ነጻ የወጣ ህዝብ[3…]

የእግዚአብሄር ፈቃድ

የማሰር ስልጣኖች
በማይታዘዙ ዜጎች ላይ የሚያርፍ ቅጣት አለ፣ ይህ የማንኛውም ሃገረ- መንግስት ድንጋጌ ነው። የምድር መንግስታት ህግ አውጥተው ዜጎችን በዚያ ካላስተዳደሩ ምድር ሰላም አታገኝም፤ በዚህ ምክኒያት የትኞቹም ዜጎች ለሚገዙለት መንግስት ሊታዘዙ የግድ ሆኖአል። የእግዚአብሄር ወገኖችን ካየን እነርሱ በምድር ሳሉ የሰማይ መንግስት ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ የምድር መንግስትም ጭምር እንደሆኑ ማስተዋል ይገባቸዋል። ስለዚህ እነርሱንም የምድር መንግስት ህግ ይመለከታቸዋል ማለት ነው። በጠቅላላው ህጉ እያንዳንዱን የሚመለከት እንደመሆኑ ሁሉ ልብ ሊሉ ያስፈልጋል። እሺ ያሉ በመታዘዝ የዜግነት ግዴታን አክብረዋል። ስለታዘዙ በሙሉ ጸጥና ዝግ ብለው እንዲኖሩ ያስችላቸዋል፤ ንጉሳቸውን በመቀበልም እርስ በርስ ተዋድደው በሰላም እንዲኖሩ ተገብቶአቸዋል። በተቃራኒው በመንግስት ግዛት ውስጥ ያለ አመጸኛ ሲከሰት ይገሰጻል፣ ይማራል፣ ይነጥራል፣ ይጠራል፣ በጭከና ከታበየም ይኮነናል (እስከ ሞት በሚደርስ ፍርድ)። ከተግሳጽ በሁዋላ ግን ወደ ራሱ የተመለሰ በንሰሃ ወደ ግዛቱ ህግ ስር ገብቶ ዳግም በሰላም እንዲኖር ያስችለዋል።
እስራት አመጸኞች የሚታገዱበት፣ ከማናችውም እንቅስቃሴያቸው የሚገቱበትና ለሰሩት ጥፋት መቀጣጫ እንዲሆን ታስቦ ከጥቅማቸው አካባቢ የሚወገዱበት መንገድ ነው። በምድር ላይ ላለ ህይወት ከእግዚአብሄር ዘንድ የማሰርና የመፍታት ስልጣን የተቀበሉ መንግስትና ቤተክርስቲያን ናቸው። ሁለቱም ባለስልጣኖች የሚያመሳስላቸው የተቀበሉት ስልጣን ከእግዚአብሄር እንጂ ከሰው ያለመሆኑና ሁለቱም የእግዚአብሄርን ስርአት ተላላፊዎች የሚቀጡ መሆናቸው ነው፤ ልዩነታቸው መንግስት በምድራዊ አስተዳደር ላይ የሚሰለጥንና ስልጣኑ በስጋ ላይ ሲሆን ቤተክርስቲያን ግን አስተዳደርዋ በግዚአብሄር መንግስት በሚሆን ነገር ሆኖ ስልጣንዋ በመንፈሳዊ ጉዳይ ላይ ብቻ ይሆናል።
– የመንግስት ስልጣን
ማር.15:7-8 “በዓመፅም ነፍስ ከገደሉት ከዓመፀኞች ጋር የታሰረ በርባን የተባለ ነበረ። ሕዝቡም ወጥተው እንደ ልማዱ ያደርግላቸው ዘንድ እየጮኹ ይለምኑት ጀመር።”
መንግስት በሃገሩ የሚገኙትን ህዝብ ደህንነት ይጠብቅ ዘንድና መንግስቱን በሰላም ያጸና ዘንድ በዓመፅ ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች ተከታትሎና በቁጥጥር ስር አውሎ በህግ ይዳኛል። እግዚአብሄርን የሚፈሩ ሰዎችን በተመለከተ እነርሱ ለሚኖሩበት የግዛት አስተዳደር ታዛዥ ሆነው በሰላም እንዲኖሩ ያዝዛል፦
ሮሜ.13:1-4 “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ስለዚህ ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል፤ የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ።ገዥዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና። ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትወዳለህን? መልካሙን አድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሃል፤ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና። በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቍጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና።”
በዘመናችን እንዳሉ ሰዎች እንደሚያስቡት ሳይሆን እግዚአብሄር እንደወሰነልን ስንሄድ በገዢዎችና በስልጣናት ላይ መነሳት፣ መሸመቅ፣ ማመጽም እንደማንችል ቃሉ ያሳስባል። ጸጥና ዝግ ብለን መኖራችን ከእግዚአብሄርም ከምድር ባለስልጣንም ሞገስን እንቀበላለን።
ቃሉ ነፍስ/ሰው ሁሉ እግዚአብሄር ለሾማቸው የበላይ ባለ ሥልጣኖች ታዛዥ እንዲሆን ያዛል፣ ቃሉ ተገዛ ይላል። የምድር መንግስት ክፉ ገዢ ይኑረው ወይ ደግ፣ ጨካኝ ባለስልጣን ምድሩ ላይ ይሰልጥን ወይም ሩህሩህ ከየትም አልመጣም፣ በሰውም ወደ ዙፋን አልቀረበም፣ ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር፣ ሥልጣን መቼም ከርሱ ካልሆነ የለም፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው ሲልም በኛ ዘመን በምድራችን ላይ የሰለጠኑት መሪዎች በራሳቸው መንገድ ተቃንቶላቸው ዙፋን የወረሱ እንዳይመስለን ማንም ይሁን ምን ከእግዚአብሄር የተነሳ በምድሩና በህዝቡ ላይ ነግሶአልና እንድንቀበለው ታዝዞአል ።
ስለዚህ ባለ ሥልጣንን በጎ አደረገ ክፉ በራሱ ከአምላኩ ምላሹን ይቀበላል፣ ዜጋው ግን ቢቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማልና በእግዚአብሄር ይቀጣል፤ የሚቃወሙት ከሌላ ሳይሆን በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ። ምክኒያቱም የተሾሙ ገዥዎች አመጽ ለሚያደርጉ ለክፉ አድራጊዎች እንጂ መልካም ለሚያደርጉ አያስፈሩም፣ ዝግ ብለው ለሚኖሩና ለሚታዘዙም መቅሰፍት አይሆኑም። አንተ የሃገሬው ዜጋ የሆንክ ባለ ሥልጣንን እንዳትፈራ ትወዳለህን? በክፉ ስራ ከመሸማቀቅ ይልቅ መልካሙን በማድረግ ሞገስን መቀበልና በነጻነት መኖር ይሻልሃል፤ እግዚአብሄር ለምድሪቱ መልካም ነገር ያደርግ ዘንድ ሲያስብ በምድሪቱ ላይ በሾመው ባለስልጣን በኩል ስለሆነ የእግዚአብሔር አገልጋይነቱ የተመሰከረ ሆኖአል። ክፉ አድራጊንም እግዚአብሄር በእርሱ በኩል ስለሚቀጣ ይህ የምድር መንግስት ክፉ አድራጊውን የሚበቀል የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና።
– የቤተክርስቲያን ስልጣን
1ቆሮ.6:1-3 “ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን? ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ ብትፈርዱ ከሁሉ ይልቅ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ አትበቁምን? የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን?”
ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካል በመሆንዋ ስልጣን ራስ ከሆነው ጌታ ተቀብላለች፤ በዚህ ስልጣንዋ አመጸኞችን ማሰር ትችላለች፤ ስልጣንዋ በሰውና በተጣሉ መላእክትም ላይ እንደሆነ ቃሉ ይናገራል።
ማቴ.16:17-19 “ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ። እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም። የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።”
ማቴ.18:15-20 “ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤ እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ። እውነት እላችኋለሁ፥ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል። ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል። ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።”
ከስልጣን ውጪ አሳሪ
ዲያቢሎስ አመጸኛ ፍጥረት በመሆኑ ባልተሰጠው ስልጣን ሰዎችን በእስራት ይይዛል፤ ክፉ በመሆኑ በክፋት ያስራል፤ አመጸኛ በመሆኑ ሰዎችን ሊያጠቃ ያስራል፤ ከእግዚአብሄር ጋር ጠላት ስለሆነ የእግዚአብሄርን ወዳጆች ይተናኮላል፤ የርሱ አመጽ ተቆጥሮ አያልቅም፦
ሉቃ.13:11-17 እነሆም፥ ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ የድካም መንፈስ ያደረባት ሴት ነበረች፥ እርስዋም ጐባጣ ነበረች ቀንታም ልትቆም ከቶ አልተቻላትም። ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና፦ አንቺ ሴት፥ ከድካምሽ ተፈትተሻል አላት፥ እጁንም ጫነባት፤ ያን ጊዜም ቀጥ አለች፥ እግዚአብሔርንም አመሰገነች። የምኵራብ አለቃ ግን ኢየሱስ በሰንበት ስለ ፈወሰ ተቈጥቶ መለሰና ሕዝቡን፦ ሊሠራባቸው የሚገባ ስድስት ቀኖች አሉ፤ እንግዲህ በእነርሱ መጥታችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት አይደለም አለ።ጌታም መልሶ፦ እናንተ ግብዞች፥ ከእናንተ እያንዳንዱ በሰንበት በሬውን ወይስ አህያውን ከግርግሙ ፈትቶ ውኃ ሊያጠጣው ይወስደው የለምን? ይህችም የአብርሃም ልጅ ሆና ከአሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ሰይጣን ያሰራት በሰንበት ቀን ከዚህ እስራት ልትፈታ አይገባምን? አለው። ይህንም ሲናገር ሳለ የተቃወሙት ሁሉ አፈሩ፤ ከእርሱም በተደረገው ድንቅ ሁሉ ሕዝቡ ሁሉ ደስ አላቸው።
ሃሥ. 8:20-24 “ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፦ የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም። እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንሰሐ ግባ፥ ምናልባትም የልብህን አሳብ ይቅር ይልህ እንደ ሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን፤ በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና። ሲሞንም መልሶ፦ ካላችሁት አንዳች እንዳይደርስብኝ እናንተው ወደ ጌታ ለምኑልኝ አላቸው።”
የፍቅር እስራት
የፍቅር እስራት ከእስራቶች ሁሉ የተለየ ባህሪ አለው፣ በፍቅር መታሰር ወዶ ዘማችነትን ይፈጥራል። የታሰርን በማንም ሳንገድድ ከፍቅር ግፊት የተነሳ ብቻ (ውስጣችን አድርግ አድርግ ይለናልና) ያንን ታዝዘን ብዙ ነገር እናደርጋለን፦ የሰው ነገር ሳናይ፣ ከሰው አንዳች ጥቅም ሳንሻ በውስጥ ግፊት ብዙ መስዋእት እንከፍላለን። ፍቅር ሃይለኛ በመሆኑ እየወደድን ለፈተና ይሁን ለችግር፣ ለጭንቀት ይሁን ለመከራ ራሳችንን አሳልፈን እንሰጣለን። ቢያመንም ያስደስተናል፣ ብንጨነቅም ህሊናችን ባደረግነው ነገር ሙሉ እርካታ የተሞላ ነው። በፍቅር ጉዳት የነፍስ ጸጸት የለም።
ሃሥ.21:11-15 “ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጁንና እግሩን አስሮ፦ እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ፦ ይህ መታጠቂያ ያለውን ሰው አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደዚህ ያስሩታል በአሕዛብም እጅ አሳልፈው ይሰጡታል ይላል አለ።ይህንም በሰማን ጊዜ እኛም በዚያ የሚኖሩትም ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ለመንነው።ምጳውሎስ ግን መልሶ፦ እያለቀሳችሁ ልቤንም እየሰበራችሁ ምን ማድረጋችሁ ነው? እኔ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቼአለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም አለ።ምክርንም ሊቀበል እምቢ ባለ ጊዜ፦ የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን። ከዚህም ቀን በኋላ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን።”
ሃዋርያው ጳውሎስ በመልእክቶቹ ውስጥ በክርስቶስ ኢየሱስ ከእርሱ ጋር ስለታሰሩ ወንድሞች ያነሳ ነበር፤ ስማቸውን እየጠቀሰ ለአብያተክርስቲያናት ሰላምታ ይልክም ነበር። ለአገልግሎቱ ታማኝ፣ አብረውት ለሚያገለግሉም የፍቅር ሸክም ያለው ሲሆን ከምንም በላይ ለተለየለት ጌታ ፍቅሩ ክፍተኛ ነበር። ይህ ጌታ በህዝቡ መሃል ሲያድርም የሚሰጠውን የምህረትና የፍቅር መንፈስ በማስተዋል በዚያ በኩል ሁሎቹም እንዲተሳሰሩ ሲል መልእክቱን ይልካል፦
“የወንድማማች መዋደድ ይኑር። እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና። ከእነርሱ ጋር እንደ ታሰረ ሆናችሁ እስሮችን አስቡ፥ የተጨነቁትንም ራሳችሁ ደግሞ በሥጋ እንዳለ ሆናችሁ አስቡ።” (እብ.13:2-3)። በሌላ ስፍራ ሃዋርያው አንድ የፍቅር ምርኮኛን በሚከተለው ጥቅስ ውስጥ ያስተዋውቃል፤ ይህ ምርኮኛ አስቀድሞ በፍቅር እጦት ሊሆን ይችላል ብቻ በጥል ምክኒያት በወህኒ የታሰረ ነበር፤ የጌታ ኢየሱስ ፍቅር ሲያገኘው ግን የእርሱ ምርኮኛ ሆነ፦
ፊል.1:9-14 “ይልቁንም እንደዚህ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ሽማግሌው፥ አሁንም ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ እስር የሆንሁ፥ ስለ ፍቅር እለምናለሁ። አስቀድሞ ስላልጠቀመህ፥ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም ስለሚጠቅም በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ አናሲሞስ እለምንሃለሁ። አስቀድሞ ስላልጠቀመህ፥ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም ስለሚጠቅም በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ አናሲሞስ እለምንሃለሁ።እርሱን እልከዋለሁ፤አንተም ልቤ እንደሚሆን ተቀበለው። እኔስ በወንጌል እስራት ስለ አንተ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው እፈቅድ ነበር፥ነገር ግን በጎነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን፥ ሳልማከርህ ምንም እንኳ ላደርግ አልወደድሁም።”
በሌላ በኩል መጽሃፍ ቅዱስ ባልና ሚስት በፍቅር ህግ በአንድነት የታሰሩና እንደ አንድ አካል የሚቆጠሩ እንጂ እንደ ተለያየ ባለ ሁለት ፈቃድ ግለሰብ ሆነው በተለያየ አቅጣጫ በመገስገስ የታሰሩበትን ፍቅር በማስጨነቅ ሊጓተቱ እንደማይገባ ያስገነዝባል። ብዙ ባለትዳር ያን ሳይገነዘብ ገመዱን አክርሮ እየሳበ በጥሶአል። ቃሉ ግን በ1ቆሮ.7:39-40 ላይ እንዲህ ይላል፦ “ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሰረች ናት፤ ባልዋ ቢሞት ግን በጌታ ይሁን እንጂ የወደደችውን ልታገባ ነጻነት አላት። እንደ ምክሬ ግን እንዳለች ብትኖር ደስተኛ ናት፤ እኔም ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ያለ ይመስለኛል።”
ሴት ከባልዋ ጋር በትዳር ህግና በፍቅር ህግ የታሰረች ናት፤ ሁለቱ የታሰሩበትን ገመድ እግዚአብሄር ጊዜና ዘመን እያየ አያላላውም አይፈታውምም። እግዚአብሄር ህያው ነውና፤ የእግዚአብሄርም ቃል ዘመናዊ አይደለም፣ ዘላለማዊ እንጂ፤ በመሆኑም በየዘመኑ በሰው ልጅ አእምሮ ላይ ለሚመጡ የስንፍና አሳቦች አያጎነብስም (ቃሉ የገለጠው የትዳር ህጉም ጭምር)፣ ቃሉ የሰውን አሳብ የሚቀበል ሳይሆን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ብቻ የሚያስተናግድ ነውና።
በዚህ ትውልድ የሚታየው ትዳር የጠበቀ፣ ቃል ኪዳን ያለውና በፍቅር ገመድ የተሳሰረ ማንነት ያለው አይደለም። ተጋቢዎች ገና እንደተጋቡ ፍቺን በውስጣቸው በእኩል አማራጭነት ይዘው ነው በአንድ ጣራ ስር የሚገቡት። በዚህ ምክኒያት አንዱ የሌላውን ነገር በተቻለ መጠን ተረድቶ መደገፍ ላይ አያተኩርም፤ ይልቅ በምኑም በምኑም ተተናኩሶ ለመገፋተር ይፈጥናል እንጂ፤ እንዲሁ አንዱ ሌላውን ጥሎ በማለፍ በብዙ ድካም ያቆመውን ጣራ ያፈርሳል። የእግዚአብሄር ቃል ግን ለነዚህ ደካሞች ብሎ ከክብሩ ዝቅ አይልም።
1ቆሮ. 7:10-11 “ሚስትም ከባልዋ አትለያይ፥ ብትለያይ ግን ሳታገባ ትኑር ወይም ከባልዋ ትታረቅ፥ ባልም ሚስቱን አይተዋት ብዬ የተጋቡትን አዛቸዋለሁ፥ እኔ ግን አላዝም፥ ጌታ እንጂ።”
የእስራት ፍርድ
እግዚአብሄር በፍጥረታት ላይ ገዢ እንደመሆኑ በመንግስቱ ላይ ያመጹትን ሲፈርድባቸው ይታያል፤ በተለይ በመላእክት ላይ ያደረገው ፍርድ በሰዎች ላይ ካደረገው ይልቅ እጅግ ብርቱ ነበር፦ በዚህም ከመንግስቱ ነቅሎ ያባረራቸው ያሉትን ያህል በእስራት ውስጥ አኑሮ ለፍርድ የጠበቃቸውም እንዳሉ ቃሉ ያስረዳል።
ይሁዳ1:6 “መኖሪያቸውንም የተዉትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል።”
እንዳይሰሩና እንዳይነቃነቁ የተፈረደባቸው ክፉ መንፍስት አሉ፤ እነዚህ መናፍስት አለቆች የነበሩ መላእክት ሲሆኑ ከተመደበላቸው ስፍራም የተንሸራተቱ ስለዚህ ከእግዚአብሄር ተግሳጽ ስር የዋሉ ናቸው። እንዲሁም በ2ጴጥ. 2:4-5 ላይ ሲናገር፦
“እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ ከሰጣቸው፥ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ…” እያለ እግዚአብሄር ፍርዱን በተለያየ ጊዜ በአመጸኞች ላይ እንደገለጠ ቃሉ ያስተምረናል። ነገር ግን፦
“ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፥ በደለኞችንም ይልቁንም በርኵስ ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱትን ጌትነትንም የሚንቁትን እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል።” (2ጴጥ. 2:9)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *