የፍቅር ግዛቶች [4..]

የእውነት እውቀት

እግዚአብሄርን ለምን እንወደዋለን? መውደዱ ዋስትናችን ስለሆነ አይደለምን?
መዝ.145:20 “እግዚአብሔር የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል” ስለሚል፡፡
እንዲሁም እግዚአብሄር ውደዱ ያለን ነገር እንዳለ ሁሉ እንድንጠላው የሚፈልገው ነገርም አለ፡፡ ጥሉ ያለንን ነገር እግዚአብሄር በእኛ ዘንድ ሊያያቸው እንደማይሻ ከቃሉ መመልከት እንችላለን፡-
1ሳሙ.28:16-19 ”ሳሙኤልም አለ፡- እግዚአብሔር ከራቀህ ጠላትም ከሆነህ ለምን ትጠይቀኛለህ? እግዚአብሔርም በቃሌ እንደ ተናገረ አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም መንግሥትህን ከእጅህ ነጥቆ ለጎረቤትህ ለዳዊት ሰጥቶታል። የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህምና፥ በአማሌቅም ላይ ታላቅ የሆነ ቍጣውን አላደረግህምና ስለዚህ ዛሬ እግዚአብሔር ይህን ነገር አድርጎብሃል። እግዚአብሔርም እስራኤልን ከአንተ ጋር በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ይሰጣል፤ ነገም አንተና ልጆችህ ከእኔ ጋር ትሆናላችሁ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ጭፍራ ደግሞ በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ይሰጣል።”
እግዚአብሄር ወድዶት የነበረውን ንጉስ ለምን ጠላው? አጥፋቸው ያለውን ጠላቶቹን በህይወት ስላኖረና ቃሉን ስላልታዘዘ ነው የጠላው፡፡ ለሚከተለው እግዚአብሄር ሁሌም የሚናገረው ቃል አለው፣ እስከሰሙ ድረስ ለልጆቹ እንዲሁ ይናገራል፣ አልሰማም ካሉና ወደ አመጽ ካዘነበሉ ግን ላያገኛቸው ይርቃቸዋል፣ ቁጣውንም ያስከትልባቸዋል፡፡ እግዚአብሄር ሲርቅ መከራ ይዞ ከተፍ ለማለት የሰይጣን ፍጥነት ልዩ ነው፡፡ በዚያ ሁኔታ ስንሆን የእግዚአብሄር ምህረትና ጥበቃ ስለሚነሳ ህይወታችን ባዶ ሆኖ ወደ አደጋ ያመራል፡፡
የማይወደው ምን አለ?
1.ግፍን የሚያስቡና ሽንገላን የሚናገሩ ክፉ ሰዎች ያስቆጡታል፣ ሰዎች በእንዲህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው በፊቱ ሲመላለሱ ያዝናል፡፡
”ልጄ ሆይ፥ በክፉ ሰዎች አትቅና፥ ከእነርሱ ጋርም መሆንን አትውደድ፤ ልባቸው ግፍን ታስባለችና፥ ከንፈራቸውም ሽንገላን ትናገራለችና።” (ምሳ.24:1-2)
ግፈኞች ግፍ እንዳያስተላልፉበት፣ ሸንጋዮች የሸንገላን ባህሪ እንዳያለማምዱት፣ክፉዎችም ወደ ክፋት መርተው በእግዚአብሄር እንዳያስቆጡት ሰው ከነዚህ ሰዎች አካባቢ ዞር ማለት ይገባዋል፡፡ ኃጢአተኛ እግዚአብሔርን ስለሚያበሳጭ በጎ ምሳሌ የለውምና በእርሱ አትቅና፤ ግፈኛ ነው፣ በእርሱ ፊት እግዚአብሔር የለም። ጻድቅ ሰው ለምን መንገዱ ወደ ረከሰ አለማዊ ሰው ያዘነብላል? ይህ ሰው በፊቱ ቅን ፍርድ የለውምና፡፡ ክፉ ሰው በልቡ ደንዳናነት መልካም ገጥሞኛል፣ ኑሮ ተሳክቶልኛል፣ እኔም ትውልዴም ክፉ አያገኘንም ሲል ራሱን ይሸነግላል፡፡ እግዚአብሄርን የሚያስከፋ ሰው አፉ መርገምንና ሽንገላን ተንኰልንም የተመላ ነው፤ ከምላሱ በታች ጉዳትና መከራ ነው ያለው ሲል ቃሉ ያጋልጠዋል። እንግዲህ የተጠጉት በንክሻው ይደማሉ፣ በሰወረው ወጥመዱ ላይ ይወድቃሉ፡፡ እግዚአብሄር ግን ይህን ሰው ስለሚመለከተው በቁጣው ይገለጥበታል፡፡(መዝ.10:4)
2.የእግዚአብሄር ልጆች በጣኦት አምልኮ ውስጥ ሲገቡ እግዚአብሄር ይጠላቸዋል
2ነገ.17:20-23”እግዚአብሔርም የእስራኤልን ዘር ሁሉ ጠላ፥ አስጨነቃቸውም፥ ከፊቱም እስኪጥላቸው ድረስ በበዝባዦች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው።እስራኤልንም ከዳዊት ቤት ለየ፤ የናባጥንም ልጅ ኢዮርብዓምን አነገሡ፤ ኢዮርብዓምም እግዚአብሔርን ከመከተል እስራኤልን መለሰ፥ ታላቅም ኃጢአት አሠራቸው። የእስራኤልም ልጆች ኢዮርብዓም ባደረገው ኃጢአት ሁሉ ሄዱ፤እግዚአብሔርም በባሪያዎቹ በነቢያቱ ሁሉ አፍ እንደ ተናገረው እስራኤልን ከፊቱ እስኪያወጣ ድረስ ከእርስዋ አልራቁም። እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከምድሩ ወደ አሦር ፈለሰ።”
እግዚአብሄርን ለመውደድ ስንመኝ የሚጠላቸውን ማወቅ፣ ማስተዋልና ሙሉ እውቀት ማግኘት ይገባናል፡፡ የእስራኤል ዘር ሊያውም ለእግዚአብሄር ህዝብነት የተመረጠ ዘር በእግዚአብሄር መጠላቱ እጅግ አስፈሪ ክስተት ነው፡፡ ህዝቡ እግዚአብሄር የሰጣቸውን ምድር በግፍና በአመጽ ሞልተው በማሰጨነቃቸው በፈንታው እግዚአብሄር አስጨነቃቸው፥ ከፊቱም እስኪጥላቸውና አጋዥ እስኪያጡ ድረስ በበዝባዦች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፣ ለውርደትም ዳረጋቸው።
ኢሳ.44:9-10”የተቀረጸውን ምስል የሚሠሩ ሁሉ ከንቱዎች ናቸው፥ የወደዱትም ነገር አይረባቸውም፤ ምስክሮቻቸውም አያዩምና አያውቁም፤ ስለዚህ ያፍራሉ። አምላክን የሠራ ወይስ ለምንም የማይረባ ምስልን የቀረጸ ማን ነው?”
እግዚአብሄር መልካምና ቸር በመሆኑ ነው ክፋትን በልጆቹ ዘንድ ማየት የማይሻው፤ የክፋት መሰረትና ስር የሆኑትን ሰዎች እንዲሁ ስለማይታገሳቸው ከነርሱ እንርቅ ዘንድ ይሻል፡፡ ያእቆብ በእግዚአብሄር የተወደደ፣ በአላማ የተጠራና የተስፋ ቃል የተሰጠው ሰው ነበር፡፡ እርሱ ከእግዚአብሄር ጋር ተጣብቆ በመልካም ህይወት ወደ አምላኩ የተሰበሰበ ቢሆንም ዘሮቹ ግን የአባታቸውን ራእይ ይዘውና የጠራቸውን አምላክ ተከትለው የሚጉዋዙ አልሆነም፡፡ የጠሉዋቸውን አህዛብ ወድደውና የወደዳቸውን እግዚአብሄር ቸል ብለው ከጣኦታት ጋር መጣበቅ ስለመረጡ እግዚአብሄር ተቆጥቶ ከፊቱ ጥሎአቸዋል፤ ለጠላቶቻቸው ግፍም አሳልፎ ሰጥቶአቸዋል፡፡
3.ክፉ ድርጊቶች ሁሉ በፊቱ የተጠሉ ናቸው
መዝ.5:4-6 ”አንተ በደልን የማትወድድ አምላክ ነህና፤ ክፉ ከአንተ ጋር አያድርም። በከንቱ የሚመኩ በዓይኖችህ ፊት አይኖሩም፤ ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ጠላህ። ሐሰትን የሚናገሩትን ታጠፋቸዋለህ፤ ደም አፍሳሹንና ሸንጋዩን ሰው እግዚአብሔር ይጸየፋል።”
ንጉስ ዳዊት እግዚአብሄር ሀጢያትን የሚጸየፍ አምላክ እንደሆነ አውቆአል፡፡ እግዚአብሄር በባህሪው ቅዱስ በመሆኑ አመጸኞችን እንደማይታገስ ሲያይ በከንቱ የሚመኩ በዓይኖችህ ፊት አይኖሩም፤ ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ጠላህ አለ። እግዚአብሄር መሀሪ ነው፣ ሆኖም ጨካኞችን ሲያይ ይቆጣል፡፡ የፈጠረውን ፍጥረት የሚወድ አምላክ ሰው በገዛ ስራው ሲጠላለፍ አይደሰትበትም፡፡ አመጸኞች እግዚአብሄርን ይጠላሉ፣ ይህ ተግባራቸው ግን ማለቂያ በሌለው መከራና ጥፋት ውስጥ ይከታቸዋል፡፡ የእግዚአብሄር ህዝብ ግን በመታዘዝ ሲያድግ፣ ከሀጢያት ሲርቅ፣ በስምም ሲኖርና በመቀባበል ሲመላለስ እግዚአብሄር በቤተክርስቲያን ይከብራል፡፡ ነፍሳት ወደ ጌታ ደስታ የሚመጡት የእግዘአብሄር መንፈስ በህዝቡ መሀል ሲሰራ ነው፡፡ ቅዱሳን እግዚአብሄርን አክብረው ያስከብራሉ፣ በጥልና በንትርክ ሲዋጡ ግን ነውር ይስባሉ፡፡ በሀጢያት መጨከን እንጂ አንዱ በሌላው ላይ እንዲያ ሊሆን አልተጠራም፡፡ በቤተክርስቲያን ውስጥ ዘላቂ እድገትና በረከት የሚያብበው ደቀመዛሙርት ራሳቸውን ለእግዚአብሄር መንፈስ ሲያስገዙ እንዲሁም በቃሉ ሲመሩ ነው፡፡
4.ላመፁና ቅዱስ መንፈሱን ላስመረሩ ተመልሶ ጠላት ሆናቸው
ኢሳ.63:7-10 “እግዚአብሔር እንደ ሰጠን ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን ቸርነትና የእግዚአብሔርን ምስጋና፥ እንደ ምሕረቱና እንደ ቸርነቱም ብዛት ለእስራኤል ቤት የሰጠውን ትልቅ በጎነት አሳስባለሁ።እርሱም፡- በእውነት ሕዝቤ፥ ሐሰትን የማያደርጉ ልጆች፥ ናቸው አለ፤ መድኃኒትም ሆነላቸው።በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ፥ የፊቱም መልአክ አዳናቸው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው፥ በቀደመውም ዘመን ሁሉ አንሥቶ ተሸከማቸው።እነርሱ ግን ዐመፁ ቅዱስ መንፈሱንም አስመረሩ፤ ስለዚህ ተመልሶ ጠላት ሆናቸው፥ እርሱም ተዋጋቸው።”
እግዚአብሔር እንደ ሰጠው ቸርነትና ትልቅ በጎነት መጠን እስራኤል አላመሰገነም፣ እርሱ ግን የሰራላቸውን ስራ እያነሳ በፍቅር ያሳስባቸው ነበር፤ ህዝቡ የዘነጋውን በቀደመው ዘመን ለአባቶቻቸው የሰራውን እንዲያስታውሱና እንዲመለሱ ይናገራቸው ነበር፤ እርሱ ቅዱሱን መንፈስ በመካከላቸው አኑሮ እንደመራቸው፣ በሙሴ ቀኝ የከበረ ክንዱን ያስሄደ እርሱ እንደነበር፣ ለራሱም የዘላለምን ስም ያደርግ ዘንድ ውኃውን በፊታቸው ከፍሎ እነርሱን እንዳሻገረ፣ በምድረ በዳም እንደሚያልፍ ፈረስ፥ በቀላይ ውስጥ ያለ ዕንቅፋት እንዳሳለፋቸው ያስታውሱ ዘንድ ነገራቸው፡፡
ሕዝቤ ላለው እስራኤል መድኃኒት ሆኖላቸዋል፤ የርህራሄው ብዛት በጭንቃቸው ሁሉ እንዲጨነቅ አድርጎታል፤ በድካማቸው ውስጥ ሆነው ሲያያቸው በፍርድ ሳይሆን በርህራሄ ረዳቸው፣ ሳይጠፉም ወዲያውም የፊቱን መልአክ ልኮ አዳናቸው፤ የምድረ-በዳ ስቃይ ሳይውጣቸው በፍቅሩና በርኅራኄው ተቤዣቸው፥ በቀደመውም ዘመን ሁሉ አንሥቶ እንደዚህ ተሸከማቸው። እነርሱ ግን ምን አደረጉ? ዐመፁ! ቅዱስ መንፈሱንም ባለመታዘዝ አስመረሩ! ስለዚህ ሊያድን፣ ሊመራና ሊያበረታ የመጣው መንፈስ ተመልሶ ጠላት ሆናቸው፥ እርሱም ተዋጋቸው።
5.በዚህም ዘመን በቤተክርስቲያን ውስጥ አይቶ የማይደሰትባቸው ነገሮች አሉ
እነዚህ ነገሮች ከፍቅር ጋር በአብሮነት ሊጉዋዙ የማይችሉ ናቸው (1ቆሮ.13:1-13)፡፡
• መንፈሳዊ ነገር ሲበዛልን ጸጋ ተገልጦ በህይወታችን በሀይል ይሰራል፡፡ መንገዳችን በብዙ ተሰርቶ፣ የጸሎት ጸጋ በዝቶልን በሰዎችና በመላእክት ልሳን እስከመናገር እናድጋለን፡፡ ነገር ግን በቅርብም በሩቅም ካሉ ሰዎች ጋር ያለን ቅርበት ፍቅር ጎድሎታል? ያ ከሆነ በእኛ ዘንድ ያለው የጸሎት ህይወት ምንም እንኩዋን በሰዎችና በመላእክት ልሳን እስከመናገር የደረሰ ቢሆንም እግዚአብሄር እርሱን እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል አድርጎ ብቻ ያየዋል እንጂ በሞገስ አይቀበለውም።
• ማህበሩን የሚያንጽ ትንቢት መናገር በእግዚአብሄር ቃል ውስጥ ያለውን ምሥጢር ሁሉና መንፈሳዊ እውቀትን ሁሉ ማወቅ ምንም ቢሰጠኝ፣ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ ጠንካራ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ እንደ እግዚአብሄር ቃል በሆነ መውደድ ሰውን የምወድበት ፍቅር ግን ከሌለኝ ባዶ ወይም ከንቱ ሆኜ በእግዚአብሄር ፊት የምቆጠር ነኝ።
• የርህራሄ መንፈስ በዝቶልኝ ድሆችን ልመግብ፣ ያለኝንም ሁሉ ላካፍል፣ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ልሰጥ የሚያስችል ጸጋ በዝቶልኝ ብመላለስም ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።
እግዚአብሄር በመንፈስ ቅዱስ በልባችን የሚያፈሰው ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፣ አይከስምም፡፡ የተቀበልናቸው ነገሮች ሁሉ የሚሻሩ ናቸው፡-ትንቢት ቢሆን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል። ምክኒያቱም እነዚህን ሁሉ በሙላት አልተቀበልናቸውም፤ ስለዚህ ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና ከትንቢትም ከፍለን እንናገራለንና፤ ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ተከፍሎ የነበረው ይሻራል። ዛሬ የምናውቀው ከእውቀት ከፍለን ነው፣ በዚያን ጊዜ ግን እኛም ደግሞ እንደ ታወቅን አናውቃለን። እግዚአብሄር ግን የማይሻርና የሚጸና ፍቅሩን በመንፈስ ቅዱስ አፍስሶልናልና ፍቅር እንደ እምነትና ተስፋ ጸንቶ ይኖራል።
በእግዚአብሄር የተወደደ ነገር
1. ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ እግዚአብሔር ይወዳል
1ጢሞ.2:1-2 “እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር፥ ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ። ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው።አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው”
ደቀመዛሙርት ጸላይ ወገኖች እንዲሆኑ እግዚአብሄር ይፈልጋል፡፡ ቤተክርስቲያን ለሰዎች እንዲሁም ላለለችበት ስፍራ ሁሉ ሰላምን፣ እረፍትን፣ ምህረትንና በረከትን እንድትለምን፣ ሰዎች ከሚመጣው ጥፋት ይድኑ ዘንድ ከዲያቢሎስ መንግስት ወደ እግዚአብሄር መንግስት እንዲፈልሱ በጸሎት እንድታግዝ፣ ለሰዎች በደል፣ ሀጢያትና ጥፋት መማለድ እንዲኖርባት ቃሉ ያዛል፡፡ በዚሀ መንገድ ሰዎች ወደ እግዚአብሄር እንዲቀርቡና እንዲድኑ እግዚአብሄር ፈቃዱ ሆኖአል፡፡ ቤተክርስቲያን በቃልም ይሁን በስራ የምታደርገው ሁሉ በኢየሱስ ስም ሲሆን የስሙ ሀይል ስጦታውን ማለትም ሰዎች እንዲድኑ የቆረሰው ስጋውና ያፈሰሰው ደሙ እንደሚሰራ አምና ሊሆን ይገባል፡፡
2.ሰዎችን መቀሰፍ፣ ማጥፋት ሳይሆን መማር ይወዳል
ሚክ.7:18-20 “በደልን ይቅር የሚል፥ የርስቱንም ቅሬታ ዓመፅ የሚያሳልፍ እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? ምሕረትን ይወድዳልና ቍጣውን ለዘላለም አይጠብቅም። ተመልሶ ይምረናል፤ ክፋታችንንም ይጠቀጥቃል፥ ኃጢአታችንንም በባሕሩ ጥልቅ ይጥለዋል።ከቀድሞ ዘመን ጀምረህ ለአባቶቻችን የማልህላቸውን እውነት ለያዕቆብ፥ ምሕረትንም ለአብርሃም ታደርጋለህ።”
እግዚአብሄር የበደለውን ሰው ከሚገባው ቅጣት አስመልጦ በህይወት ማኖሩ የቸርነቱ መገለጫ ነው፤ ሀጢያት በእግዚአብሄር ዘንድ አጸያፊ ነው ግን በሰፊው ትእግስቱ ሀጢያተኛውን ይምረዋል፡፡ የሰውን ጭንቀት፣ መከራ፣ ዋይታና ዘላለማዊ ቅጣት ቀድሞ ስለሚያይ ያ ሳይመጣ አስቀድሞ ተው እያለ፣ እምቢ ብሎ ሲሸሸው እየተከተለ፣ እየጠበቀ፣ እየከለለ በብዙ ትእግስት የምህረት ስራን ሲሰራ ይታያል፡፡ በዘላለም ምህረት ሊሰራ ያለውን ስራ በማመልከት እርሱ በክርስቶስ ደም በጥምቀት ውስጥ የሀጢያት ስርየትን እንደሚሰጥ በነቢዩ አፍ ሲናገር እናያለን፡፡ ይህም እግዚአብሄር እኛን በመማር እንጂ በማጥፋት እንደማይደሰት ያመለክታል፡፡
መዝ.37:28-29 “እግዚአብሔር ፍርዱን ይወድዳልና፥ ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና፤ ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል ለንጹሓንም ይበቀልላቸዋል፤ የኅጥኣን ዘር ግን ይጠፋል።ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፥ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።”
3.ፈጣሪን መውደድ
ማር.12:28-30 “ከጻፎችም አንዱ ቀርቦ ሲከራከሩ ሰማና መልካም አድርጎ እንደ መለሰላቸው አስተውሎ። ከሁሉ ፊተኛይቱ ትእዛዝ ማናቸይቱ ናት? ብሎ ጠየቀው።ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፡- ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፡- እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።ሁለተኛይቱም። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም።”
– እግዚአብሄር እርሱ ብቻ መውደድ ያለበት ሳይሆን ከማንም አስቀድሞና አስበልጦ መወደድ እንዳለበት ቃሉ ያስተምራል፡፡
– ህዝቡ እስራኤል እግዚአብሄርን አጥብቆ እንዲሰማ ያሳስባል፣ እንዲህ ሲል፡- ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው ብሎ፡፡ እግዚአብሄር አንድ ነው፣ ዙፋኑም አንድ ነው፡፡ መንግስቱ አንድ ነው፣ አካሉም አንድ ነው፡፡ መንገዱ አንድ ነው…. ህዝቡም ሳይቀር አንድ ነው፡፡
1ነገ.22:19 “ሚክያስም አለ፡- እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ።… ”