የአዲስ ኪዳን መጽሃፍ መጀመርያ፦ በመጀመርያ ቃል ነበረ
ብሉይ ኪዳን ሲጀምር በመጀመርያ እግዚአብሄር ሰማይና ምድርን ፈጠረ ሲል በአዲስ ኪዳን በዮሃንስ ወንጌል መጀመሪያ ላይ በመጀመርያው ቃል ነበር ይላል። ስለዚህ በመጀመሪያው ቃል ከነበር፣ በፍጥረት አፈጣጠር ውስጥም ጅማሬውን እግዚአብሄር እንደጀመረው ካመለከተን ከፍጥረታት በፊት የነበረው ቃል የነበረው እግዚአብሄር ብቻ እንደሆነ እንመለከታለን፤ እግዚአብሄር ያለና የሚኖር መሆኑን ባወጀው መሰረት በፍጥረታት ስራው ጊዜ አጋዥ ነበረው ልንል አንችልም፣ ረዳት አስፈለገው ማለትም አያስደፍርም፣ ከእርሱ ጋር አጋዥ ወይም ተመጣጣኝ አምላክ ነበረ የሚያሰኝ ምልክት አናይም፤ ምክኒያቱም ያሉና የነበሩ የሚባሉ አማልክት፣ አካላት፣ አገዛዞች የሉምና። እንዲያውም በስራው አካባቢ ማንንም እንዳላስገባ ሲናገር እንዲህ ብሎአል፦
‘’ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸውም፥ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፥ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፥ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፥ እጅህንም እይዛለሁ እጠብቅህማለሁ፥ የዕውሩንም ዓይን ትከፍት ዘንድ የተጋዘውንም ከግዞት ቤት በጨለማም የተቀመጡትን ከወህኒ ቤት ታወጣ ዘንድ ለሕዝብ ቃል ኪዳን ለአሕዛብም ብርሃን አድርጌ እሰጥሃለሁ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም።እነሆ፥ የቀድሞው ነገር ተፈጸመ፥ አዲስ ነገርንም እናገራለሁ፤ አስቀድሞም ሳይበቅል እርሱን አስታውቃችኋለሁ።’’ ይላል። (ኢሳ.42:5-9)
ከእግዚአብሄር ሌላ አማልክት፣ ፈጣሪዎች፣ አካላት፣ እኩያዎች እያልን በሰዋዊ አሳብ እንዳንታመን ሰማያትን የፈጠረ እንጂ የፈጠሩ፣ የዘረጋቸው እንጂ የዘረጉዋቸው ሲል አልተሰማም፤ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና እንጂ ያጸኑ የሚልም ከቶ በቃሉ ላይ አልተመለከተም፤ በምድር ለሚኖሩ የሰው ልጆች እስትንፋስን የሰጠ አንድ አምላክ ሊኖር ተገብቶታል እንጂ ተባብረው እስትንፋሳቸውን ለሰው ያዋጡ አምላኮች የሉም። ለምን አህዛብ እግዚአብሄርን በግብር፣ በንግግር፣ በመለኮት፣ በአካል ሊያበዙት አስፈለጋቸው፣ በእርግጥ ይህ ፍላጎት የሰው ልጆች ሳይሆን መነሻው ክፉ መንፈስ የሆነው ሰይጣን መሆኑ ነው፦
‘’እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ አንተ ታምናለህ፤ መልካም ታደርጋለህ፤ አጋንንት ደግሞ ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል።’’ (ያእ.2:19)
የሰው እግዚአብሄርን በአንድነቱ አምኖ መቀበል እንደ መልካም ድርጊት ተቆጥሮ ተቀባይነት ሲያሰጠው አጋንንት የሚያምኑት የእግዚአብሄር አንድነት መልካም ሊያደርጉ የሚገፋቸው ሳይሆን በርሱ እውቀት ላይ ተነስተው የሰውን አስተሳሰብ ለማሳት የሚያጣምሙ ትምህርቶችን የሚፈጥሩበት በመሆኑ የስራቸው ፍርድ ያንቀጥቅጣቸዋል።
በመጀመሪያ ቃል ነበረ?
በመጀመሪያው የፍጥረት ስራው ጊዜ እግዚአብሄር ቃል ከነበረ አሁን ማን ነው? ምንድንስ ነው? ብለን መጠየቅ ይገባል፦ ቃሉም በራሱ መልስ አለው። ሃዋርያው በፍጥረት መጀመሪያ አስቀድሞ የነበረው ፈጣሪ ቃል እንጂ ፍጥረት ያለመሆኑን ይልቅ የተፈጠረው የቃሉ ተከታይ ውጤት መሆኑን ያመለክትና ቃል የነበረው ደግሞ ስጋ እንደሆነ በም.1:14 ላይ ያበስረናል። እግዚአብሄር የቃል ባህሪ የነበረው አምላክ ሲሆን ቃልም ከውስጡ አውጥቶ የሚናገርና የሚፈጥር በአዲስ ኪዳን ላይ ሲደርስ የሰራበትን፣ የፈጠረበትን፣ በኤደን ገነት መሃል እየተመላለሰ ሰውን የጎበኘበትን ቃል ስጋ ሆኖአል ይለዋል። አሁን በፍጥረት ጊዜ የምናውቀው እግዚአብሄርና ቃሉን ሳይሆን እግዚአብሄርና ስጋውን ይሆናል። እስራኤላውያን ‘አማኑኤል’ እግዚአብሄር ከእኛ ጋር ማለታቸው እውነት ስለነበር ነው፤ አማኑኤል ለነርሱ ትልቅ ነገር ነውና፦ ያለና የሚኖር እኔ ነኝ ብሎአቸው ስለነበር፣ እንዲሁም ከእኔ በቀር አምላክ አይሁንላቸሁ ብሎአቸውም ስለነበር፤ በዚህ ሁሉ ምክኒያት ደፍረው እግዚአብሄር በመሃከላችን ተገኘ አሉ፤ የጠበቁት፣ የፈለጉትንም በእርግጥ ስላገኙ ይህን አዋጅ አወጁ። ለአህዛብ ግን አማኑኤል እንግዳ አምላክ ነበር፤ በ1ጢሞ. 3:16 ላይ ሰዎች አማኑኤል ማለት ምን እንደሆነ ይረዱ ዘንድ ይናገራል፦
‘’እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ።’’ ይላልና።
እግዚአብሄር በስጋ ተገለጠ፦ በብሉይ ኪዳን ዘመን በቃሉ ተገልጦ እንደነበረው ሁሉ አሁን በስጋ መገለጡን ያሳያል፤ በተጨማሪ ለመላእክት ታየ የሚለው ቃል ደግሞ ልብን የሚይዝ እውቀት ነው። እግዚአብሄርን ያየው አንድ ስንኳ አልነበረም በብሉይ ኪዳን ዘመን፤ እግዚአብሄር ግን በስጋ ሲገለጥ መላእክት አይተው ታላቅ ምስጋናን አቅርበዋል፦
‘’እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ። በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና። ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል።’’ (ቆላ. 2:8-10)
በሙሴ ትምህርት ላይ የተቀመጠው ህግ እግዚአብሄርን ያየ ማንም የለምና አንዳችም መልክ ለራስህ አትውሰድ ብሎ ያስጠነቀቀ ሲሆን የክርስቶስ ትምህርት መለኮት የተባለው እግዚአብሄር ባዘጋጀው የክርስቶስ ሰውነት ውስጥ ለአንዴና ለዘላልም ተገልጦ ሊኖር እንደወሰነ አስተማሪ ነው።
ዮሐ.1:18 ‘’መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።’’
የፍልስፍና ትምህርት በሃዋርያው ዘንድ የተረገመ የሆነበት ምክኒያት አለው፦
1ኛ የአይሁድ ፍልስፍና እግዚአብሄር አንድ ብቻ ነው ይልና ነገር ግን ይህ እግዚአብሄር በክርስቶስ ኢየሱስ አልተገለጠም የሚል ነው። በዚህ ሳቢያ ጌታን አቁመው ሲከራከሩት እናያለን፤ አንተ ሰው ስትሆን ራስህን አምላክ አድርገሃል ብለው ሊወግሩትም የተነሱበት አጋጣሚም ነበር። በመካከላቸው በመገኘቱ አባቱንና እናቱን የምናውቃቸው አይደሉምን ራሱን እንደ ሌላ ለምን አድርጎ ይቆጥራል? ሲሉ የዘበቱበት አጋጣሚ የእግዚአብሄርን ፈቃድ ያለማወቅና የመጋፋት ውድቀት እንዲጥላቸው አድርጎአል፦
ዮሐ.1:10-13 ‘’በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም። የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።’’
-የመጣው እግዚአብሄር አይደለም ላሉ ከራሱ ከእግዚአብሄር እንዳይወለዱ እንቅፋት ሆነባቸው
-ጥንት የነበረው ራሱ መጣ ብለው ያላመኑ ሌላ አማልክት ፈጠሩ
-ወገኔ ብሎ ከመጣው ህዝብ እግዚአብሄር አምልኮም እምነትም ያለማግኘቱ አሳዛኝ ክስተት ፈጠረ
-አህዛብም አንዱን የእስራኤል አምላክ እንደቃሉ ሊቀበሉት እንደተሳናቸው እንመለከታለን።
2ኛ የአህዛብ ፍልስፍና እግዚአብሄርም ሰውነቱም አምላክ ናቸው የሚል ነው፤ ይህ ደግሞ የሁለት አማልክት እሳቤን ወለደ፦ከዚህ ሰዋዊ ፍልስፍና አብ አምላክ ነው፣ ወልድም (የተወለደው ልጅም) አምልክ ነው የሚል ፍልስፍና በቀለ ማለት ነው። ይህ ፍልስፍና ባለ ብዙ ዘርፍ ሆኖ ሲቀጥል የለየለት መጥፊያ፣ የማይተራረቁ አሳቦች መፍለቂያ በመጨረሻም የእርግማን እውቀት ሆኖ ቀጥሎ እናያለን። በዚህ ዘመን የእግዚአብሄር እስትንፋስም ሌላ አምላክ ሆኖአል፤ ደግሞ ከማርያም የተወለደ ሌላ አምላክም ተነስቶአል፣ እንዲሁ እስከ አለም ፍጻሜ የጥፋት ትምህርት እየወጣ ይቀጥላል። መፍትሄው ግን የክርስቶስ ትምህርት ብቻ ነው። እንዲህ የሚለው፦
የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፥ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም።(ዮሐ.10:29)
አባቱ ለምን ከሁሉ ይበልጣል? ደግሞስ አባት ከልጁስ አይበልጥምን? አባት የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪና አስገኝ ነው፤ እንዲሁም የልጁ ምንጭ ነው፣ ወልዶታልና፤ ስለዚህ አባት ከልጁ ይበልጣል፤ አብና ወልድ እኩል ናቸው የሚሉ በዚህ ተሳስተዋል።
1ቆሮ.8:5-7 ‘’መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ ነገር ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ፥ ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን። ነገር ግን ይህ እውቀት በሁሉ ዘንድ አይገኝም፤ አንዳንዶች ግን ጣዖትን እስከ አሁን ድረስ ስለለመዱ፦ ለጣዖት የተሠዋ ነው ብለው ይበላሉና ሕሊናቸው ደካማ ስለ ሆነ ይረክሳል።’’
አብ አምላክ ነው፣ ወልድ አምላክ ነው፣ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው የሚለውን ትምህርት ይህ ቃል እንደሚሽረው ግልጥ ነው፤ አንድ አምላክ ግን በወልድ ውስጥ ይኖራል።
እኔና አብ አንድ ነን።(ዮሐ.10:30)
ልጅ አባቴ ይበልጣል ካለ እንዴት ደፍሮ ሁለታችን አንድ ነን ይላል? ይህ በአይሁድ ዘንድ ቁጣንና ወገራን ያነሳሳ አባባል ነበር፤ አህዛብም አብና ወልድ እኩል የሆኑ አምላክ ናቸው የሚል ትምህርት ስላላቸው የጌታ ንግግር አይስማማቸውም፤ ምስጢሩ ግን ያለው አባትና ልጅ በአንድ አካል በውህደት መኖራቸው ላይ ነውና ንግግሩ አጉረምራሚ አድሮጎአቸዋል።
‘’ደግሞም ኢየሱስ፤- እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም ብሎ ተናገራቸው። ፈሪሳውያንም፦ አንተ ስለ ራስህ ትመሰክራለህ፤ ምስክርነትህ እውነት አይደለም አሉት።ኢየሱስ መለሰ አላቸውም፦ እኔ ስለ ራሴ ምንም እንኳ ብመሰክር ከወዴት እንደመጣሁ ወዴትም እንድሄድ አውቃለሁና ምስክርነቴ እውነት ነው፤ እናንተ ግን ከወዴት እንደ መጣሁ ወዴትም እንድሄድ አታውቁም።… እንግዲህ፦ አባትህ ወዴት ነው? አሉት። ኢየሱስ መልሶ፦ እኔንም ወይም አባቴንም አታውቁም፤ እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር አላቸው።’’ (ዮሃ. 8:12-19)
እኔን ስንኳ ባታምኑ አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ ታውቁና ታስተውሉ ዘንድ ሥራውን እመኑ። (ዮሐ.10:38)
ይህን ንግግሩን ማመን ያልፈለገ ካለ ችላ ይለው ይሆናል እንጂ ግልጥ ያለ እውነትን የያዘ ነው፤ ለመሆኑ ስለምንድነው አብ በወልድ ውስጥ ወልድም በአብ ውስጥ ሆነው በአንድ አካል ባለመለያየት እንደሚኖሩ ሊታመን የማይችለው? ስህተታችን እርግማን ውስጥ እንደሚጥለን በጣም ሊታየን ያስፈልጋል።
ዮሃ.14:8-11 ‘’ፊልጶስ- ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው።ኢየሱስም አለው፦ አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ። አብን አሳየን ትላለህ?እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል። እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ባይሆንስ ስለ ራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ።’’
መሰረታዊ እውቀት፦ አንድ አምላክ አብ ከሆነና ወደኛ የመጣው በወልድ በኩል እንደሆነ ካመለከተን፣ እንዲሁም አብ በወልድ ውስጥ ወልድም በአብ ውስጥ ከሆነ ኢየሱስ አብም ወልድም ነው ማለት ነው!
ቆላ.2:8-9 ‘’እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፥ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ። በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና።’’
የጌታ ኢየሱስን ቃል እያጣመመ ያስቸገረ ሰዋዊ ትረካ፣ በተለይ በአይሁድ ዘንድ የሚዘወተር ትውልድ ቆጠራ፣ መንፈሳዊነት የሌለው አለማዊ ትምህርት፣ በተለይ በአህዛብ የተቋቋሙ መንፈሳዊ የሚባሉ ትምህርት ቤቶች የሚቀምሩዋቸው እውቀት መሳይ ወጎች፣ በመለኮታዊ ምስጢር ላይ የተነሳ ፍልስፍና በተለይ ሳይንስንና ፍልስፍናን መሰረት አድርጎ መለኮታዊ ትንተና ላይ የተመረኮዘ እውቀት… ይሄና የመሳሰለው ሁሉ ከጌታ የሚያርቅ እንደሆን እንጂ አንዳቸውም ውጤት የላቸውም፤ ልጆችሽ ከእግዚአብሄር የተማሩ ይሆናሉ እንደሚል ቃሉ።
‘’እውነትን የምታውቁ ስለ ሆናችሁ፥ ውሸትም ሁሉ ከእውነት እንዳልሆነ ስለምታውቁ እንጂ እውነትን ስለማታውቁ አልጽፍላችሁም። ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው። ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ እንኳ የለውም፤ በወልድ የሚታመን አብ ደግሞ አለው። እናንተስ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ጸንቶ ይኑር። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ቢኖር፥ እናንተ ደግሞ በወልድና በአብ ትኖራላችሁ።’’ (1ዮሃ.2:21-24)
