የፍቅር ግዛቶች [6..]

የእውነት እውቀት

ስለእግዚአብሄር ማንነት በሚወራበት ስፍራ ሁሉ ከእርሱ ጋር ስለፍቅር ሳይነሳ መታለፍ አይችልም፤ ፍቅር የእግዚአብሄር ታላቅ ባህሪ በመሆኑ በተለይ ለእኛ የእግዚአብሄር ፍቅር ማለት እጅግ ብዙ ትርጉም አለውና እርሱን አንስተን ብናወራ፣ ደጋግመን እግዚአብሄር ስለእኛ የገለጠውን የፍቅር ብርታት ብናስታውስ ሲያንስ እንጂ አይበዛም፡፡
መጽሀፍ ቅዱስ እግዚአብሄር ፍቅር እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ፍቅር እንደመሆኑ ሁሉ ይመኩበታል፣  ሁሉ ይጠጉታል፣ ሁሉም ያምኑበታል፡፡ ፍቅሩ ረቂቅና ጥልቅ ስለሆነ መለኪያ የለውም፣ ሰዎች በሙላት አያስተውሉትምም፡፡ እኛ ሳንቀርበው አስቀድሞ እርሱ ወደ እኛ ሲመጣ እንኩዋን መለኪያ/የመቅረቢያ ቅድመ-ሁኔታ አይሰፍርም፡፡ ያ ምክኒያት ሆነናም ታላቅ ፍቅሩን ገልጦ ታላቅ ሀጢያታችንን ደመሰሰው፡፡ በእርሱ ላይ እንዳደረግነው መጠን ሳይሆን እንደመውደዱ መጠን ቀርቦ ነጻ አወጣን፡፡
የእኛ ሀጢያት በግኡዙ አለም ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊው አለም ሳይቀር እየተከታተለ ለሚያሳድደን፣ ጠልፎ ጥሎም  ወደ ሲኦል ለሚወረውረን የሞት መንፈስ አሳልፎ የሚሰጥ ከሰይጣን የወረስነው የአመጽ መንፈስ ነው፤ ሞትም ከሲኦል ጋር በአንድነት የሰውን ነፍስ በማነቅ አስሮ የሚያስቀር የበረታ የጭንቅና የጣር መንፈስ ነው፡፡ ሀጢያት መንፈሳዊ ነገር ነው፤ ተግባሩ በስጋችን ባለ ልምምድ ቢገለጥም ውጤቱ በመንፈሳዊው አለም ላይ የሚወሰን ነው፡፡ የሀጢያት ምንጭ ሰይጣን ነው፣ ሀጢያት አንድ ብሎ የመነጨው ከርሱ ነው፡፡ በእኛ ያለመታዘዝ ከእርሱ ወደ እኛ በመተላለፉ ሁላችንም እርግማን እንድንቀበል ሆነ፡፡ እርግማኑም ሞት ሆነ፡፡ ሞት ደስታና ፍሰሀ ሳይሆን ፍርሀትን በነፍሳችን ላይ የሚሰድድ የፍርድ መንፈስ ነው፡፡ ፍርሀቱ እጅግ ልቆ ጣር እስኪደርስ መንፈስን ነፍስን ይተናነቃል፡፡ ይህ ብርቱ ጣር በአንድ ወቅት ጌታ ድረስ ቀርቦ መጣና በመስቀል ላይ ታገለው፤ እግዚአብሄር ግን ይህን የሞት ጣር አጥፍቶ ከሞት አስነሳው፡፡ ዛሬ ወደ ኢየሱስ የመጣን ከዚህ ጣር በጌታ ምክኒያት አምልጠናል፡፡
እግዚአብሄር ከስጋችን እስከ ሲኦል ድረስ በተዘረጋው የአመጽ ቅብብሎሽ (በስጋ፣ በአለምና በእርኩሳን መናፍስት መሀል ባለ ተላላፊ የመንፈስ አሰራር) ውስጥ ያለውን የሀጢያት መንፈስ በልጁ ደም ሀይል ይቆርጠው ዘንድ በሀያል የፍቅር መንፈስ ተገልጦአል፡፡ ቃሉም  ሲያረጋግጥ እንዲህ ይላል፡-
​​​​​​​​ሮሜ.5:5-9 ”በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም። ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና። ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን።”
እግዚአብሄር ለእኛ ባለው ፍቅር ምክኒያት የልጁን ውድ ደም ረጨብንና የሀጢያትንና የአመጽን ሀይል ከላያችን አወረደው፣ ሻረው እንዲሁም ከእኛ አራቀው እንጂ እኛ ማድረግ የቻልነው ኢምንት ነገር አልነበረም፡፡
ጌታ ደሙን ብቻ አፍስሶ አልቀረም፣ ደሙን ካፈሰሰበት መስቀል ወደ መቃብር እንዳኖሩት ስጋውን በዚያ ትቶ ወደ ሲኦል  ወረደና ሞትንም ሲኦልንም ተገናኘ፤ ሁለቱ ግን ተባብረው በዚያ ሊያስቀሩት አልቻሉም፤ ጌታ በትንሳኤው ሀይል አሸንፎአቸው ተነሳ! ​​​​​​​​በራእ.1:17-18 ፡-
”ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩ በታች ወደቅሁ። ቀኝ እጁንም ጫነብኝ እንዲህም አለኝ፦ አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥ ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ።” ይላል፡፡
ጌታን በዚህ ሁሉ አስፈሪ መንገድ ማን እንዲያልፍ አስገደደው? ብንል የእግዚአብሄር ፍቅር ብቻ እንደሆነ ቃሉ አስረግጦ ይመልስልናል፡፡
​​​​​​​​ሮሜ.5 ላይ ገና ደካሞች ሳለን የሚለው ከክርስቶስ በስጋ መምጣት በፊት አዳምና ዘሩ ሁሉ በሀጥያት ጉልበት ተሸንፎ እንደነበር፣ ወደ እግዚአብሄር ቀና የሚልበትና ስሙን የሚጠራበት ሀይልም ስላልነበረው በዲያቢሎስ የተገዛ ህይወት ውስጥ ይኖር እንደነበረ ነው የሚያሳየው፡፡ የድካም ህይወት የሀጢያት ህይወት ስለሆነ የሚወደው ወይም በሞገስ የሚቀበለው አሜን የሚልም ማንም የለም፤ ያ ህይወት በአምላክ ፊት ቀርቶ በባለ አእምሮ ሰው ፊት እንኩዋን በሞገስ አያቆምም፡፡ እግዚአብሄር ግን ያንን አጸያፊ የህይወታችንን ክፍል ያጥብና ይሽረው ዘንድ በብርቱ ፍቅር ተገለጠ! ክርስቶስ ስጋውንና ደሙን ለመድሀኒትነት የሚያቀርብበት የተወሰነው ዘመን ሲደርስ ልጁ ስለ ኃጢአተኞች ሞተ። እርሱ የሞተው ገና የእግዚአብሄር ፍቅር በህይወታችን ሳይገለጥና እግዚአብሄር ምህረቱን በእኛ ላይ ሳይገልጥ በፊት እጅግ ሩቅ ሳለን (ኃጢአተኞች ሳለን) ስለነበር የኛ ብለን እንደ አስተዋጽኦ ወደ እርሱ የምናቀርበው፣ በጽድቃችን መመካት የሚያስችለን ምንም ነገር አልነበረም፡፡ የወንጌል ብስራት እንደሚለው ክርስቶስ ስለ እኛ መከራ ተቀበለ፣ ሞተም፡፡ መሞቱም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር የሚያስረዳ ታላቅ ሰማያዊ መረጃ ነበረ፡፡ ፍቅሩ በክርስቶስ ውስጥ ተወስኖ የቀረ አይደለም፤ የእርሱ ፍቅር እርሱን የጽድቅ ልብስ አድርገው በለበሱት ህይወቶች ዘንድ እየተባዛ የሰውን ዘር የሚወርስ ነው፡፡ የጌታ ሀያል ፍቅር ተላላፊ ባህሪ አለው፤ በዚህ ባህሪው ምክኒያት ጌታ ኢየሱስ ውስጥ የተገለጠ የእግዚአብሄር ፍቅር ወደ ሰው ልጆች በመንፈሱ በኩል ሊፈስስ ችሎአል፡፡
ግራ የሚያጋባውና በሰው ዘንድ እንዳይመለስ የሚያዳግተው ጉዳይ ወደ እኛ ህይወት ውስጥ የተጋባው መለኮታዊ ፍቅር በይዘቱ ልክ ተጠብቆ ይኖራል ወይ? ወይም ደግሞ ወደ ሌሎች እርሱ እንዳሰበው መተላለፍ ችሎአል ወይ? የሚለውን ጥያቄ መመለሱ ላይ ነው፡፡ ፍቅር መጠን ሳይሆን ሊለውጥ የሚችል አቅም ነው፣ ያን ለማስተዋል የእግዚአብሄርን ፍቅር ባህሪ መመርመር በእኛ ህይወት ውስጥ ያለውን አሰራር መመልከትም ያስፈልጋል፡- ስፋትና ጥልቀት እያልን በወርዱ በእርዝመቱ ልንለካው ያልያም ልንዳስሰው ስንቡዋጥጥ ብንከርም የሚገለጥ የእግዚአብሄር ባህሪ የለም፤ ግን ስንቀበለው ሙላትን ፣ ብቃትን፣ ልዩነትንም መፍጠር የሚችል ነው፡፡

  • በሰው ዘንድ በልብ የተጠበቀ ፍቅር በአሰራሩ እንዴት ያለ ድል፣ እንዴት ያለ ለውጥ፣ እንዴት ያለ ምርኮ ያመጣል?!

​​​​​​​​ፍቅር የድል ምልክት ነው፤ የገዙንን የኛን ነገሮች አሸናፊ ነውና፤ በሀጢያት ላይ እንዴት እንረግጣለን፣ አመጽን እንዴት መቃወም እንችላለን? መልስ ያስፈልጋል፡፡ ነፍሳችን ላይ ጌታ የሆኑ አንዳንድ ባህሪዎች አሉ፣ የሚያስጮሁዋት፣ የሚያስምጡዋት የኛው የራሳችን እነዚህ ነገሮች ስጋችን ውስጥ ተሰንቅረው ነፍስን ይወጋሉ፤ እርሱዋ ከውስጥ ትጮሀለች፣ እነርሱ ግን ተጭነው ቆልፈዋታል፡፡ እነዚህ ላይ የእግዚአብሄር መንፈስ ሲመጣ ስፍራቸውን ያስለቅቃል፡፡ የልባችንን ጥንካሬ የሚያውቅ አምላክ በእልከኝነት ከስንፍናችን ጋር ተጣብቀን በእምቢታ እንዳንቀጥል በመንፈሱ በኩል በሚያፈስሰው የፍቅር ሀይል ያገኘናል፡፡ የወረደብን የፍቅር መንፈስ ስለሚያሸንፈን በእኛ ዘንድ ያለውን ሀጢያትና መተላለፍ በቀላሉ ያስወግዳል፡፡
ሰዎች የተባልን በሞላ አስቀድሞ በዚህ አለም ገዢ መንፈስ ቁጥጥር ስር በነበርን ጊዜ ዋና መገለጫችን አመጽና ሀጢያት እንደነበረ ሁሉ አሁን በጌታ ስንሆን መገለጫችን ከእርሱ የወረስነው ፍቅር ነው፡፡ ፍቅሩ እግዚአብሄርን ባልንጀራችንንም እንድንወድ የሚያደርግ ነው፡፡ የሚወደድ ለባልንጀራው በጎውን ያስባል፣ ያደርጋልም፡፡ የሚወድድ ለባልንጀራ የሚጠቅም ነገርን ይፈጽማል፤ በዚህ ክፉ ትውልድ መሀል ይህን ለማድረግ የሚገፋ ምክኒያት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ የፍቅር ጉልበት የተሻለ ነገር ሰው ለተባለ ሁሉ እንድናከናውን እንድናስብም ልብና አእምሮአችንን ያነጻል፡፡
​​​​​​​​1ቆሮ.9:20-25 ”አይሁድንም እጠቅም ዘንድ ከአይሁድ ጋር እንደ አይሁዳዊ ሆንሁ፤ ከሕግ በታች ያሉትን እጠቅም ዘንድ፥ እኔ ራሴ ከሕግ በታች ሳልሆን፥ ከሕግ በታች ላሉት ከሕግ በታች እንዳለሁ ሆንሁ፤ ​​​​​​​​ሕግ የሌላቸውን እጠቅም ዘንድ፥ ያለ እግዚአብሔር ህግ ሳልኖር ነገር ግን በክርስቶስ ሕግ በታች ሳለሁ፥ ሕግ ለሌላቸው ሕግ እንደ ሌለኝ ሆንሁ፤ደካሞችን እጠቅም ዘንድ ለደካሞች እንደ ደካማ ሆንሁ፤ በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፥ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ።በወንጌልም ማኅበረተኛ እሆን ዘንድ ስለ ወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ።በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ።የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል፤ እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው፥ እኛ ግን የማይጠፋውን።”
ሃዋርያው በሸክም መንፈስ ለሰው ሁሉ እንዲራራ የገፋው የጌታ ፍቅር እንደሆነ ግልጽ ነው፤ እርሱ ባይነካው ኖሮ በነፍሰ-ገዳይነቱ በቀጠለ ነበርና፡፡ ታሪኩን የለወጠው የጌታ ኢየሱስ በፍቅር መንካት ነበር፡፡
ጌታ በስጋ በአይሁድ መሀል ሲመላለስ በነበረ ጊዜ የህዝቡ ልብ ከፍቅር እጅግ የራቀ ነበር፤ እነርሱ እጅግ ጠንካራ ልብ ስለነበራቸው ሰውንም እግዚአብሄርንም ተፈታትነዋል፤ መጽሃፋቸውን ሳያስተውሉ መድሀኒትን ጠሉ፣ የመከራ በትር አሳረፉበት፣ ገደሉት፣ ቀበሩት! እነርሱ በግልጥ የእግዚአብሄርን ትእግስት የተፈታተኑ ህዝቦች ነበሩ፡፡ እግዚአብሄር ግን በፍቅሩ ትእግስት እስከመጨረሻው ጠብቆአቸዋል፡፡ የትእግስቱ ስፋት የተጋባበት አገልጋይ ዋና አድርጎ የተነሳበት አላማ እንደሚያሳየው ከእግዚአብሄር ምህረት ርቀው የቆሙትን ወገኖቹ አይሁድን ለመጥቅም በነርሱ የኑሮ ስርአት ውስጥ በመሳተፍ ሊያድናቸው እንደጣረ ያሳያል፡፡ ፍቅር ሸክም ስለሆነ በጌታ ያገኘውን ነጻነቱን ሳይጠቀም ዝቅ ብሎ ሲያገለግል እንመለከታለን፡፡
ስለፍቅር ሸክም ሲል በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፥ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ አለ።
ሐዋ.9፡11-17 ”ደማስቆም ሐናንያ የሚሉት አንድ ደቀ መዝሙር ነበረ፥ ጌታም በራእይ፡- ሐናንያ ሆይ፥ አለው። እርሱም፡- ጌታ ሆይ፥ እነሆኝ አለ። ጌታም፡- ተነሥተህ ቅን ወደ ሚባለው መንገድ ሂድ፥ በይሁዳ ቤትም ሳውል የሚሉትን አንድ የጠርሴስ ሰው ፈልግ፤እነሆ፥ እርሱ ይጸልያልና፤ ሐናንያ የሚሉትም ሰው ገብቶ ደግሞ እንዲያይ እጁን ሲጭንበት አይቶአል አለው።ሐናንያም መልሶ፡- ጌታ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም በቅዱሳንህ ላይ ስንት ክፉ እንዳደረገ ስለዚህ ሰው ከብዙዎች ሰምቼአለሁ፤ በዚህም ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን አለው አለ። ጌታም፡- ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና አለው። ሐናንያም ሄዶ ወደ ቤቱ ገባ፥ እጁንም ጭኖበት፡- ወንድሜ ሳውል ሆይ፥ ጌታ፥ እርሱም በመጣህበት መንገድ የታየህ ኢየሱስ ነው፥ ደግሞ ታይ ዘንድና መንፈስ ቅዱስ ይሞላብህ ዘንድ ላከኝ አለ።”
የጳውሎስ የቀደመ ታሪኩ ነፍሰ-ገዳይነት ቢሆንም የእግዚአብሄር ፍቅር ሀይል እንደምን ለውጦት ለሰው ልጆች የሚራራና ራሱን አሳልፎ እስኪሰጥ ርህራሄ የተሞላ ሰው እንደሆነ የምናየው ነገር ነው፡፡ እርሱም ያለው ያንን ነው፡-
1ጢሞ.1፡12-16”ለአገልግሎቱ ሾሞኝ ታማኝ አድርጎ ስለ ቈጠረኝ፥ ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ፤አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን፥ ይህን አደረገልኝ፤ ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምህረትን አገኘሁ፥የጌታችንም ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ ካሉ ከእምነትና ከፍቅር ጋር አብልጦ በዛ። ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ፤ ስለዚህ ግን፥ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ፥ ምህረትን አገኘሁ።”

የጌታችንም ጸጋ ክርስቶስ ኢየሱስን አምነው በጥምቀት ከለበሱ፣ መንፈሱን ጠጥተውም ዳግም ከተወለዱ ጋር በእምነትና በፍቅር አብልጦ እየበዛ ፍጥረትን ያዳርሳል። የጌታ ፈቃድም ኃጢአተኞችን ለማዳን አለሙንም በፍቅሩ ለመሳብ ነውና፡፡ ሃዋርያው ጳውሎስ መለስ ብሎ መዳኑን ሲያስታውስ ክርስቶስ ኢየሱስ ከኃጢአተኞች ዋና የሆንኩትን እኔን አድኖኛል፤ ይህም የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን ነው ይላል፡፡

  • ፍቅር በተግባር ውስጥ ይታያል

​​​​​​ዮሐ.21:13-19 ”ኢየሱስም መጣና እንጀራ አንሥቶ ሰጣቸው፥ እንዲሁም ዓሣውን። ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥላቸው ይህ ሦስተኛው ጊዜ ነበረ። ምሳ ከበሉ በኋላም ኢየሱስ ስምዖን ጴጥሮስን፡- የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ከእነዚህ ይልቅ ትወደኛለህን? አለው። አዎን ጌታ ሆይ፥ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ግልገሎቼን አሰማራ አለው። አለው።ጠቦቶቼን ጠብቅ አለው። ሦስተኛ ጊዜ። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ ትወደኛለህን? አለው። ሦስተኛ። ትወደኛለህን? ስላለው ጴጥሮስ አዘነና። ጌታ ሆይ፥ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ እንድወድህ አንተ ታውቃለህ አለው። ኢየሱስም። በጎቼን አሰማራ።እውነት እውነት እልሃለሁ፥ አንተ ጐልማሳ ሳለህ ወገብህን በገዛ ራስህ ታጥቀህ ወደምትወደው ትሄድ ነበር፤ ነገር ግን በሸመገልህ ጊዜ እጆችህን ትዘረጋለህ፥ ሌላውም ያስታጥቅሃል ወደማትወደውም ይወስድሃል አለው።በምን ዓይነት ሞት እግዚአብሔርን ያከብር ዘንድ እንዳለው ሲያመለክት ይህን አለ። ይህንም ብሎ። ተከተለኝ አለው።”
በእርግጥ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና የሰው ልጅ በሙሉ ወደ አለም የመጣውን ጌታ እንዲቀበለው የተገባ ነው፤ የተቀበሉት አማኞችም ወደ አለም የመጣውን እርሱን ያሳውቁ ዘንድ በህይወታቸውና በምስክርነታቸው ሊገልጡትም የተገባ ነው፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ አማኝ በጽድቅ መገለጥ ካለበት መገለጥ የሚችለው በንግግር ሳይሆን ፍቅሩን ለሰውም ለእግዚአብሄርም በመግለጥ ነው፤ ህይወታችን ተግባራዊ መገለጫ አለው፣ ዋናው መገለጫም ፍቅር ነው፡፡
የሃዋርያቶች ፍቅር በተግባር የሚገለጥበት ሰአት በደረሰ ጊዜ ጌታ ኢየሱስ ፊተኛውን ሃዋርያ ጠርቶ ጠየቀው፤ የእርሱ ፍቅር አልፎ ወደ መንጋው የሚያልፍበት ሰአት ደርሶ ነበርና ያን እንዲያስተውሉ ጌታ ጴጥሮስን አቁሞ ያን አመልክቶታል፡፡ መለኮታዊ ፍቅር በተግባር ሲገለጥ ብዙ መንፈሳዊ ፍሬዎች ስለሚያሳይ የዚያን ፍሬያማነት ለወንጌሉ ተሸካሚዎች ማስተዋልን ጭምር በመስጠጥ ጌታ ኢየሱስ አሳስቦአቸዋል፡፡ እነዚህ ደቀመዝሙርት በታዘዙት የፍቅር ትእዛዝ ውስጥ አልፈውና አፍርተው ከቆዩ በሁዋላ የጌታን ፍሬያማ ፍቅር ለደቀመዛሙርት ሲያሳስቡ እናያለን፡-
​​​​​​​​”እኛ ወንድሞችን የምንወድ ስለ ሆንን ከሞት ወደ ሕይወት እንደ ተሻገርን እናውቃለን፤ ወንድሙን የማይወድ በሞት ይኖራል። ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ። እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል፤ እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል። ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው፥ ወንድሙም የሚያስፈልገው ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን፥ የእግዚአብሔር ፍቅር በእርሱ እንዴት ይኖራል?” (1ዮሐ.3:14-18)
እኛም ስለ ወንድሞቻችን ነፍሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ይገባናል ካልን በጥቂቱ እንኩዋን ስለወንድማችን ህይወት ልናስብ ይገባናል ማለት ነው፡- ስለወንድማችን የመንፈስም የስጋም ህይወት፡፡ ስናስብ በሸክም፣ በፍቅር፣ በጥንቃቄና ለእርሱ ጥቅም ስንል ብቻ ሊሆንም ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ዘመን በእኛ ላይ ሊታይ አጉዋጊ የሆነው የእግዚአብሄር ፈቃድ ይህ ነው፡፡ አለምን ልትለውጥ ብትፈቅድ አለም የምትለወጠው በምትሰጠው አስተያየት ሳይሆን በምታሳየው የፍቅር ስራ ነውና፡፡