ህግ ፈጽሞ ሊያነጻ ያለመቻሉ

እንደ አማኝና የጌታን ምህረት ተስፋ እንዳደረገ ክርስቲያን ትልቁ ፍላጎታችንና ልንደርስበት የምንፈልገው መሻታችን በእግዚአብሄር ፊት ነጽተንና ጻድቅ ሆነን መገኘት ነው፤ እግዚአብሄር በልጅነት ተቀብሎን፣ መንፈሱን ሰጥቶን የርሱን መንግስት ወራሽ እንሆን ዘንድ ነው፣ የሰውነታችን (አዲሱ ሰው የመሆናችን) መልካም መጨረሻ ይህ ነው። በዚህ አሰራር በኩል ልንደርስበት የምንሻውም ከኛነታችን ውጪ (ነጻ አውጥቶን) እግዚአብሄር አመጸኛ ሆነን እንዳይቆጥረን (ደግሞ እንዲቀበለን) እና በፊቱ ምህረትና ሞገስ እንድናገኝ መሻትም አለን፤ በትልቁ ገጽ ግን ማየትና መጠበቅ ያለብን እግዚአብሄር በፊቱ ብርሃን ተቀብሎን ጻድቅ ሆነንና ተቀባይነት አግኝተን ከርሱ ጋር ለዘላለም መኖር ነው። ከእግዚአብሄር ጋር የተጣላንበት ዘመን እንዲያብቃ፣ ከአሳቡ ጋር በመጋጨት በጠላትነት የቆምንበት ዘመንም እንዲዘጋ፣ ያለፈው አመጸኝነታችን ተሽሮ ታዛዥ የእግዚአብሄር ልጅነት ዘመን እንዲፈጠርልን ብንሻ ይህ የባለ አእምሮ ፍለጋና መሻት እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም። ምክኒያቱም የቃሉ ምስክር አለንና፦
‘’በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው።በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥’’ (ኤፌ.2:1-2-5)
በደል ነበረብን፣ ኃጢአት ነበረብን፣ ሙትም ነበርን፤ በዚህ የህይወት ይዘት እንዳለን ይህን ዓለም እያጎሳቆለ በሚገዛው የመንፈስ አለቃ ( በአየር ላይ ሥልጣን ባለው አለቃ) ፈቃድ ስር ሆነን ተመላልሰን ነበር። በሙት መንፈሳችን ምክንያት የእግዚአብሄር ማስተዋል ስለተነጠቅን የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን፣ እንዲህ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን። ነገር ግን ከዚህ ሁሉ የጥፋት አሰራርና ህይወት ያወጣን ዘንድ እግዚአብሔር ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ በክርስቶስ ሞት ለሃጢያት ሞተን በትንሳኤው አሰራር ሕያው አደረገን ይህንም የጸጋ ድነት ሰጠን። በአዲሱ ህይወት የምንመላለስ እኛ ወደፊት የሚጠብቀንን የሰማይ ተስፋ እንድንጨብጥ አምላካችን የሰጠንን ጸጋ አጥብቀን በመያዝ መጓዝ ብቻ ነው ከእንግዲህ የሚያስፈልገው።
ነገር ግን ከምህረቱ አሰራር ተንሸራትተን በምንጓዝ ጊዜ ስህተት ላይ እንወድቃለን፤ ያ ብቻ ሳይሆን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ላለን የራሳችንን ውስኔና አመለካከት ከቃሉ ጋር በትህትና ብናመሳክር ሁልግዜ የምንደርስበት ድምዳሜ የሚያሳየን የራስ አቅማችንን መመካት እንደማንችል፣ ብልሃታችንን ታምነን በምናደርገው ጥረት የተመኘነው መንፈሳዊ ነገር ፈጽሞ እንደማይሆንልንና እንደማይሳካልን እናረጋግጣለን። በአጭሩ እኛን የሚፈርድ አምላክ ቅዱስ ሲሆን እኛ የሰው ልጆች ግን እንደዚያ አይደለንም፣ ከፍጥረታችን ሃጢያተኛነታችን የተገለጠ በቃሉም የተረጋገጠ እውነት ነውና። በኢሳ.64:6 ላይ ያለው ቃል ወደ ኋዋላ ለምንመለከት ግልጽ ማስጠንቀቂያ ይሰጣል፦
‘’ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው፤ ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል።’’ ይላል። ይህ ቃል ከእግዚአብሄር ፊት የወደቀውን ሰው (የአሮጌውን ሰው) ውስጣዊ መልክ የሚያሳይ ነው። በእግዚአብሄር ፊት የአዳም መንፈሳዊ ደረጃ አንድ ነው፤ እንደመርገም ጨርቅ አጸያፊ የሆነ ወይም ነውር ያለበት ነው። በዚህ ደረጃ ላይ ያለ የሰው ልጆች ጽድቅም የእግዚአብሄር ቁጣ ምክኒያት ነው።
‘’ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።’’ (1ዮሃ.1:8-10)
የእግዚአብሄር ቃል እንድናውቅ የሚያሳስበን ምንድነው? በምድር ላይ ያለን ሰዎች ጽድቃችን ቆሽሾ በፊቱ የታየው ከተወሰኑ ግለሰቦች ህይወት ብቻ ሃጢያት እየመነጨ ስለሆነ ሳይሆን ነገር ግን የሰው ዘር በሙሉ በሃጢያት ስለተበከለና የህይወት ይዘቱ ከክብሩ እጅግ ስላሽቆለቆለ ነው፤ በዚህ የህይወት ይዘቱም ተስፋ ያጣና ከፍርድ ማምለጥ የማይችል መሆኑን በኢሳ.64:6 ላይ ያለው እውነት ያሳየናል፤ ይህ ሁኔታ ሁላችንን ስለሚመለከት ላስተዋለ ፍርዱ እጅግ አሳዛኝና ለእርግማን አሳልፎ የሰጠ መሆኑ ይገለጥለታል።
ህግ የተሰጣቸው አይሁድ የሚያስቡት ምንድን ነው? የህጉን ጥላነት ያልተቀበሉ የህጉ መሰጠት ድካማችንን ይበልጥ እንዳጎላው እንጂ ሊያግዘን እንዳልቻለ መቀበል አልፈለጉም። በእርግጥ ህግ መንፈሳዊ ነው፣ ያም በመሆኑ በእግዚአብሄር ፊት መቆም የሚችል ሰው ማን መሆኑን በግልጥ ያሳየናል።
ሮሜ.3:23 ‘’ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል’’ የሚለው ቃልም በእግዚአብሄር እርዳታ ብቻ ያጣነውን ክብር ማስመለስ እንደምንችል ያመለክታል። ከዚህ መለስ ምንም እንሁን፣ ምንም እናድርግ፣ ምንም ያህል የጎላ ክብር ይታይ፣ ብቻ በማንም አይሞላም ነው፣ የተነጠቅነውም ቢሆን አንዳች ሰው አይመለስልንም፤ ስለዚህ በዚህ የህይወት ይዘት እስካለ የሰው ልጅ ለዘላለም ጥፋት ተጋልጦአል፣ ተፈርዶበታል።
አለም አንድ ነገር ትወቅ ከተባለ፦ ከእግዚአብሄር በጎነት ውጪ መኖር የማይችል የሰው ልጅ ዳግም ወደ እግዚአብሄር የሚያደርሰው አንድ መንገድ ሊገለጥ አስፈላጊ ነው፤ ይህ እውቀት በወንጌል ግልጽ ሊሆንለት ይገባል። አንዴ በሰው ልጅ ሃጢያት ምክኒያት በቅዱስ አምላክ ላይ የተደረገ አመጽ ፍርድ ተገብቶታልና፤ ፍርዱም የሰው ልጅን ለዘላለም ከእግዚአብሄር የሚለይበት ሁኔታ ላይ ነው የጣለው። ለአይሁድ የተሰጠው የሙሴ ህግም ሰውን ከእግዚአብሄር ጋር የሚያስታርቅ አልሆነም፤ የሰውን ሁኔታ፣ የጽድቅ ደረጃውንና ማንነቱን የሚያጋልጥ እንጂ ወደ እግዚአብሄር የሚያቀርበውና በፊቱ መመላለስ የሚችልበትን አቅም የሚሰጠው አይደለም። እስራኤል በህግ ላይ ለምን ተመኩ፣ ትምክታቸውስ ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን አልሆነም? ይህ የልብ ጥንካሬያቸው በፍርድ ውስጥ እንዲኖሩ አደረገ እንጂ እንዳላራቃቸው ይልቁንም እንደጣላቸው የሚያሳይ ነው። ላመኑት አይሁድ ግን ተስፋቸው ክርስቶስ ሆአል፦
‘’ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ፥’’ (1ጴጥ.:18)
ሰዎች በስራቸው የማይጸድቁ ከሆነ የሚያጸድቀውን የእግዚአብሄርን መንገድ ለምን አንከተልም? የሰው ልጆች ከእግዚአብሄር ጸጋ ይልቅ መታመኛ/መደገፊያ እንዲኖረን በመመኘታችን ሌላ ውድቀት ሆኖአል። በሰው ልጅ ዙርያ ካለው የውድቀት ታሪክ አንጻርና ከእስራኤል የተሳሳተ መንገድ አንጻር አንድም ሰው አቅም አግኝቶ ህግን የፈጸመ የለም፤ ስለዚህ በህግ መጽደቅ አይቻልም ተብሎ ስለተደመደመ ፍለጋችን ከንቱ እንዳይሆን ልባም መሆን ያሻል።
በሕጉ ውስጥ መኖር አለመቻል የህጉ ቃል የፈጠረው እንቅፋት ወይም እግዚአብሄር እንወድቅ ዘንድ ያስቀመጠብን ማሰናከያ ሳይሆን ሰው በራሱ ሰበብ በላዩ ላይ የሳበው ጥፋት እንዲሁም በዚያ ምክኒያት በተከሰተ የጽድቅ እጦት ሰበብ የሆነ ብቻ ነው፣ የሰው መንፈሳዊ የህይወት ይዘት ምስቅልቅል ውስጥ ስለመኖሩ በአለም ላይ እየሆነ ያለውም ሁኔታ ምስክር ነው፤ በእግዚአብሄር ያለመታመን የፈጠረው ጥልቅ ችግር ከሰው ሞልቶ ተርፎ ምድር መሸከም እስኪያቅታት እንዲሰፍንባት አድርጎአል፤ አዳም ምድርን አስረግሞ ሲያበቃ እርስዋም በተራዋ የሰውን ልጅ የተባለን ሳትለይ ሃሳር ውስጥ ጥላለች፦
ዘፍ.3:17-19 ‘’አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ። ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ ፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህና።’’
ስለዚህ ሰው ያለ ክርስቶስ (ያለ እግዚአብሄር ጽድቅ) በእግዚአብሄር ፊት እንዳይቆም እንደተደረገና የገባበት የአመጽ ፍርድ ከአምላክ ምህረት ውጪ እንዳደረገው በቅን ልብ በመቀበል ሊረዳው ወደሚችል የእግዚአብሄር አሰራር ውስጥ ሊገባ ተገብቶታል። አዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ይላል፦
‘’ይህን ብቻ ከእናንተ እንድማር እወዳለሁ፤ በሕግ ሥራ ወይም ከእምነት ጋር በሆነ መስማት መንፈስን ተቀበላችሁን? እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጽማላችሁን? በውኑ ከንቱ እንደ ሆነስ እንደዚህ ያለ መከራ በከንቱ ተቀበላችሁን? እንግዲህ መንፈስን የሚሰጣችሁ በእናንተም ዘንድ ተአምራት የሚያደርግ፥ በሕግ ሥራ ነውን ወይስ ከእምነት ጋር በሆነ መስማት ነው? እንዲሁ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ።’’ (ገላ.3:2-7)
በብሉይ ኪዳን ዘመን የእግዚአብሄርን ተስፋ ቃል ያመነ አብረሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ እንደተቆጠረለት ሁሉ በአዲስ ኪዳንም በኢየሱስ የቤዛነት ስራ ያመነ እንደሚድን የታመነ ነው፤ እምነት መንፈሳዊ ነውና፣ በማመን ዳንን፣ በማመን ጽድቅን ተቀበልን፣ በማመን መንፈሱ ወረደልን፤ በየትኛውስ የህግ ቃል እንዲህ ሆነ? ህጉ ብዙዎችን በፍርድ ገድሎአቸዋል፣ ኢየሱስን በማመን ግን ሁሉ ድነዋል።
ክብር ያጣና የወደቀ ባህሪ፣ የተጠላና የረከሰ ጽድቅ፣ የሞተ ኃጢአተኛ መንፈስ፣ ይህን የተሸከመ የተኮነነው አዳም እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ጽድቅ ይኖረዋል? መጽሃፍ ቅዱስ ሰዎች ራሳችንን በዚህ ደረጃ እንድንመለከት ይፈልጋል፤ ይህ ያለ ምክኒያት የሆነ አይደለም፤ ሁሉ ነገራችንን ረስተን በራሳችን ሙሉነት የሚሰማን፣ ጥፋት እንዳለ ልብ የማንልና ዝቅ ብለን ንሰሃ ልንገባ የማንሻ እጅግ ብዙ ስለሆንን ነው።እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ የመጨረሻው ዘመን ዝንባሌ ለትውልዱ የሚያስፈራ እውቀት እያወረሰው መሆኑ ነው፤ ሰው ራሱን አምላክ እስኪያደርግ ስላስታበየው፣ እውነተኛው አምላክ ሊደርስለትና ከጥፋት ያድነው ዘንድ እያስፈለገ ባለበት በዚህ አስጨናቂ ወቅት በከንቱ ፍልስፍናና በዲያቢሎስ ኩራት ተነፍቶ መዳንን ቸል በማለቱ ከፍተኛ ጥፋት ሆኖአል።
‘’ከፈሪሳውያን ወገን ግን ያመኑት አንዳንዶቹ ተነሥተው። ትገርዙአቸው ዘንድና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ታዙአቸው ዘንድ ይገባል አሉ።ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ስለዚህ ነገር ለመማከር ተሰበሰቡ።ከብዙ ክርክርም በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው ወንድሞች ሆይ፥ አሕዛብ ከአፌ የወንጌልን ቃል ሰምተው ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር በመጀመሪያው ዘመን ከእናንተ እኔን እንደ መረጠኝ እናንተ ታውቃላችሁ።ልብንም የሚያውቅ አምላክ ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሰከረላቸው፤ልባቸውንም በእምነት ሲያነጻ በእኛና በእነርሱ መካከል አንዳች አልለየም።እንግዲህ አባቶቻችንና እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ በመጫን እግዚአብሔርን አሁን ስለ ምን ትፈታተናላችሁ?ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እንደ እነርሱ ደግሞ እንድን ዘንድ እናምናለን።’’ (ሃስ. 15:5-11)
በጌታ ምህረትና ጽድቅ በእምነትም ይኖሩ ወደነበሩ ከአህዛብ ወደ ጌታ ደቀመዝሙርነት ወደ ተለወጡ አማኞች ከይሁዳ የወረዱ አንዳንድ ሰዎች እንቅፋት የሆነ ትምህርታቸውን ይዘው ደረሱ፤ ይህ ትምህርት ወገኖች እንዲሰናከሉ በዲያብሎስ የተላኩ ሰዎች ወንድሞችን ለማወክ እና ቤተ ክርስቲያንን ለማስጨነቅ የተሰናዱ ነበሩ።
እነርሱም ካልተገረዛችሁ በቀር እምነታችሁ ከንቱ ናት በሚል ምክኒያት በኢየሱስ ላይ ያላቸውን እምነት አናወጡባቸው። የእውነተኛው አምላክ አማኞች የሆኑ አብዛኛዎቹ አይሁዳውያን የአህዛብን በኢየሱስ ብቻ መዳን ተቀብለው ሲኖሩ፣ እነርሱም ያለ ብሉይ ኪዳን የግርዘት ስርአት ለአዲስ ልደት በሚሆን መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ ድነው በመሃከላቸው በጸጥታ በአብሮነት እንዲኖሩ የፈቀዱ ሲሆን ሌሎች የአይሁድ ክፍል ግን ወደ ክርስትና መጥተውም በብሉይ ኪዳን ስርአት ትምክህት የጸኑትን እያናወጡ ነበር። በአንዳንድ አይሁዶች ዘንድ እንደሚታየው በጌታ ኢየሱስ ድነው ሳለ በክርስትናን ህይወት ከቀጠሉ በሁዋላ ዳግም ወደተዉት ተመልሰውና ሁከት ፈጥረው ውዝግብ እንዲቀጥል ለምን ሆነ?
አይሁዶች በተለይ በቆሮንቶስ፣ በገላትያና በፊልጵስዩስ ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት ያስቸገሩ እና ለቅዱስ ጳውሎስ ታላቅ ጠላት የሆኑ ሐሰተኛ ሐዋርያት ነበሩ፤ ተገረዙ ሕጉንም ሁሉ ጠብቁ እያሉ ሲጫኑ በጸጋ የዳኑትን ከመንገድ ሊያወጡ ሞክረዋል።
‘’ያን ጊዜ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ከቤተ ክርስቲያኑ ሁሉ ጋር ከእነርሱ የተመረጡትን ሰዎች ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር ወደ አንጾኪያ ይልኩ ዘንድ ፈቀዱ፤ እነርሱም በወንድሞች መካከል ዋናዎች ሆነው በርስያን የተባለው ይሁዳና ሲላስ ነበሩ።እንዲህም ጽፈው በእነርሱ እጅ ላኩ። ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ወንድሞችም በአንጾኪያና በሶርያ በኪልቅያም ለሚኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለሆኑ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርባሉ።ያላዘዝናቸው ሰዎች ከእኛ ወጥተው። ትገረዙ ዘንድና ሕግን ትጠብቁ ዘንድ ይገባችኋል ብለው ልባችሁን እያወኩ በቃል እንዳናወጡአችሁ ስለ ሰማን፥ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነፍሳቸውን ከሰጡት ከምንወዳቸው ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር የተመረጡትን ሰዎች ወደ እናንተ እንልክ ዘንድ በአንድ ልብ ሆነን ፈቀድን።ራሳቸውም ደግሞ በቃላቸው ያንኑ ይነግሩአችሁ ዘንድ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል። ለጣዖት ከተሠዋ፥ ከደምም፥ ከታነቀም፥ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና፤ ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ።’’ (ሃስ. 15:22-28)
እንደ ሙሴ ሥርዓት መገረዝ አለባቸው የሚለው ትምህርት መዳንን የሚጣረስ አሳብ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሄርን የደህንነት አሰራር የሚቃወም ነው፤ ካልነቁና ካልተጠነቀቁም በዚህ አሳብ ብዙዎችን ከጸጋው እንዲወድቁ እንደሚያደርግ ግልጽ ነው። ገላ 5፡4 ላይ ‘’በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል።’’ ሲል ያረጋግጣልና። ማድረግ በማትችሉት ነገር መቻል አስባችኋል፣ መሆን ያቃታችሁን መተው አቅቶአችኋል፣ እግዚአብሄር የሰጣችሁን አንድ ተስፋ መቀበል ተስኖአችኋል፣ እያለ ነው።
ሐሰተኛ ሐዋርያትና አስተማሪዎች በአካል ከይሁዳ ወጥተው እንደመጡ ሁሉ ከሐዋርያትም መንፈሳዊ ህብረት የወጡ ሃሰተኞች ሰዎች ነበሩ። ሃዋርያው ዮሐንስ ስለዚህ ከእኛ ዘንድ ወጡ ነገር ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም ይላል (1ዮሐ 2፡19)።
በክርስቶስ ሞት ከሥርዓትና ከሕግ ሁሉ ነፃ እንደወጣን ካመንን የወንጌል እምነትን አጥብቀን እንያዝ።
ደግሞ በራሳችን ጥረት መጽደቅ እንደማንችል ሁሉ፣ በራሳችን ጥረት ቅድስናችንን ማሳደግ እንደማንችል ይህን እውነት መጠበቅ ይገባናል። ነገር ግን “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ስለሚል ከጌታ ኢየሱስ ጋር የምንኖረው ኑሮ ወደ እርሱ በማደግ የህይወት ለውጥ እንድናመጣ ያደርጋል።
በቅድስና ሂደት ውስጥ እድገት አለ ብሎ መቀበልና ማሰብ ሞኝነት ቢመስልም መንፈሳዊነት ነው፣ እግዚአብሄርን ተስፋ ማድረግ ነው፣ በአሰራሩ መተማመን ነው፣ በእግዚአብሄር ምሪት በጽድቅ መኖር ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *