ጊዜ ጌታ? [3..]

ቤተክርስቲያን

– ጊዜ ፈራጁ?
ጊዜ ፈራጅ ነው አንበል፣ ፈራጅስ ጌታ ነው፦
መዝ.50:5-6 ”ከእርሱ ጋር ለመሥዋዕት ኪዳን የቆሙትን ቅዱሳኑን ሰብስቡለት። ሰማያት ጽድቁን ይናገራሉ፥ እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና።”
የወቅትን ፈራጅነት ለማሳየት ጊዜ በሰው ላይ እንደሚሰለጥንም ለማመልከት ሰዎች በልማድ ያን ይሉታል፡፡ ግን እግዚአብሄር በጊዜያቱ ለሚሆኑት ነገሮች ባለቤት ከሆነ ጊዜ በነገሮቹ ላይ ስልጣን ሊኖረው አይችልም፤ ጊዜ ራሱ ጌታ ካለው የገዢነት ቦታ እንዴት ሊወስድ ይችላል? የህይወታችን ዘመን በጊዜ መቆጠሩና ገዢያችን እግዚአብሄርም በህይወታችን ላይ ተጽእኖውን ሊገልጥ በጊዜ ውስጥ ስለሚመጣ የነገሮች ሁሉ ፍጻሜ ጊዜ እንደሆነ ልንቆጥር እንችላለን። አሁን ግን አስተዋዮች ጌትነትን ከጊዜ ላይ አንስተን የሁሉ ፈጣሪ ለሆነው የሰማይ አምላክ እንስጥ፣ ይህ እንዲያውም አንዱ የእምነት ማረጋገጫ ነው።
– ጊዜ ጌታ?
ጊዜ ጌታ ነውም አንበል፣ የሁሉ ጌታ ኢየሱስ ከረስቶስ ነውና እርሱን በላያችን ላይ አናንግሰው፦
ሮሜ.10:11-13 ”መጽሐፍ፦ በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላልና። በአይሁዳዊና በግሪክ ሰው መካከል ልዩነት የለምና፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።”
ጊዜን አትፍራ በጊዜ ላይ የሰለጠነውን ጌታ ግን እርሱን ፍራ፤ ዘመንህን በተድላ እንድትኖር እርሱን ጥራ፣ እመንም።
ሐዋ.10:36 ”የሁሉ ጌታ በሚሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እየሰበከ ይህን ቃል ወደ እስራኤል ልጆች ላከ።” ይላል።
– ነገርን ሁሉ በጊዜ ሰራው
እግዚአብሄር ጊዜን እንደ መሳርያ ይጠቀምበታል፤ ጊዜን ወስኖ ፈቃዱን ይገልጣል። አንድ ነገር ከእግዚአብሄር ዘንድ የሚገለጠው ፈቃዱ በወሰነው ዘመን ሲገለጥ በመሆኑ እግዚአብሄርን የሚያውቁ አማኞች ዘመኑን እየተጠባበቁ ፈቃዱ ይገለጥ ዘንድ እንዲለምኑ ይሻል፦
ሐዋ.1:6-9 ”እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ፦ ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን? ብለው ጠየቁት። እርሱም፦ አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ። ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው።”
መክ.3:11፣14 ”ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው። …እግዚአብሔር ያደረገው ሁሉ ለዘላለም እንዲኖር አወቅሁ፤ ሊጨመርበት ወይም ከእርሱ ሊጐድል አይቻልም፤ እግዚአብሔርም በፊቱ ይፈሩ ዘንድ አደረገ።”
በጊዜው ተገልጦ የሚሰራ አምላክ በሰራው ስራ ላይ እንከን አይገኝበትም፤ ስራው ለተገለጠበት ትውልድ ላይመች ቢችልም የሰራው አምላክ ስለማይሳሳት የቱም ነገር ጸንቶ ይኖር ዘንድ እግዚአብሄር እንደፈጠረው ሆኖ የሚቀጥል ነው፤ መስሎ እንዳለ ሳይሆን ሆኖ እንዳለ መኖሩ ነው የእግዚአብሄርን መኖር የሚገልጠው፡፡ እግዚአብሄር ሁሉን ሲፈጥር ያሰበውን ሊፈጽምበት እንደሆነ ካላስተዋልን ግን በማታስተውለው አለም እየሆነ እንዳለው ምስቅልቅል እኛም የምንንገዋለል ነው የሚሆነው፡፡
ነገሮችም በዚህ ውስጥ ከተፈጠሩለት አላማ ውጪ ካሉ ፈጽሞ ትክክል ነገር ላይ እንደማይቆሙ አስረግጠን ማወቅ አለብን፡፡
በአለም ያለ ሰውም ከእግዚአብሄር መፍትሄ ይልቅ የራሱን አቁዋራጭ መንገድ ሊጠቀም የሚወድደው በርሱ ጊዜ እግዚአብሄር መሻቱን እንደማይፈጽም ስለሚቆጥር ነው፤ የሰው ችኩልነት የሚታየውም ለዚህ ነው።
እግዚአብሄር ዘላለማዊ ሆኖ ጊዜ የማይገዛው ቢሆንም ሰዎችን ለመገናኘት ጊዜን ይጠብቃል፡፡ ስለዚህ በጊዜ የሚገልጠውን ስራውን በትእግስት ሊጠባበቅና ሊያስተውል እንደሚገባው የሰው ልጅ ማወቅ አለበት ማለት ነው፡፡
መዝ.130:5-6 ”አቤቱ፥ ስለ ስምህ ተስፋ አደረግሁህ፤ ነፍሴ በሕግህ ታገሠች። ከማለዳው ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊት ነፍሴ በእግዚአብሔር ታመነች።”
– እግዚአብሄር አድራጊ ፈጣሪም ነው
ከሰማይ የሆነ ስራ ሲገለጥ በጊዜው የተገለጠው ነገር ሁሉ የርሱ ነው፡፡
መክ.9:11-12 ”እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ሰልፍም ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። ሰውም ጊዜውን አያውቅም፤ በክፉ መረብ እንደ ተጠመዱ ዓሣዎች፥ በወጥመድም እንደ ተያዙ ወፎች፥ እንዲሁ የሰው ልጆች በክፉ ጊዜ በድንገት ሲወድቅባቸው ይጠመዳሉ።”
መክ.3:16,17 ”ደግሞም ከፀሐይ በታች በፍርድ ስፍራ ኃጢአት፥ በጽድቅም ስፍራ ኃጢአት እንዳለ አየሁ። እኔም በልቤ፡- በዚያ ለነገር ሁሉና ለሥራ ሁሉ ጊዜ አለውና በጻድቅና በኃጢአተኛ ላይ እግዚአብሔር ይፈርዳል አልሁ።”
ኢዮ.24:1-2 ”ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ ዘመናት አልተሰወረምና እርሱን የሚያውቁ ለምን ወራቱን አያዩም? የድንበሩን ምልክት የሚያፈርሱ አሉ፤ መንጋዎቹን በዝብዘው ያሰማራሉ።”
ሁሉን የሚችል አምላክ የዘመናት ባለቤት እንደመሆኑ የእያንዳንዱ ዘመን አመጣጥና አካሄድ በእርሱ ዘንድ ግልጥ የሆነ ነው፤ እንዲሁም በዘመን ውስጥ የሚገለጡት ነገሮች እንዲሁ ግልጥ ናቸው፡፡ እርሱን የሚያውቁ ወገኖች ካላስተዋሉ እግዚአብሄር የሚሰራውን ስራና የሚሰራበትን ዘመን አያውቁም፡፡
መክ.1:9-10 ”የሆነው ነገር እርሱ የሚሆን ነው፥ የተደረገውም ነገር እርሱ የሚደረግ ነው፤ ከፀሐይም በታች አዲስ ነገር የለም።ማንም። እነሆ፥ ይህ ነገር አዲስ ነው ይል ዘንድ ይችላልን? እርሱ ከእኛ በፊት በነበሩት ዘመናት ተደርጎአል።”
ዳን.2:20 ”ዳንኤልም ተናገረ እንዲህም አለ። ጥበብና ኃይል ለእርሱ ነውና የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ፤ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል፤ ነገሥታትን ያፈልሳል፥ ነገሥታትንም ያስነሣል፤ ጥበብን ለጠቢባን እውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል።”
– ጊዜውን ያልዋጀ ወደቀ
ጊዜን ያልዋጀ አንድ የግብጽ ንጉስ ከእግዚአብሄር ፈቃድ ጋር እንዴት እንደተጋጨ ቀጥሎ ባለው ቃል ውስጥ ይገኛል፦
ዘጸ.1:9-14 ”እርሱም ሕዝቡን፦ እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ሕዝብ ከእኛ ይልቅ በዝተዋል በርትተውማል፤ እንዳይበዙ፥ ሰልፍም በተነሳብን ጊዜ ጠላቶቻችንን አግዘው እንዳይወጉን ከምድሪቱም እንዳይወጡ፥ ኑ እንጠበብባቸው አለ። በብርቱ ሥራም ያስጨንቁአቸው ዘንድ ግብር አስገባሪዎችን ሾመባቸው፤ ለፈርዖንም ፊቶምንና ራምሴን ጽኑ ከተሞች አድርገው ሠሩ። ነገር ግን እንዳስጨነቁአቸው መጠን እንዲሁ በዙ፥ እጅግም ጸኑ፤ ከእስራኤልም ልጆች የተነሣ ተጸይፈዋቸው ነበር። ግብፃውያንም የእስራኤልን ልጆች በመከራ ገዙአቸው። በጽኑ ሥራ፥ በጭቃ፥ በጡብም በእርሻም ሥራ ሁሉ፥ በመከራም በሚያሠሩአቸው ሥራ ሁሉ፥ ሕይወታቸውን ያስመርሩአቸው ነበር።”
ይህ ንጉስ ጊዜው የእርሱ ሳይሆን የእግዚአብሄር መሆኑን ስላልተረዳ ከእግዚአብሄር ጋር ሲጋጭ ይታያል፤ በእግዚአብሄር ጊዜ የእግዚአብሄር ፈቃድ ብቻ ስለሚገለጥ ያን ያልተረዳ ከፈቃዱ ጋር ይላተማል። በሆነ ዘመን የእስራኤል ልጆች ወደ ግብጽ እንዲገቡ የእግዚአብሄር ፈቃድ ሆኖ ነበር፤ ህዝቡ እስከተወሰነው ዘመን ድረስ በዚያ እንዲኖር፣ እንዲዋለድና እንዲበዛ ፈቃዱ ነበር። እግዚአብሄር እስራኤል ከግብጽ የሚወጣበት ዘመን እንደደረሰ ሲያውቅ ህዝቡን መቀስቀስ ጀመረ። ያን የጊዜ ፍሰት ያላወቀ የአህዛብ ንጉስም ከአምላክ ጋር ተጋጨ።
እግዚአብሄር ይህን እቅድ ለአብረሃም አስቀድሞ ነግሮት ነበር፤ ይህን የእግዚአብሄር ፈቃድ ፈራኦን ስለማያውቅ ዘመኑን የሚዋጅ ጥበብ አልነበረውም።
ዘጸ.6:1-6 ”እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦በጸናች እጅ ይለቅቃችኋልና፥ በጸናችም እጅ ከምድሩ አስወጥቶ ይሰድዳቸዋልና አሁን በፈርዖን የማደርገውን ታያለህ።እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው አለውም። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ለአብርሃምም ለይስሐቅም ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ፤ ነገር ግን ስሜ እግዚአብሔር አልታወቀላቸውም ነበር። የተሰደዱባትንም ምድር፥ የእንግድነታቸውን የከነዓንን ምድር፥ እሰጣቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳኔን አቆምሁ።ደግሞ እኔ ግብፃውያን የገዙአቸውን የእስራኤልን ልጆች ልቅሶ ሰማሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አሰብሁ። ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከግብፃውያንም ባርነት አወጣችኋለሁ፥ ከተገዥነታቸውም አድናችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ”
ጊዜን ባልዋጀ ባሪያው ዘንድ መዘናጋትና ስንፍና ሆኖ እንደሆን ጌታው ድንገት በሚመጣ ጊዜ ብርቱ ቅጣት ይሆናል፤ እግዚአብሄር በወሰነው ሰአት ሲመጣ ተፈጽሞ ሊያየው የሚሻው እቅዱን በቸልታ ለሚመለከተው ቁጣውን እንደሚገልጥበት ቃሉ ይመሰክራል፦
ማቴ.24:42-51 ”ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና። እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ያ ክፉ ባሪያ ግን፡- ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ፥ ባልንጀሮቹን ባሮች ሊመታ ቢጀምር ከሰካሮችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥ የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፥ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል፥ እድሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።”
– ጊዜውን የዋጀ ነቢይ
ኢሳ.12:2-4 ”እነሆ፥ አምላክ መድኃኒቴ ነው፤ ጌታ እግዚአብሔር ኃይሌና ዝማሬዬ ነውና፥ መድኃኒቴም ሆኖአልና በእርሱ ታምኜ አልፈራም ትላለህ። ውኃውንም ከመድኃኒት ምንጮች በደስታ ትቀዳላችሁ። በዚያም ቀን እንዲህ ትላላችሁ። እግዚአብሔርን አመስግኑ፥ ስሙንም ጥሩ፤ በአሕዛብ መካከል ሥራውን አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ያለ እንደ ሆነ ተናገሩ።”
የአምላኩን አሰራር የሚያውቅ ባሪያ ማን ነው? ይህ ባሪያ የእግዚአብሄርን ጌትነት ብቻ ሳይሆን የሚሰራበትን ዘመን የሚያስተውል ነው።
ዳን.9:1-3 ”በከለዳውያን መንግሥት ላይ በነገሠ፥ ከሜዶን ዘር በነበረ በአሕሻዊሮስ ልጅ በዳርዮስ በመጀመሪያ ዓመት፥በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት እኔ ዳንኤል የኢየሩሳሌም መፍረስ የሚፈጸምበትን ሰባውን ዓመት፥ እግዚአብሔር በቃሉ ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረውን የዓመቱን ቍጥር በመጽሐፍ አስተዋልሁ። ማቅ ለብሼ በአመድም ላይ ሆኜ ስጾም እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ ወደ አምላክ አቀናሁ።”
የእግዚአብሄርን የስራ ዘመን የሚያስተውሉ ሰዎች የእርሱ ምርጦች ናቸው፣ እግዚአብሄርን እንዲሰራ ዘወትር ይለምኑታልና፣ ተስፋውን ይፈጽም ዘንድም በጸሎታቸው ዘወትር ያሳስቡታልና፤ እርሱም ስራውን ብቻ ሳይሆን የሚፈጸምበትንም ጊዜ በመንፈሱ ያመለክታቸዋል። በሚሰጣቸው ራእይ ጅማሬና ፍጻሜን፣ የፊተኛውንና የሁዋለኛውንም ዘመን ያመለክታቸዋል፦
ዳን.12:1-4 ”በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል፤ ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል፤ በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል። በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ፤ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና። ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ። ዳንኤል ሆይ፥ አንተ ግን እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ቃሉን ዝጋ፥ መጽሐፉንም አትም፤ ብዙ ሰዎች ይመረምራሉ፥ እውቀትም ይበዛል።”
ሰቆ.5:1-22 ”አቤቱ፥ የሆነብንን አስብ፤ ተመልከት ስድባችንንም እይ። ርስታችን ለእንግዶች፥ ቤቶቻችን ለሌሎች ሆኑ። ድሀ አደጎችና አባት የሌለን ሆነናል፤ እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆነዋል። የልባችን ደስታ ቀርቶአል፤ ዘፈናችን ወደ ልቅሶ ተለውጦአል። አክሊል ከራሳችን ወድቆአል፤ ኃጢአት ሠርተናልና ወዮልን! ስለዚህ ልባችን ታምሞአል፤ ስለዚህም ነገር ዓይናችን ፈዝዞአል፤ ስለ ጽዮን ተራራ፥ ባድማ ሆናለችና፥ ቀበሮችም ተመላልሰውባታልና። አቤቱ፥ አንተ ለዘላለም ትኖራለህ፤ ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው። ስለ ምን ለዘላለም ትረሳናለህ? ስለ ምንስ ለረጅም ዘመን ትተወናለህ? አቤቱ፥ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ። ”