አንድ ትሁት ንጉስ በግዛቱ ያለውን ህዝብ በማክበር የእራት ግብዣ ጠራ።የተጠራው ህዝብ የንጉሱን ክብር ባይመጠንም ንጉሱ ያንን ሳይቆጥር ወደ እርሱ የክብር ስፍራ ሁሉን ጋበዘ።ንጉስ ፈራጅ ነው፣ነገር ግን ያን ስልጣኑንና ፍርድን አስቀምጦ በርሱ ግዛት በየትኛውም የህይወት ይዘት ያሉትን በርህራሄ ተመልክቶ ጋብዞአቸዋል።ንጉሱ ባለ ሞገስና የተፈራ ነው።ነገር ግን የጠራቸውን ምስኪኖች ውርደታቸውን ገለል አድርጎና በክብር አይቶ በዙርያው ካሉ ባለማእረጎች ጋር አስተካከለና ቆጠራቸው።በመሃከላቸውም ሊቀመጥና ከነርሱ ጋር ሊጋበዝ ወሰነ።ንጉስ ባዘጋጀው ታላቅ ዝግጅት አማካኝነትም እንዲያ ታላቅ ትህትናውን ገለጠ።በገለጠው ቸርነት ንጉሱ ለተዋረደው (ተገዢ ለሆነው) ህዝቡ ክብሩን ከማሳየቱም ሌላ በተለያየ የውድቀት ህይወት የሚኖረውን አንስቶ በማእረግ ሊያስቀምጥ ያሰበው እቅዱ ለህዝቡ ትልቅ እድል ፈንታ እንዲሆን አደረገ።ይህ በብዙዎች ትውልድ የማይገኝ መልካም አጋጣሚ ነው።
ቃሉ በኢሳ.25:6-9 ላይ ስለንጉሱ እግዚአብሄር ግብዣ ይናገራል፦
“የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ ታላቅ የሰባ ግብዣ፥ ያረጀ የወይን ጠጅ፥ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፥ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል።በዚህም ተራራ ላይ በወገኖች ሁሉ ላይ የተጣለውን መጋረጃ፥ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋውን መሸፈኛ ያጠፋል።ሞትን ለዘላለም ይውጣል፥ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፥ የሕዝቡን ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።“
በቃሉ ውስጥ ጎልተው የምናያቸው እግዚአብሄር፣ህዝቡ ታላቅ የሰባ ግብዣ የተባሉትን ልብ እንበል፦እግዚአብሄር በታላቅ ፍቅር ወደ ህዝቡ አልመጣም ወይ?ሃዘናቸውን የሚሽር ደስታንም የሚሰጥ ግብዣ አላደረገም ወይ? ዘላለማዊ ጠላትንስ አልዋጠውም ወይ?….
ሆኖም እግዚአብሄር ወገኖች ያላቸውን አይሁድ ወደ ዘላለማዊ የልጅነት ክብር ሊጠራቸው ሲመጣ አልተቀበሉትም ነበር።የቃልኪዳን አምላክ ቃሉን አክብሮ በአይሁድ መሃከል ቢገኝም አቀባበላቸው ያሳያቸውን ፍቅር የሚመጥን አልነበረም።
ዮሐ.1:10-12 “በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም።የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም
አልተቀበሉትም።ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን
ሰጣቸው“ ይላል።
ወገኔ ህዝቤ ያላቸው አይሁድ ስለምን አምላካቸውን ሊቀበሉ አልቻሉም?አጠባበቃቸውንና አቀባበላቸውን በማየት ማስተዋልና የልብ ዝግጅት ያለመኖር በብዙ እንደጎዳቸው እናስተውላለን፦
ያለመጠባበቅ
ማቴ.2:1-2 “ኢየሱስም በይሁዳ ቤተልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል፡- የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፥ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር…“
ካህናት፣ጻፍትና ፈሪሳውያን በምኩራብ ዘወትር ቢመላለሱም ዘመናትን ማስተዋልና የእግዚአብሄርን ተስፋ ቃል መጠባበቅ አልቻሉም ነበር።ስለዚህ የጌታ መወለድ ብስራት ሳይሆን ፍርሃት ሆነባቸው።
እግዚአብሄር ሲመጣ ባዝጋጀው ግብዣ ውስጥ ብዙ ነገር ለእስራኤላውያን አቅዶ ነበር።ወገኖች የተባሉት ሁሉ ላይ የተጣለውን ያለማወቅ መጋረጃ ሊገፍፍ፣ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋ ጽድቅ የሚሰውር መሸፈኛን ሊያጠፋ፣በአጠቃላይ በሰው ልጅ ላይ የተጣለውን የሞት ፍርድ ለዘላለም ሊውጥና የዘላለምን ሃሳር ከሰው ልጅ ላይ በማስወገድ ከፊት ሁሉ እንባን ሊያብስ፣ የሕዝቡንም ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ሊያስወግድ አቅዶ መጣ።እስራኤላውያን ግን ይህን ያህል አልተጠባበቁም።አባት ወደ ቤቱ እንደሆነው ሁሉ ቤተኛውም በናፍቆት ወደ አባቱ መሆን ሲገባው ተቀባይ የተባለው የቤተሰብ አባል ሁሉ በባይተዋርነት የአባት አመጣጥ ድንጋጤ ሲሆንበት ማየት እንዴት ያሳዝናል?
ያለማወቅ
እመጣለሁ ያለውና የመጣው ሁለት ሳይሆንባቸው አልቀረም፤በሲና ተራራ ላይ በእሳት ወርዶ ያዩት አምላክ በሰውነት መምጣቱ ብዙዎችን አሰናክሎአልና።ቃሉ ግን የተረጋገጠ ነው፦
ማቴ.1:21 “ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። በነቢይ ከጌታ ዘንድ፡- እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም፡- እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።“
“የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም።“ የሚለው ቃል ለእስራኤል ትላንት የተናገረው ዛሬ እንደተናገረው ያደረገው እርሱ መሆኑ ያለመታወቁ ውድቀት እንዳመጣባቸው ያሳያል።
ያለማክበር
የእግዚአብሄርን ጥሪ ያለመጠበቅና ያለማክበራቸው የዘላለም ደስታን አሳጥቶአቸዋል።እግዚአብሄር የትህትና አምላክ ነው፤ለትሁታን ጸጋን ይሰጣል።አይሁድ ግን ያ ስላልነበራቸው የጸጋ አምላክ እንዲተዋቸው አደረጉ።ስራቸውም ያን ያሳያል፦
ሉቃ14:15-19 “ከተቀመጡትም አንዱ ይህን ሰምቶ፦ በእግዚአብሔር መንግሥት እንጀራ የሚበላ ብፁዕ ነው አለው።እርሱ ግን እንዲህ አለው፦ አንድ ሰው ታላቅ እራት አድርጎ ብዙዎችን ጠራ፤በእራትም ሰዓት የታደሙትን፦ አሁን ተዘጋጅቶአልና ኑ እንዲላቸው ባሪያውን ላከ።ሁላቸውም በአንድነት ያመካኙ ጀመር። የፊተኛው፟፦ መሬት ገዝቼአለሁ ወጥቼም ላየው በግድ ያስፈልገኛል፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው።ሌላውም፦ አምስት ጥምድ በሬዎች ገዝቼአለሁ ልፈትናቸውም እሄዳለሁ፤ ይቅር እንድትለኝ እለምንሃለሁ አለው።“
ክብር መስጠት የሚከበረውን ከልብ መቀበል የሚንጸባረቅበት አካሄድ ነው።መከበር የሚገባው ቃሉ ተሰምቶ ሊያይ ይፈልጋል።እንዲያ ከሆነ አክባሪ ብዙ የቃል ብዛቶችን ሊደረድርለት ሳይሆን አሜንንና መታዘዝን ሊያሳይ ተገቢ ነው። በተመሳሳይ በእግዚአብሔር መንግሥት እንጀራ የሚበላ ብፁዕ ነው ብሎ የቃላት ሞቅታ መፍጠርና በተግባር የእራት ሰዓትህን ልታደም አልችልም ብሎ ማመካኘት ለየቅል ነው።
ያለመቀበል
እግዚአብሄር ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑት ሰዎች ሁሉ ያለ ልዩነት ልጆቹ ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጥቶአቸዋል።ወገኖች የተባሉት ግን ስላልተጠባበቁት/ስላልናፈቁት መቀበል ተስኖአቸው እናያለን።ተስፋ የተነገረው ከአባቶቻቸው ጀምሮ ለነርሱ ነበር፤ያን ግን አላስተዋሉም።
“በዚያም ቀን፦ እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፤ ተስፋ አድርገነዋል፥ ያድነንማል፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ ጠብቀነዋል፤ በማዳኑ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን ይባላል።“ የሚለው የተስፋ ቃል ግን ማዳኑን በደስታ የተቀበሉ እንደሚኖሩ አመልካች ነው።
በማጠቃለያው ያከበረን ጠሪያችን ክቡር ጥሪው አሁንም እንዳላቆመ ማሰብ አለብን።ጥሪው እንደትላንቱ ዛሬም ያው ነው።እንዲሁ ለወገኖቹ ያዘጋጀው ግብዣ ያለ ልዩነትና መድሎ ለአህዛብም ያው ነው።ዋናው ነገር ግብዣውን አክብሮ በርን ለጠሪው መክፈት ነው።ይህን ዛሬም ስለሚያሳስብ መርሳት አያስፈልግም፦
“እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።“(ራእ.3:20)
የሰባ ግብዣ ተካፋይ ለሚያደርግ ክብር እንድንበቃ መሃሪ አምላክ ይርዳን።