የቤተክርስቲያን ጥሪ[true call; true church]

ቤተክርስቲያን

ሀ.ቤተክርስቲያን የበጉ ሙሽራ እንድትሆን ዝግጁ መሆን አለባት፡፡
በዚህ ዘመን ያለች ቤተክርስቲያን በተረጋገጠ  የመዳን መንገድ  ውስጥ  መኖር ከፈለገች  እውነተኞች ሀዋርያት የሄዱበትን የእምነት መንገድ መከተል እንጂ ሌላ ከንቱ ትምህርት ውስጥ መስጠም አስፈላጊ እንዳልሆነ ማስተዋልና ልብወለድ ትምህርቶችን (መናፍቃዊ ትምህርቶችን) በብርቱ መቁዋቁዋም አለባት፡፡
2ቆሮ.11:2-3 ”በእግዚአብሔር ቅንዓት እቀናላችኋለሁና፥ እንደ  ንጽሕት ድንግል እናንተን  ለክርስቶስ  ላቀርብ  ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ።”
ቤተክርስቲያን በአለም ባሉ በክርስትና ስም በሚጠሩ እምነቶች ዘንድ ያለውን ያልጠራ አምልኮና የመለኮት እውቀት በሚያርም መልኩ ብርሀን ሆና መጉላት ይጠበቅባታል፡፡ከጥንት ጀምሮ ዛሬ ድረስ የአህዛብ እምነቶች ጌታ አስቀድሞ ወደ ገዛ ወገኖቹ (ወደ አይሁድ) የመምጣቱን እውቀትና ቃልኪዳን በመዘንጋት እውነተኛውን የአብረሃም አምላክ ከአይሁድ ውጪ ማድረግና በትምህርታቸው እሱ ከመሰረቱ የአህዛብ አምላክ እንደሆነ ለማሳመን የሚመክሩበትን መንገድ በመቁዋቁዋም የፈጠራ እምነት ህይወት እንደሌለው ልታሳይ ይገባል፡፡፡
ሮሜ.9:4 ውስጥ ቃሉ ሲናገር፡-
”እነርሱ  እስራኤላውያን ናቸውና፥  ልጅነትና ክብር  ኪዳንም የሕግም መሰጠት  የመቅደስም ሥርዓት  የተስፋውም  ቃላት  ለእነርሱ ናቸውና፤ አባቶችም ለእነርሱ ናቸውና፤ ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን።”
ጌታ ወደ ገዛ ወገኖቹ የመጣው አንዱን የሙሴ አምላክ በሚጠሩና አንድ ጌታ ሆኖ እንዲገዛቸው በሚሹ ወገኖቹ መሀል ለማደር ነበር፡፡ይህም አስቀድሞ አይሁድን በመቀጠል አህዛብን ለማዳን የመጣ እንጂ የአህዛብን አምልኮ ሊያበረታታ ፈጽሞ እንዳልሆነ ማስተረዋል ይገባል፡፡እንደዚያ ከሆነ ደግሞ የአህዛብ ቤተክርስቲያን በቃልም ሆነ በስራ ሀዋሪያዊ ልትሆን ተገቢ ነው፡-ያ የጸና የጌታ ምስክር ያለው ነውና፡፡ይህ አባባል ከስም ባለፈ በተግባር የተፈተሸ እንዲሆን በቃሉ ላይ እንደተጻፈው ሊታመኑና ሊጉዋዙ ያስፈልጋል፡፡
ሀዋሪያዊ ተልእኮ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ከሀዋርያት ስራ 2 ጀምሮ የተገለጠና እስከ ምድር ዳርቻ እንዲሁም እስከ አለም ፍጻሜ ድረስ ሳያቁዋርጥ ሊጉዋዝ የተገባ ነው፡፡በበአለ-ሀምሳ ቀን የተወለደችው እውነተኛዋ ቤተክርስቲያን ዛሬም በመንፈስ ቅዱስ በሚሰበክ ወንጌል ልትሰፋና በእርሱዋ የተወለዱ ልጆችን ለመንግስቱ ብቁ እንዲሆኑ ልታሳድግ ሀላፊነት ተሸክማለች፡፡
ለ.ወገኖች በሃዋርያዊ ወግና ልምምድ መኖር ይገባቸዋል፡፡
2 1ቆሮ.11:1-2 ”እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ።ወንድሞች ሆይ፥ በሁሉ ስለምታስቡኝና አሳልፌ እንደ ሰጠኋችሁ ወግን ፈጽማችሁ ስለ ያዛችሁ አመሰግናችኋለሁ።”
ክርስቶስን መምሰል የተለማመዱትን ሀዋርያቶች መንገድ መከተል፣ እምነትና ወጋቸውን አጥብቆ መያዝ ለዚህ ዘመን ቤተክርስቲያን ወደ ሰማያዊ ጥሪ መቅረቢያዋ መንገድ ነው፡፡የአለም ወግ አለማዊ እንደሚያደርግ ሁሉ የሀዋርያት ወግ ሀዋርያዊ ያደርጋልና ቤተክርስቲያን በዚህ ዘመን አጥብቃ በዚህ ሂደት ልትቀጥል ይገባል፡፡የሀዋርያትን እምነትና ወግ ያልያዙ ኢየሱስን እንደሚያምኑ ቢናገሩም እንኩዋን ተግባራዊ ህይወታቸው አለማዊ ሽታ ያለው ነው፣ምክኒያቱም የህይወት ዘይቤአቸው ሊለወጥ ስላልቻለ፡፡ስለዚህ የሀዋርያትን ወግ በሚከተሉ ክርስቲያኖችና አለማዊ/አህዛባዊ ልማድ ይዘው በሚጉዋዙት መካከል ልዩነቱ የሰፋ በመሆኑ በስምምና በአንድነት ሊጉዋዙ አልቻሉም፣ ደግሞም መቼም አይችሉም፡፡
ሀዋርያዊ ተልእኮ ከሀዋርያት እምነትና ወግ ጋር ይያያዛል፡፡ወጉ በተለይ ከወጡበት አይሁዳውያን ማህበረሰብ የተለየ ቢሆንም የአህዛብን መንገድ የተከተለ ግን አይደለም፡፡በሀዋርያት ወግ ውስጥ ጎልቶ ይታይ የነበረውም የአባቶች ልማድና ባህል ሳይሆን አዲስ ሰማያዊ ቤተሰብን ያቀፈ የክርስቶስን ህይወት የሚገልጥ ህብረትና የጽድቅ ልምምድ ነበረ፡፡ ሀዋርያቶች የጌታ ኢየሱስ ደቀመዛሙርት እንደመሆናቸው የተሰጡለት ወንጌል ከጠራቸው ጋር ያስተሳሰራቸው ነበሩ፡፡ በዚህም ዘመን የነርሱን ትምህርት፣ እምነትና ኑሮ ምሳሌ አድርገን ስንይዝ እውነትን እንድንኖር ያግዘናል ማለት ነው፡፡
ቤተክርሰቲያን የበጉ ሙሽራ በመሆንዋ በሀዋርያትና በነብያት የትምህርት መሰረት ላይ የታነጸች ናት፡፡የቤተክርስቲያን ባለቤት ግን ኢየሱስ እንጂ ሃዋርያት አይደሉም፡፡
ኤፌ2:20-22” በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ።”
ማቴ.16:16” ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ፡- አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ።ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፡- የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።”