ቤተክርስቲያን የአዲስ ኪዳን አገልጋዮች ባስተማሩት ወንጌል ላይ መሰረትዋን የጣለች የክርስቶስ አካል ነች፡፡ክርስቶስን አምነው በጥምቀት የለበሱት፣ እርሱን በማወቅና በማደግ እስከ ሙላቱ ድረስ በቃሉና በመንፈሱ ለመታነጽ በአንድነት ተያይዘው የሚኖሩባት ማህበር ናት፡፡ይህች ቤተክርስቲያን በዚህ ዘመን ከሚገኙት ቤተ እምነቶች በዋናነት የምትለየው ሰው ሁሉ ጌታ የሰጠውንና ሀዋርያት እንደተቀበሉት ያስተማሩትን ትምህርት ብቻ በመቀበልና በማመን መንግስተ ሰማይ እንደሚገባ ማመንዋ ነው፡፡
ኢየሱስ በገዛ ደሙ የዋጃት የእግዚአብሄር ቤተክርስቲያን ለኢየሱስ ክርስቶስ የተለዩ ወገኖች ማህበር ሆና ከክርስቶስ ጋር በተሳሰረችበት ስሙ አማካይነት መልካሙን ስራ ለማድረግ የተፈጠረች ናት፡፡ዋና መለያዋም ቅዱሱና አዳኙ ስም – ኢየሱስ መሆኑ ታላቅ ክብር ሆኖአታል፡፡
ኤፌ2:10 “እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን።”
በትውልዳችን መሀል የምትገኝ ማህበር/ቤተክርስቲያን በሐዋርያት ስራ ምእራፍ ሁለት ላይ ከተፈጠረችው ጋር አንድ ስለመሆንዋ በሚከተለው መለያ አውነተኛነትዋ ሊረጋገጥ ይችላል፡፡ ዋና ዋናዎቹ ምክኒያቶች ፡-
ሀ.የትምህርቱን መሰረት በተመለከተ፡-አስራ-ሁለቱ የክርስቶስ ሀዋርያት ብቻ እውነተኞች በመሆናቸው የእነርሱን ትምህርት መሰረት ማድረግ ተገቢ ነው ብላ ልታምን ይገባል፡፡
ሀዋርያቶች ስለምን ይታመናሉ?የእነርሱን መመረጥና መሾም የሚያጸድቁ ብዙ መረጃዎች በቃሉ ላይ ስላሉዋቸው ይታመናሉ፡፡ሀዋርያቶች ስለራሳቸው እግዚአብሄርን ምስክር ጠርተው እውነተኛነታቸውን አረጋግጠዋል፡-
1ዮሐ.4:6 “እኛ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም። የእውነትን መንፈስና የስሕተትን መንፈስ በዚህ እናውቃለን።”አሉ፡፡
የኢየሱስ ሀዋርያት በእውነት መንፈስ የተመሩ ስለነበሩ ትምህርታቸው እውነተኛውን የመዳን ወንጌል የሚገልጥ ነበር፡፡ሀዋርያት ብቻ በእግዚአብሄር ተቀባይነት ያላቸው ስለመሆናቸው ጌታ ራሱ መንፈስ ቅዱስን በማውረድ አረጋግጦአል፡፡
ከሀዋርያት ህልፈት በሁዋላ እጅግ ብዙ አስተማሪዎች ከልባቸው ያፈለቁትን ትምህርት ለክርስቲያኖች አስተዋውቀዋል፡፡ይሁን እንጂ አንዳቸውም ደፍረው “እግዚአብሄርን የሚያውቅ እኛን ይሰማል” በሚል ጽኑ ቃል ስለራሳቸው መመስከር አይችሉም፡፡መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ሊመሰክርላቸው አይችልምና፡፡ስለዚህ በዚህም ዘመን ያለች እውነተኛ ቤተክርስቲያን የሀዋርያትን ዱካ ልትከተል፣ በሄዱበት መንገድ ልትሄድ፣ በጽናታቸው ልትጸና፣ወጋቸውን ልትቀበል ያስፈልጋል፡፡ምክኒያቱም በዚያ ልምምድ ውስጥ አብሮአቸው የተጉዋዘ ጌታ እንዲህ በምትለማመድ ቤተክርስቲያን ውስጥ ሊገኝ ፈቃዱ ነውና፡፡
ማቴ.10:40 “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።”
ለ.የወንጌልን ምስጠር በተመለከተ፡-ለእነዚህ ሃዋርያቶች ብቻ የመንግስተ ሰማያት መክፈቻ እንደተሰጠ ማወቅ አለባት፡፡
ጌታ ኢየሱስ የመረጣቸውን ደቀመዛሙርት የመንግስቱን እውቀት ከማንም ይልቅ ገልጦላቸዋል፡፡ሀዋርያው ጳውሎስ ይህን መስክሮአል፡-
ኤፌ3:3-6 “አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍሁ፥ ይህን ምሥጢር በመግለጥ አስታወቀኝ፤ይህንም ስታነቡ የክርስቶስን ምሥጢር እንዴት እንደማስተውል ልትመለከቱ ትችላላችሁ፤ይህም፥ አሕዛብ አብረው እንዲወርሱ፥ በአንድ አካልም አብረው እንዲሆኑ፥ በወንጌልም መስበክ በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነ የተስፋ ቃል አብረው እንዲካፈሉ፥ ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለነቢያት በመንፈስ አሁን እንደ ተገለጠ በሌሎቹ ትውልዶች ዘንድ ለሰው ልጆች አልታወቀም።”
በእነርሱ የወንጌል እውቀት ላይ የሰው ልጅ መሰረቱን እንዲጥል መንፈስ ቅዱስም አብሮአቸው እየሰራ ጉዳዩ እውነተኛ መሆኑን አረጋግጦአል፡፡
ማቴ.16:18-19 “ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፡- የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።”
ከዚህ ጥቅስ ውስጥ ያለ ትልቅ ምስጢር እንደሚያሳየው የመንግስተ ሰማያት ቁልፍ የሃዋርያቶች ትምህርት ውስጥ እንዳለና ከእነርሱ ትምህርት ውጪ የዘላለም ሞት እንጂ ህይወት እንደማይገኝም ምስክር ነው፡፡
ሐዋ.15:7 “ከብዙ ክርክርም በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው ወንድሞች ሆይ፥ አሕዛብ ከአፌ የወንጌልን ቃል ሰምተው ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር በመጀመሪያው ዘመን ከእናንተ እኔን እንደ መረጠኝ እናንተ ታውቃላችሁ።”