• ጥርጥር የእምነት ጠላት ነው።
• ጥርጥር የተስፋ ጠላት ነው።
• ጥርጥር የመዳን ጠላት ነው።
• ጥርጥር የመጎብኘት ጠላት ነው።
• ጥርጥር የሞገስ ጠላት ነው።
• ጥርጥር የምህረት ጠላት ነው።
• ጥርጥር የጽናት ጠላት ነው።
• ጥርጥር የፍቅር ጠላት ነው።
• ጥረጥር የሰላም ጠላት ነው።
• የሚጠራጠር አያምንም፣ ስለማያምን አይጸናም።
• የሚጠራጠር ተስፋ አያደርግም፣ ተስፋ ስለማያደርግ ነገን አያይም።
• የሚጠራጠር መዳን አያገኝም፣ ተጠራጣሪ ስለሆነ በእግዚአብሄር አይጸናምና።
• የሚጠራጠር በእግዚአብሄር አይጎበኝም፣ እግዚአብሄርን በእምነት አይጠራምና።
• የሚጠራጠር ሞገስ የለውም፣ እግዚአብሄር ከእርሱ ሩቅ ነውና።
• የሚጠራጠር ምህረት አያገኝም፣ መሃሪውን አምላክ አላመነምና።
• የሚጠራጠር አይጸናም፣ ስለማያምን አይረጋጋምና፣ ስለማይረጋጋ እርፍ ብሎ መቀመጥ አይችልምና።
• የሚጠራጠር ፍቅር ከቶ አያውቅም፣ ማንንም አያምንም፣ አይቀበልም፣ ልቡ አያስገባም።
• የሚጠራጠር ሰላም የለውም፣ የሚያምነውና የሚደገፍበት እከሌ የሚለው ስለሌለው ብቻውንና ባዶውን ይሰቃያል።
ጥርጥር ክፉ አጥር ነው፦
ጥረጥር የምናነክስበት አምሮአዊ ጉድለትና ውሳኔ በሚል አንጻር ብናየው ራሳችንን ወደ እግዚአብሄር እንዳናስጠጋ አጥሮ ያስቀመጥን እንቅፋት እንደሆነ እንገነዘባለን፤ ጥርጥሩ ለእግዚአብሄር ሳይሆን ለጠላት ዲያቢሎስ ያጋልጣል፣ እግዚአብሄርን ሲያርቅ ለዲያቢሎስ በር ይከፍታል። ጥርጥር ሁል ጊዜ መጥፎ መጥፎውን ያሳስባል፣ ማመንታት ይፈጥራል፣ ይሆናልን እያየ አይሆንምን ያሳያል። ጥርጥር ወደ ትዳር ውስጥ ሲገባ የተጋቢዎችን ጥምረት እያላላና እያሳሳ ወደ ማፍረስ ያደርሳል፣ በጥርጥር ብዙ ጥቅሞች ስለሚጠፉ ህይወትን ያናጋል፣ ህይወቱ የተናጋ ሰውም ስነልቦናው በብርቱ ይጎዳል። ጥርጥር በአማኝ ዘንድ ከሰረጸ መዳንን ያስጥለዋል። ሰው እግዚአብሄርን በምንም መልኩና በየትኛውም ደረጃ ከተጠራጠረ ጠላትነትን ከእርሱ ጋር ይፈጥራል። ጥርጥር አያጸናም፣ ስለዚህ መሃል መንገድ ላይ አስቀርቶ ወደ ሁዋላ ያንሸራትታል። የሚጠራጠር ሰው ለመልካም ነገር አቅም ስለሌለው ክፉ ነገር ያደርጋል፤ የሚጠራጠር ሰላማዊ አይደለምና አመጽ ውስጥ ይገባል።
መጠራጠር እርግጠኛ አለመሆን ነው፤ ሰው በከረመ ተጠራጣሪነት ከተያዘ ድብርት ላይ ይወድቃል። ተጠራጣሪነት በሰዎች መሃል ሲሰፍን አለመተማመን ይፈጠራል። ተጠራጣሪነት ማለት ስለ አንድ ሰው ወይም ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ አለመሆን ማለት ስለሆነ ሰው በዚህ ስሜት ከተወሰደ በሆነው ባልሆነው ነገር በጎ ባልሆነ ስሜት እንዲጨነቅ ይገደዳል። እርግጠኛ አለመሆንም ከእርግጠኝነት የልብ ሙላት አውጥቶ ሙሉ በሙሉ የጥፋተኝነት ድምዳሜ ውስጥ ይከታል። በተለይ የአንድ ነገር ጅማሮን በጥረጣሬ አንድ ካልነው የተለምነው ስኬት/ውጤት ላይ አንደርስም፣ ያም የውድቀት መጨረሻ ያለው ነው የሚሆነው። እኛም ለውሳኔ ስንነሳ ምን ማድረግ እንዳለብን ማሰብና ወደ ተግባር መግባት እንጂ ጭፍን ባለ የጥርጣሬ አሳብ መጨናነቅ ተገቢ አይደለም፤ ያ መንገድ የሰውን መጨረሻ የሃዘን ሊያደርገው ይችላል፤ ምክኒያቱ ደግሞ ጥርጥሩ ውጤቱን በተስፋ እንዳያይ ስለሚያደርግ ነው።
በማመን መፍራት እንዳለ ባለማመን መፍራትም አለ። በማመን መፍራት እግዚአብሄርን በአምላክነቱ፣ በቻይነቱና በሃያልነቱ በማወቅ ይፈጠራል። ያጠፋኝ ይሆን በሚልና አይቀበለኝ ይሆናል በሚል ጥርጥር እግዚአብሄርን ማየት (ነው ማለት) ያለማመን ፍርሃት ያስከትላል። እግዚአብሄር ይህን የጥርጥር ፍርሃት ይጠላል።
እግዚአብሄርን የመጠራጠር ችግር ሰፊና ጥልቅ ነው፦ በዋናነት ስናየው ቃሉን በበጎና እንደመንፈሱ እንዳንተረጉም የሚያደርግ ነው። ችግሩ ታላቅ ነው፣ የነጠረ ቃሉን የጠረጠረ አምላኩን ይጠላልና፤ ከፈቃዱ ጋር ስለሚጋጭ፣ ከማንነቱ ጋር ስለሚጋጭም ጭምር። ችግሩ ግን ከቃሉ አፈንግጦ ሲወጣ እግዚአብሄር ወዳልፈቀደው አቅጣጫ ሰውን በመንዳት ጥፋት ላይ የሚጥል ነው የሚሆነው።
በሌላ በኩል ጥርጣሬ አንድ ነገር ላይ ችግር ይኖራል ከሚል ግምት በመነሳት የሚፈጠር ስጋት ነው። አንድ ነገር ስናስብ ሆኖ ማየት የምንፈልግበት መንገድ አለ፣ ውጤቱ እንዲሆን የምንመኘው ነገር ስለሆነ በዚያ አቅጣጫ እንጥራለን፤ አይሆንም የሚል ስጋት በውስጣችን በሚፈጠርበት ጊዜ ግን ስጋቱ ተስፋችንን ያስርና የማይፈለግ አቅጣጫ እንድንከተል ሊያደርግ ይችላል። ጥርጣሬ ከስጋት የተነሳ ግምታዊ ትንበያ እንጂ በመረጃ ላይ ተመስርቶ የተወሰደ ድምዳሜ ስላልሆነ የቆረጠ ውሳኔ ላይ እንዳንደርስ ልባችንን አንጠልጥሎ፣ መንፈሳችንን አውኮና ሰላማችንን አናግቶ ያስቀምጠናል። ጥርጣሬ በአእምሮ የተያዙ ግምቶች እንዲፈልቁ በር ስለሚከፍት፣ ውስጣችን በተለያዩ ያልተጨበጡ አሳቦች እንዲሞላና እንድንረበሽ በር ይከፍታልና እንጠንቀቀው።
በጥርጣሬ ውስጥ ተቀምጦ ሰላም የሚባል ነገር አይታሰብም። በጥርጥር ያለመታመን፣ ባለመታመን ዝግ መሆንና መታፈን(በውስጥ መጨነቅ) ይፈጠራል፤ የተጨነቀ ማመዛዘን አይችልም፦መረበሽና መታወክ ብቻ ነው እንጂ ውጤት የለውም። ይህ ሁኔታ ከቆየ አእምሮን በከፍተኛ ሁኔታ ያናጋል፣ ስነልቦናዊ ችግርም ሊያመጣ ይችላል። ጥርጥር ነገሮች ላይ እርግጠኞች እንዳንሆን ያደርጋል። እርግጠኛ ያለመሆን ብዙ ነገር ይጎትታል፦ በቤተሰባችን እርግጠኛ ካልሆንን፣ በጉዋደኛችን እርግጠኛ ካልሆንን አደጋ አለው፤ እየባሰ ሲመጣ እኮ በራሳችን እንኩዋን እርግጠኛ ላንሆን እንችላለን። ታዲያ ይህ የህይወት መዛባት እንዴት ለጠላት አይመቸው! እንዴት ለጥቃት ሰውን አይሰጥ! እንዴት የሰው ህይወት በጠላት ሊመሳቅል በር አይከፈትለት! ከባድ አደጋ ነው።
ጥርጥር የእምነት ጠንቅ ነው፦ ሰው በእግዚአብሄር ቤት ሲኖር ብዙ ነገር ያያል፣ ይገጥመዋልም። በጎው ነገር ሁሉ ከጠሪው አምላክ ፈልቆ ወደ ልጆቹ ይደርሳል። ግን በእግዚአብሄር ቤት የሚኖር ሁሉ ከፈተና ውጪ ነው ማለት አይደለም፤ መጽናት በሚያስፈልገን ወቅት ሁሉ ከእግዚአብሄር ዘንድ ማለፍ ያለብን ነገር ይመጣል (አንዳቸውም ግን ለክፉ አይሰጡም)፣ በአጋንንት መነሳሳት በኩል የሚላክ ፈተና አለ (ካላስተዋልን ሊጥለንና ከመንገድ ሊያስተን ይመጣል)፣ በእኛው በራሳችን ስጋዊ አካሄድ ምክኒያት የምንጠራው ፈተናም አለ (ያን ግን እንደገባንበት መውጣት ይጠበቅብናል)። ያም ሆነ ይህ በነዚህ ሁሉ ሂደቶች ውስጥ ስናልፍ መረዳቱ ከሌለን እየሆነ ያለውን ስለማናስተውል ማመንታትና ጥርጥር ውስጥ እንገባለን። መጠራጠር በዋናነት በእግዚአብሄር ላይ የሚሆነው ሃላፊነቱን በሙሉ እሱ ላይ በማድረግ፣ እየሆነ ያለውንና የሆነው በርሱ ምክኒያት እንደሆነ በማሰብ እግዚአብሄር ትቶኝ ነው ብለንም ስለምንገምት ነው።
ኢዮ.7:12-21 ”ጠባቂ ታስነሣብኝ ዘንድ፥ እኔ ባሕር ወይስ አንበሪ ነኝን? እኔም፦ አልጋዬ ያጽናናኛል፥ መኝታዬም የኀዘን እንጕርጕሮዬን ያቀልልኛል ባልሁ ጊዜ፥ አንተ በሕልም ታስፈራራኛለህ፥ በራእይም ታስደነግጠኛለህ፤ ነፍሴም ከአጥንቴ ይልቅ መታነቅንና ሞትን መረጠች። ሕይወቴን ናቅኋት፤ ለዘላለም ልኖር አልወድድም። የሕይወቴ ዘመን እስትንፋስ ነውና ተወኝ። ሰው ምንድር ነው ታከብረው ዘንድ፥ ልብህንስ ትጥልበት ዘንድ፥ ማለዳ ማለዳስ ትጐበኘው ዘንድ፥ ሁልጊዜስ ትፈታተነው ዘንድ? የማትተወኝ እስከ መቼ ነው? ምራቄንስ እስክውጥ ድረስ የማትለቅቀኝ እስከ መቼ ነው? ሰውን የምትጠብቅ ሆይ፥ በድዬስ እንደ ሆነ ምን ላድርግልህ? ስለ ምን እኔን ለአንተ ዓላማ አደረግኸኝ? ስለ ምን እኔ ሸክም ሆንሁብህ? ስለ ምን መተላለፌን ይቅር አትልም? ኃጢአቴንስ ስለ ምን አታስወግድልኝም? አሁን በምድር ውስጥ እተኛለሁ፤ ማለዳ ትፈልገኛለህ፥ አታገኘኝም።”
ኢዮብ በድንገት ፈተና ውስጥ ወደቀ። ፈተናው ቢመጣም ግን ከአምላኩ ጋር እንደሆነ ተሰምቶት ነበረና በእግዚአብሄር ጸንቶ ቆመ። ያም በመሆኑ በሚሆነው ነገር ባለመናወጥና በልቡ ጽናት ከሚስቱ የመጣውን የስንፍና ንግግር ገሰጸ፤ ጉዋደኞቹ ያልተገባ አሳብ ባንጸባረቁ ጊዜም ተቃወማቸው። ፈተናው እየተደራረበ፣ እየጠነከረና ስቃዩ እየበዛ ሲሄድ ግን ጥያቄዎች በልቡ ይነሱ ያዙ፤ ቆይቶም በእግዚአብሄር ላይ ጥርጣሬን አመጣ፤ ትቶኝ ይሆናል የሚል ማመንታት ልቡን አስጨነቀው።
ኢዮብ የእግዚአብሄር ፈቃድ በእርሱ ፈተና ውስጥ የሚሰራውን እስኪያስተውል ድረስ ነገሩ ሁሉ እንደጨለመበት ግልጽ ነው፤ ይህ የሰው ልጆች ሁሉ ድካም ነው። እግዚአብሄር በጊዜው ሁሉን ሲያስረዳን ወደ ምስጋና እንገባለን እንጂ በፈተናችን ሰሞን በልባችንና በአንደበታችን የሚመላለሰው ቃል የሚያቆራርጥ ነው፤ እርሱ ግን ድካማችንን የሚያውቅ አምላክ እንደመሆኑ በፈተና ወቅት የምንናገረውን ስንፍና ሳይቆጥር ሁሉን በምህረት ያሳልፈውና ምስጋናን እንደገና ይሞላናል። ቀጥሎ የምናየው ቃል በፈተና ወቅት የኢዮብ ሁኔታ የእምነቱን ድካም እንደተገዳደረው የሚያሳይ ነው ፦
ኢዮ.17:11-16 ”… ዕድሜዬ አለፈች፤ አሳቤና የልቤ መሣርያ ተቈረጠ። ሌሊቱን ወደ ቀን ይለውጣሉ፤ ብርሃኑም ወደ ጨለማ የቀረበ ይመስላቸዋል። ተስፋ ባደርግ ሲኦል ቤቴ ናት፤ ምንጣፌንም በጨለማ ዘርግቻለሁ። መበስበስን፦ አንተ አባቴ ነህ፤ ትልንም፦ አንቺ እናቴ እኅቴም ነሽ ብያለሁ። እንግዲህ ተስፋዬ ወዴት ነው? ተስፋዬንስ የሚያይ ማን ነው? አብረን በመሬት ውስጥ ስናርፍ፥ ወደ ሲኦል ይወርዳል።”
ጥርጥር ከከፍታ አውርዶና አዋርዶ አሳዛኝ ያደርጋል፦ ”ዕድሜዬ አለፈች ብዬ ጠረጠርኩ፤ አሳቤና የልቤ መሣርያ ተቈረጠ ብዬ ደመደምኩ፤ ተስፋ የለኝም፣ ተስፋ ባደርግ እንኩዋን ሲኦል ቤቴ ናት እል ይሆናል እንጂ የቀን ብርሃንን ዳግመኛ እንዴት አያለሁ፤ በቃ ብዬ ደምድሜአለሁና ምንጣፌን አዘጋጅቼ ለሚውጠኝ ጨለማ በሬን ከፍቻለሁ። ህይወት ከእንግዲህ ሰለማይቀጥል ስጋዬን ለሚበላው መበስበስ፦ አንተ አባቴ ነህ አልኩት፤ ትልንም፦ አንቺ እናቴ እኅቴም ነሽ ብያለሁ፣ ከጥፋትም ጋር ተስማምቼአለሁ። እንግዲህ የቀረ ምን ተስፋ አለ፣ ካለስ ወዴት ነው? እግዚአብሄር ትቶኛልና ተስፋዬንስ የሚያይ ሌላ ማን ነው?” ያስብላል።
ጥርጥር የእምነት ጠላት ነው
በመጠራጠራችን ብቻ ብዙ ነገር ልናጣ እንደምንችል ከቃሉ መረዳት የምንችለው እውነት ነው። በተለይ ከእግዚአብሄር ጋር ባለን ጉዞ እርሱን ተጠራጥረነው እንደሆነ በመጠራጠራችን ከፈቃዱ እስከመለየት የሚያደርስ ችግር ውስጥ እንገባለን። የጥርጥር መንፈስ የጠላት መንፈስ ስለሆነ ከሚወደን አምላክ ጨርሶ ያለያየናል።
ሉቃ24:13-26 ”እነሆም፥ ከእነርሱ ሁለቱ በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ያህል ወደሚርቅ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤ ስለዚህም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። ሲነጋገሩና ሲመራመሩም፥ ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ነበር፤ ነገር ግን እንዳያውቁት ዓይናቸው ተይዞ ነበር። እርሱም፦ እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ፥ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሩአቸው እነዚህ ነገሮች ምንድር ናቸው? አላቸው። ቀለዮጳ የሚባልም አንዱ መልሶ፦ አንተ በኢየሩሳሌም እንግዳ ሆነህ ለብቻህ ትኖራለህን? በእነዚህ ቀኖች በዚያ የሆነውን ነገር አታውቅምን? አለው። እርሱም፦ ይህ ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት። በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ፤ እርሱንም የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው። እኛ ግን እስራኤልን እንዲቤዥ ያለው እርሱ እንደ ሆነ ተስፋ አድርገን ነበር፤ ደግሞም ከዚህ ሁሉ ጋር ይህ ከሆነ ዛሬ ሦስተኛው ቀን ነው። ደግሞም ከእኛ ውስጥ ማልደው ከመቃብሩ ዘንድ የነበሩት አንዳንድ ሴቶች አስገረሙን፤ ሥጋውንም ባጡ ጊዜ፦ ሕያው ነው የሚሉ የመላእክትን ራእይ ደግሞ አየን ሲሉ መጥተው ነበር። ከእኛም ጋር ከነበሩት ወደ መቃብር ሄደው ሴቶች እንደ ተናገሩት ሆኖ አገኙት፥ እርሱን ግን አላዩትም። እርሱም፦ እናንተ የማታስተውሉ፥ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤ ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? አላቸው።”
ከዚህ ሁኔታ አስቀድሞ ከደቀመዛሙርት መሃል ስለክርስቶስ ከሙታን መነሳት የሰሙ ነበሩ፣ የሰሙት ግን የተነገራቸውን ቃል ተጠራጥረው ስለነበር ማመንታት ውስጥ ገብተው ነበር። ትንሳኤውን ለሐዋርያት የነገሩአቸው መግደላዊት ማርያምና ዮሐና የያዕቆብም እናት ማርያም ከእነርሱም ጋር የነበሩት ሌሎች ሴቶች ነበሩ። የነገሩዋቸው እውነት ቅዠት መስሎ ታያቸውና አላመኑአቸውም። ነገሩ ጌታ ኢየሱስ ከመሆኑ አስቀድሞ ተናግሮ የነበረውን አምነው ቢሆን ማስተዋል በቻሉ ባልተጠራጠሩም ነበር።
ጌታ በቃሉ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ተናግሮ ነበር፤ ሆኖም በቃሉ ላይ አስተውሎት እንዳነሳቸው ነው የሚታየው፤ ያኔ እየጠወለጉ ከኢየሩሳሌም ወጥተው ሲጉዋዙ ተገኝተዋልና።
ጥርጥር የእምነት ጠላት ስለሆነ ለእስራኤል የመጣውን መድሃኒት እያስጣለ ክፉ ነገር ያመጣባቸው ነበር፤ ጌታ ያን ተመልክቶ ደቀመዛሙርቱ ጥፋት እንዳያገኛቸው ሲል፦ እናንተ የማታስተውሉ፥ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤ ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? አላቸው።