የፍቅር ግዛቶች [7..]

የእውነት እውቀት

ፍቅር ጥልቅና ሰፊ መለኮታዊ ባህሪ ያለው ነገር ነው። ሰው ስለፍቅር ያለው ግንዛቤና ትርጉዋሜ በእርግጥ ወደ ስጋዊነት የሚያጋድልና ይበልጥ ሰዋዊ ነው። ወደ ስጋዊነት የሚያደላ እንደመሆኑ በአብዛኛው መገለጫው የሚሆነው ስሜት ሲሆን ሰዋዊ እንደመሆኑ የፍቅር ግንኙነቱ የሚያጋድለው በሰውና በሰው መሀከል ነው ማለት ነው። እርግጥ ነው ፍቅር በሰው መሃል ይኖር ዘንድ የፈቀደው የፈጠረን አምላክ ነው። ነገር ግን በሰው መሃል ከሚፈጠር ግንኙንት በላይ የእግዚአብሄር ፈቃድ ያለበት በሰውና በፈጣሪ መሃል የሚገኝ ፍቅር አለ።
እግዚአብሄር በእርሱና በሰው መሃል ላለው የፍቅር ግንኙነት ቅድሚያ እንድንሰጥ በህግ ጭምር ያስትወቀው ነገር ነው፤ ሰው እርስ በርሱ ይዋደድ ዘንድ ቀጥሎ የሚመጣ መለኮታዊ ተእዛዝ ነው፦
ማቴ.22:34-40 ”ፈሪሳውያንም ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው በሰሙ ጊዜ አብረው ተሰበሰቡ። ከእነርሱም አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው፡- መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፡- ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ።ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም፡- ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል። ”
ጌታ ኢየሱስ ጴጥሮስን ደጋግሞ ትወደኛለህ ብሎ ጠይቆት ነበር፤ ጴጥሮስም አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ያኔ ጌታ ኢየሱስ፡- በጎቼን አሰማራ አለው። ቀጥሎ የነገረው ደግሞ ስለፍቅሩ ሊከፍል ያለውን አመልካች ነበር፡-
”እውነት እውነት እልሃለሁ፥ አንተ ጐልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፥ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል አለው። በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ። ይህንም ብሎ፡- ተከተለኝ አለው። ጴጥሮስም ዘወር ብሎ ኢየሱስ ይወደው የነበረውን ደቀ መዝሙር ሲከተለው አየ፤ እርሱም ደግሞ በእራት ጊዜ በደረቱ ተጠግቶ፡- ጌታ ሆይ፥ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው? ያለው ነበረ። ጴጥሮስም ይህን አይቶ ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ ይህስ እንዴት ይሆናል? አለው። ኢየሱስም፡- እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ብወድስ፥ ምን አግዶህ? አንተ ተከተለኝ አለው።”(ዮሐ.21:18-22)
እንግዲህ ጴጥሮስ እንዲያስተውለው ያስፈልገውን ስለ ፍቅር የሆነውን ነገር ተረድቶ እንደሆን እንዴት ያመነውን ጌታ ስለፍቅር እንደሚከተለው፣ እንዴትስ እንደሚያመልከው፣ እንደሚያገለግለውና በህይወቱ እንዴት እንደሚያከብረው ሊያስተውል የሚገባ ትልቅ ነገር ደግሞ ነበር ማለት ነው፡፡
– ስለፍቅር የሚሸነፍ የእኛ ነገር
በእግዚአብሄር ዘንድ ያለ ታላቅና ውድ ነገር ነው ፍቅር፡፡ ይህ ውድ መለኮታዊ ስጦታ ከየትም አይገኝም፤ ሆኖም ወደ እርሱ ከተጠጋን ሊሰጠን ፈቃዱ ነው፡፡ እግዚአብሄር እንዳለው ፈቅዶ የእርሱን ፍቅር እንድንቀበል መንፈሱን ካፈሰሰልን በሁዋላ ግን በህይወታችን ተገልጦ የሚሰራው አሰራር ፍጹም የተለየ ማንነት የሚሰጥ ነው፡፡
2ጴጥ.1:4-9 ”ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትሆኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን ሰጠን። ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ። እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጉአችኋልና፤ እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና፥ በቅርብም ያለውን ብቻ ያያል፥ የቀደመውንም ኃጢአቱን መንጻት ረስቶአል።”
የእግዚአብሄር ፍቅር የስጋን ግድብ አካሄድ የሚሰብር መንፈሳዊ ሃይል አለው፤ በመንፈሱ ያፍስሰው እንጂ የእኛ ነገር እስከወዲያኛው መቀየሩ አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህም ነው ብዙ መሸነፍ ያለባቸው የሰው ልጅ እክሎች (ባልንጀራን ለመውደድ ያለመቻል እክል፣ ለማካፈል፣ ፍላጎትን፣ ስሜትንና የመሳሰሉትን አሳልፎ ለመስጠት ያለመሻት)፣ ጉድለቶች(ስንፍና በሙሉ)፣ አጉል ባህሪዎች(እግዚአብሄር የማይከብርባቸው በማንነታችን ውስጥ ያሉ) እና እንከኖች( ነውር ነገሮች በሙሉ) ተሸንፈው ለፍቅር እጅ ሊሰጡ የሚችሉት፡፡ እግዚአብሄር ለሰው ልጆች የሰጠው ፍቅር ጠንካራ አቁዋም በሰው ልጆች ህይወት ውስጥ የመፍጠር አቅም ስላለው የፍቅር ልብ ከታደልን ከውጫዊ እንቅስቃሴ አንስቶ እስከ ውስጥ ህይወታችን ድረስ ያሉ ነገሮቻችን ይታደሳሉ ያልያም ይቀየራሉ፡፡ ፍቅራችን እግዚአብሄርን ካከበረ የእግዚአብሄርን ነገር አንድም ሳያስቀር ጎትቶ ወደ ህይወታችን ያመጣልም፡፡
1ጴጥ.4:7-8 ”ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ፥ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ፤ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።”
አጥብቀን ከመዋደድ ውጪ የእኛ ህይወት በስንፍና ቢታነቅ በብዙ የነፍስ መውጊያ እንደሚጎዳ አስቀድሞ ማየት እንጂ መገረም አይገባም፤ ይልቅ ሳናስተውል በፈንታው ተቃራኒ መንገድ ሄደን እንደሆን በቂምና ጥላቻ ወጥመድ ስለምንያዝ ወጥመዱን በቃሉ ጥበብና ማስተዋል ለማለፍ ተጨንቀንም እንትጋ፤ ጥላቻ ፍቅርን ከልብ ውስጥ መንቀል የሚችል ክፉ አደጋ በመሆኑ እንጸየፈው፣ ክእግዚአብሔር ስለሚያርቅና ሰይጣንንም ስለሚጋብዝ እንፍራ፤ በሚጠላ ልማድና ዝንባሌ ውስጥ የሚያደክም የህይወት ስርአት ስለሚበረታበት በክፋቱ መልካም የሆነ ነገር ሁሉ ከህይወት ውስጥ ያሸፍታልና፡፡ ትልቁ የምስራች፣ በፍቅር ምክኒያት ብዙ ድካማችን በእግዚአብሄር ስለሚሸፈንልን ወደ እርሱ መለስ እንበልና ጸጋ እንቀበል እንጂ ብዙ ምህረት ከእግዚአብሄር ዘንድ ተገልጦ ከማጥ ውስጥ ፈንቅሎ ያወጣል፡፡
1ዮሐ.2:5 ”ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሞአል። በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን”
የመለኮታዊ ፍቅር አሰራርና ታላቅነት በሙላት የሚታየን ጉልበቱ እንደምን በጌታ ህይወት ላይ እንደተገለጠ ስናስተውል ነው፡፡ አንድ የቃሉ አድናቂ ሲናገሩ የፍቅርን ምንነት በጥቂቱ እንኩዋን ለማስተዋል ሲያስፈልግ ለእኛ በመንፈስ ቅዱስ ያፈሰሰልንን ፍቅር ባህሪ ከርሱ ማንነት ጋር አዛምዶ ለማየት በመቻል ነው ይላሉ፡፡ ለምሳሌ የጌታን ስም በፍቅር ውስጥ አስገብተን ብንመለከት እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እናገኝ ይሆን? እንዲህ ይላል፡-
”እግዚአብሔር፥ ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው፥ ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና። በእምነትና በትዕግሥትም የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ፥ ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን።”(ዕብ.6:10-12)
የአግዚአብሄር ፍቅር ስሙን በምናከብርበት ህይወት ውስጥ ሲገለጥ በህይወታችን ብዙ ምህረትና በረከት እንደሚያመጣ ቃሉ ምስክር ነው፡፡ ፍቅራችን ለስሙ ሙሉ እውቅና ሲሰጥ ሁሉ ነገራችን በስሙ ይገዛል፡፡ ለሰው ልጅ አስቸጋሪ የሆነ ነገር ለቃሉ መገዛት ሲሆን በጌታ ስም ፍቅር ምክኒያት ግን ትልቅ መታዘዝ ይፈጠርና አለመታዘዝ ይሻራል፡፡
2ዮሐ.6 ”እንደ ትእዛዛቱም እንሄድ ዘንድ ይህ ፍቅር ነው፤ ከመጀመሪያ እንደ ሰማችሁ፥ በእርስዋ ትሄዱ ዘንድ ትእዛዙ ይህች ናት።”
ይሄ ቃል በአንደበት ብቻ ፍቅርን ሊገልጡ የሚወዱ በተግባር ግን ከእግዚአብሄር ፍቅር ለራቁ ሰዎች ጥብቅ ማሳሰቢያ ነው፡፡
ዮሐ.14:21-25 ”ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ። የአስቆሮቱ ያይደለ ይሁዳ፡- ጌታ ሆይ፥ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ ልትገልጥ ያለህ እንዴት ነው? አለው።ኢየሱስም መለሰ አለውም፡- የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን። የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም። ከእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ”
የጌታ ኢየሱስ ስም የሚገለጥ ነው፤ ስሙ ተገልጦ የእግዚአብሄር ፍቅር በመጣ ጊዜ ሀይል በህይወታችን ይንቀሳቀሳል፤ የጌታ ማንነትም በፍቅሩ ውስጥ በጉልህ ይታያል፡- በውስጡ የምንረዳው ጥልቅ የጌታ ማንነት አለ፤ ይህ እውቀት እርሱን በፍቅር በመጠጋት የሚገኝ ነው፡፡ እኛም በጌታ ሆነን ባዳበርነው መንፈሳዊነት በኩል የፍቅር ባህሪ ውስጣችንን ተቆጣጥሮ በፍቅር ላይ የሚኖረንን እምነትና አንድነት ያሰፋልናል፤ በተያዝንበትም በእግዚአብሄር ፍቅር ሀይል ባልንጀሮቻችንን መቀበል እንችላለን፡፡
– በፍቅር ብቻ ደካማን መቀበል ይቻላል
እግዚአብሄር በድንቅ ፍቅሩ ሲጠራን ከነደካማነታችን ነበር፣ ይህ የዛሬው ማንነት መነሻችን ስለሆነ ሆኖ የነበረው (የተለወጥንበት አሰራር ያደረገውን ነገር) መዘንጋት የለበትም፡-
1ቆሮ.1፡26-27 ”ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁን ተመልከቱ፤ እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፥ ኀያላን የሆኑ ብዙዎች፥ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም። ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ”
እግዚአብሄር በአዋቂዎች ፊት አላዋቂ የተባሉትንና በሀያላን ፊት አቅም የሌላቸው ተደርገው የተቆጠሩትን ሰዎች በሰው መስፈርት ሳይመዝንና ሳይጥላቸው፣ ሰው እንዳደረገባቸው ዋጋቢስ ብሎ ሳይፈርጃቸው የእርሱ እጅ ስራ ውጤት መሆናቸውን ብቻ ቆጥሮ ዛሬ ላይ እንዲደርሱ በጸጋው እየመከረ፣ እየደገፈና እያበቃ በእምነት ከፍ አድርጎአቸዋል። ይህ እንዲህ ከሆነ እርዳታ ለሚፈልገው ደካማ ሰው ሌላው ሊደርስ የማይፈቅደው ለምን ነው? ያን የሚሞላ መስዋእትነት መቀበል እንዲሁም የፍቅር ሸክምን ሊሸከም የተዘጋጀ ሆኖ መገኘት እንዲቻል የጌታን ውለታ ማሰብ አስፈላጊ ነው። ፍቅር ካሌለ መሰልቸት አለ፣ ያዘሉትን መጣል ሆኖም አሳዛኝ ፍጻሜ ይከሰታል፤ መስዋእቱ እንደ ቀድሞ በፍቅር ካልታሸ ይታግሳል ብሎ መጠበቅ ውጤታማ አያደርግም፣ ቀላልም አይደለም፡፡
1ቆሮ.9፡20-22 ”ከሰው ሁሉ አርነት የወጣሁ ስሆን የሚበልጡትን እንድጠቅም እንደ ባሪያ ራሴን ለሁሉ አስገዛለሁ። አይሁድንም እጠቅም ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ ከሕግ በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ፥ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፥ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንሁ፤ ሕግ የሌላቸውን እጠቅም ዘንድ፥ ያለ እግዚአብሔር ህግ ሳልኖር ነገር ግን በክርስቶስ ሕግ በታች ሳለሁ፥ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደ ሌለኝ ሆንሁ፤ ደካሞችን እጠቅም ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፥ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ።”
አስተውሉ፣ በክርስቶስ መንፈስ አርነት ወጥቼ ሳለሁ በክርስቶስ የዳኑትንና በርሱ ጸንተው ይቆሙ ዘንድ (ስለፍቅር ስል) ሁሉን እተዋልሁ ይላል ሃዋርያው።
– የፍቅር ጽናት
የህግ ፍጻሜ ፍቅር ሲገለጥ የሰውን ልጅ ካለበት ከህግ በታች አውጥቶ በእግዚአብሄር ፊት ፍጹም ሆኖ እንዲቆም ያደርጋል፤ ሀይሉ በሰው ዘንድ ያለውን ጎደሎ ነገር በሙሉ ሸፍኖም በሞገስ በእግዚአብሄር መገኛ ያቆመዋል፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሄር ፍቅር ምክኒያት የተሰጠን ጸጋ እንዳንናወጥ ስላጸናን በፊቱም ሞገስን ሰጠጥቶ ማምለክና መባረክ እንድንችል ስላደረገ ክብሩን የሚቀበል እርሱ ነው፡፡ ህጉ ሰውን በሰራው በደልና ሃጢያት አጥምዶ ለፍርድ ያቀረበውና ሰውም ከህጉ ሊያመልጥ ያልቻለው ህጉ ያስቀመጠውን መስፈርት ሊያሙዋላ ስላልበቃ ነው እንጂ ህጉ በራሱ አመጸኛ ሆኖ አልነበረም። የእግዚአብሄር ፍቅር ሲገለጥ ግን ጸጋው መጣና የሰውን ልጅ ከፍ አደረገው።
ሮሜ.13:8-10 ”እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፥ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞታልና። አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በውሸት አትመስክር፥ አትመኝ የሚለው ከሌላይቱ ትእዛዝ ሁሉ ጋር በዚህ፦ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ በሚለው ቃል ተጠቅልሎአል። ፍቅር ለባልንጀራው ክፉ አያደርግም፤ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።”
– ፍቅር ከሁሉም ነገሮች በላይ የመኖርና የመጽናት ባህሪ አለው
ፍቅር አይወድቅም፡፡ ስለማይወድቅ አይረሳም፣ በማንምም ዝቅ አይልም፣ ዲያቢሎስ እንኩዋን አያናውጠውም፡፡ የሰው ልጆች በምድር ላይ ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ ካስፈለገ የፍቅር ሀይል የሰውን አሳብና ልብ ሊገዛ የግድ ይላል፡፡ የሰው ልጆች ለራሳቸው ደህንነት ሲሉ እርስ በርሳቸው በዚህ ፍቅር ሊዋደዱ ይገባል፣ እንዲሁም ደግሞ ለእግዚአብሄር ትእዛዝ ተገዢ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ሰዎች ራሳቸውን የጠሉ እለትና ባልንጀራቸው ላይ ቁጣቸውን ያነሱ እለት ግን ፍጻሜአቸው ይሆናል፡፡
ሮሜ.8:35-39 ”ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን?ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን :ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው።በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።፡፡”
ምድር በሰው ልጆች በተፈጠሩ እጅግ አደገኛ የጦር መሳርያ ታጭቃ አይደል ወይ? ነገር ግን ሰዎች ለራሳቸው ስፍራ ባይሰጡ፣ በደመ-ነፍስም ቢሆን (በህሊና አስተውለው ሳይሆን) ለባልንጀራቸው ጥቂትም መውደድ ባያሳዩ ኖሮ ምድርን በብዙ ቁጥር አቃጥለው ባነደድዋት ነበር፡፡
1ቆሮ.13:8-12 ”ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል። ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና፥ ከትንቢትም ከፍለን እንናገራለንና፤ ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ተከፍሎ የነበረው ይሻራል። ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፥ እንደ ልጅም አስብ ነበር፥ እንደ ልጅም እቈጥር ነበር፤ ጎልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ። ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ። እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።”
ይህ ፍቅር መሸቃቀጥና መለወጥ የማይችል ከስጦታዎች ሁሉ የላቀ ስጦታ ነው፡፡ በጠላት ሊያዝ፣ ሊሻር አይችልም፣ መለኮታዊ ስጦታ ስለሆነ፡፡ ስጦታዎች በሙሉ እድሜያቸው የተቆረጠ ነው፣ ነገር ግን ፍቅር ብቻ የእድሜ ገደብ የማይዘው ጸንቶ የሚኖር ስጦታ ሆነ፡፡ ስጦታዎች ሁሉ ጊዜያዊ ናቸው፣ እነርሱ የእግዚአብሄርን ስራ የሚሸከሙና በጊዜያዊነት ተመጥነው/ተገድበው የሚተላልፉ ናቸው፡፡ ፍቅር ግን የእግዚአብሄርን ማንነት እየገለጠ የሚኖር ሆነ።
1ቆሮ.13:9-13 ”ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና፥ ከትንቢትም ከፍለን እንናገራለንና፤ ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ተከፍሎ የነበረው ይሻራል። ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፥ እንደ ልጅም አስብ ነበር፥ እንደ ልጅም እቈጥር ነበር፤ ጎልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ። ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ። እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።”