ባላንጣዎች ሁሌም በቅራኔ ውስጥ ያሉ ወገኖች ናቸው፡፡በውጊያ ሜዳ ይገናኙ እንጂ ከመፋለም ወደሁዋላ አይሉም፡፡አሸናፊ ለይቶ አንዱ ለሌላው እጅ ሳይሰጥም ፍልሚያው አያቁዋርጥም፡፡ በሁለቱም ተዋጊዎች በኩል በየጊዜው ለውጊያ ዝግጅት አለ፤ ላለመሸነፍ እጅ ላለመስጠትና ላለመገዛት ትግል አለ፡፡የተያዘም እንዲሁ ያመልጥ ዘንድ እስከሞት በሚደርስ ትግል ሳያቁዋርጥ ለነጻነት ይታገላል፤ ይህ የውጊያ ተፈጥሮ ነው፡፡
ውጊያ መንፈሳዊም ስጋዊም ነው፡፡ ስጋዊ ውጊያ በማይግባቡ፣ በተጣሉና ጦርነትን በመረጡ አካላት ወይም ቡድኖች መሃል ይከናወናል፣ ለእርቅም ግን በር አለው፡፡መንፈሳዊ ውጊያ ግን መንፈሳዊውን አለም ያማከለ ጦርነት ሆኖ እርቅ የሌለውና በመንፈስ የታገዘ ነው፡፡ በመንፈሱ አለም የሚከናወኑ የውጊያ አሰላለፎችና አይነቶች በመጽሀፍ ቅዱስ አንጻር እንደሚከተለው ይከፈላሉ፡-
የብሉይ ኪዳን ዘመን ውጊያ፡- የእግዚአብሄር ህዝብ ውጊያ ጣኦት ከሚያመልኩ አህዛብ ጋር ነበር፡፡ በዚህ ምክኒያት የእግዚአብሄር ልጆች በእግዚአብሄር ምሪት ሲወጡ ጣኦት በሚያመልኩ አህዛብ ላይ ድል ያገኙ ነበር፡፡
ዘጸ.23:20-25 ”በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ። በፊቱ ተጠንቀቁ፥ ቃሉንም አድምጡ፤ ስሜም በእርሱ ስለ ሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት።አንተ ግን ቃሉን ብትሰማ፥ ያልሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ጠላቶችህን እጣላቸዋለሁ፥ የሚያስጨንቁህንም አስጨንቃቸዋለሁ። መልአኬ በፊትህ ይሄዳልና፥ ወደ አሞራውያንም ወደ ኬጢያውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ከነዓናውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ያገባሃል፤ እኔም አጠፋቸዋለሁ። ለአማልክቶቻቸው አትስገድ፥ አታምልካቸውም፤ እንደ ሥራቸውም አትሥራ፤ ነገር ግን ፈጽመህ አፍርሳቸው፥ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብራቸው። አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ታመልኩታላችሁ፥ እርሱም እህልህንና ውኃህን ይባርካል፤ በሽታንም ከመካከልህ አርቃለሁ።” ይላል፡፡
የአዲስ ኪዳን ዘመን ውጊያ፡- የእግዚአብሄር ልጆች ሰልፍ የሚወጡት ፊትለፊት ከአጋንንት ጋር ውጊያ ለመግጠም ነው (ውጊያው ከስጋና ከደም /ከሰው ዘር ጋር መሆኑ ቀርቶአል)፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊ ሰው ከሌላ ሰው ጋር ሰይፍ መዝዞ የሚፋለምበት የውጊያ መንገድ በእግዚአብሄር ፊት ተዘግቶአል፡፡
ኤፌ6:12-13 ”መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ።”
ያልተሰናዳ ተዋጊ?
”በኮሬብ ተራራ ቁም” በሚለው ጽሁፍ ውስጥ ሳኦል የሚረዳው አምላክ አብሮት ስላልወጣ በሄደበት እንደቀረ ስናይ ነበር፤ ንጉሱ መያዝ የነበረበትን ዘንግቶአልና በጊልቦአ ተራራ ላይ በጠላት እጅ ወደቀ፡፡ለውጊያ በተገኘበት ተራራ ላይ ከአምላኩ ሀይል አልተቀበለም ወይም አልተቀባም፡፡ በዚህ ምክኒያት እግዚአብሄር ባልተገለጠበት ጠላት ግን ባደባበት ስፍራ ብቻውን ስለወጣ የጦርነቱ ሰለባ ሊሆን በቃ፡፡ እግዚአብሄር በሚገኝበት ስፍራ እንጂ በፈቀድነው አካባቢ የርሱን መገኘት ማሰብ እንደማንችል የሳኦል ህይወት ያስተምራል፡፡
1ሳሙ.31:1-3 ”ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ተዋጉ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፥ ተወግተውም በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወደቁ። ፍልስጥኤማውያንም ሳኦልንና ልጆቹን በእግር በእግራቸው ተከትለው አባረሩአቸው፤ ፍልስጥኤማውያንም የሳኦልን ልጆች ዮናታንንና አሚናዳብን ሜልኪሳንም ገደሉ። ሰልፍም በሳኦል ላይ ጠነከረ፥ ቀስተኞችም አገኙት፤ እርሱም ከቀስተኞቹ የተነሣ እጅግ ተጨነቀ።”
የሳኦል ዝግጅት ስጋዊ ብቻ ነበር፡፡ስለዚህ ከአጋንንት ጋር የወጣው የፍልስጥኤማውያን ሰራዊት ያልተዘጋጀውን የእግዚአብሄር ህዝብ ወግቶ አሸነፈ፤ የእስራኤል ሰዎች በተሸነፈ ስሜት ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ብዙዎችም ተወግተው በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወደቁ። ፍልስጥኤማውያንም የእግዚአብሄርን ህዝብ ይመሩ የነበሩትን ሳኦልንና ልጆቹን በእግር በእግራቸው ተከትለው አባረሩአቸው፤ ከእግዚአብሄር እጅ ወጥተው የወደቁት ንጉሱ፣ ልጆቹና ተከታዩ ህዝብ በፍልስጥኤማውያን እጅ ውስጥ ገብተው የውርደት ሞት ሞቱ፡፡ ጠላቶች ህዝቡን አዋርደው እስኪጥሉአቸው ማሳደድን አልተዉም ነበር፡፡… ሰልፍም እግዚአብሄር በተወው በሳኦል ላይ ጠነከረ፥ የሚረዳው አጥቶ ብቻውን ሳለ ቀስተኞች አገኙት፤ እርሱም ከቀስተኞቹ የተነሣ የሞት ጭንቅ ተጨነቀ። በጌታ መንፈስ ዝግጅት ያልተሰናዳ ተዋጊ ድንገት በጠላቶቹ እጅ ወድቆ እንደሚጠፋም ጠፋ፡፡
”ጽኑአን ሰዎች ሁሉ ተነሥተው የሳኦልን ሬሳ የልጆቹንም ሬሳ ወሰዱ፥ ወደ ኢያቢስም አመጡአቸው፤ በኢያቢስም ካለው ከትልቁ ዛፍ በታች አጥንቶቻቸውን ቀበሩ፥ ሰባት ቀንም ጾሙ።እንዲሁ ሳኦል በእግዚአብሔር ላይ ስላደረገው ኃጢአት፥ የእግዚአብሔርንም ቃል ስላልጠበቀ ሞተ። ደግሞም መናፍስት ጠሪ ስለ ጠየቀ እግዚአብሔርንም ስላልጠየቀ፥ ስለዚህ ገደለው፥ መንግሥቱንም ወደ እሴይ ልጅ ወደ ዳዊት አሳለፈው።”(1ዜና.10:12-14)
ይህ ንጉስ እግዚአብሄርን አላስቀደመም፤ በምትኩ መናፍስትን አማካሪ አደረገ፡፡ ስለዚህ መናፍስት ጠሪ ስለጠየቀ እግዚአብሔርንም ስላልጠየቀ እግዚአብሄር ራሱ ቀጣው፡፡
ከአምላኩ ጋር የተስማማ ሰው ግን በመንፈሳዊውም ሆነ በአለም ያለውን ትግል ታግሎ ማሸነፍ ይችላል፡፡ እንዲያውም ውጊያው የሰው መሆኑ ቀርቶ የራሱ የእግዚአብሄር ይሆንና ጠላቶቹን ጸጥ ያደርግለታል፡-
2ዜና.17:1-12 ”… ኢዮሳፍጥ ነገሠ፥ በእስራኤልም ላይ ጠነከረ።… እግዚአብሔርም ከኢዮሳፍጥ ጋር ነበረ፥ በፊተኛይቱ በአባቱ በዳዊት መንገድ ሄዶአልና፥ በኣሊምንም አልፈለገምና፤ነገር ግን የአባቱን አምላክ ፈለገ፥ በትእዛዙም ሄደ፥ የእስራኤልንም ሥራ አልሠራም።እግዚአብሔርም መንግሥቱን በእጁ አጸና፤… ልቡም በእግዚአብሔር መንገድ ከፍ ከፍ አለ፤ የኮረብታውን መስገጃዎችና የማምለኪያ ዐፀዱንም ከይሁዳ አስወገደ። በነገሠም በሦስተኛው ዓመት በይሁዳ ከተሞች ያስተምሩ ዘንድ መሳፍንቱን፥ ቤንኃይልን፥ አብድያስን፥ ዘካርያስን፥ ናትናኤልን፥ ሚክያስን፥ ሰደደ።… እነርሱም የእግዚአብሔርን የሕጉን መጽሐፍ ይዘው በይሁዳ ያስተምሩ ነበር፤ ወደ ይሁዳም ከተሞች ሁሉ ሄደው ሕዝቡን ያስተምሩ ነበር።በይሁዳም ዙሪያ በነበሩ መንግሥታት ሁሉ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ድንጋጤ ሆነ፥ ከኢዮሳፍጥም ጋር አልተዋጉም።… ኢዮሳፍጥም እየበረታና እጅግም እየከበረ ሄደ፤ በይሁዳም ግንቦችንና የጎተራ ከተሞችን ሠራ።”
ከላይ ባለው የንጉስ ኢዮሳፍጥ ታሪክ ውስጥ ለንጉሱ ብርታትና መክበር የርሱ ብልሀትና የጦር ስልት እንደጠቀመው አንመለከትም፡፡ ይህ ንጉስ ወይ የራሱን ያልያም በዙርያው ያከማቸውን ሰራዊት ገድል አያወራም፣ ወይም በራሱ ነገር አልተመካም፡፡ ነገር ግን ንጉሱ ከአምላኩ ጋር መስማማቱን፣ የአምላኩ ስርአት በህዝቡና በምድሩ ላይ ይሰፍን ዘንድ የእግዚአብሄር መልእክተኞችን ማሰማራቱን እንመለከታለን፡፡
በተመሳሳይ በአምላኩ ነገር በተዘጋጀ ህዝብ ፊት የጠላት አካሄድ እንዴት በመንፈስ በተገለጠ እውቀት ቀድሞ እንደሚታወቅ ቀጥሎ ያለው ቃል ያሳያል፡-
2ነገ.6:8-12 ”የሶርያም ንጉሥ ከእስራኤል ጋር ይዋጋ ነበር፤ ከባሪያዎቹም ጋር ተማክሮ፡- በዚህ ተደብቀን እንሰፍራለን አለ። የእግዚአብሔርም ሰው፡- ሶርያውያን በዚያ ተደብቀዋልና በዚያ ስፍራ እንዳታልፍ ተጠንቀቅ ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ላከ። የእስራኤልም ንጉሥ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ነገረው ስፍራ ሰደደ፤ አንድ ጊዜም ሳይሆን፥ ሁለት ጊዜም ሳይሆን በዚያ ራሱን አዳነ። የሶርያም ንጉሥ ልብ ስለዚህ እጅግ ታወከ፤ ባሪያዎቹንም ጠርቶ፡- ከእኛ ዘንድ ከእስራኤል ንጉሥ ጋር የተወዳጀ እንዳለ አትነግሩኝምን? አላቸው። ከባሪያዎቹም አንዱ፡- ጌታዬ ሆይ፥ እንዲህ እኮ አይደለም፤ ነገር ግን በእልፍኝህ ውስጥ ሆነህ የምትናገረውን በእስራኤል ዘንድ ያለ ነቢይ ኤልሳዕ ለእስራኤል ንጉሥ ይነግረዋል አለ።”
በመንፈሳዊ ህይወት (በቅድስና፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በንሰሃና በአምልኮ) ዝግጁ የሆነና አምላኩን ሊሰማ የተሰናዳ ሰው የጠላት አሰራር ገና በመንፈሳዊ አለም በመቀነባበር ላይ ሳለ እንደዚህ ባለ ሁኔታ ይታየዋል፣ ይሰማዋል ወይም ከአምላኩ ዘንድ የጥንቃቄ ደውል እንዲያገኝ ይሆናል፡፡
ንጉስ ዳዊት የጠላትን መንገድ የሚያስተውልበትንና ድል የሚያደርግበትን ቅባት ገና ብላቴና ሳለ ተቀባ፡፡ ስለዚህ ይህ ብላቴና ወደ ጦርነት ገና ሳይገባ የሀይል መንፈስ አገኘ፤ ከቅባትም በሁዋላ የእግዚአብሄርን ጦርነት ተዋጊ ሆነ (የእግዚአብሄር ፈቃድ ያለበትን ውጊያ በእግዚአብሄር ምሪት ይዋጋ ነበር)፡፡
1ሳሙ.16:13 ”ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ በኃይል መጣ። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ አርማቴም ሄደ።”
የስጋ ጦርነት ስጋዊ መሰናዶ አለበት፤ የእግዚአብሄር ጦርነት ግን መንፈሳዊ የጦር እቃና መንፈሳዊ የህይወት ዝግጅት አለበት፡፡ ከስጋ ነገር ተለይተው የተቀደሱ እግዚአብሄር የቅባቱን ሀይል ይሞላቸዋል፡፡ የድላቸውም ሚስጥር ፍቺ ያለው በዚያ ላይ ነው፡-
መዝ.20:6-8 ”እግዚአብሔር የቀባውን እንዳዳነው ዛሬ አወቅሁ፤ ከሰማይ መቅደሱ ይመልስለታል፤ በቀኙ ብርታት ማዳን። እነዚያ በሰረገላ እነዚያም በፈረስ ይታመናሉ፤ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ከፍ ከፍ እንላለን። እነርሱ ተሰነካክለው ወደቁ፤ እኛ ግን ተነሣን፥ ጸንተንም ቆምን።” አለ ዳዊት፡፡
ዳዊት በብዙ ጦርነት መሀል ቢገባም ሁሉንም በድል አልፎአል፡፡ ንጉሱ ጦርነቶቹን በሙሉ ያሸነፈው በነበረው የጦር እውቀትና ብርታት ሳይሆን በተቀባው ቅባት ምክኒያት እንደሆነ እጅግ አስተውሎ ነበር፡፡ ስለዚህ በሰረገላና በፈረስ ብዛት (በስጋ ሀይል) አላሸንፍም፣ ማዳኔ ግን በቀባኝና ስሙን በሰጠኝ አምላክ ነው የሚል ሙሉ እምነት ነበረው፡፡ ገና በጠላት ፊት ሳይቀርብ ይህን አዋጅ ለህዝቡ ያወጀ የእግዚአብሄር ጀግና ብላቴናው ዳዊት ነበር፡፡ ይህም በስጋ ለሚታመነው ንጉስ ሳኦል እፍረት ነበር፡-
1ሳሙ.17:30-38፤ ”ዳዊትም ከእርሱ ወደ ሌላ ሰው ዘወር አለ፥ እንደዚህም ያለ ነገር ተናገረ፤ ሕዝቡም እንደ ቀድሞው ያለ ነገር መለሱለት።ዳዊትም የተናገረው ቃል ተሰማ፥ ለሳኦልም ነገሩት፤ ወደ እርሱም አስጠራው። ዳዊትም ሳኦልን፡- ስለ እርሱ የማንም ልብ አይውደቅ፤ እኔ ባሪያህ ሄጄ ያንን ፍልስጥኤማዊ እወጋዋለሁ አለው። ሳኦልም ዳዊትን፡- አንተ ገና ብላቴና ነህና፥ እርሱም ከብላቴንነቱ ጀምሮ ጦረኛ ነውና ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም ለው። ዳዊትም ሳኦልን አለው፡- እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳና ድብ ይመጣ ነበር፥ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር። በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፥ ከአፉም አስጥለው ነበር፤ በተነሣብኝም ጊዜ ጕሮሮውን ይዤ እመታውና እገድለው ነበር። እኔ ባሪያህ አንበሳና ድብ መታሁ፤ ይህም ያልተገረዘው ፍልስጥኤማዊ የሕያውን አምላክ ጭፍሮች ተገዳድሮአልና ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። ዳዊትም፡- ከአንበሳና ከድብ እጅ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል አለ። ሳኦልም ዳዊትን፡- ሂድ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል አለው።”
ዳዊት ስለራሱ ዝግጅት ሲናገር እውቀቱን ወይም የጦር ስልቱን አልዘረዘረም፤ ከአንበሳና ከድብ እጅ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል ብቻ አለ።
ከእግዚአብሄር ጋር በመስማማት የተሰናዳ የእግዚአብሄር ተዋጊ አንድ ታናሽ ብላቴና ታላላቆቹን ያሳፈረበት መንገድ ያስደንቃል፡፡ የዳዊት ወንድሞች የዳዊት እምነት አልተዋጠላቸውም፣ በስጋ ነበር የተዘጋጁትና ወንድማቸውን አልተረዱትም፡፡ እርሱ ግን በእግዚአብሄር ላይ የነበረው እምነት ከፍ ያለ ስለነበረ በጦር አውድማ (መንፈሱ በተሸነፈ ህዝብ ፊት ቆሞ) የድልና የእምነት አዋጅ ሲናገር ለሰሚዎቹ ግራ ያጋባ ነበረ፡፡
የእግዚአብሄር ህዝብ እርዳታ ከማን ይቀበል?
ኢሳ.31:1-3 ”ስለ እርዳታ ወደ ግብጽ ለሚወርዱ በፈረሶችም ለሚደገፉ፥ ስለ ብዛታቸውም በሰረገሎች፥ እጅግ ብርቱዎችም ስለ ሆኑ በፈረሰኞች ለሚታመኑ፥ ወደ እስራኤልም ቅዱስ ለማይመለከቱ እግዚአብሔርንም ለማይፈልጉ ወዮላቸው! እርሱ ግን ደግሞ ጠቢብ ነው፥ ክፉንም ነገር ያመጣል፥ ቃሉንም አይመልስም፥ በክፉም አድራጊዎች ቤት ላይ በደልንም በሚሠሩ ረዳት ላይ ይነሣል። ግብጻውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፥ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤ እግዚአብሔርም እጁን በዘረጋ ጊዜ፥ ረጂው ይሰናከላል ተረጂውም ይወድቃል፥ ሁሉም በአንድ ላይ ይጠፋሉ።”
ነቢዩ ኢሳያስ እስራኤልን በሁለት ሀጢያት ይከሳቸዋል፣ በግብጽ ሰረገሎች በመታመናቸውና እግዚአብሄርን ባለመፈለጋቸው፡፡ መንፈሳዊያን ተዋጊዎች ግን የድል ዝግጅታቸው መንፈስ በሆነው አምላካቸው ላይ ያላቸው ትምክህት እንጂ ሀጢያተኛዋ አለም የምትሰጣቸው ብርታት አይደለም፡፡ የይሁዳ ሰዎች በግብጽ ሰረገሎች ብዛት ታምነዋል፣ በፈረሶቻቸውም ብርታት ተደግፈዋል፡፡ ይህ መታመናቸው በፊታቸው የእግዚአብሄርን ሀያልነት አሳንሶአል፡፡ሀጢያትም ሆኖባቸዋል፡፡ እግዚአብሄር ግን ከግብጻውያን ፈረስ ይልቅ ብርቱ ነው፡፡ ስለዚህ ግብጻውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፥ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም ሲል ያስጠነቅቃቸዋል፡፡
እግዚአብሄር ለሚታመኑት ተዋጊያቸው ነው፡፡ እርሱ ለእስራኤላውያን እንደ አንድ ሰው ሆኖ ተዋጋላቸው፤ የተዋጋላቸውም ከአጋንንቶችና ከአጋንንት መጠቀሚያ ግብጻውያን ጋር ነበር፡፡ ከባርነት ምድር ከግብጽ በሚወጡበት ወቅት ያቃቱዋቸውን የግብጽ ፈረሶችና ሰረገሎች በባህር ጥሎላቸዋል፡፡ ስለዚህ የጠላቶቻቸውን ሬሳ በአይናቸው ሲያዩ የደስታ ዝማሬ ዘመሩ፡-
”ጕልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፥… ” ሲሉ ከፍ አደረጉት፡፡
”… መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነውማለሁ፥ የአባቴ አምላክ ነው ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ፡፡እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው፥የፈርዖንን ሰረገሎች ሠራዊቱንም በባሕር ጣላቸው፤ የተመረጡት ሦስተኞች በኤርትራ ባሕር ሰጠሙ። ቀላያትም ከደኑአቸው፤ ወደ ባሕር ጥልቀት እንደ ድንጋይ ሰጠሙ። አቤቱ፥ ቀኝህ በኃይል ከበረ፤ አቤቱ፥ ቀኝህ ጠላቱን አደቀቀ። በክብርህም ብዛት የተነሡብህን አጠፋህ፤ ቍጣህን ሰድደህ፥ እንደ ገለባም በላቸው። በአፍንጫህ እስትንፋስ ውኆች ተከመሩ፥ ፈሳሾቹም እንደ ክምር ቆሙ፤ ሞገዱም በባሕር ውስጥ ረጋ። ጠላትም፡- አሳድጄ እይዛቸዋለሁ፥ ምርኮም እካፈላለሁ፥ ነፍሴም ትጠግባቸዋለች፤ ሰይፌንም እመዝዛለሁ፥ እጄም ታጠፋቸዋለች አለ። ነፋስህን አነፈስህ፥ ባሕርም ከደናቸው፤ በኃይለኞች ውኆችም እንደ አረር ሰጠሙ። አቤቱ፥ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፥ ድንቅንም የምታደርግ፥ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?” እያሉ ከፍ አደረጉት (ዘጸ.15:2-6)፡፡
ለእግዚአብሄር የዘመሩት አባቶቻቸው ካለፉ በሁዋላ ከሩቅ ትውልዶች መሃል የበቀሉት ልጆቻቸው ግን የሚያሳፍር ህይወት ውስጥ ተገኝተዋል፡፡ በዝማሬ ፋንታ የስንፍና ንግግር በእግዚአብሄር ላይ ተናገሩ፤ የእግዚአብሄር ችሎታ ደበዘዘባቸው፣ ስለዚህ አባቶቻቸውን ወደ ገዙ ጠላቶች ልባቸውን አዘነበሉ፤ ይህም ታላቅ ሀጢያት ሆነባቸው (ኢሳ.31:1-3 )፡፡
እግዚአብሄር ስለኛ ስንቴ ተዋግቶ አሸነፈልን? ስንቴ ከሞት አስመለጠን? ስንቴስ የጠላትን መውጊያ ሰበረልን? እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ባይሆን በከንቱ በጠፋን ነበር እንደተባለ፡፡
መንፈሳዊ አይኖቻችን ቢከፈቱልን በመንፈሳዊው አለም ያሉትን የጠላት ሰራዊትና እቅድ ልናስተውል እንችላለን፣ ከዚያ በላይ ደግሞ የሁሉን ቻይ ጌታ ማዳን በርቶ እናገኛለን፡፡ ክፉ መናፍስት እኛን ለመጣልና ከመንገድ ለማስቀረት የሚያቅዱት የተለያየ የክፋት አሰራር ብዙ ነው፡፡በጊዜና በስፍራ ሲገለጡ የሚያሳዩት ባህሪ የሚከተለውን ይመስላል፡-
- በሌሊት ግርማ ያስፈራራሉ (ስለዚህ እምነታችን ከውስጣችን ጠፍቶ በፍርሀት መንፈስ እንድንያዝና የእግዚአብሄርን ማዳን እንድንጥል፣ በነርሱም እጅ ወድቀን የአላማቸው ማስፈጸሚያ እንድንሆን ያደርጋሉ)
- እንደ አዳኝ አውሬ ሊያጠምዱን ያደባሉ (ይዘው ሊሰባብሩንና ከእግዚአብሄር ነገር ውጪ ሊያደርጉን እንዲያ ያደርጋሉ)
- በቀን በሚበርር ፍላጻ ሊወጉን ይወረውራሉ (በመቅሰፍት ወግተው ሊያጠፉን የተለያየ መዋጊያ ያዘጋጃሉ)
- በጨለማ በሚሄድ ክፉ ነገር ሊይዙን ይንቀሳቀሳሉ (በተለያየ የአመጽ ማጥቂያ መንገድ ሊይዙን ይሞክራሉ)
- አደጋና የቀትር ጋኔን መንገዳችን ላይ ይጠብቁናል፡፡
ነገር ግን እርሱ አምላክ ነውና ከነርሱ ሁሉ ይጋርደናል፤ ጋሻ ጦረኛን ከጠላት ፍላጻ እንደሚያስጥል ይከብብና ከነርሱ ወጥመድ ያሳልፈናል፡፡ይህን ሁሉ የጠላት አሰራር አስተውለን ስለጥበቃው አምላካችንን በማመስገን የምንንቀሳቀስ ስንት ነን? አላስተዋልን እንደሆነ ነው እንጂ እርሱ እለት በእለት በአጠገባችን ሺህዎችን በቀኛችንም አሥር ሺህዎችን እየጣለ እዚህ አድርሶናል፣ቃልኪዳኑን የሚጠብቅ አምላክ ታማኝ ስለሆነ ለተደገፉት ይህን ያደርጋል፡፡
የዳዊት የምስጋና መዝሙር
”በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል።እግዚአብሔርን፡- አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ፤ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ።እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና።በላባዎቹ ይጋርድሃል፥ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፤ እውነት እንደ ጋሻ ይከብብሃል።ከሌሊት ግርማ፥ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፥በጨለማ ከሚሄድ ክፉ ነገር፥ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም።በአጠገብህ ሺህ በቀኝህም አሥር ሺህ ይወድቃሉ፤ ወደ አንተ ግን አይቀርብም።”(መዝ.91:1-7)
እንደ ዳዊት የእግዚአብሄርን ስራ በምስጋና የሚያሞግስ ሰው በአምላኩ የታመነ፣ በእርሱ ውስጥ የተሸሸገና በሁሉን ቻይነቱ የተማመነ ነው፡፡እንዲህ አይነት ሰው ንቁ መንፈስ ያለውና ከአምላኩ ጋር በመንፈስ የሚገናኝ በመሆኑ ከእግዚአብሄር ዘንድ የሚያስፈልገውን የሚቀበል ብርቱ ተዋጊ ነው፡፡የተዘናጋው/ያልተሰናዳው ተዋጊ ግን በቀላሉ እጅ የሚሰጥ ነው፡፡