ጊዜ ጌታ? [1..]

ቤተክርስቲያን

 
የሁሉ አምላክ እግዚአብሄር ስለእኛ ሲል ጊዜን ፈጥሮአል (ዘፍ.1.14-17)፡-
”እግዚአብሔርም አለ፡- ቀንና ሌሊትን ይለዩ ዘንድ ብርሃናት በሰማይ ጠፈር ይሁኑ፤ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም ይሁኑ፤ በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር ብርሃናት ይሁኑ፤ እንዲሁም ሆነ። እግዚአብሔርም ሁለት ታላላቆች ብርሃናትን አደረገ፤ ትልቁ ብርሃን በቀን እንዲሠለጥን፥ ትንሹም ብርሃን በሌሊት እንዲሰለጥን፤ ከዋክብትንም ደግሞ አደረገ። እግዚአብሔርም በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ በሰማይ ጠፈር አኖራቸው”
ብርሃናት በሰማይ ጠፈር እንዲሆኑ ሲያዝ ለምልክቶች ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም እንዲሆኑ ነበር፤ እንዲሁም በምድር ላይ ያበሩ ዘንድ ሰጣቸው። በጠፈር ላይ እግዚአብሄር ያኖራቸው እነዚህ ብርሃናት ጊዜያትን ለመለየት ተፈጥረዋልና ቀንና ምሽት፣ ክረምትና በጋ ሁሎችም የሚለዋወጡት በጸሀይና በጨረቃ ምክኒያት እንዲሁም ምድር በምታደርገው እንቅስቃሴ ምክኒያት ነው፡፡ ስለዚህ የጸሀይ መታየት ቀንን ሲፈጥር የጸሀይ መሰወር ምሽትን ያመጣል፡፡ እንዲሁም ጸሀይ ወደ ምድር ወገብ ስትጠጋ (የምድር መሽከርከር በሚፈጥረው አቅጣጫ)  በጋ፣ ስትርቅ ክረምት እየተፈጠረና ክስተቱ ሳያቁዋርጥ ሁሉን እያፈራረቀ ምድር ላይ ይገልጣቸዋል፡፡ በእያንዳንዱ የጊዜ ፍጥነት ውስጥ እግዚአብሄር ስላለ ፈቃዱ በጊዜና በአመታት መካከል የሚገለጥ ሆኖአል፡፡
​​​​​​​​መክ.3:1 ”ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው።” ይላል፤ በዚህ ምክኒያት ነገሮች በጊዜ በተወሰነ ኡደት ውስጥ ማለፋቸው በጊዜ በተወሰነ ተራ እንደሚከሰቱ የሚያሳይ ነው ፣ በጊዜ ውስጥ እንደሚቀያየሩና ስለእግዚአብሄር ፈቃድ ብለው ሳይዛቡ የሚገለጡ መሆኑንም የሚያሳዩ ናቸው። እንዲሁም ነገሮች ሲከሰቱ ድንገት የሆኑ ይምሰልን እንጂ ለሁላቸውም መከሰት እግዚአብሄር ዘመን እንደሰጣቸው ከቃሉ የምናስተውለው ነው።
​​​​​​​​ዕን.3:2 ”አቤቱ፥ ዝናህን ሰምቼ ፈራሁ፤ አቤቱ፥ በዓመታት መካከል ሥራህን ፈጽም፤ በዓመታት መካከል ትታወቅ፤ በመዓት ጊዜ ምሕረትን አስብ።”
ነቢዩ የእግዚአብሄርን ማንነት ባስተዋለ ጊዜ ታላቅነቱ አስፈርቶታል፣ በሌላ በኩል ሊሰራ ያለው ሲታሰበው ደግሞ ተጽናናና ስራውን በጊዜው እንዲሰራውና እንዲገልጠው በእምነት ጸለየ። ዝናው የሚያስፈራ አምላክ  በዓመታት መካከል ተገልጦ የሚሰራው ሥራ ላስተዋለው ግሩም አስደናቂም ነው። ነቢዩ በጊዜው የሚገለጠው የእግዚአብሄር ፍርድ በመጣ ጊዜም ምሕረትን ለሚጠባበቁት ያን ይሰጣቸው ዘንድ ማለዶአል።
የጊዜ መኖር ምድር ላይ ማናቸውም ተግባራት መሆን የሚገባቸውን ነገር እንዲሆኑ አቅጣጫ የሚወስንላቸው መንገድ ነው፡፡ እያንዳንዱ የጊዜ ሽርፍራፊ ለአላማ ተወስኖአል፤ የእግዚአብሄር አሳብ ወደ ፍጥረቱ በተለይ ወደ ሰው ልጅ የሚደርስበት መንገድ በዚያ እንዲገለጥም ሆኖአል።በመክ.3:11 ላይ ሲናገር፦
”ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው።” አለ።
እግዚአብሄር ብርሀንን በቀን አድርጎ በቀኑ የሚጠበቀውን ስራና እቅድ እንድንፈጽም ያደርጋል፡፡ ነገር ግን የሰማይ ብርሃናት በራሳቸውና ለራሳቸው አልተፈጠሩም፤ በአላማ እንደመፈጠራቸው በዚያው ልክ የፈጠራቸው አምላክ ለእርሱ ፈቃድ እንዲያገለግሉ አድርጎአቸዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህ የብርሃን አካላት እኛን ለመጥቀምና ለማስደሰት ከአምላካችን ተሰጥተውናል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሄር ብርሃንን ስላበራልን ወጥተን ተመልሰናል፣ ተኝተን ተነስተናል፣ ሰርተን ገብተናል፣ ተምረናል፣… ለዚህ ስኬት የሰማይ ሰራዊት እኛን እንዲያግዙ እግዚአብሄር ተክሎአቸዋል፡፡ ዋናው ነገር እግዚአብሄር እኛን ለማገልገል ፍጥረታትን እንዲህ ቢያጸናም እኛስ እግዚአብርን ለማገልገል ዝግጁ ነን ወይ? እርሱ ግን ነገሮቹን በጊዜያቸው ውብ አድርጎ ሠርቶአቸዋል። እንዲያውም ሲጠይቅ እኔ የምሰራበትን የዘመኑን ምልክት መለየት አትችሉምን? ሲል ይጠይቃል።
​​​​​​​​ማቴ.16:1-3 ”ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንም ቀርበው ሲፈትኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ለመኑት። እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው፡- በመሸ ጊዜ፡- ሰማዩ ቀልቶአልና ብራ ይሆናል ትላላችሁ፤ማለዳም፡- ሰማዩ ደምኖ ቀልቶአልና ዛሬ ይዘንባል ትላላችሁ። የሰማዩን ፊትማ መለየት ታውቃላችሁ፥ የዘመኑንስ ምልክት መለየት አትችሉምን?”
ጊዜ፣ ወቅት፣ ዘመን… ለፍጥረት በሙሉ የተሰጠ የእድሜ መለኪያ ነው፤ የወቅትን እርዝማኔ፣ የጊዜን መቀያየር፣ የነገሮችን እድሜ በነርሱ እናይበታለን፡፡ በሌላ በኩል ጊዜ የእድሜ ቁጥር ብቻ ሳይሆን የክንዋኔና የስርአት መዘውር ርዝማኔም ነው፡፡ ጊዜ የሁኔታዎች ክስተት መገለጫ ወቅት በመሆን ምድራዊ ኑሮን ትርጉም ይሰጠዋል፤ ለፍጥረት የተሰጠ የህልውናቸው መለኪያ እንደመሆኑም ያለጊዜ ፍጥረት እድሜ የለውም፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ፍጥረትና ጊዜ ያላቸውን ቁርኝት እንደሚከተለው ያሳያል፡-
ዘፍ.2:4 ”እግዚአብሔር አምላክ ሰማይንና ምድርን ባደረገ  ቀን፥ በተፈጠሩ ጊዜ የሰማይና የምድር ልደት ይህ ነው።”
እግዚአብሄር ዘመናትን ከሰራው ስራ ጋር ያቆራኛቸዋል። ደግሞ በእርሱ ጊዜ ውስጥ ተጀምረው የማይጠናቀቁ ስራዎች ፈጽሞ የሉም። በዘመናችን ሁሉ የሚሰራ አምላክ የጊዜ አምላክ ነው፤ የሰጠውን ጊዜና ዘመን በትክክል ያልተጠቀመበት ሰው የተሰጠውንና ያባከነውን ያን መልሶ አይቀበለውም። ከቃሉ ስንመለከት ለሰው ልጅ ከግዚአብሄር ጋር የሚኖርበት አጋጣሚ የተሰጠው ገና ከመፈጠሩ አንስቶ ነበር። ያን አጋጣሚ ግን አልተጠቀመበትም።
ዘፍ.3:16 ”ለሴቲቱም አለ፡- በፀነስሽ ጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል።”
በዘመን ላይ የሚገለጥ የእግዚአብሄር ፈቃድ እኛ ላይ የገለጠው ምንድር ነው? እግዚአብሄርን ባለማወቅ ምክኒያት የሚያመልጠን ሊሰጠን ግን የተገባ የእግዚአብሄር ነገር ዘመናችን የበረከትና የተድላ እንዳይሆን እንዳደረገው ከላይ ባለው ቃል ላይ እናገኘዋለን። የሄዋን ያለማስተዋል ለጠላት አጋለጣት፣ ጠላትም ከእግዚአብሄር ፈቃድ አለያያት። በተፈጠረች ጊዜ ከእግዚአብሄር የተሰጣት ነገር ተገልብጦ ከበጎ ወደ ጭንቅ፣ ፈቃድዋ ከርስዋ ወጥቶ ለሌላ ሰው የሆነውም በትክክለኛው ጊዜ ትክክለኛ ውሳኔ ባለመውሰድዋ ጊዜዋንም ከእግዚአብሄር ጊዜ ጋር አንድ ባለማድረጋዋ ነበር።
ኢዮ.9:19 ”የኃይል ነገር ቢሆን እርሱ ኃያል ነው፤ የፍርድ ነገር ቢሆን፦ ጊዜን ወሳኙ ማን ነው? ይላል።”
ጊዜ የእግዚአብሄርን ሃይልና ፍርድ ይገልጣል። ፍጥረት የማይታየው እግዚአብሄርን ለማመን ቢያዳግታቸውም እርሱ ህያው መሆኑን በተለየ መንገድ ያረጋግጣል። የእግዚአብሄር ስራ የምናየው አንድ ፍጥረት መቼ ተፈጠረ፣ ተወለደ፣ ወይም ተገኘ? ምን ያህል ዘመንስ ኖረ? እንደ ምድር ያለ ፍጥረት ከተፈጠረ ጊዜ አንስቶ ምን ያህል ጊዜ ኖሮአል? ምን ያህል ዘመንስ ወደፊት ይኖራል? ብለን በመጠየቅ ብቻ አይደለም።
መዝ.19:1-6 ”ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል። ቀን ለቀን ነገርን ታወጣለች፥ ሌሊትም ለሌሊት እውቀትን ትናገራለች። ነገር የለም መናገርም የለም፥ ድምፃቸውም አይሰማም። ድምፃቸው ወደ ምድር ሁሉ፥ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ። በእነርሱም ውስጥ የፀሐይን ድንኳን አደረገ፥ እርሱም እንደ ሙሽራ ከእልፍኙ ይወጣል፤ እንደ አርበኛ በመንገዱ ለመሮጥ ደስ ይለዋል። አወጣጡ ከሰማያት ዳርቻ ነው፥ ዙረቱም እስከ ዳርቻቸው ነው፤ ከትኩሳቱም የሚሰወር የለም።”

  • ተወሰንን ነን

ሰዎች ስራቸውን በጊዜ በተገደበ ሁኔታ ያከናውናሉ፡፡ እኛም ብንሆን በእድሜ የተገደብን ነን። ቀናት፣ ሳምንታት፣ አመታት ይሁን ብቻ ከግባቸው እስኪደርሱ ነገሮች በትእግስት ይፈጽሙታል፡፡ ለምሳሌ አንድ ተማሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚያጠናቅቅበትን ቢያንስ 12 አመታት በትእግስት ማሳለፍ ይጠበቅበታል፡፡ ተማሪው እውቀቱን በጊዜ በተገደበ ስርአት ሊቀበል አምኖ ትምህርት ቤት ገብቶአል፤ ስለዚህ ያለጊዜው ክፍሎችን ዘልሎ ሊሻገር ፈጽሞ አይሞክርም ማለት ነው።  የነገሮችም ኡደት ቢሆን እንዲሁ የጊዜ ስርአትን ተከትለው የሚሄዱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የወቅቶች መፈራረቅ በጊዜ ርዝመት የተለካና ኡደትን ጠብቆ የሚጉዋዝ ነው፡፡ ከላይ ያየናቸው ሁኔታዎች በጊዜ የተገደቡ እንደመሆናቸው የጊዜ ተጽእኖ በላያቸው ጎልቶ ይታያል፡፡
​​​​​​​​መክ.3:1-9 ”ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። ለመወለድ ጊዜ አለው፥ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፤ ለመግደል ጊዜ አለው፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው፤ ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ ለመሥራትም ጊዜ አለው፤ ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው፤ ድንጋይን ለመጣል ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፤ ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፤ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፤ ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፤ ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው። ለሠራተኛ የድካሙ ትርፍ ምንድር ነው?”
ይህ ጥቅስ አለም ባለማቁዋረጥ እየተለወጠች ያለበትን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ለውጥዋ በጊዜ የሚገለጥ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በምትለዋወጠው አለም ውስጥ የተለያዩ ክስተቶች መስተናገዳቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ በህይወታችን ውስጥ የሚከሰቱት ገጠመኞች በሙሉ ከምድር ዙረት ተከታታይነት ጋር የሚፈራረቁ በመሆኑ በጊዜ ውስጥ ይገለጣሉ፡፡ በዚህ የተፈጥሮ ኡደት ውስጥ የሰው ነገር እንደዚያው እየተገለጠ የሚሄድ ሲሆን የተለያየው ገጠመኝም በጊዜ ገደብ የተወሰነ ይሆናል፡፡ አለም በጊዜ ተጽእኖ ስትለዋወጥ የመለዋወጥዋ መልክ የሰውን የኑሮ ሁኔታ ይለዋውጠዋል፡፡ ልክ የአየር ንብረት በተጽኖዋ እንደሚለውዋወጠው ሁሉ ማለት ነው። በጊዜ ውስጥ ተገልጠው በእኛ ስሜትና ኑሮ ላይ ተጽእኖ የሚያደርጉ ነገሮች ግን በእግዚአብሄር ሀይል ቁጥጥር ስር መዋል የሚችሉ ናቸው፣ ገዢና ተቆጣጣሪው እርሱ ነውና፡፡ ሊሆኑ ያላቸው ነገሮች እንደተወሰነላቸው ከመሆን ውጪ በሌላ መልክ መገለጥ የሚችሉበት ሁኔታ አይኖርም ምክኒያቱም የተከሰቱት ነገሮች የሆኑት ባለቤት በሆነው  እግዚአብሄር ፍቃድ በመሆኑና እኛም የሚሆነውን ከመቀበል ውጪ የሆነውን መለወጥ የማንችል በመሆናችን ነው፡፡
​​​​​​​​መዝ.74:12-17 ”እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ። አንተ ባሕርን በኃይልህ አጸናሃት፤ አንተ የእባቦችን ራስ በውኃ ውስጥ ሰበርህ። አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፤ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው። አንተ ምንጮቹንና ፈሳሾቹን ሰነጠቅህ፤ አንተ ሁልጊዜ የሚፈስሱትን ወንዞች አደረቅህ። ቀኑ የአንተ ነው ሌሊቱም የአንተ ነው፤ አንተ ፀሓዩንና ጨረቃውን አዘጋጀህ።አንተ የምድርን ዳርቻ ሁሉ ሠራህ፤ በጋንም ክረምትንም አንተ አደረግህ።”
ጊዜያቶች በእግዚአብሄር እጅ ሲሆኑ መልካም ነገርን ይገልጣሉ፣ ነገሮች ሁሉ በጊዜያቸው በእጁ ሲከናወኑ ውብ የሆነ ፍጻሜ እንዳላቸው በተናገረው መሰረት፤ በሰው እጅ ግን ያን መጠበቅ አንችልም።
እኛን የሚመለከቱ ነገሮች በጊዜያቱ ሲመጡ በማስተዋል እንይዛቸው ዘንድ እንደሚያስፈልግ በቃሉ ተጽፎልናል፡፡ ጊዜያቶች በእርሱ የተወሰኑ ስለሆኑ በራሳችን ልንለውጣቸው አንችልም፡፡ ሀያል አምላክ ግን ያን ሊያደርግ የላቀ ሀይል አለው፣ ጊዜያትን በዚያ ይቆጣጠራል፣ ጊዜና ወቅቶች በእርሱ እስከተፈጠሩ ድረስ በነርሱ ውስጥ እኛ ማለፋችን የግድ እንጂ አማራጭ የለውም፡፡ በራሳችን ነገሮችን ልንወስን ቀናቶቻችንን ልናረዝምም ሆነ ልናሳጥር አልተፈቀደም/ስልጣን የለንም፣ በተቀጠረልን እድሜ ከመኖር ውጪ የምናደርገው ምንም የለም፡፡ በዚህ ምኞት ውስጥ የሚያልፉ ጠላት ዲያቢሎስ የሚሸነግላቸው ሰዎች ናቸው፣ ይህ አሳብ መነሻው ከእርሱ ስለሆነ፦
​​​​​​​​ዳን.7:25-27 ”በልዑሉም ላይ ቃልን ይናገራል፥ የልዑልንም ቅዱሳን ይሰባብራል፥ ዘመናትንና ሕግን ይለውጥ ዘንድ ያስባል፤ እስከ ዘመንና እስከ ዘመናት እስከ እኵሌታ ዘመንም በእጁ ይሰጣሉ።ነገር ግን ፍርድ ይሆናል፥ እስከ ፍጻሜም ድረስ ያፈርሱትና ያጠፉት ዘንድ ግዛቱን ያስወግዱታል።መንግሥትም ግዛትም ከሰማይም ሁሉ በታች ያሉ የመንግሥታት ታላቅነት ለልዑሉ ቅዱሳን ሕዝብ ይሰጣል፤ መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ነው፥ ግዛቶችም ሁሉ ይገዙለታል ይታዘዙለትማል።”
ከሰይጣን በወረስነው ትእቢት ምክኒያት ሰዎች በራሳችን የህይወት ሁኔታ ነገሮችን የምንለውጥ የሚመስለን ጊዜ አለ፡፡ ገንዘብ፣ ስልጣን ያልያም እውቀት ካለን ያሻንን ልናደርግ፣ በእግዚአብሄር እየተከናወኑ ያሉ በጊዜው የሚገለጡትን ነገሮች የምንለውጥም ሊመስለን ይችላል፣ ያን ለማድረግ እንሞክራለንም፡፡ እርምጃችን የማይገባ ቦታ የሚያስገባን፣ ተቀባይነት የማያተርፍ ድርጊትም እንድንፈጽም የሚገፋ ሊሆን የሚችል ነው፡፡
አለም በማያቁዋርጥ ለውጥ ላይ ናት፣ የሰዎች የህይወት ይዘት የተዘበራረቀ ነው፣ በስምምነት መኖር እስኪያቅት ድረስ በመሃላችን የሚሆን መልካም ያልሆነ ነገር አለ፤ ግን ይሄም ይሁን ያ በመለዋወጥዋ ውስጥ እኛ በራሳችን ፈቃድ ምድርን መዘወር፣ ጊዜን መለዋወጥ እንደምንችል እስኪሰማን የምንሄደው አካሄድ ችግር እየሆነብን ነው፡፡
​​​​​​​​መክ.3:12-15 ”ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። እግዚአብሔር ያደረገው ሁሉ ለዘላለም እንዲኖር አወቅሁ፤ ሊጨመርበት ወይም ከእርሱ ሊጐድል አይቻልም፤ እግዚአብሔርም በፊቱ ይፈሩ ዘንድ አደረገ። አሁን ያለው በፊት ነበረ፥ የሚሆነውም በፊት ሆኖ ነበር፤ እግዚአብሔርም ያለፈውን መልሶ ይሻዋል።”
የእግዚአብሔር ስጦታ ሙሉ ነው፤ ሰው ተቀብሎ አምላኩን እያመሰገነ እንዲጠቀምበት ተሰጥቶታል፤ ታዝዞ በመኖር አምላኩን እንደሚያስደስት እንጂ በሕይወቱ ሳለ ሌላ መልካም ነገር እንደማያተርፍ ቢያስተውል በዚህ ይባረካል። ጊዜ የማይወስነው ዘላለማዊ አምላክ እርሱ የሰራውን፣ ያቀደውንና የፈቀደውን ሰው ቢያስተውል ሞገሱን የሚሰጥ ቸር አምላክ ነው፤ ያን የማያስተውል ትውልድ ምን ያገኘው ይሆን?
​​​​​​​​ሮሜ.1:18-23 ”እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣልና፤እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው፥ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና።የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ።ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ፥የማይጠፋውንም የእግዚአብሔር ክብር በሚጠፋ ሰውና በወፎች አራት እግር ባላቸውም በሚንቀሳቀሱትም መልክ መስለው ለወጡ።”