የፈራሽ ቤት መሃንዲሶች

የእውነት እውቀት

ህያው ነፍስ ያለን የሰው ልጆች የሚናድ፣ የሚፈርስና የሚከስም ጊዜያዊ መኖርያ ውስጥ እንደምንኖር መቼም ልንዘነጋው የማይገባ ነው። የእግዚአብሄር ፈቃድ የፈጠረውን አካል ከምድር እንዳወጣው መልሶ በምድር ወስጥ እንዲከስም ወስኖአል።ነቢዩ በኢሳ.38:12-16 ላይ፦
“ማደሪያዬ ተነቀለች፥ እንደ እረኛ ድንኳንም ከእኔ ዘንድ ተወገደች፤ ሕይወቴንም እንደ ሸማኔ ጠቀለልሁ፥ እርሱም ከመጠቅለያው ይቈርጠኛል፤ ከማለዳም ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ታጠፋኛለህ። እስኪነጋ ድረስ ቈይቼ ነበር፤ እርሱ እንደ አንበሳ አጥንቴን ሁሉ ሰበረ፤ ከማለዳ ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ታጠፋኛለህ። እንደ ጨረባና እንደ ሽመላ ተንጫጫሁ፥ እንደ ርግብም አጕረመረምሁ፤ ዓይኖቼ ወደ ላይ ከማየት ደከሙ። ጌታ ሆይ፥ ተጨንቄአለሁና መከታ ሁነኝ። ምን እላለሁ? እርሱ ተናግሮኛል፥ እርሱ ራሱም ይህን አድርጎአል፤ በዘመኔ ሁሉ ስለ ነፍሴ ምሬት ቀስ ብዬ እሄዳለሁ። ጌታ ሆይ፥ በዚህ ነገር ሰዎች በሕይወት ይኖራሉ፥ በዚህም ሁሉ የመንፈሴ ሕይወት ነው፤ አንተም ፈወስኸኝ ወደ ሕይወትም መለስኸኝ።“ አለ።
ይህ ነቢይ ስጋዊ አካሉን በእረኛ ድንኳን መስሎታል።ደግሞም መንፈሳዊ ህይወት ያን ስጋ እያኖረው እንዳለ በማስተዋል ይናገራል። የእረኛ ድንኳን በቀላሉ ይተከላል፣ በፍጥነት ይነቀላል። ጥንታዊ የአረብ እረኞች ከቆዳ የሚሰሩት ድንኩዋን በቀላሉ የሚዘረጋ፣ በቀላሉ የሚፈርስ፣ የሚጠቀለልና ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ያለችግር የሚጓጓዝ ነበር።በተመሳሳይ የነፍሳችን እረኛ በሰው ህይወት ፍጻሜ ላይ መጥቶ ስጋዊውን ድንኳን እንደ እረኞቹ በቅጽበት ይነቅልና ወደ ምድር ሆድ ያስወግደዋል።
በእርግጥ ስጋችን በመልካሙ ሰራተኛ እግዚአብሄር እጅ በጥበብ የታነጸ መኖርያ ነው። አስተውለን ብንመለከት በጥበበኛው መሃንዲስ የተገነባው መኖርያ የነፍስ ማደሪያ እንደሆነ ልንገነዘብ እንችላለን። ይህ ቤት ልዩ የሚያደርገው ህይወት ያለውና በራሱ ሃይል መንቀሳቀስ የሚችል መሆኑ ነው።በተጨማሪም ስሜት ያለው ሆኖ የተፈጠረ፣ማደግ፣ መስፋት፣ መጎልመስና መፍረስ የሚችል ሲሆን ከዚህ በላቀ መንገድ ማስተውል እንዲችል ተደርጎ በፈጣሪው የተሰራ ነው።መራባት ወይም ትውልዱን መተካት እንዲችልም በሙሉነት አንዴ ተፈጥሮአል።
ይህ ምድራዊ መኖሪያ የሆነው ስጋዊ አካላችን እድሜው ውስን ሲሆን መኖር የሚችለውም በጥቂት አመታት በሚለካ ጊዜ ውስጥ ነው። የሚያስደንቀው ግን በርሱ ሆነን ስንኖር በየእለቱ የሚገጥሙን ነገሮች ያን የሚያዘናጉ ስብከቶች ሆነው ወደ ስህተት እየመሩን ይገኛሉ። በእግዚአብሄር በኩል ዘላለም በሚባል ዘመን የለሽ ጊዜ ውስጥ በክብር ልንኖር ታላቅ ዝግጅት እንዳለ እስክንረሳ ድረስ በአለም ላይ የሚታየው ጥበብ፣ እውቀት፣ ባህል፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ… ከርሱም የተነሳ የሚታየው አሸብራቂ ክስተት አጓጊና የሚያዘናጋ እየሆነብን ነው።ቃሉ ግን ስጋችንና ኑሮአችን ጊዜያዊ መሆኑን የሚያሳይ ነው፦
2ቆሮ.5:1 “ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለንና።“
ይህን ቃል ያስተዋለ ሰው ጊዜያዊ በሆነውና ዘላለማዊ በሆነው መሃል ያለውን ልዩነት ተገንዝቦ ውሳኔውን ማስተካከል ይገባዋል። የእግዚአብሄርን መኖር ያመነም በዚች ሕይወት ብቻ (በጊዜያዊው ኑሮ ብቻ) ክርስቶስን ተስፋ አድርጎ ከሆነ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪን ተብሎ የተፈረጀ አማኝ ነው።
ሃዋርያቶች ለዘላለም ቤታችን እንድንጨነቅ በዚያም ላይ እንድናተኩር አጥብቀው አስተምረዋል።ለጊዜው በሚሆነውና በምድር በሚያስቀረው የህይወት ዘይቤ እንዳንሰጥም አሳስበውናል።እግዚአብሄር የጠራን ዘላለማዊ መኖርያ የሆነውን እንድናገኝ ነውና፡-
ዕብ.9:11-13 “ነገር ግን ክርስቶስ ይመጣ ዘንድ ላለው መልካም ነገር ሊቀ ካህናት ሆኖ፥በምትበልጠውና በምትሻለው በእጆችም ባልተሠራች ማለት ለዚህ ፍጥረት ባልሆነች ድንኳን፥የዘላለምን ቤዛነት አግኝቶ አንድ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ቅድስት በገዛ ደሙ ገባ እንጂ በፍየሎችና በጥጆች ደም አይደለም።“ ስላለ ትኩረታችንን ወደፊት በሚመጣው መልካምና ዘላለማዊ ነገር ላይ እንድናደርግ ያስጠነቅቀናል።
የፈራሽ ቤት ግንባታ ለምን?
የሚከተለው ቃል ያስደንግጥና ልብን ይመልስ!
ፊል3:18-21 “ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ። መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።“
በክርስቶስ የመስቀል ስራ ላይ እንዴት ጠላት መሆን ይቻላል?፦ ለሚጠፋ ነገር በመስራት፣ የእግዚአብሄርን የዘላለም እቅድ በጊዜያዊ ትርፍ በመለወጥ፣ ምድራዊ ነገርን ለማትረፍ ከሰማያዊ ነገር በመጉደል፣ ነውረኛን ነገርን ሁሉ በማስተናገድ በአጠቃላይ ዘላለማዊው የእግዚአብሄር እቅድ ላይ እንቅፋት በማኖር።
በዘላለም ቤት የመኖር ተስፋን የማያስጨብጥ እምነት ፍጻሜው እንዲህ ከንቱ ነው። ነፍሳትን ለዘላለም ህይወት የማያበቁ አስተማሪዎች ግን የጊዜያዊ ቤት መሃንዲሶች ናቸው። የሚያንጹበት ትምህርት የእግዚአብሄርን የዘላለም ፈቃድ ስላልያዘ ለውድቀት ይጋብዛል። በሚያሳዝን ጎኑ አለም የተሞላችው በነዚህ አስተማሪዎች ነው። መሃንዲሶቹ በጭካኔ ወገናቸው ላይ ፈርደዋል፣ ምክንያቱም እያነጹ ያለው ቤት ፈራሽ ሆኖ ሳለ (በዚህ ማንነትና ሰውነት ለዘላለም መኖርን በመጠበቅ) ለጊዜያዊ ጥቅም ብቻ ሊኖሩበት መርጠውታል፣ተማሪውም ያን እንዲከተል ፈርደውበታል።
ያዕ.3:1-2 “ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ፥ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና።
ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው“ በማለት ሰዎች በስጋዊ አእምሮ እየተመሩ የጌታን ትምህርት እንዳያበላሹ ያስጠነቅቃል።
የእግዚአብሄር ፈቃድ ሰዎች ክርስቶስን በመልበስ ልጆቹ እንድንሆን፣ ከውሃና ከመንፈስ በመወለድ ሰማያዊ ዘር ተካፋይ እንድንሆንና ከማይጠፋው ዘር ተወልደን መጨረሻችን ከምድራዊ አድራሻ ወደ ሰማያዊው እንዲለወጥ ከሆነ ከሚጠፋና ተዋርዶ ሊወድቅ እንዲሁም ወደ አፈር ገብቶ ሊበሰብስ ከሚጠበቀው የተዋረደ ሰውነታችን እንዳንላቀቅ የሚያስተምሩን ስለምን ነው?
1ቆሮ.15:12-20 “ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ ግን ከእናንተ አንዳንዶቹ፦ ትንሣኤ ሙታን የለም እንዴት ይላሉ? ትንሣኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤ ደግሞም፦ ክርስቶስን አስነሥቶታል ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለ መሰከርን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን ግን የማይነሡ ከሆነ እርሱን አላስነሣውም። ሙታን የማይነሡ ከሆነ ክርስቶስ አልተነሣማ፤ ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ናት፤ እስከ አሁን ድረስ በኃጢአታችሁ አላችሁ። እንግዲያስ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ ጠፍተዋላ። በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን። አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል።“
ጌታም ጊዜያዊውን ነገርን እንዳንመረጥ በዮሐ.6:27 ላይ ሲያስጠነቅቅ፦
“ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና።“ ብሎአል።
ለሚጠፋ መብል፣ ለሚጠፋ ዝና፣ ለሚጠፋ እውቀት፣ ለሚሰረዝ ጥበብ፣ ለሚደበዝዝ ክብር…..በአጠቃላይ በአለም ላይ ላለ ጠፊ ነገር ሁሉ ልብን፣ መንፈስንና ነፍስን አሳልፎ መስጠት ከፈራሽ ጋር ተጨምሮ መፍረስን ያመጣል።
1ጴጥ.1:24-25 “ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤ ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤
የጌታ ቃል ግን ለዘላለም ይኖራል። በወንጌልም የተሰበከላችሁ ቃል ይህ ነው።“ ይላልና።
ስለዚህ ሊጠወልግ ያለው ሳር ነፍስንም ቀፍድዶ አብሮ እንዳያጠወልግ እንጠንቀቅ፣ ሊረግፍ ያለው ሰዋዊ ክብርም ዘላለማዊ ክብር የሆነውን መዳንና ሰማያዊ ሰውነት እንዳያረግፍ እንዲሁ ፈጽመን እንጠንቀቅ።