– ጊዜ ጌታ?
የቀን ምንነት ለሚያሳስበውና ለሚመረምረው አንድ የሚታየው ጉልህ እውነት የነገው እለት ከዛሬው ጋር ተመሳሳይ መሆኑ ነው፤ ቀን ቀለም የለው የትኛውም እለት አይወዳደርበትም፣ አንዱ ከሌላው ከፍና ዝቅ አይል እግዚአብሄር እኩል አድርጎና ወስኖ ፈጥሮታል፣ ሰው በእርሱ ላይ ተጽእኖ የለውም ስለዚህ እንደተፈለገው ሊዘወር አይቻልም… ሰለዚህ የትላንትናው ቀን የነበረው ሰአት ዛሬም አለው፣ ነገም ከነገ ወዲያም እንዲሁ፤ ዋናው ነገር ያለው ቀኑ ይዞት የሚመጣው ነገር መለያየቱ ላይ ነው፣ በቀኑ ላይ የሚገለጠው ብዛቱ፣ አይነቱ የተወሳሰበ መሆኑ! በማቴ.6:34 ላይ፦
”ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።” ይላል፣ እያንዳንዱ ቀን ከራሱ የቤት ስራ ጋር ስለሚገለጥ ማለት ነው።
በእግዚአብሄር እቅድ ውስጥ ቀናቶች የእግዚአብሄርን ፈቃድ ስለሚገልጡ እኛ በራሳችን ጉዳይም ይሁን በሌላው እጅግ ተወጣጥረን ወይም ስሜታችን ቅዝቅዝ ብሎ ቀኑን መቀበል አያስፈልግም፡፡ ምክኒያቱም ቀኑ የእግዚአብሄር ነውና። ከእኛ የሚጠበቀው በቀኑ ውስጥ እየተገለጠ ያለውን ሁኔታ መገንዘብ፣ መከታተልና በእርሱ ላይ መወሰን ነው (ግን የእኛ በሆነው ነገር ላይ ብቻ)። በቀኑ ላይ ያለውን የርሱን ፈቃድ የመረዳት ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ማስተዋልም ያስፈልጋል፡፡
በእስራኤላውያን መሃከል ያሉ የይሳኮር ልጆች ለእስራኤል በተመደቡት ዘመናት ውስጥ ሊገለጥ ያለውን የእግዚአብሄር ፈቃድ መርምረው መግለጥ የሚችል ጥበብ ተሰጥቶአቸው ስለነበር ለወንድሞቻቸው ምሪት የሚሰጡ አስፈላጊ ሰዎች እበሩ።
1ዜና.12:32፤ ”እስራኤልም የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች የይሳኮር ልጆች አለቆች ሁለት መቶ ነበሩ፤ ወንድሞቻቸውም ሁሉ ይታዘዙአቸው ነበር።”
የጌታ ፈቃድ በዘመኖቻችን ውስጥ ምን እንደሆነ በመገንዘብ ዘመኑ ላይ እንድንሰለጥን ይጠበቅብናል። ቃሉ አንድ ጥበበኛ አማኝ በማስተዋል ራሱን በጥንቃቄ እንዲጠብቅና እየመጡ ያሉትን ክፉዎች ቀኖች ልብ እያለ ዘመኑን እንዲዋጅ እንጂ እንደ ሞኞች የጌታን ፈቃድ ሳያስተውል እንዳይወድቅ ይመክራል። በኤፌ5:15-17 ውስጥ ሲናገር፦
”እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ።”
በእግዚአብሄር አሰራር ተቃራኒ የሚመስሉ ነገሮች ተራቸውን ጠብቀው ይገለጣሉ፤ በእርሱ ፈቃድ ስለሆኑ ያለመናወጥና ያለመተረማመስ ልክ እንደታዘዙት ይሆናሉ፣ እንደተነገረላቸውም ይከሰታሉ፡፡ በእግዚአብሄር ፈቃድ ሲሆኑ እንደተባሉት ስለሚሆኑ ምንም የሚናጉ ነገሮች አይመጡም። እኛ ግን የእግዚአብሄርን ፈቃድ ብንከተል፣ ድምጹ ቢመራን እጅግ ተጠቃሚ ነን። በቃሉ ላይ የሚታዩ ዋነኞቹን ጉዳዮች ልብ እንበል፦ ዘመንና የጌታ ፈቃድ።
ቀናት በእርሱ ተፈጥረዋልና ቀን(ብርሃን ያለበት ክፍለ-ቀን) እና ምሽት ( ጨለማ የሚቆጣጠረው ክፍለ-ቀን) በየእለቱ ይፈራረቃሉ፡፡ ቀን ተገልጦ እንዳበቃ ለምሽት ስፍራውን ይለቃል፣ ምሽትም ለቀን እንዲሁ ያደርጋል፤ ወቅቶችም ተመሳሳይ ነገር ይታይባቸዋል፡፡ በጋና ክረምት አሉ፣ በጋ ይመጣል እርሱም ጊዜውን ጠብቆ በክረምት ይተካል፣ ክረምትም ጊዜውን ሲጨርስ ለበጋ ዳግም ይለቃል፤ አንዱ ለሌላው እንቅፋት ላይሆን አንዱ ሌላው ላይ ላያምጽ እግዚአብሄር ያፈራርቃቸዋል፤ ይህ የእግዚአብሄር ስራ ነው።
በጊዜ ውስጥ ደግሞ ድርጊቶችም ይፈራረቃሉ፡-ሃዘን በደስታ ይተካል፣ ደመና እንደ ዳመነ አይቀርም ጸሀይ ትወጣለች፣ ደክመን አንቀርም ብርታትም ይሆናል፤ ሁሉም በጊዜ ውስጥ ይከታተላሉ፤ ሁሎቹም ግን በተመሳሳይ ጊዜ አይሆኑም፣ ተራቸውን ይጠብቃሉ፡፡ ለሁሉም ጊዜ ተመድቦላቸዋል፤ እግዚአብሄር እንደፈቀደ ይህን አድርጎአል። ዘመኑን መዋጀት ደግሞ ይህን ያስረዳል፦
”ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። ለመወለድ ጊዜ አለው፥ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፤ ለመግደል ጊዜ አለው፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው፤ ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ ለመሥራትም ጊዜ አለው፤ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው፤ ድንጋይን ለመጣል ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፤ ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፤ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፤ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፤ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው። ለሠራተኛ የድካሙ ትርፍ ምንድር ነው? እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ይደክሙበት ዘንድ የሰጣቸውን ጥረት አይቻለሁ።” (መክ.3:1-10)
ጥቅሱ ነገሮች ሁሉ በጊዜ በተገደበ ለውጥ ውስጥ እንደሚያልፉ ያሳያል። በተለይ እግዚአብሄር በፈጠረው ነገር ላይ አላማውን ይፈጽም ዘንድ ጊዜ እንዳስቀመጠና የሚሆነውም በተራ እንዲሆን፣ እያንዳንዱ ክንዋኔውም በጊዜ ወሰን እንደታጠረ የሚታይ እውነት ነው። ለምሳሌ ሰው ተጸንሶ እስኪወለድ ጊዜ እንደሚፈልግ ሁሉ ያድግ ዘንድ ቀጣይ የሆነ ጊዜ ይጠይቃል፤ በእርሱ ላይ ሂደቱ በቀጠለ ቁጠርም በዚያው ልክ ጊዜ ያስፈልጋል። በእርሱ ላይ እየተከታተለ ለሆነው ነገር ሁሉ ጊዜ አስፈላጊ ነው፤ ለዚህም ነው ቃሉ ለሁሉም ጊዜ አለው የሚለው።
የምንኖረው በለውጥ ላይ ባለች ዓለም ውስጥ ነው፤ በጊዜ ውስጥ የሚያልፉት በርካታ ክስተቶች (የሰው ሕይወትና ሁኔታዎችን ጨምሮ) ቋሚነት ያላቸው ሳይሆኑ በጊዜ የሚለዋወጥ ተፈጥሮ ነው ያላቸው፤ በለውጥ ውስጥ የሚያልፉ ሁሉም አንዳቸው ከሌላው በእጅጉ የሚለያዩ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የሚከሰቱትም ያለማቋረጥ በለውጣቸው ውስጥ የሚያልፉ መሆኑ ነው። ደግሞ በየእለቱ፣ በየሳምንቱ፣ በየወሩ እና በየአመቱ በሚከሰቱ የለውጥ እንቅስቃሴዎች መካከል ማለፍ ግዴታ አለባቸው። በሌላ በኩል በተፈጥሮ ያሉ የለውጥ ሒደቶች መፍጠንና መዘግየት ስለሚፈራረቅባቸው ሁሎችም በጊዜ የተገደበ ተጽጸኖ እንዳረፈባቸው እናያለን። ነገሮች ግን የሚለዋወጡት በጊዜ ተጽእኖ ምክኒያት ሳይሆን በእግዚአብሄር ፈቃድ ብቻ ነው።
ማናቸውም በእኛ ላይ የሚሆኑ ለውጦች ከወቅት እና ከጊዜ ጋር የተያያዙ ቢሆኑም/ በነርሱ ውስጥ የሚያልፍ ቢሆንም/ ሁሎቹም የእግዚአብሄርን ጣልቃ ገብነት ይፈልጋሉ። እኛም የሚሆኑትን መቀበል የሚገባን አድራጊም ፈጣሪም እርሱ በመሆኑና በእኛ ለሚሆነው ነገር ሌላ ተጠያቂ ባለመኖሩ ነው።
ለሁሉም ነገር ፍጻሜ ዘመን አለው፣ አንዱ ነገር ከሌላው ጋር አብሮ ይኖራል እንጂ በለውጥ ውስጥ የራሱን ሰአት (የተወሰነ እድሜ) ይዞ የሚጉዋዝ ነው። ለምሳሌ ምድርና ጸሃይ በለውጥ ሂደት ውስጥ የሚያልፉ የእግዚአብሄር እጅ ስራ ናቸው፤ ሁለቱም በጊዜ በሚለካ የለውጥ ዘመን ውስጥ ይለፉ እንጂ የሚለወጡበት ፍጥነት አንድ ነው ማለት አይደለም። እያንዳንዳቸው የየራሳቸውን ዘመን ይቆጥራሉ በዚያ ውስጥም ያልፋሉ። ተከታታይ ክስተቶችም ቢሆኑ የየራሳቸውን ጊዜ ይሻሉ፦ ከላይ እንደተባለው በምድር ላይ የሚገለጡ ቀንና ምሽት አሉ፤ ቀኑ ለሌሊት ሌሊትም ለቀኑ በመፈራረቅ ቦታ ይለቃል፣ ይህን በጊዜ ገደብ ያደርጉታል። ክረምት ነው? ትንሽ ቆይ፣ በጋ ይመጣል። እያንዳንዱ ክስተት የባለቤቱ ዓላማ መገለጫ ነውና የራሱ ጊዜ ተሰጥቶታል። በጣም ጥርት ያለ ሰማይ ከነፍካቱ ይታያል፣ ቆይቶ ግን ደመና ይሆናል፣ አንዱ ሌላውን ሊተካ ግድ ይላልና፤ ደስታ ካለ እንዲሁ ሀዘንም ነው፣ ሁለቱም በሆነ ወቅት ይመጣል።
ካስተዋልን ለእኛ በጣም ተራ እና የሚታለፉ የሚመስሉን ነገሮች በእግዚአብሔር ምክርና በቀደመ እውቀቱ የተወስኑና የተገለጡ ናቸው፤ ሁሉም ሰዓታቸው የተወሰነ ነው፤ በዚህ ምክኒያት ለሁሉም ጊዜ አለው ተባለላቸው፣ በተለይ የእግዚአብሄር አላማ ያለባቸው ነገሮች ሲመጡ ሰከንድ አያዛንፉም። ጊዜን በአግባቡ የሚጠቀምበት ሁሉን የፈጠረ የጊዜም ጌታ የሆነው እርሱ ነው፤ ስለዚህ የሚሆኑት ነገሮች ለእኛ በጊዜ ተጽእኖ ምክኒያት የሚከናወኑ ይመስለናል እንጂ አከናዋኙስ ፈጣሪ አምላክ ብቻ ነው። ጊዜን የፈጠረ እርሱ አይደለምን? በጊዜ ውስጥ እጁን አሾልኮ የሚመጣስ እርሱ አይደለምን? እርሱን ማየት ያልቻለ ግን ማየት የሚችለው ጊዜውን ብቻ ነው የሚሆነው።
”እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው። የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው። ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል።” (ቆላ.1:15-16)
በጌታ ኢየሱስ ፈቃድ መፈጠራችንስ ምን ያመላክተናል፦
• እርሱ ሲፈጥረን አንድ ነገር በሂደት እንዲያልፍብን አድርጎአል፤ ለመወለድ ጊዜ አለው ለመሞትም ጊዜ አለው ብሎ በጊዜ የተገደብን እንድንሆን አድርጎአል። እነዚህ አሰራሮች በመለኮታዊ ምክር የተወሰኑ ናቸው፤ በተቀጠረው ጊዜ እንደ ተወለድን እንዲሁ በወሰነልን ጊዜ እንሞታለን። በነዚህ ሂደቶችም በኩል የእግዚአብሄር ማንነትን እናውቃለን፣ ባለቤትነቱንም እናስተውላለን።
• የእግዚአብሄርን አላማ ሰፋ አድርገን ስናየው ደግሞ እግዚአብሔር ሕዝብን የሚፈጥርበትና የሚተክልበት ጊዜ እንዳለው እናያለን፤ እግዚአብሄር ከግብጽ አውጥቶ እስራኤልን በከነዓን ተክሎአል፤ ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ስለ እስራኤል ሃጢያት ዳግሞ ይነቀሉና ይጠፉ ዘንድ ወስኖአል፤ የበደላቸው ጽዋ በሞላ ጊዜ ስለ እስራኤል በተናገረው መሰረት በተቀጠረውም ጊዜ ያን አድርጎአል። የህዝቡን ታሪክ ስናጠና የሆነባቸው ሁሉ የሆነውና የተገለጠው በእግዚአብሄር ጊዜ ነው። እርሱ በዚህ ዘመን የአብረሃም ዘሮች ግብጽ ይገባሉ አለ፣ ይህን ያህል ዘመን በዚያ ይቆያሉ፣ ይህን ያህል ዘመን ከግብጽ ወጥተው ይጉዋዛሉ… እያለ በጊዜ የተወሰነላቸውን ፕሮግራም አውጥቶአል፣ አከናውኖአልም፤ ምክኒያቱም ከሰማይ በታች ለሚደረግ ነገር ሁሉ ጊዜ ስላለው፣ ደግሞም እንዲሆኑ የሚያዝዝ አምላክ በመኖሩ። ከአብረሃምና ከዘሩ የሚፈለገው ዘመኑን መዋጀት ብቻ( በየትኛው ዘመን የቱን ላድርግ ሲል መጠየቅ ብቻ)፣ በአብረሃም ላይ የተናገረውን አድራጊውማ እግዚአብሄር ነው።
• ለመግደል ጊዜ አለው ሲባል የእግዚአብሔር ፍርድ በምድሪቱ ላይ የሚገለጥበት ጊዜ አለው፣ ያኔ ሁሉንም የሚያፈርስበት ጊዜ ይሆናል ማለት ነው። በምሕረት መንገድ ላይ ሲመለስ ግን ያጠፋውን ህዝብ የሚፈውስበት ጊዜ ይመጣል (ሆሴዕ 6፡1፤ ሆሴ 6፡2)፤ ህዝቡን ካስጨነቀው ጊዜ በኋላ ያንኑ ሕዝብ የሚያጽናናበት ጊዜ ይመጣል።
• እግዚአብሄር በአመጽ ምክኒያት ቤተሰብን፣ አገርን፣ መንግሥትን የሚያፈርስበት ጊዜ አለው፤ ሰዎች ግን ተመልሰው ንስሐ ቢገቡ ያፈረሰውን ለማነጽ ጊዜን ይሰጣል። እግዚአብሔር ጽዮንን የሚሠራበት ጊዜ ያ በእርሱ የተወሰነ ጊዜ ነው(መዝ 102:13፣ መዝ 102፡16)።
”ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና፥ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናል፥ እርሱም ይጠግነናል። ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፤ በሦስተኛውም ቀን ያስነሣናል፥ በፊቱም በሕይወት እንኖራለን። እንወቅ፤ እናውቀውም ዘንድ እግዚአብሔርን እንከተል፤ እንደ ወገግታም ተዘጋጅቶ እናገኘዋለን፤ እንደ ዝናብም ምድርንም እንደሚያጠጣ እንደ መጨረሻ ዝናብ ይመጣል። ምሕረታችሁ እንደ ማለዳ ደመና፥ በማለዳም እንደሚያልፍ ጠል ነውና ኤፍሬም ሆይ፥ ምን ላድርግልህ? ይሁዳ ሆይ፥ ምን ላድርግልህ?ስለዚህ በነቢያት እጅ ቈረጥኋቸው፥ በአፌም ቃል ገደልኋቸው፤ ፍርዴም እንደ ብርሃን ይወጣል።” (ሆሴ.6:1-5)
እዚህ ላይ እግዚአብሄር ነገሮችን በወሰነው ሰአት ሲያከናውን እናያለን፤ ከዚሁ ጋር አንድ አስፈላጊ ነገር ደግሞ እንድናውቅ ይጋብዛል፦ እርሱን እንወቅ ሲል ይናገራል፤ ደግሞ እናውቀውም ዘንድ እግዚአብሔርን እንከተል፤ እንደ ወገግታም ተዘጋጅቶ እናገኘዋለን፤ እንደ ዝናብም ምድርንም እንደሚያጠጣ እንደ መጨረሻ ዝናብ ይመጣል ይላል። ሲመጣና ስናውቀው የሁሉ ጌታንና የእርሱን ስራ እናስተውላለን፤ በጊዜ ውስጥ የሰራውን አምላክ ፊት ለፊት እናየዋለን፣ በዚያም እርሱን እናነግሰዋለን በራሳችን ላይ ጌታ እናደርገዋለን።
• የእግዚአብሄር የስራ ጊዜ ብዙ ነገር ይገጣል፤ ከዚያም መሃል ስለሃዘን የሚሆነው ነገር ነው፦ እግዚአብሔር የማልቀስ እና የማዘንን ጊዜ በጠራ ወቅት ቸልተኞች ሰዎች እውቀትና ጥበባቸውን ተመክተው ቢለፉም ከዚያ አያመልጡም፤ ለምልጃ ሲጠራ ይልቅ ጥሪውን አክብረው የሚያለቅሱ ብቻ የሚድኑበት ነው፣ ችግሩ እርሱ ጥፋትና አደጋ በደጅ ላይ መሆናቸውን አይቶ ሲናገር እኛ የጊዜውን ሁኔታ ስለማናስተውል እንቢ ብለን እንጎዳለን (ዘመኑን መዋጀት ይሳነናል)።
ኢሳ.22:12 ሲናገር ”በዚያም ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወደ ልቅሶና ወደ ዋይታ ራስን ወደ መንጨትና ማቅንም ወደ መልበስ ጠራ።” ይላል። በተጣራ ጊዜ ግን ማን ሰምቶ መጣ? ያንን ነው እግዚአብሄር የሚያየው፣ ዘመኑን የዋጀና ለርሱ ጥሪ የመለሰ ይኖር እንደሆን አስተዋይን ከሰው ልጆች መሃል በዚያ ይፈልጋል።
በሌላ በኩል፣ እግዚአብሔር ደስታን የሚጠራበት ጊዜ አለ፣ ለመሳቅም ለመቦረቅም ጊዜ አለውና። አትኩሮና አስተውሎ የተመለከተ ካለ ያኔ እርሱን በምስጋናና በልብ ደስታ ያገለግለው ዘንድ ይጠብቃል።
ወደ ተነሳንበት ስንመለስ ጊዜ በሰው እጣ ፋንታ ላይ ተጽእኖ ሊያደርግ የሚችል ገዢ ነው ሲሉ ጊዜን በጌትነት ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ ወገኖች ጥቂት እንዳይደሉ እንመለከታለን፡፡ ለምሳሌ የዘመን ቁጥር ነገርን ሲገልጠው የምናየው በጊዜ ውስጥ መውደቅ በጊዜ ውስጥም መነሳት ያለፈ በመሆኑ ነው፡፡ ያን ተከትሎ የሂደትና የክስተት መፈራረቅ በተሰጣቸው የውስጥ ጉልበት በነገሮቹ ላይ ሊመላለሱ አይቀሬ በመሆኑ ሰዎች በመልሱ በሚደርስባቸው ነገር ሊከፉ ወይም ሊደሰቱ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ ጊዜና ሁኔታ ሲገጣጠሙ የሆነ ክስተት በሆነ ዘመን ላይ እንዲህ ሆኖ ይታይ እንጂ ጊዜው ሃይል አውጥቶ የትኛውንም ነገር በራሱ ጉልበት አላደረገውም፣ ሊያመጣውም አይችልም።
ስራውን በጊዜ ውስጥ የሚሰራ አምላክ
ኤር.5:24”በልባቸውም፦ የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ በጊዜው የሚሰጠውን፥ ለመከርም የተመደቡትን ወራት የሚጠብቅልንን አምላካችንን እግዚአብሔርን እንፍራ አላሉም።” ይላል።
ልብን የሚመረምር አምላክ የሰውን የአሳብ ይዘት መዝኖ የተናገረው ይህ ቃል ሰው በእግዚአብሄር ስራ ላይ ያለውን የግንዛቤ ችግርና ትኩረቱ እንደምን አቅጣጫውን እንደሚስት በግልጽ ያመለክታል፦
ዝናብ ሲመጣ፣ ወቅቱን ጠብቆ ሲፈራረቅ አላየንም? አይተናል፣ ሆኖም አፈራራቂውን/አዝናቢውን ልብ አላልንም። ስለዚህ ጊዜን አጉልተን ጌትነት ደረጃ ላይ አደረስነው ማለት ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ ካየነውና ከሰማነው፣ በተለምዶ ከሚነገሩ አባባሎች ተነስተን፣ እንዲሁም ሌላ አማራጭ/የተሸለ ባለቤት እንዳለ በግምታዊ እውቀት በመደምደማችን… የተለያዩ ነገሮች ያን እንድንልና እንድናምን ሆኖአል፡፡ ቃሉ ግን እንወቅ፤ እናውቀውም ዘንድ እግዚአብሔርን እንከተል ካለ እግዚአብሄርን ከማወቅ ቀጥሎ ለእኛ የሚመጣ የሚጠቅመን እውቀት (የጊዜን ሁኔታ የሚያሳውቀውን ጨምሮ) አለ ማለት ነው።