ጸጋ የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ (1…)

የእውነት እውቀት

‘’የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቸር ስጦታ አውቃችኋልና፤ ሀብታም ሲሆን፥ እናንተ በእርሱ ድህነት ባለ ጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሀ ሆነ።’’ (2ቆሮ.8:9)
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠው በእግዚአብሄር ፊት ብቁ አድርጎ የሚያቆመንን ጸጋ ሊሰጠን ነበር፤ ጸጋው ዋጋ የማይተመንለት፣ ሰዋዊ ያልሆነ መለኮታዊ ቸር ስጦታ ነው፤ እምነታችንም የሚጸናው ይህን መለኮታዊ ስጦታ በመረዳትና በመቀበል ላይ ነው። ቃሉም ሲናገር፦
‘’እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ።’’ ይላል (ዮሃ.1:16-17)።
ጌታ ኢየሱስ መለኮታዊ ቃል ነበረ፣ ሰውን ይታደግ ዘንድ ግን ሃጢያተኛ ሰውን ሊመስል ተገባው፣ ቃልም ስጋ የመሆኑ ምስጢር በዚህ ነው፤ እርሱ ክብሩን እንዲጥልና በመለኮታዊ ቃልነት ሁሉን የፈጠረ ሆኖ ሳለ የሃጢያተኛውን አዳም መልክ ወስዶ በሰዎች መሃል በባዶነት እንዲመላለስ መሆኑ አንድ በምድራዊ ሰዎች ላይ ጥገኛ የሆነ ተራ ሰው ነበር ያስመሰለው፤ እርሱ ግን የተጠጉትን ሁሉ የጽድቅ ባለጠጋ የሚያደርግ አማኑኤል ነበር፤ ሆኖም ይህች ምድር በበጎ ተቀብላ አላስተናገደችውም። እርሱ ግን ለተቀበሉትና በስሙ ለሚያምኑ ሁሉ በዳግም ልደት የእግዚአብሄር ልጆች እንዲሆኑ በማድረግ የጸጋ አሰራሩን ለሁሉ ያካፍላል።
‘’በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።’’ (ዮሃ.1:10-13)
በእኛም ትውልድ እግዚአብሄር ታላቅ እውቀት የሆነውን የጸጋ መረዳትና ምንነቱን የሚያሳውቀውን እውቀት እንዲገለጥልን ይሻል፡፡ ምክኒያቱም እኛን ከሚያደቅቀው አለማዊ አመጽና ከክፉ መናፍስት እስራት ሊነጥቀን የሚችልበት አሰራር እርሱ ብቻ ስለሆነ ነው። በጸጋው ጉልበት ብቻ ነጻነታችን ስለሚረጋገጥ ከሃጢያት ነጻ የሆነ ማንነት ይዘን እንድንቆም ይህን ልንቀበል ግድ ይሆናል። በዚህ መረዳት በመቅረብ ጸጋን ስንለምንም እግዚአብሄር በቸርነቱ ይሞላናል።
‘’አሁንም ጸጋን ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔርን ለምኑ፤ ይህ ከእጃችሁ የተሰጠ ሲሆን ከቶ ፊታችሁን ይቀበላልን? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።’’ (ሚል.1:9)
የእግዚአብሄር ጸጋ የሚፈለግ ነው፤ ይህን የሚያውቅ ጌታ ስለጸጋው ባህሪና አሰራር እንድናውቅ እንዲሁም በህይወታችን ተገልጦ እንዲሰራ ፈቃዱ ነው፡፡ በእግዚአብሄር ያመንን የእግዚአብሄር ጸጋ እንዲመጣና በህይወታችን እንዲሰራ ከፈቀድን ያለ ጥርጥር ለውጥ በህይወታችን ይፈጠራል፡፡ በመንፈሳዊ ህይወት ልምምድ ውስጥ ጠልቀን ስንገባ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የእግዚአብሄር እርዳታ በጸጋ ውስጥ እንዳለ እናስተውላለን፡፡ የእግዚአብሄር ታላቅነትና የአሰራር መንገዱ ያለው በጸጋ ውስጥ ነው፡፡ መረዳታችን ሲያድግ ይህን ማወቅ ብቻ ሳይሆን መፈለግም እንጀምራለን፡፡ ይህን ያስተዋለ ሃዋርያ ወገኖችን ለጸጋው አደራ ሲሰጥ እንመለከታለን፦
‘’አሁንም ለእግዚአብሔርና ያንጻችሁ ዘንድ በቅዱሳንም ሁሉ መካከል ርስትን ይሰጣችሁ ዘንድ ለሚችል ለጸጋው ቃል አደራ ሰጥቻችኋለሁ።’’ ይላል (ሃስ. 20:32)።
ወደ እግዚአብሄር የቀረበ ህይወት ጸጋ ይቀበላል፣ እንዲቀበል ግን ከእግዚአብሄር ዘንድ ሊሞላለት የሚያስፈልገው ጉድለት እንዳለው ሲያውቅ ብቻ ነው። አማኞች በዚያ መረዳት ውስጥ አብዝተን ስንሆን በእግዚአብሄር ክብር ጥማት ተይዘንና የአቅማችንን ድካምና ጎዶሎነት መሙላት ሽተን ስለሚሆን በብርቱ ፍለጋ ውስጥ ልንገባ እንችላለን፤ በዚያ ግፊትም በጸጋው ሙሉነት ህይወታችንን ልናደላድል በብርቱ እንጠማለንን፡፡ ደስታ የሚሰጠውም ነገር እግዚአብሄር የሚያበቃ ጸጋ እንዳለው ማመናችን ነው፣ ደግሞ እርሱ ወዳየው የመንፈሳዊ ህይወት አቅጣጫ አትኩሮ መገስገስ ወደ ከፍታ የሚያደርስ እውነት ነው። ይህንን የሚያህል ትልቅ መሻት በስተመጨረሻ ሊፈጽምልን ችሎታ ያለው የእግዚአብሄር ቸር ስጦታ የሆነ ጸጋው በመሆኑ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት መቅረብ ይገባል።
‘’ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን እንደዚያው አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ሞተዋልና፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የሆነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዛ። አንድ ሰውም ኃጢአትን በማድረጉ እንደ ሆነው መጠን እንደዚያው ስጦታው አይደለም፤ ፍርድ ከአንድ ሰው ለኵነኔ መጥቶአልና፥ ስጦታው ግን በብዙ በደል ለማጽደቅ መጣ። በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ። እንግዲህ በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኵነኔ ወደ ሰው ሁሉ እንደ መጣ፥ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ ምክንያት ስጦታው ሕይወትን ለማጽደቅ ወደ ሰው ሁሉ መጣ።’’ (ሮሜ.5:16-20)
አግዚአብሄር በጠራን ጊዜ ስለ ደካማነታችን ራርቶ ብቻ ዝም ሳይል ከዚያ የድካም ሕይወት የምንወጣበትንና ወደ እርሱ መገኘት ውስጥ የምንገባበትን ሀይል በጸጋው አማካይነት ሊሰጠን ፈቅዶአል፡፡ በእርሱ አሰራር ከኃጢአት አርነት በጸጋው ስለወጣን በጽድቅ ለእግዚአብሔር በተገዛ ህይወት እንድንኖር አስችሎናል፣ የዚህም መጨረሻ የዘላለም ሕይወት ወራሽ የሚያደርግ ነው።
‘’የኃጢአት ባሪያዎች ሳላችሁ ከጽድቅ ነፃ ነበራችሁና። እንግዲህ ዛሬ ከምታፍሩበት ነገር ያን ጊዜ ምን ፍሬ ነበራችሁ? የዚህ ነገር መጨረሻው ሞት ነውና። አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው። የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።’’ (ሮሜ.6:22-25)
ጸጋ ለሰው ሁለንተናዊ ጉድለት (በተለይ በመንፈሳዊው በኩል ላለው) ሙላትን የሚሰጥ በእግዚአብሄር ብቻ የሚሰጥ ነጻ መንፈሳዊ ስጦታ ነው፡፡ በእግዚአብሄር መጽሃፍ ውስጥ “የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቸር ስጦታ ” ተብሎ እንደተጠራ ሁሉ ጸጋን የሚሻ ሁሉ ወደዚህ ቸር ጌታ በእምነት መቅረብ ይገባዋል፡፡ ጸጋ ሊቀበል የተራበ ሰው ይህን ጌታ ወዳጁ፣ አባቱና አምላኩ ያደርግ ዘንድ ይገባል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ በጸጋ ባለጠጋ ነው፡፡ እኛ ደግሞ ሁሉን በጠላት የተነጠቅን፣ በከሰረ መንፈሳዊ ህይወት የምንኖርና በመንፈስ የተራቆትን ምስኪኖች ነን፡፡ ይህንን የሚያውቅ አምላክም የእኛን የተራቆተ ማንነት ካስወገደልን በሁዋላ ከመንፈስ ሀብቱ መንፈሳዊ ህይወታችንን መሙላት ይጀምራል፡፡
‘’በክርስቶስ ኢየሱስ ስላመናችሁ በተሰጣችሁ በእግዚአብሔር ጸጋ ምክንያት ሁልጊዜ ስለ እናንተ አምላክን አመሰግናለሁ፤ ለክርስቶስ መመስከሬ በእናንተ ዘንድ እንደ ጸና፥ በነገር ሁሉ በቃልም ሁሉ በእውቀትም ሁሉ በእርሱ ባለ ጠጎች እንድትሆኑ ተደርጋችኋልና። እንደዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ ስትጠባበቁ አንድ የጸጋ ስጦታ እንኳ አይጎድልባችሁም፤ እርሱም ደግሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ያለ ነቀፋ እንድትሆኑ እስከ ፍጻሜ ድረስ ያጸናችኋል። ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው። ‘’ (1ቆሮ.1:4-9)
ጸጋ በእግዚአብሄር ዘንድ ያለ የተተርፈረፈ የመንፈስ ሀብት በመሆኑ መንፈሳዊ ልጆቹ የተራቡትን ባለጠግነት በጸጋው አድርጎ ይሞላቸዋል፡፡ ጌታ እኛን ሃብታም ሊያደርገን እርሱ ደሀ ሆነ፣ ሙሉ ሲሆን ጎደሎ መሰለ፣ መስጠት የሚችል ሆኖ ሳለ ለመነ፣ የሚያውቅ ሆኖ ሳለ ጠየቀ፣ የሚያጠግብ እንጀራ ሆነ ሳለ ተራበ፡፡ ጌታ ምድር ላይ ተገኝቶ በየትኛው የከበረ ሕይወት ተመላለሰ? የትኛው ወገኑ ተቀበለው? በጌትነቱ ስንቱ አከበረው? ስለማነቱ ማን ተሙዋገተለት? በዙፋኑ ዙርያ ያለ እጅግ ድንቅ ክብሩን በዚያ ትቶና እኛ ሀጢያተኞችን መስሎ በተጓዝንበት የሚያደክም መንገድ ተጓዘ፣ እንደበላነው በላ፣ እንደጠጣነው ጠጣ፣ እንደተንከራተትነውም ተንከራተተ፡፡ እኛ በህግ እንደኖርን፣ የህግ ባሪያዎች እንደነበርንም እርሱም ያን ያይ ዘንድና ከህግ አርነት ያወጣን ዘንድ ከሴት ተወለደ፡፡ ከሴት የተወለደ ሁሉ ከህግ በታችና ከፍርድ በታች በመሆኑ ፍርደኞች መሃል ይገኝና ነጻ ያወጣቸው ዘንድ ከሴት ተወለደ፡፡ ጌታ ስለምን ከሰው ውጪ በሆነ አሰራር ቃሉን ስጋ አያደርግም ነበር? ሰው ማህጸን ውስጥ ማደር ለምን አስፈለገው? የሰውን የአወላለድ ስርአት ተከትሎ ዘጠኝ ወር መጠበቅ ስለምን አስፈለገው? የዚህ አሰራር ሁሉ ምስጢር የእግዚአብሄርን በጎ ውሳኔ የሚገልጥ ነው፡፡ ሰው ተረዳውም አልተረዳው ይህ የእግዚአብሄር የዘላለም አሳብ ነበር፡፡
‘’ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን። በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን። በውድ ልጁም እንዲያው የሰጠን የጸጋው ክብር ይመሰገን ዘንድ ይህን አደረገ። በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት። ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን። በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ፥ የፈቃዱን ምሥጢር አስታውቆናልና፤ በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።’’ (ኢፌ.1:4-10)
የእግዚአብሄር ዘላለማዊ ውጥንና ትኩረት በሀጢያት ባህር ውስጥ የጠለቀችውን ነፍስ እንዴት አውጥቶ እነደሚያነጻትና እንደሚቀድሳት ላይ ያተኮረ ነበርና የጌታ ጭንቀቱ (በቀራንዮ ተሰቅሎ ያሰማው ጩሀቱ) ስራውንና እቅዱን በመከራው፣ በሞቱና በትንሳኤው እንዲፈጽም መወሰኑን ያረጋገጠ ነበር፤ ይህን ድንቅ ስራ የፈጸመው ጌታ ወደ ክብሩ ከተመለሰ ወዲያ እኛን የሚያድንበት ጸጋ በመንፈሱ መፍሰስ በኩል እንድንቀበል አድርጎአል፤ አሁን እርሱ ስለኛ የሚያተኩርበት ነገር የኛ መታጠብና መንጻት ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ያላቀቀንና ያስጣለን ሀጢያት በእኛ ላይ ዳግም ጉልበት እንዳያገኝ ዘወትር በመንፈሱ እኛን በጸጋው ማገዝ ነው፡፡
‘’ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤’’ (ቲቶ.2:11-3)
በመንፈሳዊ ህይወት አንጻር ሲታይ ሰው ጸጋን ብቸኛው የሞትና የየትኛውም መንፈሳዊ ጥቃት ማምለጫ አድርጎ ሊፈልገው፣ ሊቀበለውና በርሱ ሊኖር ያስፈልጋል፤ መንፈሳዊ ተስፋዎችና አሰራሮቹም ጭምር እውን ሆነው የሚታዩት ጸጋ ሲበዛ ብቻ ነውና፡፡ በእግዚአብሄር ቤት ስንመላለስ የእግዚአብሄርን ስራ በማስተዋል እንኖርበት ዘንድ ስራው በጸጋ ተገልጦአል፡፡ እንዲህ በጸጋ ስንሞላ በመንፈሳዊ ህይወት ውስጥ ጠልቀን በመሞላት ያለእንቅፋት፣ ያለድካምና ያለማንከስ በበረከት እንኖራለን፡፡
‘’ለክርስቶስ መመስከሬ በእናንተ ዘንድ እንደ ጸና፥ በነገር ሁሉ በቃልም ሁሉ በእውቀትም ሁሉ በእርሱ ባለ ጠጎች እንድትሆኑ ተደርጋችኋልና። እንደዚህ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ ስትጠባበቁ አንድ የጸጋ ስጦታ እንኳ አይጎድልባችሁም፤ እርሱም ደግሞ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ያለ ነቀፋ እንድትሆኑ እስከ ፍጻሜ ድረስ ያጸናችኋል።’’ (1ቆሮ.1:5-9)
ያም ሆኖ ከእግዚአብሄር ነገር ወደ ኋላ የሚጎትቱን ብዙ ነገሮች እንዳሉ ማስተዋል ይገባናል፣ እነርሱ ግን የመንፈሳዊ ድካሞች ተጽእኖና የጸጋ መጉዋደል ውጤቶች ናቸውና አጥብቀን ልንጠነቀቃቸው ያስፈልጋል፡፡
‘’እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።’’ (እብ.4:16)