ያለመታዘዝ ጠንቅ

ቤተክርስቲያን

ታዝዘው የቀረቡና የተጠጉ ልባቸው ከእምነት በዛለ ጊዜ ያለመታዘዝ እንደሚያሸንፋቸው ቃሉ ያስተምራል፡፡ታዝዘው ወደ ምድረ-በዳ የወጡት እስራኤላውያን ባልታዘዙ ወቅት በነበሩበት ምድረ-በዳ አልቀዋል፡፡ድምጹን እየሰሙ ለድምጹ ተግባራዊ ምላሽ የማይሰጡ በህይወት ላይ በሚፈጠር ጠንቅ ይጠቃሉ፡፡እግዚአብሄር በባሪያው በኢያሱ እጅ ምሪትን ብቻ ሳይሆን እረፍትን ሊሰጣቸው እቅድ ነበረው፡፡እስራኤላውያን ግን ባለመታዘዛቸው የታሰበላቸውን ሊያገኙ አልቻሉም፡፡
ዕብ.4:6-9 ”እንግዲህ አንዳንዶች በዚያ እንዲገቡ ስለ ቀሩ፥ ቀድሞም የምስራች የተሰበከላቸው ባለመታዘዝ ጠንቅ ስላልገቡ፡-
ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ በፊት እንደ ተባለ፥ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ በዳዊት ሲናገር፡- ዛሬ ብሎ አንድ ቀን እንደ ገና ይቀጥራል።”
አለመታዘዝ እምቢተኝነት ነው፣ ፈቃድን መከልከል ነው፣ ልብን መዝጋት ነው፡፡ባለመታዘዝ እልከኝነት ይገለጣል፣ በአለመታዘዝ ምክኒያት ከአዛዥ ጋር መጣላት ይከሰታል፡፡ የአዛዥን ፈቃድ መጣስ ያዘዘው ክፍል ያወጣውን የቅጣት አዋጅ ተፈጻሚ እንደሚያስደርግ ግልጽ ነው፡፡በቃሉ የተናገረን እግዚአብሄር ነው፤ ድምጹን ከሰማን በሁዋላ ለድምጹ መልስ መንፈግም ሆነ ድምጹ ላይ ማመጽ ጥፋቱ እኩል ነው፡፡
አንዳንድ ለወንጌል ታዘው የነበሩ አማኞች መሃል መንገድ ላይ መታዘዛቸውን ወደ አለመታዘዝ ይቀይራሉ፡፡ እግዚአብሄር ልጆች ብሎ የጠራቸው አለመታዘዝ ላይ እንደወደቁ ቃሉ ያመለክታል፡፡ ያለመታዘዝ ጠንቅ በእምቢተኝነትና በእልከኝነት ምክኒያት የሚከተለውን ክፉ ነገር የሚያመለክት ነው፡፡ጠንቅ ክፉ ውጤት አለው፡፡
1ጴጥ.4:17 ”ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፤ አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን?” ሲል የእግዚአብሄርን ቤት የሚጎበኝ ፍርድ ባለመታዘዝ ጠንቅ የሚፈጠር ስለመሆኑ ያስረዳል፡፡
ለእግዚአብሄር መታዘዝ ግን ለእርሱ መገዛት፣ በፊቱ መንበርከክና መስገድ ነው፡፡
መዝ.95:6-7 ”ኑ፥ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ፤ በእርሱ ባደረገን በእግዚአብሔር ፊት እንበርከክ፤ እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና።”
የመታዘዝ ብድራት አለ፡-
የመታዘዝ ብድራት የዘላለም መዳን ያመጣል፡፡
ዕብ.5:9-10 ”ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው።”
1ጴጥ.1:1-2 ”የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ጴጥሮስ፥ እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው በመንፈስም እንደሚቀደሱ፥ ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ ለተመረጡት በጳንጦስና በገላትያ በቀጰዶቅያም በእስያም በቢታንያም ለተበተኑ መጻተኞች፤ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።”
እግዚአብሄርና በመታዘዝ ላይ ያስቀመጠው ዋጋ፡-
ኢሳ.1:19-20 ”እሺ ብትሉ ለእኔም ብትታዘዙ፥ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እምቢ ብትሉ ግን ብታምፁም፥ ሰይፍ ይበላችኋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።”
ሐዋ.5:32 ”እኛም ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፥ ደግሞም እግዚአብሔር ለሚታዘዙት የሰጠው መንፈስ ቅዱስ ምስክር ነው።”
ያለመታዘዝ ጠንቅ ከመንገድ ያስቀራል፡-
ዕብ.4:6-8 ”እንግዲህ አንዳንዶች በዚያ እንዲገቡ ስለ ቀሩ፥ ቀድሞም የምስራች የተሰበከላቸው ባለመታዘዝ ጠንቅ ስላልገቡ።ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ በፊት እንደ ተባለ፥ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ በዳዊት ሲናገር። ዛሬ ብሎ አንድ ቀን እንደ ገና ይቀጥራል።ኢያሱ አሳርፎአቸው ኖሮ ቢሆንስ፥ ከዚያ በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር።”
ዕብ.3:18-19 ”ካልታዘዙትም በቀር ወደ እረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ?ባለማመናቸውም ጠንቅ ሊገቡ እንዳልተቻላቸው እናያለን።”
የሰው ልብ ለመታዘዝ ይከብዳል ተፈጥሮ ግን ትታዘዛለች፡-
ማቴ.8:27-28 ሰዎቹም፡- ነፋሳትና ባሕርስ ስንኳ የሚታዘዙለት፥ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው? እያሉ ተደነቁ። ወደ ማዶም ወደ ጌርጋሴኖን አገር በመጣ ጊዜ፥ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከመቃብር ወጥተው ተገናኙት፤ እነርሱም ሰው በዚያ መንገድ ማለፍ እስኪሳነው ድረስ እጅግ ክፉዎች ነበሩ።
የአማኝ ያለመታዘዝ እውነት እንዲሰደብ ያደርጋል፡-
2ጴጥ.2:2-4 ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሉአቸዋል በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል።ገንዘብንም በመመኘት በተፈጠረ ነገር ይረቡባችኋል፤ ፍርዳቸውም ከጥንት ጀምሮ አይዘገይም ጥፋታቸውም አያንቀላፋም።እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ ከሰጣቸው፥
ያለመታዘዝ እንቢኝነትና አመጸኝነት ነው፡፡እንቢተኝነት ትእቢት በልብ ሲሞላ ይከሰታል፡፡መታዘዝ እሺታና ማድረግ ሰሆን በአንደበት የሚነገር ቃል ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ እንቅስቃሴን የሚጠይቅ ነው፡፡
የክርስቲያን ያለመታዘዝ መዘዝ ያስከትላል፡-
ዕብ.2:2 ”በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ፥ መተላለፍና አለመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ፥ እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው፥ እንዴት እናመልጣለን?”
ያለመታዘዝ ጠንቅ ባልታዘዝንበት ሰአት ሊያጠፋን ይችላል፣ ወይም ከተወሰነ ጊዜ በሁዋላ ሊመጣ ይችላል፣ ወይ ደግሞ ከቀናት በሁዋላ፣ ከአመታት በሁዋላ ያልያም በእድሜ ፍጻሜያችን ላይ ጥፋት ሊያስከትል ይችላል፡፡ልንሞት ስንል እንዴት ያጠፋናል ? ብንል ነገሩን እንዲህ እንየው፡-በህይወት ዘመናችን ምንም እንኩዋን ሰንካላ ህይወት የመራን ቢሆንም በእግዚአብሄር ላይ በኩራት ልባችንን አላነሳንምና ከመሰብሰባችን አስቀድሞ እግዚአብሄር የንሰሀ በር ይከፍትልናል፡፡በዚያ ውስጥ አሳልፎም ለመንግስቱ ይጠብቀናል፡፡
የእስራኤላውያን አለመታዘዝ ጥፋት አምጥቶባቸዋል፡-
ሮሜ.10:16-18 ”ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ፦ ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአልና።እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።ዳሩ ግን፦ ባይሰሙ ነው ወይ? እላለሁ። በእውነት፦“ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ።”
ሮሜ.11:31-32 ”እንዲሁ በተማራችሁበት ምሕረት እነርሱ ደግሞ ምሕረትን ያገኙ ዘንድ እነዚህ ደግሞ አሁን አልታዘዙም።እግዚአብሔር ሁሉን ይምር ዘንድ ሁሉን በአለመታዘዝ ዘግቶታልና።”
የአለም ህዝብ አለመታዘዝ ችግር የዘላለም ጥፋት የሚያመጣ ነው (ቀድሞ ግኡዙ አለም በውሀ እንዲጠፋ አድርጎአል፣ በመጨረሻው ዘመንም ከመንፈሳዊው አለም የመጥፋት ፍርድ ውስጥ የሚከተው አለመታዘዝ ነው)፡፡
1ጴጥ.3:20-22 ”ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፥ የእግዚአብሔር ትዕግሥት በኖኅ ዘመን በቈየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም።ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቅት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፥ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፥ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፥ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፤እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ።”
በወንጌል ጉልበት አለመታዘዝ ይረታል፡-
2ቆሮ.10:5 ”የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥”
ሉቃ1:17 ”እርሱም የተዘጋጁትን ሕዝብ ለጌታ እንዲያሰናዳ፥ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች የማይታዘዙትንም ወደ ጻድቃን ጥበብ ይመልስ ዘንድ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።”
ሐዋ.6:7 ”የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፥ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቍጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ።”
አንዳንድ የመጨረሻው ዘመን አማኞች ገጽታ፡-
ሮሜ.1:30-32 ”ሐሜተኞች፥ አምላክን የሚጠሉ፥ የሚያንገላቱ፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክህተኞች፥ ክፋትን የሚፈላለጉ፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥የማያስተውሉ፥ ውል የሚያፈርሱ፥ ፍቅር የሌላቸው፥ ምሕረት ያጡ ናቸው፤እንደነዚህ ለሚያደርጉት ሞት ይገባቸዋል የሚለውን የእግዚአብሔርን ሕግ እያወቁ እነዚህን ከሚያደርጉ ጋር ይስማማሉ እንጂ አድራጊዎች ብቻ አይደሉም።”
ሮሜ.2:8-10 ”ለዓመፃ በሚታዘዙ እንጂ ለእውነት በማይታዘዙትና በአድመኞች ላይ ግን ቍጣና መቅሠፍት ይሆንባቸዋል።ክፉውን በሚያደርግ ሰው ነፍስ ሁሉ መከራና ጭንቀት ይሆንበታል፥ አስቀድሞ በአይሁዳዊ ደግሞም በግሪክ ሰው፤ነገር ግን በጎ ሥራ ለሚያደርጉ ሁሉ ምስጋናና ክብር ሰላምም ይሆንላቸዋል፥ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው።”
ቆላ.3:5-7 ”እንግዲህ በምድር ያሉቱን ብልቶቻችሁን ግደሉ፥ እነዚህም ዝሙትና ርኵሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣኦትንም ማምለክ የሆነ መጎምጀት ነው።በእነዚህም ጠንቅ የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ ይመጣል።እናንተም ደግሞ ትኖሩባቸው በነበራችሁ ጊዜ፥ በፊት በእነዚህ ተመላለሳችሁ።”
ኤፌ4:18-20 ”እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ፥ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ፤ደንዝዘውም በመመኘት ርኵሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ።እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፤”
የአመጽ አለቃ አለ፡-
ኤፌ2:1-8 ”በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው።በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን።ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥ ከዚህ የተነሣ በማይታዘዙት ልጆች ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ይመጣልና ማንም በከንቱ ንግግር አያታልላችሁ።እንግዲህ ከእነርሱ ጋር ተካፋዮች አትሁኑ፤ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤”
የአመጽ አለቃ ተጽእኖ በተለያ መንገድ ይገለጣል፡-
የአማኝ አለመታዘዝ ሲፈጥር – የነፍስ ክሳት ይሆናል
የአህዛብ አለመታዘዝም ከመዳን አርቆአቸዋል
የነገስታት አለመታዘዝ (እንደ ሳኦል) ጥፋት አስከትሎአል – ሳኦል ባለመታዘዙ ንግስናውን አጥቶአል፣ እስራኤልን ከጠላት እጅ አስገብቶአል
እስራኤላውያን አልታዘዙም ነበርና – ባለመታዘዛቸው ለጠላት ተላልፈው 70 አመት ከምድራቸው ተነቅለዋል
በአዲስ ኪዳን ዘመንም አይሁድ ባለመታዘዛቸው ዳግም ከሀገራቸው ተነቀለው ነበር፡፡
ዛሬም ያለመታዘዝ ጠንቅ የሚገልጥበት መንገድ ሰፊና ጥልቅ እንደመሆኑ በመታዘዝ ብቻ ጠንቁን ወደ ምህረት ማስቀየር እንደሚቻል በትህትና ማስተዋል ይሻላል፣ነገሮች ሲደርሱ ጥፋታቸው በሰበብ የሚታለፍ አይደለምና፡፡