የፍቅር ክልል በስፋት፣ በርዝመትና በጥልቀት የማይለካ ግን ልብን አእምሮንና ነፍስን የሚቆጣጠር ብርቱ ሀይል፣ ሰውንም ያለጉልበት መግዛት የሚችል ታላቅ መለኮታዊ ስጦታ ነው፡፡ ክፉ የተባለውን የሰው ልብ ሌላ ምን አይነት ጉልበት ሊያቆመው ችሎአል? እርሱን ለመለወጥ የሚችል ፈቃድስ ምን ነበር? እግዚአብሄር ለብዙ ዘመናት ቃሉን፣ ህጉን፣ ስርአቱንና መንገዱን ቢሰጥም የሰው ልብ እሺ ብሎ የተገዛው መቼ ነበር? እግዚአብሄር ግን ያን አመጸኛ ብልት በቁጥጥር ስር ማድረግ የሚችልበትን ልዩ ጉልበት በዚሁ በሰው ልብ ውስጥ በማስገባት አሸንፎታል፡-
ሮሜ.5:2-6 ”በእርሱም ደግሞ ወደ ቆምንበት ወደዚህ ጸጋ በእምነት መግባትን አግኝተናል፤ በእግዚአብሔር ክብርም ተስፋ እንመካለን። ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ፥ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን፥ በመከራችን ደግሞ እንመካለን፤ በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም። ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና።”
ፍቅር በክርስቲያን ህይወት ውስጥ ሲገባ እየሰፋ፣ እያደገና እየወረሰ የሚሄድ የመንፈስ ቅዱስ ነጻ ርስት ነው፡፡ ከእግዚአብሄር ብዙ የተማረ ከእርሱ የፍቅርን ርስት ይወርሳል፡፡ ከጌታ ኢየሱስ ጋር በፈተናው ሁሉ የጸኑት ደቀመዛሙርት በስተመጨረሻ ብርቱ የፍቅር ሰዎች ነበር የሆኑት፡፡ የርሱ የፍቅር ጉልበት የልባቸውን ክልል ወርሶት ስለነበር ፈቃዱ በህይወታቸው ተገልጦ ሊሰራ ችሎአል፡፡
የእግዚአብሄር ፍቅር ሰውን በውዴታ ለመስዋእት ያቀርባል፣ ለእግዚአብሄር ድልም ቢሆን ያቀርባል፡፡ በጌታ ፍቅር የተጠመደ በሰው ልጅ ፍቅር ይጠመዳል፣ በሃላፊነት ሸክም ይጥለቀለቃል (በፍቅር ነፍሳትን መድረስ፣ በመማረክና በጥንቃቄ ሸክም ይሞላል)፤ በፍቅር የሚፈጠረውን የድል ዋንጫ ቅርብ ይሁን ሩቅ ብቻ ከአምላኩ እንደሚያገኘው ያምናል፣ በዚህ አለም ላይቀበለው ቢችልም፡፡ የፍቅር ክፍያ እጅ በእጅ አይደለም፤ አፍቃሪ ደምሮና ቀንሶ ስለማይወድ፣ ለራሱ ጥቅም ብሎ ፍቅሩን ስለማያውልና መልሱ ይፈጥንለት ዘንድ ስለማይጉዋጉዋም፣ ነገር ግን በብርቱ ትእግስት ማፍቀሩን ከነሸክሙ መቀበል ከቶ አይሳነውም፡፡ አዎ ያ ብርቅዬ የሆነ የእግዚአብሄር ልጅ በርሱ የተወደደ ነውና እግዚአብሄር እጅ ላይ ያለ ውድ ሰው ይሆናል፡፡
አመጽ በበረታበት አለም ፍቅር እንዴት ባለ ትግስትና ጥበቃ ሁሉን ሊታገስ ይችላል? መታገስ በግፊት መሀል ችሎ ማለፍ ካስፈለገው፣ መጠበቅ ከጠየቀና ራስን መከለል እንዲሁም የሌላውን ድካም በፍቅር መሸፈኛ መሸፈን ከጠየቀ ይህ ፍቅር የሚሉት ውስጣዊ ሀይል መስዋእትነትን ከእኛ ይጠብቃል ማለት አይደል? ፍቅር እኮ ሀይል አለው የምንለው የሰውን አመጽ፣ በደልና ሀጢያት ሳይመለከት፣ ሳይቆጥርና በርሱ ምክኒያት እርምጃ ውስጥ ሳይገባ የሆነውን ሁሉ መሸከም ስለሚችል ነው፡፡ የፍቅር ነገር የንግግር ጉዳይ ሳይሆን በተግባር መገለጥ ያለበት መስዋእትነት ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ምን አይነት የሚያስችል ጉልበት ነው በፍቅር ውስጥ ያለ ጉልበት?
ፍቅር የሰው ሀይል፣ እውቀትና ሀብት ባልተገባ መንገድ ጥፋት ላይ እንዳይውል የሚገታ መንፈሳዊ ብርታት ነው፤ ከውድቀት የሚከልል የሰው ልብ መጠበቂያ በጎ ጉልበትም ነው፡፡ ኤሊ የምትባል እንስሳ እንደ ድንጋይ ያለ ቅርፊት ተሸክማ መኖርዋ የሚከብዳት ቢሆንም እጅግ የሚጠቅማት እንዲያውም የሚታደጋት በጎ ጎን አለው፤ ሸክሙ እንደልብ ላያስሮጣት ይችላል፣ ቀርፋፋ አድርጎም ለብዙ አጥቂዎች በቀላሉ መጠመጃነት የሚያጋልጣት ይመስላል፤ ይሁን እንጂ ከዚህ ባሻገር ብርቱ በጎ ነገር ይጠብቅላታል፡፡ ኤሊ በለበሰችው ድንጋይ ምክኒያት በጠላት የመጠቃት አጋጣሚዋ አነስተኛ ነው፡፡ ታላላቅ አውሬዎች እንኩዋን በላይዋ ቢሰፍሩ በቀላሉ አያጠፉዋትም፡፡ ስለዚህ ፈጣን ናቸው የተባሉ እንስሳት የሌላቸውን ማስተማመኛ ለብሳ ቀርፋፋ በሚልዋት መሀል ትንጎራደዳለች፣ እንደሚሰማቸው ያለ ስጋት ሳያሰጋት ትኖራለች፡፡
ፍቅር የተላበሰ ማንነት እንደ ኤሊዋ በህይወት ሩጫ ላይ የተጎተተ ቢመስልም ከብዙ ነገር የሚከለልበትን ጠንካራ የጸጋ ልባስ ከአምላኩ ዘንድ ተጎናጽፎአል፡፡
በ1ጴጥ.4:8 ላይ ያለው ቃል እንዲህ ይላል፡-
”… ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።”
አለምን ያጥለቀለቀ የኃጢአት ብዛት ራቁት ሳያስቀር በፊት የአማኝ ህይወት በምን ይሸፈን? ግልጽ ነው፣ ፍቅር በተባለ ነፍስን ከጥፋት መጋረድ በሚችል ታላቅ ሸማ እንጂ በሌላ በማንም አይሸፈን፡፡ የሀጢያትን ግፊት የሚመክት ጉልበት ከእግዚአብሄር የተቀበልነው በመንፈስ ቅዱስ በልባችን የፈሰሰው የእግዚአብሄር ፍቅር ብቻ ነው፡፡ ፈቃዳችን በስጋችን ታግቶ ወደ ሀጢያት ወጥመድ የሚገፋበት ሁኔታ ብዙ ነው፡፡ እያንዳንዱ የተሸነፈ ፈቃዳችን ከሀጢያት ጋር መደራደርና እጅ መስጠት ስለሚከጅለው በፍቅር ሀይል ፈጥኖ መጋረዱ ይበጀዋል፣ ያ ካልተሳካ በሀጢያት መታሰር በጥፋትም ላይ የመውደቅ አጋጣሚ የማይቀር መጨረሻ ነው፡፡ እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ የሚለው የልኡል ምክር ለሰው መትረፊያ ለጠላት ብርቱ ጥቃት ነው፤ የጸና መዋደድ የሚፈጥረው ክበብ በክፉ መናፍስት ግዛት ውስጥ እንደ መታደጊያ አጥር የሚያገለግል ነውና፡፡ ሰይጣን የአመጽ ምንጭ እንደመሆኑ የሰላምና የስምምነት መንፈስ በወረደበት አካባቢ የሚያተርፈው ነገር ስለማይኖር ያ አያስደሰተውም፡፡ ሰው ሲዋከብ ይመቸዋል፣ ሲጣደፍ ይቀለዋል፣ ሲራኮት፣ ሲጣላና ቂም ሲያያዝ እቅዱን ያፋጥንለታል፡፡ ፍቅር ግን ያባርረዋል፣ ያርቀዋል፣ ያሸንፈዋል!
እርስ በርስ በማፋጠጥ፣ በማራኮትና በማባላት የሚከብር ከሆነ የሰዎች ስምምነት ለርሱ ጠላትነት አይደል? ደግሞ በአንድ ልብ ወደ እግዚአብሄር ፈቃድ ማዘንበል በሰዎች መሀል ካለ እርሱን ይበልጥ አያስቆጣውምን? አዎ ይቆጣ እንጂ እኛ አጥብቀንና ተጠባብቀን እንዋደድ፣ በዚህም የልኡሉን ትእዛዝ እንፈጽም፡፡
ምሳ.10:12 ”ጥል ክርክርን ታስነሣለች፤ ፍቅር ግን ኃጢአትን ሁሉ ትከድናለች።” ይላል፡፡
ጥል በሰዎች መሀል እንደምን ይበቅላል? የቁዋንቁዋ መደበላለቅና የሰላም መጥፋት ከየት ይመነጫል? አመጽና በደል ከተመሉ ልቦች ውስጥ አይደለምን? ልባችን ግን ገር ቢሆን፣ ከእልህ ይልቅ የዋህነትን ቢመርጥ እንዲሁም ከበቀል ጉንጉን ወጥቶ በምህረት ቢመለከትና በእርቅ ቢቀርብ ወደ ፍርድ ሊያወርደው ያደባበት ኃጢአት ተከደነ ማለት አይደል?
ምሳ.17:9 ”ኃጢአትን የሚከድን ሰው ፍቅርን ይሻል፤ ነገርን የሚደጋግም ግን የተማመኑትን ወዳጆቹን ይለያያል።”
በሆነ ዘመን በምድር ላይ አመጽ በዝቶ ፈጣሪን ሳይቀር ባስጨነቀ ወቅት የእግዚአብሄርን ልብ በምህረት የሚያዘነብል ኖህ የተባለ ሰው በምድር ላይ ተገኘ፡፡ ይህ ሰው በነበረው ፍቅርና ሸክም ለአለም በሞላ የእግዚአብሄርን ቁጣ መቅረብ አወጀ፣ ማምለጫውንም አመለከተ፤ የሰሙት ቤተሰቡና የታዘዙት እንስሳት ብቻ ሆኑና ከውሀ ጥፋት ዳኑ፡፡ የቀሩት ፍቅር የሌላቸው ኃጢአትን የተለማመዱ ህዝቦች ግን በሙሉ ከምድረ-ገጽ ጠፉ፡፡
ቀጥሎ የሆነው የተለየ ነበር፡- ፍቅር ተግባርን ስለሚጠይቅ ወደ ኖህ የቤተሰብ አባል ወርዶ ልጆቹን ይፈትን ገባ፡፡ ስለዚህ ራቁት ገመናን መግለጥና መሸፈን በቤተሰቡ ላይ ተገልጦአል፡፡ መውደድ ከሸክም ጋር ስለሆነ የሚወድዱ ገመናን በጥንቃቄ ሲሸፍኑ እናያለን፡፡ እንዲህ ይላል፡-
”ኖኅም ገበሬ መሆን ጀመረ፥ ወይንም ተከለ። ከወይን ጠጁም ጠጣና ሰከረ፤ በድንኳኑም ውስጥ ዕራቁቱን ሆነ። የከነዓን አባት ካምም የአባቱን ዕራቁትነት አየ፥ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው። ሴምና ያፌትም ሸማ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉ፥ የኋሊትም ሄደው የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ፤ ፊታቸውም ወደ ኋላ ነበረ፥ የአባታቸውንም ዕራቁትነት አላዩም። ኖኅም ከወይን ጠጁ ስካር ነቃ፥ ታናሹ ልጁ ያደረገበትንም አወቀ።” (ዘፍ.9:20-24)
ፍቅር እንዴት ሀጢያትን ይሸፍናል? ፍቅር ነገሮቻችንን ከእፍረትና ውርደት ሲሸፍን፡- የሰውን ድካም ሲደግፍ፣ ጉድለት ሲሞላ፣ በደልና ሀጢያት አጋልጦ ለሌላ ኪሳራ አሳልፎ ከመስጠት ሸፍኖ ማትረፍ ሲችል ማለት ነው፡፡ ስለ ሰው ድካም አዋጅ ማስነገርን ከመሰለ ስብራት የከፋ ምን አለ? ሰውን ርእስ እያደረጉ ወዳጅነትን እንደመግፋት ያለ ነውር የለም፡፡ አካሄዱ ተበዳዩን ሰው ያሸማቅቃል፡፡
ሰው በተፈጠረበት የሀሜት ሀፍረት በልቡ ስብራት አንካሳ ሆኖ እስኪቀርና አንገት እስኪደፋ የሚቆልፍ ድርጊት ቢኖር ስለሰው ነገር አዋጅ መንዛትና ማማት ነው፡፡ ቃሉ የወንጌል አዋጅ ነጋሪ እንድንሆን አመልክቶን እያለ የሰውን ድካም አንጠልጥለን ብንነዛና ብናውጅ ትልቅ ኪሳራ ውስጥ እንገባለን፡፡ ነገር ግን በፍቅር የተሞላ ልብ ስናገኝ ጣት መቀሰርን ያስቀርልንና እጃችንን በአፋችን ላይ እንድንጭን ያስገድደናል፡፡
1ተሰ.5:12-15 ”ወንድሞች ሆይ፥ እንመክራችኋለን፤ ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጹአቸው፤ ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ። ማንም ለሌላው በክፉ ፈንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፥ ነገር ግን ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ለሁሉም መልካሙን ለማድረግ ትጉ።”
ፍቅር ሁሉን ያምናል፣ ይመን እንጂ ከውሸት ጋር አይደራደርም፡፡ እንዲያውም እውነተኛ አፍቃሪ ውሸትን አይቀርብም፡፡ በፍቅር ውስጥ ሁሉን በየዋህነት መስማት፣ መታገስና ሁኔታዎችን ማስጨረስ ነገር ቢኖርም አመጽን የመቀበል ሁኔታ አይታይበትም፡፡ ፍቅር ያለው ሰው ተሞኝቶ በመታለል ሳይሆን የአመጸኛውን ጉዳት ባለመሻት በሚፈጠር ርህራሄ ምክኒያት በዳይን በምህረት ይቀበላል፡፡ ሰዎችን በሸክም ስለሚቀበል በበጎ እምነት ነገሮችን ያልፋል፡፡
እውነተኛው ፍቅር መለኮታዊ በመሆኑ የእግዚአብሄርን ፈቃድ በርሱ እንድንፈጽም ያስገድዳል፡፡ ሁኔታው በስጋ ሲታይ ያለማስተዋል/ ሞኝነት የሚመስል ነገር ስለሆነ በውስጡ የሚገለጠው የእግዚአብሄር አሳብ ለአለም ሰው ይከብዳል፡፡
ፍቅር በወገኖች መሀል ሲኖር ግንኙነት ላይ መተማመንን ያሰፍናል፡፡ በፍቅር መልካም ጎኖች ብቻ ጎልተው ይወጣሉ፤ ነገሮች በየዋህነት ስለሚካሄዱ የሰውን ልቦናም መልካም በሆነ አያያዝ ስለሚያሰኬዱ መተማመንን ይፈጥራሉ፡፡ ዮናታንና ዳዊትን ለምሳሌ እንይ፡-
1ሳሙ.18:1-4 ”ዳዊትም ለሳኦል መናገሩን በፈጸመ ጊዜ የዮናታን ነፍስ በዳዊት ነፍስ ታሰረች፥ ዮናታንም እንደ ነፍሱ ወደደው። በዚያም ቀን ሳኦል ወሰደው፥ ወደ አባቱም ቤት ይመልሰው ዘንድ አልተወውም። ዮናታንም እንደ ነፍሱ ስለ ወደደው ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ዮናታንም የለበሰውን ካባ አውልቆ እርሱንና ልብሱን ሰይፉንም ሸለመው። ዮናታንም የለበሰውን ካባ አውልቆ እርሱንና ልብሱን ሰይፉንም ቀስቱንም መታጠቂያውንም ለዳዊት ሸለመው።”
የዮናታንና የዳዊት ግንኙነት በአንድ መስፍንና እረኛ መሀል እንዳለ ግንኙነት ያለ አልነበረም፡፡ በመሀከላቸው የወረደው የፍቅር መንፈስ በስጋ ባለው ክብር ምክኒያት አንዱን ከሌላው የለያየ ሳይሆን የነፍስ መተሳሰርን የፈጠረ ነበር፡፡ እንዲህ ያለ ፍቅር የሚበርድ ስላልሆነም ዘመናት የሚሽሩት አይነት አልነበረም፡፡ በዚህ መንገድ የተሳሰረ ፍቅር አሻግሮ ተስፋ ያደርጋል፣ ስለዚህ በርሱ ውስጥ ወደፊትን በመልካም መቀበልና መጠበቅ እንጂ አጨልሞ ማየት ጨርሶ አይኖርም፡፡ በእግዚአብሄር መታመንና ቃል-ኪዳኑን በማሰብ ወደፊትን በመልካም መጠበቅ የሚቻለው እንዲህ ባለ የፍቅር መንፈስ ተይዞ ነው፡-
1ሳሙ.23:16-18 ”የሳኦልም ልጅ ዮናታን ተነሥቶ ወደ ዳዊት ወደ ጥሻው ስጥ ሄደ፤ እጁንም በእግዚአብሔር አጽንቶ፡-የአባቴ የሳኦል እጅ አታገኝህምና አትፍራ፤ አንተም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆናለህ፥ እኔም ከአንተ በታች ሁለተኛ እሆናለሁ፤ ይህን ደግሞ አባቴ ሳኦል ያውቃል አለው። ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረጉ፤ ዳዊትም በጥሻው ውስጥ ተቀመጠ፥ ዮናታንም ወደ ቤቱ ሄደ።”
የሁለቱ ወጣቶች ፍቅር ከፍ ያለ ነበር፡፡ መስፍኑ ዮናታን ስለፍቅር ራሱን ከአንድ እረኛ በታች አውርዶም ስንመለከት እግዚአብሄር የሚሰጠን ፍቅር በህይወታችን እንደምን ክብር ያለው ስራ እንደሚሰራ የእግዚአብሄርን ፈቃድም እንዲፈጽም እናስተውላለን (የዮናታን ፍቅር ዳዊት የእስራኤል ንጉስ እንዲሆን እግዚአብሄር ያሰበውን አሳብ የሚቀበልና የሚፈቅድ ነበርና)፡፡
በነዳዊት መዋደድ ውስጥ ትግስትንም እንመለከታለን (ፍቅር ሁሉን ይታገሳል ስለሚል)፡፡ ዳዊት እግዚአብሄር በእስራኤል ላይ እንደቀባው አስተውሎአል፡፡ ነገር ግን በእርሱና በዮናታን መሀል በነበረው ቃልኪዳን ምክኒያት ብዙ መከራዎችን በትእግስት ተቀብሎአል፡፡ በዚያ ወቅት ሳኦል በርሱ ላይ ያደረሰውን በደል ታገሶ ሲይዝም ለርሱ ተከራካሪ የነበረው ዮናታን ሆኖ ነበር፡፡
ትእግስት የጊዜ ገዢ ነው፣ ትእግስት የሚፈልገውን ጊዜ እኛም ካልሰጠነው አናተርፍበትም፤ ጊዜ ትእግስትን ሲገዛ የምንፈልገው ውጤት ያለ ሰአቱ ሊጨነግፍ ይችላል፡፡ አብዛኞቻችን ነገሮችን የምንታገሰው በጊዜ ባለመጠባበቅ ስለሆነ (ጊዜ ሰጥተን ሳይሆን) ያሰብነው ይሆናል ብለን የምናምነውና ተስፋ የምናደርገው እስከተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ነገር ወሰኑን ሲያልፍ የኛም ትግስት፣ እምነትና ተስፋ እንደጉም ይበንናል፡፡ ሆኖም ያን ትግስት የሚያስቀጥል፣ ተስፋ የሚረዝም ወይም እምነታችንን እስከ እግዚአብር ራእይ መዳረሻ ድረስ የሚያሰፋና የሚያጠልቅ ከእግዚአብሄር ዘንድ የሚሆን ፍቅር ሲያገኘን ሁሉም ይሳካል፡፡
ፍቅር ሲይዝ እምነት ስለምንሞላ ተስፋ ቢስነት አይጠልፈንም፣ ብርሀን ስለሚታየን ጥርጣሬ አይወርሰንም ወይም አለማመን አያጎድለንም፡፡ ፈተናው አለ፣ ግፊያው አለ፣ መከራውም አለ፤ ከዚያ የላቀ የተጋፈጡን ፊት በትእግስት የሚያጸናን የእግዚአብሄር ፍቅር ደግሞ እንዳንናወጥ በውስጣችን አለ፣ ስለዚህ ከእግዚአብሄር የሰማነውን ለመጠበቅ አናወላውልም፡፡
ሮሜ.5:2-5 ”በእርሱም ደግሞ ወደ ቆምንበት ወደዚህ ጸጋ በእምነት መግባትን አግኝተናል፤ በእግዚአብሔር ክብርም ተስፋ እንመካለን። ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ፥ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን፥ በመከራችን ደግሞ እንመካለን፤ በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም።”
በሌላ በኩል ፍቅር እንዲገዛው የፈቀደ ማንነት ተቆጣጣሪ አካል/ ወታደር በህይወቱ ውስጥ የሾመ ቆፍጣና ሰው እንደማለት ነው፡፡ ወታደር የስርአት ጠበቃ፣ የህግ አስከባሪና ክፉን ተዋጊ ሀይል ነው፡፡ በመንፈሳዊ ህይወታችን እንዲያ ያለ ወታደር ከሾምን ማንነታችን ውስጥ ክፉ እንዳይገባ፣ ገብቶ ከሆነም ስፍራ እንዳይኖረው፣ ስፍራ ከያዘም ስር እንዳይሰድ ስር ከሰደደ ደግሞ ተመችቶት እንዳያድግ አድጎም ፍሬ እንዳያፈራ ይሞግታል፣ ይዋጋል፣ ያጠፋል፡፡ በውስጣችን የፈሰሰ የእግዚአብሄር ፍቅር እንድምን ያለ ብርቱ ስራ ያደርግ (ፈቅደን ስለሾምነው እንዴት ያለ ስራ ይሰራ)? እንደምን ብርቱ የሆነ ትእግስተኛና በክፉው አለም የማይንበረከክ ሰው ያደርግ?
ጌታ አይዞአችሁ እኔ አለምን አሸንፌዋለሁ ያለው አሸናፊ ፍቅርን በውስጣችን እንደሚያፈስና እንደሚሰራን ስለሚያውቅ ነው፡፡ ጳውሎስም ያንን የፍቅር ብርታት ሲናገር ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? አለ፡፡ የፍቅር ወታደር ከፍቅር ጠላቶች ጋር ይዋጋል፡፡ የፍቅር ጠላቶች ቅንአት፣ አድመኝነት፣ መለያየት፣ ራስ ወዳድነት፣ የመሳሰሉ ናቸው፡፡ እነዚህ በሰው ውስጥ ደግመውና ደጋግመው የሚመጡ እያሳሳቱ የሚከሰቱ ያልያም የሚፈትኑ ናቸው፡፡ ክፋት ደግሞ አስጊ ጠላት ነው፡፡ ሲገባ አለሳልሶ ነው፤ አስቀድሞ ተራ ሆኖ ስለሚቀርብ ሳናስተውል እናስጠልለዋለን፣ በፍቅር ትእግስት ምክኒያት አመካኝቶ፡፡ ተቆርቋሪ ስለሚመስል ለእኛ ያደላና የጠቀመ ይመስላል፡፡ ደግሞ ደጋግሞ ሲከሰት ወደ አጥቂነት ይሸጋገራል፡፡ ውስጣችንን ሲያውክ ገና ያኔ እንረዳለን፤ ይህም ሲሆን ከመታገስ እናልፋለን፡፡ አይቆምም እሱ፣ ውስጣችንን በማሰቃየት ይቀጥላል፡፡ በፍቅር ሀይል ግን እርሱን መዋጋት ስንጀምር ምልልሱ ይገታል፡፡ እንዲሁም በፍቅር ውስጥ ያለ ትግስት እያገዘን ደጋግመን በውስጣችን የተቀመጠን ክፋት መዋጋት እንቀጥላለን፡፡ የጎዳንን ይቅር እያልን በዚያው የፍቅር ሀይል ሰውን መውደድ እንቀጥላለን፡፡ እምነት እያገዘን ሳናቁዋርጥ የምንታገልበት የፍቅር አሰራር ጉዳታችን የሚቀንስና በፍቅር ምክኒያት ያደረግነውን ትግል ውጤታማ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ በሚያበረታን በርሱ ያጥቃንን ጉዳት በይቅርታ እንቁዋቁዋመዋለን፤ ቢደግም ቢደጋግም በትእግስት እንይዘዋለን፤ ያ ካልበቃ ክፉውን በእምነት እንታገለዋለን፣ ፍቅር የሚሰጠን እምነት ጠንካራ ነውና ቶሎ ተስፋ አንቆርጥም፤ ደጋግሞ ሊጎዳን የሚታገለን ክፋትና አመጽ ሳያቆመን በቃሉ ላይ በተቀመጠልን ተስፋ ምክኒያት በፍቅር መታገሉን እንቀጥላለን፡፡
የእግዚአብሄር ተስፋ በፍቅር ውስጥ ያለውን ከፍ ያለ መለኮታዊ አሰራር ስለሚሞላም ብርታት ይሰጣል፡፡ እውነተኛ ድላችን የሚረጋገጠው በእርሱ ፍቅር የታጠቅነው የፍቅር አሰራር በእንዲህ ያለ መንገድ እኛን ወርሶ በጉልህ ሲገለጥ ነው፡፡ ድሉም በዚህ ሁሉ የጦርነት ደረጃ ውስጥ አልፎ የሚገኝ በመሆኑ ፍቅር ከምንም በላይ ከፍ ብሎ የሚቀመጥ ነው፡፡ የጌታ ኢየሱስ ፍቅር ከምንም በላይ በእኛ ይገለጥ፣ እንዲህ አድርጎ ይስራንም፡፡