ያለጊዜው አትፍረዱ(1… )

ቤተክርስቲያን

እግዚአብሄር ሁሉን የፈጠረው ነገሩ ከሚኖርበት ጊዜና ስፍራ አንጻር ነው፣ ስለዚህ ምንም በርሱ የተፈጠረ ነገር ይኑር እንደተጀመረ ሁሉ እርሱ ባለው ጊዜና በወሰነው ስፍራ ይፈጸማል፣ እርሱ በፈቀደው ስፍራ ይኖራል ያበቃልም ፣ ይህ የማይሻር እውነት አማኞች ሊጠብቁት የተገባ ነው፦
‘’ስለዚህም በጨለማ የተሰወረውን ደግሞ ወደ ብርሃን የሚያወጣ የልብንም ምክር የሚገልጥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ፤ በዚያን ጊዜም ለእያንዳንዱ ምስጋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሆናል።’’ (1ቆሮ.4:5)
የእግዚአብሄር ልጆች ጊዜው ሳይደርስ እንዳንፈርድ እግዚአብሄር ያዛል፦ ይህ ትእዛዝ የተሰጠው ለፍርድ መጣደፍን ለመግታትና በውስጣችን እንደመጣልን የፍርድ ውሳኔን ከማሳለፍ ራሳችንን ያዝ ለማድረግ ነው፤ ለፍርድ የዘገየን፣ ለምህረት የፈጠንን እንሆን ዘንድ ስለተገባም ነው። በርጋታ ካስተዋልነው በችኮላ የመጣልንን ከባድ ቃል ከማውጣት መታቀብ ከብዙ ነገር እንደሚያተርፍ ማየት እንችላለን፣ የምናወጣው ፍርድ አስቀድሞ እኛኑ ፈትኖ ወደ ሌላው የሚያልፍ ነውና በምንፈርድበት ነገር እኛም እንዳንጎበኝ ስንል ለራስ መጠንቀቅ፣ ለሰውም መራራት የግድ ነው፤ በዚህም እግዚአብሄር ወዳሰበውና ወደ ወሰነው ሰአት ነገሮች በርሱ ፈቃድ ብቻ እንዲሄዱ የሚያደርግና በሚጎበኝ ጊዜ እኛው በተፈረደው ነገር እንዳንፈተን ለመጠንቀቅ የሚያግዝ ነው። የእግዚአብሄር ፍርድ የተቆረጠ ጊዜ ካለው ከዚያ ሰአት ጋር የምንጋፋው ስለምን ነው?
ጌታ ሊያደርግ፣ ሊፈርድ፣ ሊጎበኝ ይመጣል፣ እንደፈቃዱ ሊሰራ፣ የሚጸናውን ለማጽናት፣ የሚፈጠረውን ለመፍጠር፣ የሚሻረውን ለመሻር እንደፈቃዱ ይገለጣል። እርሱ ለነገሮች ጊዜ ወስኖአልና፣ በደረሰ ጊዜ ነገሩ በቅጽበትና ባሰበው ልክ ይሆናል። እግዚአብሄር የእስራኤልን ቤት ተመለከተና ስለኑሮአቸው ሁኔታና ስለሚሰሩት ሃጢያት ይገስጻቸውና ወደ ጸጸት ይመልሳቸው ዘንድ በነቢዩ አንደበት እንዲህ ተናገረ፦
‘’ለዓመፀኛውም ቤት ምሳሌን ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጣድ፥ ምንቸቲቱን ጣድ፥ ውኃም ጨምርባት።ቍራጭዋንም፥ መልካሙን ቍራጭ ሁሉ፥ ጭኑንና ወርቹን በእርስዋ ውስጥ ሰብስብ፥ የተመረጡትንም አጥንቶች ሙላባት።ከመንጋው የተመረጠውን ውሰድ፥ አጥንቶቹም እንዲበስሉ እንጨት በበታችዋ ማግድ፤ አጥንቶቹም በውስጥዋ ይቀቀሉ።ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዝገትዋ ላለባት ዝገትዋም ከእርስዋ ላልወጣ ምንቸት፥ ለደም ከተማ ወዮላት! ቍራጭ ቍራጩን አውጣ፤ ዕጣ አልወደቀባትም።ደምዋ በውስጥዋ አለ። በተራቈተ ድንጋይ ላይ አደረገችው እንጂ በአፈር ይከደን ዘንድ በመሬት ላይ አላፈሰሰችውም፤መዓቴን አወጣ ዘንድ፥ በቀሌንም እበቀል ዘንድ፥ ደምዋ እንዳይከደን በተራቈተ ድንጋይ ላይ አደረግሁ። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለደም ከተማ ወዮላት! እኔ ደግሞ ማገዶዋን ታላቅ አደርገዋለሁ።እንጨቱን አብዛ፤ እሳቱን አንድድ፤ ሥጋውን ቀቅል፤ መረቁን አጣፍጠው፤ አጥንቶቹ ይቃጠሉ።ትሞቅም ዘንድ ናስዋም ትግል ዘንድ ርኵሰትዋም በውስጥዋ ይቀልጥ ዘንድ ዝገትዋም ይጠፋ ዘንድ ባዶዋን በፍም ላይ አድርጋት። በርኵሰትሽ ሴሰኝነት አለ፤ አነጻሁሽ አልነጻሽምና መዓቴን በላይሽ እስክጨርስ ድረስ እንግዲህ ከርኵሰትሽ አትነጺም። እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ ይመጣል፥ እኔም አደርገዋለሁ፤ አልመለስም፥ አልራራም፥ አልጸጸትም፤ እንደ መንገድሽና እንደ ሥራሽ ይፈርዱብሻል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’’ ​​​​​​​​(ሕዝ.24:3-14)
መቼም እግዚአብሄር በእያንዳንዱ እስራኤላዊ ዘንድና በሚኖርበት ምድር ላይ እየሆነ የነበረውን የአመጽ ስራ አይቶአል፣ ነገር ግን የመመለሻ ጊዜ ለህዝቡ ሰጥቶ ነበር፣ የመውጫ መንገድ አሳይቶም ከቁጣው የሚያመልጡበትን መንገድ እየጠቆመ ነበር። ያ የመመለሻ ጊዜያቸው ሊያቆመው የነበረውን መቅሰፍት ብንመለከት የህዝቡ በጊዜ በንሰሃ መመለስ ከስንት ጥፋት ሊያድነው እንደሚችል እንማራለን።
​​​​​​​​ኢዩ.2:12-7 ‘’አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ፥ ቍጣው የዘገየ፥ ምሕረቱም የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ።የሚመለስና የሚጸጸት እንደ ሆነ፥ ለአምላካችሁም ለእግዚአብሔር የእህልና የመጠጥ KWrባን የሚሆነውን በረከት የሚያተርፍ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?በጽዮን መለከትን ንፉ፥ ጾምንም ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፥ሕዝቡንም አከማቹ፥ ማኅበሩንም ቀድሱ፥ ሽማግሌዎቹንም ሰብስቡ፥ ሕፃናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ፤ ሙሽራው ከእልፍኙ፥ ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ።የእግዚአብሔርም አገልጋዬች ካህናት ከወለሉና ከመሠዊያው መካከል እያለቀሱ። አቤቱ፥ ለሕዝብህ ራራ፥ አሕዛብም እንዳይነቅፉአቸው ርስትህን ለማላገጫ አሳልፈህ አትስጥ፤ ከአሕዛብ መካከል። አምላካቸው ወዴት ነው? ስለ ምን ይላሉ? ይበሉ።’’
ሁል ጊዜም ቢሆን እኛ በራሳችን የማናውቀው ግን እግዚአብሄር ሊያደርገው የወሰነው ነገር መቼ እንደሚሆን አንወቅ እንጂ የተናገረው ነገር እርሱ እንዳለው እንደሚሆን እርግጠኛ መሆን እንችላለን። እርሱ ሊፈርድ በተነሳ ወቅት እያንዳንዱ የጨለማ ስራ በብርሃኑ ምክኒያት ግልጥ ይላል፣ መሰወሪያውን ካደረገበት ስርጉጥጓጥ በጉብኝቱ ጊዜ ነገራችን ግልጥ ይሆናል፤ የሰራነውን የሰወረው፣ ነገራችንን የከደነው መሸፈኛም አንድ ቀን ይከፈታል፣ የተሰወረው በብርሃን ይገለጣል። የመሸገ ምሽጉ ይፈርስበታል፣ ያደባ ይጋለጣል፣ የተመሳሰለም በጌታ ብርሃን ተለይቶ ማንነቱ ይለያል። ይሄ ሁሉ በእርሱ ውሳኔ እለት የሚሆን ከሆነ ብዙም ማስተዋል የሌለው የሰው ዘር ስለምን ወደ ወጥመዱ ይጣደፋል?
​​​​​​​​መክ.12:13-14‘’የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፥ ትእዛዙንም ጠብቅ። እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፥ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፥ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።’’
በጨለማ ተሰውሮ በሰው ውስጥ የሚመሽግ ብዙ የልብ ፈቃድ አለ፣ ያም ጌታ እስኪገልጠው በጽልመቱ ውስጥ ይሰወራል፦ ከሰው ክፉ አሳብና ስራ መሃል ሞራል አልባነት አንዱ ነው፣ በማንነት ውስጥ ያደሩ አሳፋሪ ድርጊቶችም ይመሽጋሉ፣ የልብ አመጾችም በተግባር እስኪገለጡ ተቀብረው ነፍስን ይዘውራሉ… ቢቆጠሩ ሁሉ ብዙ ናቸው። ሃሰተኞች ልብ ውስጥም ብዙ ሰዋዊና አጋንንታዊ አሳብ ይታጨቃል፣ አመጸኞችም ዱለታቸው፣ ጻድቅ ከበባቸው፣ የክፋት ቀስታቸውና የሰወሩት እኩይ ገመናቸው ከተቀመጠበት ማንነት ወጥቶ ግልጥልጥ የሚልበት እለት አለው። ከዚያ ሁሉ በፊት ግን የንሰሃ ጊዜን ይጠቀሙበት እንደው እግዚአብሄር በትእግስት ያያቸዋል።
​​​​​​​​ኤር.31:18-20 ‘’ኤፍሬም፦ ቀጣኸኝ እኔም እንዳልተገራ ወይፈን ተቀጣሁ፤ አንተ እግዚአብሔር አምላኬ ነህና መልሰኝ እኔም እመለሳለሁ።ከተመለስሁ በኋላ ተጸጸትሁ፥ ከተገሠጽሁም በኋላ ጭኔን ጸፋሁ፤ የብላቴንነቴንም ስድብ ተሸክሜአለሁና አፈርሁ፥ ተዋረድሁም ብሎ ሲያለቅስ ሰማሁ።በእውነት ኤፍሬም ለእኔ የከበረ ልጅ ነውን? ወይስ የተወደደ ሕፃን ነውን? በእርሱ ላይ በተናገርሁ ቍጥር አስበዋለሁ፤ ስለዚህ አንጀቴ ታወከችለት ርኅራኄም እራራለታለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።’’
በምህረት እንዲህ የሚያደርግ አምላክ እኛ ሃጢያተኞች እስክንመለስ በትእግስት የሚጠብቅ ከሆነ ድንገት ጥልቅ የሚል ችኩል የሰው ድምዳሜ ስለምን የተዘረጋልንን የደህንነት ዘመን ሊቆርጥብን የጣደፋል?
ማንም ይመረምር ዘንድ ባይንቀሳቀስም፣ ነገሮች የተሰወሩ ቢመስልም የልብ ምክር እንደሁ መገለጡ አይቀርም፦ አመለካከታችንና እቅዳችን ፍላጎታችንስ ምን ነበር? ያኔ ይገለጣል በርሱ ጊዜ። የሰው አሳብ የእግዚብሄርን ክብር አይሰራምና ልብ ያን ሳያስተውል በተቃርኖ ተነስቶ እንደሆነ የሚጋለጥበት ጊዜ ሊመጣበት የግድ ነው፦ የእኔነት ባርነት፣ ለራስ ከንቱ አሳብ አገልጋይ መሆን፣ ከራስ ክልል መውጣት ያለመቻልና ለመመለስ የሚሆን አሳብ ያለመኖር፣ ፍላጎት፣ እርምጃና የጸጸት ጊዜ ያለመሻትም የጌታ ቀን ብቅ ሲልበት መከራ ይሆንበታል።
በዚያ የፍርድ ጊዜ ለርሱ ምስጋና ከአምላኩ ዘንድ የሚሆንለት ግን ማን ነው? ለወንጌሉ ጥሪ ምላሽ በመስጠት ለአዲስ ልደት በሚሆን መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ አምላኩ የተቀበለው እርሱ ነው፣ ይህ ሰው በመታደስ የዳነች ነፍስ ስላለችው የዘላለማዊ ምህረት ተስፋ ያለው ነው። ነፍሱ የዳነች ሰው ደግሞ ቅድስናውን በጌታ ጸጋ የጠበቀ ከሆነና አምላኩን ለመገናኘት የሚዘጋጅ ልብ ያለው ከሆነ በዚያን ቀን ምስጋናን ይቀበላል።
​​​​​​​​ማቴ.25:21 ‘’ጌታውም፡- መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ​ግባ አለው።’’
ሳንፈርድ የምንቀበለው የለም?
እግዚአብሄር ለደከሙ ይራራል ስለዚህ፦ ​​​​​​​​ሕዝ.34:16፤ ‘’የጠፋውንም እፈልጋለሁ የባዘነውንም እመልሳለሁ የተሰበረውንም እጠግናለሁ የደከመውንም አጸናለሁ.. ‘’ ይላል።
ሰዎች ትሁት ሆነን ከፍርድና ከማስጨነቅ የተለየ ነገር በማድረግ ላይ አዘንብለን እንደሆን እግዚአብሄርን ደስ እናሰኛለን። አእምሮአችን በእግዚአብሄር ፈቃድ እውቀት ሲጎለምስ የምንሻውም ያንን ነው፤ መልካም በማድረግ በተለይ በሰው ዘንድ በጎ የሆነ አመለካከትና አቀባበል ሲኖረን የእግዚአብሄር ፈቃድ በዚያ ውስጥ ይፈጸማል፤ ስለዚህ ቃሉ በ​​​​​​​​ሮሜ.14:1 ላይ ሲናገር፦
‘’በእምነት የደከመውንም ተቀበሉት፥ በአሳቡም ላይ አትፍረዱ።’’ ይላል። በእምነት የደከመውን ካገኘን በድካሙ ምክኒያት እየሆነ ያለውን ሁኔታ ሳይሆን ያደከመውን መሰረታዊ ችግር ተመልክተን፣ ባለመቻሉ መሸነፉንም አስተውለን በርህራሄና በማጽናናት በመቀበል፣ በጌታ ቃል ብርታት ዳግም ወደፊት መራመድ እንዲያገኝ፣ የጌታን ችሎት ተመልክቶም በእምነት ዳግም እንዲነሳ ማገዝ ይጠበቅብናል።
​​​​​​​​ቆላ.3:12-14 ‘’እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፥ ምሕረትን፥ ርኅራኄን፥ ቸርነትን፥ ትህትናን፥ የዋህነትን፥ ትዕግሥትን ልበሱ። እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፥ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፥ ይቅር ተባባሉ። ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።​​​​​​​​በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።’’
በእምነት ለደከመው ብርቱ ጥንቃቄ ያሻል፦ ከላይ ያየነው ቃል በተለይ የሚመለከተው በእምነት ለበረቱ የቃሉን ምስጢር ላስተዋሉም ነው፤ እምነት ሲደክም ብዙ መንፈሳዊ ነገር ይዳከማል፣ በእምነት በኩል እናደርግ የነበረው መንፈሳዊ ህይወታችንን የሚመለከት ነገር ሁሉ ይቀዛቀዛል። በእምነት ያልጠነከሩ ወገኖች በቃሉ እውቀት ስር ያልሰደዱ በመሆናቸው ክፍተት አግኝቶ ጠላት እንዳይነቅላቸው የሚያሳዩትን ልጅነት እየተሸከምን አድገው እስኪጠነክሩ በፍጹም ፍቅር ልንታገሳቸው ይገባል፤ ስር ላልሰደዱና በእምነታቸው ለደከሙም እንዴት ያለ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባን ቃሉ የሚናገረው አለው። በሮሜ ለሚገኙ አማኞች በጌታ ሆነው የጸጋውን አሰራር ገና ያላስተዋሉ፣ በእምነት ልጆች ለሆኑ በርህራሄ እንዲመለከቷቸው፣ እንዲጸልዩላቸውና እንዲጠነቀቁላቸው እንጂ እንዳያሸማቅቁዋቸው፣ እንዳያስጨንቁዋቸው ወይም እንዳይፈርዱባቸው ቃሉ ያመለክታቸዋል። ጌታ ያመኑትን ሁሉ ያድን ዘንድ ይችላል፣ ያም ሆኖ በእምነት ልጅ የሆነውን የእምነቱ ጥብቅና ጥልቅ ያለመሆን ውስን ክልል ውስጥ ስለሚያኖረው በውስጡ ባለ የሚዋዥቅ ተሰርቶ ያላለቀ ማንነት በመሸነፍ ጸንቶና አጥርቶ አምላኩን ማየት እንዳይችል ይሆናል፣ ያም ብቻ ሳይሆን ቃሉን ተቀብሎ የአምላኩን ሃይል እንዳይለማመድ ይጎትተዋል።
ሁላችን ብንሆን ወደ ሁዋላ የሚጎትት ስጋዊ መሻት በረታን ወቅት ሁሉ እየተሳብን ከእምነት እንደምንጎድልና ባለማመን ሳቢያም መንፈሳዊነት ዳገት እንደሚሆንብን መርሳት የለብንም፤ በራሳችን ዙርያ ስናጠነጥን የእግዚአብሄርን አሰራር ስለምንስት ከእምነት እንጎድላለን። ያንዲት የታመመ ብላቴና አባት ጌታ ጋ ቀርቦ ቢቻልህ ልጄን እርዳው አለ፦

‘’ኢየሱስም፦ ቢቻልህ ትላለህ፤ ለሚያምን ሁሉ ይቻላል አለው። ወዲያውም የብላቴናው አባት ጮኾ፦ አምናለሁ፤ አለማመኔን እርዳው አለ።’’ (ማር.​​​​9:23-24)
አንዳንዴ ነገራችን ከመረዳቱ አስቀድሞ ይልባችን እምነት አስቀድሞ ሊረዳ ግድ የሚሆንበት ጊዜ አለ፤ ያ ሳይሆን ቀረቶ ከሆነ ብዙ የልብ መሳት እምነትን ወደ ሁዋላ ያደርጋል፤ የደከመ መንፈሳዊነት ካለ፣ የአሳብ መዋዠቅ ካዘወተረ፣ በእግዚአብሄር ፈቃድ ላይ መጽናትም ከሌለና በአምላክ ቃል ላይ መደገፍ ካቃተ ብዙ ጉዳት ይሆናል፤ እንዲህ ላሉ ወገኖች ጥልቅ ርህራሄ የግድ ነው፣ የሸክም ጸሎት አስፈላጊ ነው፣ ትግስት ያለው ምሪትም እንዲሁ የሚያስፈልግ ነው። ጸጋ ለጎደላቸው የቃሉ ወተት ያስፈልጋቸዋል፣ የቃሉ ጉልበት በውስጥ ሰውነታቸው ላልሰረጸም ጸሎት ያስፈልጋቸዋል። በእምነት ያልበረቱ አማኞች ህጻናት ባህሪያቸው እንደሚቀያየር ሁሉ እምነታቸውም እንደዚያው የሚዋዥቅ ነው፤ ጌታ ኢየሱስ የሰጣቸውን አርነት አስተውለው ሳይኖሩ በትክክል መራመድ ይሳናቸዋልና። ለነዚህ ሁሉ ወገኖች ብርቱ ክትትል፣ ምሪትና ርህራሄ ይገባል። አይሁዳውያን በጌታ ኢየሱስ መንገድ መሄድ የተሳናቸው ነበሩ፤ ከርሱ ቃልና ምሪት ይልቅ ህግና ስራታቸውን ያስበልጡ ነበር፤ በተገለጠው የእግዚአብሄር ጸጋ ከመጠቀም ይልቅ በህጋቸው ሊጸድቁ ይመኙ ነበር፤ በጌታ የወንጌል ምስራች ሳይታደሉ ስላለፉ ከአርነት ፈቀቅ ብለዋል። ይህ አመለካከትና አካሄድ በዘመናቸው ለነበሩ አማኞች እንቅፋት ነበር።
​​​​​​​​ሮሜ.2:1-8 ‘’ስለዚህ፥ አንተ የምትፈርድ ሰው ሁሉ ሆይ፥ የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው በምትፈርድበት ነገር ራስህን ትኰንናለህና፤ አንተው ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና።እንደዚህም በሚያደርጉት ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እንደ ሆነ እናውቃለን።አንተም እንደዚህ በሚያደርጉ የምትፈርድ ያንም የምታደርግ ሰው ሆይ፥ አንተ ከእግዚአብሔር ፍርድ የምታመልጥ ይመስልሃልን?ወይስ የእግዚአብሔር ቸርነት ወደ ንስሐ እንዲመራህ ሳታውቅ የቸርነቱንና የመቻሉን የትዕግሥቱንም ባለጠግነት ትንቃለህን?ነገር ግን እንደ ጥንካሬህና ንስሐ እንደማይገባ ልብህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ በሚገለጥበት በቍጣ ቀን ቍጣን በራስህ ላይ ታከማቻለህ።እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል፤በበጎ ሥራ በመጽናት ምስጋናንና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል፤ለዓመፃ በሚታዘዙ እንጂ ለእውነት በማይታዘዙትና በአድመኞች ላይ ግን ቍጣና መቅሠፍት ይሆንባቸዋል።’’