ፊትህን አሳየን{3..}

የመጨረሻ ዘመን

ከፊቴ ያለ ጠላት
ከፊት የሚወጣ ጠላት እስካልተቐቐምኩት ድረስ ከእርምጃዬ የሚፈጥን፣ ከጅማሬዬ ቀድሞ ያሻውን የሚፈጽም፣ ከጉዞዬ ፊትም ወጥቶ መሰናክል የሚሆን ነው፣ በእቅዴና በስራዬ እንዳይቀድመኝና እንዳያሰናክለኝ ምኞቴ ቢሆንም እኔ ያን ማሳካት እንደምችል በራሴ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡
የሚያደባ ጠላት መንገዴ ላይ የሚያተኩረው ከእውነት ሊያስተኝ እግሬንም ሊያሰናክለው ካልሆነ ለሌላ ለምንም አይሆንም፡፡ በዚያ ተልእኮው ስንቴ ወጥመድ አጠመደብኝ? ስንቴ ማሰናከያ ድንጋይ አኖረብኝ? ስንቴስ ጉድጉዋድ ቆፈረብኝ? በስውርና በማመሳሰል የሰራቸውን ደባዎች መቁጠር ባልችልም በቃሉ ላይ የማያቸው የየእለት ክፋቶች በአምላኬ እርዳታ አልፌአቸው ሆኖ እንጂ እንደ እቅዱ ቢሆን ኖሮ የክፋቱ መዘዝ የት በጣለኝ ነበር፡፡
መዝ.91:3-8 ”እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና። በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፤ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል። ከሌሊት ግርማ፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፥ በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ነገር፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም። በአጠገብህ ሺህ በቀኝህም አሥር ሺህ ይወድቃሉ፤ ወደ አንተ ግን አይቀርብም። በዓይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፥ የኃጥኣንንም ብድራት ታያለህ።”
ለዚህ ምህረቱ የእግዚአብሄርን በጎነት በጥብቅ ማሰላሰል ያስፈልጋል፡- የማናየው ቢሆንም በእምነት የሰራ የርሱ ሀይል ነጻነትን ሲሰጠንና ከከበበን ጫና ሲያላቅቀን ተመልክተናል፣ ምስጋናውም በውስጣችን እየተፍለቀለቀ ደስታን የሞላን በውስጣችን ያኖረው መንፈስ ህያው መሆኑን አስተውለናል፡፡ ነገሩ እርግጥ ነው፣ የሚሰራ የእግዚአብሄር አሰራር ሁሌም ገዢ ሆኖ ስለሚቆጣጠረው የክፉው ስራ ሳይወጋን አምልጠናል፣ በወጥመዱም ተቆራርጠን ከማለቅ ተርፈናል፡፡
ከዚህ መለስ ትኩረትን የሚሻ ነገር ደግሞ አለ፡- የጠላት አሰራር ሰፊና ጥልቅ መሆኑን አይተናል፤ ግን በዚያው ልክ የራሳችንን ድክመት በርሱ ላይ የምናላክክበት አጋጣሚ ለምን በዛ? ሰበባችን ከእኛ ዞር ካላለ ራሳችንን መግለጥ እንደማንችል ማወቅ ይገባል፡፡ በርሱ ተንኮል ብቻ ሳይሆን በራሳችን ስንፍና ምክኒያት ዳር የምንወጣንበት አካሄድ በግልጽ ካልተተቸ ከተሰወረ ወጥመድ ደጋግመን መውደቃችን አይቀርምና ይህ ነገር ጉልህ ትኩረት ይቸረው!
መዝ.124:6-8 ”ለጥርሳቸው ንክሻ ያላደረገን እግዚአብሔር ይባረክ። ነፍሳችን እንደ ወፍ ከአዳኞች ወጥመድ አመለጠች። ወጥመድ ተሰበረ እኛም አመለጥን። ረድኤታችን ሰማይንና ምድርን በሠራ በእግዚአብሔር ስም ነው።”
የጽድቅን መንገድ ለቅቀን ጭልጥ ባልንባቸው ዘመናት ከፊት ፊታችን ሲሽቀዳደሙን የነበሩ የአጋንንት ሰራዊት ምን ያህል ጊዜ እንደተሳካላቸው መገመት ቢያዳግትም እኛን ማሳታቸውና በፈቃዳቸው ስር ገዝተው ማኖራቸው ብዙ ነገር አመልካች ነው፤ ከዚህ በተጨማሪ የውድቀት ዘመኖቻችን ራሳቸው የእኛን ጉዳት አመልካች ናቸው፡፡ እግዚአብሄር ግን እንደኛ ሳይሆን እንደ እርሱ አሳብ ወጥቶ ከፊታችን ይገኛል(1ዜና.17:8)፡-
“በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ፤ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደ ታላላቆች ስም ለአንተ ስም አደርጋለሁ።”
የእግዚአብሄር አብሮነት ሁሌም መተማመንና ደህንነት ይፈጥራል፡፡ ጠላትማ አዘውትሮ ከፊት መውጣት ይሻል፣ የጥላቻውን ምኞት ይፈጽምብን ዘንድ ይቸኩላል፡፡ ከርሱ ፈጽሞ ቀድሞ ፊተኛ የሚሆን እግዚአብሄር ግን ከጥፋት በፊት የሚያዘጋጅልን ማምለጫ መንገድ ያድነናል፡፡ ከማምለጥ ወደ ድል መንገድ ስንሻገርም በመንፈስ ጥቃት በሚታወከው መንፈሳዊ ይዘታችን ላይ የመንፈሱን ሀይል ልኮ የሚሞላን በረከት ደግሞ አለ፣ በረከቱ ወደ ፈቃዱ በተሻገርን ወቅት ፍሬ አድርጎ የሚሰጠን ውጤታማ ህይወት ነው፡፡
ይህ ዜና በየትኛውም ጊዜና በማንኛውም ስፍራ የሚሰራ የታመነ ተስፋ ነው፣ ግን ተስፋው እንዲሞላና ሊያሰናክል የሚቀድምን ጠላት እግዚአብሄር እንዲያስወግድ መንገድን ለእግዚአብሄር አደራ መስጠት ተገቢ ነው፡፡
1. የሰው ፊት – በፊቴ ገበታን አዘጋጀልኝ
እንደ አማኝ ሰው የማስበው፣ የምመኘውና የምለው ነገር ጠላት ከፊቴ ይወገድ አምላኬ ደግሞ ከፊቴ ይሁን የሚል ነው፡፡ የጻድቅ ሰው ጽኑ እምነት ያን አስተማሪ ነው (2ሳሙ.22:24)፡-
”የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፥ በአምላኬም አላመፅሁምና። ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነበረና፤ ከሥርዓቱም አልራቅሁምና። በእርሱ ዘንድ ቅን ነበርሁ፥ ከኃጢአቴም ተጠበቅሁ።”
አምላኬ በፊቴ እንዲቀድም ልመኝ እንጂ ቃሉ እንደሚያመለክተኝ እርሱ ይገኝ ዘንድ መንገዱን መጠበቅ፣ ፍርዱን በፊቴ ማድረግና ከሥርዓቱ ያለመራቅ ይገባኛል፡፡
ከጠላት እሸቅድምድም የማይተናነስ የራስ ጉዳይ በፊታችን ሲቀደም እግዚአብሄር ሊሰራልን ላቀደው በጎ ስራ እንቅፋት እንሆናለን፡፡ ስለዚህ ቢያንስ ሰዎች ካለፍን በሁዋላ ከሁዋላችን የምንትወው ስራ እንዳለ እርሱም ፍርድ እንዳይስብብን የጠራ አካሄድ ሊኖረን እንዲገባ እንወቅ፣ እንደ እግዚአብሄር ቃል ልንኖር ስንተጋ ተጠባባቂና የውሳኔ ሰው እንድንሆን የግድ ስለሚገባ በቂ የአእምሮ ዝግጁነት ሊኖረንም አስፈላጊ ነው፤ ከዚህ አለም ስናልፍ ስራችን ከሁዋላ ሆኖ ለበጎም ይሁን ለክፉ የሚከተለን ይሆኖአልና!
ምሳ.21:2”የሰው መንገድ ሁሉ በዓይኑ ፊት የቀናች ትመስለዋለች፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ይመዝናል።” ሲል ያሳስባል፡፡
2. በእግዚአብሄር ፊት – በሉም ጠጡም
መዝ.23:5-6 ”በፊቴ ገበታን አዘጋጀህልኝ በጠላቶቼ ፊት ለፊት ራሴን በዘይት ቀባህ፥ ጽዋዬም የተረፈ ነው። ቸርነትህና ምሕረትህ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ይከተሉኛል፥ በእግዚአሔርም ቤት ለዘላለም እኖራለሁ።”
የእግዚአብሄርን ማንነት የሚያውቁ ልጆቹ ከእርሱ ምን እንዲያገኙ ያውቃሉ፤ ይህ ብቻ ሳይሆን ከእጁ እንዴት እንዲቀበሉም ያስተውላሉ፡፡ ከነዚህ አስተዋዮች መሃል አንዱ ንጉሱ ዳዊት ነበር፡፡ ንጉሱ የዘላለም አድራሻውን አስቦ የዘላለም መኖሪያዬ የእግዚአብሄር ቤት ነው ይላል፤ እስከዚያ በምድር የህይወቴ ዘመን ቸርነቱና ምህረቱ አጅበው ይከተሉኛል፣ ከርሱ ጋር የምኖረውም ያዘጋጀልኝን ገበታ እየተመገብኩና ጽዋውን እየጠጣሁ ነው፣ በጠላቴ ፊት ስመላለስም አንገቴን ሳልደፋ በርሱ ታምኜና በዘይቱ ተቀብቼ ነው ይላል፡፡
እግዚአብሄር ሲመግብ የሚመግበው ከእርሱ ጋር የሚያኖር ሀይል የምንቀበልበትን ሰማያዊ ምግብ ነው፡፡ የወረደው መና በምድረበዳ ለእስራኤል ሙሉ ምግብ ነበር፡፡ ለራባቸውም ከሰማይ እንጀራ ሰጣቸው፥ ለጥማታቸውም ከዓለቱ ውኃ አመጣላቸው፤ ወደ ማለላቸውም ምድር ገብተው ይወርሱ ዘንድም አዘዛቸው እንደተባለ (ነህ.9:15)።
ዘጸ.24:9-11 ”ሙሴም አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወጡ፤ የእስራኤልንም አምላክ አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ሰማይ መልክ የሚያበራ እንደ ብሩህ ሰንፔር ድንጋይ የሚመስል ወለል ነበረ። እጁንም በእስራኤል አዛውንቶች ላይ አልዘረጋም፤ እነርሱም እግዚአብሔርን አዩ፥ በሉም ጠጡም።”
በእግዚአብሄር ፊት መመላለስ የህይወት አቅጣጫን በርሱ ፈቃድ ውስጥ ለማጽናትም ይረዳል፡፡ የእስራእል ሽማግሌዎች በፊቱ በመገኘታቸው ክብሩን ሊያዩ በቁ፣ ህዝቡን እየመሩ ወደፊት ይጉዋዙ ዘንድ ከእግዚአብሄር ጋር ህብረት የማድረግና ያዘጋጀላቸውን ገበታ መመገብ ቻሉ፣ ይህ ትልቅ እድል ነበር፡፡ የእስራኤልን ህዝብ በእግዚአብሄር ድምጽ እየተመሩ ማገልገል የተገባቸው እነዚህ ሽማግሌዎች አስቀድመው የእግዚአብሄርን ክብር ባያዩና የርሱን አብሮነት ባያረጋግጡ ኖሮ ህዝባቸውን አበረታተው ጭው ያለውን ምድረበዳ ማለፍም ሆነ ማሳለፍ ባልቻሉ ነበር፡፡
ዘዳ.9:3-4 ”አምላክህም እግዚአብሔር እንደሚበላ እሳት ሆኖ በፊትህ እንዲያልፍ ዛሬ እወቅ፤ እርሱ ያጠፋቸዋል፥ በፊትህም ያዋርዳቸዋል፤ እግዚአብሔርም እንደ ነገረህ አንተ ታሳድዳቸዋለህ፥ ፈጥነህም ታጠፋቸዋለህ። አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ ካወጣቸው በኋላ። ስለ ጽድቄ እወርሳት ዘንድ ወደዚች ምድር እግዚአብሔር አገባኝ ስትል በልብህ አትናገር፤ እነዚህን አሕዛብ ስለ ኃጢአታቸው እግዚአብሔር ከፊትህ ያወጣቸዋል።”
በእግዚአብሄር ፊት የሄደና የእግዚአብሄርን ገበታ የተካፈለ ህዝብ በፊቱ እንደሚበላ እሳት ሆኖ የሚያልፍ ተዋጊ አምላክ እንዳለው ከማወቅ ሌላ ምን እረፍት አለው?
3. የእግዚአብሄር ክብር እንዳይገለጥ የሚጋርዱ ከፍታዎች፣ ጠማማዎችና ስርጉጥጉዋጦች (ኢሳ40)
እግዚአብሄርን የማየው እርሱ ከአጠገቤ ሲኖር፣ ሲገለጥ፣ ሲታይና ሲመጣ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ክብር ባልተገለጠበት ሁኔታ እግዚአብሄን ማየት (በእምነት) አይቻልም፡፡ሙሴ ፊቱን እንዲያይ ይገለጥለት ዘንድ ጠይቆአል፡፡ እግዚአብሄር እንዳይገለጥና ከፊታችን እንዳይወጣ የሚያደርጉ ብዙ ምክኒያቶች አሉ፡፡ እግዚአብሄር በተገለጠባቸው ሁኔታዎች ሁሉ ያሳስብ የነበረው እርሱን ስለሚጋርዱ የእኛ ጉዳዮች ነው፤ ይህን ከእስራኤላውያን የጉዞ ታሪክ የምንማረው ነው፡-
የጽድቅና የልብ ቅንነት ማጣት
ዘዳ.9:5-6 ”ምድራቸውን ትወርሳት ዘንድ የምትገባው ስለ ጽድቅህና ስለ ልብህ ቅንነት አይደለም፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ከፊትህ በሚያጠፋቸው በእነዚያ አሕዛብ ኃጢአት ምክንያትና ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም የማለላቸውን ቃል ይፈጽም ዘንድ ነው። እንግዲህ አንተ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነህና አምላክህ እግዚአብሔር ይህችን መልካም ምድር ርስት አድርጎ የሰጠህ ስለ ጽድቅህ እንዳይደለ እወቅ።”
የኃጢአት ስራና ክፉ የሆነ ድርጊት
ዘዳ.9:18-19 ”ስለ ሠራችሁት ኃጢአት ሁሉ፥ እርሱንም ለማስቈጣት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ስላደረጋችሁ፥ እግዚአብሔር ሊያጠፋችሁ ከተቈጣባችሁ ከቍጣውና ከመዓቱ የተነሣ ስለ ፈራሁ፥ እንደ ፊተኛው በእግዚአብሔር ፊት አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ወደቅሁ፤ እንጀራ አልበላሁም፥ ውኃም አልጠጣሁም። እግዚአብሔርም በዚያን ጊዜ ደግሞ ሰማኝ።”
በቃሉ ላይ ማመፅ፣ በእርሱም አለማመን፣ ድምፁንም አለመስማት
ዘዳ.9:23-25 ”እግዚአብሔርም፡- ውጡ የሰጠኋችሁንም ምድር ውረሱ ብሎ ከቃዴስ በርኔ በላካችሁ ጊዜ፥ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ቃል ዐመፃችሁ፥ በእርሱም አላመናችሁም፥ ድምፁንም አልሰማችሁም። እናንተን ካወቅሁበት ቀን ጀምሮ በእግዚአብሔር ዓመፀኞች ነበራችሁ። እግዚአብሔርም፡- አጠፋችኋለሁ ብሎ ስለ ተናገረ በወደቅሁበት ዘመን አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በእግዚአብሔር ፊት ወደቅሁ።”
እግዚአብሄር ህዝቡን በግልጽ አልመከረምን? የህይወት ይዘታቸውንስ በጉልህ ገልጦ አላሳየምን?
ቃሉ በግልጽ ለእስራኤል የሚያስገነዝበው ነገር በመጀመርያ እግዚአብሄር ወደ ከነአን ምድር ያገባቸው ስለጽድቅ ስራቸው አለመሆኑን፣ ይልቅ በማዳኑና በምህረቱ ብዛት በምድረበዳ ሳይጠፉ ተርፈው ወደ ተገባላቸው የተስፋ ምድር መድረሳቸውን፣ በሌላ በኩል ምድሪቱን ከወረሱ በሁዋላ ከክፋታቸው የተነሳ እግዚአብሄርን የሚተዉ መሆናቸውን፡፡
ዛሬ ከእስራኤል ህይወት ተሞክሮ ለእያንዳንዳችን የሚወጣው ምክር የሚያሳየው በነጻ የተቀበልነው የእግዚአብሄር ጸጋ በከንቱ የሚጣል ሳይሆን የቀድሞ አሳፋሪ ህይወታችንን አስታውሰን በዚያ አፍረንና ተጸጽተን፣ ስለነበረብን የሀጢያት ሸክምም አዝነን ወደዚያ እንዳንመለስ ይልቅ ከእግዚአብሄር ዘንድ የተቀበልነውን ነጻ ያወጣንንና ደስተኛ ያደረገንን ተጠንቅቀን መያዝ የተገባ መሆኑን ነው፡፡ የልብ ኩራትና የአይን ትእቢት የሚወጣው ፈጥነን የዳንበትን የእግዚአብሄር ምህረት በመዘንጋትና ራስን የገዛ ራስ ጠባቂ ማድረግ ስንጀምር በመሆኑ በእግዚአብሄር ፊት ዳግመኛ በደልን ላለማርገዝ ጥረት ማድረግ ተቀዳሚ እርምጃ መሆን አለበት፡፡