ፊትህን አሳየን{2..}

የመጨረሻ ዘመን

የእግዚአብሄርን ታላቅነትና አስፈሪ ክብር ማወቅ ለሚፈልግና ሀይሉን ሊረዳ የሚፈቅድ ካለ እግዚአብሄር ለህዝቡ የተገለጠበትን ሁኔታ እንዲያይ እንዲያስፈልግ ለመታሰቢያነት በቃሉ ላይ ሰፍሮአል፡-
ዘጸ.19:10-11 “እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፡- ወደ ሕዝቡ ሂድ፥ ዛሬና ነገም ቀድሳቸው፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፤ በሦስተኛው ቀን ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ይወርዳልና ለሦስተኛው ቀን ይዘጋጁ።”
የእስራኤል ህዝብ በግብጽ ሳለ በሙሴ በኩል ስለ እግዚአብሄር አዳኝነት ሰምቶ ነበር፡፡ በተወሰነለት ቀንም የእግዚአብሄርን ክብር የመመልከት እድል አግኝቶአል፡፡ ያም ህዝቡ በእርሱ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጠነክሩና እርሱን በመፍራት እንዲኖሩ የሚረዳ መገለጥ ሆኖ ነበር፡፡
ዘጸ.19:16-25 “እንዲህም ሆነ፤ በሦስተኛው ቀን በማለዳ ጊዜ ነጐድጓድና መብረቅ ከባድም ደመና እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምጽ በተራራው ላይ ሆነ፤ በሰፈሩም የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተንቀጠቀጡ። ሙሴም ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር ለማገናኘት ከሰፈር አወጣቸው፤ ከተራራውም እግርጌ ቆሙ። እግዚአብሔርም በእሳት ስለ ወረደበት የሲና ተራራ ሁሉ ይጤስ ነበር፤ ከእርሱም እንደ እቶን ጢስ ያለ ጢስ ይወጣ ነበር፥ ተራራውም ሁሉ እጅግ ይናወጥ ነበር። የቀንደ መለከቱም ድምፅ እጅግ በበረታና በጸና ጊዜ ሙሴ ተናገረ እግዚአብሔርም በድምፅ መለሰለት። እግዚአብሔርም በሲና ተራራ ላይ ወደ ተራራው ራስ ወረደ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ወደ ተራራው ራስ ጠራው፤ ሙሴም ወጣ።”
የእግዚአብሄርን ክብር ያዩ ህዝቦች ቀጣዩ ጉዞአቸው እንዴት ነበር፣ አንዳዩትና እንደሰሙት ወይስ ፈጥኖ የሰራውን ስራ በዘንጋ መንፈስ? የአርባ አመቱ የበረሀ ጉዞአቸው በብዙ ማንከስና እንጉርጉሮ እንደነበር ስንረዳ በተገለጠላቸው አምላክ ፊት እንዴት ባለ ድካም እንደኖሩ፣ እርሱ ግን ቃሉን ሳያዛንፍና ሳያጎድል እንደተገለጠበት አገላለጥ ወዳሰበላቸው ምድር እንዳገባቸው እንመለከታለን፡፡
በእግዚአብሄር ፊት ስንመላለስ በረከትና ምህረት በሚያመጣ አካሄድ ውስጥ መሆናችን ቀርቶ በፊቱ ሳለን መተላለፍን ከወደድን እስከመርገም በሚያደርስ ጥፋት ውስጥ ልንወድቅ እንችላለን፣ ለዚህም እስራኤላውያን ምሳሌ ናቸው፡፡ በሲና ተራራ በሚያስፈራ ክብር የመጣው አምላክ ዛሬም አለ ወይም ከዘመን ብዛት ሲቆይ አልተለወጠም፣ ስለኛ ሲልም ራሱን አልቀየረም፡፡
ዘዳ.31:16-18” እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፡- እነሆ፥ ከአባቶችህ ጋር ትተኛለህ፤ ይህም ሕዝብ ይነሣል፥ ይቀመጥባትም ዘንድ በሚሄድባት ምድር መካከል ያሉትን ሌሎችን አማልክት ተከትሎ ያመነዝራል፥ እኔንም ይተወኛል፥ ከእነርሱም ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ያፈርሳሉ፡፡ በዚያም ቀን ቍጣዬ ይነድድባቸዋል፥ እተዋቸውማለሁ፥ ፊቴንም እሰውርባቸዋለሁ፥ ለአሕዛብ መብል ይሆናሉ፤ በዚያም ቀን፡- በእውነት እግዚአብሔር በእኛ መካከል የለምና ይህ ክፉ ነገር ሁሉ አገኘን እስኪሉ ድረስ ብዙ ክፉ ነገርና ጭንቀት ይደርስባቸዋል። ሌሎችን አማልክት ተከትለዋልና ስላደረጉት ክፋት ሁሉ እኔ በዚያ ቀን ፈጽሜ ፊቴን እሰውራለሁ።”
እግዚአብሄር ከባሪያው ከሙሴ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበረው፤ ሊሰበስበው በፈቀደም ጊዜ ያን እቅዱን (የመጨረሻ የመሰብሰቢያ ሰአቱን) ሳይቀር ነገረው፡፡ ህዝቡን በተመለከተ ግን ከርሱ ሞት በሁዋላ እንደሚተዉት ሙሴ በህይወት ሳለ መስክሮባቸዋል፡፡ እግዚአብሄር ያን የተናገረው ህዝቡ ሊሄዱ ያለበትን አካሄዳቸውን አስቀድሞ ስላየ እንጂ እርሱ በህይወታቸው የሚፈጠረው ስህተት አልነበረም፤ ያ ክፋታቸውም ፊቱን እንዲሰውርባቸው አድርጎአል፡፡
እግዚአብሄር መቼም ይገለጥ፣ ሲገለጥ ግን ቁጣውን በሚያነሳሳ አካሄድ ውስጥ ሆነን አያግኘን፣ ፍርድ ውስጥም አይክተተን፤ ይልቅ በምህረት ይመልከተን፣ ለጠላት አሰራርም አሳልፎ አይስጠን፣ ጠላታችንን ይዋጋልን እንጂ፡፡
1. ለታመነው ፊቱ ተገልጦ ጠላትን ይምታለት
ከእግዚአብሄር ጋር ጠላት ሆኖ መኖር እንዴት ይቻላል፣ እስከ ምን ያህል የጊዜ ርዝመትስ በዚያ ህይወት ውስጥ መቀጠል ይቻላል? ያን እውቀት ባለማስተዋል ምክኒያት ነው እግዚአብሄርን ትቶና ያለማወቅ ውስጥ ታስሮ ወደ ብዙ ጥፋት መወርወር የሚከተለው፡፡ የዚያ ያለማወቃችን ምንጭ የተለያየ ምክኒያት ቢኖረውም፣ የፈቃዱንም ሙሉ ምስል ለማየት ቢያዳግተንም ባለማወቃችን ጠንቅ ቁጣውን ወደሚያነሳሳ እንቅስቃሴ ውስጥ ላለመግባት ስንል ቆም ልንል ይገባል፡፡ ብዙ መንፈሳዊ እውቀት ቢኖረን፣ በአለም ያሉ መንፈሳዊ ጥበቦቹ ቢበሩልን ወደ ፈቃዱ እውቀት ካልደረስን ረጋ ስክን እንበል፤ ብዙ ከማውራት፣ የገመትነውን ከማድረግ፣ ያየነውንም ከመመኘት እንዲሁም እርግጠኛ ባልሆንበት ጉዳይ ዘው ከማለት ሰብሰብ ማለት፣ ያን ማድረግ አይጎዳንም እንዲያውም ያለማወቃችን እንዳያጠፋን ያስጥለናል እንጂ፡፡ እግዚአብሄርን አውቀዋለሁ ብለን ታምነን እንኩዋን ቢሆን እግዚአብሄር የሚቀጥለውን ስራውን አስኪነግረን/እስኪያሳየን መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ጸሎት አለ፣ ቃሉን መጠበቅ አለ፡፡ ለምሳሌ እስራኤላውያን ከንጉሳቸው ከዳዊት ጋር ሆነው በእግዚአብሄር ፊት በደስታና በምስጋና ውስጥ ሳሉ ባለማስተዋሉ ምክኒያት እግዚአብሄርን ያስቆጣ ዖዛ የሚባል ሰው በእግዚአብሄር ፊት ተቀጽፎ ነበር፡-
”የእግዚአብሔርንም ታቦት በአዲስ ሰረገላ ላይ ጫኑ፥ በኮረብታውም ላይ ከነበረው ከአሚናዳብ ቤት አመጡት፤ የአሚናዳብ ልጆችም ዖዛ እና አሒዮ አዲሱን ሰረገላ ይነዱ ነበር። በኮረብታውም ላይ ከነበረው ከአሚናዳብ ቤት የእግዚአብሔርን ታቦት ባመጡ ጊዜ አሒዮ በታቦቱ ፊት ይሄድ ነበር። ዳዊትና የእስራኤልም ቤት ሁሉ በቅኔና በበገና በመሰንቆም በከበሮም በነጋሪትና በጸናጽል በእግዚአብሔር ፊት በሙሉ ኃይላቸው ይጫወቱ ነበር። ወደ ናኮንም አውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ ይፋንኑ ነበርና ዖዛ እጁን ዘርግቶ የእግዚአብሔርን ታቦት ያዘ። የእግዚአብሔርም ቍጣ በዖዛ ላይ ነደደ፥ እግዚአብሔርም ስለ ድፍረቱ በዚያው ቀሠፈው፤ በእግዚአብሔርም ታቦት አጠገብ በዚያው ሞተ። እግዚአብሔርም ዖዛን ስለ ሰበረው ዳዊት አዘነ፤ እስከ ዛሬም ድረስ የዚያ ስፍራ ስም የዖዛ ስብራት ተብሎ ተጠራ።” (2ሳሙ.6:3-8)
ለዖዛ መቀሰፍ እግዚአብሄር ምክኒያት ሊሆን ይችላልን? ዖዛ በእግዚአብሄር ፊት በደስታ ተገኝቶ እያመሰገነ አልነበር? ግን የእግዚአብሄርን አሰራር፣ ፈቃድና ፍላጎት ማስተዋልና የሚገባውን ብቻ ማድረግ እንደሚገባው አላወቀም፤ በዚያ ምክኒያት መላው እስራኤልን የሚያስደነግጥ መቅሰፍት እንዲመጣ ጥፋትን ሳበ፡፡
እግዚአብሄርን በማወቅ ውስጥ መረሳት የሌለበት ሌላው ነገር፡- ልክ እንደ ንጉሱ ዳዊት በእግዚአብሄር ፊት ሙሉ የመመላለስ ጥንቃቄ ማደረግ የተገባ መሆኑን ማስረገጥ፤ በተጨማሪ የአምልኮ ነጻነት ላይ ምንም አይነት ድርድር ያለመኖሩን ማወቅ፡፡ ያለምንም ገደብ ከእግዚአብሄር ጋር በጥንቃቄ ለሚመላለሰው ለርሱ እግዚአብሄር ይዋጋለታል፡-
መዝ.17:13-15 ”አቤቱ፥ ተነሥ፤ ቀድመህ ወደ ታች ጣለው፤ ነፍሴን ከኃጢአተኛ በሰይፍህ አድናት። አቤቱ፥ ከሰዎች፥ እድል ፈንታቸው በሕይወታቸው ከሆነች ከዚህ ዓለም ሰዎች በእጅህ አድነኝ፤ ከሰወርኸው መዝገብህ ሆዳቸውን አጠገብህ፤ ልጆቻቸው ብዙ ናቸው የተረፋቸውንም ለሕፃናቶቻቸው ያተርፋሉ። እኔ ግን በጽድቅ ፊትህን አያለሁ፤ ክብርህን ሳይ እጠግባለሁ።”
ደጋግሞ እንደተባለው ንጉስ ዳዊት እግዚአብሄርን የሚወድ ንጉስ ነበር፡፡ የእግዚአብሄርን አሳብ የሚያውቅ ፊቱን ሁልጊዜ የሚፈልግና እግዚአብሄር እንደልቤ ያለው ሰውም ነበር፡፡ በአምላኩ የታመነው ይህ ንጉስ እግዚአብሄርን እንደማወቁ መጠን ቸልተኛ ሳይሆን እግዚአብሄርን የሚፈራ ነበር፣ አምላኩ እንዲያየው ተማጽኖአል፣እንዲዋጋለትም ዘወትር ፊቱን ፈልጎአል፡፡ በመዝ.31:14-24 ውስጥ ሲናገር አንዲህ ይል ነበር፡-
”አቤቱ፥ እኔ ግን በአንተ ታመንሁ፤ አንተ አምላኬ ነህ አልሁ። ርስቴ በእጅህ ነው፤ ከጠላቶቼ እጅና ከሚያሳድዱኝ አድነኝ። ፊትህን በባሪያህ ላይ አብራ፥ ስለ ምሕረትህም አድነኝ። አቤቱ፥ አንተን ጠርቻለሁና አልፈር፤ ክፉዎች ይፈሩ በሲኦልም ዝም ይበሉ። በድፍረትና በትዕቢት በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ። በአንተ ለሚያምኑ በሰው ልጆች ፊት ያዘጋጀሃት ለሚፈሩህም የሰወርሃት፥ ቸርነትህ እንደ ምን በዛች! በፊትህ መጋረጃ ከሰው ክርክር ትጋርዳቸዋለህ፥ በድንኳንህም ከአንደበት ክርክር ትሸፍናቸዋለህ። በተከበበ ከተማ የሚያስደንቅ ምሕረቱን በእኔ የገለጠ እግዚአብሔር ይመስገን። እኔስ ከዓይንህ ፊት ተጣልሁ፥ በድንጋጤ አልሁ፤ አንተ ግን ወደ አንተ በጮኽሁ ጊዜ የልመናዬን ቃል ሰማኸኝ።”
ንጉሱ በእግዚአብሄር ፊት ሆኖ ሲናገር በአምላኩ ላይ ያለውን መደገፍ አንስቶ ነው፤ በአምላኩ ሲታመን በስጋው ችሎታ ላይ ልቡን አሳርፎ ሳይሆን እግዚአብሄር በሰጠው ችሎታ በመተማመን ነው፡፡ ከብዙ ፈተናና መከራ ያመለጠበት ሁኔታ ለዚህ ምስክሩ ነው፡፡ ዳዊት ፈተና በበረታበትና ችግሩ በጸናበት ወቅት ጠላት እግዚአብሄር እንደተወው እያወራ ህሊናውን ቢከሰውም እርሱ ግን በእግዚአብሄር መተማመኑን ሳያቁዋርጥ በፊቱ ጸንቶ የቆመበት ወቅት ነበር፡፡ እግዚአብሄርም ከፈተናው በሁዋላ እንደመለሰለት ሁሎችም በአይናቸው ሲያዩ እርሱን እግዚአብሄር እንዳልተወውና ረዳቱ አምላኩ እንደሆነ አስተዋሉ፡፡ እኛ የእግዚአብሄርን ፊት የምንፈልግም በእግዚአብሄር መተማመናችንና መጠባበቃችን ስላላቁዋረጥን ትልቅ ዋጋ እንዳለን ከንጉሱ ህይወት ልንማር ይገባል፡፡
“ከብርቱዎች ጠላቶቼ ከሚጠሉኝም አዳነኝ፥ በርትተውብኝ ነበርና። በመከራዬ ቀን ደረሱብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ደገፋዬ ሆነ። ወደ ሰፊ ስፍራም አወጣኝ፤ ወድዶኛልና አዳነኝ። እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ ይከፍለኛል፤ እንደ እጄ ንጽሕና ይመልስልኛል። የእግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፥ በአምላኬም አላመፅሁም። ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነበረና፥ ሥርዓቱንም ከፊቴ አላራቅሁም። በእርሱ ዘንድ ቅን ነበርሁ፥ ከኃጢአቴም ተጠበቅሁ። እግዚአብሔርም እንደ ጽድቄ እንደ እጄም ንጽሕና በዓይኖቹ ፊት መለሰልኝ።” ሲል በመዝ.18:17-24 ውስጥ ያወጀው ማዳኑ የኛንም ልብ ጨምሮ ተስፋ ይሞላል፡፡
2. የጠላት ፊት – በጠላት ፊት ራሴን ቀባህ
አንድ አስፈሪ ፊት ቢኖር የጠላት ፊት የምንለው አስደንጋጭ ክፉ ግርማ ሲሆን ያም የጠላት አሰራር ተገልጦ የሚሰራበት ወቅትና ቅጽበት ነው፡፡ የጠላት ፊት የሴራና የጥላቻ ጥላ ነው፣ ፍቅር የሌለው አጋንንታዊ ተንኮል የሚገለጥበት አካሄድ ነው፡፡ ሰዎች በጠላት ፊት ሲከበቡ ሞገስ ሳይሆን ውርደት ውስጥ ይገባሉ፣ ከሀይል ይልቅ ድካም ይይዛቸዋል፣ ጥፋትም ይከብባቸዋል፡፡
የጠላትን መንገድ የሚያስተውለው ንጉስ በመዝሙር ወደ እግዚአብሄር ልመናውን ያሰማል፤ የጠላት አሰራር በዙርያውና በሁኔታው ላይ አይሎበት ነበርና ልቡ ተስፋ ቈርጦ ይጮኸል፤ የተስፋ ጭላንጭል በመሃሉ በታየው ጊዜ ደግሞ አንድ ነገር ይላል፡-”ጽኑ ግንብ በጠላት ፊት ተስፋዬም ሆነኸኛልና መራኸኝ። በድንኳንህ ለዘላለም እኖራለሁ፤ በክንፎችህም ጥላ እጋረዳለሁ” በማለት(መዝ.61፡3)፡፡
ከብርቱ ፈተና በሁዋላ ድል በሆነ ጊዜ ደግሞ ይቀኛል (መዝ.23:5-6)፡-
”በፊቴ ገበታን አዘጋጀህልኝ በጠላቶቼ ፊት ለፊት ራሴን በዘይት ቀባህ፥ ጽዋዬም የተረፈ ነው። ቸርነትህና ምሕረትህ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ይከተሉኛል፥ በእግዚአሔርም ቤት ለዘላለም እኖራለሁ።”
የጠላት ፊትንና ከእግዚአብሄር ዘንድ የሆነን ዘይትና ጽዋ ማነጻጸር አንድ ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ ጥፋት ፈጣሪ የጠላት ፊት አጠገብ የነበረው ሀዘንተኛ ሰው ውድቀቱን እየጠበቁለት ባለበት ሰአት የእግዚአብሄር እጅ ደርሳለት መለኮታዊ ቅባት ሲፈስበት እንዲሁም በሀዘን ከሞላው ጽዋው ውስጥ የአምላኩ ደስታ፣ ብርታትና ምህረት ገብቶ ሲትረፈረፍ ያለው አጋጣሚ እንደምን ታላቅ ነው! ደካማው ሰው ከከሳሹና ጠላቱ ጋር በአምላኩ ፊት ቆሞ ለፍርድ ሲጠበቅ ከቸሩ አምላክ ዘንድ ምህረት ተቀብሎና ዘይት ተቀብቶ ታሪኩ ሲለወጥ ከማየት በላይ በጠላት ዲያቢሎስ ላይ ሌላ ምን ታላቅ በቀል አለ?
ዘካ.3:1-5”እርሱም ታላቁን ካህን ኢያሱን በእግዚአብሔር መልአክ ፊት ቆሞ አሳየኝ፥ ሰይጣንም ይከስሰው ዘንድ በስተ ቀኙ ቆሞ ነበር። እግዚአብሔርም ሰይጣንን፡- ሰይጣን ሆይ፥ እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤ ኢየሩሳሌምን የመረጠ እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤ በውኑ ይህ ከእሳት የተነጠቀ ትንታግ አይደለምን? አለው። ኢያሱም እድፋም ልብስ ለብሶ በመልአኩ ፊት ቆሞ ነበር። እርሱም መልሶ በፊቱ የቆሙትን፡- እድፋሙን ልብስ ከእርሱ ላይ አውልቁ አላቸው። እርሱንም፡- እነሆ፥ አበሳህን ከአንተ አርቄአለሁ፥ ጥሩ ልብስም አለብስሃለሁ አለው። ደግሞ፡- ንጹሕ ጥምጥም በራሱ ላይ አድርጉ አለ። እነርሱም በራሱ ላይ ንጹሕ ጥምጥም አደረጉ፥ ልብስንም አለበሱት፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በአጠገቡ ቆሞ ነበር።”
ከላይ እንደተመለከትነው የጠላት ፊት ለመልካም የህይወት ውጤት የሚቆምበት ስፍራ አይደለም፤ ፊቱ አስፈሪ፣ አስጨናቂ፣ ሰላም የሌለበት፣ ወዳጅ ሳይሆን አጥፊ ጠላት የበረታበት ሁኔታ ስለሆነ ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፊት ለበረከትና ለምህረት የሚገለጥ ሲሆን የጠላት ፊት ለክፋትና ለእርማን የሚገለጥ ነው፡፡ ኢያሱ በእግዚአብሄር ፊት ለምህረት ቆሞ ሳለ ጠላት ወደ ፍርድ ሊያስገባው በቀኙ ቆሞ ነበር፡፡ የእግዚአብሄር ማጽናኛ ቃል ግን የጠላትን ክስ የተሻገረ ብርታት አመጣለት፡፡
እግዚአብሄር ስለህዝቡ ሲዋጋና ሲሙዋገት የህዝቡ ልብ ወደ አምላኩ ሊያቀና ተገቢ ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ የጠላት ዲያቢሎስን ፈቃድ ከተከተለ እግዚአብሄር ጥበቃውን ከህዝቡ ላይ እንደሚያነሳ ብዙ ጊዜ አስጠንቅቆአል፡፡ ለጠላት ተላልፎ የተሰጠ ያ ሰውም ጠላት በግላጭ አግኝቶ መጫወቻ ያደርገዋል፡፡
ኤር.18:14-17 ”በውኑ የሊባኖስ በረዶ የምድረ በዳውን ድንጋይ ይተዋልን? ወይስ ከሩቅ የምትመጣው ቀዝቃዛይቱ ፈሳሽ ውኃ ትደርቃለችን? ሕዝቤ ግን ረስተውኛል ለከንቱ ነገርም ዐጥነዋል፤ ከመንገዱም ተሰናክለዋል ከቀድሞውም ጐዳና ርቀው ወዳልተሠራው ወደ ጠማማው መንገድ ፈቀቅ ብለዋል። ምድራቸውን ለመደነቂያና ለዘላለም ማፍዋጫ አድርገዋል፤ የሚያልፍባት ሁሉ ይደነቃል፥ ራሱንም ያነቃንቃል። በጠላት ፊት እንደ ምሥራቅ ነፋስ እበትናቸዋለሁ፥ በጥፋታቸውም ቀን ጀርባዬን እንጂ ፊቴን አላሳያቸውም።”
እግዚአብሄር ተቆጥቶ በጠላት ፊት እበትናቸዋለሁ፣ በጥፋታቸውም ቀን ጀርባዬን እንጂ ፊቴን አላሳያቸውም የሚላቸው ሰዎች እንደምን ባለ ፍርድ ውስጥ የተጣሉ ናቸው? ማንስ ነው ከዚህ የሚያድናቸው? ማንም ያለመኖሩን ካመንን ራሳችንን በመፈተሽ ተገቢ ውሳኔ ላይ እንድረስ፡፡