ጥሪ ለእግዚአብሄር አገልግሎትና ለመንግስቱ ወራሽ የመሆን ግብዣን ቢያጠቃልልም በተለይ ለእግዚአብሄር ስራ ለመለየት ከእግዚአብሄር ዘንድ የሚመጣ ግብዣ ግን የወንጌሉ አገልጋይ ከመሆን ጋር ይያያዛል። እግዚአብሄር በብሉይ ኪዳን ውስጥ ለመንግስቱ የተጠሩ የእስራኤል ህዝብን ከግብጽ ምድር አውጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር አፍልሶአቸዋል። ይህም በአዲስ ኪዳን ከአለም ወጥተው ወደ እግዚአብሄር መንግስት ለሚፈልሱ የእግዚአብሄር ልጆች ምሳሌ ነበረ። እግዚአብሄር እስራኤላውያንን ከግብጽ ምድር እንዳወጣ ያደረገው በህዝቡና በእርሱ መሃከል ሆነው የሚያገለግሉ የካህናት ወገኖችን ከመሃከል መለየት ስለነበር እነዚህን ወገኖች ሲመርጥ ከአስራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች መሃል ሌዋውያንን ለክህነት አገልግሎቱ ለይቶአቸዋል። በአዲስ ኪዳንም ቤተክርስቲያንን በየስፍራው ሲመሰርት በቤተክርስቲያን ውስጥ የወንጌሉ አገልጋይ ካህናት ይሆኑ ዘንድ የሚጠራቸው አሉ።
ለእግዚአብሄር መለየት ምን አይነት አካሄድን ይከተላል? የተጠሩ እንዴትስ እግዚአብሄርን ያገለግላሉ? ለእነዚህ መልስ የሚሆን የአንድ ካህን ህይወት ምሳሌ እንደሚከተለው ይቀርባል፤ ይህ ካህን የብሉይ ኪዳን የመጨረሻው ካህን የሆነ ክህነቱን ለአዲስኪዳን ሊቀካህናት ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ የጠረገ የካህኑ ዘካርያስ ልጅ መጥምቁ ዮሃንስ ነው።
1. ለእግዚአብሄር መሰጠት
ለእግዚአብሄር መሰጠት ለጠሪው አምላክ ራስን መስጠት ነው፤ ለእግዚአብሄር ባሪያ መሆን ነው፤ እግዚአብሄርና ድምጹን ብቻ ተከትሎ መሄድ ማለት ነው፤ የራስ ፈቃድን መጣል የእግዚአብሄርን ማንሳት ማለት ነው። መጥምቁ ዮሃንስ ወደ አገልግሎት ሲገባ በእድሜው 30ዎቹ መጀመሪያ ላይ የነበረ በርሱም በስድስት ወር ገደማ ከክርስቶስ ምድራዊ እድሜ የሚበልጥ ሰው ነበር። ለእስራኤል በተገለጠ ወቅት ከማህበረሰቡ በተለየ መንገድ ልብስ ደርቦና መጫሚያ አድርጎ ስለነበር በወቅቱ በብዙዎች ፊት ትኩረት ተደርጎበት ነበር። በጊዜው የሃይማኖት አስተማሪዎች ከነበራቸው የክብር ልብስ ይልቅ በቆዳ የተሰራ እራፊ በላዩ ደርቦ ተገልጦአል። አመጋገቡም በሰው የተዘጋጀ/የበሰለ ምግብ ሳይሆን የዱር ምግብ እርሱም አንበጣና ማር ነበር። ይህ ወጣት ሰባኪ በአይሁድ ዘንድ ልዩ ትኩረት የተሰጠውን ሃይለኛ መልእክት ያሰማ ስለነበር የአይሁድ ቀልብ በርሱ ላይ ሆነ። ከአይሁድም ወደ እርሱ የሚመጡ ከጥቂቶች ጀምሮ እያደር እየበዙ በሺዎች የሚቆጠሩ ከይሁዳና ከገሊላ ወደ እርሱ ይጎርፉ ነበር። እነርሱም ከከተሞች ወደ በረሃ ወደ እርሱ ድምጹን ይሰሙ ዘንድ ይጎርፉ ነበር። የወጣቱ ዮሃንስ የስብከት ሃይል ህዝቡን ወደ ቃሉ መሳብ ብቻ ሳይሆን የሚናገረው ነገር በኢየሩሳሌም የነበሩ የሃይማኖት ሰዎችንም ጥርጥር ውስጥ አስገብቶአል። በዚህም ምክኒያት ስለእርሱ ያመነቱ የህዝቡ አለቆች የርሱን ማንነት እርግጡን ያውቁ ዘንድ ሰዎች ተልከው ወደ እርሱ መጡ።
2. የእግዚአብሄር የሆነውን ብቻ መግለጥ
ሃዋርያው ዮሃንስ ከኢየሩሳሌም የተላኩ መልእክተኞች ወደ መጥምቁ ዮሃንስ በመጡ ጊዜ ያዩትን ነገር በዮሃ.1፡19-23 ውስጥ አስፍሮአል፦
“አይሁድም፦ አንተ ማን ነህ? ብለው ይጠይቁት ዘንድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው። መሰከረም አልካደምም፤ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም ብሎ መሰከረ። እንኪያስ ማን ነህ? ኤልያስ ነህን? ብለው ጠየቁት። አይደለሁም አለ፦ ነቢዩ ነህን? አይደለሁም ብሎ መለሰ። እንኪያስ፦ ማን ነህ? ለላኩን መልስ እንድንሰጥ፤ ስለራስህ ምን ትላለህ? አሉት። እርሱም፦ ነቢዩ ኢሳይያስ እንዳለ፦ የጌታን መንገድ አቅኑ ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ እኔ ነኝ አለ። የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና። እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፥ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት። ዮሐንስ መልሶ፦ እኔ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው አላቸው።”
ከኢየሩሳሌም ከሊቀ-ካህናቱ ዘንድ የተላኩ ካህናትና ሌዋውያን ነበሩ፤ እነዚህ ሰዎች ግን ባዩትና በሰሙት ነገር ደስተኞች አልሆኑም፤ ሰባኪውን ሲያዩት እንደመጤ ቆጠሩት እንጂ ልባቸውን አልሰጡትም፤ በርሱ ዘንድ የነበረው አቀራረብ እንደ አስተማሪዎቻቸው አልሆነምና ዝቅ አደረጉት። ይህን ሰው በምኩራብ ሲያስተምር አላዩትም ግን ከባድ መልእክቶች ነበሩት፣ የትኛውም ፈሪሳዊ እግር ስር ሆኖ ሲማር እንደነበር የሚያስረዳ ታሪክ አልነበረውም፣ ግን እንደነርሱ ያልሆነ ትምህርት ነበረው፤ በማንኛውም ሊቀ-ካህናት ሲሾም አልታየም ግን በስልጣን ያውጅ ነበር። መጥምቁ ዮሃንስ ከታላላቅ ሃይማኖተኞች አካባቢ ሳይሆን ተራ ከሆኑ ማህበረሰብ መሃል ወጥቶ ከላይኛው የህብረተሰብ ክፍል የተቀመጡት ሳይቀሩ የሚናወጡበትን መልእክት ይናገር ስለነበር የብዙዎች ትኩረት በእርሱ ላይ እየጨመረ ነበር። በተለይ የሃይማኖት አስተማሪዎች ስጋት ውስጥ ስለገቡ ተከታተሉት። ከኢየሩሳሌም የተላኩት ሰዎችም ያንኑ ይዘው ስለመጡ የጠየቁት አንተ ማነህ? በማለት ነበር፣ ከምትናገረው ነገር በላይ አንተ ማነህ? እንደማለት ነው። በዙሪያው ይወጣ የነበረ መሲሁ ሊሆን ይችላል የሚለውም ግምታዊ ንግግር ብዙ የጥርጣሬ ጥያቄ ስለፈጠረባችው መልሱ በጥቂት ማብራሪያ የሚመለስ አልነበረም። የመጥምቁ ዮሃንስን መልስ ሃዋርያው ዮሃንስ እንደሚከተለው ያስቀምጠዋል፦
ዮሃ.1:19-20 “አይሁድም፦ አንተ ማን ነህ? ብለው ይጠይቁት ዘንድ ከኢየሩሳሌም ካህናትንና ሌዋውያንን በላኩበት ጊዜ፥ የዮሐንስ ምስክርነት ይህ ነው። መሰከረም አልካደምም፤ እኔ ክርስቶስ አይደለሁም ብሎ መሰከረ።”
መጥምቁ ዮሃንስ እርግጡን መሰከረ እኔ እርሱን አይደለሁም አለ፤ እንዲያምኑት ወይም እንዲቀበሉት የሚያባብል ቃላት መጠቀም አላስፈለገውም። እነርሱም ደግመው ጠየቁ፦ ኤልያስ ነህን? አሉ። ይህን የጠየቁበት ምክኒያት በሚል.4:5 ውስጥ ኤልያስን እንደሚልክላቸው ተናግሮ ስለነበር ነቢይ ከተነሳ እርሱ ይሆናል ብለው ገምተዋል፤ ያን ይዘውም ጠየቁት።
በኤልያስ መንፈስ የሚመጣ ነቢይ በአዲስ ኪዳን የተሰጠው አገልግሎት ነበር፣ እርሱም የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የልጆችንም ወደ አባቶች ይመልስ ዘንድ። የሚልኪያስ ትንቢት ከተነገረ ወደ 400 አመታት ተቆጥረው ነበር፤ በነዚያ ዘመናት ሁሉ እስራኤላውያን የኤልያስን ዳግም መመለስ ሲጠብበቁ ነበር። ኤልያስ የተባለ ነቢይ እጅግ ቆፍጣናና ፍርሃት የማይመልሰው ነቢይ ነበር፤ በእርሱ በኩል በህዝቡ ላይ ፍርድ እንዲመጣ ሆኖአል። አሁንም ዮሃንስ ላይ ፍርሃት የሌለበት ንግግርና ውሳኔ ያስተላልፍ ስለነበር ነቢዩ ኤልያስ ትዝ ብሎአቸው ነበር። በዚህ ዮሃንስን ኤልያስ ነህን ብለው ጠይቀውት ነበር። ዮሃንስም ሲመልስ እኔ እርሱን አይደለሁም አለ። ሰው ከሞተ በሁዋላ ዳግም በሌላ አካል እንደማይመጣ እንዲያውቁ አጠንክሮ የሚያሳስብ ነበር። በእርግጥ በማቴ.17:10-122 “ደቀ መዛሙርቱም:- እንግዲህ ጻፎች:- ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ ይገባዋል ስለ ምን ይላሉ? ብለው ጠየቁት። ኢየሱስም መልሶ፦ ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናል፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ኤልያስ ከዚህ በፊት መጣ፤ የወደዱትንም ሁሉ አደረጉበት እንጂ አላወቁትም” ይህንን ጌታ ስለምን ተናገረ? በሉቃ1:13-17 የተባለ ነገር አለ፦
“መልአኩም እንዲህ አለው፦ ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፥ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል። በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል፤ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል።… እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።”
3. በእግዚአብሄር ነገር ላይ ማተኮር
አንዳንዴ በአገልግሎት ውስጥ አዲስ ነገር ሊገጥም ይችላል፤ ይህም ከማህበረሰቡ ልማድ የወጣ ቢመስልም ከእግዚአብሄር ዘንድ የተገለጠ እውነት እስከሆነ ድረስ ያን አጥብቆ መያዝ ያስፈልጋል።
እግዚአብሄር በነቢያት ተናግሮ እንደነበረው ከኢየሱስ በፊት በመምጣት ዮሃንስ በኤሊያስ መንፈስ እንደሚያገለግል ተነግሮ ነበር፤ የዮሃንስ አገልግሎት እንደ ኤልያስ ያለ ነበር። የተላኩት ሰዎች ሲጠይቁት፡ ታዲያ አንተ ማን ነህ፣ ነቢዩ ነህን? አሉ። ነቢዩ ሲሉ እየጠቀሱ የነበረው በዘዳ.18:15 የተጻፈውን ነበር፦
ዘዳ.18:16 “አምላክህን እግዚአብሔርን በኮሬብ ስብሰባ ተደርጎ በነበረበት ቀን፦ እንዳልሞት የአምላኬን የእግዚአብሔርን ድምፅ ደግሞ አልስማ፥ ይህችን ታላቅ እሳት ደግሞ አልይ ብለህ እንደ ለመንኸው ሁሉ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል፤ እርሱንም ታደምጣለህ።”
አንዳንዶች ነቢዩ የተባለው ኤርሚያስ ነው ብለው ነበር፤ ሌሎችም የሚመጣውን ባለማወቃቸው ነቢዩ ነህን? አሉት፤ የዮሃንስም መልስ በአጭሩ አይደለሁም የሚል ነበር። ስለርሱ የሚናገረው የትንቢት ቃል በኢሳ.40:3 ላይ ሲናገር፦
“የአዋጅ ነጋሪ ቃል፦ የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካከሉ። ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፥ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማውም ይቃናል፥ ስርጓጕጡም ሜዳ ይሆናል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ በአንድነት ያየዋል፥ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።” ተብሎ በተናገረው መንፈስ የመጣ ነበር። ነገሩ ግራ አጋቢ ቢመስልም ዮሃንስ ግን በትንቢቱ ላይ የጸና ነበር። ዮሃንስ ይሄንን የተስፋ ቃል ሲያመለክት ስለእኔ ስራ ምስክር ከፈለጋችሁ ሂዱና ስለእኔ ትንቢት የተናገረውን ነቢይ ጠይቁና አረጋግጡ የሚል መልእክት እያስተላለፈ ነበር።
ጥሪ እግዚአብሄር በሚሰጠን ምሪት መጽናት እንደሚጠይቀን የነቢዩ መልስ ያስተምራል። ዮሃንስ የኢሳያስን ትንቢት ያሳያቸው እርሱ ከድምጹ አስቀድሞ ስለተማረና በእርሱ ስለተማመነ ነው። ወደ አገልግሎት ከመውጣቱ በፊት የነቢዩን ትንቢት በመንፈስ ተረድቶአል፣ በእግዚአብሄር ቃል ተማምኖአል፣ ለጥሪው ምላሽ ይሰጥ ዘንድም ከምድረ-በዳ ወደ ጠፉት የእስራኤል ቤት ወጥቶአል ማለት ነው። ስለአወላለዱም ቤተሰቦቹ በትንቢት የመወለዱን ተአምር ሳያስተምሩትም አልቀረም፣ ስለዚህ ይህ ሰው እግዚአብሄርን ለማገልገል ሳያመነታ ወጣ። ከእናቱ ማህጸን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ የተሞላና በእግዚአብሄር ቅባት የተለየ አገልጋይ መሆኑን አስተውሎ የእግዚአብሄርን ፈቅድ ሊፈጽም ራሱን ያዘጋጀም ነበረ። ራሱን ለአገልግሎት ሲያዘጋጅ እግዚአብሄር በእኔ በኩል ምን ሊያደርግ ይሻል ብሎ ሲመለከት እግዚአብሄር በነቢዩ ኢሳያስ በኩል ሊሰራ የሚገባውን አመልክቶታል ማለት ነው፤ አገልጋይ ለእግዚአብሄር በመለየት የእግዚአብሄርን ፊት ሲፈልግ እግዚአብሄር ድምጹን እንደሚልክና አቅጣጫ እንደሚያሳየው የዮሃንስ ታሪክ ያስተምራል።
መጥምቁ ዮሃንስ ስለአገልግሎቱ ከቃሉ እንደተማረ የገባው ነገር አለ፦ አዎ እርሱ የጌታን መንገድ የሚያስተካክል፣ መንገዱ የመዳኛ እንጂ የመሰናከያ እንዳይሆን አጥብቆ በመንገዱ ላይ እንዲያተኩር አስገንዝቦታል፤ መንገዱም ምድረ-በዳ ላይ መንገድ የሚዘረጋ እንደመሆኑ መንገዱን ለማስተካከል መስዋእት ሊኖረው እንደሚገባ አስተውሎአል ማለት ነው። መንገዱ ሰዎች ወደ እግዚአብሄር የሚሄዱበት ሳይሆን እግዚአብሄር ራሱ ወደ ሰዎች የሚመጣበት ነበር። የመንገዱን የግንባታ አሰራር አመልክቶትም ነበር፦ መንገዱ ሲሰራ ሸለቆው እስኪሞላ ትሰራለህ፣ ተራራው ተጎርዶ መሬት ድረስ እስኪወርድ ትለፋለህ፣ ጠማማው እስኪስተካከል ታቃናዋለህ፣ ጎርበጥባጣውን ሜዳ ታደርጋለህ፣ ያኔ እግዚአብሄር ይገለጣል ሲል ነቢዩ የስራውን ጅማሬና ፍጻሜ አመልክቶትል።
4. በእውነተኛ አገልግሎት ሰዎች ይለወጣሉ
በመጥምቁ ዮሃንስ በእስራኤል ምድር መገለጥ ምክኒያት ታላቅ መንፈሳዊ መነቃቃት መጥቶአል። ሰዎች በንሰሃ ተመልሰዋል፤ ብዙዎችም በንሰሃ ጥምቀት ለመጠመቅ ወደ እርሱ ይመጡ ነበር። የእግዚአብሄር አገልጋይ አትኩሮቱን በዙርያው በሚሆነው ነገር ላይ ከጣለ መሳቡ አይቀርም፤ በደከመና ተስፋው በመነመነ ማህበረሰብ መሃል ሆኖ ራሱን ያላበረታ ከሆነ ቆይቶም ቢሆን ይዋጣል፤ የላከውን አምላክ ተመክቶና በጥሪው ተበራትቶ ትኩረቱ በአገልግሎቱ ላይ ብቻ ከሆነ ግን ከመስመጥ ተርፎ እንዲያውም የተዘፈቁትን ሊያድንና ወደ ጥሪው ከፍታ ሊያወጣቸው ይችላል። ተራራ ልብ በበዛበት የእግዚአብሄር ትህትናን ተላብሶና ታግሶ ህዝብን ወደ መንፈሳዊ ለውጥ ማድረስ ሲቻል፣ ስርጉጥጉዋጥ በበዛበትም እንዲሁ ተደፋፍሮና እምነትን አበራትቶ የሰማይን መንገድ ለማሳየት መሮጥ ይገባል።
ሲሮጥ መታከት ካለ፣ ውጤታማ አይደለሁ ይሆናል ብሎም ማመንታት ካለ፣ በሁኔታዎች መጨነቅና መጫጫን ውስጥ ከተገባ የእግዚአብሄርን አላማ መጣል ሊከተል ይችላል፤ ውጤታማ ያለመሆን ተስፋ አስቆራጭ ነገር ቢሰማም ጨክኖና ፈጥኖ መነሳትና ራስን ወደላይ ቀና ማድረግ፣ የጠራኝ ከኔ ጋር አለ ብሎ መታመን፣ አይተወኝም ይረድኛል ብሎም መበርታት አስፈላጊ ነው።
የሚያገለግል ሸለቆው አጠገብ ደርሶ የሚቆም ሳይሆን በሸለቆው ውስጥ አልፎ የሚሰራውን ትውልድ ይዞ መውጣት በዚያ በዝቅታው ውስጥ ሆኖ ለሚገጥመው ነገር ግን የስራው ባለቤት ሃላፊ እንደሆነ አምኖ መሰማራት ይጠይቃል። አገልጋይ ማመንና መታመን ይጠበቅበታል፣ በራስ ችሎታ መታመን፣ ወይም ስጋ ለባሽን መደገፍ ጨርሶ አይጠበቅበትም፣ አገልግሎቱን ያቃጥላልና። ከፊት ተራራ ሲገጥም ድጋሜ አይንን ወደ ነገሩ ሳይሆን ወደላይ አሻቅቦ መመልከትና ከታች እንደወጣሁ ከፊቴ አላሳልፍ ብሎ የተጋረጠውን በእርሱ እሻገራለሁ በሚል እምነት መጋፈጥ የጠይቃል። ትግሉ ሁሌም ባህር ላይ በማእበል እንደምትናጥ ጀልባ በከፍታና በዝቅታ ውስጥ የሚያታግል ቢሆንም ሃይልን የሚሰጥ ጌታ ጠሪው እርሱ በመሆኑ ሁሌም ከባርያው ጋር መሆኑ ማስተማመኛና እረፍት ይሰጣል።