ጥርጥር የተስፋ ጠላት ነው
ተስፋ ነገን መመልከቻ መነጽር ነው፤ ተስፋ የሌለውን ነገር እንዳለና ሩቅ ያለንም አቅርቦ መመልከቻ መነጽር ነው፤ ተስፋ በእግዚአብሄር በመታመን ምክኒያት ያደርገዋል ብለን የምንጠባበቅበት መያዣችን ነው። ተስፋ ይመለከታል፣ ተስፋ በልቦና እጅ በመታገዝ ከሩቅ ያለውን ነገር አቅርቦ ይጨብጣል፣ በዚህ ምክኒያት የእግዚአብሄር ህዝብ በመንፈስ እጁን እየዘረጋ የእግዚአብሄር የሆነውን ሁሉ በእምነት ይጨብጣል፣ በእውን እስከሚያገኝ ከእግዚአብሄር ጋር በቃሉ ተስፋ ይጓዛል፤ የሚያሳዝነውና የሚያስደነግጠው ነገር ያለ እግዚአብሄር ተስፋ ህዝብ ካለ ባዶ ህይወትና ምሪት አልባ ነው የሚሆነው። በዘዳ.9:23-29 ላይ ሙሴ ከግብጽ ለወጣው የእስራኤል ህዝብ ይናገራል፣ ንግግሩ እነርሱ ቸል ያሉት የተስፋ ቃል እምነታቸውን እንዴት እንዳስጣለና ድምጹን መለየት እስኪያቅታቸው እንዳራቃቸው የሚያስጠነቅቅ ነበር፦
”እግዚአብሔርም፦ ውጡ የሰጠኋችሁንም ምድር ውረሱ ብሎ ከቃዴስ በርኔ በላካችሁ ጊዜ፥ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ቃል ዐመፃችሁ፥ በእርሱም አላመናችሁም፥ ድምፁንም አልሰማችሁም። እናንተን ካወቅሁበት ቀን ጀምሮ በእግዚአብሔር ዓመፀኞች ነበራችሁ። እግዚአብሔርም፦ አጠፋችኋለሁ ብሎ ስለ ተናገረ በወደቅሁበት ዘመን አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በእግዚአብሔር ፊት ወደቅሁ። በእግዚአብሔርም ፊት እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ በታላቅነትህ የተቤዠኸውን፥ በጠነከረችውም እጅ ከግብፅ ያወጣኸውን ሕዝብህንና ርስትህን አታጥፋ። ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን ያዕቆብንም አስብ፤ የዚህን ሕዝብ ደንዳንነት ክፋቱንም ኃጢአቱንም አትመልከት፤ ከእርስዋ እኛን ያወጣህባት ምድር ሰዎች፦ እግዚአብሔር ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ያገባቸው ዘንድ አልቻለምና፥ ጠልቶአቸውማልና ስለዚህ በምድረ በዳ ሊገድላቸው አወጣቸው እንዳይሉ። እነርሱም በታላቅ ኃይልህ በተዘረጋውም ክንድህ ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸው።”
ተስፋ ግን ጥርጥር በሚባል በሽታ በቀላሉ ይጠቃል፤ ጥርጥር ማመንታትንና ማወላወልን በሰው ልብ ውስጥ ልኮ በእምነት ያየነውን የእግዚአብሄር ቃል ኪዳን ያደበዝዛል፣ ቸል እንድንለው ያደርጋል፣ ያለማመንን ይፈጥራል።
እስራኤል ለምን አላመነም? ወይም ሊያምጽስ ለምን ደፈረ?
የተስፋ ነገር እንዳይጎድልብን ብርቱ ጥረት ያስፈልጋል፤ ብናስበው እኮ እግዚአብሄር በቃሉ የተናገረውን የተቀበልነው፣ እንዳለውም ሊሆንልን የቻለው ቃሉን ተስፋ አድርገን ስላመንን ብቻ ነው፣ የሚያምኑ ተስፋ ያደርጉታል፣ ባለው ልክ ይቀበሉታልና። ይህን የሚያጠፋና የሚያኮስስ ጥርጥር የሚባል ክፉ ነገር ግን ሁሉን ያሳጣል።
እስራኤልን እንመልከት፦ ተጉዋዙ በግፊት ነው፣ ተቀመጡ በግፊት ነው፣ ብሉ በግፊት ነው… ምንም በፈቃዳቸው የሚያደርጉት ነገር አልነበረም። ሙሴ ለዚህ ህዝብ፦ እነሆ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ምድሪቱን በፊትህ አድርጎአል፤ የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር እንዳለህ፥ ውጣ፥ ውረሳት፤ አትፍራ፥ አትደንግጥም አላቸው። ቢታዘዙ ኖሮ እነዚህን የሚያህሉ ጉትጎታዎች እምነታቸውን ሊያበረቱና ጥርጥራቸውን ሊሰብሩ የሚችሉ ነበሩ።
ሙሴ ግን አጽንቶ እየተ`ናገረ ነበረ፤ እነርሱ ተስፋ እንዳላደረጉና ጥርጥር እንዳበዙ መጠንም በነርሱ ላይ የሚመጣው ክፉ መሆኑን አመልክቶአል፦
ዘዳ.1:29-36 ”እኔም አልኋችሁ፦ አትደንግጡ፥ ከእነርሱም አትፍሩ፤በፊታችሁ የሚሄደው አምላካችሁ እግዚአብሔር፥ እናንተ ስታዩ በግብፅና በምድረ በዳ እንዳደረገላችሁ ሁሉ፥ ስለ እናንተ ይዋጋል፤ ወደዚህም ስፋራ እስክትመጡ ድረስ በሄዳችሁበት መንገድ ሁሉ፥ ሰው ልጁን እንዲሸከም አምላክህ እግዚአብሔር እንደተሸከመህ አንተ አይተሃል። ዳሩ ግን ለሰፈራችሁ የሚገባውን ስፍራ እንዲፈልግላችሁ፥ ትሄዱበት ዘንድ የሚገባውንም መንገድ እንዲያሳያችሁ ሌሊት በእሳት፥ ቀን በደመና በፊታችሁ በመንገድ ሲሄድ የነበረውን አምላካችሁን እግዚአብሔርን በዚህ ነገር አላመናችሁም። እግዚአብሔርም የቃላችሁን ድምፅ ሰምቶ ተቆጣ። ለአባቶቻችሁ እሰጣት ዘንድ የማልሁላቸውን መልካሚቱን ምድር ከእነዚህ ሰዎች ከዚህ ክፉ ትውልድ ማንም አያይም፥ከዮፎኒ ልጅ ከካሌብ በቀር እርሱ ግን ያያታል፤ እግዚአብሔርን ፈጽሞ ተከትሎአልና የረገጣትን ምድር ለእርሱ ለልጆቹም እሰጣለሁ ብሎ ማለ።”
ሙሴ ሲናገር ልብ ብሎ የሰማው፣ የተቀበለውና ያመነው ካሌብ ከአርባ ረጅም ዘመናት በኋላ ተስፋውን የጨበጠው ባለመጠራጠሩ ነበር።
ጥርጥር የመዳን ጠላት ነው
ተጠራጥሮ የማይጣል ነገር የለም፣ ከእጅ የማይወድቅ የጸና የነበረ፣ እንዲሁም ተማምነውት የነበረ ሳይቀር መጥፋቱ እውነት ነው። በጥርጥር ብርቱ ፍትጊያ ልብ ስለሚዝልና እምነት ስለሚጠፋ ነገሩን የሚያከብድ ነው። መዳንም ቢሆን እንዲሁ።
መዳን ግን በብዙ ተስፋ የጸና የእግዚአብሄር ስጦታ ሆኖ ሳለ ይህን የሚያስጥል የከፋ አሳብ ውስጣችንን ከተቆጣጠረ እምነታችን መውደቁ አይቀርም። የሚጠራጠር ሳይሆን የሚያምን ሰለአምላኩ ማዳን ያበስራል፣ ይናገራል፣ ያምናል፤ ከተጠራጠረ ግን በእምነቱ ስለማይጸና ልቡን ሞልቶ መናገር ይሳነዋል።
ሮሜ.10:15-21 ”መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ? ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ፦ ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአልና። እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። ዳሩ ግን፦ ባይሰሙ ነው ወይ? እላለሁ። በእውነት፦“ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ። ነገር ግን፦ እስራኤል ባያውቁ ነው ወይ? እላለሁ። ሙሴ አስቀድሞ፦“እኔ ሕዝብ በማይሆነው አስቀናችኋለሁ በማያስተውልም ሕዝብ አስቆጣችኋለሁ ብሎአል። ኢሳይያስም ደፍሮ፦“ላልፈለጉኝ ተገኘሁ፥ ላልጠየቁኝም ተገለጥሁ“ አለ። ስለ እስራኤል ግን፦ ቀኑን ሁሉ ወደማይታዘዝና ወደሚቃወም ሕዝብ እጆቼን ዘረጋሁ ይላል።”
እዚህ ላይ ቃሉን የሰሙ ሆነው ሳለ ማመንና መዳን የማይችሉበትን በእንቅፋት የተሞላ አካሄድ ተከትለው ሲሄዱ እናያለን፦ ወንጌልን የሰሙ መስማትስ ሰምተው ነበር፣ ልባቸው ውስጥ አድሮ ከነፍስ መሻታቸው ጋር ሊዋሃድ፣ ፈቃዳቸውን ደግሞ ሊያሸንፍ ያልቻለበት ዋና ነገር ጥርጥር በወለደው ያለመታዘዝና ተቃውሞ መሸነፋቸው መሆኑን እንመለከታለን።
ጥርጥር መሆን የሚችልን እንደማይሆን አድርጎ ያፈርሳል፤ ጥርጥር ሙሉ የሆነ ተስፋን ባዶ ያደርጋል። በተለይ በቃሉ ላይ ሰው እንዳይደገፍ አድርጎ ከእምነት ሲያስወግድ የነፍስ ክሳትን ያመጣል።
ከዚህ በተለየ መንገድ ተስፋን የሚያስጥል ነገር በንጉስ ሄሮደስ ላይ ሲወድቅ በሚከተለው ቃል ውስጥ እናያለን፤ ሄሮድስ ጨካኝ ንጉስ እንደነበር ታሪኩ ያስረዳል። ይህ ሰው በአጋጣሚ ወንጌል በተጀመረበት ዘመን ላይ ስለነበረ መልካሙን የምስራች ይሰማ ዘንድ ታድሎ ነበር። ሆኖም በዙሪያው የሚበተኑት ውዥንብሮች ስላጭበረበሩት እንዳይወስን አደናገሩት፦
ሉቃ9:1-9 ”አሥራ ሁለቱንም ሐዋርያት በአንድነት ወደ እርሱ ጠርቶ በአጋንንት ሁሉ ላይ ደዌንም ይፈውሱ ዘንድ ኃይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤ የእግዚአብሔርንም መንግሥት እንዲሰብኩና ድውዮችን እንዲፈውሱ ላካቸው፥እንዲህም አላቸው። በትርም ቢሆን፥ ከረጢትም ቢሆን፥ እንጀራም ቢሆን፥ ብርም ቢሆን ለመንገድ ምንም አትያዙ፥ ሁለት እጀ ጠባብም አይሁንላችሁ። በማናቸውም በምትገቡበት ቤት በዚያ ተቀመጡ ከዚያም ውጡ። ማናቸውም የማይቀበሉአችሁ ቢሆኑ፥ ከዚያ ከተማ ወጥታችሁ ምስክር እንዲሆንባቸው ከእግራችሁ ትቢያ አራግፉ። ወጥተውም ወንጌልን እየሰበኩና በስፍራው ሁሉ እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር። የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም የተደረገውን ነገር ሁሉ ሰምቶ፥ አንዳንድ ሰዎች፦ዮሐንስ ከሙታን ተነሣ፥ ሌሎችም፦ ኤልያስ ተገለጠ፥ ሌሎችም፦ ከቀደሙት ነቢያት አንዱ ተነሥቶአል ይሉ ስለ ነበሩ አመነታ። ሄሮድስም፦ ዮሐንስንስ እኔ ራሱን አስቈረጥሁት፤ ይህ እንዲህ ያለ ነገር የምሰማበት ማን ነው? አለ። ሊያየውም ይሻ ነበር። ”
ሄሮድስ ምድሩ ላይ የወጣውን የህይወት ቃል በጨረፍታ ስለሰማ የመማረክ አዝማምያ አሳይቶአል፤ ነገር ግን ክያንዳንዱ የእምነት ጎራ የሚወረወረው ባዶ እውቀት እውነትን አስረግጦ እንዳያምንና ውስጡ እንዳያስገባ ማመንታት ፈጠረበት፣ በትክክለኛው እውቀት ላይ እንዳይርፍም የሃሰት አስተማሪዎች አጭበረበሩት።
ጥርጥር የእውቀት ጠላት ነው
ዮሐ.14:5-12 ”ቶማስም፦ ጌታ ሆይ፥ ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን? አለው። ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። ከአሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል አለው። ፊልጶስ፦ ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው። ኢየሱስም አለው፦ አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ፦ አብን አሳየን ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል። እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ባይሆንስ ስለ ራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ። እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፥”
የሃዋርያት የልብ ማመንታት ከጥርጣሬ የተነሳ መሆኑ ያስታውቃል፦ ጌታ ኢየሱስ ስለራሱ በብዙ ስፍራና ጊዜ ስለተናገረ ስለርሱ መታወቅ ያለባቸው ነገሮች ግልጥ ሆነው በውስጣቸው ሊታመን ተገቢ ነበር። ግን እነርሱ ወደ ሁዋላ የቀሩ ነበሩ፤ ከማመን የዘገዩም ነበሩ፤ እንዳያምኑና በሙሉ ልብ እንዳይከተሉት ሁሌ ሲያውካቸው የነበረው የራሳቸው የጥርጣሬ አመለካከት ነበር።
ህዝቡ በአጠቃላይ ብዙ ጊዜ ከሚናገራቸው ቃል ይልቅ ግምታችውን ሲናገሩ ይታያሉ፦ ከሰማይ ስለመውረዱ ነገራቸው፣ እኛስ አናቅህምን? አንተ የማርያምና የዮሴፍስ ልጅ አይደለህምን? ወንድሞችና እህቶችህስ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደለምን? እያሉ በቃሉ እንደማይታመኑ ያረጋግጡ ነበር። ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ፣ ስጋዬን የበላ ደሜንም የጠጣ የዘላለም ህይወት ያገኛል ሲል ይህ ሰው እንዴት ስጋዬን ብሉ ይላል እያሉ በብዙ ጥርጣሬ ሰማያዊውን እውቀት ሲገፉ ነበር። በመንፈሳዊ እውቀት ዙርያና እምነት አካባቢ እንዴት ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄ ብዙም መልስ አያገኝም፣ ነገሩ በእምነት ማየትንና መስማትን ስለሚፈልግ። አንድ የእስራኤል መምህር በትምህርቱ የእግዚአብሄርን እውቀት ሲጋፋ የሚያሳይ ክፍል በዮሐ.3 ውስጥ ይገኛል፡-
”ከፈሪሳውያንም ወገን የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ፦
መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው።ኢየሱስም መልሶ። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው።ኒቆዲሞስም። ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው።ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል። እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው።ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ።ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው።ኒቆዲሞስ መልሶ፦ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? አለው።ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?እውነት እውነት እልሃለሁ፥ የምናውቀውን እንናገራለን ያየነውንም እንመሰክራለን፥ ምስክራችንንም አትቀበሉትም። ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው።”
ይህ ሰው መንፈሳዊ መምህር ይሁን እንጂ የእግዚአብሄርን አሰራር የተረዳ ሰው ስላልነበር ተጠራጣሪ ነበር። አነጋገሩም ያን ይመስክራል፤ ከዚህ አመለካከቱና እምነቱ የምንማረው ለእግዚአብሄር እንዴት ይሆናል? እንዴት ይቻላል? የሚሉ የውስጥ ጥርጣሬን የሚገልጡ ጥያቄዎች ስናወጣ ሞገስ እናጣለን።
በሰማይ እውቀት ላይ መጠራጠር መዳን ላይ እንቅፋት መሆን ማለት እንደሆነ የአይሁድን ክርክር በማየት ማስተዋል ይቻላል፦
ዮሐ.6:32-40 ”ኢየሱስም፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ እውነተኛ እንጀራ ከሰማይ የሚሰጣችሁ አባቴ ነው እንጂ ከሰማይ እንጀራ የሰጣችሁ ሙሴ አይደለም፤ የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና አላቸው። ስለዚህ፦ ጌታ ሆይ፥ ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም። ነገር ግን አይታችሁኝ እንዳላመናችሁ አልኋችሁ። … እንግዲህ አይሁድ፦ ከሰማይ የወረደ እንጀራ እኔ ነኝ ስላለ ስለ እርሱ አንጐራጐሩና፦ አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው ይህ የዮሴፍ ልጅ ኢየሱስ አይደለምን? እንግዲህ፦ ከሰማይ ወርጃለሁ እንዴት ይላል? አሉ። ኢየሱስ መለሰ አላቸውም፦ እርስ በርሳችሁ አታንጐራጕሩ። የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሁሉም ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ ተብሎ በነቢያት ተጽፎአል፤ እንግዲህ ከአብ የሰማ የተማረም ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል።”
የሰው ጥርጥር የእግዚአብሄርን እውነት ባይሽርም ሰውን ግን በጥርጥር ከዘላለም ህይወት ያርቃል። ጌታ ትምህርቱ ወደ ዘላለሙ መንግስት የሚያስገባ ብቸኛ እውቀት መሆኑን ስለሚያውቅ ንግግሩን ቀጥሎ ነበር፦
ዮሐ.6:48-60 ”የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ። አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ ሞቱም፤ሰው ከእርሱ በልቶ እንዳይሞት ከሰማይ አሁን የወረደ እንጀራ ይህ ነው። ከሰማይ የወረደ ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፤ ሰው ከዚህ እንጀራ ቢበላ ለዘላለም ይኖራል፤ እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው። እንግዲህ አይሁድ፦ ይህ ሰው ሥጋውን ልንበላ ይሰጠን ዘንድ እንዴት ይችላል? ብለው እርስ በርሳቸው ተከራከሩ። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ በራሳችሁ ሕይወት የላችሁም። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፥ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሣዋለሁ። ሥጋዬ እውነተኛ መብል ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና። ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ። ሕያው አብ እንደ ላከኝ እኔም ከአብ የተነሣ ሕያው እንደምሆን፥ እንዲሁ የሚበላኝ ደግሞ ከእኔ የተነሣ ሕያው ይሆናል። ከሰማይ የወረደ እንጀራ ይህ ነው፤ አባቶቻችሁ መና በልተው እንደ ሞቱ አይደለም፤ ይህን እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ይኖራል፤ በቅፍርናሆም ሲያስተምር ይህን በምኵራብ አለ።ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎች በሰሙ ጊዜ፦ ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል? አሉ።
ስጋዊ እውቀት የሰው ስጋ እንደማይበላ ያሳውቀናል፣ እንኩዋን የሰው የእንስሳም ደም እንደማይጠጣም እንዲሁ፤ ይህ ግን አንድ ነገር ነው፤ ችግሩ የሚፈጠረው ወይም የጥርጣሬው ምንጭ የሚመጣው ሰማያዊው ትምህርት (የክርስቶስን ስጋ መብላት፣ ደሙን መጠጣትና የዘላለም ህይወት ትምህርት) ከምናውቀው እውቀት ጋር በልዩነት ሳናየው ሲቀር፣ ክርስቶስ ቃሉ መለኮታዊ እንደሆነ ሳይታመን ሲቀርና እርሱ እኮ እንደኛ መሃላችን ከሚገኙ ከእናቱና ከአባቱ የተወለደ አንድ ተራ ሰው ነው የሚል የተሳሳተ አመለካከት ሲያዝ እምነትን በሞላ የሚጠፋ መሆኑ ነው። እነርሱም በስጋ እውቀታቸው የተናገረውን ሊቀበሉ ስለቸገራቸው፦ ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል? አሉ።
እውቀቱም ላይ ተመሳሳይ አመለካከት ነበራቸው፤ ጌታ ትምህርት ቤት ገብቶ ሲማር አላዩትም፣ ከነብያት ቤተሰብ እንዳልተወለደም ያውቃሉ፤ ሆኖም የነቢያት ድምጽ አልነበራቸውም፣ መምህራኖቻቸውም ሰማያዊ እውቀት የሚያስጨብጡ ወይም የነብያትን ድምጽ የሚያሰሙ ሳይሆኑ ምድራዊ ስርአት ላይ ያተኮሩ ስለነበሩ ህዝቡን በብዙ አስተው ነበር፤ ስለዚህ ሲጠይቁና ሲፈልጉ እንኩዋን ከሞገስ ውጪ በሆነ አካሄድ የሚያደርጉት ነበረ፦
ዮሐ.7:10-16 ”ወንድሞቹ ግን ወደ በዓሉ ከወጡ በኋላ በዚያን ጊዜ እርሱ ደግሞ በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ወጣ። አይሁድም፦ እርሱ ወዴት ነው? እያሉ በበዓሉ ይፈልጉት ነበር። በሕዝብም መካከል ስለ እርሱ ብዙ ማንጐራጐር ነበረ፤ አንዳንዱም፦ ደግ ሰው ነው፤ ሌሎች ግን፦ አይደለም፥ ሕዝቡን ግን ያስታል ይሉ ነበር። ዳሩ ግን አይሁድን ስለ ፈሩ ማንም ስለ እርሱ በግልጥ አይናገርም ነበር። አሁንም በበዓሉ እኩሌታ ኢየሱስ ወደ መቅደስ ወጥቶ ያስተምር ነበር። አይሁድም፦ ይህ ሰው ሳይማር መጻሕፍትን እንዴት ያውቃል? ብለው ይደነቁ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው። ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም”