የእግዚአብሄር ቃል በዮሃንስ ወንጌል መጀመሪያ ላይ ለሰው ልጆች በሚገልጠው የምስራች ላይ እንዲህ ብሎአል፦
‘’… ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም።’’ (ዮሐ.1:9-11)
ከአዳም የተገኘ ትውልድ ሁሉ በአንድ ስም ሰው ተብሎ ከርሱም ለእያንዳንዱ ትውልድ እውነትን ያሳውቅ ዘንድ እግዚአብሄር በተለያየ መንገድ አለምን ይጎበኝ እንደነበር ያሳያል። እግዚአብሄር በንግግሩ ውስጥ ያለና የሚኖር አምላክ መሆኑን በሚገልጥ መንገድ ይናገራል፤ ወደ አለምም ሲመላለስ ሳለ አለም ማን መሆኑን ባይረዳውም አስቀድሞ በነበሩት ዘመናት እቅዱን ይዞ ወደ አለም ይመላለስ ነበር። እግዚአብሄር በምን አላማ ይመጣ ነበር? ለሰው ሁሉ ሊያበራና ሃጥያት ላይ የወደቀው አዳምና ዘሩ ጨርሶ እንዳይጠፋ የጽድቅ መንገድ ሊያሳየው ይመጣ እንደነበር ያመለክታል፤ ሰው ከእግዚአብሄር መገኛ አካባቢ ወጥቶና በሰይጣን አሰራር ላይ ወድቆ ሳለም በተለያየ መልክ የሰውን ልጅ ያገኝ ዘንድ ይመጣ ነበር፡- በተስፋ ቃል በኩል፣ በራእይና በህልም ውስጥ፣ በመልአክ አፍ ቃሉን አኑሮ፣ በቀጥታ ድምጹን እያሰማም በተለያዩ ዘመናትና ትውልድ መሃል ምስክርነቱን ገልጦአል። ከአዳም ልጆች መሃል በተለይ ላመኑትና ለተከተሉት ወገኖች ይበልጥ አምላክነቱን እያሳወቀ ከላይ ባየናቸው መንገዶች ሲያነጋግራቸው አቅርቦም ወገኔ ሲላቸው ይታያል። እግዚአብሄር አመጣጡን ጠበቅ አድርጎ ሲመጣም እይታውን ወገኔ ወዳላቸው ህዝቦች አድርጎአል፤ ያ ብዙ ምክኒያት ቢኖረውም በዋናነት ግን እርሱ አስቀድሞ በቅርብ ላልተገለጠለት ወገን አልመጣምና ነው።አዎ አስቀድሞ ላልተናገረውና ላልተገለጠለት በእርግጥ አልመጣም (በተለይ አህዛብ የሆንን ህዝቦች ይህን እውነት ከልብ መቀበል ይኖርብናል)፤ አላማ ብሎ የመጣው ተስፋውን ወዳኖረው ህዝብ ስለነበር የቀረው አለም ወደ ምድር በስጋ በመጣ ጊዜ ፈጽሞ ሊጠባበቀውና ሊፈልገው አልቻለም ። ይህ ልዩ ህዝብ፣ ምርጥ ህዝብ፣ በእግዚአብሄር ሲጎበኝ የነበረ በእርሱም የታሰበ ህዝብም ቢሆን እንደተሰጠው ስፍራ ግብረ መልሱ በጎ አልሆነም፤ ዛሬ አለም ብዙ ነገር ብትልም ቃሉ ግን የሚለው፦
ወደ ገዛ ወገኖቹ መጣ ሲል በማወጅ ነው፣ በእርግጥ የመጣው አስቀድሞ፦
-ወደ ጠበቁት አባቶች ልጆች ነው
-አስቀድመው ወደ ፈለጉት ሰዎች ምድር ነው
-ተስፋ ወዳረጉት በዘመኑ በነበሩ አማኞች ነው
-በአጠቃላይ ግን ከርሱ ጋር ወደተሳሰሩት ህዝቦች ነው
ሆኖም የገዛ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም፣ በዚህም፦
-ለረጅም ዘመናት አቅንተው የጠበቁት በደረሰ ጊዜ ተለውጠው እንዳልተቀበሉት ቸል እንዳሉት ያሳያል
-ተስፋ ሰጥቻቸዋለሁ ወዳለላቸው ህዝቦች መሃል በተገኘ ጊዜ እንግዳ ሆነውበታል
-በቃሉ እንደሚያውቁት ያረጋገጠላቸው፣ ተስፋውን የጠበቁ እንደሆኑ የመሰከረላቸው ህዝቦች ግን እንደርሱ ታማኝነታቸውን አላሳዩም
-የራሱ ህዝቦች ወይም የመረጣቸው ህዝቦች ወይም እንደቅርብ ዘመድ የቆጠራቸው ወገኖች በመምጣቱ አሳፍረውታል
-በእግዚአብሄር ክብር ላይ ንቀት አሳይተዋል
እስራኤላውያን የአብረሃም ልጆችና በእግዚአብሄር ዘንድ ስለአባታቸው የወገንነት መብት አግኝተው ሳለ በምግባራቸው ያን ሊያንጸባርቁ ስላልቻሉ እግዚአብሄር ሲተዋቸው እናያለን፤ ይህን አጋጣሚ ሃዋርያው ጳውሎስ በቁጭት ይገልጠዋል፤ ተሰጥቶአቸው ስለነበረ የተለየ ስጦታና ክብር ይዘረዝራል። በየትኛውም የሰው ልጅ ዘንድ ሊገኝ ያልቻለ ታላቅ ስጦታ ከእጃቸው ሲያመልጥ እጅግ የሚያሳዝን ጉዳት ሆኖ አለም የተመልከተው ነው።
እግዚአብሄር በአመጣጥ ደረጃ አስቀድሞም በአለም ነበረ፣ አለሙ የራሱ ንብረት ስለሆነ የፈጠረውን አለም ሊጎበኝ ይመጣ ነበር፣ የርሱ መምጣትና መመላለስ አዲስ ክስተት አይደለም፤ አዲሱ ክስተት የሆነው መገለጡ እንዲሁም የአመጣጡ መንገድ ነው፤ እንዴት?
በብሉይ ኪዳን በብዙ አይነትና በብዙ ጎዳና፣ ነገር ግን በአዲስ ኪዳን በልጁ በኩል ሆኖአል፦
‘’ ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን’’ (ዕብ.1:1-2)
በብሉይ ኪዳን ወደገዛ ወገኖቹ ለጉብኝት ሲመጣ መምጫው አይነቱም ጎዳናውም የበዛ እንደነበረ ቃሉ ምስክር ነው ፤ ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ ግን ሁኔታው የተለየ እንደሆነ እንመለከታለን፤ በብሉይ ኪዳን ከበዛው አይነትና ጎዳና ይልቅ በአንድ መንገድ ሊመጣ እንደወሰነ ከቃሉ እንማራለን፤ እነዚያ የብሉይ ኪዳን መንገዶች አይነታቸው ብዙ ነው፤ የአዲስ ኪዳኑ ግን አንድ ብቻ ነው፤ የበዙት የብሉይ ኪዳን መገለጫዎች ለአዲስ ኪዳኑ አንዱ መገለጫ እንደጊዜያዊ መንገድ የተዘጋጁ ስለነበሩ አንዱ መንገድ (አንድያ ልጁ) ሲገለጥ የብሉይ ኪዳን አማራጮች ተዘግተዋል፤ እርሱ ራሱ ይህን ሲያረጋግጥ እንዲህ የሚል ድምጽ አሰምቶአል (በተለይ ለገዛ ወገኖቹ)!
‘’ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን፡- ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ። እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው፡- በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር። ’’ (ማቴ.17:1-6)
በዚህ የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍል የምናገኛቸው ነብያት ከጌታ ኢየሱስ በፊት እግዚአብሄርን ያገለገሉ ሰዎች ነበሩ፤ እግዚአብሄር በነዚህ ሰዎች አንደበት ተጠቅሞ ለህዝቡ ተናግሮአል፤ በአዲስ ኪዳን ግን እነዚህን ሰዎች ለአይሁድ ገልጦ አሁን ልትሰሙ የሚገባው ብቸኛው መንገድ ክርስቶስ ነው ይላቸው ነበር፤ እናንተ ሰዎች ስለሆናችሁ በየዘመናችሁ ተጠቅሜባችኋለሁ ይህ ልጄ ግን እንደእናነተ አይደለም ዘላለማዊ ነው፣ፍጹም ነው፣ እኔ ደግሞ በእርሱ በመገለጥ እናገራለሁና እርሱን ስሙት ሲል ምስክርነቱን ሰጠ፤ ሃዋርያቶችም ድምጹን ሰምተው በፊታቸው ወደቁ።
አንድ እውነት ልንጨብጥ ያስፈጋል፦ እርሱም ሃዋርያት እግዚአብሄር የገለጣቸውን የብሉይ ኪዳን ባሪያዎቹን በዚያ የመገለጫ ስፍራ እንዳሉ እንዲቀሩ እንዲያውም በዙሪያቸው አኑረው ከእያንዳንዱ ድምጽ እየሰሙ ሊገለገሉ ፈልገው ቢሆን እንኳን የእግዚአብሄር ፈቃድ ግን በአንድያ ልጁ በኩል ለዘላለም በመንገስ ለወገኖቹ ድምጹን ማሰማት ነው። በሌላ ስፍራ ጌታ ለነዚህ ሃዋርያቶቹ ምን አለ?
‘’ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል አለው። ፊልጶስ፦ ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው። ኢየሱስም አለው፦ አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ፦ አብን አሳየን ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል። እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ባይሆንስ ስለ ራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ።’’ (ዮሐ.14:6-10)። በዚህ ዘለግ ባለ የቃሉ ክፍል ጌታ የሚያስተምረን ብዙ ነገር አለ፤ ግን በጥቅሉ ጌታ ማን ነው? ስንል ማንነቱን እኔ ብሎ መንገድ፣ እውነት ህይወት ነኝ ይላል፤ ይሄ ምን ያስተምረናል፣ ያስታውሰናልስ? በአለም የነበረውና ወደ አለም ይመጣ የነበረውን እውነተኛ የህይወት ብርሃን ማን መሆኑን አያስታውሰንም? በብሉይ ኪዳን ወደገዛ ወገኖቹ በተለያየ አይነትና ጎዳና ቢመጣም አሁን አንድ ጎዳና/መንገድ መገለጡን እርሱም እራሱ ኢየሱስ መሆኑን፤ በሌላ በኩል እውነተኛው ብርሃን፣ ለሰውም ህይወት የሆነው በብሉይ ኪዳን በተለያየ አይነትና ጎዳና ቢመጣም አሁን መንገድ አድርጎ ስጋውን እንደተገለጠና እርሱም ሲመሰክር እኔ እውነት ህይወትም ነኝ ማለቱን ከገዛ ራሱ አንደበት ሰምተናል፤ ይህን እውነት ሲያፍታታውም እኔን ያየ (አካሌን፣ ስጋዬን) አብን (መንፈስ የሆነውን አምላክ፣ ህይወት የሆነውን አምላክ፣ እውነትም የሆነውን አምላክ) አይቶአል፣ ምክኒያቱም እግዚአብሄር አብ በስጋ ተገልጦአልና ማለቱ ነው። ቀጥሎም በተለይየ አይነትና ጎዳና የተጠቀመው አንዱ አምላክ አብ አሁን አንድ መንገድ (ስጋውን ወይም ልጁን) ተጠቅሞና ውስጡ እየኖረ እንደሚናገር መግለጡ ነው፦
‘’እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል።’’ ይላልና (ዮሐ.14:10)።
የተናገረውን አስተውለን ለማየት ያህል፦
እሱ እንዲህ አለ፦ እኔ የእግዚአብሄር አንድያ ልጁ በእኔ በሚኖረው በአብ( በአባቴ) ምክኒያት ህያው ሆኜ እንዳለሁ አብም(አባቴም) በእኔ ውስጥ አድሮ እየተናገረ፣እያዳነ፣እየታረቀህም ጭምር እንዳለ አታምንምን?
ስለዚህ፦ ‘’እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል። እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ባይሆንስ ስለ ራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ’’ አለ።
ጌታ ኢየሱስ ይህን ሲል በራሱ ሙሉ ማንነት ስለሌለው ነው ወይ ብለን እንድንጠይቅ ያስገድዳል? ራሱ ከነፍሱ ከሚወጣ ፈቃድ አሳቡን መናገርስ አይችልምን? ለምን እኔ የምነግራችሁ ከራሴ (በውስጤ ያለውን የራሴን ሳይሆን የእግዚአብሄርን ድምጽ በአንደበቴ በኩል ሰማችሁ፤ ስለዚህ የርሱ ንግግር ወደ እናንተ እየመጣ ነው የሚል ንግግር ለምን ተናገረ? በሰማችሁት ድምጽ የዳናችሁት፣ የተከናወነላችሁም ስራውን የርሱ ድምጽ ስለሰራው ነውና የአብን መኖሪያ አስተውሉ የሚል እውነትን ያሳያል።
በዚህ አሰራር ውስጥ ወደ ገዛ ወገኖቹ የመጣው አብ አንድ ህያው መኖሪያ እንዳዘጋጀ እናያለን፤ የምወደው ልጄን እርሱን ስሙት ማለቱ ላይ ጌታ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፣ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ… ሲል በግልጥ እግዚአብሄር አንድያ ልጄን እርሱን ስሙት የማለቱን ምስጢር ይገልጥልናል። ጌታ ኢየሱስ ጨምሮ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ አለ፤ የገዛ ወገኖቹ ሊቀበሉት ያልቻሉት ለምን እንደሆነ እዚህ ላይ በግልጥ ይታያል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በአካል ሲታይ ሰውን ይመስላል፣እንዲያውም ያደገበትን የአይሁድ ማህበረሰብ ይመስላል(በተለይ በባህልና በስራ ሁሉ)፤ በአካል ብቻ ሳይሆን በስነልቦና፣ በእምነትና በኑሮ ዘይቤ ከአይሁድ መለየት እስከሚያቅት ድረስ ከነርሱ ጋር ይመሳሰላል። ነገር ግን እርሱ ይህን ሁሉ ይምሰል እንጂ ሰውን /አባታችን አዳምን ጨርሶ አይደለም፤ እርሱ የእግዚአብሄር ልጅ ብቻ ነው(እግዚአብሄር የወለደው፣ ስለዚህ ከእግዚአብሄር ውስጥ የወጣ ነው)። ይህ ምስጢር ለእስራኤላውያን ያለመገለጡ እርሱን እንዳይቀበሉት አድርጎአቸዋል፤ ወደ ገዛ ወገኖቹ የመጣውን በስጋ የተገለጠውን አምላክ ትተዋል፣ ሲጠጋቸው ተቃውመዋል፣ ሲያስተምራቸው ክደዋል። በአንድ አጋጣሚ ሲናገሩና ሲቃወሙት ይህን የልባቸውን የተቃውሞ ምስጢር ገልጠው አሳይተዋል፦
‘’አይሁድም እርሱን ከበው፦ እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሪ ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ገልጠህ ንገረን አሉት። ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ ሲል፦ ነገርኋችሁ አታምኑምም እኔ በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ይህ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ እናንተ ግን እንደ ነገርኋችሁ ከበጎቼ ስላልሆናችሁ አታምኑም። በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። እኔና አብ አንድ ነን። አይሁድ ሊወግሩት ደግመው ድንጋይ አነሡ። ኢየሱስ፦ ከአባቴ ብዙ መልካም ሥራ አሳየኋችሁ፤ ከእነርሱ ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ? ብሎ መለሰላቸው። አይሁድም፦ ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ፤ አንተም ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ ነው እንጂ ብለው መለሱለት።’’ (ዮሐ.10:24-33)
ወደ ገዛ ወገኖቹ መጣ የሚለውን ቃል ይዘን እንዴት መጣ የሚለውን እየመረመርን ስንቀጥል በዚህ ቃል መሰረት የምናየው ብርሃን የሚያረጋግጠው እውነት አለ፦
ክርስቶስ እንደሆንህ ገልጠህ ንገረን አሉት፦ በእስራኤል ዘንድ የነበረ ተስፋ በአንድ ታላቅ የጥርጥር መንፈስ ታንቆ ነበርና ህዝቡ በሚያየውና በሚሰማው መሃል ባለ ልዩነት ፍጹም እንደተምታታ ይታያል፤ የተስፋው ቃል በህግ፣ በመዝሙራትና በነብያት እንደተነገረው ኢየሱስን ክርስቶስ አድርጎ ቢያስረግጥላቸውም በህዝቡ መሃል መሰናክል ሆነው ይመላለሱ የነበሩ የተለያዩ የሃይማኖት ክፍሎች የህዝቡን ልብ ጥርጥር ውስጥ አስገብተውት ነበር። እነዚህ ሰዱቃውያን፣ ጸሃፍትና ፈሪሳውያን በተምታታ ትምህርታቸው የአይሁድን ህዝብ እንዳያምን በማድረጋቸው ወደ ገዛ ወገኖቹ የመጣውን አምላክ ወገኖቹ እንዳይቀበሉ እንቅፋት አኑረዋል፤ በዚህ ምክኒያት ጌታን እስከሞት አሳድደውታል። ስለ ማናቸው ሥራ ትወግሩኛላችሁ? ብሎ መለሰላቸው።አይሁድም፦ ስለ መልካም ሥራ አንወግርህም፤ ስለ ስድብ (ወይም ጸያፍ ስለሆነ አነጋገርህ፣ አሳብና ድፍረትህ)፤ አንተም ሰው ስትሆን (ከእኛ እንደአንዱ ሆነህ ሳለ፣እናትና አባትህን እያወቅን) ራስህን አምላክ ስለ ማድረግህ (ያለና የሚኖር እኔ ነኝ ያለውን አንድ አምላክ እኔ እርሱ ነኝ በማለትህ) ነው እንጂ ብለው መለሱለት።
ጌታ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ/የእግዚአብሄር ማደሪያ መቅደስ ሊሆን የተቀባ መሆኑን ማመን እንደስድብ ቆጥረዋል፤ እኔና አብ አንድ ነን ያለውም ቃል እጅግ ከንክኖአቸዋል፤ የእግዚአብሄር ልጅ ነኝ ማለቱም አስቆጥቶአቸዋል። ይሄ ሁሉ የሆነው ግን በስህተት ትምህርት ምክኒያት ነበር፤ ቃሉን ባለመስማት ምክኒያት፤ የነቢያትን ድምጽ ባለማመንም ምክኒያት የሆነ ነበረ፤ ንጉስ ዳዊት እንዲህ አለ፦
መዝ.2:6-9 ‘’እኔ ግን ንጉሤን ሾምሁ በተቀደሰው ተራራዬ በጽዮን ላይ። ትእዛዙን እናገራለሁ፤ እግዚአብሔር አለኝ፦ አንተ ልጄ ነህ፥ እኔ ዛሬ ወለድሁህ።ለምነኝ፥ አሕዛብን ለርስትህ የምድርንም ዳርቻ ለግዛትህ እሰጥሃለሁ። በብረት በትር ትጠብቃቸዋለህ፥ እንደ ሸክላ ሠሪ ዕቃዎች ትቀጠቅጣቸዋለህ።’’
የእስራኤል ንጉስ ከርሱ ከፍ ያለ ሰማያዊ ንጉስ በላዩ እንዴት ሊሾም እንደወሰነ ስንመለከት ማንነቱን ማስተዋል እንደቻለም አብረን እናያለን፤ ያላስተዋሉ የዚህ ንጉስ ዘመዶች ግን የሚነግስባቸውን ተቃውመዋል፤ ዳዊት በመንፈስ ተረድቶ አመነ፣ የርሱ ዘሮች ግን አይተው ሊያምኑ ተስኖአቸው ነበር። እግዚአብሄርን ማወቅ የሚባል ትልቅ ስጦታ ምንኛ አስፈላጊ ነው? ዳዊት እግዚአብሄር ልጅ እንደሚወልድ ስላመለከተው በእግዚአብሄር መንግስት ላይ የሚነግስ እርሱ እንደሆነ አስተውሎአል፤ የመንግስቱን ርስትም በመንፈስ ተረድቶአል፤ የንጉሱን የአገዛዝ ጉልበት እንዲሁ በዚያ ውስጥ አስተውሎአል። እያዩ አለማመን ታላቅ ቁጣ ነው፤ እየሰሙ ያለመቀበል፣ የታዘዙትን እምቢ ማለት፣ እንዲሁም ፍቅርን መናቅ ይህ ሁሉ ለእስራኤላውያን መጣልን ያተረፈ አጉል የልብ ድንዳኔ ነው፤ጌታ ኢየሱስ በወሳኝ ምእራፍ ላይ ያስቀመጠላቸውን ማስጠንቀቂያ ማየት በቂ ነው፦
ዮሐ.8:21-27 ‘’ኢየሱስም ደግሞ፦ እኔ እሄዳለሁ ትፈልጉኛላችሁም በኃጢአታችሁም ትሞታላችሁ እኔ ወደምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም አላቸው። አይሁድም፦ እኔ ወደ ምሄድበት እናንተ ልትመጡ አትችሉም ማለቱ ራሱን ይገድላልን? እንጃ አሉ። እናንተ ከታች ናችሁ፥ እኔ ከላይ ነኝ፤ እናንተ ከዚህ ዓለም ናችሁ፥ እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም። እንግዲህ፦ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ አልኋችሁ፤ እኔ እንደሆንሁ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁና አላቸው። እንግዲህ፦ አንተ ማን ነህ? አሉት። ኢየሱስም፦ ከመጀመሪያ ለእናንተ የተናገርሁት ነኝ። ስለ እናንተ የምናገረው የምፈርደውም ብዙ ነገር አለኝ፤ ዳሩ ግን የላከኝ እውነተኛ ነው እኔም ከእርሱ የሰማሁትን ይህን ለዓለም እናገራለሁ አላቸው።ስለ አብ እንደ ነገራቸው አላስተዋሉም።’’
አይሁድ የጌታ ንግግር ፈጽሞ ሊገባቸው ለምን እንዳልቻለ የተረዱት አይመስልም። ምክኒያቱም ወደ ወገኖቹ ወደነርሱ ወደ ራሳቸው ሲመጣ አመጣጡን ስላልተቀበሉ፣ ሹመቱን/መቀባቱን ስላልተቀበሉ፣ ማንነቱን ስላልተቀበሉ የሚነግራቸውን ሁሉ በጠላትነት አቅጣጫ ይመነዝሩት ነበር፣ ይህም የነርሱ ታላቅ ውድቀት ነው።
