‘’እግዚአብሔርም ሙሴን፦ ያለና የሚኖር እኔ ነኝ አለው፤ እንዲህ ለእስራኤል ልጆች፦ ያለና የሚኖር ወደ እናንተ ላከኝ ትላለህ አለው።’’ (ዘጸ.3:14)
ያለና የሚኖር አምላክ የተባለው በራሱ የሚኖር፣ በሌላ የሚያኖር ሃይል የማይኖር፣ ለመኖር ጅማሬ የሌለው፣ ህያውነቱን የሚለካ የሌለ፣ ለህልውናው ድጋፍም መስፈርትም መመኪያም የሌለው፣ ለሌሎች መኖር መሰረት የሆነ፣ ፍጥረታት በርሱ በመፈጠራቸው ጅማሬያቸው ከርሱ የሆነ መሆኑን ያመለክታል። ይህን ታላቅ መልእክት እስራኤላውያን ይስሙ ሲል ያለና የሚኖር አምላክ በሙሴ አፍ ላከው።
ያለና የሚኖር ሁሉንም ይናገራል፦ ስለእግዚአብሄር ማንነት፣ ስለመላእክት፣ ስለሰውም ማንነት ጭምር የሚናገር ስም ነው። አምላክ በሰውኛ አመለካከት እንደማይለካ ያለና የሚኖር ያሳየናል፤ ምክኒያቱም የሰው ህልውና ጅማሬ እስካለው ድረስ በሰዎች የሚፍጠሩ አማልክታዊ ትንታኔዎች ከንቱ ስለሚሆኑ ነው። ሰዎች ግን ከእግዚአብሄር እውቅት ስለራቁ በአእምሮአቸው የማስተዋል ሃይል ብቻ ይመካሉ፣ ስለዚህ አምላክ ፈጣሪ እስከመሆን ይደርሳሉ፤ ሁሉን ያወቁ ይመስላቸዋልና፤ የአስተሳሰባቸው ጥልቀት የፍጥረትን መጀመሪያና መጨረሻ፣ የፍጥረትን እድሜና የሃይላትን ምንጭ ለመተንተንና ከሰዎች በላይ ያን የሚያደርግ እንደሌለ እስከማመን ያደርሳቸዋል።
እግዚአብሄር ግን ያለና የሚኖር በመሆኑ በምንም ሁኔታ ውስጥ ይሁን በየትኛውም ጊዜ መጠራት የሚችል እርሱ ብቻ፣ በአምላክነት የኖረውም ያለውም እርሱ ብቻ እንደሆነ ያሳስባል፤ በቀድሞውም የፍጥረት ዘመን እርሱ፣ በኋለኞችም ዘመን ሊሆኑ ባላቸው ነገሮች መሃል ያለው እርሱ ብቻ ነው። የሁሉ አስገኝ እርሱ፣ ፍጥረታት የሚጠሩት በርሱ ብቻ እንደሆነም ቃሉ ያስተምረናል።
እግዚአብሄር ፍጥረታትን የሚመለከትበት፣ የሚዳኝበት፣ አምልኮ የሚቀበልበትም ጭምር አንድ ዙፋን አለው፤ የአንድ ዙፋን ክብር ለመንፈሳዊ እውቀት ምን ፋይዳ አለው? ይህ እውቀት እኮ ነው እግዚአብሄር አንድ አካል እንዳለው የሚያሳየን፣ የሚያሳስበንና የሚያሳምነን፤ ይህ እውቀት ባለ ብዙ አካልና አምሳል ከሚያመልክ የአህዛብ ክርስትና እምነት ፈጽሞ የሚለይና ወደ አብረሃም እምነት የሚያመጣ ነው፤ አንድ የእግዚአብሄር ዙፋን በአንድ ሰማያዊ መንግስት ውስጥ ብቻ ያለ ነው።
ወደ እግዚአብሄር ቀርበው የእግዚአብሄርን ድምጽ የሚሰሙ ቅዱሳን የሚመጣውን ድምጽ በጥንቃቄ ሊሰሙ ግዴታ ነው፤ የሰሙትንም ማመንና መግለጥ ሌላው የሚጠበቅ ነገር ነው። በቀጥታ ከአምላክ በተቀበሉትና ከሰዎች የተነገራቸውን በሰሙት መሃል የማስተዋል ክፍተት ሲፈጠር ግን ትልቅ የመልእክት መዛባትና እውነቱን የማዳከም ሂደት ይፈጠራል። በዚህ ስህትት የሚፈጠረው ነገር እግዚአብሄር በቃሉ ሊሰራ የፈቀደውን ስራ በሰዎች ህይወት እንዳይሰራ ከማድረጉም ሌላ ሊቀበለን እንደመጣ ሁሉ እንዲቃወመን ያደርጋል፦ ሊባርክ የመጣውን ይህን አምላክ እንዲረግም፣ ሊፈውስ የመጣውን መሃሪ አምላክ እንዲመታ፣ ሊጠራ የመጣውን ቅርብ አምላክ እንዲያሳድድ እንዲርቅም ያደርጉታል። በረከት ወደ መርገም ከተለወጠ እንዲለወጥ የሚያደርጉ ቢኖሩ እነዚህ በቃሉ የሚነሱ ትእቢተኞች ሰዎች ናቸው።
በዘጸ.3:14 ውስጥ እግዚአብሄር ሙሴን ሲናገር ሙሴ በጥንቃቄ ባይሰማ የሚፈጠረው የስህተት እውቀት በእስራኤል ዘንድ ምን ሊሆን ይችል ነበር? እግዚአብሄርም ሙሴን፦ ያለና የሚኖር እኔ ነኝ አለው፤ ሙሴ እንደሰማ ባይሆንና ቢተረጉመው ኖሮ ያለና የሚኖር በሚል ፋንታ ያሉና የሚኖሩ፣ እኔ ነኝ ባለው ፈንታ እነርሱ ቢል ያለጥርጥር አሁን በዚህ ዘመን ያሉ የአህዛብ አስተማሪዎች የፈጠሩትን እውቀት በአይሁድ ዘንድ አስቀድሞውን እናገኘው ነበር። እንዲሁም ወደ እናንተ ላከኝ የሚለውን ወደ እናንተ ላኩኝ ቢልስ? ምን እንጠብቃለን፣ እኛ አስቀድሞ መሰረታችን የአጋንንት እምነት የነበረ አህዛብ?
በኢሳ.6:1-9 ንጉሡ ዖዝያን በሞተበት ዓመት ነቢዩ ኢሳያስ ታላቅ ራእይ አይቶ ነበር፤ በራእዩ ውስጥ ነቢዩ በቀጥታ እግዚአብሄርን በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ አየ (ባየው እርግጠኛ አልነበረም ወይ?)፣ እንዲሁም ሲናገር ድምጹን ሰማ (ከእግዚአብሄር አፍ ድምጹ እንደወጣ እርግጠኛ መሆንም ይገባል)። ያየውን እግዚአብሄር በትክክል ባይሰማና ድምጹን በትክክል ባይሰማ ምን ይሆናል? እግዚአብሔርን አየሁት ሳይሆን አየሁዋቸው ሊል ነው፣፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር ሳይሆን የልብሳቸው ዘርፎች መቅደሱን ሞልተውት ነበር፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች ሲል የተሰማውን የመላእክት ድምጽ ምድር ሁሉ ከክብራቸው ተሞልታለች ማለት፣ ዓይኖቼ የሠራዊትን ጌታ ንጉሡን እግዚአብሔርን ስለ አዩ የሚለውን ስላየሁዋቸው ቢል ምን አይነት እግዚአብሄር ሊሆን ይችል ነበር? እስቲ አህዛብ ሁላችን ዛሬ ላይ ይህን እናስብ፤ አሁን አሁን እውነታው እንደሚያሳየን ከሆነ ሰዎች በተለይ የአህዛብ አስተማሪዎች የነቢዩን አምላክ ከቃሉ መንፈስ በተቃራኒ መንገድ ሲቀርጹት ይታያል።
እግዚአብሄር በአንድ ስፍራ ጥብቅ መልእክት ሲያስተላልፍ እንመለከታለን፦
‘’እርሱም ይላል፦ አማልክቶቻቸው የት ናቸው? ይታመኑባቸው የነበሩት አማልክት? የመሥዋዕታቸውን ስብ የበሉ፥ የመጠጥ ቍርባናቸውንም የወይን ጠጅ የጠጡ? እነርሱ ይነሡ፥ ይርዱአችሁም፥ መጠጊያም ይሁኑላችሁ። አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደ ሆንሁ፥ ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ፤ እኔ እገድላለሁ፥ አድንማለሁ፤ እኔ እመታለሁ፥ እፈውስማለሁ፤ ከእጄም የሚያድን የለም። እጄን ወደ ሰማይ እዘረጋለሁና፥ እንዲህም እላለሁ፦ ለዘላለም እኔ ሕያው ነኝና የሚንቦገቦግ ሰይፌን እስለዋለሁ፥ እጄም ፍርድን ትይዛለች፥ ጠላቶቼንም እበቀላለሁ፥ ለሚጠሉኝም ፍዳቸውን እከፍላለሁ።’’ (ዘዳ. 32:37-41)
እግዚአብሄር በዚህ ክፍል ሲናገር ሙሴ ወደ ተሳሳቱት ሰዎች ፊቱን አቅንቶ እንዲያይና እንዲታዘባቸው ያደርገዋል፣ በነርሱ ዘንድ ያለውን የአምላክ አይነት እንዲታዘብ ያደርገውና መልሶ ወደ አብረሃም አምላክ እንዲመለከትና ወደ ማስተዋል እንዲመጣ ያደርገዋል፦ በአህዛብ ዘንድ ያለው አምልኮ ሃሰተኛ አምልኮ ነው፣ ከአንድ በላይ አምላክ ያለው እምነት ስለሆነ በአጋንንት የረከሰ ነው፤ ሙሴ ወደ እግዚአብሄር ሲመለከት ግን እግዚአብሄር እየኝ ይለውና ስታየኝ ከእኔ በቀር በእኔ ዘንድ ማንን አይተሃል? ይለዋል። በእርግጥ ያለና የሚኖር በርሱም ሆነ በሚመጡት ትውልዶች ከርሱ በቀር አምላክ እንደማይኖር የሚያረጋግጥለት ነበር።
አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደ ሆንሁ ማለቱ ሙሴ ስታየኝ በአንድ አካል፣ ስታስበኝ ነጥለህ እኔን ብቻ እያለ ነው፤ ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ ሲል ሁለትና ከዚያም በላይ የሚመለክ አምላክ አለ ብለህ ፈጽሞ አታስብ አሉ ቢባልም ወደ እነርሱም ጨርሶ አትይ እያለው ነበር፤ በተለይ እጄን ወደ ሰማይ እዘረጋለሁ ሲል እናያለን፣ እግዚአብሄር የት ሆኖ ወደ የት እጁን እየዘረጋ ነው? ይህን በልብ መያዝ ከእግዚአብሄር ጋር ያኖራል።
እግዚአብሄርን የሚያውቅ ንጉስ ጸሎት፦
‘’ሕዝቅያስም ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ጸለየ፦ አቤቱ፥ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ አንተ ብቻህን የምድር መንግሥታት ሁሉ አምላክ ነህ፤ ሰማይንና ምድርን ፈጥረሃል። አቤቱ፥ ጆሮህን አዘንብልና ስማ፤ አቤቱ፥ ዓይንህን ክፈትና እይ፤ በሕያው አምላክ ላይ ይገዳደር ዘንድ የላከውን የሰናክሬም ቃል ስማ።አቤቱ፥ በእውነት የአሦር ነገሥታት ዓለሙን ሁሉ አገሮቻቸውንም አፍርሰዋል፥አማልክቶቻቸውንም በእሳት ላይ ጥለዋል፤ የእንጨትና የድንጋይ የሰው እጅ ሥራ ነበሩ እንጂ አማልክት አልነበሩምና ስለዚህ አጥፍተዋቸዋል።እንግዲህም አምላካችን አቤቱ፥ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ ብቻ እግዚአብሔር እንደ ሆንህ ያውቁ ዘንድ ከእጁ አድነን።’’ (ኢሳ. 37:15-20)
ይህ ንጉስ ወደ እውነተኛ አምላክ በእውቀት መጸለይን ያስተምረናል፤ ከአብረሃም አምላክ መልስ የሚፈልግ እንደሆነና (ሰይጣን የብርሃን መልአክ መስሎ እየመለሰ እንደሆነ ያሳስባልና) እርሱን ማወቅና በእውቀት ወደ እርሱ መጸለይ እውነተኛ መልስ እንዳለው ያሳየናል። በኪሩቤል ላይ የሚቀመጥ አንድ አካል ሊኖር ይገባል፣ እርሱም ኢሳያስ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ክብሩን ያየው የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ነው፤ ንጉስ ህዝቂያስ ይህ እውቀት ስላለው አንተ ብቻህን የምድር መንግሥታት ሁሉ አምላክ ነህ፣ በዙፋንህ ለብቻህ ተቀምጠሃልና፤ ሰማይንና ምድርን ያል ረዳት፣ ያለ አማካሪ ብቻህን ፈጥረሃልና ሲል አምላኩን የጠራል።
ይህ አምላክ በፍጥረታት መጀመርያ ሲፈጥር ሁሉን ለብቻው ፈጥሮ ነበር፣ እርሱ ሲነግስ ብቻውን፣ ሲናገር ብቻውን፣ ሲሰማ ብቻውን፣ ሲታይ ብቻውን ነው። ይህ የአይሁድ አምላክ ባህሪ ለአህዛብ እንዲታወቅም የተገለጠው በዚህ መንገድ ነው። እግዚአብሄር አህዛብን ሲጠራ ህዝቡ በአብረሃም እምነት በኩል እንዲድን ነው፤ የእግዚአብሄር ፈቃድ አህዛብ መንፈሳዊ እስራኤል ይሆኑ ዘንድም ነው፤ መንፈሳዊ እስራኤል የአብረሃም የመንፈስ ዘሮች ናቸው፤ እግዚአብሄር በእምነት የአብረሃም ዘር አድርጎአቸዋል። ለአብረሃም ልጅ የሆኑትም በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ነው። ስለዚህ አህዛብ በእምነት በኩል የአብረሃም ልጆች ከሆንን የአብረሃምን አምላክ በአብረሃም መንገድ ማምለክ ግዴታችን ነው፤ ልጅነቱን ወስደን በራሳችን መንገድ እግዚአብሄርን እናምልከው ማለት አይቻልም።
ትውልድ በየትኛውም ዘመን ሲጠራ ከእግዚአብሄር ዘንድ የሚወጣው እውቀት በማንነቱ ላይ አጽንኦት የሚሰጥ ነው፤ ይህም የሆነበት ምክኒያት እግዚአብሄር እርሱን የሚያውቅ ትውልድ እንዲኖር፣ እርሱ ብቻ አምላክ እንደሆነ እንዲያስተውል የሚመጡት ትውልዶችም በዚህ እውቀት ህይወታቸው እንዲቃኝና ንጹህ አምልኮ ወደ እርሱ እንዲቀርብ ነው።
‘’ይህን የሠራና ያደረገ፥ ትውልድንም ከጥንት የጠራ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር፥ ፊተኛው በኋላኞችም ዘንድ የምኖር እኔ ነኝ።’’ ብሎአልና።(ኢሳ. 41:4)
የሰውን ልጅ ከእግዚአብሄር ፍቅር ያለያየ ሰይጣን ማለያየት ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሄርን የማንነት እውቀት ከሰው ልብና ነፍስ ጠርጎ አስወግዶአል፤ ስለዚህ የትኛውም ሰው በየትኛውም ዘመን ይነሳ በልብ ቅንነትና መሻት እግዚአብሄርን ቢፈልግ እንኳን አፈላለጉ በጠራ ራእይና እውቀት ላይ ተመስርቶ አይሆንም፤ ሰይጣን እውቀቱን ስላረከሰ፣ እግዚአብሄር ማን መሆኑ ስላጠፋበት እውቀቱ ትልቅ ፈውስ የሚያስፈልገው ሆኖ ተገኝቶአል። ቀጥሎ ባለው ቃል ውስጥ እግዚአብሄር እርሱን የማወቅ ምስጢር ለምን መቅደም እንዳለበት ያሳስባል፦
‘’ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር፤ ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም። እኔ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም። ተናግሬአለሁ አድኜማለሁ አሳይቼማለሁ፥ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምላክ አልነበረም፤ ስለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እኔም አምላክ ነኝ። ከጥንት ጀምሮ እኔ ነኝ ከእጄም የሚያመልጥ የለም፤ እሠራለሁ፥ የሚከለክልስ ማን ነው?’’ ይላል።(ኢሳ. 43:10-13)
ማወቅ፣ ማመን፣ ማስተዋል፣ ምስክር መሆን ብሎ የሚያመለክተን መለኮታዊ ጥበብ በህይወታችን ውስጥ ከታተመ በመንፈሳዊ ህይወታችን እድገት ይፈጠራል፣ ወደ እግዚአብሄርም እንቀርባለን፤ እግዚአብሄርን መታዘዛችን ምስክሮቹ እስከመሆን የሚያደርስ ክብርን ያጎናጽፋል። እግዚአብሄር ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ሲል በአስተሳሰባቸውና በግብራቸው አምላክ የሚቀርጹና ከአብረሃም አምላክ በፊት አድርገውት በዚያ መንፈስ የሚያመልኩ አጥፊዎች ስላሉ ነው፤ ከእኔም በኋላ አይሆንም ሲል እግዚአብሄር ከተገለጠልህ በሁዋላ እንደ እግዚአብሄርነቱ መቀበልና ማምለክ ትተህ በራስህ አእምሮና ምኞት አዲስ ባህሪ ልትፈጥርለት ትሞክራለህን ብሎ ሲያስጠነቅቀን ነው። በመንፈሳችን ላይ የሚቀመጥ እግዚአብሄርን የማወቅ ጥበብ ሲመጣ ግን ብርሃን ሆኖ ማንነቱ በልባችን ይበራል። ስለዚህ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም። ተናግሬአለሁ አድኜማለሁ አሳይቼማለሁ፥ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምላክ አልነበረም፤ ስለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ የሚለው አባባል ፍንትው ብሎ ይታየናል።
ጨምሮ በኢሳ. 44:6-8 ሲናገር፦
‘’የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም። እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ይነሣና ይጥራ ይናገርም፤ ከጥንት የፈጠርሁትን ሕዝብ ያዘጋጅልኝ፥ የሚመጣውም ነገር ሳይደርስ ይንገሩኝ። አትፍሩ አትደንግጡም፤ ከጥንቱ ጀምሬ አልነገርኋችሁምን? ወይስ አላሳየኋችሁምን? እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። ከእኔ ሌላ አምላክ አለን? አምባ የለም፤ ማንንም አላውቅም።’’ ይላል።
ቆይ ምን ማለቱ ነው? አለም እንዳሻት አምላክን መቅረጽ ይቅርና በታያት መንገድ ልትጠራውም ልታመልከውም አትችልም ማለት አይደለምን? ታዲያ የሰው ልጅ ስለምን በራሱ መንገድ አምልኮን ይመርጣል?
‘’ያዕቆብ ሆይ፥ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ፤ እኔ ነኝ፤ እኔ ፊተኛው ነኝ እኔም ኋለኛው ነኝ። እጄም ምድርን መሥርታለች ቀኜም ሰማያትን ዘርግታለች፤ በጠራኋቸው ጊዜ በአንድነት ይቆማሉ።’’ (ኢሳ. 48:12-13)
‘’እኔን ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደ ሆነ፥ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም፥ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ። እኔ ራሴ አየዋለሁ፥ ዓይኖቼም ይመለከቱታል፥ ከእኔም ሌላ አይደለም። ልቤ በመናፈቅ ዝሎአል።’’ (ኢዮ. 19:25-27)