ያለጊዜው አትፍረዱ(2… )

ቤተክርስቲያን

ያለጊዜው ፍርድ ለምን?
​​​​​​​​‘’በጨለማ የተሰወረውን ደግሞ ወደ ብርሃን የሚያወጣ የልብንም ምክር የሚገልጥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ፤ በዚያን ጊዜም ለእያንዳንዱ ምስጋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሆናል።’’ (1ቆሮ.4:5)
ያለጊዜው ፍርድ አንድም ፈራጅ ሳይሆኑ በፍርድ ወንበር መሰየም ነው፣ ደግሞም የፍርድ ሰአት ሳይሆን ፈጥኖ ፍርድ ማኖር ነው። እውነታ ደግሞ ከእግዚአብሄር ዘንድ ፍርድ የሚወጣበት ትክክለኛው ጊዜ ሳይደርስ በፊት ድምዳሜ ላይ ደርሶ የፍርድ ቃል ማውጣት ነፍሳትን ከህይወት መንገድ ማናጋት መፍጠር፣ ብሎም ላይመለሱ ወደ ሞት መንገድ መምራት ነው። ነገር ግን ፍርድ የእግዚአብሄር ነው፤ ስለዚህ በርሱ ቦታ ሆነን አንዳችን በሌላችን ላይ ያን ማውጣት አንችልም፤ እንዲያ ከሆነ ራሳችንን ከፍርድ በታች አስቀምጠናል ማለት ነው፤ የፍርድ ጊዜ ከዛሬ አልፎ ነገ እንዲሆን እግዚአብሄር ቢወስን በዛሬና በነገ መሃል ያለውን የምህረት ወቅት ጣልቃ በመግባት በአንድ ነፍስ ላይ እንኳን እንቅፋት መሆን በእግዚአብሄር ዘንድ ያስጠይቃል።
​​​​​​​​ሉቃ6:36-37 ‘’አባታችሁ ርኅሩኅ እንደ ሆነ ርኅሩኆች ሁኑ። አትፍረዱ አይፈረድባችሁምም፤ አትኰንኑ አትኰነኑምም። ይቅር በሉ ይቅርም ትባላላችሁ።’’
እግዚአብሄር ይቅር ባይ ነውና ለሰው የመመለሻ ጊዜ ይሰጣል፣ እኛ ራሳችን የምህረት ጊዜ ፍሬዎች ነንና። ስለዚህ ያን የጠፋውን ሰው እግዚአብሄር በወንጌል ሊጠራው የንሰሃ ጊዜም ሊሰጠው ይችላል። በሰጠን በዚያ ጊዜ ውስጥ ሰዎች ከክፉ ስራችን እንመለስ ዘንድ እርሱ ይታገሳል፤ በቤቱ አለን በምንልበት ወቅት እንኳን ደግመን ደጋግመን እንድንጠራ በቃሉ ያሳስባል፣ ራሳችንን እንፈትሽ ዘንድ ይመክረናል። ሰዎች ይድኑ ዘንድ ከሃጢያታቸው እንዲመለሱ እግዚአብሄር ፈቃዱ ነውና። ሰለዚህ ያን የሚሻ ታጋሽ ጌታ እያለ ሰዎች በርሱ ውሳኔ ላይ ጣልቃ በመግባት የነፍሳትን መዳን ማደናቀፍ ከፍተኛ ቁጣ ያስከትላል።
​​​​​​​​ማቴ.7:1-5 ‘’እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል። በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፥ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም?ወይም ወንድምህን፡- ከዓይንህ ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ እንዴትስ ትለዋለህ? እነሆም፥ በዓይንህ ምሰሶ አለ። ​አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፥ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ።’’
እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ ስለሚል የሰውን ሁኔታ አይተን፣ ዝንባሌውን ተመልክተን አባባሉንም ገምተን ከመፍረድ መታቀብ አለብን። ነገር ግን በቤተክርስቲያን የሚተላለፍ ውሳኔ አለ፣ እግዚአብሄር የሾማቸው በዚህ ጉዳይ ላይ ይህን ያደርጉ ዘንድ ፈቃድ ብቻ ሳይሆን ሃላፊነት አለባቸው፤ እግዚአብሄር የምድር መንግስትንና አስተዳደርን ሰጥቶአልና ፍርድ ቤቶች በአመጸኞች ላይ ውሳኔ ያስተላልፋሉ፣ ሰዎች በሰላም እንዲኖሩ በእግዚአብሄር ቦታ ሆነው ቅን ፍርድ ለተበደሉት ይፈርዳሉ። መንግስት ለበጎ ነገር የእግዚአብሄር አገልጋይ በመሆኑ ቅን ፍርድን በህዝቡ መሃል በማስፈን እንዲገዛ ፍርዱን ይጠብቃል። እያንዳንድችንም በግል ከስሜታችን በመነሳት ውሳኔ ላይ ከመድረስ መታቀብ፣ በግምት ከመፍረድ መታቀብ፣ ከዚያ ይልቅ በወገኔ የሚሆን በእኔም የሚደርስ ነው በማለት ነገሮችን አስፍቶ መመልከት ከማይገባ ፍርድ ያድናል።
አባታችን እግዚአብሄር ሩህሩና መሃሪ እንደመሆኑ ልጆቹም እንደዚያው እንድንሆንና እርስ በርስ በሆደ-ሰፊነት እንድንቀባበል ይፈልጋል፤ የሰዎችን የውስጥ ነገር ለማወቅ በሚሻ አተያይ እያዩ ግምትንም እየሰጡ አእምሮአችን የተለየ ውሳኔ ድምዳሜ ውስጥ እንዳይገባ መጠንቀቅ አለብን፤ ይህም ልባችን ፍርድ እንዳይሰጥ ያደርገዋል።
በጻድቅ ህይወት ላይ ፍርድ አይጸናም
ዘፍ.49:22-26 ሲናገር፦ ‘’ዮሴፍ ትንሹ የፍሬ ዛፍ ነው፥ በምንጭ አጠገብ የሚያፈራ የፍሬ ዛፍ፤ አረጎቹ በቅጥር ላይ ያድጋሉ። ቀስተኞች አስቸገሩት፥ ነደፉትም፥ ተቃወሙትም፤ ነገር ግን ቀስቱ እንደ ጸና ቀረ፤ የእጆቹም ክንድ በያዕቆብ አምላክ እጅ በረታ፥ በዚያው በጠባቂው በእስራኤል ዓምድ፥ በአባትህ አምላክ እርሱም የሚረዳህ፥ ሁሉንም በሚችል አምላክ እርሱም የሚባርክህ፥ በሰማይ በረከት ከላይ በሚገኝ፥ በጥልቅም በረከት ከታች በሚሠራጭ፥ በጡትና በማኅፀን በረከት። የአባትህ በረከቶች ጽኑዓን ከሆኑ ከተራሮች በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፤ ዘላለማውያን ከሆኑ ከኮረፍቶችም በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፤ እነርሱም በዮሴፍ ራስ ላይ ይሆናሉ፥ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነው ራስ አናት ላይ።’’
የዮሴፍ ህይወት ፍሬ በአካሉ ሙሉ እንደተሸከመ ቅርንጫፍ የተመሰለ በያእቆብ ልጆች መሃል ግን ታናሽ የሆነ ነበረ፤ ፍሬይማነቱ እስኪመጣ ብርቱ ትግል ነበረበት፣ የወንድሞቹ ፍላጻ ይወጋው ዘንድ በጭክኔ ተወርውሮበታል፣ ለጠላት እጅ ተላልፎ ሁሉ ተሰጥቶአል። የህይወቱ በረከት ሲገለጥ ግን የወለዳቸው ሁለቱ ልጆቹ አፍርተውና በዝተው ሁለት የእስራኤል ነገድ እስከመሆን ደርሰዋል። ከዚያ በፊት ዮሴፍ በግፍ በወንድሞቹ ተሸጦ በነበረ ሰአት ወደ ግብጽ ተነድቶአል፤ በታናሽነቱ መከራን ተቀበለ፣ የተስፋ ዘር የግብጽ ባሪያ ሆነ፤ በእግዚአብሄር የተባረከ ቢሆንም ወንድሞቹ ግን ረገሙት፤ አውጥተው ጣሉት፣ አንስተውም ለምናምንቴዎች አሳልፈው ሰጡት። ቃል የገባለት አምላክ ግን ከርሱ ጋር ወደ ግብጽ በመውረድ በዚያ በሄደበት ምድር ጠበቀው፤ ብላቴናው ፍሬያማ ሆኖ ለጠሉት ወንድሞቹ ሳይቀር መጠለያ፣ መትረፊያና የበረከት ምንጭ እንዲሆንም አደረገው።
ፍሬያማነት በሚገኝበት በእግዚአብሄር ቤት ውስጥ ሰዎች ከአምላካቸው ጋር ተጣብቀው ቢኖሩ በለመለመ መስክ እንዳለ አበባ ይዋባሉ፤ በወንዝ ዳር እንደተተከለ ዛፍ፣ ዘወትር እንደለመለመና ፍሬያማ እንደሆነ ተክል ይበዛሉ፤ ይህን ያላስተዋሉ፣ የሚቸኩሉና ያለጊዜው የሚፈርዱ ግን ያን ፍሬያማነት ለማጨንገፍ ይሮጣሉ።
ልምላሜ ያለጊዜው እንዳይቀጭጭ እንጠንቀቅ፣ በእግዚአብሄር መንፈስ የለመለሙ፣ ቅርንጫፋቸው የሰፋና ለብዙዎች ጥላ ሊሆኑ የተዘጋጁ ነፍሳትን በፍርድ ቃል ቆርጦ ከማጥፋት መጠንቀቅ ተገቢ ነው። የዮሴፍ ተገዳዳሪ ሰዎች ቀስተኞች ነበሩ፣ በቀስትና በደጋናቸው በውስጣቸው በታመቀ ጉልበትም ሊያጠቁት የተሰለፉበት በውስጡ የተቀመጠው መለኮታዊ ስጦታ ስላልታያቸውና የጥፋት አሳብ ስለገዛቸው ነበር። በርሱ ህይወት ውስጥ ይገለጥ ዘንድ የነበረ በጎነት፣ ምህረት፣ ጥበብ፣ ማዳንና የእግዚአብሄር ስራ በሙሉ ያለጊዜው እንዲጨነግፍና ጠላት የሞት እቅዱን በህዝቡ ላይ እንዲያሳካ መንገድ በመሆን አገልግለዋል። ያም ያለጊዜው በተፈጠረ የፍርድ ልብ የሆነ ነበር።
የአባቱ ባርኮት ‘’በአባትህ አምላክ እርሱም የሚረዳህ ’’ እንዳለ የዮሴፍ እጆች የበረቱት በእርሱ ነበር፣ ከጠላቶቹ ተግዳሮት ያመልጥ ዘንድ ጋሻ ሆኖታል፤ የባርነት ቀንበር የገባበት ትከሻው ሳይጎብጥ እንዲበረታ በርሱ በአምላኩ ተደርጎአል፤ ዮሴፍ በጥቃት ጨርሶ ከመውደቁ በፊት በነርሱ ላይ ቀስቱን ደግኖ ያስፈነጥር ዘንድ ጅማትና አጥንቶቹን የሚያፈረጥም ጉልበት ተሰጥቶታል፤ የርሱ ታሪክ የሚተርክልንና የሚያሳየን ቅዱሳን በጠላታቸው ላይ በርትተው የተላከባቸውን ቀስት እንዲመክቱ የጌታ ሃይል የሚጋርዳቸው መሆኑን ነው።
‘’አቤቱ፥ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ተአምራትህንም ሁሉ እነግራለሁ።በአንተ ደስ ይለኛል፥ ሐሤትንም አደርጋለሁ፤ ልዑል ሆይ፥ ለስምህ እዘምራለሁ።ጠላቶቼ ወደ ኋላ በተመለሱ ጊዜ፥ ይሰናከላሉ ከፊትህም ይጠፋሉ።ፍርዴንና በቀሌን አድርገህልኛልና፤ ጽድቅን እየፈረድህ በዙፋንህ ላይ ተቀመጥህ።’’ (​​​​​​​መዝ.9:1-3)

በጊዜው ፍርድ የሚያስፈልገውን እንወቅ
​​​​​​​​እግዚአብሄር በእስራኤል ላይ የፍርድ በትር ከማውጣቱ በፊት ነብዩ አሞጽ ወጥቶ ለህዝቡ ከፍርድ ያመልጡ ዘንድ አሳሰባቸው፤
እግዚአብሄር ከፍርድ አስቀድሞ ንሰሃን ልኮላችኋልና እድሉን ተጠቀሙበት አላቸው፦
‘’የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በእናንተ ላይ ለሙሾ የማነሣውን ይህን ቃል ስሙ። የእስራኤል ድንግል ወደቀች፥ ከእንግዲህም ወዲህ አትነሣም፤ በምድርዋ ላይ ተጣለች፥ የሚያስነሣትም የለም። ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላልና። ሺህ ከሚወጣባት ከተማ መቶ ይቀርላታል፥ መቶም ከሚወጣባት ከተማ ለእስራኤል ቤት አሥር ይቀርላታል። እግዚአብሔርም ለእስራኤል ቤት እንዲህ ይላልና። እኔን ፈልጉ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ ነገር ግን ጌልገላ ፈጽሞ ትማረካለችና፥ ቤቴልም ከንቱ ትሆናለችና ቤቴልን አትፈልጉ፥ ወደ ጌልገላም አትግቡ፥ ወደ ቤርሳቤህም አትለፉ። በዮሴፍ ቤት እሳት እንዳትቃጠል፥ በቤቴል የሚያጠፋትም ሳይኖር እንዳትበላ፥ እግዚአብሔርን ፈልጉ፥ በሕይወትም ትኖራላችሁ።’’ ​​​​​​​​(አሞ.5:1-6)
ያዕ.4:5-8 ሲናገር እንዲህ ይላል፦ ‘’ወይስ መጽሐፍ፦ በእኛ ዘንድ ያሳደረው መንፈስ በቅንዓት ይመኛል ያለው በከንቱ እንደ ተናገረ ይመስላችኋልን? ነገር ግን ጸጋን አብልጦ ይሰጣል፤ ስለዚህ፦ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል። እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል፤ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ።’’
ሰይጣንና ጭፍሮቹ የማይታረቁ፣ ንሰሃ ያልተገባቸውና የማይጸጸቱ የእግዚአብሄር ጠላቶች ናቸው፣ ስለዚህ ተፈርዶባቸዋል፣ ከእግዚአብሄር ፊት ተጥለዋልም። እነርሱ የሰው ልጆች ጠላቶችም ስለሆኑ ያለርህርሄ እኛ በነርሱ ላይ የፍርድ ቃል እንድናወጣ ስልጣን ተሰጥቶናል። እውነቱ ይህ ቢሆንም በነርሱ ምክኒያትና በሰው ልብ አስቸጋሪነት አመጽ በአለም ላይ ጸንቶአል። ከኛ ድካም በላይ ግን የእግዚአብሄር ጸጋ ታላቅ ነው። ስለዚህ በነርሱ ላይ የጸናው የእግዚአብሄር ፍርድ የማይለወጥ በመሆኑ ዘወትር በነርሱ ላይ እርሱን አንስተን እንድንቀጠቅጣቸው እግዚአብሄር ስልጣን ሰጠን፤ ሰው ላይ የወጣው ፍርድ በኢየሱስ ሞት ምክኒያት ስለተሻረ ማንም ወደ እርሱ የሚመጣ የሰው ዘር ከፍርድ የማምለጥ ተስፋ ስላለው ያለጊዜው በሰው ላይ መፍረድ አይቻልም።
1.ሰይጣንና ጭፍሮቹ በሚካኤል ተሸንፈዋል፦ እኛን ለማሸንፍ ግን አይተኙልንም፣ ከቻሉ ፍርድ ያገኘን ዘንድና ይፈረድብን ዘንድ በሃጢያት እንድንሸነፍ ይሰራሉ
2.ሰይጣንና ጭፍሮቹ ወደ ምድር ተጥለዋል፦ ዳግመኛ ወደ እግዚአብሄር መገኛ አካባቢ ላይጠጉ ተረግመዋል፣ ፍርድም ተዘጋጅቶላቸዋል
3.እነርሱ ከእኛ ጋር እየተናነቁና እየታገሉ ነው፦ ክፉ መናፍስት ተዋርደውና ተጥለው ባሉበት ስፍራ የሰውን ልጅ በተለያየ እስራት ያጎሰቁሉታል፤ ከፈጣሪው ይለዩት ዘንድ ይሰራሉ፤ እግዚአብሄር በሚሰጠን የጸጋ ሃይል ግን ከነርሱ እንበልጣለን፤ በተሰጠን ሃያል ስም እንቀጠቅጣቸውማለን።
​​​​​​​​ኤፌ6:10-12 ‘’በቀረውስ በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ። የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።’’
ስለዚህ በጌታ በኢየሱስ ስም ልንታገላቸው፣ ልንዋጋቸውና ልናሸንፋቸው የስሙ ስልጣን ይደግፈናል። ይህን ለማድረግ የሚያበቃን ከአምላካችን ጋር የሚኖረን መጣበቅ ብቻ ነው፤ እግዚአብሄርን በቀረብነው ቁጥር ሃይሉ ይቀርባል፣ በራቅነውም መጠን ሃይሉ ሩቅ ይሆናል። አጋንንትም የዚህ እውቀት ስላላቸው ዋና ተግባራቸው እኛን ከፈጠረን አምላክ ማራቅ ነው።
በጌታ ለመበርታት ግን ሁሌም የሚሰራ ስልጣን ተሰጥቶናል፣ በሃይሉ ችሎትም ታግዘን እናሸንፍ ዘንድ ፈቃዱ ነው፤ ይህም ሃይለኛ ከሆነ ጠላት የምናመልጥበትና የምንረታበት መንገድ እንደመሆኑ መጠን በዚህ ታምነን እንድንሰማራ ያስፈልጋል። በእኛ ሰዋዊ ጉልበት ውጊያው የማይሆን መሆኑን ተረድተናልና ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ታመነን በአምላካችን ላይ መደገፍ ይፈለጋል፤ እግዚአብሄር ለደካማ ሃይልን ይሰጣል፣ ሃይል የእግዚአብሄር ነውና፤ ስለዚህ ከሃይለኛው ከእግዚአብሄር ክንድ በታች ሆኖ የጠላትን ፍላጻ ማምከንና ማምለጥ ይቻላል።
​​​​​​​​1ጴጥ.5:6-11 ‘’እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁምል ያበረታችሁማል። ለእርሱ ክብርና ኃይል እስከዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።’’