የፍቅር ግዛቶች [2…]

የእውነት እውቀት

ስለ ፍቅር፡-
ፍቅር የሚባል ስጦታ ከመለኮት የመነጨና ልዩ ባህሪ ያለው፣ ከነገሮቻችን መሀል ከፍ ያለ የተሰጠን የማንነታችን ገዢ ነው፡፡ እግዚአብሄር የሰጠን ፍቅር ጥልቅ በመሆኑ አእምሮን ያልፋል፣ የልብ ፈቃድን ያልፋል፣ የነፍስ ምኞትን ያልፋል፣ ከመንፈስ ይዘትም ይልቃል፡፡ የእግዚአብሄር ፍቅር ሲገባ ሁሉ ነገራችንን ያሸንፋል፣ ይቆጣጠራልም፡፡ እውነተኛ ፍቅር ልብ፣ አእምሮና አሳብን በመግዛትና ወደ ፈለገው አቅጣጫ በመምራት የደስታ ስሜትን በሁለንተናችን ያፈልቃል፡፡ ያኔ ሰውን ስናፈቅር በስሜት ተሞልተን ነው፤ በማየት መውደድ፣ በማሰብ መውደድ፣ በመናገር መውደድና ስሜቱን በመጋራት መውደድ ተቆጣጥሮን ነው፡፡
የእግዚአብሄር ፍቅር ከምናስበውና ከምንናገረው በላይ ይልቃል፣ በብዙ ዘርፍም ይገለጣል፡- በማመን ውስጥ ባለ መውደድ፣ በማምለክ ውስጥ ባለ መውደድ፣ እንዲሁም በመገዛት ውስጥ ባለ መውደድም ይታያል፤ አንድ ነህ በማለት፣ አንተ ብቻ አምላክና ፈጣሪም ነህ በማለት ይጸናል፡፡ እግዚአብሄር አሳምሮ ሰራኝ ብሎ ራስን መውደድ፤ ባልንጀራንም ስጋዬ ብሎ እንደራስ መውደድ በሰው ዘንድ እንዲቻል ያደርጋል፡፡ ስለመንግስተ ሰማይ፣ ስለ ወንድም፣ ስለጌታ መስዋእት፣ ስለቃሉ፣ ስለጸሎት፣ ስለጾም፣ ስለ መገዛትና ስለመሳሰሉ እውቀቶች ያስገነዝባል፤ በማሳወቅ ውስጥም ማስተዋልን በመፍጠር ህይወትን በሰላም ያትማል፡፡
ሰው ስለመኖሩ ብቻ የሚደሰተው፣ መከራ ውስጥ፣ ህመም ውስጥ ሆነ ችግርና ፈተና ውስጥ ሆኖም ልቡ ወደ ፍቅር የሚዘነብለው  የእግዚአብሄር ፍቅር አስቀድሞ ልቡን ሲሞላ ነው፡፡ የእናትና አባት ፍቅር፣ የቤተሰብ ፍቅርም ሆነ የባልንጀራሞች ፍቅር ህልውናው መሰረቱ እዚህ የእግዚአብሄር ፍቅር ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ መኖር የተመሰረተው በእግዚአብሄር መኖር እስከሆነ ድረስ ሰው በፍቅር እርስ በርሱ የሚተሳሰረው እርሱ በሰጠው ፍቅር ምክኒያት ነው ማለት ነው፡፡
ጾታዊ ፍቅርን በተመለከተ፡-
ጅማሬው የአዳምና የሄዋን መፈጠር ነው፡፡ በእርግጥ የእነርሱ ፍቅር ጾታዊ እንደመሆኑ በሁለቱ መሀል የተወሰነ ነው፡፡ በዚህ ፍቅራቸው ምክኒያት በስሜታቸው፣ በአሳባቸውና በአብሮነታቸው የሚደሰቱና የሚተሳሰሩ ናቸው፡፡እንዲህም ሆኖ ግን ገዢ የሆነና ከነርሱ በላይ የሆነው መለኮታዊ ፍቅር በመሃላቸው ያለ ነበር፡፡
እግዚአብሄር በውስጣቸው በፈጠረው ፍቅር ምክኒያት ሁለቱም በንጹህ ህሊና የሚዋደዱ ሰዎች ነበሩ፡፡ አዳም ለሄዋን ያለው የመውደድ ይዘት ግን ለልጆቹ ካለው ፍቅር የተለየ ነበር፤ ያን ያደርገው ደግሞ ከርሱዋ ጋር የነበረው አካላዊና ስነልቦናዊ መተሳሰር ነው፣ ይህ ቃልኪዳንም ያለው ነው (ማቴ.19:4)፡፡
​​​​​​​​በመሃላቸው የነበረው ይህ ፍቅር ይዘቱ ንጹህ ሆኖ (ጥርጥር፣ አመጽ፣ ቅናትና የመሳሰለው ሳይኖርበት) የቀጠለው እነዚህ ጥንዶች በሀጢያት ከመውደቃቸው በፊት ብቻ እንደነበር ማስታወስ ይገባል፡፡ ቆይቶ ሁኔታዎች በተለወጡ ጊዜ ሀጢያት ወደ አለም ገባና ያ ንጹህና ቅንነት ያለበት ጾታዊ ፍቅር ሊረክስ ቻለ፡፡ በዚያም አላበቃም፣ ሀጢያት በሁለቱ አለመታዘዝ ምክኒያት በመጽናቱ የአለም መልክ ሌላ ሆኖ ተቀየረ፤ አለምን በሰላምና በስርአት ያስተሳሰረ መለኮታዊ እቅድ ሳይቀር በዚያ ያለመታዘዝ ተበላሸ፡፡ ውጤቱ የሰው ልጆች ግንኙነትን (በሁሉም መስክ ያለውን ግንኙነት) አርክሶአል፡፡
ዛሬ በአለም የምናየው ጾታዊ ፍቅር ዘቅጦ በመውረዱ ዝሙት፣ ግልሙትናና ሴሰኝነት በሰፊው የተንሰራፋ ነው፡፡ እነዚህ ልማዶች ሰይጣን በእውነተኛው ጾታዊ ፍቅር መሀል ያስገባቸው ጥፋቶች በመሆናቸው መለኮታዊ ትዛዝን የሚተላለፉ ከባድ አመጾች ሆነዋል፡፡ ቃሉ ከዓመፃ ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች​​​​​​​​ (ማቴ24:12) ስላለ አመጹ በሁሉም አቅጣጫ ተሰራጭቶ እግዚአብሄር የሰጠውን ፍቅር እያቀዘቀዘ ስጋዊ፣ አለማዊና የነዋይ ፍቅርን በሰው ልብ ሊዘራ በቅቶአል፡፡
በመጨረሻው ዘመን ያለ የተጋቢዎች ዝንባሌ እግዚአብሄር በሰጠው የትዳር ቃል-ኪዳን ላይ የተነሳ ነው፡፡ እንዲያውም እግዚአብሄርን እንፈራለን የሚሉ ሳይቀሩ ፍቺን ሲያከናወኑ (እግዚአብሄር በቃል-ኪዳን ያሰረውን ቁዋጠሮ ለመፍታት) ብዙም ያዳገታቸው አልሆነም፡፡ ይህ ድፍረት ግን የትውልድ ዝቅጠትን እየጨመረ ነው (እግዚአብሄር በምህረቱ የከለከለውን ቁጣ እየሳበ ነው)፡፡
​​​​​​​​ማቴ.19:3-12 ”ፈሪሳውያንም ወደ እርሱ ቀረቡና ሲፈትኑት፡- ሰው በሆነው ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን? አሉት።እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አለ፡- ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፥ አለም፡- ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን? ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው። እነርሱም፡- እንኪያስ ሙሴ የፍችዋን ጽሕፈት ሰጥተው እንዲፈቱአት ስለ ምን አዘዘ? አሉት።እርሱም፡- ሙሴስ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ ፈቀደላችሁ፤ ከጥንት ግን እንዲህ አልነበረም።እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል አላቸው። ደቀ መዛሙርቱም፡- የባልና የሚስት ሥርዓት እንዲህ ከሆነ መጋባት አይጠቅምም አሉት። እርሱ ግን፡- ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም፤ በእናት ማኅፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ፥ ሰውም የሰለባቸው ጃንደረቦች አሉ፥ ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ። ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው አላቸው።”
በመጨረሻው ዘመን የሰው ዘር በምድር እየበዛ ሲሄድ ምን እየሆነ ነው? በግልጽ እንደሚታየው በጎነት እየተመለሰ ሳይሆን አመጽ እያደገና እየሰፋ ነው፤ እግዚአብሄር በአዳምና በሄዋን ህይወት ያስቀመጠው ጾታዊ ፍቅር እየተደለዘ (ባህሪው እየተቀየረ) አዳም ከአዳም፣ ሄዋንም ከሄዋን ጋር በአመጽ መንፈስ ተሳሰረው ሲጎመጁ ወደሚያጸይፍ ግንኙነት ተላልፈዋል፡፡ አለምም በዚህ ተግባር በመጥለቅለቁዋ አስፈሪ ፍርድ ውስጥ ገብታለች፡፡ ቃሉ በ​​​​​​​​ሮሜ.1:22-28 ውስጥ ሲናገር፡-
”ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ፥የማይጠፋውንም የእግዚአብሔር ክብር በሚጠፋ ሰውና በወፎች አራት እግር ባላቸውም በሚንቀሳቀሱትም መልክ መስለው ለወጡ። ስለዚህ እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ እግዚአብሔር በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵስነት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም የእግዚአብሔርን እውነት በውሸት ስለ ለወጡ በፈጣሪም ፈንታ የተፈጠረውን ስላመለኩና ስላገለገሉ ነው፤ እርሱም ለዘላለም የተባረከ ነው አሜን። ስለዚህ እግዚአብሔር ለሚያስነውር ምኞት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ ወንዶችም በወንዶች ነውር አድርገው በስሕተታቸው የሚገባውን ብድራት በራሳቸው ተቀበሉ።እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው”
በወንድ ለወንድና ሴት ለሴት ፍትወት መቃጠል ምክኒያት አለም እንዴት የማይፈታ ፍርድ ውስጥ መግባት እንደቻለች የምናስተውል መነሻ ከሆነው አንድ አዳም ለአንድ ሄዋን ተገቢነት ያለው መፈላለግና መጣበቅ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባናል፤ በተለይ በዚህ ፍጻሜ ዘመን፡፡
በጊዜው ላይ የተገለጠውን ክፉ አካሄድ ለማምለጥ የቃሉን ምክር አጥብቆ መያዝም ተገቢ ነው፡፡ በ​​​​​​​​ኤፌ.5:28-33 ውስጥ ሲናገር ፡-
” እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፥ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል ይከባከበውማል። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ።ሆኖም ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት፥ ሚስቱም ባልዋን ትፍራ።”

  • የቤተሰብ ፍቅር

አስቀድሞ እንዳየነው ይህ ፍቅር በቤተሰብ መሀል የሚፈጠርና መዋደድን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ የፍቅሩ ጉልበት በእናትና በልጆች፣ በአባትና በልጆች እንዲሁም በወንድምና በእህት መሀል የሚሰራና የሚያስተሳስር ነው፡፡ የቤተሰብ ፍቅር በእናትና በአባት መሃል ካለ ፍቅር ላይ የሚደረብ ፍቅር ነው፡፡ የቤተሰብ ፍቅር የወላጆችን ፍቅር ሊደመስስ ወይም ሊከፍል አይገባም፡፡ እናትና አባት በመሀከላቸው ያለውን ፍቅር ልጆቻቸው ላይ ካላቸው መውደድ ጋር በአብሮነት ማሰኬድ ይችሉ ዘንድ በማስተዋል መራመድ አለባቸው፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎች አስገዳጅነት አንደኛው ወላጅ ፍቅሩን ወደ ልጆች ያዘነብላል፡፡ ያም ኩርፊያና ተስፋ መቁረጥ በሌላኛው በኩል ስለሚፈጥር በቤተሰብ መሀል ክፍተትን ያመጣል፡፡
በአለም ላይ ከሚሆነው በተቃራኒ የወላጆች ፍቅር በልጆች ፍቅር የሚፋፋ እንጂ የሚጠፋ መሆን የለበትም፡፡ ወላጆች በፍቅራቸው መሀል ልጆች ሲያፈሩ ሌላ ደስታና ፍቅር (በእርግጥ ሸክም ጭምር የሆነውን) ያገኛሉ፡፡ ወላጆች አሁን ልበ-ሰፊና ታጋሽነትን ጨምረው ከፍ ወዳለ የፍቅር ይዘት ውስጥ ሊገቡ ነው ማለት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ግን በታጋሽነት ፈንታ ግዴለሽነት ሲተካ፣ ሸክምን በመከፋፈል ፈንታ ለአንዱ በተለይ ለእናት ብቻ ሲተው ፍቅር ድርብርብና አስደሳች መሆኑ ይቀርና እንደ እዳ ሆኖ የወላጅን ፍቅር ሳይቀር ያደክማል፡፡
እናትና አባት ልፋታቸውን በፍቅር ካልደገፉ ቤተሰባቸውን ያውካሉ፤ ልጆች እርስ በርስ በመዋደድና በመተሳሰብ እንዳይተሳሰሩም እንቅፋት ይሆናሉ፤ ይህ ችግር በተለይ በታዳጊው አለም (የባሎች አምባገነንነት በሚያይልበት አለም በሙሉ) የሚታወቅ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ስለዚህ የቤተሰብ ፍቅር እንዳይቀጭጭ ከጾታዊ ፍቅር ጋር አብሮ ማስኬድና የቤተሰብን ሚዛን መጠበቅ ተገቢ ነው፤ እንደዚህ ካልተጠበቀ ፍቅር ይንገዳገዳል፤ ወድቆም ፍቺ (የቤተሰብ መበተን) ይከተላል፡፡
​​​​​​​​ኤፌ6:1-4” ልጆች ሆይ፥ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፥ ይህ የሚገባ ነውና። መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት። እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው።”
​​​​​​​​ቲቶ2:4-5” ቆነጃጅትም የእግዚአብሔር ቃል እንዳይሰደብ፥ ባሎቻቸውን የሚወዱ፥ ልጆቻቸውን የሚወዱ፥ ራሳቸውን የሚገዙ፥ ንጹሖች፥ በቤት የሚሠሩ፥ በጎዎች፥ ለባሎቻቸው የሚታዘዙ እንዲሆኑ ይምከሩአቸው።”

  • የባልንጀራሞች ፍቅር

ብዙ ጊዜ ባልንጀርነት በአጋጣሚ በሚመስል ትውውቅ ይጀምርና ወደ ጠበቀ ግንኙነት ያድጋል፡፡ የተዋወቁ ሰዎች ልብ ለልብ ሲግባቡ ወደዚህ ፍቅር ውስጥ ይገባሉ፡፡ ይህ ፍቅር የሚመጣው ከቤተሰብ ውጪ ባለ ግንኙነት በመሆኑ ቢጤዎች (በአሳብ፣ በስሜትና በባህሪ የሚቀራረቡ) የልባቸውን ሰው ሲያገኙ ወደዚህ ፍቅር ይገባሉ፡፡ ይህ ፍቅር ምስጢርንና በቤተሰብ ሊዳሰስ የማይችል ችግርን ተካፋይ በመሆኑ ከሌሎቹ በተለየ ጠንካራ ነው፡፡ የዮናታንና የዳዊት ፍቅር እንደዚያ ከቤተሰባቸው ፍቅር የላቀ ነበር፤ ምስጢር ተካፋይነት ነበረበት፤ ቃልኪዳንና እስከትውልድ ተሸጋሪ ትስስርን ፈጥሮ የነበረ በመሆኑም ልዩ ነበር፡፡ ዮናታን በጦርነት ከሞተ ከጊዜ በሁዋላ እንኩዋን ዳዊት ወዳጁን አስታውሶ ድሮ የተገባቡትን ቃልኪዳን ሊፈጽም ሲሻ እናያለን፡-
2ሳሙ.9:1-7 ”ዳዊትም፡- ስለ ዮናታን ቸርነት አደርግለት ዘንድ ከሳኦል ቤት አንድ ሰው ቀርቶአልን? አለ። ከሳኦልም ቤት ሲባ የሚባል አንድ ባሪያ ነበረ፥ ወደ ዳዊትም ጠሩት፤ ንጉሡም። አንተ ሲባ ነህን? አለው። እርሱም፡- እኔ ባሪያህ ነኝ አለ።ንጉሡም፡- የእግዚአብሔርን ቸርነት አደርግለት ዘንድ ከሳኦል ቤት አንድ ሰው አልቀረምን? አለ። ሲባም ንጉሡን፡- እግሩ ሽባ የሆነ አንድ የዮናታን ልጅ አለ አለው።ንጉሡም፡- ወዴት ነው? አለው፤ ሲባም ንጉሡን፡- እነሆ፥ እርሱ በሎዶባር በዓሚኤል ልጅ በማኪር ቤት አለ አለው።ንጉሡም ዳዊት ልኮ ከሎዶባር ከዓሚኤል ልጅ ከማኪር ቤት አስመጣው።የሳኦልም ልጅ የዮናታን ልጅ ሜምፊቦስቴ ወደ ዳዊት መጣ፥ በግምባሩም ወድቆ እጅ ነሣ፤ ዳዊትም፡- ሜምፊቦስቴ ሆይ፥ አለ፤ እርሱም፡- እነሆኝ ባሪያህ አለ።ዳዊትም፡- ስለ አባትህ ስለ ዮናታን ቸርነት ፈጽሜ አደርግልሃለሁና አትፍራ፤ የአባትህንም የሳኦልን ምድር ሁሉ እመልስልሃለሁ፥ አንተም ሁልጊዜ ከገበታዬ እንጀራ ትበላለህ አለው።”
የፍቅር ሚዛናዊነት
በተለያየ መልኩ ያየነው ፍቅር አንድ ትልቅ ነገር የሚያሳየን ነው፤ ይሀውም ሰው በፍቅር ላይ ያለው መደገፍና ፍቅር በርሱ ህይወት ላይ የሚያሳድራቸው ተጽእኖ ናቸው፡፡ በዚህ ውጥንቅጡ በወጣ አለም ውስጥ ያለው የኑሮ ተጽእኖ እጅግ ከባድና ውስብስብ ቢሆንም ሰው ነገን በተስፋ ይኖር ዘንድ ብርታት እንዲያገኝ ካደረጉ ነገሮች ዋነኛው የፍቅር መኖር ነው፡፡ ይህን የእግዚአብሄር ስጦታ ሰው በአግባቡ እስካስቀጠለው ድረስ የሰው በጎነትም የተረጋገጠ ነው፡፡ ቃሉ ግን በመጨረሻው ዘመን በአለም ላይ ፍቅር እጅግ እንደሚቀዘቅዝ ያመለክታል፡፡ ስለዚህ ፍቅርን በትዳርም፣ በቤተሰብም ሆነ በባልነጀራሞች መሀል ጠብቆ ለማቆየት የግድ ወደ እግዚአብሄር ትእዛዝ ማዘንበል ለአለም ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡
እግዚአብሄር እርሱን መውደድ ይስጠን፣ በእርሱ መውደድ በኩል የባልንጀራን ይጨምርልን፡፡ በጎ ምኞት!