የእግዚአብሄር ፊት ከቅርበቱ፣ ከክብሩ፣ ከእይታው፣ ከሞገሱ፣ ከጉብኝቱ፣ ከመገኛው፣ ከገጽታውና ከማንነቱ ጋር ይያያዛል፡፡ የእግዚአብሄር ፊት ሲታይ ክብሩ ይታያል፣ ሀይሉ ከሞገስና ከማስፈራቱ ጋር ይገለጣል፡፡ ሰው በእግዚአብሄር ፊት ሲሆን ለምህረት ይቆማል፣ በረከት ሊቀበል ይቆማል፣ ትእዛዝ ሊቀበል፣ ፍርድ ሊቀበል፣ ደግሞም ሀይል ይሞላ ዘንድ ሀያሉ አምላክ ፊት ይቆማል፡፡ የሰው ልጅ የመጨረሻው አቁዋቁዋሙ ግን ዘላለማዊውን ኑሮ መወሰኛ ሰአት ይሆናል፡-
ራእ.20:12 “ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፥ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ።”
በእግዚአብሄር ፊት ቆሞ ፊት ለፊት ከእርሱ ጋር እንደሙሴ መነጋገር ደስ እንደሚያሰኝ ሁሉ ወደፊቱ እንደማሪያም ተጠርቶ የቅጣት ፍርድ መቀበል ደግሞ እጅግ ያስፈራል፡፡ እንደ ነቢዩ ኤልያስ ከእግዚአብሄር ፊት በተስፋና በሀይል ተሞልቶ መውጣት ቢያስደስትም እንደ ቃየን በእግዚአብሄር ላይ ተቆጥቶ መውጣት ደግሞ ያሳፍራል፡፡
የእግዚአብሄር ፊት እግዚአብሄር ለሰው የመገለጡን ሁኔታ የሚያመለክት እንጂ የሚዳሰስ አካሉን የሚያሳይ አይደለም፣ እግዚአብሄር መንፈስ ስለሆነ የሚዳሰስ አካላዊ ፊት የለውም፡፡ የእግዚአብሄር ፊት አካባቢ ብርታት፣ ማዳን፣ እቅዱን በተግባር ማሳየት፣ ስሙን በዘመንና በትውልድ መሀል መግለጥ ይሆናል፡፡
በዘፍ.3:8 ውስጥ እግዚአብሄር ለአዳምና ለሄዋን ሲገለጥ ይታያል፡-
”እነርሱም ቀኑ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔርን የአምላክን ድምፅ ከገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰሙ፤ አዳምና ሚስቱም ከእግዚአብሔር ከአምላክ ፊት በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ።”
አዳም በሰራው ሀጢያት ደንግጦና እግዚአብሄርን ፈርቶ ከመገኛው/ከፊቱ ሊሰወር ሞከረ፡፡ በዚህ መንገድ ሁለቱም ከእግዚአብሔር አምላክ ፊት ሊርቁ አሰቡና በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ፤ ድምጹን ከሰሙበት አካባቢ የራቁ መሰላቸውም። እውነቱ ግን እግዚአብሄር ሲገለጥና በክብሩ ፊት ስንሆን አንድም ነገራችን ሊሰወር እንደማይችል ነው፡፡ በዘፍ.4:16 ላይ ስለ ቃየል የሚናገረው ታሪክ ተመሳሳይ ሁኔታን ገልጦ ያሳየናል፡-
”ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፤ ከዔድንም ወደ ምሥራቅ በኖድ ምድር ተቀመጠ።”
እሱ ከእግዚአብሄር ፊት ወጣ፤ ወጣና ከአምላኩ በልቡ ራቀ፤ በፊቱ ማምለክ እስኪያዳግተው፣ በሰላም መኖር እስኪያቅተውና በመልካም ህይወት መቀጠል እስኪሳነው ድረስ ከአምላኩ መገኛ አካባቢ ረቀ፡፡ ቃየል ከእግዚአብሄር ፊት ሲወጣ ጥሎ የሄደው የእግዚአብሄርን ጥበቃ ነበር፤ የሚባርከው የእግዚአብሄር አብሮነት ላይም አምጾ መሸሹ ነበር፡፡
እግዚአብሄርን ለሚወደው ግን፡-
ፊቱ ተገልጦ ሞገስን ይሰጠዋል፣ ተቀባይ ያደርገዋል፤
ፊቱን አብርቶ መገኘቱን ይገልጣል፣ ጠላትንም ይመታለታል፤
ፊቱን አሳይቶ ማንነቱን ይገልጣል፤
በፊቱ በመሆን በመገኘቱ ሰውን ያኖራል፤
ከፊት ቀድሞም እለፍ ይላል፣ ይመራል፣ ይመክታል፡፡
አዎ እርግጥ ነው፣ የጠራቸው በፊቱ ተቀምጠው በልተዋል፣ ጠጥተዋል፣ ረክተዋል፣ ድነዋል፤ ከእርሱ ጋር አፍ ለአፍ ተነጋግረዋል፡- ፊቱን ስለገለጠላቸው ያን በረከት ታድለዋል፡፡
ዘጸ.33:11-23 ”እግዚአብሔርም ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ፊት ለፊት ከሙሴ ጋር ይነጋገር ነበር። … ሙሴም እግዚአብሔርን፡- እነሆ አንተ:- ይህን ሕዝብ አውጣ ትለኛለህ፤ ከእኔም ጋር የምትልከውን አላስታወቅኸኝም። አንተም፡- በስምህ አወቅሁህ፥ ደግሞም በእኔ ፊት ሞገስን አገኘህ አልኸኝ። አሁንም በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ አውቅህ ዘንድ በፊትህም ሞገስን አገኝ ዘንድ መንገድህን እባክህ አሳየኝ፤ … በምድርም ፊት ካለው ሕዝብ ሁሉ እኔና ሕዝብህ የተለየን እንሆን ዘንድ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህ፥ እኔና ሕዝብህ በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘታችን በምን ይታወቃል? አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን፡- በፊቴ ሞገስ ስላገኘህ በስምህም ስላወቅሁህ ይህን ያልኸውን ነገር አደርጋለሁ አለው። እርሱም፡- እባክህ ክብርህን አሳየኝ አለ።እግዚአብሔርም፡- እኔ መልካምነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ስም በፊትህ አውጃለሁ፤ ይቅርም የምለውን ይቅር እላለሁ፥ የምምረውንም እምራለሁ አለ።ደግሞም፡- ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም አለ።እግዚአብሔርም አለ፡- እነሆ ስፍራ በእኔ ዘንድ አለ፥ በዓለቱም ላይ ትቆማለህ፤ክብሬም ባለፈ ጊዜ በሰንጣቃው ዓለት አኖርሃለሁ፥ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፤ እጄንም ፈቀቅ አደርጋለሁ፥ ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም።”
ልክ እንደ ሙሴ በእምነት የሚኖር ሰው በእግዚአብር ፊት የሚመላለስ ሰው ነው፡፡ ሆኖም ሙሴ ባለሞገስ ሰው ይሁን እንጂ በአምላኩ ፊት ቅንና ትሁት ነበር፡፡ ከእግዚአብሄር የተቀበለው ያ ሞገስ ከባህሪው ጋር ተዳምሮ እጅግ ትሁትና እግዚአብሄርን የሚፈራ አድርጎታል፡፡ ይህ አካሄዱና ልምምዱ በእግዚአብሄር ዘንድ ስፍራ ሲያሰጠው በአገልግሎቱም የአምላኩን ፍጹም ጥበቃ አስገኝቶለታል፡፡
ዘጸ.33:11 ” እግዚአብሔርም ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ፊት ለፊት ከሙሴ ጋር ይነጋገር ነበር። ሙሴም ወደ ሰፈሩ ይመለስ ነበር፤ ነገር ግን ሎሌው ብላቴና የነዌ ልጅ ኢያሱ ከድንኳኑ አይለይም ነበር።”
ሙሴ እባክህ ክብርህን አሳየኝ ብሎ በጠየቀው መሰረት እግዚአብሄር ጥያቄውን ተቀብሎ በአዎነታዊ መልስ መለሰለት፤ ሆኖም የሙሴ ጥማት ከቀደመው በላይ ሆኖ በመገኘቱ እስራኤል ወደተስፋ ምድር በሚያደርገው ጉዞ ሁሉ እግዚአብሄር አብሮነቱ እንዳይለየው የሚጠይቅ ሆነ፡፡ ሙሴ በዚያ አላበቃም ወደ እግዚአብሄር ይበልጥ መጠጋትንና ክብሩን ማየት ጠየቀ፡፡ እስራኤል ካለበት ሁኔታ አንጻር የበለጠ መንፈሳዊ መነቃቃት መለመንና ከህዝቡ ጋር አብሮነቱን መለመኑ የሙሴን ትክክለኛ አመራር አመልካች ነበር፤ እርሱ ወደ እግዚአብሄር ፊት በሞገስ ቢቀርብ ገና ወደ ሁዋላ ለቀረው ህዝብ ምልጃ ማቅረቡ የሙሴ ምልጃና ልመና ትክክለኛና እውነተኛ መሆኑን አመልካች ነበር፡፡ የሙሴ ህይወት በራሱ በረከትና ተቀባይነት ዙሪያ የሚሽከረከር አልነበረም፣ ከርሱ ሁዋላ ላለው የእግዚአብሄር መንጋ እንጂ፡፡
የእግዚአብሄርን ፊት ያየ ሰው ይበልጥ መጠጋትን ይሻል እንጂ ረከቶ በልምምዱ አይቆምም፤ ከምንም በላይ ሌላው ሰው እርሱ ያየውን ክብር እንዲያይና እንዲያገኝ ይማልዳል፣ ስለሞገሱ ይለምናል፣ በረከቱ እንዲበዛ ይጸልያል፣ ትውልድ አምላኩን እንዲገናኝ ይጠይቃል፡- የእግዚአብሄርን ፊት ማየት እንዲህ ያደርጋል፡፡
እኛስ በፊቱ እንዴት እንቅረብ? ንጉስ ሰለሞን በምሳ.3:1-5 ይህን ያስተምረናል፡-
”ልጄ ሆይ፥ ሕጌን አትርሳ፥ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ። ብዙ ዘመናትና ረጅም ዕድሜ ሰላምም ይጨምሩልሃልና። ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ። በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ”
ነገሩ እንዲህ ነው፡- የእግዚአብሄርን ፊት የሚያውቅ አካሄዱን ዘወትር ይመረምራል፣ ያስተካክላልም፡፡ ልቡ አጥብቆ የሚያያዘው በቃሉ ከሚወጣው ትእዛዝ ጋር ስለሚሆንም ዘወትር እራሱን በስፍራው የሚያጸናው ነው፤ እግዚአብሄር ዘወትር ይገኛል ስለሚል፣ በነገሮች ሁሉ ያየኛል ብሎ ስለሚያምንና ስራዬን ያስተውላል ስለሚልም ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔርም አያሳፍረውም፤ በፊቱ እንዲመላለስና በሞገስ እንዲኖር ያደርገዋል።
ቃሉ እንደሚያስተምረን በፊቱ ሆነን መቼም መዘንጋት በሌለበት አካሄድ የእግዚአብሄርን ቃል ከመንገዳችን ያለማውጣት፣ እርሱ አትኩሮት ከሰጠው ነገር ሁሉ ላይ ልባችንን ያለማንሳት፣ በነገር ሁሉ እርሱን በጸሎት ከማሳሰብ ውጪ በሚያስጨንቅና በሚያዋክ አካሄድ ውስጥ ያለመግባት በፊቱ እንድንመላለስ ይረዳል፡፡ ራሳቸውን የሚያውቁ ሰዎች ራሳቸውን ተሰባሪ የሸክላ እቃ አድገው ስለሚቆጥሩ ሁልጊዜ በእግዚአብሄር ጥበቃ ስር መሆንን ይፈቅዳሉ፣ ይሻሉም፡፡ የዚህ አመለካከት አንዱ መገለጫ በእግዚአብሄር ጥበብ ላይ መደገፍ፣ የህይወት ምሪትን በርሱ ላይ ማድረግ ነው፡፡
በሙሴ ዘመን በቀንና በሌሊትም ይሄዱ ዘንድ፥ መንገድ ሊያሳያቸው ቀን በደመና ዓምድ፥ ሊያበራላቸውም ሌሊት በእሳት ዓምድ የሰራውን እግዚአብሔር የተቃውሙና በእርሱ ላይ የተነሱ ጥበብ የጎደላቸው ሰዎች ተቀስፈው ከፊቱ እንደተወገዱ ሁሉ፤ የእግዚአብሄርን ምሪት የተቀበሉት እድሜአቸው ረዝሞ የእግዚአብሄርን ተስፋ በተሰጣቸው ምድር ላይ ተፈጽመው አይተዋል፡፡
”ስሕተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ። የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ ባሪያህን ጠብቅ፤ የዚያን ጊዜ ፍጹም እሆናለሁ፥ ከታላቁም ኃጢአት እነጻለሁ። አቤቱ፥ ረድኤቴ መድኃኒቴም፥ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን።” (መዝ.19:12-14)
የዳዊት ልመና ወሳኝ ጉዳዮችን የዳሰሰ እንደነበር ማስተዋል ይገባናል፡፡ ምክኒያቱም የእግዚአብሄር ፊት እንዲገለጥ ወይም እንዲሰወር ምክኒያት የሚሆነውን ዋና ጉዳይ ስለሚያነሳ ነው፡፡
የእግዚአብሄርን ፊት ማየት የሚወዱ በፊቱ መገለጥ ምክኒያት የሚሆነውን አሰራር የሚያስተውሉ ናቸው፡፡ እነዚህ የእግዚአብሄር ሰዎች ከሚጠብቁዋቸው በጎነቶች መሀል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፡-
1. በፊቱ ብርሃን መጎብኘት
የአምላካችን የፊቱ ብርሀን የደስታችን፣ የምህረታችንና የበረከታችን ምንጭ ነው፡፡ እግዚአብሄር እኮ ተዋጊ ሃያል ብቻ ሳይሆን መሸሸጊያ አምባም ነው፡፡ እጅግ የበዙ የጠላት አሰራሮች ሲያደክሙን፣ ሲወጉንና ሞት አፋፍ እስክንደርስ ሲገፉን እግዚአብሄር ደርሶ በላያቸው ፊቱን ያበራል፣ ገለል ያደርጋቸውማል፡፡ ጠላቶቻችንን ከላያችን ካባረረ በሁዋላ ግን በዙሪያችን ሆኖ ይጠነቀቅልናል፡፡
መዝ.4:6-8” በጎውን ማን ያሳየናል? የሚሉ ብዙ ናቸው። አቤቱ፥ የፊትህ ብርሃን በላያችን ታወቀ። በልቤ ደስታን ጨመርህ፤ ከስንዴ ፍሬና ከወይን ከዘይትም ይልቅ በዛ። በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም፤ አቤቱ፥ አንተ ብቻህን በእምነት አሳድረኸኛልና።”
እግዚአብሄርን የሚያውቁ ፊትህ ይብራልን ሲሉ ይለምናሉ፡፡ በፊቱ መብራት ምክኒያት የሚወርደውን ሞገስ ሊቀበሉና ከምህረቱ የተነሳ በመገኘቱ ውስጥ ሊመላለሱ ተመኝተው ፊቱ እንዲያበራላቸው በዚያ መንገድ ይለምኑታል፡፡ ዳዊት በንጉስ ሳኦል በደረሰበት መከራ፣ ስደትና ስቃይ ብዛት አምላኩን አላማረረም፤ ዘወትር ያመሰግናል፣ ይዘምራል፣ ያመልካል፤ በስደት ውስጥም ሆኖ በነፍሱ በረከት ይመላለሳል፣ አምላኩን ስለተማመነ ዘወትር በመከራው ውስጥ እንዳለም የፊቱን ብርሀን ይናፍቅና ይመኛል፡-
መዝ.5:3-8 ”በማለዳ ድምፄን ትሰማለህ፥ በማለዳ በፊትህ እቆማለሁ፥ እጠብቃለሁም። አንተ በደልን የማትወድድ አምላክ ነህና፤ ክፉ ከአንተ ጋር አያድርም። በከንቱ የሚመኩ በዓይኖችህ ፊት አይኖሩም፤ ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ጠላህ። ሐሰትን የሚናገሩትን ታጠፋቸዋለህ፤ ደም አፍሳሹንና ሸንጋዩን ሰው እግዚአብሔር ይጸየፋል። እኔ ግን በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ፤ አንተን በመፍራት ወደ ቅድስናህ መቅደስ እሰግዳለሁ። አቤቱ፥ ስለ ጠላቶቼ በጽድቅህ ምራኝ፤ መንገዴን በፊትህ አቅና።”
የእግዚአብሄር ፊት በርቶ በሰው ላይ ከሚፈጥረው የመንፈስ ደስታ ሌላ በህይወት ውስጥ የሚገልጠው ሰማያዊ መንገድ እስከ ዘላለም ይመራል፡፡ የእግዚአብሄር አገልጋይ ያን አሰራር ስለሚረዳ ሁልጊዜ እግዚአብሄርን ከማሳሰብ አያቆምም፡፡ ንጉሱበመዝ.16:11 ሲያስታውስ፡-
”የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን አጠገብኸኝ፥ በቀኝህም የዘላለም ፍሥሐ አለ።” ብሎአል፡፡
በእግዚአብሄር መገኘት የረካ የደስታና የምስጋና ድምጽ የማያወጣው እንዴት ነው? ልቡ ከሞላው ፍሰሃ ሞልቶ የሚፈሰው ምስጋናና አምልኮ መሆን ነው ያለበት፡፡ አይናችን ዘወትር ወደ አምላካችን ቢሆን ምስጋናችን የተትረፈረፈ፣ እምነታችን የበዛ በሆነ ነበር፡፡ በእግዚአብሄር ፊት ሆነን፣ ምህረቱ ከብቦንና በጎነቱ ተንከባክቦን ከውስጥ ከነፍሳችን የደስታ ምስጋና ባናወጣ የእኛን ስንፍና ከመግለጥ ውጪ የተረፈ ነገር ምን ሊኖር ይችላል?
2. የፊቱን መሰወር አስተውሎ የንሰሀ ጸሎት ማቅረብ
የእግዚአብሄርን ማንነት የሚያውቁ ባሪያዎቹ የእግዚአብሄር ፊት ተገልጦ ሲያዩ እንደሚደሰቱ ሁሉ ፊቱን ሲያከብድባቸው ወይም ሲሰውርባቸው ፈጥነው ይነቃሉ፤ ለምህረትም ወደ እርሱ ይጮሀሉ፡፡ የእግዚአብሄር ፊት ከተሰወረ ሞገሱ ይሰወራልና በእርግጥም ላስተዋለው ያስፈራል፡፡ እግዚአብሄር ፊቱን ሲሰውር ጠላት ተገልጦም መስራት ይጀምራል፤ ብርሀን ሲሰወር ጨለማ አካባቢውን እንደሚቆጣጠር ሁሉ፡፡
” ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር። (መዝ.13:1-2) አቤቱ፥ እስከ መቼ ፈጽመህ ትረሳኛለህ? እስከ መቼስ ፊትህን ከእኔ ትሰውራለህ? እስከ መቼ በነፍሴ እመካከራለሁ? ትካዜስ እስከ መቼ ሁልጊዜ ይሆናል? እስከ መቼ ጠላቴ በላዬ ይጓደዳል?”
የእግዚአብሄር ፊት ተሰወረ ማለት የህይወት አጥር ላላ ፈረሰም ማለት ነውና አስደንጋጭ ይሆናል፤ በነፍስ ላይ የተገነባው ደስታ ተፈረካክሶ በትካዜ ይዋጣል፡፡ በእግዚአብሄር መሰወር ምክኒያት የሚደርስብን መንፈሳዊ ጥቃት ከፍተኛ ነው፤ የማንረዳው ስርአት ውስጥ ያስገባናል፣ መንፈሳዊውን መርህ ጥሰን ልቅ መንፈስ ውስጥ እንገባለን፣ በዚያ አጋንንት ያገኙናል፣ ከከራረምን ይማርኩናል፡፡ በዚህ ዘይቤ ውስጥ በድንጋጤ ተይዞ በውስጥ ማጉረምረም መራመድ መቼም ይከብዳል፡፡ ሰው ስለማያይ አይረዳንም፣ እግዚአብሄርም አይቶ ማጉረምረማችንን አይቀበልም፡፡ እንዲያውም ሰው ከምስጋና ርቆ ማጉረምረም ውስጥ ሲገባ ፈጥኖ የሚጠጋው ጠላት ብቻ ነው፣ እግዚአብሄር ትቶሃል ብሎ፣ አይሰማህም ብሎና ተወው ብሎ ነው የሚመጣው፡፡
መዝ.19:12-14 ”ስሕተትን ማን ያስተውላታል? ከተሰወረ ኃጢአት አንጻኝ። የድፍረት ኃጢአት እንዳይገዛኝ ባሪያህን ጠብቅ፤ የዚያን ጊዜ ፍጹም እሆናለሁ፥ ከታላቁም ኃጢአት እነጻለሁ። አቤቱ፥ ረድኤቴ መድኃኒቴም፥ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን።”
መዝ.25:16-22 ”እኔ ብቻዬንና ችግረኛ ነኝና ፊትህን ወደ እኔ አድርግ ማረኝም። የልቤ ችግር ብዙ ነው፤ ከጭንቀቴ አውጣኝ። ድካሜንና መከራዬን እይ፥ ኃጢአቴንም ሁሉ ይቅር በለኝ። ጠላቶቼ እንደ በዙ እይ፥ የግፍም ጥል ጠልተውኛል። ነፍሴን ጠብቅና አድነኝ፤ አንተን ታምኛለሁና አልፈር። አንተን ተስፋ አድርጌአለሁና የውሃትና ቅንነት ይጠብቁኝ። አቤቱ፥ እስራኤልን ከመከራው ሁሉ አድነው።”
መዝ.27:7-9 ”አቤቱ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን ቃሌን ስማኝ። ማረኝና አድምጠኝ። አንተ ፊቴን እሹት ባልህ ጊዜ፡- አቤቱ፥ ፊትህን እሻለሁ ልቤ አንተን አለ። ፊትህን ከእኔ አትሰውር፥ ተቈጥተህ ከባሪያህ ፈቀቅ አትበል፤ ረዳት ሁነኝ፥ አትጣለኝም፥ የመድኃኒቴም አምላክ ሆይ፥ አትተውኝ።”