የፍቅር ግዛቶች[3..]

የእውነት እውቀት

”ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል። እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል።” (1ዮሐ.4:10-12)
ፍቅርን ስናስብ የማንነቱ ነገር/ እርሱ ማን መሆኑን እንድናስብ ያደርጋል፣ አልፎም በባህሪው በኩል እንድንመለከተው አቅጣጫ ይጠቁማል፡፡ ሰዎች ስለፍቅር ለማወቅ በጉጉት እንመረምራለን፣ ምክኒያቱም ፍቅር ለሰዎች የተሰጠና ከፍ ያለ፣ ክብር ያለውና ውስጣዊ ሃይል ስለሆነ፡፡ ስለዚህ እንደማሰባችንና ለማወቅ እንደመጉዋጉዋታችን ከዚህ ቀደም በሰማናቸው ትርጉዋሜዎች የራሳችን ድምዳሜ ላይ ደርሰን ሊሆን ቢችልም ካወቅነው ትርጉዋሜ በተለየ እግዚአብሄር የተናገረውን እርሱ በሚያበራው እውቀት በኩል ስንረዳ እርሱ ያ ነው ወይ ይሄ ነው ማለት እናቆማለን፣ እንደ አዲስ የፍቅር ተማሪም እንሆናለን፤ እውቀቱ ከግምታዊነት ይልቅ እግዚእብሄርን በቃሉ ስለሚገልጥልን፣ ፍቅር እንደዚህ ነው ያለውን (በክርስቶስ የሰጠውን የፍቅር ስጦታ ምንነት) እንድንረዳውም ስለሚያደርግልን፡፡
ይህ የተባለው የእግዚአብሄር ፍቅር እግዚአብሄር ራሱ በሰው ልጆች መሃል በሰውነት እንዲገለጥ ያደረገ፣ በስጋው በኩል የሀጢያት ስርየትን ለሰዎች ያመጣው ተጨባጭ ፍቅር ነው፡፡ ፍቅሩ ልዩና በሌሎች ዘንድ ሊገኝ የማይችል ነው፡፡
ፍቅሩ ከላይ ከሰማይ ሲጀምርና በምድር በሰው ልጆች ህይወት ውስጥ ሲፈስስ (ሰማያዊውና ከመለኮት የሚመነጨው ፍቅር ብቻ ፍጹም ፍቅር እንደመሆኑ) ለተቀባዩ ትልቅ ነገር ይሆናል፣ የተጨበጠ ለውጥም በህይወቱ ይመጣል፣ መለኮታዊ ባህሪ ተካፋይነት ይቀበላልም፡፡ ሰዎች ይህን አውቀው ፍቅሩን ሲመርጡ፣ ሲቀደሱና ሲለምኑ ከርሱ ዘንድ በመንፈሱ መሻታቸው ይሞላል፣ መፍትሄ ይሆንላቸዋል፡፡ በጥላቻና በቅንአት ተሞልቶ ክርስቲያኖችን ያሰቃየ ነፍሰ ገዳይ ጳውሎስ በፍቅር ሲማረክ ለወደደው ጌታ እጁን አንስቶአል፣ ስለርሱ በብዙ ተቸግሮአል፣ መስክሮአል፣ ስለፍቅሩ ሲልም ተሰውቶአል፡፡ ሃዋርያው ያን የተማረከበትን ሀይል በሮሜ.5:5 ውስጥ እንዲህ ይለዋል፡-
”በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም።”
ከላይ የጀመረው ፍቅር ወዴት አቅጣጫ ያመለክታል? ሰው መስጠት ያለበትን ፍቅር ቅድሚያ ለእግዚአብሄር እንዲያደርግ፣ በማስከተል ከርሱ ዘንድ ለሚገኘው ጎረቤቱ መውደዱን በተግባር ሊገልጥ እንዲገባ ይህን ያመለክታል፡፡
ዘሌ.19:17-18 ”ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ በባልንጀራህ ምክንያት ኃጢአት እንዳይሆንብህ ገሥጸው። አትበቀልም፥ በሕዝብህም ልጆች ቂም አትያዝ፥ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”
በመንፈስ ቅዱስ መፍሰስ ምክኒያት የምንቀበለው የእግዚአብሄር ፍቅር ስጦታ እንጂ እኛ የምንፈጥረው ነገር ከቶ አይደለም፡፡ ይህ ከመለኮት የወረደ ፍቅር ግን በእኛ እንዲሰራ አደራ አለን፣ ያንም አጥብቀን ልንኖረው እንዲገባ ማስተዋል አለብን፡- እግዚአብሄርን ቅድሚያ እንወድድ ዘንድ፣ በማስከተልም እራሳችንንና ባልንጀራችንን በእኩል ለመውደድ ስፍራ እንድንሰጥ፣ ይሄን ተግባርም ቸል እንዳንል፤ በዚህ ሁሉ ደግሞ እግዚአብሄር አጥብቆ እንደሚያሳስበን ማስተዋል አለብን፡፡
ይህ የተገለጠ የፍቅር ተዋረድ እንደ እግዚአብሄር ቃል ይጠበቅ ዘንድ ተደጋግሞ ተገልጾአል፡፡ ስለዚህ ቅድሚያ ራስን ወይም ባልንጀራን በመውደድና እግዚአብሄርን ሁዋለኛ አድርጎ በማስከተል በአንደበት ብቻ እወድዳለሁ ማለት ዋጋ የለውም፣ በዚህ አካሄድ መለኮታዊ ፍቅርን ማግኘት ማንም ስለማይችል እንዲህ ያለ ከቃሉ የወጣን ልምምድ ሆነ ስርአት መተውና በጌታም ዘንድ ያ እንደማይጸና ማወቅ ይገባል፡፡ እርሱ ራሱ በሉቃ14:26 ላይ ሲናገር፡-
”ማንም ወደ እኔ የሚመጣ ቢኖር አባቱንና እናቱን ሚስቱንም ልጆቹንም ወንድሞቹንም እኅቶቹንም የራሱን ሕይወት ስንኳ ሳይቀር ባይጠላ፥ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።” ብሎአል፡፡
እንዲሁ በማቴ10:37 ውስጥ ሲያስጠነቅቅ ”ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም” ብሎአል፡፡
ከዚህ ጋር አያይዘን የርሱን መለኮታዊ ፍቅር እናውቅ ዘንድ እግዚአብሄርን እንዴት እንወቀው/እንቅረብ ብለን ብንጠይቅ ክፉ አይሆንም፡፡ እግዚአብሄር ፍቅር ወይስ ፍቅር እግዚአብሄር ነው እንበል? በብዙዎች መሀል ቃሉ በተለዋዋጭነት እየተነገረ ቢሆንም በሁለቱ አባባል መሃል ልዩነት ስላለ እንዳያሳስተን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ቃሉ ደጋግሞ እንደሚያረጋግጠው እግዚአብሄር ፍቅር ነው፡፡ ምክኒያቱም ፍቅር በእግዚአብሄር ውስጥ ስላለ፣ ከባህሪዎቹ መሃል አንደኛው ስለሆነ፣ ከርሱ ፍቅር የተነሳ በሰው ውስጥ ፍቅር የሚፈጥርም ስለሆነ አባባሉን እርግጠኛ ያደርገዋል፡፡
1ዮሐ.4:7-21 ”ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ። ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና። በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል። እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል። ከመንፈሱ ስለ ሰጠን፥ በእርሱ እንድንኖር እርሱም በእኛ እንዲኖር በዚህ እናውቃለን። እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን እንደ ላከው እንመሰክራለን። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል። እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል።በፍርድ ቀን ድፍረት ይሆንልን ዘንድ ፍቅር በዚህ ከእኛ ጋር ተፈጽሞአል፤ እርሱ እንዳለ እኛ ደግሞ እንዲሁ በዚህ ዓለም ነንና። ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም፥ ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም። እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን። ማንም፡- እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?”
ፍቅር ከእግዚአብሔር ነው፣ እግዚአብሔርም ፍቅር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፣ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው ግን ከቶ አይደለም!
እግዚአብሄር ፍቅር ይሁን፣ ፍቅር ግን እግዚአብሄር እንዴት ይሆናል? ፍቅርስ እግዚአብሄር ከሆነ የቀሩት የእግዚአብሄር መለኮታዊ ባህሪዎች ምን ይሆናሉ? ለምሳሌ እርሱ ፍቅር እንደሆነው ሁሉ የሚበላ እሳትም ነው፡፡ እንዲሁ ከምንም ነገር አስቀድሞ/ ከመጀመሪያው ያለው እግዚአብሄር ብቻ እስከሆነ ድረስ ከእግዚአብሄር የሆነ ፍቅር ከእርሱ በፊት ሊሆን እንዴት ይችላል? ባህሪው ከባለቤቱ ሊቀድም አይችልምና፡፡ እግዚአብሄር በፍቅር ውስጥ ተጠቅልሎ አይቀመጥም፣ እግዚአብሄር ከፍቅር ውስጥም አይፈልቅም፣ ፍቅር ከእግዚአብሄር እንጂ፡፡ ስለዚህ ፍቅር የእግዚአብሄር ባህሪ ከሆነ በተገላቢጦሽ እግዚአብሄር የፍቅር አንደኛው ባህሪይ ሊሆን አይችልም፡፡ እግዚአብሄር ሁሉን አስገኚ ከሆነ ፍቅር የሁሉ አስገኚ መሆን አይችልም፡፡
እግዚአብሄር ግን በእርግጥ ፍቅር ነው፣ ያ ስለሆነ ሲወድ በፍጹም ነው፤ ሲምር፣ ሲታገስ፣ ሲራራ፣ ሲሰጥም በለጋስነት ነው፡፡ ገና በጠዋት ከለጋነታችን ጀምሮ፣ ስለ እርሱ ብዙም በማናውቅበት ዘመን በፍቅሩ የመራንና ያሳደገን እርሱ ነው፤ በዚያ ዘመን ውስጥ (በረጅም ጉዞ ውስጥ) አልፈን ወደ ማስተዋል እንድንደርስ ስንቴ አግዞናል መርቶናልም፡፡ በልጅነት ወራት/ባላስተዋልንባቸው ዘመናት የሰራናቸውን በደሎች፣ መተላለፎችና ሀጢያቶች በብዙ ምህረት እየከደነ በትእግስት ሲከታተለን ነበር፣ ሊያድነን፣ ሊያሻግረንና ወደ ማስተዋል ሊያደርሰን በፍቅሩ ሲምረን ነበር፡፡ ስለዚህ ነገር ሲናገር እንዲህ ይላል፡-
”እስራኤል ሕፃን በነበረ ጊዜ ወደድሁት፥ ልጄንም ከግብጽ ጠራሁት። አብዝቼ ብጠራቸው አጥብቀው ከፊቴ ራቁ፤ ለበኣሊምም ይሠዉ ነበር፥ ለተቀረጹ ምስሎችም ያጥኑ ነበር። እኔም ኤፍሬምን ክንዱን ይዤ በእግሩ እንዲሄድ መራሁት፤ እኔም እፈውሳቸው እንደ ነበርሁ አላወቁም። በሰው ገመድ በፍቅርም እስራት ሳብኋቸው፤ ለእነርሱም ቀምበርን ከጫንቃቸው ላይ እንደሚያነሣ ሆንሁ፥ ድርቆሽም ጣልሁላቸው።” (ሆሴ.11:1-4)
የእግዚአብሄርን አሰራር ከቃሉ ስናስተውል እንዴት ባለ የፍቅር ስበት ሊስበን እንደወደደ እንረዳለን፡፡ በእድገታችንም ውስጥ ሲከታተለን፣ በፍቅሩ ሲያሳድገንና የትእግስቱን ብዛት ሲያሳየን ሌላ ሳይሆን በህጻንነት ወራት ውስጥ እየዳከርን በዚያው እንዳንቀር ወይም ያለ ለውጥ እድሜ ዘመናችንን እንዳንፈጅ ወደ እድገት ሊመራን ነው፤ ከዳዴ ህይወት በቶሎ ወጥተን በማደግ በእግራችን እንራመድ ዘንድና ወተት ከመመገብ ወጥተን ጠንካራ ምግብ መመገብ እንድንችልም ነው፡፡
እግዚአብሄር ፍቅር ነው የሚለውን በቃሉ ልናውቅ ከቻልን እግዚአብሄር ለእኛ ያለውን ፍቅርስ በምን መንገድ ገለጠው እንበል?
ይህን እንድናስተውል የሚያግዝ ቃል በሮሜ.5:5-10 ውስጥ ይገኛል፣ ስለ ተገለጠው የእግዚአብሄር ፍቅርም ሲናገር፡- ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ መሞቱ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል ይላል።
የክርስቶስ ሞትና የእግዚአብሄር የውስጡ ፍቅር የሚገናኙበት መንገድ አለ፤ ክርስቶስ ከእግዚአብሄር የወጣ መሆኑን ካየን፤ እግዚአብሄር የወለደው ብቸኛ ልጅ እርሱ ብቻ መሆኑም ከተገለጠልን (ከእግዚአብሄር የወጣው ቃል ስጋ በመሆኑ)፤ የክብሩም መገለጫ እርሱ መሆኑና እግዚአብሄር ሙላቱ ሁሉ ለአለም የሚገለጠው በክርስቶስ ሰውነት ብቻ መሆኑ ከበራልን ፍቅሩ ተገለጠልን ማለት አይደል? ሰማያዊውን የክብር ቦታ የተወ ክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ለሀጢያተኞች ሞገስና ክብር ሊሆን መሞቱ የእግዚአብሄርን ክብር የሚያዋርድ ቢመስልም የፍቅሩን ጥልቅነት ገላጭ ነው፡፡ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ መሞት እርግማን ነው፣ ያም ቢሆን ግን ስለተረገሙ ሰዎች ሲል ጻድቁ ጌታ ወደዚያ ስፍራ ድረስ መውረዱ ጥልቅ የእግዚአብሄር ፍቅር በክርስቶስ መገለጡን የሚያሳይ ነው፡፡ እንግዲያውስ ከተገለጠው የክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? ይህን የተገለጠ ፍቅር በመስበካችን የሆነብን መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ከርሱ የሚለየን ነውን? ሲል ሃዋርያው ጳውሎስ በመደነቅ ይጠይቃል፡፡ የእርሱ ፍቅር ወደ ውስጣችን እስከፈሰሰ ድረስ እርስ በርሳችን ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ እንዳይኖርብን የሚል ሃዋርያዊ ምክርም ቀርቦልናል፤ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞታልና። አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በውሸት አትመስክር፥ አትመኝ የሚለው ከሌላይቱ ትእዛዝ ሁሉ ጋር በዚህ፦ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ በሚለው ቃል ተጠቅልሎአል። ፍቅር ለባልንጀራው ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።
ይህ የእግዚአብሄር ፍቅር በሁኔታዎች መለዋወጥ አይቀየርም፣ ጊዜ አይበግረውም፣ ችግርም አያናውጠውም፡፡ በእግዚአብሄር ፍቅር የተያዙ ደግሞ በዚያ ህይወት አልፈዋል/ያልፋሉም፡፡
ጌታ ኢየሱስ በዮሐ.15:10-15 ላይ ሲናገር ”እኔ የአባቴን ትእዛዝ እንደ ጠበቅሁ በፍቅሩም እንደምኖር፥ ትእዛዜን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ። ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን ነግሬአችኋለሁ። እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት። ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም። እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ።” ብሎአል፡፡
ስለዚህ ደቀመዛሙርት በግላችን ለእያንዳንዳችን የተሰጠ እዳ ባልንጀራን እንደራስ አድርጎ መውደድ መሆኑን ልብ እንበል፡፡ እዳ የተባለበትም ምክኒያት የሚያስከፍል ነገር ስላለው ነው፡፡ እዳ አያሳርፍም፣ የባልንጀራ ፍቅርም እንደሚከፈል የሰው እዳ ሸክም ሆኖ ለሌላው መጨነቅን፣ ማብሰልሰልን፣ መራራትን፣ ምን ላድርግለት በሚል ማሰብን ያመጣል፣ አእምሮን እረፍት ይነሳል፣ ዝም አያሰኝም፣ ስስትም አያውቅም፡፡ ባለ እዳ ለአበደረው ክብርን እንደሚሰጥ ባልንጀራን በትህትናና በማክበር እንድንመለከተው ፍቅር ያስገድዳል፡፡ በመውደድ ውስጥ ውለታን መቁጠርም ሆነ ሰጥቶ መቀበል መርህን መጠበቅ አይቻልም፡፡
1ዮሐ.4:10-12 ”ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል። እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል።”
ፍቅር ሀይል ስላለው ሰው በእውነትና በመንፈስ እግዚአብሄርን እንዲወድና እንዲታዘዝ ያስገድደዋል፣ ቃሉን በእግዚአብሄር ፍርሀት እንዲወድና የነገረውን ትእዛዝ ሳያሰላ እንዲቀበል ያደርገዋል፡፡ በፍቅሩ የተያዘ ሰው ቁጣውንም ሆነ ቅጣቱን ሳያጉረመርም አሜን ይላል፡፡ የወደደው ሰው ለእግዚአብሄር ያለውን ፍቅር እንደዚያ ይገልጻል፡፡
1ዮሐ.4:7-13 ”ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ። ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና። በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል።እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል።”
ባልንጀራውን የማይወድ ቢኖር እርሱ የእግዚአብሄርን ፍቅር ማወቅ አይችልም፡፡ ምክኒያቱም እግዚአብሄር የመጨረሻ የተባለ መስዋእትን ለአለም የከፈለው ይህን ፍቅሩን ለመስጠት ስለሆነ ነው፡፡ ትንሹን የባልንጀራ የፍቅር ዋጋ የማያውቅ ሰው እንዴት የእግዚአብሄርን ታላቅ ክፍያ ያከብራል፣ ያውቃልስ? እግዚአብሄር ክርስቶስ ሰው እንዲሆነ (የባሪያን መልክ እንዲይዝ) ከውስጡ ባወጣው ቃል ስጋና ደም አድርጎ አዘጋጅቶት ነው፣ ሲያዘጋጀውም እጅግ ለከበረ አላማ ነው፡- እግዚአብሄር በአለም ላይ በልጁ እጅ ሊፈርድ፣ በእርሱ አካል ውስጥ አድሮ በዙፋን ላይ ሊቀመጥና ሊነግስ፣ የክብሩን ነጸብራቅ በርሱ ሰውነት ላይ አድርጎ እግዚአብሄር በርሱ ሊታይ… ነው፡፡ ግን ያን መለኮታዊ እቅድ ያቀደ አምላክ ስለ ሰዎች መዳን ሲል ሰውነቱን አዋረደ፣ ለመስቀል ሞት አሳልፎም ሰጠው፡፡ ከሞት በሁዋላ ግን ትንሳኤ ሊሰጠው፣ ክብርን ሊያጎናጽፈው፣ ለሰዎችም ሁሉ መድሃኒት አድርጎ ሊያቆመው ያን በፍቅር አንዴ አድርጎአል፡፡
ፊል2:1-9 ”በክርስቶስም አንዳች ምክር ቢሆን፥ የፍቅር መጽናናት ቢሆን፥ የመንፈስ ኅብረት ቢሆን፥ ምሕረትና ርኅራኄ ቢሆኑ፥ ደስታዬን ፈጽሙልኝ፤ በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ። በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ። በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው”
እግዚአብሔር ልጁን ያለ ልክ ከፍ ከፍ ከማድረጉ በፊት ስለእያንዳንዳችን ሲልና ስለራሱ ፍቅር ሲል ዝቅ አደረገው፤ የሀጢያት ባርያ እንደሆነው እንደ አዳም በመስቀል ላይ ይሞት ዘንድ ለሀጢያተኞች አሳልፎ ሰጠው፣ ይህም የእግዚአብሄር ፍቅር ዋጋ ነው፡፡
1ቆሮ.8:1-4 ”ለጣዖት ስለ ተሠዋ ሥጋም፥ ሁላችን እውቀት እንዳለን እናውቃለን። እውቀት ያስታብያል ፍቅር ግን ያንጻል።ማንም አንዳች የሚያውቅ ቢመስለው ሊያውቅ እንደሚገባው ገና አላወቀም፤ማንም ግን እግዚአብሔርን ቢወድ እርሱ በእርሱ ዘንድ የታወቀ ነው። እንግዲህ ለጣዖት የተሠዋውን ሥጋ ስለ መብላት፥ ጣዖት ሁሉ በዓለም ከንቱ እንደ ሆነ ከአንዱም በቀር ማንም አምላክ እንደሌለ እናውቃለን።”
ከእግዚአብሄር የተቀበልነውን ውድ የፍቅር ዋጋ የምናስተውል ካለን ልንረሳው የማይገባውን ትእዛዝ ጨምረን እንወቅ፣ እርሱም፡- አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ የሚል ነው፡፡
ማስተዋል የሌለበት እውቀት ቢኖር እርሱ አስቶ ያስታብያል፣ አክብረን የምንይዘው ፍቅር ካለ ግን ያንጸናል፡፡ ሆኖም ሁለቱም በተለያየ አቅጣጫ ላይ እንዳሉ ሆነው በባህሪያቸው ማሳደግ እንደሚችሉ ማየት እንችላለን፤ በህይወታችን ውስጥ ሲገቡ ያለጥርጥር ተጽእኖ ያደርጋሉና፡፡ አንዱ ሲያስታብይ ሌላው የማነጹ ምስጢር ደግሞ በህይወታችን ውስጥ ተጽእኖአቸው ከፍተኛ መሆኑን ያመለክታል፡፡ የሚያስታብይ ነገር ስሜት የሚያሳብጥ ነው፣ በአየር እንደሚነፋ አረፋ በውስጥ ባዶ አድርጎ በእይታ የሚያገዝፍ ነው፡፡ ማነጽ ግን እንደ ህንጻ ውስጥንም ውጪንም በሁሉ ነገር የሚገነባ ነው፡፡ ክርስቲያን በሁሉም አቅጣጫ እንደ ህንጻ እያደገ እንዲታነጽ እንጂ በመንፈሳዊ ህይወቱ በሽንገላ ባዶ ሆኖ ሊኮፈስ አልተጠራም፡፡ ትክክለኛው የደቀመዝሙር እድገት እንዲህ እንደ ህንጻው በፍቅር ሆኖ የሚገለጥ በመሆኑ ያን የእድገት ህይወትና መርህ የሚከተል ውጤታማ ነው፡፡