ያለ እውነተኛ አምላክ ኑሮ

የመጨረሻ ዘመን

እውነተኛ አምላክ ባልተገለጠበት ስፍራና ዘመን የሃሰት አማልክት ተገልጠው ይሰራሉ (2ዜና.15:3)።በዚያን ጊዜ አጋንንት በድፍረትና በግልጽ ስለሚንቀሳቀሱ ተጽኖአቸው ከፍተኛ ነው።የጣኦታት ወረራም ነፃነት አሳጥቶ ማስተዋል እስኪሳን ድረስ ክፋት ይነግሳል፡፡የፍጥረታት ሁሉ ጌታ ግን ፍጥረቶቹ በርሱ ጥላ ስር ተማምነው እንዲኖሩ እንጂ ባለቤት ወዳልሆኑ አማልክት ፊታቸውን እንዲመልሱ አይሻም። እውነተኛ አምላክ የሌለው ትውልድ በክፉ መናፍስት የተጠቃ እንደሆነ የንጉስ አሞጽ ታሪክ ያሳየናል፦
2ነገ.21:19-22 “አሞጽም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ሁለት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሁለት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዮጥባ ሰው የሐሩስ ልጅ ሜሶላም ነበረች።አባቱም ምናሴ እንዳደረገ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሠራ።አባቱም በሄደበት መንገድ ሁሉ ሄደ፥ አባቱም ያመለካቸውን ጣዖታት አመለከ ሰገደላቸውም።የአባቶቹንም አምላክ እግዚአብሔርን ተወ፥ በእግዚአብሔርም መንገድ አልሄደም።“
ንጉስ አሞጽ በህሊናው ሳይመራና እግዚአብሄርን ሳይፈራ በክፋት መንፈስ ተነድቶ ነበር።የተቆጣጠረው ይህ መንፈስ በጎውን እንዳያስብም ስለያዘው በአመጸኛነቱ እስከመጨረሻው ገፋበት።የበረከት አምላክ እግዚአብሄር በመረጠው ስፍራ ውስጥ ተክዶ ነጣቂ ሃይላት ቦታና አእምሮን ተቆጣጠሩ። ፈቃዳቸውንም በንጉሱ ላይ ገልጠው አጋጣሚውን ሁሉ ለእስራኤል ጥፋት የሚሆን ስራን ሰሩበት።ከዚህ በተጨማሪ የአመጽ ምንጭ የሆኑት መናፍስቶቹ ምድሪቱን ሳይቀር በሰው ደም አረከሱዋት።
2ነገ.21:16 “… ደግሞም ምናሴ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ይሠራ ዘንድ ይሁዳን ካሳተበት ኃጢአት ሌላ ከዳር እስከ ዳር
ኢየሩሳሌምን እስኪሞላት ድረስ እጅግ ብዙ ንጹሕ ደም አፈሰሰ።“
በየትኛውም ዘመን ቢሆን በአለም ላይ ስርአት የጎደለው አካሄድ የሚበረታው ሰው እንደዚህ ባለ ክፉ ህይወት ውስጥ ሲዘፈቅ ነው።በግልጽ እንደሚታየው አምላክ የሌለው ትውልድ እውነትን ባለማወቁ በሃሰት መንገድ ላይ ተንከራታችና ጨቃኝ ነው።
የስጋ ፈቃድ ለአለም ተጽእኖና ለአጋንንት ስቃይ ያጋልጣል። እውነተኛው አምላክ ተገልጦ በሚሰራበት ትውልድ ውስጥ ሊገለጥ ያለው ምህረት፣ ጸጋና በረከትም መንገድ ለጠፋው ትውልድ እንግዳ ነገር ይሆናል።ብዙዎች በዚህ ሰበብ በአጋንንት ወጥመድ ላይ ወድቀው ይሰቃያሉ። ፍትህም ከምድር ላይ ይጠፋል።ሰላም በሁከት ተውጦ እረፍት ከሰው ልጆች ይርቃል።በመቀጠል የተጠቀሱት ቃላት የሚያሳዩን ይሄንን ነው፦
“እስራኤልም ብዙ ዘመን ያለ እውነተኛ አምላክ፥ ያለ አስተማሪም ካህን፥ ያለ ሕግም ይኖሩ ነበር።“ እስራኤል በእግዚአብሄር የተወደደና የተመረጠ ትውልድ ነበር።ነገር ግን ብዙ ዘመን ከግዚአብሄር ራቀ፣ከዘመኑ እርዝማኔም ጋር መዘንጋት ተከትሎ አምላኩን ረሳ።በራቀበት በዚያ ዘመን ግን ተራቆተ።አስተምሮ የሚመልሰው አስተማሪ ካህን አልነበረውምና እውነተኛውን መንገድ ሳያይ ኖረ።የእግዚአብሄርን ህግ ረስቶአልና የቀና መንፈስ ራቀው።እጅግም ተጎሳቆለ፣ብዙ ዘመን እስራኤል ተሰቃየ፣ተጎሳቆለ።
በምድሩ የሚኖሩ ህዝቦች ሲወጡ በስጋት ሲገቡም በፍርሃት ሆነ።በውስጣቸው ሰላም ጠፋ።በዙሪያቸው እንዲሁ ጠላት በዛ።ይህ ሁሉ የሆነባቸው ጠባቂያቸው እግዚያብሄር በዙሪያቸው ስላልነበረ ነው።በአጠቃላይ የእስራኤል ምድር በእግዚአብሄር መንፈስ አማካይነት የእረፍት ምድር መሆኑ ቀረና በሃጢያት ሳቢያ ድንጋጤ የሞላበት ሆነ።ነገር ግን ህዝቡ በእግዚአብሄር ክልል ውስጥ በሆነና እግዚአብሄርን በፈራ ኖሮ ከነዚህ ሁሉ መከራ በተጋረደ ንጹህ ደምም እንደ ውሃ ባልፈሰሰ ነበረ፦
“እግዚአብሔር በመከራው ሁሉ ያስጨንቃቸው ነበርና ወገን ከወገን ጋር፥ ከተማም ከከተማ ጋር ይዋጋ ነበር።“ (2ዜና.15:6)
ቃሉ ስለመመለስና ስለ እግዚአብሄር ፈጣን የበጎነት ምላሽ ሲገልጽ ደግሞ እንዲህ አለ፦
2ዜና.15:4 “በመከራቸውም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው በፈለጉት ጊዜ አገኙት።“
እስራኤላውያን ወደ መረጣቸው አምላክ ከመመለስና ከመጎብኘት ውጪ ተስፋ አልነበራቸውም። ሰላም በክህደት ከገቡበት አለም አልተገኘም።
እንዲሁ ምድር ጸጥ ብላ ለሰው ልጆች የምትመቸውም አጋንንት በእግዚአብሄር ሲገሰጹ ብቻ ነው።የእግዚአብሄር ቀና መንገድ ተገልጦ በምድር ላይ ሲሰራ ብቻ ሰዎች በእግዚአብሄር መንፈስ ተጠብቀው ይኖራሉ።ዛሬ ከተማ ከከተማ ጋር ለምን ይዋጋል?ህዝብስ ከህዝብ ጋር ለምን ይጋጫል? ሰው የፈጠረውን አምላክ ስለረሳ አይደለም? እንዲሁም አጋንንትን ከእግሩ በታች የቀጠቀጠው ጌታ በተዘጋ ልብ ላይ ሊሰራ ስላልቻለስ አይደል?
2ዜና.15:7 “እናንተ ግን ለሥራችሁ ብድራት ይሆንላችኋልና በርቱ፥ እጃችሁም አይላላ።“ የሚል ቃል ደግሞ ለተከፈተ ልብ ሲነገር ይታያል።
በትውልዱ ላይ የተነሳ አሳ የሚባል የእስራኤል ንጉስ መንገዱን እጅግ ስላስተዋለ ወደ እግዚአብሄር መጠጋት ቻለ።እንደተጠጋውም መጠን ከእግዚአብሄር የሆነውን መልካም ነገር ሁሉ በዘመኑ አገኘ።ለንጉስ የተሳካ አስተዳደር ለህዝቡ ቅን ፍርድ የሚገኝበት ብቸኛው መንገድ የአሳ መንገድ ነው።
2ዜና.15:8-14 “አሳም ይህን ቃልና የነቢዩን የዖዴድን ትንቢት በሰማ ጊዜ ልቡ ጸና፥ ከይሁዳና ከቢንያምም አገር ሁሉ በተራራማውም በኤፍሬም አገር ከያዛቸው ከተሞች ጸያፉን ነገር አስወገደ፤ በእግዚአብሔርም ቤት ፊት የነበረውን የእግዚአብሔርን መሠዊያ አደሰ።አምላኩም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደ ሆነ ባዩ ጊዜ ከእስራኤል ዘንድ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተጠግተው ነበርና እርሱ ይሁዳንና ብንያምን ሁሉ፥ ከኤፍሬምና ከምናሴም ከስምዖንም መጥተው ከእነርሱ ጋር የተቀመጡትን ሰበሰበ።አሳም በነገሠ በአሥራ አምስተኛው ዓመት በሦስተኛው ወር በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ።በዚያም ቀን ካመጡት ምርኮ ሰባት መቶ በሬዎችና ሰባት ሺህ በጎች ለእግዚአብሔር ሠዉ።በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ይሹ ዘንድ ቃል ኪዳን አደረጉ፤የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን የማይፈልግ፥ ታናሽ ወይም ታላቅ፥ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን፥ ይገደል ዘንድ ማሉ።ለእግዚአብሔርም በታላቅ ድምፅና በእልልታ፥ በእምቢልታና በቀንደ መለከት ማሉ።“
አሳ ያለአንዳች ሌላ ምክኒያት ልቡንና ፍቃዱን ለአምላኩ በመስጠቱ ከርሱ ተርፎ ለህዝቡ የበረከት ምንጭ ሊሆን ችሎአል።የተጨነቀችው ምድር ሳትቀር በእግዚአብሄር በረከት ልትሞላ፣ህዝቡም በእግዚአብሄር ደስታ ደስ ተሰኝቶ አምላኩን በፍጹም ልብ ሊያመልክ ያ የንጉስ የእውነት መንገድ እንዴት ወሳኝ እንደነበር ማየት ይቻላል።ዛሬ የሰላምና የበረከትን ምስጢር አለም እንድትደርስበት ከመቼውም ይልቅ የጌታ ብርህን ሊያበራ ያስፈልጋል።ብርሃኑም በወንጌል አማካይነት ወደ ሰው ልብ ይደርሳል።እንዲህ ስላለ፦
ኢሳ.40:9-11 “የምስራች የምትነግሪ ጽዮን ሆይ፥ ከፍ ወዳለው ተራራ ውጪ የምስራች የምትነግሪ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ድምፅሽን በኃይል አንሺ፤ አንሺ፥ አትፍሪ፤ ለይሁዳም ከተሞች፦ እነሆ፥ አምላካችሁ! ብለሽ ንገሪ።እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይመጣል ክንዱም ስለ እርሱ ይገዛል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ደመወዙም በፊቱ ነው።መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።“
አንድ የምስራች ሊባልለት የተገባ እውነተኛ አምላክ ተነገረለት፦
• ቀድሞ አልታየም ነበር።ግን የቀጠረው ቀን ሲመጣ እንደሚገለጥ ያም የምስራች ተብሎ እንዲታወጅ ከዘመናት በፊት አስነግሮ ነበርና።
ኢሳ.41:26-27 “እናውቅ ዘንድ ከጥንት የተናገረው፣ እውነት ነው እንልም ዘንድ ቀድሞ የተናገረው ማን ነው? የሚናገር የለም፥ የሚገልጥም የለም፥ ቃላችሁንም የሚሰማ የለም።በመጀመሪያ ለጽዮን፦ እነኋቸው እላለሁ፤ ለኢየሩሳሌምም የምስራች ነጋሪን እሰጣለሁ።“
• ለይሁዳም ከተሞች መነገር የነበረበት በጎ ዜና ምስራቹ ነበር። እነሆ፥ አምላካችሁ! ብሎ መልካም ዜና አብሳሪው ሲያውጅ አንድ አስደናቂ ትእይንት በመካከላቸው ተገለጠ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኃያል ሰው መጣ፣ ክንዱም በመካከላቸው እየተመላለሰ አጋንንትንና ስልጣናትን ከእግሩ በታች አድርጎ ገዛ፣ በመግዛትም ላይ ነው።
ያለ እውነተኛ አምላክ ኑሮን የመሰለ ጎዶሎ ኑሮ የለምና ለአለም ሁሉ ሙሉ የሆነ የበረከት አምላክ በዘመናችን ይገለጥ፣ወንጌሉ ከዳር እስከ ዳር ያብራ፣ማን መሆኑ ይታወቅ፣ የዳኑትን መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራ፣ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከም፣ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይምራ፦ጽዮንም ድምጹዋን ከፍ አድርጋ ትሰማ።