የእግዚአብሄር ቃል በዕብ.11:3 ላይ ሲናገር፦
‘’ዓለሞች በእግዚአብሔር ቃል እንደ ተዘጋጁ፥ ስለዚህም የሚታየው ነገር ከሚታዩት እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን።’’ ይላል።
የማይታይ አምላክ እግዚአብሄር በማይታይ ቃሉ የሚታዩ ነገሮችን ፈጥሮአል፤ ይህ በእምነት የምንቀበለው እውነት ነው፤ ይህ የማይታይ አምላክ የማይታይ እቅድ፣ አሳብ፣ ፈቃድና ትእዛዝ ሁልጊዜ አለው፤ ስለዚህ ከዚያ ውስጥ የሚወጣ አካል የሚሆን እቅድ በእግዚአብሄር ዘንድ አለ ብሎ ማመን ከሰው ይጠበቃል ማለት ነው። ጥንት በእግዚአብሄር የተፈጠሩ ነገሮች በሙሉ ከርሱ ከወጡ አሁንም ሊወጡ ያላቸው ነገሮች አሉ ማለት ነው፤ እኛ ታዲያ ምን እናድርግ? እኛማ እንመን፣ እግዚአብሄር ያቀዳቸው ይሆናሉ፣ የተናገራቸው ይፈጸማሉ እንበል፤ እንጠብቅም። ደግሞስ ለኛ የተናገራቸው ቃሎች አሉ አይደለምን? ታዲያ እነርሱስ ቢሆኑ ይፈጸሙ የለምን? አዎ እነርሱን ተስፋ እናድርጋቸው፣ በእርግጥ ይሆኑልናል። በአዲስ ኪዳን መባቻ ላይ የሆነ የታላቅ እምነት ብስራት ትእይንት ሲገለጥ ይታያል፤ በዚህ ተይንት ውስጥ እምነትና ተስፋ በሰዎች ህይወት አፍርተው አካል ሆነው ሲገለጡ የምናይበት ነው፦
1. እረኞች ተስፋ ያለበት የምስራች ቃል ሰሙ፣ ሆኖ ያዩ ዘንድም በእምነት ተንቀሳቀሱ
ሉቃ2:8-14‘’በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ። ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፦ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ።’’
ይህ ታላቅ የምስራች በእረኞች መንፈስ ላይ ታላቅ ጉጉትና ተስፋ ሞላና የምስራቹን እንደሚያዩ በእርግጥ አመኑ፤ ስለዚህ መላእክት ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ ወዲያው ተማከሩና እርስ በርሳቸው፦ እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ ተባባሉ። እግዚአብሄር በመላእክት በኩል የተናገረውን እውነተኛ ቃል ሆኖ ያዩ ዘንድ ተስፋ አድረገው በእምነት ወደ ቤተልሔም ተንቀስቀሱ፤ ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። ለሌሎች እምነት ይሆን ዘንድ እግዚአብሄር አስቀድሞ ስለዚህ ሕፃን የተነገረላቸውን ነገር ገለጡ።
2. የተስፋ ቃል የተቀበለ ተስፋው ተፈጽሞ አየና አመሰገነ
ሉቃ2:22-25‘’ እንደ ሙሴም ሕግ የመንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ በጌታ ሕግ፦ የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል ተብሎ እንደ ተጻፈ በጌታ ፊት ሊያቆሙት፥ በጌታም ሕግ፦ ሁለት ዋሊያ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፥ መሥዋዕት ሊያቀርቡ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት።እነሆም፥ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል ሰው ነበረ፥ ይህም ሰው የእስራኤልን መጽናናት ይጠባበቅ ነበር፤ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፥ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ።በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር።’’
በዚህ ሰው ላይ የእግዚአብሄር መንፈስ ስለነበረበት ጻድቅና ትጉህ ነበረ፣ በእምነት አንዳችም አልደከመም፣ እምነቱ አንድ ታላቅ ነገር እስኪያሳየው ድረስ የበረታ ነበረ። የእግዚአብሄር መንፈስ ያስረዳውን በትእግስት ጠብቆና አይኖቹ እስኪፈዝዙ ድረስ ተስፋ ሳይቆርጥ ይዞ ይኖር የነበረ ስምዖን የሚባል ይህ ጻድቅ ሰው እግዚአብሄር የነገረው ቃል መፈጸሚያው ቀንና ሰአት በደረሰ ጊዜ እግዚአብሄር ቀስቅሶ ወደመቅደስ መራው፤ እግዚአብሄር የተናገረው መፈጸሚያው ሰአት ምንም ያህል የረዘመ ጊዜ ቢወስድብንም የሚሆነውን ከማየት ሰከንድ እንኳን ዝንፍ አትልብም። ይህ ሰውም እንዲያ ይሆንለት ዘንድ በመንፈስ ወደ መቅደስ ወጣ፤ ወላጆቹም እንደ ሕጉ ልማድ ያደርጉለት ዘንድ ሕፃኑን ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ፥እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ፦
‘’ጌታ ሆይ፥ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።’’
በእርግጥ ለታመኑት ይሆናል፣ ቃሉ ይፈጸማል፤ ነገር ግን ከእኛ ትእግስትና ጨክኖ መጠበቅ ይፈልግብን ይሆናል፤ ይህ ሰው ገና የተወለደውን ህጻን ከማየቱ እረፍቱን ስለምን ፈጥኖ ለመነ? ምን ያህል ጊዜ በጥበቃ እንደተቸገረ፣ ፍጻሜውን እንደናፈቀ፣ ተስፋው ሆኖ ያይ ዘንድ እንደጸለየና በሁኔታዎች መለዋወጥ ምክኒያት ከሚላተመው አለማመን ጋር እንደታገለ በዚህ ውስጥ እናያለንና ተስፋችንን እስክንጨብጥ በእምነት እንበርታ የሚል መልክት በዚያ ውስጥ እኛም ልናገኝ እንችላለን።
3. የተስፋ ቃል የተቀበለች ተስፋው ተፈጽሞ አየችና አመሰገነች
በአዲስ ኪዳን መባቻ ላይ የተገኙ ምስክሮች ብርቱ የተስፋ ቃል ይዘው ዘመናቸውን በሙሉ በጌታ ፊት በጾምና በጸሎት ይጠባበቁ እንደነበር ሓና የምትባል ሰው ታሪክ ያሳየናል፤ ጻድቃን ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደሆነ ስለቆጠሩ ምንም ቢያረጁ እንኳን ስለሞታቸው አልተጨነቁም፣ የተስፋው ቃል ጊዜን የሚያልፍ ነውና፣ እድሜንም የሚቀጥል ነውና፦
ሉቃ2:36-38 ‘’ከአሴር ወገንም የምትሆን የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች፤ እርስዋም ከድንግልናዋ ጀምራ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ኖረች፤ እርስዋም ሰማኒያ አራት ዓመት ያህል መበለት ሆና በጣም አርጅታ ነበር፤ በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም ነበር። በዚያችም ሰዓት ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር።’’
4. ጥርጥር ተስፋን ያጨልማል
በእርግጥ በእግዚአብሄር ቃል ላይ ተደግፎ መኖር ካስፈለገ የስጋ አይንና ጆሮን ለመንፈሳዊ ድምጽ ዝግ ማድረግ ያስፈልጋል፣ ያም በራስ ማንነት ላይ አጥብቆ በመወሰን ይቻላል፤ ወደ ቅዱሱ አምላክ ለመጠጋት በመንፈስ ወደ አምላክ መቅረብ እንጂ በስጋ የሆነ እንቅስቃሴ ምንም አይነት ውጤት አያመጣም፤ ቃሉን በመስማትና መንፈሱን በመቀበል የጀመርነው እምነት የስጋ ፈቃዳችንን ስበን ካጣበቅንበት ነገአችን ይጨልማል፤ በመንፈስ ጀምረን በስጋ መፈጸም ከእምነት የማፈንገጥ ችግር መሆኑ ልብ ይባል፦
(ዮሃ. 4:21-25) ‘’ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን። ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። ሴቲቱ፦ ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው።’’
ይህች ሳምራዊት እምነት ቢኖራትም እምነትዋ ከአባቶችዋ በተቀበለችው ልማዳዊ አባባል ተበራርዞ ጫፍ ይዛ እንድትሮጥና ስህተት ውስጥ እንድትገባ አድርጓት ነበር፤ ያም በልቧ ያለመረጋጋት ፈጥሮባታል፤ አእምሮዋም እዚህና እዚያ እንዲረግጥ ሆኖአል። እኛም በፈንታችን የትኛውም መንፈሳዊ ነገር ስጋዊ ጥረት ሊገባበት እንዳያስፈልግ እርግጠኞች መሆን አለብን።
መንፈስ የሆነ አምላክ ከመንፈስ የሚወጣ ቃል ይሰጣል፤ ቃሉ እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ የተነገረነው፤ መስማት የሚጠበቀው ከእኛ ነው፣ የተናገረውን ማመንም የእኛ ጉዳይ ነው፤ ከሩቅም ከቅርብም ሊሆን ያለውን እግዚአብሄር ቢያመለክት፣ አደርገዋለሁ ያለውና ተስፋ የገባልን ቅዱስ አምላክ እርሱ በመሆኑ ለጥርጥር እድል አንስጥ! የከበረ ሰው የምንለውን ስጋ ለባሽ እንኳ በተናገረው ላይ አለማመን ሃጢያት እስኪመስለን እንቀበለው የለም ወይ? ታላቅነቱን አይተን ቃሉን አያጥፍም ስንል እርሱን ሳይሆን የራሳችንን ውስጣዊ ጠያቂ ህሊና ዝም እናሰኛለንና።፤ ታዲያ እንዴት እውነተኛው አምላክ በተለያየ ጊዜ ታማኝነቱን ላሳየንስ ለርሱ እምነት ነፈግነው?
ልባችን በበረታ ጊዜ ይችላል እንደምንለውና ከርሱ ጋር በእምነት እንደምንጓዘው ሁሉ፣ ድካም ድካም ሲለን ይችል ይሆን፣ ያስበኝ ይሆን ወይስ ይተወኛል? እያልን በመወላወል የተናገረው እንዳይሆን እንቅፋት መፍጠር አይገባንም።
ያፈገፈገ ልቤ ስለ ጸሎት ጥያቄ ያነሳል፦ “ጸሎት ሞክሬአለሁ ግን እየሰራ ያለ አልመሰለኝም” ይላል፣ ወይም ‘’ነገሮች በተሳሳተ መንገድ እየሄዱ ይመስለኛል፣ እግዚአብሄር ትቶኝ ይሆንን?’’ ይላል። ያን የምንመለከተው በዘመናችን በአለም ላይ እየሰለጠነ ያለው ያለማመንና የክህደት መንፈስ በስልጣኔ በኩል እይተጫነን ነው። የተለመደ የስጋ አባባል እየመጣ ነው፣ “ማየት ማመን ነው”። ይህን እኛስ ተናግረን ይሆን? “ካየሁት ከዚያም አምናለሁ” ማለታችን መሆኑ ነው፤ መንፈሳዊን ነገር አይተን ሳይሆን ተስፋ አድርገን እናምነዋለን እንጂ።
ስጋን አጥብቀን ከሰማነው ግን ለምን በጸሎት እንዳምን ትጠይቀኛለህ? ሲል ይደውላል፤ ውስጣችንን ብንነግረውስ? እኔ በጸሎት አምናለሁ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ በማመንና በጸሎት ሕይወት ከርሱ ጋር መገናኘት እንደምችል አስተምሮአልና፤ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጅ መጸለይ ወይም ወደ አምላኩ መጮህ እንደሚገባው ተናግሯል፤ ይህም ማመን በማየት እንዳልሆነ ያሳያል። በሉቃ21:36 ላይ እንደተባለው፦ ‘’እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ።’’
ማየትን ለእምነታቸው መለኪያ የሚያደርጉ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የህይወት ደረጃ ውስጥ ያሉ በአለም ላይ ይኖራሉ። ታላላቅ ሳይንቲስቶች የሚታይና የሚዳሰስ አዲስ ነገር ፍለጋ እድሜያቸውን በሙሉ ይሰጣሉ፤ አንድ ነገር ሲሆን ያምኑ ዘንድ በምርምራቸው ውስጥ ይጠባበቃሉ፤ ሆኖ ሲያገኙትም ያምኑታል፤ እነርሱ ቁሳዊ እውነትን እስኪያገኙ ተከታታይ ሙከራዎችን በማድረግ ወደ አንፃራዊ እውቀት ይመጡ ዘንድ አይን አይኑን ያያሉ፤ በመጨረሻ የሚያገኙትን እውነት አድርገው ይወስዱታል፣ ይሰብኩታል፣ ያስወሩታል። ሆኖም የህያዋን ሆነ የግኡዛን ፍጥረታት ምንጭ እርሱ በመሆኑ እውቀቶቻችን መነሻቸው እርሱ ሊሆን የተገባ ነበር፤ ጌታ ኢየሱስ አንድ ታላቅ የእምነት ምስጢር ተናገረ እንዲህ ሲል፦
‘’እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም።’’ (ዮሐ.5:39-40)
ላመኑ የተገባ እውቀት እንደሚያሳየው የእምነት ምስጢር ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሚያርፍ ነው፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ባሕርይ ላይ ሁሉ ይመሰረታል። ይህን እምነት እርሱን በማወቅና ወደ እርሱ በመቅረብ ብቻ የምናገኘው ነው። እርሱ ስለራሱ ምን አለ? ምን አድርጉ አለ? ምንስ አደርጋለሁ አለ? የርሱ ነገር ለሰው ልጆች እንደሚሆን በዘመን የተፈጠረ ታሪክ አይደለም፤ ሰዎች የሚተርኩት የምናብ ቅንብር አይደለም፤ ነገር ግን የመጽሃፍ ቅዱስ ቃል የሚመሰክርለት የቃሉም ባለቤት ራሱ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው።
ለተጠራጠሩት አይሁድ እንዲህ ሲል መለሰ፦
ዮሐ.5:46 ‘’ሙሴንስ ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር፤ እርሱስ ለእኔ ጽፎአልና። መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?’’
ዳግም በመወለድ ያገኘነው የልጅነት ስልጣን ባዳነን በርሱ ላይ ጸንቶ ከመኖር ጋር አብሮ የሚሄድ ነው፤ እለት እለት በእምነት በርሱ ላይ ባለን መደገፍ እንዲህ እንኖራለን፤ ኑሮአችንም በእርሱ ፈቃድና የማዳን እቅድ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ካስተዋልን በርሱ ላይ ሊኖረን የሚገባን እምነትና ተስፋ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል።
አለም እንደ ውቅያኖስ ሰፊ ሆና ሳለ በላይዋ የምትቀዝፍ መርከብ የሆነች ቤተክርስቲያን ደግሞ እየተንሳፈፈች በውስጥዋ ታልፋለች፣ መርከቢቱ በውቅያኖሱ ላይ የምትጓዝ፣ አልፋም መጨረሻዋን የምታገኝና የምታርፍ ነች፤ ውቅያኖሱ ሰፊና ጥልቅ ነው፤ ማእበል አለበት፣ ስለዚህ መርከቢቱ በመልህቋ ሳትናወጥ በውሃው ላይ ለመንሳፈፍና ሚዛንዋን ለመጠበቅ ትጠቀምበታለች። ጌታ ኢየሱስ የመርከቢትዋ መሪ ስለሆነ ከወጀቡ ያሳልፋታል፣ እየመራ ወደ ፍጻሜዋ ያደርሳታል፤ ይህ መልካም የሆነ ዘላለማዊ እረፍት ያለበት ፍጻሜ የቤተክርስቲያን ተስፋ ነው። ጌታ ኢየሱስ መርከቧ ከአለት ጋር ተላትማ እንዳትፈርስ ይጠብቃታል፤ አውሎ ነፋስ እንዳይገለብጣትና በውስጧ ያሉት እንዳያልቁ የመርከብዋ መሪ ጌታ ይጠነቀቅላታል።
እብ.6:17-19‘’ስለዚህም እግዚአብሔር፥ የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደ ማይለወጥ አብልጦ ሊያሳያቸው ስለ ፈቀደ፥ እግዚአብሔር ሊዋሽ በማይቻል በሁለት በማይለወጥ ነገር፥ በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት ይሆንልን ዘንድ፥ በመሓላ በመካከል ገባ፤ ስለዚህም እግዚአብሔር፥ የተስፋውን ቃል ለሚወርሱ ፈቃዱ እንደ ማይለወጥ አብልጦ ሊያሳያቸው ስለ ፈቀደ፥ እግዚአብሔር ሊዋሽ በማይቻል በሁለት በማይለወጥ ነገር፥ በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት ይሆንልን ዘንድ፥ በመሓላ በመካከል ገባ፤ ይህም ተስፋ እንደ ነፍስ መልሕቅ አለን እርሱም እርግጥና ጽኑ የሆነ ወደ መጋረጃውም ውስጥ የገባ ነው’’
መቼም ቢሆን ይህን ጌታ ማመንና ተስፋ ማድረግ እንደሚገባ ልብ ማለት ወሳኝ ነው፤ ከሚታየውም ከማይታየውም የሚጠብቀን ጌታ ኢየሱስ፣ ከክፉ ሁሉ በክንፎቹ ጥላ የሚጋርደን እርሱ ነው፤ በርሱ ታምነው የሚኖሩ እስከ መጨረሻ አድኖ የሚጠብቃቸው እርሱ ብቻ ስለሆነ በተስፋው አያፍሩም።
(ኢሳ.26:6-9) ‘’አሁንም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአባቶቻችን ስለ ተሰጠው ስለ ተስፋ ቃል አለኝታ ልፋረድ ቆሜአለሁ። ወደዚህም ወደ ተስፋ ቃል አሥራ ሁለቱ ወገኖቻችን ሌሊትና ቀን በትጋት እያመለኩ ይደርሱ ዘንድ አለኝታ አላቸው፤ ስለዚህም አለኝታ፥ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፥ ከአይሁድ እከሰሳለሁ። እግዚአብሔር ሙታንን የሚያስነሣ እንደ ሆነ ስለ ምን በእናንተ ዘንድ የማይታመን ነገር ሆኖ ይቈጠራል? እኔም ራሴ የናዝሬቱን የኢየሱስን ስም የሚቃወም እጅግ ነገር አደርግ ዘንድ እንዲገባኝ ይመስለኝ ነበር።’’
የሚመስለን ነገር በሚበልጥ እውቀት እንዲሻር፣ የሚጸናው ደግሞ በእርሱ እውነት ፈጽሞ እንዲቆም ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይመጣል፣ ያኔ ከስፍራችን እንዳያጣን በተስፋችን ላይ ሳንናወጥ ቆመን እንጠብቅ።