የጌታ ቅዱስ አጠራር ጠሪው አምላክ ቅዱስ መሆኑንና የሚጠራቸው ሰዎችም ቅዱስ እንዲሆኑ እንደሚሻ ያመለክታል።በቅዱስ አጠራር የተጠራ ሰው ለጠሪው ሊለይና እንደተጠራ አስተውሎ ሊዘጋጅ ያስፈልጋል። እንዲሁም ቅዱስ መሆን የማይችል ሰውና ቅዱስ የሆነ አምላክ ህብረት ያደረጉበት መንገድ ላይ ትኩረት ሊያደርግ ተገቢ ነው። ለዚህም ምሪት የሚሆን የእግዚአብሄር አሰራር በቃሉ ላይ ተቀምጦአል።
አህዛብ የተጠራነው በኛ ውስጥ ባለ መልካም አሳብና ስራ ምክኒያት እይደለም። ስራ የሚባል ከእኛ የሚጠበቅ አንዳች የጽድቅ ውጤት በህይወታችን ውስጥ የተቀመጠ ቢሆን ኖሮ ያለፍርድ እግዚአብሄር በተቀበለን ነበር።
ነገር ግን “እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም“ (ቲቶ3:5) ብሎ ደህንነት የተከናወነው በምህረቱ ምክኒያት እንጂ የጽድቅ ስራ ስለነበረን እንዳልሆነ ያስረዳል።
በማስተዋል ስንመለከት የነገሮች ሚዛን የሆነው የእግዚአብሄር ቃል እንደሆነ እንረዳለን። ራሳችንን ከቃሉ ጋር ብናስተያይ ግን ቃሉን ልንመጥን ይቅርና ልናገናዝበው እንደማንበቃ የህይወት ይዘታችን የሚያሳይ ነው።ሆኖም የእግዚአብሄር ፍቅርና ጸጋ በስራችን ምክኒያት የሚገጥመንን ፍርድ ተሻግሮ ከፍ አድርጎናል። ይህን ያደረገው ከእኛ ምንም ብቁ ነገር ባልተገኘበት ሁኔታ ስለሆነ የእግዚአብሄርን አጠራር በማክበር ማስተዋል ያስፈልጋል።
ደህንነት የተባለ የአምላክ ስራ መስቀል ላይ የተፈጸመ የዘላለም አሳቡ ነው። የሰው ልጅ የሚያድነውን ስራ መፈጸም ስላልቻለ እግዚአብሄር ይህን የፍቅር ስራ መስቀል ላይ ሰርቶ አሳይቶአል።በነቢያት ትንቢት እግዚአብሄር የደህንነትን ስራ በክንዱ እንደሚፈጽም ከብዙ መቶ አመታት አስቀድሞ እንደተነገረው ሁሉ ዘመኑ ሲመጣ ለአለም መድሃኒትን ሰጥቶአል። ክንዱም ከቃሉ ያዘጋጀውን ሰውነት (ስጋ) አመልካች ነው።
ዕብ.10:4-6 “የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኃጢአትን እንዲያስወግድ የማይቻል ነውና።ስለዚህ ወደ ዓለም ሲገባ:- መሥዋዕትንና መባን አልወደድህም ሥጋን ግን አዘጋጀህልኝ፤በሙሉ በሚቃጠል መሥዋዕትና ሰለ ኃጢአት በሚሰዋ መሥዋዕት ደስ አላለህም ብሎ እነዚህም እንደ ሕግ የሚቀርቡት ናቸው፥“
እንግዲህ እግዚአብሄር በወንጌል መልእክት ጥሪ (በተዘጋጀው ደህንነት ዳኑ ብሎ) ወደ እርሱ እንድንመጣ መላው የሰውን ልጅ ጋብዞአል። እርሱም እንደስራችንና እንደ ፈቃዳችን ሳይሆን እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ ያደረገው ነው። እኛም በእግዚአብሄር የተጠራን ሁላችን በወንጌል ለመለወጥ፣ የራሳችንን ፈቃድ በእግዚአብሄር ፈቃድ ለማስገዛትና እንደ አጠራሩ ለመኖር መወሰን ይገባናል። ይህን ለማሳካት ስንልም ጥሪውን ማክበርና የተጠራንበትን የተስፋ ቃል በጥንቃቄ መያዝ አለብን። ከዚህ ባልተለየ ሁኔታ ወንጌሉ እንዳይሸቃቀጥ በመጠንቀቅ እርሱ የሚጠይቀውን ህይወት መኖርም ተገቢ ነው።
የኛ ስራ ከእግዚአብሄር ክብር የሚያርቅና ፍርድ ላይ የሚጥል ሲሆን መዳን ግን ወደ ከበረው መንግስቱ የሚያስገባ፣ ከመላእክቱ ጋር ለአምልኮ የሚያቆም፣ የጌታን ክብር የሚያሳይና ዘላለማዊ ህይወትን የሚያሠጥ የእግዚአብሄር ስራ ነው። የእግዚአብሄር ጥሪ የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ስራ ውጤት ነው። በእርሱ የጽድቅ ስራ በደሙ የሃጢያትን ስርየት ለማግኘት ችለናል።ጥሪው ይቅርታን፣ የሃጢያት ስርየትን፣መጽደቅንና መቀደስን አስገኝቶልናል።
በ1ቆሮ.6:9-11 ውስጥ ሲናገር፦
“ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል።“ ይላል።
ወደ ከበረው ግብዣ የሚደረገው ጥሪ ክብሩ ከፍ ያለበት ሌላው ምክኒያት ጠሪው እግዚአብሄር በክብር ከፍ ያለ ቅዱስ አምላክ በመሆኑ ነው።ከርሱ የሚወጣው ከፍ ያለው መለኮታዊ ጥሪ ዝቅ ላለውና በሃጢያት ለተዋረደው ሰው ባይመጥንም ጠሪው ያከበረው በመሆኑ ትልቅ ስፍራና ጥልቅ ክብር ያስፈልገዋል።
2ጢሞ.1:8-11 “…ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን፥አሁን ግን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ ታይቶአል። እርሱ ሞትን ሽሮአልና እኔ ሰባኪና ሐዋርያ አሕዛብንም አስተማሪ እንድሆን በተሾምሁበት በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል።“
እግዚአብሄር የሚጠራው በቃልኪዳኑ ልክ እንጂ በሰዎች ማንነት ልክ አይደለም ወይም ሰዎች በሚኖሩበት የህይወት ደረጃ ልክ አይደለም።የሰውን ልክማ 1ቆሮ.6:9-11 አሳየን አይደል? የእኛ የህይወት ይዘት የደህንነታችን ልክ ቢሆን ኖሮ ወደ ታላቁ ጌታ ማን የመምጣት ብቃት ይኖረው ነበር? ሆኖም በእርሱ የመንፈስ ሃይልና የመለወጥ ብቃት ለሰው ሁሉ መዳን ሆነ።
ዘዳ.33:2-4 “እንዲህም አለ፡-እግዚአብሔር ከሲና መጣ፥በሴይርም ተገለጠ፤ከፋራን ተራራ አበራላቸው፥ከአእላፋትም ቅዱሳኑ መጣ፤በስተ ቀኙም የእሳት ሕግ ነበረላቸው።ሕዝቡንም ወደዳቸው፤ ቅዱሳኑ ሁሉ በእጅህ ናቸው፤በእግሮችህም አጠገብ ተቀመጡ፤ቃሎችህን ይቀበላሉ።“
እግዚአብሄር እኛ ህዝቦቹን ከወደደን እንደተጠራንበት አጠራር መኖር ስልምን ተሳነን?
• ያለመቻል ከልክ በታች ስላደረገን
ያለመቻል ከአቅም በታች የሆነ መንፈሳዊ የህይወት ይዘት ስለሆነ ከእግዚአብሄር ፈቃድ ውጪ በማውጣት ስፍራን ያስለቅቃል(ከስፍራ ያንሸራትታል)። በዘዳ.33:2-4 ላይ እንደምናየው እግዚአብሄር እስራኤልን መውደዱን የነገረው ወደራሱ ክብር መገኛ አስጠግቶት ነው።እስራኤል ግን የመረዳትና እግዚአብሄርን የመከተል አቅም አልነበረውም።ዛሬም እኛጋ እንደ እስራኤል የአቅም ማነስ ነገር ካለ ያለመቻል በሚባል መውረድ ላይ ሆነን መንፈሳዊ ነገሮችን ለመቀበልና ለመለማመድ እንደተሳነን በሃይል እጦት እንንገላታለን (ይህ ግን የስጋ አቅም ማነስ አይደለም)። ድካሙ መንፈሳዊ ህይወታችንንም ያደናቅፋል ፦ያለመጸለይ፣ ያለመጾምና ለፍለጋ ያለመበርታት ይፈራረቁብናል፤ በቃሉ መደገፋችን ይላላል፣ በዚህ ምክኒያትም ብዙ ችግር ይጣበቅብናል። በመቀጠል ቀድሞ የተለማመድነው የመንፈስ እረፍትና ምህረት ሲርቀን ይታወቀናል።በዚህም ባዶነት ተጎድተን ስንላላ በዘመናችን ሊገለጥ ያለ የእግዚአብሄር ፍቃድ ያልፈናል፣ወደ ሁዋላም ያንደረድረናል።
• ልማድን ያለመተው ስላራቀን
እግዚአብሄር የማይቀበለው ልምምድ ካልተሻረ እርሱ ወደ ወሰነልን በጎ ነገር ልንደርስ አንችልም።ወደ ልማዳችን የመመለስ አዝማሚያ ሲታይብን የሰይጣን ደባ ወደ እኛ መሳብ ይጀምራል። እንዲህ የሚለው ጥቅስ ይታወሰን፦
ዕብ.10:37 -39 “ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፥ ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም፤ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል ወደ ኋላም ቢያፈገፍግ፥ ነፍሴ በእርሱ ደስ አይላትም።እኛ ግን ነፍሳቸውን ሊያድኑ ከሚያምኑቱ ነን እንጂ ወደ ጥፋት ከሚያፈገፍጉ አይደለንም።“
• የእውቀት ማጣት ጠንቅ ስለሆነብን
2ጴጥ.1:2-3 “የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።“
የጠራንን ማወቅ የመለኮቱን ሃይል፣ ክብሩንና በጎነቱን ማወቅ ያጠቃልላል።ከዚህ እውቀት እየተንሸራተትን ወደ ዳር ስነወጣ ያገዘንን ጸጋ እንዘነጋና የተጠራንበት አጠራር ይጠፋብናል።
• በአለም መሸነፍ ስለተደጋገመብን
ጠሪውን ያለመስማትና ቃሉን ያለማክበር ለጠላት ወጥመድ ያዘጋጃል። ከሃይል መራቅ ድካምን እንደሚያቀርብ ግልጽ ነው።ያለመስማትም መጋለጥንና መጠቃትን ይጋብዛል።ለውድቀታችን መደጋገም የግንኙነት መላላት መሆኑን አስበን እናውቃለን?
• ለቃሉ ክብር ያለመስጠት ስለተጠናወተን
አንዳንዴ ሰይጣን አትኩሮታችንን ዞር ያደርግና መጠራታችንን ያደበዝዝብናል።የመጠራታችን ልቀት አልታይ ብሎ ዝቅ ይልብናል።ነገር ግን ሁልጊዜ በቃሉ የተገለጠው እውነት ሊለወጥ አይችልም፦
ሮሜ.9:24 “የምሕረቱ ዕቃዎችም ከአይሁድ ብቻ አይደሉም፥ ነገር ግን ከአሕዛብ ደግሞ የጠራን እኛ ነን።“
ስለዚህ የተቀበለውን ስጦታ ባንጥል እንደአጠራራችን በተወሰነልን ስፍራ እንኖራለን፤ይህ ሳይሆን ቀርቶ ኮብላይና ተቅበዝባዥ ከሆንን ምርጫችን ብዙ ያስከፍለናል።
• ጸጋን መጣል ስላበዛን
ጸጋን ጥለን ደህንነታችንን ማረጋገጥ አንችልም፤ ይህን ያደረገልንን አምላክ መደገፍም አንችልም።ከተውነው እርሱም እንደሚተወን አውቀን በርሱ ላይ ያለንን እምነት አጥብቀን መያዝ አለብን።ጥሪን የማይመጥን ህይወት የሚከተለው የጽድቅ ህይወት እንድንኖር የሚያስችለንን ጸጋውን በመጣላችን ስለሚሆን ጥንቃቄን ደግመን ደጋግመን ማረጋገጥ ይገባል።