የእግዚአብሄር አሳብ ሲፈጸም፣
‘’ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ። ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም።’’(ዮሃ.1፡5-8)
እግዚአብሔር ለተለየ አገልግሎት የላከው መጥምቁ ዮሐንስ አይሁድ ሁሉ በእርሱ በኩል የተገለጠውን አሰራር ተቀብለው እንዲያምኑ እርሱ ብርሃን ስለሆነው ስለ ክርስቶስ ተልእኮና ማንነት ይመሰክር ዘንድ በትንቢት ስለእርሱ የተነገረውንም በህይወቱ ይገልጥ ዘንድ ለምስክር መጣ። እርሱ ብርሃን ስለሆነው ጌታ ሊመሰክር መጣ እንጂ እርሱስ የህይወት ብርሃን ነኝ አላለም።
ስለእርሱ በተነገረው ትንቢት መሰረትም ዮሃንስ እንደቃሉ የራሱ የስራ ድርሻ ከበራለት በሁዋላ በቀጥታ የእግዚአብሄርን አሳብ ወደ ማገልገል አዘነበለ፦
ዮሃ1፡24-25 ‘’የተላኩትም ከፈሪሳውያን ነበሩና፦ እንኪያስ አንተ ክርስቶስ ወይም ኤልያስ ወይም ነቢዩ ካይደለህ፥ ስለ ምን ታጠምቃለህ? ብለው ጠየቁት።’’
በእስራኤል ምድር አንድ ልዩ አሰራር ከእግዚአብሄር ዘንድ ተገልጦ ነበር፤ ያም ጥምቀት የተባለ አሰራር ሲሆን በአይሁድ ዘንድ አዲስ ክስተት ሆኖ ስለመጣ በዮሃንስ ስራ ብዙዎች ግራ ተጋብተው ነበር፤ በየትኛውም ዘመን በእስራኤል ምድር ጥምቀት ያጠመቀ ነብይ አልነበረምና። በእርግጥ በህጉ ስርአት ውስጥ የመታጠብ ትእዛዝ ነበር። ነገር ግን እንደ መጥምቁ ዮሃንስ ያለ ከመቅደሱ ውጪ የሚተገበር የጥምቀት አሰራር አልታየም። ስለዚህ ለምን ታጠምቃለህ ብለው መጠየቃቸው ምን አይነት ስርአት አመጣህ አይነት ጥያቄ ይዘው ነበር።
‘’ዮሐንስ መልሶ፦ እኔ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ እኔ የጫማውን ጠፍር ልፈታ የማይገባኝ፥ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ የሚከብር ይህ ነው አላቸው። ይህ ነገር ዮሐንስ ያጠምቅበት በነበረው በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ ሆነ።’’
ዮሃንስ ለምን አጠመቅህ ብለው ለጠየቁት ሲመልስ ስለሚያጠምቅበት የራሱን ምክኒያት ለማቅረብ ሳይጣደፍ ትኩረቱን ጥምቀቱ ሊገልጠው የነበረውን ታላቅ ጌታ ላይ አድርጎ ስለእርሱ መናገር ጀመረ፤ ይህ ጌታ እንዲታወቅ በመሻትና እርሱን ለመግለጥ በነበረው ተልእኮ ምክኒያት ትኩረቱን ወደ ጌታ ኢየሱስ መለሰ።
አሁን መንገድ ጠራጊ ሆኜ ልባችሁን ለንሰሃ አዘጋጅ ዘንድ፣ትሁት ሆናችሁ እግዚአብሄር ያዘጋጀውን ደህንነት እንድትቀበሉ በውኃ አጠምቃለሁ፤ ዳሩ ግን የህዝቡን ሃጢያት ሊሸከም ያለው እርሱ እናንተ የማታውቁት በመካከላችሁ ቆሞአል፤ እርሱ ማለት ለእኔ ከፍ ያለ ጌታ ሲሆን በእርሱ ፊት ታናሽ የሆንኩ የጫማውን ጠፍር ልፈታ እንኩዋን የማይገባኝ ነኝ፤ ይህ ታላቅ አምላክ ከእኔ በኋላ የሚመጣው እጅግ ልቆ የከበረ ነውና እኔን ሳይሆን እርሱን ተመልከቱ በሚል አስተምህሮ ማየት ወደሚገባቸው ይመራቸው ነበር። ጌታ ኢየሱስ በመንፈስና በእሳት ሊያጠምቅ መጥቶአል።
የዮሃንስ ጥምቀት በውጪ በኩል የማንጻት ስራ እየሰራ የተገለጠው ጌታ ደግሞ ውስጥን ማለት ነፍስና መንፈስን፣ ልብና አእምሮን አጥቦ የሚያነጻው ጌታ ይገለጥ ዘንድ ስላለው ነበር።
ዮሐንስ ያጠምቅበት የነበረው ስፍራም ትርጉም ያለው ስፍራ ነበር፤ ቃሉ ስፍራውን በዮርዳኖስ ማዶ በቢታንያ በቤተ ራባ እንደነበረ ያመለክታል፤የዚህ ስፍራ የቀድሞ ስም በትባራ ሆኖ ትርጉዋሜውም መተላለፊያ ስፍራ ነበር፤ ይህም እስራኤል ከግብጽ ምድር ወደ ከነአን አልፈው በእያሱ አመራር የገቡበት መተላለፊያ ስፍራ እንደሆነ ይታመናል፤ መጥምቁ ዮሃንስም በዚያ ወሳኝ ወቅት ሲገለጥ አስፈላጊና ትርጉም ባለው ስፍራ ሆኖ ወገኖቹን ወደ ጌታ መንገድ እየመራ ነበር።
ኢያሱ የእስራኤልን ህዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር በመምራት የጌታን አገልግሎት በምሳሌ አሳይቶአል፤ ጌታ ኢየሱስም በደሙ ያነጻቸውን ወገኖ መርቶ ሰማያዊቱ አገር እንደሚያደርስ አመልካች ነበር።
መጥምቁ ዮሃንስ ነቢይ በመሆኑ በእምነት ጌታን እየሰበከ ነበር፤ የኢሳያስ ትንቢት እየተፈጸመ መሆኑን ስላስተዋለ፣ እርሱም እንደ ትንቢቱ መንገዱን እየጠረገ መሆኑን ስለተረዳ ስለእርሱ በድፍረት ተናገረ። ያን ለአይሁድ በመሰከረ ማግስት ግን በእምነት እንዳለው ሆነ፤ ያኔ ይህን ተናገረ፦
‘’በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ። እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው። እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ። ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ። መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ። እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ:- መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ።’’
እንደ እውነተኛና ታማኝ አገልጋይ በተስፋ ቃሉ ላይ በመጣበቅና በመታመን እርሱን ማገልገል ያለጥርጥር እርሱን እንደሚገልጥ ከዚህ የእግዚአብሄር ሰው አገልግሎት እናስተውላለን።
የእግዚአብሄር አገልጋይ እንዴት ያገለግላል? ያለጥርጥር በቃሉ ላይ በመደገፍና ከእርሱ ምሪት በማግኘት ነው፣ደግሞም እንደቃሉ ሆኖ በመገኘትም ጭምር ነው። መጥምቁ ዮሃንስ ጌታን ሲሰብክና ሳያየው በእምነት ስለእርሱ ሲናገር የነበረው በኢሳያስ አንደበት አስቀድሞ ትንቢት ስለተነገረ ነበር፤ እርሱም ያን ቃል ይዞ በእምነት በመድፈርና ባለማቅማማት ለጠየቁት መለሰላቸው። ያለጥርጥር የሚከተሉት የነቢዩ ኢሳያስ የትንቢት ቃላቶች በመጥምቁ ዮሃንስ ዘንድ የታወቁ ነበር ማለት ነው፦
‘’ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።’’(ኢሳ.9:6)
ይህ ጥቅስ መጥምቁ ዮሃንስ አንድ የሚወለድ ልዩ ህጻን እንዳለ ሳያስረዳው አልቀረም፤ ያ ሕፃን በሰዎች ፈቃድ የሚወለድ አልነበረም በእግዚአብሄር ፈቃድ እንጂ። ከእግዚአብሄር ከሆነ ደግሞ የእግዚአብሄር ስጦታ ነበር ማለት ነው። እግዚአብሄር ሰውን ስጦታ አድርጎ ለአለም ሰጠ። ስጦታው በአለም ላይ የሚቆጠር ሳይሆን አለቅነትን የሚሸከም ልዩ ሰው ነበር፣ በአይሁድ ሰዎች ስምም የሚጠራ ሳይሆን ኃያሉን አምላክ የሚገልጥ ጉልበት ያለው ስም ነበረው፣ አዳማዊ ሰው አይደለምና ለዘላለም የሚዘልቅ መለኮታዊ አባትነት ያለው ነበር፣ ይህ ለፍጥረት በሙሉ አስደናቂ መገለጥ ነበር፤ ያን ያስተዋለ መጥምቁ ዮሃንስ ታላቅነቱ ጥርት ብሎ የታየው ነበርና ስለእርሱ ሲመሰክር በሙሉ ልብ ነበር። በኢሳ.53:6-7 ላይ የተጻፈውም እንዲህ ብሎአል፦
‘’እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ። ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።’’
መጥምቁ ዮሃንስም ይህ የተወለደ ልጅ ትልቅ አገልግሎት በጫንቃው ላይ እንዳለ ከቃሉ በመረዳት ስለ ጌታ ኢየሱስ ተናግሮ እንደነበር ቃሉ አመልካች ነው። አገልጋይ መለኮታዊ መረዳት ሲቀበል ትውልድን የሚለውጥ አገልግሎት ውስጥ ይገባል። መጥምቁ ዮሃንስ ክርስቶስ ኢየሱስ ማንነቱ ከመገለጡ አስቀድሞ በስጋ መስመር ባለው ቅርበት ያውቀው ነበር፤ እናቱ ኤልሳቤጥና ክርስቶስን የወለደችው ማርያም የስጋ ዝምድና እንዳላቸው ቃሉ ስለሚናገር። ስለዚህ መጥምቁ ዮሃንስ እንደ አብሮ አደግ፣ እንደ እኩያና እንደ ዘመድ በዘልማድ ኢየሱስን አውቆት ኖሮአል፤ ቃሉ ሲገለጥለት ግን በዘልማድ ካወቀው እውቀት የወጣ መገለጥ ውስጥ ገባ፤ ስለክርስቶስ የተነገሩት ትንቢቶች በመንፈስ በሩለት፤ እናም አስደናቂ መገለጡን እንዲህ ሲል ተናገረ፤ …እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው። እኔም አላውቀውም ነበር (በእግዚአብሄር በግነቱ)፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ (ተራ አይሁዳዊ ሳይሆን በትንቢት ስለእርሱ የተነገረው ቃል መፈጸሙ ታውቆ) ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ አለ። እንዲሁም ሲቀጥል፦
‘’በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥ ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ፦ እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ። ሁለቱም ደቀ መዛሙርት ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት። ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉትም አይቶ፦ ምን ትፈልጋላችሁ? አላቸው። እነርሱም፦ ረቢ፥ ወዴት ትኖራለህ? አሉት፤ ትርጓሜው መምህር ሆይ ማለት ነው። መጥታችሁ እዩ አላቸው። መጥተው የሚኖርበትን አዩ፥ በዚያም ቀን በእርሱ ዘንድ ዋሉ፤ አሥር ሰዓት ያህል ነበረ። ከዮሐንስ ዘንድ ሰምተው ከተከተሉት ከሁለቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ ነበረ። እርሱ አስቀድሞ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና። መሢሕን አግኝተናል አለው፤ ትርጓሜውም ክርስቶስ ማለት ነው።’’
የኢሳያስን ትንቢት በመንፈስ በማስተዋሉ ዮሃንስ የተማረውንና የተገለጠለትን እውቀት እናያለን፤ ኢሳያስ በትንቢቱ ውስጥ ህጻን ከድንግል እንደሚወለድ አስቀድሞ ተናግሮአል፤ ይህ ህጻን በጫንቃው ላይ የደህንነት ሃላፊነትን፣ መለኮትዊ ስልጣንን ይዞአል። በርሱ ላይ ባለው ስልጣን የሃጢያታችንን ፍርድ የሚሽር ጌታ ነው። ስለዚህ የሳትነውን የጽድቅ መንገድ አስተካክሎ የሚያመለክትና በጽድቅ መንገድ የሚመራ ጌታ እንደሚገለጥ ያስተዋለው ዮሃንስ በእምነት ሰበከው፣ ከመንፈስ ቅዱስ ምስክርነት አግኝቶም በመንፈስ መረዳት ዳግም እንዳየው በአድናቆት ተሞልቶ እነሆ ሲል ለእስራኤል ገለጠው።
መጥምቁ ዮሃንስ በአገልግሎቱ ለተጠራለት አላማ ራሱን የሰጠ ስለነበረ በራሱ የወሰነ እንደነበር ህይወቱ ያሳያል፤ እርሱ ይታወቅ የነበረው በህይወት ልምምዱ የገለጠው ከአኑዋኑዋር ዘይቤ አንስቶ እስከ መንፈሳዊ ህይወቱ ለሌሎች ምሳሌና የእግዚአብሄርን አሳብ የሚገልጥ ስለነበረ አገልግሎቱ ያለነቀፋ እንዲሆን አስችሎታል።
እግዚአብሄር ለአገልግሎት ሲጠራ የጠራውን ሰው የሚያሸክመው ራእይ በህይወቱ ውስጥ አኑሮና ከእርሱ ጋር በጉዞው ሁሉ እየተጉዋዘ በማገዝ ነው። መልአኩ ወደ ዘካርያስ በመጣ ጊዜ በወላጆቹ በኩል መደረግ የነበረበትን፣ በእግዚአብሄር በኩል ያለውን ድርሻና የሚወለደው ልጅ ሊያደርግ ያለው ስራ ተገልጾ ነበር፦
‘’መልአኩም እንዲህ አለው፦ ዘካርያስ ሆይ፥ ጸሎትህ ተሰምቶልሃልና አትፍራ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ። ደስታና ተድላም ይሆንልሃል፥ በመወለዱም ብዙዎች ደስ ይላቸዋል።በጌታ ፊት ታላቅ ይሆናልና፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ አይጠጣም፤ ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል፤ ከእስራኤልም ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው ይመልሳል።’’(ሉቃ.1:13-16)
በቃሉ መሰረት ከቤተሰቡ ይጠበቅ የነበረው ሃላፊነት ወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ እንዳይጠጣ መጠበቅና ከርሱ ማራቅ፣ በቅድስና እንዲያድግና እንዲማር መርዳት ሲሆን፣ በእግዚአብሄር በኩል ደግሞ ገና በጠዋቱ በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ሞልቶ ለአገልግሎቱ በሃይል ማዘጋጀት፣ ከልጁ መጥምቁ ዮሃንስም ይጠበቅ የነበረው ከእስራኤል ልጆች ብዙዎችን ወደ ጌታ ወደ አምላካቸው የመመለስ አገልግሎት ነበር። በነዚህ ሃላፊነቶች ውስጥ እግዚአብሄርን ከቤተሰብ እንዲሁም ከሚወለደው ልጅ አገናኝ ድልድይ የነበረው የእግዚአብሄር ቃል ነበር። የአገልግሎት ምሪትም ከጌታ እንደሚመጣ ቃሉ ያሳያል፦
‘’ደግሞም አንተ ሕፃን ሆይ፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፥ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤ እንደዚህም የኃጢአታቸው ስርየት የሆነውን የመዳን እውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፤ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፤ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል። ሕፃኑም አደገ በመንፈስም ጠነከረ፥ ለእስራኤልም እስከ ታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ።’’(ሉቃ.1:76-79)
ለትውልዱ የተገለጠ እውነተኛ አገልግሎት ከእግዚአብሄር የሚቀበሉት፣ ህያው ቃሉ የሚመራውና የእግዚአብሄር መንፈስ በድንቅና በታምራት የሚያጅበው ነው፤ ሃሰተኞች ከእውነተኞች በዚህ ምልክት ይለያሉ። እውነተኛ አገልጋይ ቃሉን በመታጠቅ፣ በመኖርና እግዚአብሄርን በመፍራት በጽድቅ በመመላለስም የጌታን መንገድ በሰው ህይወት ውስጥ መጥረግና ጌታ እንዲሰራ የተመቸ ልብ ማዘጋጀት ነው።
የጌታን ዘላለማዊ መገለጥና ለሰው ልጆች ሊያደርገው ያለውን ዘላለማዊ መስዋእትነት በማስተዋል በራሱ ዘመን ይህን ጌታ ማገልገል ተገቢ እንደሆነ በራሱ ዘመንም የተሰጠውን አደራ ጠብቆ በታማኝነት ሊያስረክብ ያስተውል ዘንድ እጅግ አስፈላጊ ነው፤ መጥምቁ ዮሃንስ ከጌታ የተሰጠው አገልግሎት በጊዜና በስፍራ የተገደበ መሆኑን ያስተዋለ ሰው ነበርና በተሰጠው ጊዜ የሚጠበቅበትን ሊፈጽም የተጋ ነበር። ለጠየቁትም በዮሃ.1:29-34 ውስጥ ሲመልስ የተናገረው፦
‘’… እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ። ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ። መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ። እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፦ መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ።’’
አገልጋይ ከመነሻው ከተቀበለው ተልእኮ በተጨማሪ በእለት ተእለት አገልግሎቱ ጌታ ቀርቦ ሊናገረውና ሊመራው እንደሚገባ ከመጥምቁ ዮሃንስ ህይወት እንመለከታለን። ቃሉ እንደሚያሳየው ኢየሱስን አውቀዋለሁ፣ ቅርቤ ስለሆነ ተለማምጀዋለሁ ማለት ሳይሆን በየእለቱ የሚመጣበትን የራሱን መንገድ እስኪገልጥልኝ እጠብቀዋለሁ፣ ተገልጦ ሲመራኝም ፈጥኜ እከተለዋለሁ ሊባል ይገባል።
‘’ዮሐንስም እንዲህ ብሎ መሰከረ፦ መንፈስ ከሰማይ እንደ ርግብ ሆኖ ሲወርድ አየሁ፤ በእርሱ ላይም ኖረ። እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን በውኃ አጠምቅ ዘንድ የላከኝ እርሱ፦ መንፈስ ሲወርድበትና ሲኖርበት የምታየው፥ በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቅ እርሱ ነው አለኝ። እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ።’’
ጠብቄዋለሁ፣እርሱም በመንፈሱ ተናግሮ አመልክቶኛል፣ እኔም የሰማሁትን አምኛለሁ ስለዚህ እርሱን ብቻ እመሰክራለሁ የሚል ትክክለኛ ምሪት ያለው አገልግሎት ለዚህም ዘመን ይሁን፣አሜን።