ያለና የሚኖር (3…)

እግዚአብሄርን የተጠጉ ስለርሱ እንዲህ ይላሉ፡-
‘’እነሆ፥ እግዚአብሔር በኃይሉ ከፍ ያለውን ነገር ያደርጋል፤ እንደ እርሱስ ያለ አስተማሪ ማን ነው? መንገዱን ማን አዘዘለት? ወይስ፦ ኃጢአትን ሠርተሃል የሚለው ማን ነው? ሰዎች የዘመሩትን ሥራውን ታከብር ዘንድ አስብ። ሰዎች ሁሉ ተመልክተውታል፤ ሰውም ከሩቅ ያየዋል። እነሆ፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም። የዘመኑም ቍጥር አይመረመርም።’’ (ኢዮ.36:22)
እርግጥ ነው፣ ያለና የሚኖረው ህያው አምላክ በፍጥረት አተሳሰብ ውስጥ ሊቀረጽ የማይችል ትልቅነት ያለው አምላክ ነው፤ ሰው በቋንቋው እርሱ ይህ ነው ብሎ በትክክል ሊገልጸው ያዳግተዋል፦ ይህ አምላክ ከምናውቀው በላይ ነው፣ ከምናስበው በላይ ነው፣ ከንግግራችንም በላይ ነው፣ ከልባችን ይልቅ (ከአእምሮአችን የማሰብ አድማስ ይልቅ) ትልቅ ነው። ታላቅነቱን ያስተዋሉም እንዲህ ይገልጡታል፦
መዝ.139:1-6 ‘’አቤቱ፥ መረመርኸኝ፥ አወቅኸኝም። አንተ መቀመጤንና መነሣቴን አወቅህ፤ አሳቤን ሁሉ ከሩቅ አስተዋልህ። ፍለጋዬንና ዕረፍቴን አንተ መረመርህ፤ መንገዶቼን ሁሉ ቀድመህ አወቅህ፥የዓመፃ ቃል በአንደበቴ እንደሌለ።አቤቱ፥ አንተ እነሆ የቀድሞውንና የኋላውን አወቅህ፤ አንተ ፈጠርኸኝ፥ እጅህንም በላዬ አደረግህ። እውቀትህ ከእኔ ይልቅ ተደነቀች፤ በረታች፥ ወደ እርስዋም ለመድረስ አልችልም።’’
ንጉስ ዳዊት የእግዚአብሄርን ታልቅነት ሲያስብና የርሱን ታናሽነት ሲያስተውል እጅግ ተደነቀ፤ በተለየ ጥንት የነበረውን፣ የአሁኑ ትውልድ ያላየውንና ያላወቀውን፣ ዛሬም የሚገኘው ትውልድ ያለው ነገር ስፋትና ብዛት፣ ነገ ስለሚፈጠረውና የሚመጣው ትውልድ የሚያደርገውንም ጭምር ሊያስብ ሲሞክር ሁሉም በእግዚአብሄር እንጂ በሰው ሊታወቅ እንደማይችል አስተዋለ፣ የርሱም ማስተዋልና እውቀት ታላቅ እንደሆነ, መሰከረ።
መዝ.90:1-9 ‘’አቤቱ፥ አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንህልን። ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ። ሰውን ወደ ኅሳር አትመልስም፤ የሰው ልጆች ሆይ፥ ተመለሱ ትላለህ፤ ሺህ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን፥ እንደ ሌሊትም ትጋት ነውና። ዘመኖች የተናቁ ይሆናሉ፥ በማለዳም እንደ ሣር ያልፋል። ማልዶ ያብባል ያልፋልም፥ በሠርክም ጠውልጎና ደርቆ ይወድቃል። እኛ በቍጣህ አልቀናልና፥ በመዓትህም ደንግጠናልና። የተሰወረውን ኃጢአታችንን በፊትህ ብርሃን፥ በደላችንንም በፊትህ አስቀመጥህ። ዘመናችን ሁሉ አልፎአልና፥ እኛም በመዓትህ አልቀናልና፤ ዘመኖቻችንም እንደ ሸረሪት ድር ይሆናሉ።’’
-ዘመናት ቢመጡና ቢያልፉ ለፍጥረት የሆኑ ናቸው
-ትውልዶች ሲፈጠሩና በጊዜያት ኖረው ሲከስሙ የምናየውም የተፈጠሩ ስለሆኑ ነው
-ፍጥረቶች ቢለዋወጡ እንኳ ለተፈጠሩለት አላማ የሚሆኑ ናቸው
-ሁሎችም ግን ወደ ገሃዱ አለም ካመጣቸው አምላክ የተሰወሩ አይደለም፣ ከፈቃዱ አንዳቸውም አያልፉም፣ በራሳቸው አንዳችም ነገር መወሰንም፣ ማድረግም አይችሉም፤ ሁሉን የፈጠረ አምላክ ያያቸዋል፣ ይቆጣጠራቸዋልም።
መዝ.139:13-19 ‘’አቤቱ፥ አንተ ኵላሊቴን ፈጥረሃልና፥ በእናቴም ሆድ ሰውረኸኛል። ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች። እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም። ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ። አቤቱ፥ አሳቦችህ በእኔ ዘንድ እንደ ምን እጅግ የተከበሩ ናቸው! ቍጥራቸውም እንደ ምን በዛ! ብቈጥራቸው ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ፤ ተነሣሁም፥ እኔም ገና ከአንተ ጋር ነኝ። አቤቱ፥ አንተ ኃጢአተኞችን የምትገድል ከሆንህስ፥ የደም ሰዎች ሆይ፥ ከእኔ ፈቀቅ በሉ።’’
ሲገባንና ስንረዳው የምናውቀው ነገር የእግዚአብሄር አሳብና ማንነት ሊደረስበት የማይችል መሆኑን የኛ ግን በርሱ ዘንድ ቅርብ፣ የታወቀ፣ የታየና የተመረመረ መሆኑን ነው፦
-እርሱ የእኛን አሳብ ሲያውቅ እኛ የርሱን አናውቅም
-እርሱ እኛ ከመፈጠራችን ከጥንት ጀምሮ ሲያውቀን እኛ በየትኛውም ደረጃ ያለ እርሱ ፈቃድ ማን መሆኑን አናስተውልም
-እርሱ ከመፈጠራችን አስቀድሞ ሲያየን እኛ የርሱ የሆነውን ያለርሱ አናይም
1ዮሐ.3:19-20 ‘’ልባችንም በእኛ ላይ በሚፈርድበት ሁሉ፥ ከእውነት እንደ ሆንን በዚህ እናውቃለን በፊቱም ልባችንን እናሳርፋለን፥ እግዚአብሔር ከልባችን ይልቅ ታላቅ ነውና ሁሉንም ያውቃል።’’
ራሱን የሚያውቅ ሲናገር ሁሉን ስለማናውቅ አንጨነቅም ነገር ግን ሁሉን ለሚያውቅ ነገራችንን ሰጥተን በእምነት እናርፋለን ምክኒያቱም እኛ አንወቅ እንጂ የሚያውቅልን አለና ይላል።
በአለም ላይ ያሉ ሁለት ታላላቅ ችግሮች፦
የመጀመሪያው እግዚአብሄርን ሳያውቁ ወይም እውነተኛውን አምላክ ሳያውቁ በራሳቸው መንገድ የሚመረምሩት፣ እግዚአብሄር ማለት ይህ ነው የሚሉት፣ ቆርጠው ለራሳቸው እውቀት የሚሟገቱ ሰዎች የፈጠሩት ነው።
ሁለተኛው እውነተኛውን አምላክ አግኝተው ባህሪውን ያላወቁት የፈጠሩት ችግር ነው። ባለማወቃቸው ላይ የሚይዙት ጥልቀት የሌለው ጥቂት የእውቀት ፍንጭ ወዲያና ወዲህ ሲያወዛውዛቸው አልፎም በትእቢት ላይ ሲጥላቸው መታየቱ የችግሩ መገለጫ ነው።
በቃሉ መሰረት ግን ከእግዚአብሄር ጋር የሚያኖረን ሁሉን በማወቅ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ሳይሆን ሁሉን የሚያውቀውን እርሱን በማመን፣ እንደሚያውቅልንና እንደሚያደርግልን በመተማመንም እርሱን ስንቀበል ነው። ደግሞ ያልተረጋገጠ እውቀታችን እንዳይገፋን ስንጠነቀቅም ነው።
በ1ቆሮ.4:3-7 ላይ ‘‘ነገር ግን በእናንተ ዘንድ ወይም በሌላ ሰው ዘንድ ብፈረድ ለእኔ ምንም አይደለም፤ እኔም በራሴ እንኳ አልፈርድም፤ በራሴ ላይ ምንም አላውቅምና፥ ነገር ግን በዚህ አልጸድቅም፤ እኔን የሚፈርድ ግን ጌታ ነው። ስለዚህም በጨለማ የተሰወረውን ደግሞ ወደ ብርሃን የሚያወጣ የልብንም ምክር የሚገልጥ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ጊዜው ሳይደርስ አንዳች አትፍረዱ፤ በዚያን ጊዜም ለእያንዳንዱ ምስጋናው ከእግዚአብሔር ዘንድ ይሆናል። ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አንዱ በአንዱ ላይ አንዳችሁም እንዳይታበዩ። ከተጻፈው አትለፍ የሚለውን በእኛ ትማሩ ዘንድ፥ ይህን በእናንተ ምክንያት ስለ ራሴና ስለ አጵሎስ እንደ ምሳሌ ተናገርሁ። አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው?’’ ይላል።
የእግዚአብሄርን ባህሪ ያለማወቅ ራስን ያለማወቅ ይፈጥራል፤ ይህ ሲሆን የምናገኘው ታናሽ እውቀት ወደ ትምክህት፣ ወደ ትችት፣ ወደ ፍርድ፣ ወደ ኩራት እያለ የጥፋት አፋፍ ድረስ ያወርዳል፤ በእግዚአብሄር ቤት የሚያኖረን ያወቅነውን ትንሽ ነገር ይዘን በፊቱ በትህትና መቅረብ በዚያ ውስጥ ሊገልጥልን ወዳለው ወደ ብርሃኑ በምስጋና መዘርጋትም ነው፤ ባወቁት ትንሽ እውቀት የተመኩ እንዴት ባለ ትምክህት ተጠልፈው ለቤተክርስቲያን የመከፋፈል ምክኒያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ማየት የምንችለው ነገር ነው ፤ ሃዋርያው በትህትና ሲመክራቸው እኔ ራሴ እንኳን በሌላው ላይ ልፈርድ ይቅርና በራሴ ላይ እንኳን ምንም አላውቅም ይላል። የእምነታችን ውሃ ልክ ቃሉ ይሁን፣ በጌታ ላይ ያለን ትምክህት እንዳይዛባና እንዳንስት ቃሉ ከሚመራን ምሪት አንውጣ፣ የእምነታችን መስመር ሃዲዱን እንዳይስት ውስጣችንን እየሰማን ከመፍረድ ይልቅ ሁሉን የሚችለውን እየሰማን ወደፊት እንራመድ። በእምነት ላይ የሚኖር አንድ ሰው የህይወት ምስቅልቅል እንዴትና ለምን እንደሚያደርስ፣ ምክኒያቱ ደግሞ ምን እንደሆነ በ1ቆሮ.8 ላይ ያለው የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍል ያስተምረናል፤ ዋናው ነገር ቁንጽል እውቀት ያስታብያል ነው፦
-ለምሳሌ ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋ ያለን እውቀት አለ፣ እርሱም ጣዖት ሁሉ በዓለም ከንቱ እንደ ሆነ ከአንዱም በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ የምናውቀው እውቀት ነው፤ ግን ይህን አውቀናል ብለን በእውቀታችን እንዳንታበይ፣ ይህ እውቀት ከፍ ከፍ አድርጎ የማይገባ ስራ ውስጥ እንድንጠመድ እንዳያደርገን እንጠንቀቅ፣ ያለበለዚያ ሌላውን እንድንጎዳ በር ይከፍታል፣ የሚሻለው ግን ነገሮችን እንዲህ ባለ ሙሉ ያልሆነ እውቀት ከመያዝ በፍቅር በኩል ቢሆን ሁሉንም ያንጻል።
-እውነት ነው ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች በአህዛብ ዘንድ የሚታመኑና የሚመለኩ አሉ፤ ቢሆንም ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ይኑሩ እንጂ እውነቱ ለእኛ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ ያለን መሆኑ ነው፣ እንዲሁም ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለ፣ በዚህ እግዚአብሄር በስጋ ተገለጠ የሚለውን ምስጢር አምነናል ተቀብለናልም።
-ይህ እውቀት ያላቸው ሰዎች ግን እያወቁ ለጣኦት የተሰዋ ምግብ ደፍረው ሲበሉ ሕሊናቸው ደካማ የሆኑትን እያሰናከሉ ነው።
-ጣኦት ምናምንቴ እንደሆነ ያመነ ምግብ ሳያማርጥና ሳይጠራጠር ጸልዮ ይበላል፣ ይህ እውቀት ይኑረው እንጂ በዚህ የተጎናጸፈው መብት ለደካሞች ዕንቅፋት እንዳይሆን ሊጠነቀቅ ይገባዋል።
-ስለዚህ ሲመክረን በአንድ በኩል እውቀት አለኝ ትላለህ እንጂ እውቀትህ ሙሉ ስላይደለ አወቅኩ ባልከው እውቀት መሰናክል መሆንህን አላወቅክም፤ በዚህ ታብየሃል ይለናል።
‘’አንተ እውቀት ያለህ በጣዖት ቤት በማዕድ ስትቀመጥ አንድ ሰው ቢያይህ፥ ደካማ ሰው ቢሆን ለጣዖት የተሠዋውን ለመብላት ሕሊናው አይታነጽበትምን? በአንተ እውቀትም ይህ ደካማ ይጠፋል፥ እርሱም ክርስቶስ የሞተለት ወንድም ነው። እንዲህም ወንድሞችን እየበደላችሁ ደካማም የሆነውን ሕሊናቸውን እያቆሰላችሁ ክርስቶስን ትበድላላችሁ። ስለዚህም መብል ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ፥ ወንድሜን እንዳላሰናክለው ለዘላለም ከቶ ሥጋ አልበላም።’’
ይሄን ምስቅልቅል ያመጣው ገሚስ እውቀት ትምክህት ሆኖ ነው፣ ያወቅነውን ግን በፍቅር ብንይዝ (ለወንድማችን እየተጠነቀቅን ቢሆን) እኛም ታንጸን ለሌሎች እንተርፋለን።
1ቆሮ.3:17-21 ‘’ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ። ማንም ራሱን አያታልል፤ ከእናንተ ማንም በዚች ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን። የዚህች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነውና። እርሱ ጥበበኞችን በተንኰላቸው የሚይዝ፤ ደግሞም። ጌታ የጥበበኞችን አሳብ ከንቱ እንደ ሆነ ያውቃል ተብሎ ተጽፎአልና። ስለዚህም ማንም በሰው አይመካ። ነገር ሁሉ የእናንተ ነውና’’
ደግሞ በራስ ጥበብ መንፈሳዊ ህይወትን መምራት ጥፋት ከሆነ ትምክህታችንን ከስጋዊ ጥበብ ላይ እናውርድና በመንፈስ እግዚአብሄር የሚያስተምረንን በትህትና እንያዝ። ሁሉን የሚችል አምላክ ለትሁታን እውቀትን፣ ማስተዋልን፣ ምሪትን ይሰጣል፤ ዛሬም ሁሌም ትምክህቱ እግዚአብሄር የሆነ፣ ረሃቡ የርሱ ክብር የሆነም ይጠግባል፤ በራሱ የማይመካ ትምክህቱ እግዚአብሄር የሆነና እርሱ እንዲመራው የፈቀደ ሞገስ ያገኛል።
1ቆሮ.4:7 ‘’አንተ እንድትበልጥ ማን አድርጎሃል? ያልተቀበልኸውስ ምን አለህ? የተቀበልህ ከሆንህ ግን እንዳልተቀበልህ የምትመካ ስለ ምንድር ነው?’’
ከእግዚአብሄር ተቀብሎ እንዳልተቀበለ የሆነና የእግዚአብሄርን ስጦታም የታበየበት አማኝ ሳንሆን ከኔ የሆነ የለም ሁሉ ከርሱ ነው ብለን መኖር የምንችልበትን ጸጋ ይስጠን፦
ያዕ.1:16-22 ‘’የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ አትሳቱ። በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ። ለፍጥረቱ የበኵራት ዓይነት እንድንሆን በእውነት ቃል አስቦ ወለደን። ስለዚህ፥ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፥ ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ ለመናገርም የዘገየ ለቍጣም የዘገየ ይሁን፤ የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ አይሠራምና።ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ። ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ።’’