ሁለቱንም ልታደርግ ስላልቻለች በጠላቷ የተንኮል ወጥመድ ላይ ወድቃለች።ሰይጣን ሊያነጋግራት ሲመጣ እንዳትቃወም በምታውቀውና በተለማመደችው እንስሳ በኩል መጣ።ችግሩ ድምጹን ልትለየው ያለመቻልዋ ነበር።የሰማችው ድምጽም አባብሎአትና ተቆጣጥሮአት ወደ ተግባር መረቶአታል።ድምጽን ለመለየት ያለመቻል በአሳብም በግብርም መሸነፍ ያመጣል።ነገር ግን በእግዚአብሄር ቃል ስንሞላ በአሳባችን ብንንሸራተት እንኩዋን በስራችን ላይ ሳንወድቅ በቃሉ ምርኩዝነት እንተርፋለን።የማስተዋል ችሎታችን ደክሞ አሳባችንን ጠላት ቢወርሰውም የቃሉ ሃይል በህሊናችን ጉዋዳ በኩል ሉጋም ያደርግልናል፣ከተግባር ውድቀትም ይታደገናል።ልባችንን የሞላ የሚያስት አሳብ ወደ ተግባር ከተለወጠ ግን ውድቀት ውስጥ ይቀረቅረናል። ሆኖም የሚረዳን የእግዚአብሄር ሃይል ሲደርስልን ብቻ ከተቀረቀርንበት ከዚያ የተግባር ውድቀት ልንወጣ እንችላለን።
2. የተቃውሞ መሳሪያ
የተቃውሞ መሳሪያ ጠላትን ማስቆሚያና ማሳደጃ መሳርያ ነው።ሊያስተን የመጣ አሳብ በተቃውሞ መሳርያ ተነቅሎ ይርቃል።እግዚአብሄር የሰጠን መሳርያ የጠላትን ፍጥነት በቅድሚያ በማቆም ቀጥሎ ወደሁዋላ እንዲያፈገፍግና በፍጥነት ካለንበት እንዲጠፋ ያደርጋል።
ያዕ.4:7-9 “እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ።
ተጨነቁና እዘኑ አልቅሱም፤ ሳቃችሁ ወደ ኀዘን ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ።“
ጠላትን በአምላካችን ጉልበት ብቻ ልንቃወመው የምንችለው ቢሆንም ሃይሉ በህይወታችን እንዲገለጥ የህይወት ዝግጅት ማድረግ ይኖርብናል።ለጥንቃቅቄ እንዲረዳን የሄዝቄዋ ልጆችን ማስታወስ እንችላለን (ሀስ.19:14)።የህይወት ዝግጅታችን ከላይ ባለው የእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ተዘርዝሮ ይታያል።ቃሉ እንደሚያዘው ኃጢአተኞች እጆቻችንን እናንጻ፤ ሁለት አሳብም ያለን ልባችንን እናጥራ።ወደ ጌታ ቀርበን የስሙን ሃይል ከመቀበል አስቀድሞ ኃጢአትን ተናዝዞ በደሙ መታጠብ ያስፈልጋልና።ቃሉ አቀራረባችንን ሲያሳየን “ተጨነቁና እዘኑ አልቅሱም፤ ሳቃችሁ ወደ ኀዘን ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ።“ ይላል።በእግዚአብሄር ፊት ያለ ትህትናና የልብ ስብራት ሞገስ ያስገኛል።በንሰሃ ልብ ይጠራል፣በኃጢአት ፋንታ የእምነት መንፈስ ይሞላል።
የጌታ የኢየሱስ ስም በጠላት ላይ ስልጣን ያለውና ገዢ ስም ስለሆነ ጠላትን ስልጣን ባለው በዚህ ስም በእምነት እንቃወማለን፣ እንገስጻለንም።በዚህ ሃያል ስም የማይገዛ ፍጥረት የለም፣ይህን በብርቱ ማመን ያስፈልጋል።ሃዋርያት በደስታ ስለስሙ ችሎታ ሲናገሩ በሚከተለው ጥቅስ ውስጥ ይታያል፦
ሉቃ10:17-20 “ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው፦ ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል አሉት።እንዲህም አላቸው፦ ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ። እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም።“
ተቃውሞ ያዝ ለቀቅ ወይም ጀመር ተወት አይደረግም።ዲያብሎስ ብርቱ ጠላት ስለሆነ ጸንቶ ያለማቁዋረጥ መቃወም ይገባል።የዚህን ጠላት ባህሪይ ለመረዳት እንድንችል በእባብ፣ በዘንዶ፣ በጊንጥ፣ በእፉኚት፣ በሚያገሳ አንበሳ … ተመስሎአል። ስለዚህ ጠላትነቱ ሳያቆም እየተሹለከለከ፣ እያስደነገጠ፣ እያስፈራራ፣ አዘናግቶ እያደባና በመሳሰለው መንገድ እየተተናኮለ ሁሌም በአቅራቢያችን ስላለ ረስተን መዘናጋት መቼም አያስፈልግም።በተቃውሞ መጽናት ይገባናል፣ቃሉም እንደዚህ ይመክረናል፦
1ጴጥ.5:9 “በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።“
ስለዚህ ተቃውሞ ያለያዝ ለቀቅ አጠንክሮና በርትቶ፣ደግሞ በእዚአብሄር ፊት በቅድስና ሆኖ!
3. ጠላትን ለምን እንደምንቃወመውና ምንስ እንደሚሰራ ማወቅ
መንፈሳዊው ጠላት የስጋ ጠላት አይነት አይደለም ወይም እንደ ስጋ ለባሽ የሚደራደር ባለጋራ ፈጽሞ አይደለም።ጌታ ባህርዪውን እንድናውቅ ገልጦ ነግሮናል፡-
ዮሐ.10:10 ”ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤ እኔ ሕይወት እንዲሆንላቸው እንዲበዛላቸውም መጣሁ።”
ስለዚህ ሌባ የሆነው ሰይጣን እርሱ አንዴ ጠልቶናልና ሲመጣ ሊሰርቅ፣ ሊያርድና ሊያጠፋ የሚደርስ እቅድ ይዞ እንጂ ደርሶ ሊመለስ አይደለም።ይህን የዘላለም ጠላትና አጠፊያችንን ካስተዋልን በህይወት ዘመናችን ስንቴ መቃወም ይጠበቅብናል? መልሱ ምንጊዜምና የትም ስፍራ የሚል ነው።ሳናቁዋርጥ መቃወም ሊያውም በእውቀት የሆነ መቃወም ያስፈልጋል።እውቀት የጠላትን አድራሻ፣ ወጥመድ፣እቅድና ፍቃዱን ያሳውቀናል።ያለማወቅ በራሱ ጠንቀኛ ነው። መለኮታዊ እውቀት ግን በህያው እግዚአብሄር ላይ ያለን ማስተዋል ነው።እውቀት ብለን የምንጠራው ፊደል ያይደል ነገር ግን በመንፈስ የሆነ ማስተዋል ያለበት ትክክለኛ ምሪት የሚሰጠን ነው። ፊደል ማነብነብማ ሰይጣንን የሚያህለው የለም። ሰይጣን በስጋችን ሆነን ጉልበታም በመንፈስ ቅዱስ ስንሆን እጅግ ደካማ ነው።ሰይጣን በአእምሮ እውቀት በኩል የላቀ አዋቂ መንፈስ ቅዱስ በሚገልጠው በእግዚአብሄር ቃል በኩል ግን መሃይም ነው።እርኩስ መንፈስ በአህዛብ በኩል ብርቱ አድመኛ (አህዛብ ስለሚገዙለትና ስለሚያመልኩት፟)፣ በሃዋርያት ወንጌል በኩል የእርያዎች መንፈስ (እርያዎች ውስጥ ልግባ ፍቀድልኝ ብሎ የሚወተውት ርካሽ መንፈስ) ነው። ዛሬ እኛ በየትኛው ወገን ነን?አድራሻችን የጠላታችንን ሃይል ለማንበርከክ ወሳኝ ሚና አለው።ቃሉ በያእቆብ የመከረን ፦“ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ“ እያለ ነው።ሁለት ሃሳብ ይዘን ከሆነ በሁለቱ አሳብ መሃል ጣልቃ የሚገባ ይመጣል ማለት ነው።የሚገባውም ክፉው መንፈስ እንጂ የእግዚአብሄር መንፈስ አይደለም።ሁለት ሃሳብ ግራና ቀኝ እያገላበጠ ያምታታል፣ያዋዥቃል፣እምነት ይሰርቃል፣አንዴ አለምን አንዴ እግዚአብሄርን ያሰኛል።
4. ለመቃወም መቻል
ዲያቢሎስን ተቃወሙ የሚለው ማሳሰቢያ የስሙን ሃይል እንድናነሳና ሁልጊዜ በተግባር እንድንጠቀምበት ያነሳሳል።ለመቃወም ግን የምንቃወምበት ደረጃ ላይ መገኘት ያስፈልጋል።የጌታ የኢየሱስን ስም በእምነት ማንሳት ለውጊያ ዝግጁ ቢያደርገንም ብቁ መንፈሳዊ ደረጃ ላይ ሆኖ መገኘት ግን ወሳኝ ነው፡፡ብቁ መንፈሳዊ ደረጃ በእምነት መሞላት፣ በደሙ ነጽቶና የመዋጊያ እቃጦርን ተላብሶ ለመንፈሳዊ ውግያ ዝግጁ መሆን ነው፡፡የአስቄዋ ልጆች (ሐዋ.19:13-16) ያለ እምነትና ቅድስና አጋንንትን ሊጋጠሙ ቢወጡም ዘሎ አነቃቸው፡፡አስቄዋ የአየሁድ ካህናት አለቃ ሆኖ ሳለ እግዚአብሄርን እንደሃዋርያት አላመለከም፡፡እንዲያውም ልጆቹ አጋንንታዊ ስራ እየሰሩ ህዝብን በእምነት ያዘቀጡ ነበር፡፡አልፈውም የጌታን ስም ለክፉ መንፈስ አሰራራቸው ሽፋን ሊያደርጉ ሲሞክሩ ተዋርደዋል፡፡ያልተዘጋጀ ተዋጊ ሰራዊት በጠላቱ ፊት ይዋረዳል እንጂ ድል አያደርግም፡፡ሀዋርያውን ግን በድሉ ውስጥ ሆኖ መመልከት እንችላለን፡-
ሐዋ.19:10-16 ”በእስያም የኖሩት ሁሉ አይሁድም የግሪክ ሰዎችም የጌታን ቃል እስኪሰሙ ድረስ ሁለት ዓመት ያህል እንዲህ ሆነ።እግዚአብሔርም በጳውሎስ እጅ የሚያስገርም ተአምራት ያደርግ ነበር፤ ስለዚህም ከአካሉ ጨርቅ ወይም ልብስ ወደ ድውዮች ይወስዱ ነበር፥ደዌያቸውም ይለቃቸው ነበር ክፉዎች መናፍስትም ይወጡ ነበር።አጋንንትንም እያወጡ ይዞሩ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶች፡- ጳውሎስ በሚሰብከው በኢየሱስ እናምላችኋለን እያሉ ክፉዎች መናፍስት ባሉባቸው ላይ የጌታን የኢየሱስን ስም ይጠሩባቸው ዘንድ ሞከሩ።የካህናትም አለቃ ለሆነ አስቄዋ ለሚሉት ለአንድ አይሁዳዊ ይህን ያደረጉ ሰባት ልጆች ነበሩት።ክፉው መንፈስ ግን መልሶ፡- ኢየሱስንስ አውቀዋለሁ ጳውሎስንም አውቀዋለሁ፤ እናንተሳ እነማን ናችሁ? አላቸው።ክፉው መንፈስም ያለበት ሰው ዘለለባቸው ቆስለውም ከዚያ ቤት ዕራቁታቸውን እስኪሸሹ ድረስ በረታባቸው አሸነፋቸውም።”
እግዚአብሄርን የሚያምኑና የሚከተሉ ጠላትን ሊቃወሙና የታሰሩትን ከዚህ ጨቃኝ ጠላት ያስለቅቁ ዘንድ በሃዋርያት ትምህርትና እምነት ላይ ጸንተው ያሉ አሸናፊነትን መቀዳጀት ይችላሉ፡፡ያለበለዚያ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እንደ አስቄዋ ልጆች ያለ መንገድ መከተል ”ዕራቁታቸውን እስኪሸሹ ድረስ በረታባቸው አሸነፋቸውም።” እስከሚያስብል ድረስ ሊያዋርድ ይችላል፡፡

1 thought on “ዲያቢሎስን መቃወም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *