ጊዜያዊ ዘላለማዊነት

የእውነት እውቀት

ባለን ልዩ ልዩ አስተሳሰብ ምክኒያት ሰዎች ጊዜያዊውን ምድራዊ ኑሮ ዘላለም እንደሆነ በመቁጠር እንኖረዋለን። እንዲያ በመሆኑም እቅዳችን ከልክ ያለፈና የተለጠጠ ነው።መዘናጋትም ይታይበታል፡፡ በጊዜያዊው አለም ዘላለማዊ የሚመስል እቅድ ውስጥ መዘፈቅ ትክክለኛ ምርጫን መዘንጋት ይፈጥራል፡፡ ቁዋሚና ዘላለማዊ ነገር ምድር ላይ ሳይኖር እኛ ግን በራሳችን ዙሪያ እንደዚያ የመሳሰሉ እቅዶችን ስናስቀምጥ በጊዜያዊ የምድር ኑሮ ዘላለማዊንትን ልንገነባ እየሞከርን ነው ማለት ነው፡፡
ቃሉ እንደሚስገነዝበን ”ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና። በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፥ከሰማይም የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም።”(2ቆሮ.5:1-3)
የኛ የማይሳካ ፕሮጀክት ማለት ይሄ ነው፡- ድንኩዋን ጸሃይና ብርድን ስንት ዘመን ሊቁዋቁዋም ይችላል? መኖሪያችን በድንጋይና በብረት እንደተገነባ ያለመመሰሉ ዘላቂነት እንደሌለው ለማመልከት ነው፡፡ ከልብ ካላሰብንበት ፈጥኖ ሊፈርስ ያለውን ይህን ድንኩዋን ዘላለማዊ አድርገን እንቆጥራለን፣ በሰማይ ያለና የሚጠብቀንን እውነተኛ ዘላለማዊ ሕይወትም እንዲያመልጠን እናደርጋለን፡፡ ሁላችንም ብንሆን ከአፍታ በሁዋላ ስለሚሆነው ነገር አናውቅም፣ ሆኖም ረጅም ዘመንን ሳንፈራ እናውጠነጥናለን፡፡ ይህን ማድረጋችን ፊታችን ያለውን ፈጥኖ መምጣት ያለበትን በጎ የእግዚአብሄር ስጦታ እንድንረሳ ያደርጋል፡፡ እግዚአብሄር ግን አሁን ባለንበት ቅጽበት ላይ የሚጠብቅብንን ህይወት በትክክል እንድንኖረው ይፈልጋል፡፡
ያዕ.4:13-16 ”አሁንም፡- ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህ ከተማ እንሄዳለን በዚያም ዓመት እንኖራለን እንነግድማለን እናተርፍማለን የምትሉ እናንተ፥ ተመልከቱ፥ ነገ የሚሆነውን አታውቁምና። ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና። በዚህ ፈንታ፡- ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን ማለት ይገባችኋል። አሁን ግን በትዕቢታችሁ ትመካላችሁ፤ እንደዚህ ያለ ትምክህት ሁሉ ክፉ ነው።”
በምድር መኖርስ እንፈልግ እናቅድ፣ ግን ዘመናችንን ያለ እግዚአብሄር ለመኖር ለምን እንፈቅዳለን? ብዙ ዘመን ያለ እግዚአብሄር ምሪት መኖር እግዚአብሄርን እንድንረሳ ያደርጋል፡፡ ማሳሰቢያው የሚለው፡-
”በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ ታደርግ ዘንድ ባትጠብቅ፥ ይህንንም አምላክህ እግዚአብሄር የተባለውን የተመሰገነውንና የተፈራውን ስም ባትፈራ፥ እግዚአብሔር መቅሠፍትህን፥ የዘርህንም መቅሠፍት፥ ብዙ ዘመንም የሚኖረውን ታላቅ መቅሠፍት፥ ብዙ ዘመን የሚኖረውንም ክፉ ደዌ ያደርግብሃል። የፈራኸውንም የግብፅ ደዌ ሁሉ እንደ ገና ያመጣብሃል፥ ይጣበቅብህማል። ደግሞም ይህ ሕግ ባለበት መጽሐፍ ውስጥ ያልተጻፈውን ደዌ ሁሉ መቅሠፍትም ሁሉ እስክትጠፋ ድረስ እግዚአብሔር ያመጣብሃል።” (ዘዳ.28:58-61)
አሁን እውነተኛው ፍላጎት ብዙ ዘመን መኖር ከሆነ ፡- ከእግዚአብሄርና በረከቱ ጋር ወይስ ከራስ ፈቃድና ብዙ መቅሰፍት ጋር መኖር? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ይገባል፡፡
2ዜና.15:3-6 ”እስራኤልም ብዙ ዘመን ያለ እውነተኛ አምላክ፥ ያለ አስተማሪም ካህን፥ ያለ ሕግም ይኖሩ ነበር። በመከራቸውም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው በፈለጉት ጊዜ አገኙት። በዚያም ዘመን ለሚወጣውና ለሚገባው ሰላም አልነበረም፥ በምድርም በሚኖሩት ሁሉ ላይ ታላቅ ድንጋጤ ነበረ። እግዚአብሔር በመከራው ሁሉ ያስጨንቃቸው ነበርና ወገን ከወገን ጋር፥ ከተማም ከከተማ ጋር ይዋጋ ነበር።”
በትክክለኛ መስመር ላይ ለቆመ ህይወት ግን እግዚአብሄር ህይወትን አብዝቶ ይጨምርለታል፡፡ ”ብኖር እግዚአብሄርም ቢፈቅድ” ለሚለው ሰው እግዚአብሄር እቅዱን ያሰምርለታል፡፡እንደ ፈቃዱ ማቀዱ መልካም ውጤት ያመጣለታልና፡-
ዘዳ.30:20 ”እግዚአብሔርም ለአባቶችህ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እንዲሰጣቸው በማለላቸው በምድሪቱ ትቀመጥ ዘንድ፥ እርሱ ሕይወትህ የዘመንህም ርዝመት ነውና አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድደው ትጠባበቀውም ቃሉንም ትሰማ ዘንድ ምረጥ።”
በምድር ላይ ለሚኖረን ረጅም እድሜ ሌላ ስሌት ማፈላለግ አይጠበቅብንም፡፡ እግዚአብሄር ለእስራኤላውያን የሚጠበቅባቸውን ተግባር እንደዚህ አመልክቶአቸው ነበር፡-ይወዱትና ያመልኩት ዘንድ፣ እርሱን በተስፋ ይጠባበቁና ቃሉን ሰምተው ይፈጽሙ ዘንድ፡፡
አምላካቸው እግዚአብሄር ታማኝ በመሆኑ ቃል ኪዳን ሲገባላቸው አይተናል፡፡ እንዲሁም እነርሱ ቃልኪዳኑን ያገኙ ዘንድ ከርሱ ጋር ሊጣበቁ እንዲገባ አዝዞአል፡፡እግዚአብሄር በርሱ ለተደገፉ እውነተኛ መተማመኛ ነው፡፡ሰዎች በርሱ እስከታመኑ ድረስ እርሱ የህይወታቸው ርዝማኔ ነው፡፡ረጅም እድሜ የአመታት ቁጥር ብቻን አያመለክትም፡፡ሰላም ያለበት፣የእግዚአብሄር ጉብኝት ያለበትና ሰላሙ የሞላበት ዘመንንም የሚያመለክት ነው፡፡እቅዳችን የእግዚአብሄር ፈቃድ የሚገለጥባቸው ከሆኑ ትክክለኛ እቅዶች ይሆናሉ፡፡መዘናጋት የሌለባቸው፣ ፈቃዱ ያለባቸው ከርሱ ጋር ስምምነት ያለባቸው ናቸውና ያስደስታሉ፡፡
የባርያው ጸሎት
”ለአባቶቻችን በሰጠኸው ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ይፈሩህ ዘንድ በመንገዶችህም ይሄዱ ዘንድ፥ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፥ ይቅርም በል፤ አንተ ብቻ የሰውን ልጆች ልብ ታውቃለህና ልቡን ለምታውቀው ሰው ሁሉ እንደ መንገዱ ሁሉ መጠን ክፈለው።”(2ዜና.6:30፤31)
እስራኤል ብዙ ዘመን መንገዳቸውን ስተው እውነተኛውን አምላክ ትተዋል፡፡በዚህ ምክኒያት በምድር ላይ እድሜያቸው አጭርና መከራ ያልተለየው ሆኖ ነበር፡፡ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው በፈለጉት ጊዜ ሊያገኙትና ይቅር ብሎ ሊቀበላቸው ግን ቃል ገብቶአል፡፡
ዕብ.7:22-25 ”እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።”
በጣም አጭር እድሜ ያለው የሰው ልጅ ዘላለማዊነትን የሚያገኘው ከጌታ ኢየሱስ በሚያገኘው ህይወት ምክኒያት እንጂ ምድር ላይ ለመሰንበት በሚያወጣው እቅድ ወይም ባለው ምኞት አይደለም፡፡ስለዚህ ትኩረቱ ቃልኪዳኑ ላይ ቢሆን እንዲሁም የእድሜው ርዝመት እርሱ መሆኑን ቢያምን የአመታት ስሌት ላይ አይደክምም፣ ፍሬያማና ደስተኛ የሚሆንበትን መንገድም ያስተውላልና አይስትም፡፡