ታላቁ ነቢይ ኤልያስ በዘመኑ የእግዚአብሄርን ህዝብ ካሳተው አጋንንታዊ አሰራር ጋር ሲዋጋ የኖረ፣ ህዝቡን ወደ አምላኩ ሊመልስ የታገለ እንዲሁም በፍጻሜው ወዳገለገለው አምላክ በክብር የተሰበሰበ የእምነት ሰው ነበር፡፡ነቢዩ በዘመኑ በእስራኤል ምድር ላይ በነገሰው የባእድ አማልክት ምክኒያት በህዝቡ ላይ የመጣውን የእግዚአብሄር ተግሳጽ ለንጉሱ አመልክቶታል፡-
”በገለዓድ ቴስቢ የነበረው ቴስብያዊው ኤልያስ አክዓብን፡- በፊቱ የቆምሁት የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! ከአፌ ቃል በቀር በእነዚህ ዓመታት ጠልና ዝናብ አይሆንም አለው። የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ሲል ለእርሱ መጣለት፡-ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሂድ፥ በዮርዳኖስም ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ውስጥ ተሸሸግ።” (1ነገ.17:1-3)
ኤልያስ የሰማውን መልእክት ካገኘ በሁዋላ ዳግም እግዚአብሄር ተገልጦ የሚሰራበትን ቀን ሲጠባበቅ እንደነበር መገመት አያዳግትም፡፡ያን እስኪያይ ስፍራ እየለዋወጠ ሲዞር ነበር፡፡ነቢዩ በእግዚአብሄር ፈቃድ ውስጥ የሚኖር ሰው ስለነበር ከአምላኩ እውቅና ውጪ የሚያከናውነው አንዳች የራሱ ፈቃድ አልነበረውም፡፡ነቢዩ ኤልያስ በእግዚአብሄር እስከተወሰደበት ጊዜ ድረስ ብዙ ዝቅታዎችንና መገፋቶችን አይቶአል፡፡ መጠለያም ሆነ ማደርያ እስከማይኖረው ድረስ ራሱን የተወ እውነተኛ አገልጋይም ነበረ፡፡ ነቢዩ ከነበረበት የጸና ስደት የተነሳ ወደ ተለያዩ ስፍራዎች ሲጉዋዝና በፈፋዎች ውስጥ ሲደበቅ ቢኖርም የእግዚአብሄር ጉብኝት ሲመጣለት በአምላኩ ፊት በሀይል የቆመባቸው ከፍታዎች ነበሩት፡፡ በህይወቱ ሳለ የእግዚአብሄርን ስራ ያየባቸው እነዚህ ከፍታዎች ኮሬብና ቀርሜሎስ ተራሮች ናቸው፡፡ቃሉ በመዝ.24:3-6 ሲናገር፡-
”ወደ እግዚአብሔር ተራራ ማን ይወጣል? በቅድስናውስ ስፍራ ማን ይቆማል? እጆቹ የነጹ፥ ልቡም ንጹሕ የሆነ፥ ነፍሱን ለከንቱ ያላነሣ፥ ለባልንጀራውም በሽንገላ ያልማለ። እርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከትን ከመድኃኒቱ አምላክም ምሕረትን ይቀበላል።” ይላል፡፡
የእግዚአብሄር ተራራዎች ክብሩ የሚገለጥባቸው ተራራዎች ናቸው፡፡እግዚአብሄር ህዝቡንና ባሪያዎቹን በቅርበት ሊያናግር ሲፈልግ ወደ ተራራው ይጠራቸው ነበር፡፡ሊባርክና ሊመራ ያቀርባችውም ነበር፡፡እግዚአብሄር ለእስራኤላውያን ሊገለጥ በፈለገ ጊዜ ሙሴን ወደ ተራራው ላይ ጠርቶታል፡፡ይህን ሁሉ ስራ እግዚአብሄር በስጋ እስኪገለጥ በነበረው ዘመን ሁሉ አድርጎአል፡፡ለምሳሌ እግዚአብሄር አብረሃም በመስዋእት ያከብረው ዘንድ ወደ ተራራው ጠርቶታል፡-
”የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ሂድ፤ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው አለ። አብርሃምም በማለዳ ተነሥቶ አህያውን ጫነ፥ ሁለቱንም ሎሌዎቹንና ልጁን ይስሕቅን ከእርሱ ጋር ወሰደ፥ እንጨትንም ለመሥዋዕት ሰነጠቀ፤ ተነሥቶም እግዚአብሔር ወዳለው ቦታ ሄደ። በሦስተኛውም ቀን አብርሃም ዓይኑን አነሣና ቦታውን ከሩቅ አየ።አብርሃምም ሎሌዎቹን አላቸው፡- አህያውን ይዛችሁ ከዚህ ቆዩ፤ እኔና ልጄ ወደዚያ ሄደን እንሰግዳለን፥ ወደ እናንተም እንመለሳለን።” (ዘፍ.22:2-5)፡፡
•ቀርሜሎስ – የእግዚአብሄር የበቀል ተራራ
በቀርሜሎስ እግዚአብሄር እንደሚገለጥ ኤልያስ ስላመነ በዚያ እንገናኝ በሚል መልእክት ህዝቡን ቀጠረ፡፡ህዝቡን በዚያ ሰብስቦ ልቡን ወደ አምላኩ በንሰሀ እንዲመልስ በጽኑ አሳሰበ፡፡የነቢዩ ጸሎትና እምነት የእግዚአብሄር እሳት እንድትገለጥ የህዝቡን ልብ እንድታነጻና ጠላትን እንድትበቀል ያደረገ ነበር፡፡
1ነገ.18:17-24 ”አክዓብም ኤልያስን ባየው ጊዜ፡- እስራኤልን የምትገለባብጥ አንተ ነህን? አለው።ኤልያስም፡- እስራኤልን የምትገለባብጡ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ በኣሊምን የተከተላችሁ፥ አንተና የአባትህ ቤት ናችሁ እንጂ እኔ አይደለሁም።አሁንም ልከህ እስራኤልን ሁሉ፥ በኤልዛቤልም ማዕድ የሚበሉትን አራት መቶ አምሳ የበኣልን ነቢያት፥ አራት መቶም የማምለኪያ ዐፀድን ነቢያት ወደ እኔ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰብስብ አለ።አክዓብም ወደ እስራኤል ልጆች ሁሉ ልኮ ነቢያቱን ሁሉ ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሰበሰበ።ኤልያስም ወደ ሕዝቡ ሁሉ ቀርቦ፡- እስከ መቼ ድረስ በሁለት አሳብ ታነክሳላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ፤ በኣል ግን አምላክ ቢሆን እርሱን ተከተሉ አለ። ሕዝቡም አንዲት ቃል አልመለሱለትም።ኤልያስም ሕዝቡን አለ፡- ከእግዚአብሔር ነቢያት እኔ ብቻ ቀርቻለሁ፤ የበኣል ነቢያት ግን አራት መቶ አምሳ ሰዎች ናቸው።ሁለት ወይፈኖች ይሰጡን፤ እነርሱም አንድ ወይፈን ይምረጡ፥ እየብልቱም ይቍረጡት፥ በእንጨትም ላይ ያኑሩት፥ በበታቹም እሳት አይጨምሩ፤ እኔም ሁለተኛውን ወይፈን አዘጋጃለሁ፥ በእንጨቱም ላይ አኖረዋለሁ፥ በበታቹም እሳት አልጨምርም።እናንተም የአምላካችሁን ስም ጥሩ፥ እኔም የእግዚአብሔርን ስም እጠራለሁ፤ ሰምቶም በእሳት የሚመልስ አምላክ፥ እርሱ አምላክ ይሁን። ሕዝቡም ሁሉ፡- ይህ ነገር መልካም ነው ብለው መለሱ።”
በቀርሜሎስ ተራራ ላይ በአብረሃም አምላክና በሲዶናውያን አማልክት መሀከል የተደረገው ውድድር የህዝቡን ልብ ከሁለት ወደ አንድ፣ ከጥርጥር አምልኮ በንጹህ ልብ እግዚአብሄርን ወደ መከተል የሚመልስ ታላቅ ስራ ሰርቶአል፡፡ሰምቶ በእሳት የሚመልስ አምላክ እውነተኛው አምላክ ነውና በቀርሜሎስ ሊመለክ ተገብቶታል፡፡
1ነገ.18:26-40 ”ወይፈኑንም ወስደው አዘጋጁ፥ ከጠዋትም እስከ ቀትር ድረስ፡- በኣል ሆይ፥ ስማን እያሉ የበኣልን ስም ጠሩ። ድምፅም አልነበረም፥ የሚመልስም አልነበረም፤ በሠሩትም መሠዊያ ዙሪያ እያነከሱ ያሸበሽቡ ነበር።…መሥዋዕተ ሠርክ በሚቀርብበት ጊዜ ነቢዩ ኤልያስ ቀርቦ፡- አቤቱ፥ የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ፥ አንተ በእስራኤል ላይ አምላክ እንደ ሆንህ፥ እኔም ባሪያህ እንደ ሆንሁ፥ ይህንም ሁሉ በቃልህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይገለጥ።አንተ፥ አቤቱ፥ አምላክ እንደ ሆንህ፥ ልባቸውንም ደግሞ እንደ መለስህ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ ስማኝ፥ አቤቱ፥ ስማኝ አለ።የእግዚአብሔርም እሳት ወደቀች፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕቱንም እንጨቱንም ድንጋዮቹንም አፈሩንም በላች፥ በጕድጓዱም ውስጥ ያለውን ውኃ ላሰች።ሕዝቡም ሁሉ ያንን ባዩ ጊዜ በግምባራቸው ተደፍተው፡- እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው አሉ።ኤልያስም፡- ከበኣል ነቢያት አንድ ሰው እንዳያመልጥ ያዙ አላቸው። ያዙአቸውም፤ ኤልያስም ወደ ቂሶን ወንዝ ወስዶ በዚያ አሳረዳቸው።”
ኤልያስ በእግዚአብሄር ክብር መገኛ ተራራ ጠላቶቹን ሊበቀል የቻለው በትክክለኛ ሰአት የእግዚአብሄርን ድምጽ ሰምቶ ወደ እርሱ በመቅረቡ ነበር፡፡ኤልያስ በቀርሜሎስ ድል አደረገ፤ ድሉ ከእግዚአብሄር ስም የተነሳ ሆነ፤ ከተገለጠው ክብር ሀይል የተነሳ የወረደው እሳት አምልኮና በቀልን አመጣ፡፡የሀሰት አማልክት በዚያ ተዋረዱ፤ በህያው አምላክ ክብር መገኛ አካባቢ አጋንንታዊ አሰራር ሊንቀሳቀስ ስለማይችል ጣኦትን ያመለኩ ነቢያቶች ሳያስተውሉ በዚያ ተጠምደው ወድቁ፡፡ቃሉ የማይሻር ቃልኪዳን አለውና፡-
ዘጸ.19:3-7 ”ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፤ እግዚአብሔርም በተራራው ጠርቶ አለው፡- ለያዕቆብ ቤት እንዲህ በል፥ ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ንገር።በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል። አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ። ለእስራኤል ልጆች የምትነግራቸው ቃል ይህ ነው።ሙሴም መጣ፥ የሕዝቡንም ሽማግሌዎች ጠርቶ እግዚአብሔር ያዘዘውን ይህን ቃል ሁሉ በፊታቸው ተናገረ።”
ሁልጊዜ በእግዚአብሄር የአምልኮ ተራራ አካባቢ የእግዚአብሄር ሀይል ተገልጦ ስለሚሰራ የእግዚአብሄር ህዝብ ቀንበር በዚያ ይሰበራል፣የጨለማ ስራ ይፈርሳል፣አንድ አምላክ ከፍ ይላል፡፡ኤልያስ ያንን አሰራር ቀድሞ ስላስተዋለ እግዚአብሄርና በአል እንዲወዳደሩ ጋበዘ፡፡እኛም ሁልጊዜ ስፍራን ለእግዚአብሄር መልቀቅ፣ በአምልኮ፣ በጽድቅና በቅድስና ወደ እርሱ መቅረብ ያለውን ጥቅም ከነብዩ መንገድ መማር ይገባናል፡፡ኤሊያስ በሀሰተኞች ነቢያት ላይ ድል ሊያደርግ የቻለው እግዚአብሄርን በማምለኩ፣ መሰዊያ ሰርቶ በዚያ መስዋእት በማቅረቡና መሰዋእቱ ሞገስ አግኝቶ እግዚአብሄር በእሳት በመመለሱ ነበር፡፡ነቢዩ በዚያ ሳያበቃ እምነቱ ወደ ጸሎት ሲመልሰው እናያለን፡፡በዚያ ብርቱ ጸሎት አድርጎ በንሰሃ ለተመለሰው ህዝብ በረከት እንዲወርድ (ለምድሪቱም ትኩሳት ማብረጃ የሚያረሰርስ ዝናብን እንዲሰጥ) አድርጎአል፡፡በእግዚአብሄር መንፈስ ሀይል በአካብ ፊት በፍጥነት እስኪሮጥ ድረስም በብርቱ ልምምድ አልፎአል፡፡
መዝ.43:3-5 ”ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ፥ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ። ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ፥ ጕልማስነቴንም ደስ ወዳሰኛት ወደ አምላኬ እገባለሁ፤ አቤቱ አምላኬ፥ በበገና አመሰግንሃለሁ። ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ።”
ነቢዩ በስግደቱ ሰአት በመሥዋዕተ ሠርክ ቆመና ለአምላኩ ምስጋና አቀረበ፣ስሙን ጠራ፡-አቤቱ፥ የአብርሃምና የይስሐቅ የእስራኤልም አምላክ ሆይ፥ ሲል ተጣራ፤ አንተ በእስራኤል ላይ አምላክ እንደ ሆንህ፥ እኔም ባሪያህ እንደ ሆንሁ፥ ይህንም ሁሉ በቃልህ እንዳደረግሁ ዛሬ ይገለጥ ሲልም በጠላቶች ፊት በእምነት ተናገረ።አንተ፥ አቤቱ፥ አምላክ እንደ ሆንህ፥ ልባቸውንም ደግሞ እንደ መለስህ ይህ ሕዝብ ያውቅ ዘንድ ስማኝ፥ አቤቱ፥ ስማኝ አለ።ይህንን ጸሎት እግዚአብሄር በመስማቱና መስዋእቱን በመቀበሉ የእግዚአብሔር እሳት ወደቀች፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕቱንም እንጨቱንም ድንጋዮቹንም አፈሩንም በላች፥ በጕድጓዱም ውስጥ ያለውን ውኃ ላሰች። በዚያች ቅጽበት በተገለጠው የእግዚአብሄር ተአምራት ሕዝቡ ሁሉ ፈሩና እግዚአብሄርን አከበሩ፣ በግምባራቸውም ተደፍተው፡-እግዚአብሔር እርሱ አምላክ ነው አሉ፡፡