በሚሠራበት ቀን (1…)

እግዚአብሄር ወደ ሰው ልጆች ሲመለከት አብረሃምን አየና ከቤተሰቡ መሃል ለይቶ ጠራው፣ ለምን? እግዚአብሄር የአብረሃምን ማንነት ስላወቀ፣ መጀመሪያ ላይ መጨረሻውን ስላየ፣ የአህዛብ ወራሽ መሆን እንደሚችል መንፈሱን ስለመዘነና የእርሱን መለኮታዊ አሳብ መጠበቅና መፈጸም የሚችል ሰው እርሱ መሆኑን ስለሚያውቅ፣ እንዲሁም የሰው ልጆች የእምነት አባት መሆን የሚችል እርሱ መሆኑን ስለወሰነ ነው። ያኔ በጥንት ዘመን በእግዚአብሄር ጊዜ ውስጥ የእግዚአብሄርን አላማ ማስፈጸም የሚችል ብቸኛ ሰው ሆኖ ስለተገኘ መሆኑንም ማወቅ አለብን። ሁልጊዜ ለእግዚአብሄር ጉዳይ እግዚአብሄር ያሻውን ማድረግ የሚችል ሙሉ አምላክ መሆኑን ካላወቅን ከመነሻው በአብረሃም ምርጫ ላይ ጥያቄ ይነሳል፣ ይህ የሰው ባህሪ ነው። መንፈሳዊ እውነትን በትልቅ ገጹ በኩል ያልተረዱ አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሄር የአብረሃም አምላክ ነው ሲባል ለየት ያለ ሰዋዊ ድምድሜ ላይ ሲደርሱ እናያለን፤ ነገር ግን አስተዋዮች እንዲህ ያለ ድምዳሜ ውስጥ ከመግባት ይልቅ ለእግዚአብሄር ሁሉን ቻይነትና ሁሉን አዋቂነት ቅድሚያ እንዲሰጡ፣ እንዲሁም አስቀድመው የእግዚአብሄርን ፈቃድ እንዲቀበሉ ተገቢ ነው።
አብረሃም ገና በሚኖርበት የሞቀ ህይወት ውስጥ ሳለ፣ በዘመዶች መሃል ተከብቦ በሚኖርበትም ወቅት እግዚአብሄር ድንገት መጣና ጠራው። ጥሪውም ተለይ፣ ውጣ፣ ራቅና ሂድ የሚል ስለሆነ ይህን የሚሰማ ሌላ ሰው መደናገጡ፣ መደናገሩም የማይቀር ነበር። ለአብረሃም የመጣው ቃል ግን ወደ ማታውቀው ምድርና ማህበረሰብ ዘንድ እልክሃለው የሚል ነበር፤ በአብረሃም በኩል የእግዚአብሄርን ግብዣና ጥሪ ከመቀበል ይልቅ ግራ መጋባት የሆነበት ሁኔታ ሳይሆን መታመንና ለቃሉ ቅድምያ መስጠት የሆነበት እሺታና ታዛዥነት ያለበት ስለነበር እንደጥሪው መጠን አብረሃምን አሳምኖ ያስወሰነ ነበር። ሊሆን ይችላል የሚል እምነት ነበረውና በአማኙ ዘንድ ትልቅ ምሪት ነበር፤ ነገር ግን ምንም ግራ የሚያጋባና የማይመች ጥሪ ቢሆንም ትሁት የሆነው ይህ ሰው በመታዘዝ ወጣ። እሺ ማለት ብሩህና ትሁት ልብ ይጠይቃል፣ ታማኝነት ይፈልጋል፣ ታዛዥነትም ይፈልጋል። እንዲህ አይነት ታዛዥነት፣ እግዚአብሄርን መፍራትና መፈለግ ግን በአብረሃም ትውልድ አልተገኘም፣ በሌሎች ህይወት እምነት የሚቻል አልነበረም። አብረሃም ግን ታዛዥ ነበረ፤ ትሁት ነበረ፤ ተስፈኛ ነበረ፤ ከምንም በላይ ፍጹም አማኝ ነበረ።
ዘፍ.12:1-4 ‘’እግዚአብሔርም አብራምን አለው፦ ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ። ታላቅ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም አከብረዋለሁ፤ ለበረከትም ሁን፤ የሚባርኩህንም እባርካለሁ፥ የሚረግሙህንም እረግማለሁ፤ የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ። አብራምም እግዚአብሔር እንደ ነገረው ሄደ፤ ሎጥም ከእርሱ ጋር ሄደ፤ አብራምም ከካራን በወጣ ጊዜ የሰባ አምስት ዓመት ሰው ነበረ።’’
እንዲህ ከሰማይ አምላክ ተስፋውን የተቀበለ ሰው የሰጠውን ተስፋ ማግኘቱ እርግጥ ነበር፤ ሊያውም እውነተኛ አምላክ ተናግሮ፣ ተስፋ ሰጥቶ፣ ቀርቦ አነጋግሮ እርሱን ይወቁት እንጂ መሆኑ እርግጠኛ ነው። እግዚአብሄር የሰጠው ተስፋ ከቅርብ ዘመን እስከ ሩቅ ዘመን የፍጻሜ ጊዜ የሚጠይቅ ነው፤ እንዲሁም በተነገረበት ትውልድ የሚሆን ያልያም ከብዙ ትውልዶች ህልፈት በሁዋላ ሊሆንም የሚችል ነው፤ እንዲሁም ደግሞ የትንቢቱ ፍጻሜ ስፍራ ቃል በተገባለት ህዝብ ምድር ላይ ይሆናል ያልያም ሌላ እግዚአብሄር ባዘጋጀው ስፍራ ሊሆን የሚችል ነው። አብረሃም እንዲያ አምኖአል፣ ቅሉም ይመሰክርለታል፦
ዕብ.11:8 ‘’አብርሃም የተባለው ርስት አድርጎ ሊቀበለው ወዳለው ስፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ፥ ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ። ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር፥ እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፤ መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና። ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደ ሆነ ስለ ቈጠረች፥ ሣራ ራስዋ ደግሞ ዕድሜዋ እንኳ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኃይልን በእምነት አገኘች። ስለዚህ ደግሞ በብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ እንደማይቈጠርም በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ የነበሩት የሞተን ሰው እንኳ ከመሰለው ከአንዱ ተወለዱ።’’
አብረሃምን ከሚኖርበት ያወጣው እምነት ከአንድ አነስተኛ ሰፈር ተነስቶ እስከ ሌላኛው ሰፈር ይህን ያህል
ርቀት የሚጓዝ ተብሎ የሚለካ ተስፋ አልነበረውም፤ እሩቅ የሚሄድ፣ በእምነት ይሄኛውን አለም የሚሻገር
ነበር፤ ይህን ግን እንዴት አገኘው? ከእግዚአብሄር ጋረ በመስማማቱ እጅግ የሚያስደንቅ መገለጥ ነበር
የተቀበለው ማለት ነው፤ እግዚአብሄር ሲጠራ ከእውቀት ጋር ስለሆነ፤ ከሚረዳ መንፈስም ጋር ስለሆነ
እንደ አብረሃም የታመኑቱ እስከመጨረሻው በደስታ የሚከተሉት ነው የሚሆነው።​​​​​
መዝ.77:11-13 ‘’የእግዚአብሔርን ሥራ አስታወስሁ፤ የቀደመውን ተአምራትህን አስታወሳለሁና፤ በምግባርህም ሁሉ እናገራለሁ፥ በሥራህም እጫወታለሁ። አቤቱ፥ መንገድህ በመቅደስ ውስጥ ነው፤ እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው?’’
ስራውን የሚያስተውል ወገን
በንጉስ ህዝቂያስ ዘመን በአንድ ልብ እስራኤል እግዚአብሄርን ይፈልግ ዘንድ ወደ ኢየሩሳለኢም ተሰብስቦ ነበር፤ ለአምልኮ ተዘጋጅቶ፣ በደስታ መስዋእት ሊያቀርብ ተዘጋጅቶና በህብረት የአባቶቹን አምላክ ይገናኝ ዘንድ ሽቶ ስለመጣ እግዚአብሄር በህዝቡና በንጉሱ ተደስቶ በብዙ ምህረት ተቀበላቸው። እግዚአብሄርን የሚያምን የእግዚአብሄርን ባህሪ ያስተውላልና።
እንዲህ አምላክን የሚያውቅ ህዝብ ሲገኝ የእግዚአብሄርን አሰራርም ሊረዳና ሊያስተውል ይገባዋል፤ አሰራሩን ማመን ትልቅ ነገር ነው፤ አሰራሩን ስናምን እግረመንገድ የምናስተውለው እግዚአብሄር የሚመጣበትን መንገድ የምይወሰን መሆኑን ነው፤ እናምንና እንጠብቀዋለን እንጂ አቅጣጫውን እርግጠኛ ሆነን ይህ ነው አንልም፤ ብቻ እንዲመጣ እንዲሰራም በእርግጥ እንናገራለን። ይህን አንድ ነገር ይዘን ተስፋውን በመንፈስ እንመረምራለን።
በመንፈስ አለም ውስጥ ለመመላለስ የእግዚአብሄር የሆነውንም ለመቀበል እያንዳንዱ ቀን ይዞት የሚመጣውን ነገር በቃሉ መነጽር በማየት ከዚያ ውስጥ መንፈሳዊውን ጉዳይ መለየት ይጠይቃል። በባህር ይምጣ በደረቅ ምድር ግድ የለም፤ በቀን ይምጣ በሌሊትም ግድ የለም፤ በእውን ይሁን በራእይ ያልያም በህልም ይሁን፤ የሚናገረው ለራስህ ይሁን ያልያም በባልንጀራህ በኩል እሰየው ብቻ እግዚአብሄር ይምጣ፤ ለመቀበል በመንፈስ ዝግጁ መሆን፣ ስራውን ለማየት ዝግጁ መሆን፣ የሰራውን ስራ መቀበልና አመስጋኝ ለመሆን ዝግጁ መሆን እጅግ ያስፈልጋል። መሰረቱ ግን የእግዚአብሄር ቃል፣ የምንሰማው ከእግዚአብሄር አሳብ ጋር የማይጋጭም መሆኑን በጥንቃቄ ከማስተዋል ጋር። ​​​​​​​​
መዝ.64:9-10’’ ሰዎች ሁሉ ፈሩ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ ተናገሩ፥ ሥራውንም አስተዋሉ። ጻድቅ በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል፥ በእርሱም ይታመናል፤ ልባቸውም የቀና ሁሉ እልል ይላሉ።’’ ይላል።
እግዚአብሄር በሚሰራበት ቀን ምስክር ሊሆን የሚቆም የታደለ ነው፤ ደግሞ ልባቸው ለቀና ለነርሱ እግዚአብሄር ስራውን ይገልጣል፣ እነርሱም የሚሰራበትን ጊዜ በትግስት በመመርመር፣ የአሰራሩንም መንገድ ከርሱ በመቀበል በእምነትና በትግስት አከናውኖ እስኪያዩ ሊጠብቁት የተገባ ነው። እግዚአብሄር እንደሚሰራ ማመን አንድ ነገር ነው፣ እንዴት እንደሚሰራ መቼ እንደሚሰራ ማወቅ ደግሞ ሌላ ማስተዋል ነው።​​​​​​​
መዝ.66:1-5 ’’በምድር ያላችሁ ሁሉ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፥ ለስሙም ዘምሩ፥ ለምስጋናውም ክብርን ስጡ። እግዚአብሔርን እንዲህ በሉት:- ሥራህ ግሩም ነው፤ ኃይልህ ብዙ ሲሆን ጠላቶች ዋሹብህ። በምድር ያሉ ሁሉ ለአንተ ይሰግዳሉ፥ ለአንተም ይዘምራሉ፥ ለስምህም ይዘምራሉ። ኑ የእግዚአብሔርንም ሥራ እዩ፤ ከሰው ልጆች ይልቅ በምክር ግሩም ነው።’’
የእግዚአብሄር ስራ ለልጆቹ ሁሌም መልካም፣ አስደሳችና ለበጎ ተጽእኖ ነው፤ በሚሰራበት ቀን የጠበቁትና የስራውን ፍጻሜ የጓጉ በትልቅ ምስጋና ይቀበሉታል፤ የሚያምኑት በስራው ይገረማሉ፣ ያመሰግናሉ፣ ይዘምራሉ፤ የሚጠራጠሩ ሰነፎችና ስራው እንዳይነገር የሚለፉ ክፉ መናፍስት ግን በስራው ብዙ ማመንታት እንዲኖር ይሰራሉ፤ እርሱን የሚያውቁት አብዝተው ለሰው ልጆች ምስክር እያወሩ ‘’ኑ የእግዚአብሔርንም ሥራ እዩ፤ ከሰው ልጆች ይልቅ በምክር ግሩም ነው።’’ ይላሉ።
ስራው ድንቅና ግሩም የሆነ አምላክ በሚሰራበት ቀን ምን እንዳደርግ ከእኔ ይጠብቃል?በሚሰራው ስራ እኔም እንድባረክ ምን ላድርግ? አዲስና ታላላቅ ነገሮች ከእርሱ ዘንድ ሆነው በዘመኔ እንዳይስ ምን ማድረግ አለብኝ? የሚሰራበትን ቀን ማወቅ እችላለሁ? በሚል የእግዚአብሄርን እጅ ከናፈቅን ለእነዚህ አሳቦች ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባል፤ ከዚህ በተጨማሪ እግዚአብሄር ምን ማድረግ እንደሚገባኝ በቃሉ በኩል ሊያመለክተኝ ይገባል።​​​​​​​​
መዝ.77:13-19 ‘’አቤቱ፥ መንገድህ በመቅደስ ውስጥ ነው፤ እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው? ተኣምራትን የምታደርግ አምላክ አንተ ነህ። ለሕዝብህ ኃይልን አስታወቅሃቸው። የያዕቆብንና የዮሴፍን ልጆች፥ ሕዝብህን በክንድህ አዳንሃቸው። አቤቱ፥ ውኆች አዩህ፥ ውኆችም አይተውህ ፈሩ፤ ጥልቆች ተነዋወጡ፥ ውኆችም ጮኹ። ደመኖች ድምፅን ሰጡ፥ ፍላጾችህም ወጡ። የነጐድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነበረ፤ መብረቆች ለዓለም አበሩ፤ ምድር ተናወጠች ተንቀጠቀጠችም። መንገድህ በባህር ውስጥ ነው፥ ፍለጋህም በብዙ ውኆች ነው፥ አረማመድህም አልታወቀም።’’
በየትኛውም የህይወት ሁኔታ የእግዚአብሄር ስራ መገለጡ አይቀርም፤ በሰው ልጅ በኩል ግን ስራውን የመቀበል ነገር ዋና ጉዳይ መሆን ይገባዋል።
ዳዊት በምእራፍ (77) ውስጥ ስለሚያስበው የእግዚአብሄር ነገር ይናገራል፤ በጥልቀት ስለሚያሰላስለውና መሆን ስለሚመኘው ነገርም ይገልጣል። ይህ ነቢይ የሆነ ንጉስ በእግዚአብሄር መንፈስ ሆኖ የእግዚአብሄርን አሰራር ሲመለከት፣ አምላኩ ሊሰራ የሚችለውን ሲያሰላስል በነገሩ ጥልቅ ይሆነ የርሱ ስራ ላይ የደረሰ ይመስላል።
ዳዊት በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ ቃሌም ወደ እግዚአብሔር ነው፥ እርሱም አደመጠኝ ይላል። አዎ እርሱ ድምጹን ከፍ ቢያደርግ በቀጥታ ወደ አምላኩ አርጎ እንዲሰማና ወደርሱ ያሰማው ልመናም መልስ ይዞ እንዲመጣ ማመኑን ያሳያል። ከእግዚአብሄር ዘንድ ሊመጣ ያለው የዘመኑን አደራረግ እንዴት ሊቀበል እንዳለው ንጉሱ አስተውሎአል። የዘመኑ ጉብኝት በሰው ዘንድ ያለን መጠባበቅ ይቀርጻል፤ እግዚአብሄርን በእውነት ያመለኩ ሁሉ የእርሱ ጉብኝት መናፈቅ ብቻ ሳይሆን በስጋም በመንፈስ ዝግጅት እንደነበራቸው ቃሉ ያስተምረናል፤ ቀጥሎ ባለው ቃል ውስጥ የምናየው ይህ ነው፦
‘’በከለዳውያን መንግሥት ላይ በነገሠ፥ ከሜዶን ዘር በነበረ በአሕሻዊሮስ ልጅ በዳርዮስ በመጀመሪያ ዓመት፥ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት እኔ ዳንኤል የኢየሩሳሌም መፍረስ የሚፈጸምበትን ሰባውን ዓመት፥ እግዚአብሔር በቃሉ ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረውን የዓመቱን ቍጥር በመጽሐፍ አስተዋልሁ። ማቅ ለብሼ በአመድም ላይ ሆኜ ስጾም እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ ወደ አምላክ አቀናሁ።ወደ አምላኬም ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ፥…’’ (1ዳን.9:1)
መቼ ወደ እግዚአብሄር እንማልድ፣ እንዴትና በምን ሁኔታ? ይህ እውቀት በቃሉ በኩል ምሪት በመቀበል የሚሆን እንደሆነ ከዳነኤል ልምምድ እንማራለን። ስለዚህ እያንዳንዳችን ከቃሉ ጋር ያለንን ቁርኝት በይበልጥ በማስፋት በጥብቅ በእምነት መደገፍ እንዲያስፈልግ እናያለን፤ በዚህ መንገድ ከቃሉ ውስጥ የሚወጣውም የእግዚአብሄር ጉብኝት ሳያልፈን እንደሚያገኘን በጉልህ የሚታይ ነው። ነቢዩ ዳነኤል በእግዚአብሄር መገኘት ውስጥ በጾምና በጸሎት ስለቆየ ማስተዋል ተቀበለ፤ በዚያ ውስጥም የሩቅ ጊዜውን ትንቢት አቅርቦ ሊያይ ስለቻለ ወደ ታላቅ መፈሳዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ገባ፣ ብዙዎችን ቀሰቀሰ፣ በርሱ ጸሎትና ምልጃ ብዙዎች ወደ እርምጃ ገብተው ወደተዉት፣ ወደረሱትና ወደናቁት የፈራረሰ መሰዊያ ድረስ ተጓዙ፣ ምህረቱን እንዲቀበሉም ሆነ።
በየዘመናት መሃል የሚገለጥ አምላክ እስኪመጣ ድረስ በቃሉ በኩል ይፈለጋል፣ ሲፈለግ በፍጹም እምነትና ፍለጋ ሊሆን ይገባል። የትሁት ፍለም አያቋርጥም፣ የምንኖርበት ጊዜያዊ ከፍታችን አይወስነውም፣ ዝቅታችንም እንዲሁ ሊገድበው አይችልም፤ የምንሻው እኮ ትልቁን አምላክ ነው። ስለዚህ ነገር ዳዊትም ሲናገር፦
‘’በመከራዬ ቀን እግዚአብሔርን ፈለግሁት፤ እጆቼ በሌሊት በፊቱ ናቸው፥ አላረፍሁምም፥ ነፍሴም መጽናናትን አልቻለችም። ይላል።’’ (መዝ.77:2)
በሚመገለጥበት ቀን፣ በሚሰራበትና መልሳችንን በሚመለስ ቀን የድል ቀን ይሆናል፤ የጠበቅነውን እስኪመልስ ግን እንደ ንጉሱ ዳዊት እግዚአብሄርን ልንፈልግ ይገባል። ስለዚህ እግዚአብሄር እንዲመጣ ያለ ቅድመ ሁኔታ በየትኛውምም ሁኔታ ውስጥ መፈለግ፣ ሁሌም በፊቱ መሆን፣ እስኪጎበኝ ነፍስን ያለእረፍት በፍለጋ ውስጥ ማስገባት የግድ አስፈላጊ ነው። እግዚአብሄርን የሚያውቁ እውቀታቸው በእምነታቸው ይታያልና፣ በዚያ ውስጥ ደግሞ ትህትናቸው፣ ዝቅታቸው፣ ለአምላካቸው የሚያሳዩት ፍቅር ጉልህ ነው።
አምላክ ለምን ይፈለጋል? ሲሉ ብዙ ሰዎች ይጠይቃሉ፤ እርሱ እኛን ስለሚያውቅ (ችግራችን፣ ጸሎታችን፣ የልባችን አሳብ በፊቱ የተሰወረ አይደለም ይላሉ)። አዎ ልክ ነው እያንዳንዱን ነገር ያውቃል፤ ሆኖም እኛ እኮ ፈላጊዎችና ተቀባዮች ነን፤ ለማኞች ነን። አምላክ እንዳለን እያሰብን፣ እንደሚሰጠን እያመንን፣ በፊቱ ትሁት እየሆንን፣ ፍቅራችንንና ማክበራችንን በህይወታችን እያሳየን ከርሱ ጋር መቆየት እጅግ አስፈላጊም ነገር ነው። ህያውነቱ እየታሰበን (አምላካችን ሁልጊዜ እንደሚከታተለንና እንደማይረሳን አውቀን እኛም እንደሚታይና እንደሚጎበኝ አማኝ ትክክለኛ አካሄድ እንዲኖረን) በርሱ ፊት መኖር ያስፈልጋል።
‘’ለመዘምራን አለቃ፤ በሙትላቤን፤ የዳዊት መዝሙር። አቤቱ፥ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ተአምራትህንም ሁሉ እነግራለሁ። በአንተ ደስ ይለኛል፥ ሐሤትንም አደርጋለሁ፤ ልዑል ሆይ፥ ለስምህ እዘምራለሁ።ጠላቶቼ ወደ ኋላ በተመለሱ ጊዜ፥ ይሰናከላሉ ከፊትህም ይጠፋሉ። ፍርዴንና በቀሌን አድርገህልኛልና፤ ጽድቅን እየፈረድህ በዙፋንህ ላይ ተቀመጥህ።’’ (መዝ.9:1-4)
የደስታን መንፈስ የሚያፈስ አምላክ በመንፈስ ገስግሰው የሚያገኙትን ይባርካል፦ በደስታ መንፈስ ሞልቶ ያንቀሳቅሳል። ዳዊት አብዛኛውን የእድሜ ዘመን በፈተናና በብርቱ የጠላት ትግል ውስጥ ያለፈ ሰው ነበር፤ በዚያ ጫና ውስጥ እያለ ግን ያን ሁሉ ፈተና ተሸክሞም ሳለ ሲቆዝም አናይም፤ በአምላኩ የበረታው በመከራው ውስጥ ባወጣው የእምነት ቃል፣ ዝማሬ፣ አምልኮና ጥበቃ ውስጥ ስለ ነበር ነው። ዳዊት ከመከራ ብዛት ነፍሴ ፈዘዘች ትፍዘዝ እንጂ ወደ እግዚአብሄር አምልኮዬን አላቆምኩም እርሱም በዚያ ዝቅታዬ ውስጥ ሁሌ ሲጎበኝ ስለነበር ደስታ እሞላ ነበር ይላል (መዝ.77:3 ) እልፍ ባለ ፍለጋ፣ ምስጋናና አምልኮ ምን ሊሆን እንደሚችል ቀጥሎ ካለው የዳዊት መዝሙር ውስጥ እናያለን፦​​​​​​​​
መዝ.77:5-18 ‘’የዱሮውን ዘመን አሰብሁ፤ የዘላለሙን ዓመታት አሰብሁ፤ አጠናጠንሁም​በሌሊት ከልቤ ጋር ተጫወትሁ፥ ነፍሴንም አነቃቃኋት። እግዚአብሔር ለዘላለም ይጥላልን? እንግዲህስ ቸርነቱን አይጨምርምን? ለዘላለምስ ምሕረቱ ለልጅ ልጅ ተቈረጠችን? የተናገረውስ ቃል አልቆአልን?እግዚአብሔርስ ሞገሱን ረሳን? በቍጣውስ ምሕረቱን ዘጋውን?ይህ ድካሜ ነው አልሁ፥ የልዑል ቀኝ እንደ ተለወጠ። የእግዚአብሔርን ሥራ አስታወስሁ፤ የቀደመውን ተአምራትህን አስታወሳለሁና፤በምግባርህም ሁሉ እናገራለሁ፥ በሥራህም እጫወታለሁ።’’