ረ. የሀዋርያቱን የማይለወጥ ወንጌል በተመለከተ፡-ከእነርሱ ሌላ ወንጌልን አሻሽሎ የሚያቀርብ ቢኖር ሰማይ የሚቀበለው ሳይሆን እርግማን እንደሚያስረው ስለምታስተውል ነው፡፡
ሀዋርያቶች በመልእክቶቻቸው ውስጥ አጥብቀው ካነሱት ርእስ መሀል የሀሰት ትምህርት አንዱ ነበር፡፡ከሰውና ከአጋንንት የፈለቀ የሀሰት ትምህርት ከጌታ የተቀበሉትን ትምህርት እንደሚበርዝ አስቀድመው በመንፈስ ስላስተዋሉ አጥብቀው ተቃውመውታል፡፡
ገላ.1:7-8 “እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ።ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።”
አማኞች ከእነርሱ ውጪ የሚመጡ ትምህርቶችን ፈጽመው እንዳይሰሙ፣እንዳይቀበሉና ያን መሰረት ያደረገ ክርክር ውስጥ እንዳይገቡ የሚያስገነዝብ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶአቸዋል፡፡አሁን በእኛ ትውልድ እንደምናየው በሀዋርያት ዘመንም ሀዋርያትን የሚቃወም ትምህርት ከአይሁድም ከአህዛብም ይመጣ ነበር፡፡ስለዚህ መፍትሄው ያኔም ሆነ አሁን በሀዋርያት ትምህርት ላይ መጣበቅ እንደሆነ ምክራቸው አስረጂ ነው፡፡
ሰ.የመዳንን ስረ-መሰረት በተመለከተ፡-ቤተክርስቲያን መዳን ከአይሁድ ብቻ መሆኑ ማስተዋል ይገባታል፡፡
በአለም ላይ ብዙ ትምህርቶች በክርስትና ስም ይወጣሉ፡፡ነገር ግን ሰማይ የሚያውቀው ከጌታ የተሰጠው በሀዋርያት የተሰበከው ወንጌል ብቻ ነው፡፡ይህ ወንጌል በእግዚአብሄር የዘላለም እቅድ ውስጥ የነበረ እንጂ በሀዋርያት የተፈጠረ አይደለም፡፡ሀዋርያው ጳውሎስ ይህንን መስክሮአል፡-
ገላ.1:11-12 ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም።
ሮሜ.15:18-19 “አሕዛብ እንዲታዘዙ ክርስቶስ በቃልና በሥራ፥ በምልክትና በድንቅ ነገር ኃይል፥ በመንፈስ ቅዱስም ኃይል በእኔ አድርጎ ከሠራው በቀር ምንም ልናገር አልደፍርም፤ ስለዚህ ከኢየሩሳሌም ጀምሬ እስከ እልዋሪቆን ድረስ እየዞርሁ የክርስቶስን ወንጌል ፈጽሜ፤ ሰብኬአለሁ።”
ወንጌሉ ምስኪን በሚመስሉ ተራ አይሁዳውያን ይሰበክ እንጂ የእግዚአብሄር ክብር ያለበት ወንጌል ነበር፡፡ይህ ወንጌል በአህዛብ እጅ እንዲጻፍ ኢየሱስ አልፈቀደም፡፡ምክኒያቱም የአህዛብ አምላክ በዘዳግም 6፣4 የታወጀው የአብረሃም፣የይስሀቅና የያእቆብ አምላክ ሳይሆን አጋንንት በመሆኑ/በመሆናቸው ወንጌልን መግለጥ፣መጻፍም ሆነ በእጃቸው አደራ እንዲሰጥ አልተፈቀደም፡፡
ገላ.2:7 “…ተመልሰው ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠኝ አዩ፤ለተገረዙት ሐዋርያ እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት፥ ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና…”
አህዛብ ግን ያንን ሊያስተውሉ ባለመቻላቸው በተለያዩ ዘመን እየተነሱ የየራሳቸውን ወንጌል በየጉባኤያቸው ጽፈው/ደርሰው በአለም ላይ በትነዋል፡፡እነዚህ ዝብርቅርቅና የአጋንንት ተጽእኖ ያረፈባቸው ትምህርቶች በአለም ላይ ያሉትን ኢየሱስን የሚሹ ቅን ሰዎችን አደናግረው፣አለያይተውና ከፋፍለው ወደ ሞት የሚነዱበት መንገድ ነው፡፡
2ቆሮ.11:3-4 “ነገር ግን እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፥ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ።የሚመጣውም ያልሰበክነውን ሌላ ኢየሱስ ቢሰብክ፥ ወይም ያላገኛችሁትን ልዩ መንፈስ ወይም ያልተቀበላችሁትን ልዩ ወንጌል ብታገኙ፥ በመልካም ትታገሡታላችሁ።”
ሸ.ከሀዋርያት ጋር የተካፈልነውን እምነት በተመለከተ፡- ለነርሱ የተገለጠ ሀይማኖት ፍጹም ሆኖ የተሰጠ በመሆኑ በሌሎች አዲስ በተነሱ አስተማሪዎች ሊበረዝ እንደማይችል ቤተክርስቲያን እንድታስተውል ያስፈልጋል፡፡
ይሁ.1:3-4 “ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ።”
ማር.16‹8 “….ከዚህም በኋላ ኢየሱስ ራሱ ለዘላለም ድኅነት የሆነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል ከፀሐይ መውጫ እስከ መጥለቂያው ድረስ በእጃቸው ላከው….”
በአለም ላይ ያሉ ሀይማኖቶች ኢየሱስ ላይ ያላቸው እምነትና አመለካከት የተዘበራረቀ ነው፡፡ይህ የጠራ አመለካከት ማጣት የሁዋላ የሁዋላ ጌታ እንዲደበዝዝባቸውና ሰይጣን የብርሀን መልአክ ሆኖ በህይወታቸው እንዲሰራ መንገድ ከፍቶአል፡፡ሰው ማስተዋሉ ሲወሰድና በአጋንንት ትምህርት ሲዋጥ ኢየሱስን ብኤልዘቡል ለማለት አያቅማማም፣ስሙን ከማንቁዋሸሽ አይመለስም፡፡