የፍቅር ግዛቶች [1…]

የእውነት እውቀት

የፍቅርን ጉልበት ሊረታ ማን ይችላል?
በሀይል ያልተደፈረ ጀግና ስለፍቅር እጅ ሲሰጥ በሶምሶም ታሪክ ውስጥ የምናየው ነው፤ የህዝብ ታላላቆችም ቢሆኑ በክፉ ቀን ስለሚመሩት ህዝብ ሲሉ ራሳቸውን አሳልፈው እንደሚሰጡ በእስራኤል ነገስታቶች ታሪክ ውስጥ እናያለን፤ ወዳጆችም ስለባልንጀራቸው ፍቅር ሲሉ አክብረው የያዙትን አሳልፈው ይሰጣሉ፣ ዮናታን ለዳዊት እንዳደረገው፡፡ይህ ሁሉ የሚሆነው በፍቅር የማስገደድ ጉልበት ምክኒያት ነው፡፡ ፍቅር ስጋዊ አይንን ከራስ ወዳድነት ይጋርዳል፤ የፍቅር ሀይል ጠንካራ ልብን ማሸነፍ ይችላል፤ ከራስ ፈቃድ አውጥቶ የሰው ፈቃድ ላይ ይጥላል ያስማርካልም፡፡ የፍቅር ጉልበት የውስጥ ጥንካሬን ያሽመደምዳል፤ መቀበልን ሳይሆን መስጠትን ያስለምዳል፤ መጠበቅን ሳይሆን መፍጠንን ያቻኩላል፤ የፍቅር ጉልበት የነፍስ ጥማትን ይፈጥራል፤ ኩራትን ያስማርካል፤ ውርደትን ያስወርሳል፤ ፍቅር የስግብግብ ስሜትን ሀይል ይቆርጣል፡፡
ፍቅር በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ተንከባካቢ ቢኖረው አለም መልኩዋ ባልተዥጎረጎረ ለውድቀትም ተላልፋ ባልተሰጠች ነበረ፡፡
ፍቅር ግን ጉልበታም ብቻ ሳይሆን ባለአይነትም ነው፡፡ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ አይነቱ ላይ በማተኮር በጥቂቱ እንቆያለን፡-
ጾታዊ ፍቅር፡ በወንድና በሴት መሀል የሚፈጠር የፍቅር ግንኙነት ሲሆን የተቃራኒ ጾታ መሳሳብ የሚፈጥረው መዋደድ ነው፡፡ በወንድና በሴት መሀል በመተያየት ጀምሮ በውስጥ በማፈላለግና በማሳሳብ ማጣመር የሚችል ጾታዊ ፍቅር የትውልድ ሁሉ መሰረት የሆነ የፍቅር አይነት ነው፡፡ እግዚአብሄር ይህን ፍቅር በሰዎች መሃል የሚያኖረው በአላማ ነው፡፡ ይህ ፍቅር ከሌለ ተቃራኒ ጾታዎች ላይቀራረቡ በትዳር ተሳስረውም ዘር ላያፈሩና ትውልድ ላያስቀጥሉ ነው፡፡
ዘፍ.24:67 ”ይስሐቅም ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን አገባት፥ ርብቃንም ወሰዳት፥ ሚስትም ሆነችው፥ ወደዳትም፤ ይስሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና።”
ኤፌ5:28 ”እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል”
የቤተሰብ ፍቅር፡ በቤተሰብ መሀል ያለ ፍቅር ሲሆን በእናት፣ በአባትና በልጆች እንዲሁም በወንድምና በእህት መሀል መተሳሰር የሚፈጥር መዋደድ ነው፡፡ በመልካም የወላጅ ፍቅር ምክኒያት ልጆች ከጨቅላነት እስከ አዋቂነት ያለውን ፈታኝ ጊዜ በድል ይሻገራሉ፡፡ እናትና አባት በቤተሰብ ፍቅር ታግዘው የቤተሰባቸውን አባል ይንከባከባሉ፤ ልጆችም እርስ በርስ በመዋደድ ያድጋሉ፡፡ አቅም የሚፈትነው ሰፊው የቤተሰብ አያያዝና ጥበቃ በፍቅር አበረታችነት ይጸናል፡፡ ይህ ፍቅር ከሌለ ሰዎች በአንድነት የመኖራቸው ተስፋ ይጨልማል፡፡
2ሳሙ.1:23 ”ሳኦልና ዮናታን የተዋደዱና የተስማሙ ነበሩ፤ በሕይወታቸውና በሞታቸው አልተለያዩም፤ ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ነበሩ፤ ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ።”
ዘፍ.7:1-7 ”እግዚአብሔርም ኖኅን አለው፡- አንተ ቤተሰቦችህን ሁሉ ይዘህ ወደ መርከብ ግባ፤ በዚህ ትውልድ በፊቴ ጻድቅ ሆነህ አይቼሃለሁና።.. ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁና፤ የፈጠርሁትንም ፍጥረት ሁሉ ከምድር ላይ አጠፉለሁና።ኖኅም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ አደረገ። ኖኅም የጥፋት ውኃ በምድር ላይ በሆነ ጊዜ የስድስት መቶ ዓመት ዕድሜ ነበረ።ኖኅም ስለ ጥፋት ውኃ ልጆቹንና ሚስቱን የልጆቹንም ሚስቶች ይዞ ወደ መርከብ ገባ።”
የባልንጀራ ፍቅር፡ በጉዋደኛሞች መሀል የሚፈጠር ፍቅር ነው፡፡ የአቻ ለአቻ ፍቅር በመሆኑ ጥብቅ ነው፤ በዚህ አለም ላይ ካሉ ወዳጅነቶችም ይህኛው ጠንካራ ነው፡፡ ይህን ፍቅር እግዚአብሄር በሰዎች መሀል ሲያኖር ሰዎች እርስ በርስ በመዋደድ ከቤተሰብ ባለፈ በአለም ላይ ተግባብቶ መኖርን እንዲያስቀጥሉ ነው፡፡
1ሳሙ.18:1-4 ”ዳዊትም ለሳኦል መናገሩን በፈጸመ ጊዜ የዮናታን ነፍስ በዳዊት ነፍስ ታሰረች፥ ዮናታንም እንደ ነፍሱ ወደደው። በዚያም ቀን ሳኦል ወሰደው፥ ወደ አባቱም ቤት ይመልሰው ዘንድ አልተወውም። ዮናታንም እንደ ነፍሱ ስለ ወደደው ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ዮናታንም የለበሰውን ካባ አውልቆ እርሱንና ልብሱን ሰይፉንም ሸለመው። ዮናታንም የለበሰውን ካባ አውልቆ እርሱንና ልብሱን ሰይፉንም ቀስቱንም መታጠቂያውንም ለዳዊት ሸለመው።”
የዚህን ፍቅር ጥንካሬ የሚያሳይ ምሳሌ በ2ሳሙ.1:26 ውስጥ አለ፡፡ ባለታሪኩ ዳዊት የሚወደው ባልንጀራው በሞተ ጊዜ ከፍተኛ ሀዘን ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ ስለሱ ከልብ አልቅሶአል፣ ስለፍቅሩም ጥልቅነት ተቀኝቶአል፡-
”…ወንድሜ ዮናታን ሆይ፥ እኔ ስለ አንተ እጨነቃለሁ፤ በእኔ ዘንድ ውድህ እጅግ የተለየ ነበረ፤ ከሴት ፍቅር ይልቅ ፍቅርህ ለእኔ ግሩም ነበረ።”
አጋፔ ፍቅር፡ በመስጠት፣ በመራራት፣ በመታገስ፣ በመጠበቅና በመንከባከብ ላይ የተመሰረተ ሲሆን መስዋእት ያለበት፣ የሚሸከም፣ ስለሌላ ራስን የሚያስክድ የፍቅር አይነት ነው፡፡ ይህ ፍቅር ከሌላ መልስ የማይጠብቅና ክፍያ የማይፈልግ ስጦታ ያለው ነው፡፡ ይህ ፍቅር መፈቀር የማይገባቸውን ወይም ሰው ሊጠጋቸው የማይችል ክፉዎችን እንኩዋን የሚወድ ጠንካራ ፍቅር ነው፡፡ በዚህ ፍቅር የተያዘ ሰው ሌላው ቢጠላው አንኩዋን በመልሱ የማይጠላ ነው፡፡ ፍቅሩ መንፈሳዊ ነው፡፡ መንፈሳውያንም ከእግዚአብሄር ጋር ባላቸው ቀረቤታ የሚቀበሉት ነው፡፡
​​​​​​​​ሮሜ.5:5-8 ”በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም። ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና። ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል።”
​​​​​​​​ሮሜ.15:30 ”ወንድሞች ሆይ ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር እየጸለያችሁ ከእኔ ጋር ትጋደሉ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ፍቅር እለምናችኋለሁ”
​​​​​​​​​​​​​​​​ዮሐ.15:19 ”እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ይህን አዛችኋለሁ።ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ። ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል።”
​​​​​​​​ዮሐ.15:15 ”እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት። ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም። እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ።​​​​​​​​ ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፥ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና።”
የፍቅር ሃይራርኪ (ተዋረድ)
የፍቅር ሃይራርኪ ፍቅር መነሻው ከፍ ካለ ስፍራ (ከፈጣሪ ዘንድ) ሆኖ ወደ ዝቅተኛው አካል (ወደ ፍጥረት) እንደሚወርድ የሚያመለክት የፍቅር ቅደም ተከተል ነው፡፡ ፍቅር መነሻ አለው ወይም ምንጭ አለው፤ ይህ ምንጭ የፍጥረት ሁሉ ባለቤት የሆነው እግዚአብሄር ነው፡፡ ይህ አምላክ ዙፋኑ ሰማይ በመሆኑ ሰማያዊ ፍቅሩ መነሻው ከዚያ ነው፡፡ እግዚአብሄር በዚህ አለም ላይ የፈጠራቸውን ፍጥረታት ህያው ካደረገ በሁዋላ ሁሉንም በፍቅር ህግ አስሮአቸዋል፡፡ ስለዚህ የትኛውም ፍጥረት የራሱን አምሳያ ይፈልጋል፣ ይወዳል፡፡ ለምሳሌ እባብ ሌላውን ላይወድ እንዲያውም ሊተናኮል ቢችልም የራሱን አይነት ፈልጎ ይጠጋል፣ ይወዳል፡፡ ይህ እግዚአብሄር ለፍጥረቱ የሰጠው ጾታዊና ቤተሰባዊ ፍቅር ነው፡፡ በሰው ዘንድ የምናየው የፍቅር አይነት ግን ከላይ የተጠቀሱትን አራቱንም አይነት ያጠቃልላል፡፡
መሰረታዊ ልዩነት፡- እግዚአብሄር ፍቅር ነው ፍጥረቱንም ይወዳል፡፡ ፈጣሪ እንደመሆኑ ግን የሚወደው ፍጥረቱ ላይ እንደምናየው ባለ ፍቅር አይደለም፡፡ የእግዚአብሄር ፍቅር ዘላለማዊና መንፈሳዊ ነው፡፡የፍጥረታውያን ፍቅር ስጋዊና ውሱን ፍቅር ነው፤ ዘላለማዊ ሳይሆን በአለም ውስጥ የተወሰነ ነው፡፡ ስጋዊ ፍቅር ጾታዊ፣ ቤተሰባዊና የባልንጀራ ፍቅር ነው፡፡
የፍቅር ሀይራርኪ ጥቅሙ ምንድነው? በአጭሩ ከፍ ያለውን ፍቅር መነሻ ለመረዳትና ከላይ ወደ እኛ የወረደው በእኛም ዘንድ ያለ ፍቅር ምን እንደሆነ እንድናስተውል የሚረዳ ነው፡፡ በፍቅር ሃይራርኪ ውስጥ አስቀድሞ መለኮታዊ ፍቅር ሲመጣ በመከተል ጾታዊ ፍቅር፣  ቤተሰባዊ ፍቅርና የባልንጀራ ፍቅር በቅደም ተከተል እናገኛለን፡፡ይህም ከመለኮት መኖርና ከአዳም አፈጣጠር ጋር የተገናኘ ሲሆን አዳምና ሄዋን ተባዝተው ቤተሰብ ከዚያም ባለፈ ማህበረሰብ ሲፈጥሩ የሆነውን የፍቅር ተዋረድ የምናይበት ነው፡፡
ዘፍ.1.27፣4፡1-3 ”እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም ባረካቸው፥ እንዲህም አላቸው፡- ብዙ፥ ተባዙ፥ ምድርንም ሙሉአት፥ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው።… አዳምም ሚስቱን ሔዋንን አወቀ፤ ፀነሰችም፥ ቃየንንም ወለደች። እርስዋም፡- ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ አለች።ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ፤ ቃየንም ምድርን የሚያርስ ነበረ።ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ”
እግዚአብሄር አዳምን በመፍጠር ጀመረ ከርሱም ሄዋንን፣ ከሁለቱም ቃየን፣ አቤል ሴትን እያለ ፍጥረት ምድርን እንዲሞላ አድረገ፡፡ የሰውን ልጅ መፍጠር ብቻ ሳይሆን እንደ አሸዋ በምድሩ ስፋት ሲሞላ ተሳስቦ፣ ተጠባብቆና ተቀባብሎ እንዲኖር በልቡ ጥብቅ የፍቅር ህግን አኖረ፡፡ እንዲህ ሲሆን አንዱ ከሌላው ፍቅርን አልተማረም፤ በተፈጥሮው በልቡ ታትሞ ስላለ በርሱ እየተመራ ይኖራል እንጂ፡፡ ፍቅር አምላክን ከፍጥረት እንዲሁም ፍጥረትን እርስ በርስ እስከዛሬ እያስተሳሰረ ይገኛል፣ ይሄም ሰው በሰላም እንዲኖር አድርጎአል፡፡ በመጨረሻው ዘመን ግን አመጽ በምድር ላይ በመበርታቱ በብዙዎች ዘንድ ይህ የፍቅር ህግ ተጥሶአል፡፡
​​​​​​​​ማር12:28 ”ከጻፎችም አንዱ ቀርቦ ሲከራከሩ ሰማና መልካም አድርጎ እንደ መለሰላቸው አስተውሎ፡- ከሁሉ ፊተኛይቱ ትእዛዝ ​ማናቸይቱ ናት? ብሎ ጠየቀው።ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፡- ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፡- እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፥አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።ሁለተኛይቱም፡- ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ​ሌላ ትእዛዝ የለችም።”
እግዚአብሄር ወደ እርሱ ለቀረቡ ይህን ፊተኛ ህግ እንዲያስተውሉ ይናገራል፡፡ የፍቅር ህግ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ ነገሮች ተዘልለው ሊታለፉ ይችላሉ፡፡ የፍቅር መጥፋት ግን የጥፋት ፍጻሜን የሚያቀርብ ነው፡፡

  1. የእግዚአብሄር ፍቅር፡- ከላይ የሚመጣ ፍቅር ነው፤ የእግዚአብሄር ፍቅር መለኮታዊ ፍቅር ነው፡፡ ፍቅሩ ከስጋውያን ፍቅር ይለያል፡፡ የእግዚአብሄር ፍቅር ንጹህ ነው፣ ስለዚህ አይበላሽም፣ አያረጅም፣ አይታክትም፣ በሁኔታዎች አይለወጥም፡፡ ፍቅር ከእግዚአብሄር መሆኑ ብቻ ሳይሆን የርሱ ፍቅር በሰው ላይ መጋባት የሚችል ነው፡፡

​​​​​​​​ኤር.31:3-7 ”እግዚአብሔርም ከሩቅ ተገለጠልኝ እንዲህም አለኝ፡- በዘላለም ፍቅር ወድጄሻለሁ፤ ስለዚህ በቸርነት ሳብሁሽ። የእስራኤል ድንግል ሆይ፥ እንደ ገና እሠራሻለሁ አንቺም ትሠሪያለሽ፤ እንደ ገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ከዘፋኞች ጋር ወደ ዘፈን ትወጫለሽ።እንደ ገናም በሰማርያ ተራሮች ላይ የወይን ቦታዎችን ትተክሊአለሽ፤ አትክልተኞች ይተክላሉ በፍሬውም ደስ ይላቸዋል።በኤፍሬምም ተራሮች ላይ ያሉ ጠባቆች። ተነሡ፥ ወደ ጽዮን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር እንውጣ ብለው የሚጮኹበት ቀን ይመጣልና።”
እግዚአብሄር ፍቅር ነው፤ ሰዎች በርሱ ፍቅር ሲያዙ በፍጹም ያመልኩታል፡፡ የርሱ ፍቅር መንፈሳዊ ስለሆነ ዘላለማዊ ነው፡፡ የሰው ፍቅር ግን እንደ እርሱ ፍጹም አይደለም፤ በዚህ ምክኒያት ከእግዚአብሄር ፍቅር ክብሩ ዝቅ ያለ ነው፡፡ ይህም ሰው ራሱን በሀጢያት አበላሽቶ   ከእግዚአብሄር ያገኘውን ፍጹም ፍቅር ስላጣ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ፍቅር ወደ ሰው ተመልሶ ይመጣልን? አዎ፣ ሰው መለኮታዊ ባህሪይ ያለውን ፍቅር ዳግም ልደት በሚባል የእግዚአብሄር አሰራር በእምነት ይቀበለዋል፡-
​​​​​​​​ሮሜ.5:5-8 ”በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ስለ ፈሰሰ ተስፋ አያሳፍርም። ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል።”

  1. የአዳምና ሄዋን ፍቅር፡ እግዚአብሄር አዳምና ሄዋንን በፈጠረ ጊዜ በውስጣቸው መሳሳብና መፈላለግ አስቀምጦ ስለነበር እንደተያዩ ተቀራረቡ እንጂ ባይተዋርነት አልታየባቸውም፡፡ መፈላለጋቸው ህብረት፣ መጠጋጋት፣ ስሜታቸውን መገላለጽ፣ አብሮነትና የመሳሰለውን ሊፈጥርላቸው ችሎአል፡፡ በውስጣቸው በተፈጠረው ጾታዊ ፍቅር ተገናኝተው ልጆችን አግኝተዋል፡፡

ዘፍ.2:21-25 ”እግዚአብሔር አምላክም በአዳም ከባድ እንቅልፍን ጣለበት፥ አንቀላፋም፤ ከጎኑም አንዲት አጥንትን ወስዶ ስፍራውን በሥጋ ዘጋው። እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት ወደ አዳምም አመጣት። አዳምም አለ፡- ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። አዳምና ሚስቱ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ፥ አይተፋፈሩም ነበር።”
አዳም ከዚህ በፊት እርሱን የምትመስል የሰው ዘር አይቶ አያውቅም፡፡ ሄዋንን እንዳየ ግን ወዲያው በርሱዋ ተሳበ፣ የሚገርመው ወንድ ነች አላላትም፤ እርስዋ ሴት ትባል አለ፣ ሚስት እንደሆነችም አረጋገጠ፡፡ ስለዚህ ከርስዋ ጋር በፍቅር እንደሚጣበቅ አዋጅ ለርስዋና ለራሱ እንዲሁም ለመጪው ትውልድ በተፈጠረችበት በዚያው ወቅት ተናገረ፡፡ ይሄን ሁሉ ነገር በአንድ እይታ እንዴት አስተዋለው? በእርግጠኝነት በራሱ እውቀትና ማስተዋል የሆነ አልነበረም፣ በእግዚአብሄር መንፈስ እውቀት የሆነ እንጂ፡፡