የወንጌሉ መሰረት (1…)

የወንጌሉ መሰረት ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ወንጌል የጌታን የማዳን ስራ የሚገልጥ መለኮታዊ አዋጅ ነው፤ ወንጌሉ የምስራች ሲሆን የወንጌል መነሻም መዳረሻም እሱ ሆኖ ለሰው ልጆች የማይነቃነቅና የጸና መሰረት በመሆን አስተማማኝነቱን አረጋግጦልናል፡፡ የአዲስ ኪዳን መሰረት የክርስቶስ የመስቀል ስራ ውጤት ስለሆነ ሰዎች ያን አውቀው በእምነት ይድኑ ዘንድ ለአለም ሊታወጅ የተገባው የጌታ አዋጅ ሆኖአል፤ ወንጌል የሰላም አዋጅ ስለሆነም እርሱ ተሰብኮ ሰዎች እንዲድኑ መድሀኒት የሆነ ጌታ በውስጡ ዋና መልእክት ሊሆን ይገባዋል፡፡ ስለዚህ ወንጌል ከጅማሬ እስከ ፍጻሜው ጌታ ኢየሱስን ማእከል አድርጎ ይሰብካል፣ ሰዎችም ወንጌሉ በገለጠው የማዳን ሀይል ይድናሉ፡፡ስለዚህ ለሰው ልጆች ይታወጅ ዘንድ ሃዋርያቱን የአዋጁ ነጋሪ አድርጎ በሾመው መሰረት ወደ አለም ሁሉ ሄደው ወንጌልን የምስራች የሚሉበት ስልጣን ተቀብለዋል።
አለም ስለወንጌል ልታውቅ ከሚገባት ምስጢር ጎን ለጎን የወንጌል ጀማሪም ባለቤትም ክርስቶስ ኢየሱስ መሆኑን ልታውቅ እንዲግባት ማስታወስ ይገባል፤ ይህ እውቀት ወንጌል በሰዎች የተፈጠረ ሃይማኖታዊ ትምህርት ለሚመስላቸው በአለም ለሚገኙ አዋቂዎች ማረጋገጫ ነው፣ እንዲህ ስለሚል፦
‘’ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፥ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፥ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ ​እየፈወሰ፥ በከተማዎችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር።’’ (ማቴ.9:35)
ለአይሁድ ህዝብ ያስፈልግ የነበረውን ትምህርት ከማቅረብ ጎን ለጎን እርሱን በሚገልጠው የመንግስት ወንጌል ህዝቡን እየሰበከ ይፈውሳቸው እንደነበር ቃሉ ያረጋግጣል፤ አይሁድ የብሉይ ኪዳን ባለቤት በመሆንቸው የሚያስፈልጋቸው ትምህርት ከአህዛብ ይልቅ ከፍ ያለ ነው፤ ምክኒያቱም ከወንጌሉ አስቀድሞ የብሉይ ኪዳን የጥላነት አገልግሎት እውቀት ያስፈልጋቸው ስለነበረ ነው፤ መጽሃፍት ሁሉ ስለእርሱ እንደሚናገሩ ጌታ እየነገራቸው ሳለ እንኩዋን ማስተዋል የተሳናቸው ህዝቦች በወንጌል ያለውን የመዳን ጸጋ የቀበሉ ዘንድ እንዴት እንዳስቸገራቸው ታሪካቸው አመልካች ነው። ስለዚህም አጽንተው በሚቅወሙት መሃል ወንጌል ከመሰበክ እንደማይቆም አጽኖት ሰጥቶ ሲነግራቸው እንመለከታለን፦
‘’ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው።’’ (ማቴ.11:6)
አዎ ሰው የዘላለም ህይወት ስለሚገባው ወንጌል የግድ ሊሰበክለት ይገባል፤ የዘላለም አምላክ ህይወትን የሚሰጥ ነውና በሰጠው ወንጌል በኩል ሊታወቅና ነፍሳት በእርሱ በማመን ሊድኑ የግድ ነው። የሃይማኖት መሪዎች ግን የግል እምነትና እውቀታቸው እንቅፋት ሆኖ ስለሚያሰናክላቸው ታላቅ መዳን ያልፋቸዋል።
‘’ዮሐንስም አልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና፦ ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ እያለ ወደ ገሊላ መጣ።’’ (ማር.1:14-15)
ይህ ቃል የወንጌል አዋጅ ጅማሬ ሰአት ሲደርስ የሆነውን ክንዋኔ ያስረዳል፤ በብሉይ ኪዳን ፍጻሜ ላይ የተገለጠው ካህን ዮሃንስ የክርስቶስን መገለጥ አዋጅ ሲፈጽምና ተልእኮን ሲያጠናቅቅ ጌታ ደግሞ ስራውን በወንጌል አዋጅ ሲጀምር እንመለከታለን።የወንጌልን አዋጅ የጀመረው ጌታ በቀጣይ ወንጌሉን በአለም ሊያዳርሱ የሚበቁ ሰዎች ጠራ፤ የጌታ አዋጅ በሌላ በኩል ብዙዎችን ወደራሱ ጠራ፤ የሰሙ አይሁድም ከየስፍራው ወደ እርሱ መሰብሰብ ያዙ፣ እርሱም የሚያስፈልጋቸውን እየሰራ፣ በጉብኝቱ መድሃኒት ሲሆናቸው እናያለን፤ ዛሬም እውነተኛው ወንጌል በሚሰበክበት ስፍራ ሁሉ የጌታ ስራ ይገለጣል፦
ማር.1:21-34 ’’ወደ ቅፍርናሆምም ገቡ፤ ወዲያውም በሰንበት ወደ ምኵራብ ገብቶ አስተማረ። እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበር እንጂ እንደ ጻፎች አይደለምና በትምህርቱ ተገረሙ። በዚያን ጊዜም በምኩራባቸው ርኵስ መንፈስ ያለው ሰው ነበረ፤እርሱም፦ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ። ኢየሱስም፦ ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው። ርኵሱም መንፈስ አንፈራገጠውና በታላቅ ድምፅ ጮኾ ከእርሱ ወጣ።ሁሉም፦ ይህ ምንድር ነው? በሥልጣን ርኵሳን መናፍስትን ያዝዛል፤ እነርሱም ይታዘዙለታልና ይህ አዲስ ትምህርት ምንድር ነው? ብለው እስኪጠያየቁ ድረስ አደነቁ። ዝናውም ወዲያው በየስፍራው ወደ ገሊላ ዙሪያ ሁሉ ወጣ። ወዲያውም ከምኵራብ ወጥቶ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ ስምዖንና ወደ እንድርያስ ቤት ገባ። የስምዖንም አማት በንዳድ ታማ ተኝታ ነበር፥ ስለ እርስዋም ወዲያው ነገሩት። ቀርቦም እጅዋን ይዞ አስነሣት ንዳዱም ወዲያው ለቀቃትና አገለገለቻቸው። ፀሐይም ገብቶ በመሸ ጊዜ፥ የታመሙትንና አጋንንት ያደረባቸውን ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤ከተማይቱም ሁላ በደጅ ተሰብስባ ነበር። በልዩ ልዩ ደዌም የታመሙትን ብዙዎችን ፈወሰ፥ ብዙዎችንም አጋንንት አወጣ፥ አጋንንትም ክርስቶስ መሆኑን ​አውቀው ነበርና ሊናገሩ አልፈቀደላቸውም።’’
በዚያን ወቅት በህዝቡ ዘንድ ከታወቀው ይልቅ ጌታ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑ በአጋንንት በግልጽ ታውቆ ነበር፤ ነገር ግን የክርስቶስ መታወቅ ህይወትነቱ ለህዝቡ ነውና ወንጌል በግልጽ የተሰበከው ክርስቶስ በአዋጁ ይገለጥ ዘንድ ነው፤ ክርስቶስን ቀድመው ያወቁ አጋንንት ቀጣዩ ስራቸው እውቀትን መሰወርና ልዩ ትምህርትን በማሰራጨት ሰዎች በእውነተኛው ወንጌል በኩል የክርስቶስን ማንነት አውቀው እንዳይድኑ እንቅፋት ማኖር ነው። በዚህም ዘመን ከየትኛውም ትውልድ ይልቅ የበዙ ትምህርቶችን ለአለም እያስተማረና ወንጌልን እያጣመመ ሰዎች እውነቱን እንዳያምኑ ያደርጋል፤ አለምንም በስህተቱ አስሮአል። የጌታ ትምህርት ግን ህይወትን የሚሰጥ በመሆኑ የሰሙና ያመኑ ሁሉ ወደእርሱ ይመጡ ነበር እርሱም በሚያስፈልጋቸው ሁሉ ይሞላቸው ነበር። ጌታ ኢየሱስ ባለጸጋ አምላክ ነው፤ ወደ እርሱ ለመጡና ላመኑት ሁሉ ከሙላቱ እየሰጠ ይባርካል፣ ይህ ደግሞ እግዚአብሄር ለሰው ልጆች ያዘጋጀው የወንጌል ትሩፋት ነው። ጌታ ባለፈባት ስፍራ ከተማይቱም ሁላ በደጅ ተሰብስባ ነበር፣ ህዝብ በሞላ ከቀዬው ንቅል ብሎ ወደእርሱ የሚከማቸው አንድ ህዝብን የሚስብ የጸጋ አሰራር በትምህርቱ ገልጦ ስለነበር ነው። አምነው የመጡትም አንዳች አልጎደለባቸውም ነበር፤ ለነፍሳቸው የተገባውን የህይወት ቃል ከመገበ በሁዋላ ስጋቸውንም ይመግብ፣ ይፈውስ ነበር፤ በልዩ ልዩ ደዌም የታመሙትን ብዙዎችን ሲፈውስ፣ ብዙዎችንም አጋንንት አውጥቶ ነጻ አድርጎአቸው ነበርና።
በብዙዎች አይሁድ ዘንድ የነበረው የህይወት ለውጥ ሲዘገይ የሚታየው በሚሰሙት የወንጌል ቃል ላይ በነበራቸው የላላና የደከመ እምነት ምክኒያት ነበር፤ እንዲያውም ብዙዎች እየተከተሉት የነበረው ሆዳቸውን ሊሞሉ ብቻ እንደነበረ በመንቀፍ ተናግሮአቸዋል፤ ወንጌል ግን በዋናነት ነፍስን ለማዳን ተሰበከ።
‘’ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን ያድናታል። ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?ሰውስ ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?በዚህም በዘማዊና በኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በአባቱ ክብር ​ከቅዱሳን መላእክት ጋር በመጣ ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል።’’ (ማር.8:35-38)
ሰው አለምን ቢያስቀድም አለም ለጥቂት ዘመን ብቻ ታስደስተው ይሆናል፣ የነፍስ ተስፋ ግን አትሆነውም፤ ኢየሱስ ግን የዘላለም ህይወት ሊሰጠን የታመነ ስለሆነ እርሱን ብንመርጥ ብናስቀድምም በርሱ ውስጥ ያለውን ህይወት በመስጠት የዘላለም ህይወትን ያጎናጽፈናል። እርሱ ራሱ በዮሐ.11:25-26 ላይ ሲናገር፦
‘’ኢየሱስም፦ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት።’’
በአዲስ ኪዳን መልእክት ላይ ቅድሚያና ዋነኛ ርእስ ሆኖ የሚጎላው ወንጌል ነው፤ ቅዱሳን የዳኑበትን ወንጌል ዋነኛና ለሁሉ መፍትሄ የሚሰጥ መሳርያ አድርገው እንዲመለከቱት የወንጌላት መጻህፍት በዚህ ላይ አትኩሮት ሲያደርጉ እንመለከታለን፤‘’የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ።’’ ይላል ማር.1:1።
በዚህ ዘመን ያሉ አስተማሪዎች ከአይሁድም ሆነ ከአህዛብ የሆኑ አስተምሮአቸው ፍልስፍናና ሰዋዊ ትምህርት ላይ ስለተመሰረተ በብዙ መንገድ የወንጌሉ ጸጋ ጠፍቶ፣ ቃሉ ተበርዞ ወይ ተደልዞ ያልያም አዲስ ሰዋዊ አሳብ ተጨምሮበት በመላ አለም ላይ ይሰራጫል። ወንጌል ግን ባለቤት አለው፣ ተመልካች አለው፣ ተቆጣጣሪም አለው፦
ዕብ.2:1-4 ‘’ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ፥ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል። በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ፥ መተላለፍና አለመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ፥ እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፥ እንዴት እናመልጣለን?ይህ በጌታ በመጀመሪያ የተነገረ ነበርና፥ የሰሙትም ለእኛ አጸኑት፥እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም፥ መንፈስ ቅዱስንም በማደል አብሮ መሰከረለት።’’
ሃዋርያው በመልእክቱ መሃል አይሁድን ይጠይቃል፣ ህግ የተሰጣቸውን ህዝቦች በሚያስታውስ መልኩ ስለ ህጉ ብርቱነት ያነሳል፤ በመላእክቱ አንደበት በኩል የመጣላቸው የህጉ ቃል የነበራቸው እነዚህ ህዝቦች ምን ያህል ህጉን በመተላለፋቸው እንደተቀጡ እንዲያስታውሱ እያለ ከህጉ በላይ ሆኖ በጸጋ የተገለጠ የእግዚአብሄር ማዳን እውቀት እርሱም ወንጌል ከህጉ ይልቅ እንዴት ያለ ጥንቃቄ ይፈልግ? ሲል ታላቅነቱን ያሳያል። የህጉ ቃል በረከትና መርገምን ይዞ በህዝቡ መሃል ሲኖር ህጉን መጠበቅ በተሳነው አይሁድ ላይ የመቅሰፍት በትሩ በርትቶ እንደኖረ የጽናቱን ጉልበት እንዲያስታውሱ ሁኔታውን በአጭር ቃል ይጠቁማቸዋል፤ በሌላ በኩል ምህረትና ቤዛነት ያለበት የአዲስ ኪዳን መዳን ቸል ከተባለ የዘላለም ሞት እንዲያስከትል ተረድተው እንደሆነ ታልቅ ቅጣቱን ያሳያቸዋል።
እግዚአብሄር ይህን መዳን በምልክትና በድንቅ ነገር በልዩ ልዩ ተአምራትም፥ መንፈስ ቅዱስንም በማደል እየመሰከረ ሳለ ለምን የሰው ልጅ ይህን ጌታ አላከበረም፣ አልፈራምስ? በእርግጥ የጨለማው ጥልቅነት የሰራው የጥፋት ስራ ይህን አድርጎአል።
ሉቃ4:17-19 ‘’የነቢዩንም የኢሳይያስን መጽሐፍ ሰጡት፥ መጽሐፉንም በተረተረ ጊዜ፦ የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ​ነጻ አወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት እሰብክ ዘንድ ልኮኛል ተብሎ የተጻፈበትን ስፍራ አገኘ።’’
በእግዚአብሄር በተወደደ የጌታ አመት/የእግዚአብሄር ፈቃድ ተጠብቆ ሊገለጥ ባቀደው ዘመን ላይ የህይወት ወንጌል ከአምላክ ዘንድ ተገልጦአል፣ ይህን በጌታ የተረጋገጠ እውነት አምኖ መዳን የእያንዳንዱ ሰው ፈንታ ነው።
የጸና ወንጌል፣ የማይናወጥ የማይለወጥ
ወንጌል የሰው አሳብ አይደለምና አይለዋወጥም፣ በብዙ ሃይማኖተኞች እንደሚታሰበው የሚታከልበት የሚፍታታና የሚብራራ ምስጢር የተወልን የጽሁፍ መድብል አይነት አይደለም፤ ያልያም ትውልድን እያየ እንደየትውልዱ ስነልቦና አይረዝምም፣ አያጥርም፣ አይሰፋም፣ አይጠብምም፤ የእግዚአብሄር አሳብ ነውና ፈቃዱን የሚያውቁ አምነው የሚቀበሉት የመለኮት አዋጅና የምስራች ነው፤ ትውልድን የሚመራ እንጂ ለትውልድ ሸብረክ የሚል አቅም የሚጎድለው አሳብ አይደለም፤ የሰው ፈቃድ ቢሆን ኖሮ እንደፈቅዳችን አይነት ይለዋወጥ ነበር፤ ማንነታችንን እየተከተለ በተለዋወጠ ነበር፤ እንዲሁም የሰውን አሳብ ለመሙላት የተገለጠ እውቀት አይደለም፤ ነገር ግን የሰው ልጅ እግዚአብሄር ከዘላለም ዘመናት አስቀድሞ ሊያደርገው ያቀደው፣ እስከሚሆንም ሰውሮ ያስቀመጠው የደህንነት ምስጥር ነው፤ የሰው የዘላለም ህይወት አቅጣጫ የተቀመጠበት፣ የህይወት ምንጭን የሚጠቁም መመሪያ ያለበት፣ የሰው ልጅን እምነት አንስቶ ወደ እግዚአብሄር የክብር ስፍራ የሚያገባ የጸጋ አሰራር… ያለበት መለኮታዊ ቃል ነው።
ማር.16:8 ‘’መንቀጥቀጥና መደንገጥ ይዞአቸው ነበርና ወጥተው ከመቃብር ሸሹ፤ ይፈሩ ነበርና ለማንም አንዳች አልነገሩም። ​እነርሱም ያዘዛቸውን ሁሉ ለጴጥሮስና ከእርሱ ጋር ላሉት በአጭሩ ተናገሩ። ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ራሱ ለዘላለም ድኅነት የሆነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በእጃቸው ላከው።’’
ወንጌል ለዘላለም ድኅነት የሆነና የማይለወጥ ባህሪ እንዳለው የወንጌሉ ባለቤት የሆነው ጌታ ኢየሱስ አሳይቶአል፤ ስለዚህ ለውጥ ሳይሆን ከጸሃይ መውጫ እስከ ጸሃይ መጥለቂያ በሚደርስ የምድር ስፋት ለሰው ልጅ በሙሉ አድርስ የሚል ትእዛዝ ነው የተሰጠው።
ከእግዚአብሄር ዘንድ አስተማማኝ የደህንነት ወንጌል ስለተሰጠን እግዚአብሄርን ማመስገን አለብን፤ እኛ አህዛብ ተስፋ የሌለን ወገኖች ነበርንና፤ ያንን ሽሮ ወደ እኛ የመጣን ጌታ አክብረን በሰጠን የመዳን ቃል መለወጥ ሊገኝ የማይችል በእግዚአብሄር ምህረት ምክኒያት የሆነልን ነው።
‘’አንድ ቀንም ሕዝቡን በመቅደስ ሲያስተምር ወንጌልንም ሲሰብክላቸው፥ የካህናት አለቆችና ጻፎች ከሽማግሌዎች ጋር ወደ እርሱ ቀረቡና፦እስኪ ንገረን፤ እነዚህን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ ወይስ ይህን ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው? ብለው ተናገሩት። መልሶም፦ እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፥ እናንተም ንገሩኝ፤የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? አላቸው። እርስ በርሳቸውም ሲነጋገሩ፦ ከሰማይ ብንል፦ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤ከሰው ብንል ግን ሕዝቡ ሁሉ ይወግሩናል፤ ዮሐንስ ነቢይ እንደ ነበረ ሁሉ ያምኑ ነበርና አሉ። መልሰውም፦ ከወዴት እንደ ሆነ አናውቅም አሉት።’’ (ሉቃ.20:1-7)
ሃይማኖት ከሃይማኖት ሰጪና ከራሱ አንደበት ከወጣ ወንጌል ካልሆነ አደጋው ከፍተኛ መሆኑን ከላይ ያለው ቃል ያረጋግጥልናል፤ በዘመናችን የሃይማኖት መሪዎች ክምችት አለምን እንዳስጨነቀ ከምንሰማው የትምህርት አይነት እንገነዘባለን፤ ሁሎቹም ግን የተያያዙት ጌታን መጋፋት፣ ቃሉን ማጣመም፣ ህዝብን ማሳት የመሳሰለ ጥፋት ማካሄድ እንጂ እርሱ የሰጠውን መዳን የሚናገሩ አይደሉም።
ጌታ ሕዝቡን በቤተመቅደስ እያስተማረ፣ ወንጌልንም እየሰበከ ነበር። እርሱ የራሱን ወንጌል የሚሰብክ ፊተኛው ሰባኪ ነበር። ድኅነትን በመስጠት በደሙ የገዛን ብቻ ሳይሆን ስራውን በወንጌል እውነት ያተመው ራሱ በመሆኑ ለእምነታችን ታላቅ ማረጋገጫ ነው፣ይህ ማረጋገጫው ሰዎች በተስፋና በደስታ ወንጌሉን እንድንቀበል ማበረታቻን ይሰጠናል፣ጌታ ኢየሱስ ወንጌልን ይሰብክ የነበረውና ዛሬም እንዲሰበክለት ባሪያዎቹን የሚያዘው በወንጌሉ ላይ ለሰዎች ያለው ፈቃዱ ስለተገለጠ ነው፤ ስለዚህ የወንጌል ሰባኪ ለሆኑ አገልጋዮቹ ሞገስና ክብርን ይሰጣል፤ ከአፋቸው ጋር ይሆናል፤ ምሪት ይሰጣቸዋል፤ ከማናቸውም ክፉ አሰራሮች ይጠብቃቸዋል፣ ምክኒያቱም ይዘው የሚጓዙት፣ የሚሰብኩትም የከበረውን ወንጌል ነውና። ክርስቶስ ለሰዎች ወንጌልን በመስበኩና ያን ተከትሎ በእምነት የቀቀበሉትን በደህንነት አቅሞአቸዋል፤ የተቃወሙትን ግን ከመንገድ አስወግዶአቸዋል። ለሰዎች ህይወት የሚሰጠው ወንጌል በሚሰብክበት ጊዜና ስፍራ ከክፉ መናፍስት ተልከው ጣልቃ የሚገቡ ሰዎች ይኖርሉ፤ እነዚህ ሰዎች ይህ የህይወት ቃል እንዳይነገር የማስተጓጎል ስራ ይሰራሉ፣ ነገር ግን በእግዚአብሄር መንግስት አይቀናላቸውም፤ እናስተውል፣ ሰይጣንና ወኪሎቹ የሰይጣንን መንግሥት ፍላጎት በማሰራጨት ቢጠመዱና ህይወት ያለበትን ቃል ቢገዳደሩም የወንጌሉ ባለቤት በፍርድ እንደሚይዛቸውና በዘላለም ቅጣት እንደሚቀጣቸው ተናግሮአል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *